Wednesday, September 4, 2013

ጳጉሜ/ጳጉሜን/

በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከነሐሴ በኋላ ጳጉሜን የምትባል አምስት ቀን አለች፡፡ ወር እንዳትባል አቅም ያንሳታል፡፡ ሳምንት እንዳትባል አምስት ቀን ብቻ ኾናለች፡፡ ጳጉሜን የሚለው ስያሜዋ ግን “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ መኾኑ በአበው ቃል ተነግሯል፡፡

“ኤፓጉሜኔ” ማለት ጭማሪ ማለት ነው ፡፡ በግእዝ ቋንቋችን ተውሳክ ማለት ነው፡፡ ተውሳክ ማለት ተጨማሪ ማለት ነው፡፡ “ወሰከ - ጨመረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ ኤውሮፓዎች ጳጉሜን የወር ተጨማሪ አድርገዋታል፡፡ ይኸውም ይታወቅ ዘንድ እኛ የወርን ቁጠር ሠላሳ ስናደርግ እነርሱ ሠላሳ አንድ ብለው የሚቆጥሩት ወር አላቸው፡፡ ይኹን እንጂ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ጳጉሜን የወር ተጨማሪ ሳያደርጉ የዓመት ተጨማሪ አድርገዋታል፡፡ የዓመቱንም ቀን ቁጥር ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀን ከነሱ ብለው ደምረውታል፡፡

በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጳጉሜ ወር የምንጾመው የፈቃድ ጾም ነው፡፡ ይህም ጾመ ዮዲት በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ግን እንደ አንደኛው የፈቃድ ጾም /ጽጌ ጾም/ በብዙዋኑ ዘንድ የታወቀ አይደለም፡፡ የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡ እዚህ ላይ ዮዲት ተብላ የተጠቀሰችው በቤተክርስቲያን ታሪክ ትምህርት ላይ በጥፋት ሥራዋ በተደጋጋሚ የምትጠቀሰው ዮዲት ጉዲት እንዳልሆነች ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡ ወደ ታሪኩ ስንመለስ የፋርስ ንጉስ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ሹም ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ዮዲ 2፡-2-7፡፡ እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ 12ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ 12ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋ በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡

ዮዲት ባሏ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም በቀኖና በሀዘን ተወስና ትኖራለች በተፈጠረው ጥፋት ህዝቡ ላይ ለመጣው መከራ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡ የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ እግዚአብሔር አምላክም ሕዝቡን የሚያድኑበትን መንገድ ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለፀላት፡፡ ዮዲ 8፡-2 ፡፡ ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡

ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንን ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው ጳጉሜን በፈቃድ ይጾማሉ፡፡

የጳጉሜ ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው፡፡ ይህም ጳጉሜ የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማው የክረምት ወቅት ወደ ማብቂያው የምናልፍባት እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነውና ነው፡፡

ሊቃውንቱ እንደ ሱባኤ ቀን ቀኖና እንዲፈጽምባት ለብቻ ለይተው አኑረውታል፡፡ “ይህ ዓለም ኑሮ፣ ኑሮ በመጨረሻ ያልፋል፡፡ ጌታ ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል” ሲሉ የገታ የመምጣቱ ነገር እንዲነገርባት፣ መሥዋዕት እንዲሠዋባት፣ ጾም እንዲያዝባት፣ ምጽዋት እንዲመጸወትባት ለይተው መድበዋታል፡፡

ሕዝቡ ሳይቀር “ጳጉሜን ዕድሜ ትሰጠናለች፤ በኋላም ታድነናለች” ብለው ጾም ይጾሙባታል፡፡ የዚሁም ማስረጃ በቅዱስ መልከ ጸዴቅ ድርሳን ይገኛል፡፡ ንግሥት ዘውዲቱ ምኒልክ የጾም ሥርዐት ይፈጽሙባት ነበር፡፡ ሌሎችም ሽማግሌዎችና ባልቴቶች አክብረው ይጾሙባታል፡፡ ኾኖም የጳጉሜን አቆጣጠር አንዱ ከወር ጋራ፣ ሌላውም ከዓመት ጋራ ቢያደርገውም በሀሉም አቆጣጠር ውስጥ ሕያዊት ኾና መገኘቷ የታወቀ ነው፡፡

የነቢዩ ኄኖክ መጽሐፍም ጳጉሜን ጨርሶ አልዘነጋትም፡፡

ክርስቲያኖች ሁሉ በየዓመቱ በጳጉሜ ወር ሁሉም ተሰብስበው ከሌሊት ጀምረው በቤተክርስቲያን ተገኝተው ጸበል ይጠመቃሉ፡፡ ይህንን የምናደገውም እግዚአብሔር የተባረከ ዓመት እንዲሰጠን፣ ባሳለፍነው ዓመት የሰራነውን ኃጢአት ይቅር እንዲለን ነው፡፡ የምንጠመቀውም ንስሐ ገብተን ነው፡፡ በእግዚአብሔር ስም የተቀደሰው ጸበል ደግሞ ከበሽታችን ያድነናል፣ የተቀደስንም ያደርገናል፣ መጪውንም ህይወታችን የተባረከ ያደርግልናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መልካም የአዲስ ዓመት ዋዜማ (ጷጉሜ) ይሁንላችሁ፡፡

LIKE >>> https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

http://www.youtube.com/watch?v=D4S1VUcRHSQ

No comments:

Post a Comment