Monday, September 16, 2013

የቅድስት አርሴማ ታሪክ በአጭሩ


እናታችን ቅድስት አርሴማ እግዚአብሔርን በቅንነት ያገለግሉ ከነበሩ ከከበሩ ካህናት ወገን ከሆኑ ከቅዱስ ቴዎድሮስና ከእናቷ ቅድስት አትናሲያ በስዕለት ተወለደች፡፡
ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ብሉይን ሐዲስን ተምራ እያነበበች እንዲሁም በተግባር እየተረጎመች ዘወትርም በጸሎት ትተጋ እንደነበር ገድሏ ይተርካል፡፡ በዚህ ዘመን ድርጣድስ የሚባል በአርመን የነገሠ አረማዊ ንጉሥ ለጣዖት የሚሰግድ' ፀሐይንም የሚያመልክ' ክርስቲያኖችንም እኔ ለማመልከው አምላክ መስገድ አለባችሁ በማለት መከራ ያጸናባቸው ነበር፡፡

እናታችን ቅድስት አርሴማም ተጋድሎዋን የጀመረችው የዚህ ጨካኝ ንጉሥ አገልጋይ ወይም ሹም ፳፯ ክርስቲያኖችን እንደልማዱ እየደበደበ' እየገረፈና ልዩ ልዩ ስቃይ እያደረሰባቸው ሲወስዳቸው በማየቷ ነበር፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‘‘ለእነርሱና ለአሕዛብ ምስክር እንዲሆን ስለኔ ወደገዢዎችና ወደ ነገሥታት ትወሰዳላችሁ፡፡’’ (ማቴ. ፲፡፲፮፡፲፱)፡፡ ያለውን በማሰብ ቅድስት አርሴማም ገና በሃያ ዓመቷ የዚህን ዓለም ንጉሥ እኩይ ግብሩን በመንቀፍ ስለ ክርስቶስ ከሚሰቃዩ ወገኖቿ ጋር ግንባር ቀደም በመሆን ትመሰክር ጀመር፡፡ የንጉሡም አገልጋይ በደም ግባቷና በንግግሯ ማማር ተደንቆ በዚች በፈቃዷ ልትሠዋ በወደደች ሴት ምንም ሊያደርግባት ስላልወደደ ወደ ንጉሡ ወደ ድርጣድስ ከሃያ ሰባቱ ክርስቲያኖች ጋር ወሰዳት፡፡ ንጉሡም ብዙ የተነገረላትን ወጣት ሲያይ በውበቷና በንግግሯ ተማርኮ ለዓለማዊ ደስታውና ፍላጎቱ ተመኛት፡፡ ለእርሱም ሙሽራ እንድትሆን ብዙ ወተወታት፡፡ ቅድስት አርሴማ ግን ናቀችው ‘‘እኔ የሰማያዊው ንጉሥ የክርስቶስ ሙሽራ እንጂ የዚህን ዓለም አላፊ ጠፊ የሆነውን ገንዘብና ደስታ የምሻ አይደለሁም፡፡’’ በማለትም መለሰችለት፡፡
ንጉሡም ይህንን ከእርሷ በመስማቱ እጅግ ተቆጣ፤ በመናቁም ተበሳጨ፤ አሽከሮቹንም ጠርቶ በቤተ መንግሥቱ የታሰሩትን አንበሶች እንዲለቀቅባቸው አዘዘ፡፡ አንበሶቹ ግን ይደሰቱ ነበር፡፡ በኋላም ፊታቸውን ወደ ንጉሡና አገልጋዮቹ በማዞር ሩጠው እስኪደበቁ ድረስ አሳደዷቸው፡፡ ንጉሡ ይበልጥ ነደደው ክርስቲያኖቹ በረሃብ እንዲያልቁ እንዲታሰሩ አዘዘ፡፡ እግዚአብሔርም በአምስተኛው ቀን በብርሃን ቤቱን ሞልቶት የሚበሉትን በመሶብ የሚጠጡትን በጽዋ ከሰማይ አወረደላቸው፡፡ ንጉሡም ይህንን በማየቱ ከዚያ አውጥቶ በእሳት ውስጥም አስገባቸው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅን የጠበቀ አምላክ እነርሱንም አዳናቸው፡፡ በሌላም በብዙ መንገድ ሊያጠፋቸው እንደሞከረ ገድሏ ይተርካል፡፡ በመጨረሻም ከአማካሪዎቹ ጋር ተማክሮ በሰይፍ እንዲያልቁ ይወስናሉ፡፡
እያንዳንዳቸውን ተራ በተራ ሲሰይፋቸው ቅድስት አርሴማ ለሚሰየፉት ሁሉ የድል አክሊል ከሰማይ ሲወርድላቸው ትመለከት ስለነበር የእርሷን ተራ በጉጉት ትጠብቀው ነበር፡፡ በመደሰቷም እየጸለየች አይዟችሁ ጽኑ ትላቸው ነበር፡፡
በመጨረሻም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽናቷን ተመልክቶ ቃል ኪዳን ይገባላታል፡፡ ንጉሡም ሌሎቹን አሰይፎ ሲያበቃ ወደሷ ዞሮ በቁጣ እየጮኸ አንቺን እንደ ባልንጀሮችሽ በቀላሉ አልገልሽም ስቃይሽን አጸናብሻለሁ ብሎ ለአገልጋዮቹ ትእዛዝ በመስጠት አይኗን አስወጥቶ በእጇ ያሲዛታል፤ ጡቷን ያስቆርጣል፤ በኋላም አንገቷን ያሰይፋታል በዚሁ ሁኔታ እናታችን ሰማዕትነትን ተቀበለች፡፡
ይህንን ሁሉ መከራ ስለአምላኳ ስትል እራሷን አሳልፋ የሰጠች ድንቅ ሰማዕት ናት፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ ‘‘ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ’’ (መዝ.) እንዳለ ለእናታችንም የገባላት ቃል ኪዳን ‘‘በእኔ ስም አምነሽ የዚህ ዓለም ተድላና ደስታ ሳያታልልሽ አንገትሽን ለሰይፍ ሰጥተሽ ተሰይፈሻል፤ የሰማዕትነት ተጋድሎ ፈጽመሻልና ስምሽን የጠራ፤ በዓልሽን ያከበረ፤ ዝክርሽን የዘከረ፤ ገድልሽን የጻፈና ያጻፈ፤ የሰማና ያሰማም እስከ ፲፪ ትውልድ ድረስ እምርልሻለሁ’’ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶላታል፡፡ በዚህም መሠረት በሷ አማላጅነት አምኖ እገዳሟም ሄዶ በጸሎት የተማጸናት ሁሉ ለችግሩ መፍትሄ አግኝቶ እንደሚመለስ እሙን ነው፡፡ የቅድስት አርሴማ ረድኤት በረከት ጸሎትና ምልጃ ከእኛ ጋር ይኑር፡፡ አሜን አሜን አሜን


አሜን የእናታችን በረከቷ ይደርብን!!!!

LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

No comments:

Post a Comment