Monday, January 31, 2022

ጥር 18 - ወበዛቲ ዕለት

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈሰ ቅዱስ ስም አሜን

ጥር 18-ፀሐይ ዘልዳ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዐፅሙ ተቃጥሎ አጥንቱ ተፈጭቶ በደብረ ይድራስ ተራራ ላይ የተበተነበት ዕለት ነው፡፡



+ በ34 ዓ.ም ጥምቀትን ያመጣልን ለሀገራችንም ሆነ ለአፍሪካ የመጀመሪያ ሐዋርያችን የሆነው ቅዱስ አቤላክ (ባኮስ) በዚህች ዕለት በሰሜን ተራራዎች ላይ ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት ቦታ ተሰወረ፡፡ እርሱም በጌታችን የተመረጡ የከበሩ ሐዋርያት እንኳን ወንጌልን በዓለም ለመስበክ ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት ወቅት ወደ አፍሪካ መጥቶ ወንጌልን የሰበከ ነው፡፡
+ ለቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ መምህሩ የሆኑት አባ ያዕቆብ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+ ጌታችን ከሞት ያስነሣው የቅዱስ አልዓዛር እኅቶች ማርያምና ማርታ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡
አባ ያዕቆብ፡- በገድል ተጠምደው የኖሩ እጅግ የከበሩ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉት ንጽቢን በምትባል ከተማ ቢሆንም ሶርያዊ ተብለው ይጠራሉ፡፡ የሀገረ ንጽኒቢን ኤጲስ ቆጶስ ሲሆኑ የእመቤታችንን ውዳሴ ለደረሰው ታላቅ አባት ለቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ መምህሩ ናቸው፡፡ ይህ ታላቅ አባት ከልጅነታቸው ጀምሮ ዓለምን ንቀው በመንኩስና መኖርን መርጠው መንኩሰዋል፡፡ በጠጉር ከተሠራ ማቅ በቀር ሌላ ልብስ ለብሰው አያውቁም፡፡ በቀን በሌሊት፣ በበጋ ሐሩርም ይሁን በክረምት ቁር ቢሆን ይህንን ልብሳቸውን አውልቀውት አያውቁም፡፡ ምግብም ከቅጠላ ቅጠል ውጭ ተመግበው አያወቁም፡፡ የሚጠጡትም የዝናብ ውኃ ብቻ ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ ሀብተ ትንቢትና ሀብተ ፈውስ ተሰጥቷቸው እጅግ አስገራሚ የሆኑ ተአምራትን ያደርጉ ጀመር፡፡ በአንዲት ዕለት ሴቶች በውኃ ምንጭ ላይ እርቃናቸውን ያለ ማፈር ሲጫወቱና ሲሳለቁ አይተው የውኃውን ምንጭ ወዲያው እንዲደርቅ አድርገውታል፡፡ የሴቶቹንም የራሳቸውን ጸጉር በተአምራት ነጭ ሽበት አደረጉባቸው፡፡ ሴቶቹም ተጸጽተው በአባታችን እግር ሥር ወድቀው በለመኗቸው ጊዜ የውኃውን ምንጭ መልሰው አፈለቁላቸው፡፡ እንዳይታበዩ ሲሉ ግን የራሳቸውን ጸጉር ለምልክት ነጭ አድርገው ተውላቸው፡፡ ትሩፋታቸውና ዜናቸው በበየቦታው በተሰማ ጊዜ አቡነ ያዕቆብን በንጽቢን ሀገር ላይ ኤጲስ ቆጶስነት ሾሟቸው፡፡
ጻድቁ ንጉሥ ታላቁ ቈስጠንጢኖስ 318ቱን የከበሩ አባቶች በኒቅያ እንዲሰበሰቡ ሲያደርግ ገድላኛ የሆኑት ይህ ታላቅ አባትም አንዱ ነበሩ፡፡ በጉባኤውም መካከል ሙት አስነሥተው እንዲመሰክር አድርገውታል፡፡ እርሳቸውም አርዮስን አስተምረው መክረው እምቢ ቢላቸው ረግመው አውግዘውታል፡፡ የፋርስ ንጉሥ መጥቶ ሀገረ ንጽቢን ሊወር አስቦ በከበባት ጊዜ አቡነ ያዕቆብ በጸሎታቸው የጭጋግ ደመና በሠራዊቱ ላይ አመጡባቸው፡፡ ተናዳፊ ትንኞችም ፈረሶቻቸውንና ወታደሮቻቸውን ሁሉ ነደፏቸው፡፡ ፈረሶቹም ማሠሪያቸውን እየበጠሱ ፈርጥተው ጠፉ፡፡ ንጉሡም ይህን ተአምር አይቶ እጅግ ፈርቶ ወደ ኋላው ተመልሶ ሄዷል፡፡ ጻድቁ ሕዝበ ክርስቲያኑንና ሀገራቸውን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በጽድቅ ሲያገለግሉ ኖረው በሰላም ዐርፈዋል፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!
+ + +
ስብረተ ዐፅሙ ለሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ፡- ከሃዲው ንጉሥ ዱድያኖስ እጅግ አሠቃቂ በሆኑ ብዙ መከራዎች እያሠቃየ ሦስት ጊዜም ቢገድለው ጌታችን ግን ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሞት እያስነሣው ከሃድያንን ያሳፍራቸው ነበር፡፡ ንጉሥ ዱድያኖስ የሚያደርገው ቢያጣ ጭፍሮቹን ‹‹በመንኰራኩር ፈጭታችሁ አጥንቱን ደብረ ይድራስ ተራራ ላይ ወስዳችሁ ዝሩት›› ብሎ አዘዛቸው፡፡ ጭፍሮቹም የቅዱስ ጊዮርጊስን ሥጋ በመንኰራኩር ፈጭተው ወስደው በተራራው ላይ ቢረጩት ሥጋው ያረፈበት ሳር፣ ቅጠሉ፣ ደንጊያው፣ እንጨቱ ሁሉ ‹‹ጊዮርጊስ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር፣ ጊዮርጊስ ሰማዕቱ ለእግዚአብሔር›› እያሉ አመስግነዋል፡፡ አሁንም ጌታችን ለሦስተኛ ጊዜ ከሞት አስነሣውና ሥጋውን ፈጭተው በተራራም ላይ ሥጋውን በትነውት ወደ ንጉሡ የሚመለሱትን ወታደሮች በመንገድ ከኋላቸው ሄዶ ደረሰባቸውና ‹‹ቆዩኝ ጠብቁኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም እጅግ ደንግጠው ይህ እንዴት እንደሆነ ሲጠይቁት ‹‹አምላኬ ከሞት አዳነኝ›› አላቸው፡፡ ጭፍሮቹም እጅግ ደንግጠው ከእግሩ ስር ወድቀው ‹‹ይቅር በለን›› ብለው በአምላኩ እንደሚያምኑ መሰከሩለት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ከመሬት ላይ ውሃ አመንጭቶ በጸሎት ጌታችንን ቢጠይቅ ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ አጥምቋቸዋል፡፡ እነርሱም በንጉሣቸው ፊት ሄደው ስለጌታችን በመመስከር በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዐፅሙ ተቃጥሎ አጥንቱ ተፈጭቶ በደብረ ይድራስ ተራራ ላይ የተበተነው በዚህች ዕለት ነው፡፡

የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
የመጀመሪያው የአፍሪካ ሐዋርያ ቅዱስ አቤላክ (ባኮስ)፡- ይኽም ጃንደረባ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ንግሥት የሆነችው የህንደኬ የገንዘቧ ሁሉ ኃላፊና አዛዥ የነበረ ነው፡፡ ከአባቱ እብነ መላክ ከእናቱ ስሂነ ሕይወት ታኅሣሥ 29 ቀን ተወለደ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ለበዓለ ፋሲካ በቤተ መቅደስ ይሰግዱ እንደነበረው ሁሉ ይኽም ጃንደረባ ከ4 ሺህ ማይልስ በላይ ተጉዞ ኢየሩሳሌምን ተሳልሞ በመለስ ላይ ነበረ፡፡ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ በተለይም ስለ ጌታችን መከራ መስቀል በዝርዝር የሚናገረውን ክፍል 53ኛውን ምዕራፍ ያነብ ነበር ነገር ግን ጃንደረባው ስለማን እንደሚናገር አልገባውም ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር በአካባቢው ወንጌልን ይሰብክ የነበረውን ሐዋርያውን ቅዱስ ፊሊጶስን ላከለት፡፡ እርሱም ጃንደረባው ያነበው የነበረውን መጽሐፍ ተረጎመለት፣ የከበረች ወንጌልን ሰበከለት፣ በመጨረሻም አጠመቀው፡፡ ሐዋርያው ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በጃንደረባው ላይ ወረደ፡፡ ሐዋ 8፡26-40፡፡ ይህን ለእኛ ለኢትዮጵያውን እጅግ የሚያኮራን ታሪካችን ነው፡፡ ዛሬ በእጃችን ላይ በመገኘው መጽሐፍ ውስጥ ባይኖርም በቆዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች ላይ ግን ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ ጃንደረባውን ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በኢትዮጵያው ጃንደረባ ላይ እንደወረደ ተጽፏል፡፡ (ዝኒ ከማሁ ገጽ 87፣ v.39.cord.alexand. in bible reg. angl-alique plures codd.mss)
ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ጃንደረባውን ያጠመቀበት ወንዝ ‹‹ቤተ ሳሮን›› በተባለችውና እስከዛሬም ድረስ ከኢየሩሳሌም 20 ማይልስ ርቀት በምትገኘው መንደር በኬብሮን መካከል ባለው ኮረብታ ሥር የሚመነጭ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ጸሐፊ የሆነው ሊቁ ቅዱስ ጀሮም ጃንደረባውን ‹‹የኢትዮጵያውያን ሐዋርያ›› በማለት ይጠራዋል፡፡ በሰፊው ለኢትዮጵያውያን ወንጌልን የሰበከ እርሱ ነውና፡፡ ጌታችን የመረጣቸው የከበሩ ሐዋርያት እንኳን ወንጌልን በዓለም ለመስበክ ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት ወቅት በ34 ዓ.ም ነው ቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ በክርስቶስ አምና ወንጌልን የተቀበለችው፡፡ በምድሪቱም ላይ ወንጌል መነገር የጀመረው ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡
እንሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከኢየሩሳሌም ወንጌልን ተምሮና ተጠምቆ ወደ አክሱም እንደተመለሰ በመጀመሪያ ያጠመቀው ንግሥቲቷን ሕንደኬን ነው፡፡ ከእርሷም በኋላ መኳንንቱና መሳፍንቱ ሁሉ አምነው በባኮስ እጅ ተጠመቁ፡፡ ይኸውም በ34 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚህም በኋላ ባኮስ እስከ ኑብያ ድረስ ሄዶ ወንጌልን ሰብኮ ብዙዎችን አሳምኖ አጥምቋል፡፡ በዚህም ጊዜ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በባኮስ እየተሰጠ የነበረውን የወንጌል ብርሃን የበለጠ እንዲበራ አድርጓል፡፡ ከጃንደረባውም ጋር ሆነው በብዙ ቦታዎች አብረው ወንጌልን ሰብከው አምልኮተ ጣዖትን አጥፍተዋል፡፡
ከዚህም በኋላ ባኮስ ወደ የመን በመሄድ በዚያም ክርስትናን በማስተማር ብዙዎችን አሳምኖ ካጠመቀ በኋላ ወደ ፐርሺያ ከዚያም ወደ ሕንድ በመሄድ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሟል፡፡ በመጨረሻም ጥንት ታፕሮባና (taprobana) ዛሬ ሲሎን በምትባለው ደሴት ወንጌልን በማስተማር ላይ እያለ በሰማዕትነት እንዳረፈ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ (lives of the most eminent fathers of the church, page 87) በሌላም በኩል ሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከመጠመቁ በፊት 35 ዓመት ከተጠመቀ በኋላ ደግሞ 41 ዓመት ኖሮ በኢየሩሳሌምም 3 ዓመት ተቀምጦ ወንጌልን ዞሮ ካስተማረ በኋላ በመጨረሻ በ79 ዓመቱ ጥር 18 ቀን በሰሜን ተራራዎች ላይ ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት ቦታ እንደተሰወረ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ጽፈዋል፡፡

የቅዱስ አቤላክ (ባኮስ) ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!




Like
Comment
Share

Saturday, January 22, 2022

❤ ቂርቆስ ወኢየሉጣ ❤


እንኳን ለሰማዕታት ቅዱሳን ቂርቆስ ወኢየሉጣ ወነቢይ አብድዩ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
❤ ቂርቆስ ወኢየሉጣ ❤
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካሏት ዐበይት ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ቂርቆስ ነው። በተለይ በዘመነ ሰማዕታት ተነስተው እንደ ከዋክብት ካበሩትም አንዱ ነው።
ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል፦ "መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራል።"
(ማቴ. ፯፥፲፯)
መልካም ዛፍ ቅድስት ኢየሉጣ መልካም ፍሬ ብፁዕ ቂርቆስን አፍርታ ተገኝታለችና ክብር ይገባታል። ቡርክተ ማኅጸንም እንላታለን። የተባረከ ማኅጸኗ የተባረከ ልጅን ለዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ተሸክሟልና።
በዚያ ክርስቲያን መሆን መከራ በነበረበት ዘመን ይህንን ደግ ሕፃን እርሷን መስሎ እርሷንም አህሎ እንዲገኝ አስችላለችና። አበው በትውፊት እንዳቆዩልን ከሆነ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እናታችን ቅድስት ኢየሉጣ ብፁዕ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስን ወልዳለች።
በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮም ግዛት ክርስትና ቢስፋፋም በዚያው ልክ መምለክያነ ጣዖቱ የገነኑ ነበሩ። በተለይ ከነገሥታቱ ጀምሮ ዋና ዋና የሥልጣን ቦታዎች በአሕዛብ እጅ በመሆናቸው ለዘመኑ ክርስቲያኖች ፈታኝ ነበር።
ማንኛውም ክርስቲያን መሠረታዊ ፍላጐቶቹ እንዲሟሉለት አሕዛብ ላቆሟቸው ጣዖቶች መንበርከክ ነበረበት። መብቱን ከመገፈፉ ባሻገር "ተበድያለሁ" ብሎ ወደ ፍርድ ቤት ሔዶ እንኳ የመጮህ እድል አልነበረውም። ምክንያቱም የሚሰማው የለም።
በዚያ ላይ በየጊዜው ለክርስቲያኖች ፈታኝ የሆኑ አዋጆች ይወጣሉ። የክርስትናን ጐዳና ይበልጥ የሚያጠቡ ሕጐችም ዕለት ዕለት ይፈበረኩ ነበር። ስለዚህም በወቅቱ የነበረ አንድ ክርስቲያን ሃይማኖቱን ከወደደ ወይ እስከ ሞት መታገስ ካልሆነ ደግሞ ሃገሩ ጥሎ በዱር በገደል መሰደድ ነበረበት።
እውነት ለመናገር ዜና ሰማዕታትን የማያውቅ ክርስቲያን ክርስቶሳዊ ነው ሊባል አይችልም። ምክንያቱም ዛሬ እንዲህ እንደ ዋዛ የያዝናት ሃይማኖታችን እንዴት እንደ መጣችና ምን እንደ ተከፈለባት አብዛኛው ትውልድ አያውቅምና።
ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ብፅዕት ኢየሉጣም የዚህ ዘመን (የዘመነ ሰማዕታት) ፍሬ ናቸው። በጊዜው በሮም ግዛት ሥር እስክንድሮስ የሚሉት ክፉ ንጉሥ ነግሦ ነበርና ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ። ጣዖትን ላለማምለክም ተሰው።
በዚህ ጊዜ አንጌቤናይት (ኢጣልያዊት) ብፅዕት ኢየሉጣም በመበለትነት (ባሏ በሕይወት ባለ መኖሩ) ትኖር ነበር። ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ ምንም ገና ሦስት ዓመቱ ቢሆንም ነገረ ሃይማኖትን ታስተምረው ፍቅረ ክርስቶስን ትስልበት ነበር።
እስክንድሮስ የክህደት አዋጅን ሲያውጅም ቅድስቲቱ ለሕፃን ልጇ ራርታ ሽሽትን መረጠች። ሃብት ንብረቷን፣ ወገንና ርስቷንም ትታ ሕፃን ልጇን ተሸክማ ተሰደደች። መከራው ግን በሔደችበት አለቀቃትም።
እስክንድሮስ ተከትሎ ባለችበት ቦታም አገኛት። ወታደሮች ልጇን ሳያገኙ እርሷን ብቻ ይዘው ወደ መኮንኑ አቀረቧት። መኮንኑም "ስምሽን ንገሪኝ?" ቢላት "ስሜ ክርስቲያን ነው።" አለችው። ተቆጥቶ "ትክክለኛውን ስምሽን ተናገሪ?" ቢላት "እውነተኛው ስሜ ክርስቲያን ነው። ሞክሼ (ሞክሲ) ስም ከፈለግህ ኢየሉጣ እባላለሁ።" አለችው።
"ለጣዖት ልትሰግጂ ይገባል።" ሲላትም "እውነትን ይነግረን ዘንድ የሦስት ዓመት ሕፃን ፈልገህ አምጣና ተረዳ።" ስላለችው ወታደሮቹን እንዲፈልጉ ላካቸው። የሃገሩ ሰዎች ልጆቻቸውን ስለደበቁ የተገኘ ቅዱስ ቂርቆስ ነበር።
ቅዱሱ ሕፃን በወታደሮች ተይዞ ሲቀርብ መልኩ ያበራ ነበርና መኮንኑ "በሐከ ፍሡሕ ሕፃን - ደስ የተሰኘህ ሕፃን እንዴት ነህ?" ቢለው "ትክክል ነህ! እኔ በጌታዬ ክርስቶስ ዘንድ ደስታ ይጠብቀኛል። አንተ ግን በክህደትህ ወደ ገሃነም ትወርዳለህ።" አለው።
በሕፃኑ ድፍረት የደነገጠው መኮንኑ በብስጭት "እሺ! ስምህን ንገረኝ?" አለው። ያን ጊዜ "ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ ስሜ ክርስቲያን ነው። እናቴ የሰየመችኝን ከፈለክ ግን ቂርቆስ ነው።" ሲል መለሰለት።
ከዚያም እየደጋገመ "እኔ ክርስቲያን ነኝ።" ብሎ በመጮሁ መኮንኑ ስቃይን በቅዱሱ ሕፃን እና በቡርክት እናቱ ላይ አዘዘ። ከዚህ በኋላ በእነርሱ ላይ የተፈጸመውን ግፍና የወረደባቸውን የመከራ ዶፍ እናገር (እጽፍ) ዘንድ ግን የሚቻለኝ አይመስለኝም።
በግርፋት የጀመረ ስቃይ ሊሰሙት ወደ ሚጨንቅ መከራ ቀጠለ።
ሰባት ብረት አግለው በዓይናቸው፣ በጆሯቸው፣ በአፋቸውና በልባቸው ከተቱ።
በአራት ችንካሮች ላይ አስቀመጧቸው።
በእሳት አቃጠሏቸው።
ጸጉራቸውን ከቆዳቸው ጋር ገፈፉ። ከዚህ በላይ ብዙ ስቃይንም አመጡባቸው።
እናትና ልጅ ግን ለክርስቶስ ታምነዋልና ጸኑ። ቅድስት ኢየሉጣ ብትደነግጥ ልጇ አጸናት። ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት ሲያርፉ ጌታ እንደ ቃሉ የሕፃኑን ሥጋ በሠረገላ ኤልያስ አኑሮታል። ለእኛ የሚጠቅም ብዙ ቃል ኪዳንንም ሰጥቶታል።
❤ ቅዱስ አብድዩ ነቢይ ❤
"አብድዩ" ማለት "የእግዚአብሔር አገልጋይ" ማለት ነው። ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን የቅዱስ ኤልያስ ታላቁም ደቀ መዝሙር ነው። ቅዱሳን ነቢያት ዮናስና ኤልሳዕም ባልንጀሮቹ ነበሩ።
ቅዱስ አብድዩ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስምንት ዓመት አካባቢ የከሃዲው ንጉሥ የጦር መሪ ሆኖ በሃምሳ አለቃነት አገልግሏል። ግፈኛዋ ኤልዛቤል ነቢያተ እስራኤልን ስታስፈጅ ሃምሳውን በአንድ ዋሻ ሃምሳውን ደግሞ በሌላ ዋሻ አድርጐ አትርፏቸዋል። ዘጠኝ መቶው ግን ተጨፍጭፈዋል።
ያተረፋቸውንም ክፉ ዘመን እስኪያልፍ ድረስ መግቧቸዋል። አክአብና ኤልዛቤል ከሞቱ በኋላም ቅዱስ ኤልያስን ተከትሎ ሹመቱን ትቷል። እግዚአብሔር ገልጾለትም ትንቢት ሲናገር ሕዝቡንም ሲገሥጽ ኑሯል።
በብሉይ ኪዳን ካሉ የትንቢት መጻሕፍትም በጣም አጭሩን የጻፈው ይህ ነቢይ ነው። ትንቢተ አብድዩ ባለ አንድ ምዕራፍ ብቻ ናትና። ቅዱሱ በዚህች ቀን ዐርፎ ወገኖቹ ቀብረውታል።
አምላከ ሰማዕታት በምሕረቱ ይማረን። በይቅርታው ኃጢአታችንን ይተውልን። ከበረከተ ሰማዕታትም ይክፈለን።
ጥር ፲፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ
፪.ቅዱስ አብድዩ ነቢይ
፫.ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ
፬.ቅድስት ሶፍያ
፭.ቅድስት አድምራ
፮.አሥራ አንድ ሺህ አርባ አራት ሰማዕታት (ከቅዱስ ቂርቆስ ጋር በሰማዕትነት ያለፉ።)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
፪.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት
፫.ቅድስት ክርስጢና
፬.ቅድስት እንባ መሪና
"በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ በልብህም 'ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው?' የምትል አንተ ሆይ! የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል። እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን 'ከዚያ አወርድሃለሁ።' ይላል እግዚአብሔር።"
(አብድዩ ፩፥፫-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር https://www.facebook.com/tewahdohamanotachin/
No photo description available.
103
17 Shares
Like
Comment
Share

Wednesday, January 19, 2022

💚 💛❤️ እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ💚 💛❤️

💚💛❤️🙏🏿💚💛❤️
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ። ጌታችን፣ መድኀኒታችን፣ አምላካችን፣ አባታችን፣ ብርሃናችን፣ ፀሐያችን፣ ሕይወታችን፣ እረኛችን፣ የሕይወት እንጀራችን፣ የሕይወት መጠጣችን፣ ንጉሣችን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እናመሰግንሃለን። የዘመናት አስገኝ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለዓመቱ በሰላም ያድርሰን 💚💛❤️🙏🏿💚💛❤️


 በጥምቀት ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች እና መልሶቻቸው 


#ጌታችን_ለምን_ተጠመቀ?

1. ምሥጢርን ለመግለጥ፡- 

ጌታችን በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ ምስጢረ ሥላሴ ግልፅ ሆኗል፡፡ አብ በደመና “የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው” በማለቱ አብ የወልድ አባት መሆኑ ታወቀ፡፡ መንፈስ ቅዱስም የባሕርይ ሕይወቱ መሆኑን ሲያስረዳ በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ተቀመጠ ወልድም በተለየ አካሉ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ታየ፡፡ ስለዚህ ምሥጢርን ለመግለጥ ስንል የአንድነት የሦስትነት ምስጢር በጐላ ሁኔታ እንዲታወቅ ተጠመቀ ማለት ነው፡፡ /ማቴ. 3፥16/


2. ትንቢቱን ለመፈፀም፡- 

በመዝሙር 46/47/፥16 ላይ “አቤቱ ውሆች አዩህ፣ ውሆችም አይተውህ ፈሩ ጥልቆች ተነዋወጡ ውሆችም ጮኹ፡፡” ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረውን ትንቢት ለመፈፀም ተጠመቀ፡፡


3. አርአያ ሊሆነን፡- 

ተጠምቆ እንድንጠመቅ አደረገን ሥርዓትን ሠራልን ቀድሞ በአርአያውና በአምሳሉ እንደፈጠረን አሁንም አርአያ ምሳሌ ሆነን፡፡ ለዚህም ነው ምሳሌን ከእኔ ተማሩ ያለን፡፡ /ማቴ 11፥29/ ለትምህርት ለአርአያ /ዮሐ. 13፥1-17/


4. የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ፡- 

አዳምና ሔዋን ፍዳው በፀናባቸው መከራው በበዛባቸው ጊዜ የሚያቃልልላቸው መስሏቸው ዲያብሎሰ ስመ

ግብርናችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ ባላቸው ጊዜ አዳም ገብሩ ለዲያቢሎስ (አዳም የዲያብሎስ የወንድ አገልጋይ) ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ (ሔዋን የዲያብሎስ ሴት አገልጋይ) ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ዲያብሎስም ይህንን ደብዳቤ አንዱን በሲኦል አንዱን በዮርዳኖስ አስቀመጠው፡፡ በዮርዳኖስ ያስቀመጠውን ጌታችን ሲጠመቅ እንደሰውነቱ ረግጦ ደምስሶታል፡፡ ይህንን ጽሕፈት ለመደምሰስ ነው ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተፃፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፡፡” ያለው ቆላ 2፥14



#ጌታችን_መች_ተጠመቀ?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በ5531 ዓመተ ዓለም ዘመነ ሉቃስ ማክሰኞ ጥር 11 ቀን ከሌሊቱ በ10ኛው ሰዓት ነበር፡፡ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 19 በተጠመቀም ጊዜ ዕድሜው 30 ዓመት ከ13 ቀን ነበር፡፡ /ሉቃ. 3፥23/


#ጌታችን_ስለምን_በ30_ዓመት_ተጠመቀ?

በብሉይ ኪዳን ሥርዓትና ልማድ ካህናት ለቤተ እግዚአብሔር ተልእኮ እና መንፈሳውያን አገልግሎቶች ከ30 ዓመት ዕድሜ በፊት አደባባይ አይወጡም ነበር፡፡ እጅግ አስፈላጊ እንኳ ቢሆን ከ20 እና 25 ዓመት አስቀድሞ ለአገልግሎት መሰየም ልማድ አልነበረም፡፡ የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች በዕድሜና በዕውቀት የበሰሉ፣ በጠባይና በሥራ ልምድ የተፈተኑ ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት በተገልጋዩ ሕዝብ ዘንድ የተመሰከረላቸው መሆን ነበረባቸው፡፡ /ዘፀ. 4፥3፤1ዜና መዋ. 23፥24፤ 1ጢሞ.  3፥6-10/ ያንን ሥርዓት ለመፈጸም ጌታችን የተጠመቀውና ለትምህርተ ወንጌል የተገለጠው በ30 ዓመቱ ነበር፡፡


ዮሐንስ መጥምቅም የጌታን መምጣት ለማወጅ በዮርዳኖስ ይሁዳ ምድረ በዳዎች ወጥቶ የታየው ከ30 ዓመት ዕድሜው በኋላ ነው፡፡ ሌላው ዐቢይ ምክንያት የሰው ሁሉ መጀመሪያ አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ በ40ኛ ቀን ተሰጥቶት ኋላም በኃጢአት ምክንያት ያስወሰደውን ልጅነት ለማስመለስ ነው፡፡ 


ክርስቶስ የተጠመቀው ክብር ሽቶ ሳይሆን የአብ የባሕርይ ልጅነቱን (የባሕርይ አምላክነቱን) ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ለማስመስከር፣ ውኃውን ለመቀደስ፣ የአዳምን ልጆች የእዳ ደብዳቤ ለመደምሰስና በስህተት የጠፋውን የልጅነት ክብር ለመመለስ ነው፡፡ ጌታ ተጠምቆ ከውኃው ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ በማረፍ አብ በደመና ‹‹ይህ ልጄ ነው›› ብሎ ሲመሰክርለት ምሥጢረ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በጉልህ ተረጋግጧል፡፡ /ማቴ. 3፥16/


#ጌታችን_በዮሐንስ_እጅ_ለምን_ተጠመቀ?

ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ሲሆን በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ በፍጹም ትሕትና ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ ይህንንም ያደረገልን አብነት ሊሆነን ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ቅዱስ ዮሐንስን ‹‹መጥተህ አጥምቀኝ ›› ብሎት ቢሆን ኖሮ ነገ ነገሥታቱና መኳንንቱ ካህናቱን መጥታችሁ አጥምቁን ባሉ ነበር ስለዚህ እንዲህ እንዳይሆን ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ጌታ ስሆን በባርያዬ እጅ እንደተጠመቅሁ እናንተም ወደ ቤተክርስቲያን ሄዳችሁ በካህናት እጅ ተጠመቁ›› ሲል ነው፡፡


ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው ልጅነትን የምታሰጥ ጥምቀትን ባርኮ ቀድሶ ሊሰጠን እንጂ ክብር እንዲሆነው አይደለም፡፡ ምክንያቱም፡- እርሱ እከብር አይል ክቡር እጸድቅ አይል ጻድቅ ነውና፡፡ 


#ቅዱስ_ዮሐንስ_ጌታችንን_በማን_ስም_አጠመቀው? 

ጌታችን ዮሐንስን አጥምቀኝ ባለው ጊዜ "ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ አንተን በማን ስም ላጥምቅህ? በአብ ስም እንዳላጠምቅህ አብ አባትህ ባንተ ሕልው ነው በወልድ ስም እንዳላጠምቅህ ወልድ አንተ ነህ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዳላጠምቅህ መንፈስ ቅዱስ ሕይወትህ ባንተ ሕልው ነው ታዲያ በማን ስም ላጥምቅህ?" ብሎ ቢጠይቀው ጌታም ‹‹እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት አንተ የዓለም ካህን ብርሃንን የምትገልጥ የአብ የባሕርይ ልጅ ሆይ ይቅር በለኝ›› ብለህ አጥምቀኝ አለው፡፡ 


#ዮሐንስ_ጌታን_ሲያጠምቀው_እጁን_ለምን_አልጫነበትም?

- ዮሐንስ በጥምቀት አከበረው /ልዕልና ሰጠው/ እንዳይባል፡፡

- መለኮትን በእጅ መንካት ስለማይቻል


#ጌታችን_ጥምቀቱን_ለምን_በዮርዳኖስ_አደረገው?

በኢየሩሳሌም አካባቢ ብዙ ወንዞች ኩሬዎችና ሐይቆች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ጌታ ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለዚሁ አስቀድሞ የተነገረውን ትንቢት መፈጸሙን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ‹‹ባሕር አይታ ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ›› /መዝ.113፥3/ ከዚህም ጋር ከላይ ምንጩ አንድ የሆነው ዮርዳኖስ ዝቅ ብሎ በደሴት ተከፍሎ እንደገና እንደሚገናኝ በግዝረት በቁልፈት (በመገዘርና ባለመገዘር) ተለያይተው የነበሩ ሕዝብና አሕዛብ መላው የአዳም ልጆች በጌታችን ጥምቀት አንድ መሆናቸውን የሚገልጽ ትርጉም አለው፡፡ እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምደረ ርስት ገብተዋል፡፡ ያመኑ የተጠመቁ ምዕመናንም በጥምቀት ገነት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡ ሌላው በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ይደመስስልን ዘንድ /ቈላ. 2፥14/


#ጌታችን_ለምን_በውሃ_ተጠመቀ?

እግዚአብሔር አምላክ በዘመነ ኦሪት ሰብዐ ትካትን በንፍር ውሃ ፈርኦንና ሰራዊቱን በኤርትራ ባሕር ካጠፋ በኋላ ሰዎች ውሃ ለመዓት እንጂ ለምሕረት አልተፈጠረም ይሉ ነበርና ለምሕረት እንደተፈጠረ ለማጠየቅ በውሃ ተጠመቀ ( ዘፍ 7÷17፤ ዘጸ 14÷1-29)


አንድም ውሃ እሳትን ያጠፋል እናንተም በውሃ ብትጠመቁ ከገሃነመ እሳት ትድናላችሁ ሲል ነው፡፡


አንድም ውሃ መልክን ያሳያል እናንተም በውሃ ብትጠመቁ መልክዓ ሥላሴን የአምላክን ቸርነት ርህራሔ ታያላችሁ ሲል ነው፡፡


አንድም በማር በወተት ቢጠመቅ ኖሮ እነዚህ ለባለጸጎች እንጂ ለድሆች አይገኝም ውሃ ግን በሁሉ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ጥምቀት የታዘዘ ለሁሉ ነው ሲል ነው፡፡


አንድም ማርና ወተት ቢታጠብበት ያቆሽሻል እንጂ አያነጣም ውሃ ግን እድፍን ያስለቅቃል እናንተም በማየ ገቦ ብትጠመቁ ከኃጢአት ትጠራላችሁ ሲል ነው፡፡


https://www.facebook.com/tewahdohamanotachin/


ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሀይማኖታችን (@ttewahdo) / Twitter


Tewahdo himanotachin - YouTube


https://t.me/tewhahdohaimanotachin 



Saturday, January 15, 2022

ጥር 7 ✝✞✝ እንኩዋን ለአጋእዝተ ዓለም "ሥላሴ" እና "ቅዱስ ሶል ዼጥሮስ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✝✞✝

 +*" ሥሉስ ቅዱስ "*+



=>ምሥጢራት በእምነት ለማይኖር: በትሕትናም ለማይቀርብ የሚገለጡ አይደሉም::
+እግዚአብሔር አንድም ነው: ሦስትም ነው:: ጊዜ ሣይሠፈር ዘመንም ሳይቆጠር እግዚአብሔር በስም: በአካል: በግብር ሦስትነቱ: በባሕርይ: በሕልውና: በመለኮትና በሥልጣን አንድነቱ የጸና አምላክ ነው::
+ከዓለም መፈጠር በፊት ስለ ነበረው ነገር የሚያውቅ ራሱ ሥላሴ ብቻ ነው:: ዓለምን ከፈጠረ በሁዋላም ምሥጢረ ሥላሴ (መለኮት) ብለን የምንማረው ትምሕርት እንድንና እንጠቀም ዘንድ እርሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ ነው::
+ይኼውም በየጊዜው እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ቅዱሳኑ የገለጠው ምሥጢር ነው:: ከዚህ አልፈን በሥጋዊ አዕምሯችን ጌታን "እንመርምርሕ" ብንለው ግን ፍጻሜአችን ሞት: ማደሪያችንም ገሃነመ እሳት መሆኑ አይቀርም::
+እግዚአብሔር በአንድነቱና ሦስትነቱ ሳለ ይህንን ዓለም ፈጠረ:: እግዚአብሔር ዓለምን ለምን ፈጠረ ቢሉ:- ስሙን ቀድሰን ክብሩን እንድንወርስ ነው:: ከዚህ የተረፈውን ምክንያት ግን ራሱ ያውቃል::
=>በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት): በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት) የሌለበት የዘለዓለም አምላክ: የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው:: አብ: ወልድ: መንፈስ ቅዱስ በስም: በአካል: በግብር ሦስትነት በባሕርይ: በሕልውናና በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው:: በዚህ ጊዜ ተገኙ: በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም:: መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና::
+ርሕሩሐን ናቸውና በእናት ሥርዓት "ቅድስት ሥላሴ" እንላቸዋለን:: የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም:: የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል:: በቤቱም መጥተው ያድራሉ::
+ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም:: አባታችን ቅዱስ አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን : በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል::
+አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ: እናታችን ሣራ በ89 ዓመቷ ሥላሴን በድንኩዋናቸው አስተናገዱ:: አብርሃም እግራቸውን አጠበ:: (ወይ መታደል!) በጀርባውም አዘላቸው:: (ድንቅ አባት!) ምሳቸውንም አቀረበላቸው:: እንደሚበሉ ሆኑለት:: በዚያው ዕለትም የይስሐቅን መወለድ አበሠሩት::
+ሥላሴን ያስተናገደች ድንኩዋን (ሐይመት) የድንግል እመቤታችን ማርያም ምሳሌ ናት:: በድንግል ላይ አብ ለአጽንኦ: መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ: ወልድ በተለየ አካሉ ለሥጋዌ በእርሷ ላይ አርፈዋል / አድረዋልና::
=>በዓለ ሥላሴ በዚህ ቀን የሚከበረው ስለ 2 ምክንያቶች ነው:: ቀዳሚው ሕንጻ ሰናዖርን ማፍረሳቸው ሲሆን 2ኛው ደግሞ ቅዳሴ ቤታቸው ነው::
+*" ሕንጻ ሰናዖር "*+
=>ሰናዖር ከሺዎች ዓመታት በፊት በአሁኗ ኢራቅ አካባቢ እንደ ነበረ የሚነገርለት ግዛት ሲሆን ስሙ ለሃገሪቱም: ለንጉሡም በተመሳሳይ ያገለግል ነበር:: ከናምሩድ ክፋት በሁዋላ ሰናዖርና ወገኖቹ ከሰይጣን ተወዳጁ::
+ከጥፋት ውሃ (ከኖኅ ዕረፍት) በሁዋላ በሥፍራው በአንድነት ይኖሩ ነበርና እርስ በርሳቸው "ኑ ሳንበተን ስማችን የሚጠራበትን ሕንጻ እንሥራ:: በዚያውም አባቶቻችን በውሃ ያጠፋ እግዚአብሔርን እንውጋው" ተባባሉ::
+ቀጥለውም ሰማይ ጠቀስ ፎቅን ገነቡ:: ከሕንጻው መርዘም የተነሳ በጸሐይ አብስለው በልተዋል ይባላል:: ቀጥለውም ጦር እያነሱ ፈጣሪን ሊወጉ ወርውረዋል::
+መቼም የእነዚህን ሰዎች ክፋትና ቂልነት ስንሰማ ይገርመን ይሆናል:: ግንኮ ዛሬ ሰለጠንኩ በሚለው ዓለም እየተሠራ ያለው ከዚህ የከፋ ነው:: ቸርነቱ ቢጠብቀን እንጂ እንደ ክፋታችንስ ጠፊ ነበርን::
+ርሕሩሐን ሥላሴ ግን የሰናዖር ሰዎች የሠሩትን አይተው ማጥፋት ሲችሉ አላደረጉትም:: የባሪያቸውን የኖኅን ቃል ኪዳን አስበዋልና:: ይልቁኑ "ንዑ ንረድ ወንክአው ነገሮሙ ለከለዳውያን-ቁዋንቁዋቸው እንደባልቀው" አሉ እንጂ::
+ከለዳውያን ልሳናቸው ተደበላልቆ 71 ቁዋንቁዎች ተፈጠሩ:: እነርሱም ስምምነት አጥተው ተበተኑ:: ሥላሴም ያን ሕንጻ በነፋስ ትቢያ እንዲሆን በተኑት:: ስለዚህም እስከ ዛሬ ሥፍራው "ባቢሎን (ዝሩት)" ሲባል ይኖራል::
+" ቅዳሴ ቤት "+
=>ልክ የዛሬ 324 ዓመት: አድያም ሰገድ ኢያሱ በኢትዮዽያ በነገሡ በ10ኛው ዓመት: (በ1684 ዓ/ም) በጐንደር ከተማ ንግሥተ አድባራት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተሰርታ ተጠናቃለች::
+ጥር 7 ቀንም ሊቁ ክፍለ ዮሐንስን ጨምሮ በርካታ ምዕመናን: ሠራዊት: መሣፍንትና ሊቃውንት ባሉበት ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሯል:: በዕለቱም ታላቅ ሐሴት ተደርጉዋል:: ኢያሱ አድያም ሰገድ ኃያል: ደግ: ጥበበኛ: አስተዋይ: መናኝ ንጉሥ ነውና::
+ቤተ ሥላሴን አስጊጿታልና ከዚህ ቀን ጀምሮ ጥር ሥላሴ በድምቀት የሚከበር ሆኗል:: ነገር ግን በተሠራች በ16 ዓመቷ ደጉ ኢያሱ ከተገደለ በሁዋላ ቤተ ክርስቲያኑ በአደጋ ፈርሷል:: ዛሬ የምናየው በ1708 ዓ/ም በልጁ በአፄ ዳዊት ሣልሳዊ የታነጸውን ነው::
+*" ቅዱስ ሶል ዼጥሮስ "*+
=>የሊብያው አርዮስ ጌትነት ገንዘቡ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክዶ ሊያስክድ ሲሯሯጥ በፈቃደ እግዚአብሔር: በጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጥሪ: 2348 ምሑራን ከመላው ዓለም ተሰበሰቡ::
+ከተሰበሰበው ብዙ ሰው መካከል የአበውን ደቀ መዛሙርት ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና: ምግባራቸው የጸና 318ቱ አበው ሊቃውንት ተገኙ::
+እነዚህ አባቶች "ሊቃውንት" ሲባሉ እንዲሁ በእውቀት ብቻ የበሰሉ እንዳይመስሉን:: 318ቱ አበው እኩሎቹ በዘመነ ሰማዕታት እጅና እግራቸውን የተቆረጡና ለሃይማኖታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው::
+እኩሎቹ ደግሞ በገዳማዊ ሕይወት ያጌጡ: ፍቅረ ክርስቶስ በውስጣቸው የሚነድ: የመንፈስ ቅዱስ ቤት ናቸው:: እስኪ እናውቃቸው ዘንድ የጥቂቶችን ማንነት በስምና መገለጫ እንመልከት::
1.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ (በዘመነ ሰማዕታት ለ22 ዓመት ሲቆራርጡት ኖረው በጉባኤው ላይ የተገኘው ያለ እጅ: እግር: ጀሮ: ከንፈር: ቅንድብ ነው)
2.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ (ስለ ቀናች እምነት ለ50 ዓመታት የተጋደለና ለ15 ዓመታት በስደት የኖረ ነው)
3.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ (ከሰማይ ብርሃን ይወርድለት የነበረ አባት ነው)
4.ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ (በጸሎቱ አጋንንትን ያንቀጠቀጠ: ነፍሳትን ከሲዖል የቀማና ከከዊነ እሳት የደረሰ አባት ነው)
5.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ (ስለ ቀናች እምነት መጸዳጃ ጉድጉዋድ ውስጥ ለ15 ዓመታት ተጥሎ የኖረ ሰማዕት ነው)
6.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሜራ (ከሕጻንነቱ የተቀደሰ: በበርሃ የተጋደለ: በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን የተቀበለ አባት ነው)
7.ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን (በደግነቱ ሙታንን ያስነሳ: ወንዝን በጸሎቱ ያቆመ: በንጽሕና የተጋደለ አባት ነው)
8.ቅዱስ ሶል ዼጥሮስ (ቅዱሱን ንጉሥ ያጠመቀ: ቁስጥንጥንያን በወንጌል ያበራ ሊቅ ነው)
9.ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ (ስለ ቀናች እምነቱ ብዙ ግፍ የደረሰበትና በስደት ያረፈ አባት ነው)
+እንደ አርዮስ ሐሳብ መድኃኒታችን ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ አይደለም (ሎቱ ስብሐት!!) ማለት ክርስትናን ከሥሩ ፈንቅሎ መጣል ነው::
+ስለ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ብሉይም ሐዲስም እየመሰከሩ:-
(ኢሳ. 9:6, መዝ. 46:5, 77:65, ዘካ. 14:4, ዮሐ. 1:1, 10:30, ራዕይ. 1:8, ሮሜ. 9:5 . . .)
አርዮስና የዛሬ መሰሎቹአንዲት ጥቅስ ይዘው ክርስትናን ከመሠረቱ ለመናድ መሞከራቸው በእርግጥም ከሰይጣን መላካቸውን ያሳያል::
+በወቅቱም በመወገዙ አርዮስ ወደ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ሔዶ ከሰሰ:: ቅዱሱ ንጉሥም የጉዳዩን ክብደት ተመልክቶ የዓለም ሊቃውንት ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ::
+በ325 ዓ/ም (በኛው በ318 ዓ/ም) ለ40 ቀናት የሚቆይ ሱባኤን ያዙ:: ሱባኤውን ሲጨርሱም በ4ቱ ፓትርያርኮች (እለእስክንድሮስ: ሶል ዼጥሮስ: ዮናክንዲኖስና ኤዎስጣቴዎስ) መሪነት: በእለእስክንድሮስ ሊቀ መንበርነት: በአትናቴዎስ ጸሐፊነት ጉባኤው ተጀመረ::
+በጉባኤው ሙሉ ስልጣን በሰማይ ከፈጣሪ: በምድር ከንጉሡ የተሰጣቸው አበው አርዮስን ተከራክረው ከነ ጀሌዎቹ ምላሽ አሳጡት:: ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ: ሥግው ቃል: ራሱም እግዚአብሔር መሆኑን አስረዱት::
+በጉባኤው መጨረሻም አልመለስም በማለቱ አርዮስን አወገዙ: ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚገባ አደራጁ:: አባቶችም ሥራቸውን ከጨረሱ በሁዋላ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ባርከው ወደየ ሃገረ ስብከታቸው ተመልሰዋል::
+ቅዱስ ሶል ዼጥሮስም ከጉባዔው ከተመለሰ በሁዋላ በጐ ጐዳናውን አቅንቶ ቀጥሏል:: ብዙ ድርሳናትን ደርሶ: በድካም ሰብኮ ኢአማንያንን መልሷል:: ፈላስፎችንም ድል ነስቶ አሳምኗል:: መናፍቃን ደግሞ ፈጽመው ይፈሩት ነበር:: ሊቀ ዽዽስናን በተሾመ በ11 ዓመቱም በዚህች ቀን ዐርፏል::
=>የሥላሴ ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁንና ጥር 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.በዓለ ሥሉስ ቅዱስ
2.ቅዱስ ሶል ዼጥሮስ
3.ቅዱስ ኤፍሬም
4.ቅዱስ ሰሎሞን
=>ወርሐዊ በዓላት
1.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
2.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
3.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
4.አባ ባውላ ገዳማዊ
5.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
6.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)
=>+"+ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ: የእግዚአብሔርም ፍቅር: የመንፈስ ቅዱስም ሕብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን:: አሜን:: +"+ (ቆሮ. 13:14)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

Source : ዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ facebook page