Saturday, February 26, 2022

🛑 የዐቢይ ጾም ሳምንታት - ዘወረደ 🛑


 የአብይ ጾም ሳምንታት 8 ናቸው፤
1.     ዘወረደ
2.    ቅድስት
3.    ምኩራብ
4.    መጻጉዕ
5.    ደብረዘይት
6.    ገብርሔር
7.    ኒቆዲሞስ
8.    ሆሣዕና



ስያሜአቸውና ትርጉማቸውም ፤


d

የአቢይ ጾም ሦስቱ ክፍሎች
1.     ወረደ (ጾመ ሕርቃል)፤ ይህም ጾሙ ከሚገባበት ሰኞ ጀምሮ እስከ እሑድ ያረስ ያለው 7 ቀን ነው።
2.    የጌታ ጾም፤ ይህም ከቅድስት ሰኞ እስከ ሆሣዕና ዋዜማ ዓርብ ድረስ ያለው 40 ቀን ነው።
3.    ሕማማት፤ ይህም ጌታችን በአልዓዛር ቤት ለማዕድ ከተቀመጠበት የሆሳዕና ቅዳሜ ጀምሮ እስከ ሥዑር ቅዳሜ ያለው መከራን የተቀበለበት 8 ቀን ሕማማት ነው።


ይህም 7+40+8 = 55 ቀን ማለት ነው።

«ዘወረደ» ማለት «የወረደ» ማለት ነው፡፡  አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ ማለት ነው። ይህም  ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  እኛን ለማዳንና ፍቅሩን ሊገልጽልን ከሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም የእኛን ሥጋ መዋሐዱን የሚያዘክር፤  ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመላክት፣ የሚታወስበት፣ የሚነገርበት  የዐቢይ ጾም አንደኛው ሳምንት   ነው፡፡ዮሐ.3-13፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም በገባዉ ቃልኪዳን መሰረት “  የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ልጁን ላከ” እንዳለ ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስ የጠፋዉን አዳም ፍለጋ ከአባቱ እሪና ሳይጎድል ሳይለይ ከሰማይ መዉረዱን የምናዘክርበት በዓል ነዉ።  ይህ ጾም የጾም መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት የምንጾመው ጾም ሲሆን ሕርቃል የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም “ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅየ አድንኃለሁብሎ ለአዳም ቃል ገባለት ፡፡ ዘፍ.   ፲፭  ይህ ኪዳነ አዳም ይባላል ፡፡ የቃል ኪዳን ሁሉ መሠረት ነው ፡፡ ሁለቱን ኪዳናት (ብሉይ ወሐዲስ) በፅኑዕ ተስፋ ያስተሳሰረ የረጅም ዘመናት የድኅነት ሰንሰለት ነው ፡፡ ዘወረደ እርቀ አዳም   ተስፋ አበው ትንቢተ ነቢያት ሱባኤ ካህናት መፈፀሙ ኪዳነ አዳም መሲህ መወለዱ የሚነገርበት የፍቅር አዋጅ ነው ፡፡ \ ከሰማየ ሰማያት የወረደውን፣ ከድንግል ማርያም የተወለደውን በጥንት ስሙ ወልድ፣ ቃል በኋላ ስሙ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አማኑኤል የተባለውን ሰው የኾነውን አምላክ ለማመስገን ርደቱን (ከሰማየ ሰማያት መውረዱን) ለመዘከር የሚጾም ጾም ነው፡፡ ጌታችን ጾመ ከማለት አስቀድሞ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም መወለዱን መናገር አስፈላጊ ነውና የመጀመሪያው ሳምንት ‹ዘወረደ› ተብሏል፡፡ ‹‹አንተ በሰማይ ወአንተ በምድር ወአንተ በባሕር ወአንተ በየብስ፤ አንተ በሰማይ አለህ፤ በምድር በባሕርም በየብስም አለህ፤›› የተባለውን በሰማይ በምድር ምሉዕ የኾነውን አምላክ ‹ወረደ፤ መጣ› ብሎ መናገር ‹ሰው ኾነ› ማለት ነው፡፡ ሰው ኾኖ መገለጡን ለማስረዳት ነው እንጂ መውረድ መውጣት የሚባሉ ቃላት በዅሉ ምሉዕ ለኾነው መለኮት አይስማሙትም፡፡ ቃላቱ ሰውኛ አነጋገርን የሚያመለክቱ ናቸውና፡፡ መተርጕማን አበው ‹‹‹ዘወረደ› ማለት ‹ሰው የኾነ› ማለት ነው›› ብለው ይተረጕማሉ፡፡ አምላካችን ሰው ከኾነ በኋላ ‹መጣ፤ ሔደ፤ ወረደ፤ ዐረገ› የሚሉ ቃላት ይስማሙታል፡፡ ምልዓቱን ሳይለቅ በሰው አካል ተወስኖ ታይቷልና፡፡ ስለዚህ ‹ወረደ› እግዚአብሔር ሰው ኾኖ መገለጡን፤ ‹ዐረገ› ደግሞ የሰውነቱን ሥራ መፈጸሙን ያሳያል፡፡ ዐረገ ስንልም ቀድሞ በሰማይ የለም ለማለት አይደለም፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ በዓለሙ ዅሉ ምሉዕ ነውና፡፡ጾሙን ሐዋርያት፣ ስያሜውንና የምስጋናውን ሥርዓት ቅዱስ ያሬድ አዘጋጅተዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ነቢያትን በንባብ፤ ሐዋርያትን በስብከት፤ ሊቃውንትን በትርጓሜ፤ መላእክትን በዜማ ይመስላቸዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ የመላእክትን የምስጋና ሥርዓት ወደ ምድር አምጥቷል፡፡ የነቢያትን ትንቢት፣ የሐዋርያትን ትምህርት በሚገባ ተርጒሞ፣ አብራርቶ፣ አመሥጥሮ አዘጋጅቶታል፡፡ ሐዋርያት

ጾሙን ጾመው የጾም ሕግ ደንግገዋል፤ ቅዱስ ያሬድም ለጾሙ ስያሜ ሰጥቶ ምስጋና ከነሥርዓቱ አዘጋጅቶ

አቅርቧል፡፡ቤተ ክርስቲያናችንም የመጀመሪያው የዐቢይ ጾም ሳምንትን (ዘወረደን) ስያሜ እንደ ቅዱስ ያሬድ

ከሐዋርያት ተቀብላ ታስተምራለች፡፡ ይህ የመጀመሪያው ሳምንት ‹ጾመ ሕርቃል› እየተባለም ይጠራል፡፡ ሕርቃል   (ኤራቅሊዮስ) በ፮፻፲፬ ዓ.ም የነበረ የቤዛንታይን ንጉሥ ነው፡፡ ለክርስቲያኖች ባደረገው ርዳታ ምክንያት አንድ ሳምንት ጾመውለት ነበር፡፡ ያላወቁ ‹ጾመ ሕርቃል› ብለው አንድ ጊዜ ጾመው ትተውታል፡፡ ጥንቱን የቅዱሳን ሐዋርያት መኾኑን ያወቁ ምእመናን ግን ዅልጊዜ በየዓመቱ ይጾሙት ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ጾመ ሕርቃል እየተባለ ይጠራል፡፡ ሙሉ ታሪኩ በፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ አንቀጽ ፲፭ ላይ ይገኛል፡፡ 

 


ዘወረደ ማለት?

v የምስጢረ ሥጋዌ ትምህርት ነው
v ፡፡ ዘወረደ ስንል አምላክ መጣ ፤
v ወረደ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ ፤
v በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆነ ማለታችን ነው ፡፡
v ዘወረደ በአምላክ ትህትና ክብረ አዳም የሚነገርበት ነው ፡፡
v አምላክ ሰው በመሆኑ ሰው አምላክ ሆነ ፤ ከበረ ፤ ገነነ ፤ ነገሠ ፡፡
v ሕያው አምላክ ክርስቶስ በቅድስት ሞቱ ሟቹን አዳም ዘላለማዊ ሕያው አደረገው ፡፡
v  አምላክ ወልደ አምላክ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ሞቶ ለአዳም ያለውን ታላቅ ፍቅር ገለጸ ፡፡
v የተጣላውን አዳምን በፈቃዱ ታረቀው ፡፡
v ጠላቶቹ ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን ፥ ይልቁንም ከታረቅን በኃላ በሕይወቱ እንድናለን ፡፡ ሮሜ. ፥ ፲ ፡፡ በዚህም ትህትናን ፍቅርን አስተማረን ፡፡ 

የመጀመሪያ የአቢይ ጾም መግቢያ እሁድ ዘወረደ ይባላል ደግሞም ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ስያሜውም፤ በ614 . ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ጥቃት አደረሰ፡፡ በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ በሠራችው ቤተመቅደስ ውስጥ ሲገባ ንግሥቷ በክብር አስቀምጣው የነበረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው፡፡ ቢነካው አቃጠለው ዲያቆናቱን አሸክሞ ሌላውን ንዋየ ቅድሳት ዘርፎ 60 የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ 3 የሚሆኑትን ማርኮ ከተማዋንም አቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንጉሩ ገብተው የተሸሸጉ ተሰብስበው 14 ዓመት በኋላ 628 ጩኸታቸውንና የደረሰባቸውን በደል ለክርስቲየኑ የሮም ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል፡፡ እርሱም ሐዋርያት ሰውን የገደለ እድሜውን በሙሉ ይጹም ስላሉ እንዴት ላድርገው አላቸው እኛ የአንተን እድሜ ተከፋፍለን እንጾማለን ብለው አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸው ጾሙን በሚገባ ጾመውታል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና የተማረኩ ክርስቲያኖችን ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ ተነሳበት ድል ለሕርቃል ሆነና መስቀሉን ያለበትን አጥቶ ሲቸገር መስቀሉን ሲቀብርና ዲያቆናቱን ሲያስገድል በመስኮት ሆና ያየችው ከኢየሩሳሌም የተማረከች አንዲት ብላቴና አሳይታው አውጥቶ በልብሰ መንግሥቱ ጠቅልሎ ወደ ቁስጥንጥንያ ተመለሰ፡፡ የተማረኩት በሙሉ ነጻ ወጡ ይህን ለማሰብ ለማስታወስ በተጨማሪ በኃጢአት ላይ ድል እንድናገኝ መንፈሳዊ ጦር በውስጣችን እንዲበዛልን መስቀልህ ከምርኮ እንደተመለሰ እኛንም ከኃጢአት ምርኮ መልሰን ለሕርቃል ድል መንሳትንና በጠላቶቹ ላይ ኃይልን እንደሰጠኸው ለእኛም በኃጢአት ላይ ድል መንሳት መንፈሳዊ ኃይልን ስጠን እያልን እንጾመዋለን፡፡ በጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡እዚህ ላይ በዚያን ጊዜ ለሕርቃል ሕዝቡ ሱባኤ ይዞለታል፡፡ ዛሬም እኛ ለቤተክርስቲያን ያደረግነውን በማሰብ እግዚአብሔር አምላክ ለሕርቃል የሰጠውን በጠላቶቹ ላይ ድል መንሳትን ለእኛም እንዲሰጠን የምንጠይቅበት ስለሆነ የመጀመሪያውን ሳምንት በሕርቃል ሰይመን ጾሙን እንጾማለን፡፡የእኛ ጠላት የጨለማ ገዥ የሆነው ዲያቢሎስ ነውና እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡ ጾም ስጋችንን ለነፍሳችን የምናስገዛበት ከፈጣሪ ጋር የምንገናኝበት የጽድቅ መንገድ ለስጋ ጤንነትም ቢሆን አስፈላጊያችን የሆነ አንዱና ዋነኛዉ የጽድቅ እቃ ጦራችን ነዉ፡፡ሆኖም የጾም ወቅት ሲመጣ አቀበት የሚወጡ ይመስል የሚፈሩትና የሚያማርሩት ሳይሆን እንኳን መጣልን ተብሎ  በጉጉት የሚናፈቅ መሆን አለበት፡፡ስለሆነም ማንኛዉም ሰዉ ጾሙን ሲጀምር የሚከተሉትን ጉዳዮች በደንብ ሊያጤናቸዉ ይገባል፡፡


የዲያብሎስን ሥራ ሊያፈርስየተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅም በፆም ድል ማድረግን ለእኛ አስተምሮናል። እኛምበዚህ በአብይ ፆም የለመነውና የጠየቅነው ነገር ሁሉ ከኃጢአት በስተቀርእንዲከናወንልን ፆምን ገንዘባችን እናድርግ። በፆም የተጠቀሙ ቅዱሳን አባቶችና ቅዱሳንእናቶች እንዳሉን እናስተውል። በተለይ አሁን በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰበሚታየው አስቸጋሪ ፈተና እያንዳንዳችን ልባዊ ፆም በመፆም ልዑል 
እግዚአብሔር የፀሎታችንን ምላሽ እንዲሰጠን እንማፀን።

ጾም ጸሎታችን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይቀበልልን አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment