Monday, June 9, 2014

እንኳን አደረሳችሁ, ለጦመ ሐዋርያት በሰላምና በጤና አደረሰን:

እንኳን ለጦመ ሐዋርያት በሰላምና በጤና አደረሰን:


LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

በዓለ መንፈስ ቅዱስ/ጰራቅሊጦስ

በዓለ መንፈስ ቅዱስ/ጰራቅሊጦስ

ምንም እንኳን የዕለታትና የዘመናት ሁሉ ባለቤት እርሱ እግዚአብሔር ቢሆንም በእኛ በክርስቲያኖች ዘንድ ነገር ሁሉ በሥርዓት ይሁን ብሎ ሐዋርያው እንዳስተማረን በቤተክርስቲያናችን የበዓላት ሥርዓት መሠረት ከትንሣኤ በኋላ ፶ኛው ቀን በዓለ ጰራቅሊጦስ/በዓለ ሃምሳ/በዓለ ጰንጠቆስጢ ወይንም የቤተክርስቲያን የልደት ቀን በመባል ይታወቃል ወይንም ይከበራል። በግሪክ ቋንቋ ጰራቅሊጦስ ማለት አጽናኝ ማለት ነው።

መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ሥላሴ አንዱ ሲሆን ከአብ የሰረጸ ከአብና ከወልድ ጋር በመለኮት በስልጣን በአገዛዝ በመሳሰሉት እኩል ወይንም አንድ ነው። እንደ እግዚአብሔር አብ እና እንደ እግዚአብሔር ወልድ(ኢየሱስ ክርስቶስ) መንፈስ ቅዱስ በራሱ የተለየ አካልና ግብር አለው። ዮሐ.፲፭፥፳፮። መንፈስ ቅዱስ ከዘመናት አስቀድሞ ከአብና ከወልድ ጋር ዓለማትን የፈጠረ ነው። ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙር ፴፪፥፮ ላይ <በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ> ሲል ተናግሯል።

መንፈስ ቅዱስ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበትን አላማ አበክሮ የሚገልጽና ጌታችንም ወደ ቀደመ ክብሩ በምስጋናና በእልልታ ካረገ በኋላ በ፲ኛው ቀን ለሐዋርያት ጸጋውን በማፍሰስ የተገለጸ የቤተክርስቲያን ጠባቂና መሪዋ፤ በእግዚአብሔር ልጅ ያመኑትንና በስሙ የተጠሩትን ክርስቲያኖች የሚያጽናና፣ በኃይማኖት በምግባርና በተጋድሎ የሚያጸና፣ ጥበብንና ማስተዋልንም የሚያድል ነው (ኢሣ.፲፩፥ ፪)። ክርስቲያኖች ከጌታ የተማሩትን መልካም የሆነውን የጽድቅ ሥራ እንዲሠሩ ዘወትር በልቦናቸው አድሮ የሚያሳስብ እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው። <አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔ የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል> ዮሐ. ፲፬፥፳፮ በማለት ሐዋርያት/ክርስቲያኖች በሚሠሩት ሥራ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ እንደማይለያቸው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሯል።

መንፈስ ቅዱስ በእምነት ጸንተው በጸሎት ለሚተጉ ክርስቲያኖች ሁሉ የሚሰጥ ኃብት ነው። በተለይም በአንድ ልብ ሆኖ በኅብረት በሚደረግ ጸሎት ምልጃና ጉባዔ መንፈስ ቅዱስ በቶሎ ይሰጣል/ይወርዳል/ይገኛል፤ ለሁሉም እንደ ችሎታውና እንደ አቅሙም ፀጋንና ስጦታን ያድላል። <በዓለ ኀምሳም የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፥ ተቀምጠው የነበረበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በእያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው
በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር> ሐዋ.ሥ. ፪፥ ፩-፬

መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው ሰዎች መንፈሳዊ ሥራ እንዲሠሩና ሌሎችን ወደ እግዚአብሔር እንዲስቡ እነርሱም በረከትን እንዲቀበሉ ነው። ይህም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ልዩ ልዩ እነደሆነ ሐዋረያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ እንዲህ በማለት ዘርዝሮታል፦ የጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው አሠራርም ልዩ ልዩ ነው ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ ለአንዱም ትንቢትን መናገር ለአንዱም መናፍስትን መለየት ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል። (፩.ቆሮ.፲፪፥፬-፲፩)

እዚህ ላይ በተለይ በልሳን የመናገር ስጦታ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ልሳን ማለት በአንደበት የሚነገር ትርጉሙንም ቋንቋው ሲነገር የቋንቋው ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች ሁሉ የሚረዱት የሰው ልጆች ልሳን/ቋንቋ ነው። አንዳንዶች የተለየ በዚህ ዓለም ያሉ ሰዎች የማይረዱትን ነገር እንደሚያውጡት ያለ ድምጽ እንዳልሆነ መረዳት ይገባል። በዚህ የተታለሉ እኅቶችና ወንድሞች አሉና። ሐዋርያት በልሳን በተናገሩ ጊዜ በዙሪያቸው የነበሩ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ሰዎች የእነርሱን ሃገር ልሳን/ቋንቋ ሲናገሩ ሰምተው ተገረሙ ነው የሚለው ቅዱስ ሉቃስ ( ሐዋ.፪ ፥፭-፲፫ )

ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ የወረደበት ዋናው ምክንያት ሐዋርያት ዓለምን ዞረው አሕዛብን ሁሉ በየቋንቋቸው በማስተማር የክርስቶስ መንግሥት ተካፋይ እንዲሆኑ ዕድል ፈንታ ይኖራቸው ዘንድ ነው። ሌላው በእምነትና በጽናት ተስፋ ለሚያደርጉት ሁሉ ሳይሳሳ በልግስና የሚሰጥ ቸር አምላክ መሆኑን ሲያስተምረን ነው። በዮሐንስ ወንጌል ፫፥ ፴፬ ላይ <እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና> ተብሎ እንደተጠቀሰው። በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ <ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም> ዮሐ.፲፬፥፲፰ ያለውን ቃል ይፈጽም ዘንድ ነው።

መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ወረደ ሲባል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአካል ሥጋ ለብሶ እንደተገለጸው ያለ አገላለጽ ሳይሆን ጸጋውን አደላቸው ማለት ነው። እግዚአብሔር ወልድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከደሟ ደምን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ሰው ሆኖ እግዚአብሔርን አሳይቶናል፤ አይተነዋል። ለዚህም <...እኔን ያየ አብን አይቷል...> ዮሐ.፲፬፥፰ ብሎ በቅዱስ ቃሉ በሕገ ወንጌሉ አስተምሮናል። መንፈስ ቅዱስ ግን የማይታይ የእውነት መንፈስ ነው። የሚታየው/የሚገለጸው በሚያሠራው በጎ ሥራ ነው። ዘወትር በምንሠራው የጽድቅ ሥራ ወይንም በደልና ኃጢአትን በሠራን ጊዜም በውስጣችን ሆኖ ሲወቅሰን መንፈስ ቅዱስ ከኛ ጋር እንዳለ እናውቃለን። <እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለም ከእናንተ ጋር እንዲሆን ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለሆነ ሊቀበለው የማይችለው የእውነት መንፈስ ነው ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሰጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ> ዮሐ.፲፬፥፲፭-፲፯።

መንፈስ ቅዱስ ክርስቲያኖች በድፍረት የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት እንዲመሰክሩ የሚያደርግ ነው ፩ቆሮ. ም.፲፪፥፫ የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት መመስከር ሲባልም በዘመናችን እንደምንሰማውና እንደምናስተውለው በብዙ ክሕደት ውሰጥ ሆኖ ኢየሱስ ጌታ ነው ማለት ብቻ ሳይሆን የእርሱን አምላክነት በማመን ጌትነቱ አምላካዊ የሆነና እርሱ ራሱ ምልጃን ተቀባይ እንጂ አማላጅ እንዳልሆነ በማመን መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። መንፈስ ቅዱስን የተቀበልን ክርስቲያኖችም ዘወትር በተሰጠን ፀጋና ችሎታ ቤተክርስቲያንን፣ ሌሎች ወንድሞችና እኅቶችን፣ ኅዙናንን ማገልገል ባጠቃላይ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ተብለው በሐዋርያው በቅዱስ
ጳውሎስ የተማርነውን ለመፈጸም መትጋት ይኖርብናል። እነዚህ የመንፈስ ፍሬዎች የተባሉትም ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ናቸው (ገላ.፭፥፳፪-፳፫)። መንፈስ ቅዱስን የተቀበልን ሲባልም በሥርዓተ ቤተክርስቲያን በ፵ እና በ፹ ቀን በጥምቀት የተቀበልነውን ነገር ግን በውስጣችን ተዳፍኖ ያለውን መንፈስ በበጎና በጽድቅ ሥራ መቀስቀስ ማለት ነው ። አንዳንድ የዋሃን እንደሚሉት አዲስ መንፈስ እስኪወርድልን እንደ ሐዋርያት በአንድ ቦታ ተሰብስበን ቤት ዘግተን እንቀመጥ ማለት እንዳልሆነ ልናውቅ ያስፈልጋል። እርሱም የሚያረጋጋና የሚያስደስት እንጅ የሚያስገዝፍና የሚያስጮህ እንዳልሆነ ማስተዋል ይገባናል ።

ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ሥራውን በኛ ላይ እንዲሠራ በሃይማኖት ጸንተን ራሳችንን ከክፉ ገነር በማቀብ እንድንኖር ያሻል። የያዕቆብ ወንድም ይሁዳም በመልዕክቱ እንዲሁ እንድናደርግ ነው የሚያሳስበን <እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስ እየጸለያችሁ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ> ይሁዳ ፩፥፳። በቤተክርስቲያናቸን ትምህርት መሠረት መንፈስ ቅዱስ የሚወርደው /የወረደው በተለያዩ ምሳሌዎች ነው። በሰው ተመስሎ የተገለጸበት ጊዜ አለ (ዘፍ. ፲፰፥፩) ፣ በርግብ ተመስሎ የወረደበት ጊዜ አለ (ማቴ. ፫፥፲፮)፣ በእሳት የተመሰለበት ጊዜ አለ (ሐዋ.፪፥ ፫፤ ማቴ. ፫፥፲፮)ስለሆነም ዘመናችን ብዙ የሐሰት ትምህርት የሞላበት በተለይም መንፈስ ቅዱስ ወረደልኝ፤ ይወርድልሃል፤ ይወርድልሻል፤ በሚል ማጭበርበርና ማደናገር ብዙዎች ከእውነት የተለዩበት በሐሰት መንፈስ የተወሰዱበት በመሆኑ እውነተኛውን መንፈስ ከሐሰተኛው መንፈስ ለይተን እንድናውቅ ያስፈልጋል። 

በመጨረሻም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ <የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን>ብሎ በ፪ኛ.ቆሮ.፲፫፥፲፬ ላይ አንድ እንሆን ዘንድ በኃይሉ እንዲያበረታን እንደጸለየልን እውነትን አውቀንና ተረድተን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ያስተማረችንንና የምታስተምረን ተገንዝበን እንድንኖር እርሱ መንፈስ ቅዱስ ይርዳን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር

Source: ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ሰ/ት/ቤ/ት/ክ

LIKE OUR PAGE >>>

ግንቦት 28

ግንቦት 28 በዚህች ቀን ዓለምን ንቃ የተወች ገዳማዊቷ ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ አረፈች። በበርሃ የሚኖረው አባ ዳንኤል ስለዚህች ሴት እንዲህ አለ፤ ከዕለታት በአንዱ ቀን በጨረቃ ብርሃን በርሃውን አቋርጬ ስጓዝ ተራራ ላይ የተቀመጠ ሰው አየው ግርማው ያስፈራል መላ ሰውነቱን ጸጉር ሸፍኖታል ሰው ይሁን መንፈስ ልረዳ ቀረብኩት እርሱ ግን እንደተመለከተኝ ሮጦ የተሰነ...ጠቀ አለት ውስጥ ገብቶ ተደበቀ፤ ሰው እንደሆነ አወቅኩኝ፤ አባቴ በረከትህን እሻለሁና ወደ ዋሻው አስገባኝ ብዬ ለመንኩት፤ እርሱ ግን ወደኔ መግባት አይቻልህም አለኝ፤ የሴት ድምጽ ነው፤ ለምን አለኳት፤ እርቃኔን ነኝ አለችኝ፤ የለበስኩትን አጽፍ አኖርኩላት እርሱን ለብሳ ወጣች፤ ታሪኳን ሁሉ ነገረችኝ፤ በዘንቢል ሽንብራ በኮዳ ውኃ ይዛ ከወላጆቿ ቤት እንደወጣች ለ 38 ዓመት በኤርትራ በርሃ ሰው ሳታይ ብቻዋን በተጋድሎ እንደኖረች ነገረችኝ እኔም ጻፍኩት ይለናል፤ ይህች ቅድስት እናት ኢትዮጰያዊት እንደሆነች የትውልድ ቦታዋም ሸዋ ውስጥ ተጉለት እንደሆነ በአገራችን አንድ ገዳም እንዳላት ሊቀ ብርሃናት መርቆርዮስ አረጋ "የኢትዮጰያ ተወላጆች ቅዱሳን" በሚል መጽሐፋቸው ጠቅሰውታል፤ ስንክሳሩም ሰርቶላታል፤ ግንቦት 28 በዛሬዋ ቀን እረፍቷ ነው። በረከቷን ያድለን።

LIKE OUR PAGE >>>

ግንቦት 26

ግንቦት 26 
በዚህች ዕለት ዲዲሞስ የተባለው ሐዋርያው ቶማሰ አረፈ፤ እርሱም በላይንደኬ በዛሬዋ ህንድ ወንጌልን ሰብኮ ብዙዎችን አሳመነ በዚህም መኮንኑ ተቆጥቶ ጽኑ ስቃይ አሰቃየው ቆዳውንም ገፈፈው፤በሰውነቱም ላይ ጨውና ቆምጣጣ አፈሰሱበት፤ይህንን ሁሉ ታገሰ፤በተገፈፈ ቆዳው ስምንት ሙታን አስነሳ ብዙ ገቢረ ታአምራትን አደረገ፤ይህንን አይተው መኮንኑን ጨምሮ ብዙዎች አመኑ።ከዚህ በኃላ በአቴናና መቄዶንያ ገብቶ ሰበከ ንጉሱም ይዞ አሰቃየው በመጨረሻም በጦር ተወግቶ በዛሬዋ ዕለት በሰማዕትነት አረፈ። የጌታን ጎን የዳሰሰች የሐዋርያው ቀኝ እጅ ተአምራትን እያደረገች እስከ ዛሬ በህንድ አለች፤
በረከቱ ይደርብን

LIKE OUR PAGE >>>

ግንቦት 24

ግንቦት 24

 በዚህች ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን እግዚያብሔርን ይዛ ከዮሴፍና ከሶሎሜ ጋር ወደ ግብጽ የተሰደዱበት ቀን ነው፤ ይህን ቀን ቤተክርስቲያን በደማቁ አክብራው ትውላለች፤ በመዲናችን አዲስ አበባ እንጦጦ መንበረ ንግስት ቁስቋም ቤተክርስቲያን እንዲሁም ቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ታቦተ ሕጉ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል። “እነሆ፥ የጌታ መል...አክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ። ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ። ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ። ማቴ 2፤13 በስደት የቆዩት ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ነው የእመቤታችን ስደት ለኢትዮጵያ ታላቅ በረከት ነው የጣና ደሴቶችን የዋልድባ ገዳምን አክሱምና የትግራይ አውራጃዎችን፤ ድብረ ዓባይና የጎጃም ታላላቅ ገዳማትን በርካታ የኢትዮጵያ አውራጃዎችን በኪደተ እገራቸው ባርከውታል ቀድሰውታል።፤ “የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ አለ ነብዩ ዕንባቆም፤ ዕንባቆም 3፤7። ነብዩ ምን ማለቱ ነው ? መቼ ነው የኢትዮጰያ ድንኳኖች የተጨነቁት ? እመቤታችን በስደት ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣም እይደል። ግን ግን ስደቷ ግንቦት 24 ከሆነ ለምን ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 6 ቀን የጽጌ ጾም ብለን ስደቷን እናስባለን ካሉ፤ይህ ሊቃውንቱ የሰሩት ስርዓት ነው፤ ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 25 በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ዘመነ ጽጌ ይባላል የአበባ የልምላሜ ወቅት ነው፤ እመቤታችን ደግሞ በአበባ ትመሰላለች አበባ የፍሬ እናት ነው፡፡ እመቤታችንም የተባረከ ፍሬ መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርሰቶስን ያስገኘች አማናዊቷ አበባ ናት፡ ስለዚህም ይህን የስደቷን ወራት በዘመነ ጽጌ ባሉት 40 ቀናት ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 6 ቀን ታስቦ እንዲውል የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ስርዓትን ሰሩ። 
እግርሽ ጨረቃን የሚጫማ 
በአሸዋ ስትሮጪ እግርሽ ደማ
ውቅያኖሶቹ ግራ ቀኙ የሚሰፈሩት በእፍኙ
ለእርሱ ለእርሱ ለዝናብ ጌታ ውኃ ነሱ።
ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>

እንኳን ለጌታችን ለመድሐኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የእርገት በዓል አደረሳችሁ !!!በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አ፩ዱ አምላክ አሜን

“እያዩት ወደሰማይ ዐረገ”(ሉቃ 24÷50 የሐዋ 1÷9)
ዕርገት

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል ነሥቶ
የትንሣኤያችን በኩር የሆነው ጌታ በመቃብሩ ቦታ
- ለማርያም መቅደላዊት እና ለሌሎችም ሴቶች (ማቴ 28÷1 የሐዋ 2÷1)፡፡
- ለኤማውስ መንገደኞች( ሉቃ 24÷13)
- ለደቀማዛሙርቱ በተዘጋ ቤት (ዮሐ 20÷8)
- በጥብርያዶስ ባህር ለደቀመዛሙርቱ ዮሐ 21÷4 
ሥርዓትን እያስተማረ አልፎ አልፎም በግልጥ እየታየ ፍርሐታቸውን እያስወገደ አይሁድ እንደሚሉት ሥጋውንም ደቀመዛሙርቱ እንዳልሰረቁት ይልቁንም በሞት ላይ ሥልጣንኑን አሳይቶ መቃብሩን ባዶ አድርጐ በትንሣኤው አለት ላይ ያቆመን፣ ሞት በእርሱ እንደተሸነፈ የማይታየው እየታየ፣ ዘመን የማይቆጠርለት፣ ዘላለማዊ ጌታ የማይዳሰሰው እየተዳሰሰ ለ40 ቀናት ያክል ቆይቶ ተከታዮቹን ሐዋርያትን ወደቢታንያ አወጣቸው፡፡ እያዩት በምስጋና ወደሰማይ ዐረገ፡፡ እንዲህ ተብሎ በነብዩ ዳዊት እንደተፃፈው፡- “ዐረገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለቀርን ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ” እግዚአብሔር በመለከት ድምጽ ዐረገ፣ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ፣ ዘምሩ ለንጉሣችን ዘምሩ (መዝ 46÷5)

አምላካችን ወደሰማይ ከማረጉ በፊት ደቀመዛሙርቱን ምን አዘዛቸው?

1. ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፡፡ (ሉቃ 24÷48) ደቀመዛሙርቱ ያዩትንና የሰሙትን ሞትን አሸንፎ የተነሣውን ጌታ ለዓለም ሁሉ ምስክሮች ሆነዋል፡፡ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ የዓላውያንን ነገሥታት፣ የቄሳሮችን ዛቻና ማስፈራሪያ አንዳችም ሳይፈሩ ከምድር ዳርቻ እስከምድር ዳርቻ ድረስ ሁሉን እያጡና መከራ እየተቀበሉ፣ እየታሰሩና እየተገረፉ ምስክሮች ሆነዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ በኋላ ስሙን አትጥሩና በስሙም አታስተምሩ እያሏቸው በሸንጐ ፊት ሲያቆሟቸው፣ ሲገርፏቸው ደስ እያላቸው ከሸንጐ ፊት ይወጡ ነበር፡፡ (የሐዋ 5÷40)፡፡ ስለ ስሙ ምስክር መሆን መነቀፍና መታሰር፣ መደብደብ እንዴት ደስ ይላል!፡፡ እኛም እንደ ደቀመዛሙርቱ ማንንም ሳንፈራ አፋችንን ሞልተን ስለ ስሙ እየመሰከርን ሁሉን ብናጣም ሞታችንን በሞቱ ድል የነሣልንን የሚቃወመንን ጠላታችንን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ያስወገደልንን፣ እረፍትና ሰላም የሰጠንን፣ ጨለማውን ገፎ ብርሐንን ያጐናፀፈንን፣ ያለፈውን ታሪካችንን በነበር ላስቀረልን ምስክሮች እንሁን፡፡

2. አጽናኙን እልክላችኋለሁ (ዮሐ 15÷26)፡-
- በአህዛብና በዓላውያን ነገሥታት ፊት ሲቆሙ እውነትን እንዲናገሩ የሚያፅናና ኃይል፣
- ከተዘጋ ቤት ወደ ሠገነት እንዲቆሙ የሚያደርግ ኃይል፣
- ልበ ሙሉ ሆነው ከጥርጥር ወደ ፍፁም እምነት፣ ከፍርሃት ወደ ድፍረት እንዲሸጋገሩ የሚያበረታታ አጽናኝ ኃይል እልክላችኋለሁ፡፡
ይህ ኃይል በዘመናችን በጣም ስለሚያስፈልገን በፍፁም መዘንጋት የለብንም፡፡ እውነትን ለመናገርና ለመመስከር፣ ፍርሐታችን እንዲወገድልን ከፈለግን ይህንን ኃይል ዓለም ሳይሆን የሚሰጠን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን አውቀን ጌታ ሆይ እኔን ልጅህ ያንተን ኃይል አጥቼ ደክሜያለሁ፣ ከእኔ የሆነ ኃይል ምንም የለምና ከእኔ አትራቅ፡፡
- ባስልኤልንና ኤልያብን በጥበብ መንፈስ የሞላህ (ዘፀ36÷2)
- ሶምሶንን በጾርዓና በኤሽታኦል ያነቃቃህ (መሳ 14÷18)
- ለደቀመዛሙርቱ ኃይልህን ልከህ 71 ቋንቋ የገለጥክ፣ በየዘመናቱ የተመረጡ አገልጋዮችህ ያፅናናህ፣ የእውነትን ቃል እየላክ ያበረታታህ እኛም እንድንበረታ ኃይልህን ከአርያም ላክልን፣

3. በኢየሩሳሌም ቆዩ (ሉቃ 24÷49)፡- ደቀመዛሙርቱ ከቢታንያ ወደ
ኢየሩሳሌም ተመልሰው በአንድ ልብ ሆነው በኢየሩሳሌም ቀዩ፡፡ በመቆየታቸውም
ሰማያዊ ኃይል አገኙ፡፡
እኛ ሰማያዊ ኃይል ለማግኘት የት እንቆይ?
- በኢየሩሳሌም ቤተክስቲያን መቆየት ያስፈልገናል፣
- በአንድ ልብ ሆነን በቤታችን፣ በአገልግሎታችን፣ በዘር፣ በጐሣ ሳንከፋፈል ይኸ እንዲህ ነው፣ ያ ደግሞ እንዲህ ነው ሳንል ከኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን የወጣንም እንመለስ፣
- ሰዎች ባይመቹንም፣ ክፉዎች ልባችንንን ቢያቆስሉንም፣ ሰዎች እንጂ ያልተመቹን ክርስቶስና ቤተክርስቲያን ሁልጊዜ ይመቹናል፡፡ ስለዚህም ከኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን አንውጣ፡፡ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እየበላንና እየጠጣን፣ እያገለገልን፣ ያደግንባት የእኛ ኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያናችን ብናዝን የምንጽናናባት፣ አእምሮአችን የሚያርፍባት፣ ሰላም የምናገኝባት ኢየሩሳሌም ቤትክርስቷያናችን ናት፡፡

ማጠቃለያ

አምላካችን የማዳን ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ ለተከታዮቹ ደቀመዛሙርት ምስክሮቼ ናችሁ፡፡ አጽናኙን እልክላችኋለሁ፡፡ “አንትሙ ንበሩ በሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ሃይለ እማርያም፡፡ ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ብሎ አዘዛቸው፡፡

በመጨረሻም ወደሰማይ ሲያርግ እጆችንም አንስቶ ባረካቸው፡፡ (ሉቃ 24÷51)
በብሉይ ኪዳን ተፅፎ እንደምናገኘው፡- አባታችን አብርሃምን ባርኮ ያበዛ(ዘፍ12÷1)፣ ያዕቆብን በያቦቅ ወንዝ ሲባረክ ያደረ (ዘፍ35÷9)፣ ያቤጽን ባርኮ ሀገሩን ያሰፋ(1ኛ ዜና 4÷9)፣ አምስቱን እንጀራ፣ ሁለቱን ዓሣ አብዝቶ የባረከ ጌታ ዛሬም በኑሯችን አብዝቶ የሚባርከን፣ ሥራችንን እንድንሠራ በበረከት ያጣነውን ደስታ የሚመልስልን፣ ባርኮ በበረከት ወደሚያትረፈርፍልን፣ ጉድለትን ሳይሆን ሙላትን፣ ማጣት ሳይሆን በረከትን ወደሚሰጠን ደቀመዛሙርቱ ዓይኖቻቸውንም ወደላይ ትኩር ብለው እንደተመለከቱት እንደሐዋርያት ማየት ይጠበቅብናል፡፡ እውነት ነው እርሱን ማየት ከሁሉም ይበልጣልና ወደሰማይ ያረገውን ጌታ አይናችንን አንስተን እንይ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል

LIKE OUR PAGE >>>

ግንቦት 21

ግንቦት 21

ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፤በዚህ ቀን ግብጽ ደብረ ምጥማቅ በተባለ ቦታ በተሰራች ቤተክርስቲያን እመቤታችን ጻድቃንን መልአክትን አስከትላ ትገለጽላቸው ነበር፤እስላምም ክርስቲያንም በግልጽ ይመለከቷት ነበር። ከየአገሩ ያሉ ሰዎች ይሰበሰባሉ ድንኳን ተክለው ሰቀላ ሰርተው አጎበር ጥለው ይከትማሉ ፤ድንግልም ከግንቦት 21 ቀን ጀምሮ ለአምስት ተ...ከታታይ ቀናት ሳታቋርጥ ትገለጽላቸው ነበር፤ህዝቡ የተለያየ ጥያቄ ይጠይቃታል አዳም አባታችንን አሳይን ይሏታል ገሚሱ ነብዩ ዳዊትን ገሚሱ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሳይን ይሏታል አንዳንዱም ከዚህ ቀደም የሞተ ዘመዱን እንድታሳየው ይጠይቃታል፤እርሷም ለሁሉም ፍቃዳቸውን ትፈጽምላቸው ነበር፤አዳምን ስትጠራው ከሔዋን ጋር ዳዊትን ስትጠራው ከበገናው ጋር ቅዱስ ጊዮርጊስን ስትጠራው ከጸአዳ ፈረሱ ጋር ነው። ወይ ግሩም ታዲያ ይህ በዚያ ደጉ ዘመን ነበር፤አሁን ግን ኃጢያታችን ሲበዛ በረድኤት ካልሆነ በገሃድስ ተገልጻ አትታይም ለበቁ ካልሆነ። ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን አባ መርትያኖስ አረፈ፤ ይህም በህጻንነቱ መንኩሶ ለ 67 ዓመት በፍጹም ተጋድሎ የኖረ ነው። ይህ ገድል ትሩፋቱ በሁሉ ዘንድ ተሰማ፤ እነሆ አንዲት በዝሙት ስራዋ እጅግ የምትታወቅ ሴት ዘንድ ወሬው ደረሰ፤ እርሱ እኮ የሴት ፊት ስላላየ ነው እንጂ በፍትዎት ይወድቃል ከክብሩም ይዋረዳል አለቻቸው ባልንጀሮቿም የለም በፍጹም አያደርገውም አሏት፤ እኔ በዝሙት ከጣልኩት ምን ትሰጡኛላችሁ አለቻቸው ብር እንሰጥሻለን አሏት፤በዚህ ተወራርደው ሄደች፤ ሽቶ ተቀባብታ አምራ ተውባ ሄደች፤ስንክሳሩ እጅግ ውብ መልከመልካም ነበረች ይላታል፤ እስኪመሽ ከገዳሙ አቅራቢያ ቆይታ በሩን አንኳኳች የመሸቢኝ እንግዳ ነኝ አሳድረኝ ትለዋለች፤ ነፍሱ ተጨነቀች ባስገባት የዝሙት ጦር ይነሳብኛል ብተዋት እንግዳ ሆኜ መጥቼ መቼ ተቀበላችሁኝ ብሎ ይፈርድቢኛል ደግሞም አውሬ ይበላታል ብሎ አሰበ፤ባስገባት ይሻለኛል ብሎ አስገባት የተቀበችው ሽቶ ዝሙት የሚቀሰቅስ ነው፤ ቀረበችው፤አባቴ በዚህ ማንም አያየንም አብረን እንተኛ አለችው፤እሳት እያነደደ ነበርና እሺ ምን ችግር አለው እዚህ አሳት ላይ ምንጣፍሽን አንጥፊና እንተኛለን አላት፤ አንድም እግሩን ወደ እሳቱ ማገደው ይላል አይንህ ብታሰናክልህ ካንተ አውጥተህ ጣላት አይደል የሚለው መጽሐፉ፤ ደነገጠች ምንድን ነው አባቴ አለችው፤ ይህ ያስደንቅሻልን የገሃነም እሳትን ታዲያ እንዴት ልትችይው ነው አላት እግሩ ስር ወድቃ ይቅር በለኝ አለችው እርሱም ሌሊቱን ሙሉ ሲያስተምራት አደረ፤ ሲነጋ አልተመለሰችም አመንኩሰኝ ከዚህ በኃላ ወደ ዓለም አልመለስም አለችው አመነኮሳት ከደናግል ገዳም ወስዶ ለእመምኔቷ አደራ ሰጣት፤የሚገርመው ይህች እናት ከብቃቷ የተነሳ የመፈወስ ሀብት ተሰጣት ብዙ በሽተኞች ወደርሷ እየመጡ ይፈወሱ ነበር፤ አባ መርትያኖስ ግን ድጋሚ ሌላ ሴት መጥታ እንዳትፈትነው ሰው የማይደርስበት ከባህር መካከል ባለች ደሴት ብቻውን መኖር ጀመረ፤ ከብዙ ዘመን በኃላ መርከብ ተሰብሮ ብዙዎች ሲሞቱ አንዲት ሴት በመርከቡ ስባሪ ተጣብቃ እርሱ ካለበት ደሴት ደረሰች ባያት ጊዜ ደነገጠ አደነቀም ከእርሷ ጋር በአንድነት ስለመኖሩም አዘነ፤ ይምትበላውን ሰጥቷት የምትለብሰውን አዘጋጅቶላት ሲያበቃ ተወርውሮ ወደ ባህሩ ገባ ዓሳ አንበሪም ተሸክሞ ወደ የብስ አደረሰው ከዚህ በኃላ በአንድ ቦታ ላለመቀመጥ ወስኖ በ108 አገሮች የሚገኙ ታላላቅ ገዳሞችን ዞረ በመጨረሻም በዛሬዋ ቀን በክብር አረፈ፤ እመቤታችንን ከሐና ማህጸን ፈጥሮ ከፍጥረተ ዓለም ለይቶ ከሁሉ አልቆ የእናት አማላጅ ትሁናችሁ ብሎ የሰጠን እግዚያብሔር ይመስገን፤ እኛንም ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>

ግነቦት 12

ግነቦት 12 እንኳን ለፍልሰተ አጽሙ ለአበታችን ለአበነ ተክለሀይማኖት አመታዊ ክብረ በአል በሰለም በጤና አደሰን

የአባታቸንና የኢትዮጵያ ፀሀይ የፃድቁ የተክለሀይማኖት ዐፅመ ፍልሰት ክብረ በዓል ግንቦት ፲፪ ከደብረ አሰቦ ወደ ደብረ ሊባኖስ አጽማቸው የፈለሰበት(ፍልሰተ አጽም) በዓለ ንግስናቸው ይከበራል። ይህም ማለት አባታችን 29 ዓመት ቆመው ሲጸልዩ 7ቱን ዓመት ደግሞ ባንድ እግራቸው የጸለዩና አፅማቸው በደብረ አስቦ ከተቀበረበት ወጥቶ አሁን ደብረ ሊባኖስ ገዳም የተሰራበት ቦታ ጋር የፈለሰበት ታላቅ በዓል በተለይ በደብረ ሊባኖስ በታላቅ ሀይማኖታዊ ስርዓት ይከበራል። ካህናት፣መዘምራን ሊቃውንት ሌሊቱን በማህሌት፣ጠዋት በቅዳሴ፣በወረብና፣በዝማሬ፣በስብከት ሊቃነ ጳጳሳት፣መነኮሳት፣ካህናት፣ዲያቆናትና ከዋክብተ ቤተክርስቲያን ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ይከበራል።
የፃድቁ የአባታችን የተክለሀይማኖት በረከት በሁላችን ላይ ይደር፤ አገራችን ኢትዮጵያን ደግሞ ከክፉ ይጠብቃት፤ አሜን!!!

LIKE OUR PAGE >>>

ግንቦት 11

ግንቦት 11 

በዚህች ቀን የዜማው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ወደ ብሔረ ሕያዋን የተሰወረበት ቀን ነው። ይህ ቅዱስ ከአባ ጌዴዎን ዘመዶች ወገን እርሱም በኢትዮጵያ አገር ከታነጹት አብያተ ክርስቲያናት ለምትቀድም ከአክሱም ካህናት ውስጥ ነው: እርሷም አስቀድሞ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት በውስጥዋ የተከበበ እና አምላክን በወለደች በእመቤታችን በከበረች ድንግል ማርያም ስም የከበረች ናት ::
የዚህ ቅዱስ አባት አዳም የእናቱም ስም ታውክሊያ ሲባሉ :በ512 ዓ ም በአክሱም ከተማ ተወለደ:: እናት እና አባቱም ልጃቸውን ለማስተማር ወደ ዘመዳቸው አባ ጌዴዎን ልከው እንዲማር አደረጉት : ይህም አባት አባ ጌዴዎን ትምህርትን ሊያስተምረው በጀመረ ግዜ መቀበልም ማጥናትም ተሳነው እስከ ብዙ ዘመንም መዝሙረ ዳዊትን ሲማር ኖረ ነገር ግን ከልቡ ማጥናትን እምቢ አለው:መምህሩም አብዝቶ ደበደበው ባሳመመውም ግዜ መታገስ ተሳነው ከአባቶቹ ቤትም ወቶ ዕብነ ሃኪም ወደተቀበረበት ገዳም ሄደ : በውስጡም የወርቅ የብር የልብስ መቀመጫዎች የተመሉ ናቸው: ከአንዲትም ዛፍ አጠገብ ደረሰ ከዚያም አረፈ ትልም ወደ ዛፏ ሲወጣ አየ :ወደ ዛፊቱም እኩሌታ ደርሶ ወደ ምድር ይወድቃል :ሁለተኛም ተመልሶ ወደ ላይ ይወጣል መጀመርያ ወደ ደረሰበት ሲደርስ ይወድቃል:ሲወጣ ሲወድቅ ብዙ ግዜ ያደርጋል : ወደ ሌላ ቦታም አይሄድም 
ከዚህም በኋላ በብዙ ጥረት በብዙ ትጋት በብዙ ድካም በዚያ ከዛፏ ላይ ወጣ:ከዚያችም ከዛፏ ላይ ተቀምጦ በላ :ቅዱስ ያሬድም ወደዚያ ዛፍ ላይ ይወጣ ዘንድ እንደሚተጋ ብዙ ግዜም ከላይ ሳይደርስ ከመካከል እንደሚወድቅ ከዚያም በኋላ በጭንቅ ወደ አሰበው እንደደረሰ የፈለገውንም እንዳገኘ የትሉን ትጋት ባየ ግዜ ሰውነቱን ግርፋቱን እንደምን አትታገሺም ህማሙንስ እንደምን አትችይም አላት መታገስንስ አብዝተሽ ኖሮ ቢሆን እግዚአብሄር በገለጠልሽ ነበር ይንንም ብሎ አለቀሰ ወደ መምህሩ ወደ ጌዲዮን ተመለሰ አባት ሆይ ይቅር በለን እንደቀድሞ ንገረኝ አስተምረኝም አለው:መምህሩ ጌዲዮንም እንዳልከው ይሁን አለው 150ውን መዝሙረ ዳዊት:መሃልየ ነብያትን :መሃልየ መሃልይን :የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ምስጋና ነገረው:81ዱ መጻህፍትን ትርጓሜ የሌሎች መጽሃፍትን ቁትር እና የመሳሰሉትን መጽሃፍተ ሊቃውንት ሁሉ በአንድ ቀን አጥንቶ ፈጸመ::
ከዚህ በኋላ በብዙ ለቅሶ ወደ እግዚአብሄር በለመነ ግዜ ልቡናው ብሩህ ሆኖለት በአጭር ግዜ የብሉይ እና የሃዲስ መጽሃፍትን ተምሮ ፈጸመና ዲቁና ተሾመ:በዚያም ወራት እንደዛሬ በከፍተኛ ቃል የመዝሙር ማህሌት የለም ነበር በትሁት እንጂ :: እግዚአብሄርም መታሰቢያ ሊያቆምለት በወደደ ግዜ ከኤዶም ገነት 3 አእዋፍን ላከለት እነርሱም በሰው አንደበት ተናግረውት ወደ እየሩሳሌም ሰማያዊት ከእነሱ ጋር አወጡት በዚያም 24ቱ ካህናተ ሰማይ የሚያመሰግኑበትን ማህሌት ተማረ::
ወደ አነዋወሩ ወደ ምድርም በተመለሰ ግዜ በአክሱም ዳር ወደ ከበረች ቤተ ክርስቲያን በ3 ሰዓት ገባ በታላቅም ቃል ሃሌ ሉያ ለአብ:ሃሌ ሉያ ለወልድ: ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ :የፅዮንም ደገኛዋ ሰማይን ፈጠረ ዳግመኛም እንዴት እንደሚሰራት የድንኳንን አሰራር ለሙሴ አሳየው አስተማረው አለ:: ይህቺም ምስጋና አርያም ብሎ ጠራት:የቃሉንም ድምጽ በሰሙ ግዜ ንጉሱም ንግስቲቱም ጳጳሱም ከካህናቱ ሁሉ ጋር የመንግስት ታላላቆች እና ህዝቡ ሁሉ ወደ እርሱ ሮጡ:ሲሰሙትም ዋሉ ከዚህም በኋላ ከአመት እስከ አመት በየክፍለ ዘመኑ በክረምት እና በበጋ:በመጸው እና በጸደይ:በአጽዋማት እና በባእላት :በሰንበታትም እንዲሁም በመላእክት በአል በነብያት እና በሃዋርያት በጻድቃን እና በሰማእታት በደናግልም በአል የሚሆን አድርጎ በሶስቱ ዜማው ሰራ :ይህውም ግዕዝ ዕዝል አራራይ ነው::
የሰው ንግግር የአእዋፍ የእንሥሳትና የአራዊት ጩሀት ከነዚህ ከሶስቱ ዜማ አይወጣም :በአንዲት እለትም ቅዱስ ያሬድ ከንጉስ ገበረመስቀል እግር በታች ቆሞ ሲዘምር ንጉሱም የያሬድን ድምጽ እያዳመጠ ልቡ ተመስጦ የብረት ዘንጉን ወይም መቋምያውን በያሬድ እግር ላይ ተከለው ከእርሱም ደምና ውሃ ፈሰሰ ያሬድም መሃሌቱን እስከሚፈጽም አልተሰማውም ነበር ንጉሱም አይቶ ደነገጠ በትሩንም ከእግሩ ላይ ነቀለ ስለፈሰሰው የደምህ ዋጋ የፈለከውን ለምነኝ ብሎ ለያሬድ ተናገረው ያሬድም ላትከለክለኝ ማልልኝ አለው ንጉስም በማለለት ግዜ ወደ ገዳም ሄጄ እመነኩስ ዘንድ አሰናብተኝ አለው ንጉሱም ሰምቶ ከመኳንንቱ ጋር እጅግ አዘነ ተከዘም እንዳይከለክለውም መሃላውን አሰበ እያዘነም አሰናበተው ከዚ በኋላም ቅዱስ ያሬድ ወደ በተክርስቲያን ገብቶ በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ ፈጽሞ የከበርሽ እና የተመሰገንሽ ከፍ ከፍ ያልሽ የብርሃን መውጫ የህይወት ማዕረግ የሆንሽ የሚለውን ምስጋና (አንቀጸ ብርሃን) እስከመጨረሻ በተናገረ ግዜ ክንድ ያህል ከምድር ከፍ ከፍ አለ::
ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን ሃገር ሄዶ በጾም በጸሎት ተወስኖ ስጋውን እጅግ እያደከመ ኖሮ ገድሉን በዚያ ፈጸመ እግዚአብሄር ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው ከዚ በኋላ ግንቦት 11 ቀን የተሰወረበት ቦታ በሰሜን ጠለምት ደብረ ሐዊ በተባለው ተራራ ነው፤ በዚህ ቦታ በስሙ የታነጸለት አስደናቂ ገዳም አለው፤ በመዲናችን አዲስ አበባም መስቀል ፍላዎር አካባቢ ግሩም ቤተክርስቲያን አለው ዛሬ ታቦተ ህጉ ውጥቶ በደማቁ ተከብሮ. በአንድ ወቅት እመቤ...ታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አባ ሕርያቆስን ከብሕንሳ፤ ቅዱስ ኤፍሬምን ደግሞ ከሶርያ ይዛ ለቅዱስ ያሬድ አክሱም ላይ ተገለጸችለት እንዲህም አለቻቸው በሉ አንተ ቅዳሴዬን አንተ ደግሞ ውዳሴዬን ንገሩትና በዜማ ይድረስው አለቻቸው፤ እነርሱም ነገሩት እርሱም የሚጣፍጥ ዜማ ደረሰ፤ዛሬም ድረስ ጠዋትና ማታ ቤተክርስቲያን ድምጿን ከፍ አድርጋ ይምታሰማው እነዚህ ሶስት ግሩማን አባቶች የተባበሩበትን ምስጋና ነው። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን። የአባታችን የአምሳለ ሱራፌል የሊቁ ማህሌታይ የቅዱስ ያሬድ ጸሎቱ በረከቱ ረድኤቱ በኛ በህዝበ ክርስቲያኑ ላይ በሃገራችን በኢትዮጵያ ላይ ለዘላለም በእውነት ይደርብን !!!!!አሜን

LIKE OUR PAGE >>>

ግንቦት 9


ግንቦት 9 በዚህች ቀን የጌታችን የመድሐኒታችንን የእየሱስ ክርስቶስን መስቀል ያገኘችው እሌኒ ቅድስት አረፈች። ይህችም የታላቁ ንጉስ የቆስጠንጢኖስ እናት ነች። ባለቤቷ ተርቢኖስ ይባላል ነጋዴ ነው ባህር ተሻግረው አገር አቋርጠው ለዓመት ሁለት ዓመት ነግደው ይመለሳሉ ከዕለታት በአንዱ ቀን ወደ አገገራቸው ሲመለሱ መርከብ ላይ ጨዋታ ጀመሩ፤ እኛስ በሠላም ወደ አገራችን ገባን ሚስቶቻችን ግን እንዴት ሆነው ይሆን አሉ ተርቢኖስ ሚስቱን እጅግ ያምናት ነበርና የእኔ ሚስት እንደዚህ ዓይነት ነገር አታውቅም የእናንተ ሚስቶች ያደርጉት ይሆናል እንጂ አላቸው፤ ያንተ ሚስት ከሄዋን ልጆች የተለየች ነችን እኔ ሄጄ ወድጃት ወዳኝ ...ለምጃት ለምዳኝ አፍቅሬት አፍቅራኝ ብመጣ ምን ትቀጣለህ አለው፤ እስከዛሬ የደከምኩበት ወረት ላንተ ይሁን ካልሆነልህ ግን ያንተን እወስዳለሁ አለው፤ በዚህ ተወራርደው ተለያዩ ቤቷ ሄደ አላስገባም አለችው፤ ገረዷን አስጠርቶ ሁለቱ ብቻ የሚተዋወቁበትን እቃ ስጪኝ ወርቅ ብር እሰጥሻለሁ አላት፤ እሺ አንተ ነጋዴዎች መጡ የብስ እረገጡ እያልክ በከተማው ለፍፍ አለችው እንዳለችው በከተማው እየዞረ ለፈፈ፤ ወደ እሌኒ ቅድስት ገብታ እመቤቴ ነጋዴዎች መጡ የብስ እረገጡ እየተባለ ነው ገላሽን ታጠቢ ሽቶም ተቀቢ አለቻት እርሷም ገላዋን ልትታጠብ የአንገት ሐብሏን አስቀምጣ ባኞ ገባች፤ የአንገት ሐብሏ የተርቢኖስ ስም አለበት ወስዳ ሰጠችው፤ እርሱም ሄዶ ‘’እየው ለምጃት ለምዳኝ ወድጃት ወዳኝ መጣሁ ውድ ስጦታም ሰጠችኝ” ብሎ ሐብሉን አሳየው አልተጠራጠረም አመነው የለፋበትን ወረት በሙሉ አስረክቦ እያዘነ ወደ ቤቱ ገባ፤ ምነው ጌታዬ አዝነህ አይሃለሁ ምን ሆንክብኝ አለችው ወረቴን በሙሉ መአበል ወሰደው አላት፤ ታዲያ ለእዚህ ታዝናለህ ያንተም የኔም ዘመዶች ወዳጆች ብዙ ናቸው ተበድረን ትነግዳለህ አለችው፤ እርሱም በአሽሙር ልክ ነሽ ያንቺ ወዳጆች ብዙ ናቸው እኔ ግን ወዳጅ የለኝም ደግሞ በሰጠሁበት አገር ተበድሬ በመጸወትኩበት አገር ለምኜ አልኖርም ወደ ሌላ አገር እሄዳለሁ አላት እኔም ካንተ አልለይም ብላ ተከተለችው በመርከብ ተሳፍረው ሄዱ ከባህሩ መሐከል ሲደርሱ “እሌኒ ሳምንሽ ካድሺኝ ስወድሽ ጠላሺኝ” ብሎ ሐብሉን አውጥቶ አሳያት እኔ አልሰጠሁትም ህያው እግዚያብሔር ምስክሬ ነው አለችው አላመናት ንጹሕ ከሆንሽ ፈጣሪ ያድንሽ ብሎ በሳጥን አድርጎ ከባህር ጣላት ሳጥኑ በቅዱስ ሚካኤል ጣባቂነት እየተንሳፈፈ ባህር ዳርቻ ደረሰ ቆንስጣ የሚባል ንጉስ አገኛት እጅግ መልከመልካም ነበረችና በክብር አገባት ቆስጠንጢኖስንም ወለደችው ቆንስጣ ሲሞት ልጇ ቆስጠንጢኖስ ነገሰ የጌታን መስቀል ለመፈለግ እየሩሳሌም ወረደች መስቀሉንም አገኘች የዚህ ዜና በሰፊው መስከረም 17 የሚተረክ ነው። በ 80 ዓመቷ ጌታችን ተገለጸላት ወዳጄ እሌኒ ቅድስት ወደኔ ልወስድሽ ነው ይላታል ደነገጠች ምነው መኖር ትፈልጊያለሽን ይላታል እንተን እንዳመሰግን ብዬ ነው ትለዋለች ስንት ዓመት ልጨምርልሽ ይላታል ይህማ ባንተ ቸርነት መግባት ይሆንብኝ የለምን ትለዋለች እንግዲያውስ 40 ዓመት ጨምሬልሻለሁ አላት በ 120 ዓመቷ ግንቦት 9 በዛሬዋ ቀን አርፋለች ይህች ቅድስት እናት ያገኘችው ግማደ መስቀል ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛል ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከእሌኒ ቅድስት በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ግንቦት 7

ግንቦት 7 በዚህች ቀን ታላቁ የቤተክርስቲያን ሊቅ አቡነ አትናቴዎስ አረፈ። ወላጆቹ አረማውያን ነበሩ ያላመኑ ያልተጠመቁ የአባቱ ስም ሐኪም የእናቱ ስም ማርያም ይባላል መስከረም 20 ቀን ነው የተወለደው። አትናቲዎስ ህጻን እያለ የሰፈሩ ልጆች ደስ የሚል ጨዋታ ሲጫወቱ ይመለከታል ለመሆኑ እንዴት ያለ ጨዋታ ነበር ካሉ እንደ ዘመናችን ህጻናት ሌባና ፖሊስ፤ አ...ባሮሽ፤ ኳስ፤ ወይንም እርግጫ… አልነበረም፤ ስርዓተ ቤተክርስቲያን እየሰሩ ነበር የሚጫወቱት፤ እትናቴዎስ እኔንም ከጫወታችሁ አስገቡኝ አላቸው እነሱም አንተ ያልተጠመቅህ አረማዊ ነህ ከጫወታችን አትገባም አሉት እሺ አጥምቁኝና አስገቡኝ ሲላቸው የጫወታ ጥምቀት አጠመቁት የጫወታ ሊቀ ጳጳስ አድርገው ሾሙትና ወንበር ላይ አስቀመጡት ሰገዱለት ፤ በዚያን ወራት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ የነበረው እለእስክንድሮስ ነው ደቀመዛሙርቱን አስከትሎ መንገድ ሲሄድ የእነዚህ ህጻናትን ጫወታ በመገረም ቆሞ ተመለከተ፤አባታችን ከነዚህ ህጻናት ምን ቁም ነገር ይገኛል ብለህ ትመለከታቸዋልህ አሉት፤እርሱም ይገኛል እንጂ ልጆቼ እነዚህ ህጻናት ያደረጉት በኃለኛው ዘመን እግዚያብሔር በእኔ ላይ አድሮ የሚሰራው ስርዓት ነው፤እነሆ በግብጽ ምድር ጽኑ ርሀብ ይከሰታል የዚህ ህጻን አባቱ ይሞታል እናቱም እንዳሳድገው አምጥታ ለእኔ ትሰጠኛለች ከእኔ በኃላ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ የሚሆነው ይህ ህጻን ነው ብሎ ትንቢት ተናገረለት፤ እንዳለውም ሆነ አባቱ ሲሞት እናቱ ቢኖርም ቢሞትም ከዚህ በኃላ አባቱ አንተ ነህ ብላ አደራ ሰጠችው፤እርሱም በመልካም ስነ ምግባር አሳደገው ዲቁና ቅስና ሾመው በኃላም እርሱ ሲሞት 20ኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ እድርገው ሾመውታል፤ በዚህ በሹመቱ ወራት ብዙ ድርሳናትን ተግሳጻትን መልዕክታትን ጽፏል፤ ግሩም ቅዳሴም ደርሷል፤ እንዲያውም በዛሬዋ ቀን አብዛኞቹ አብያተክርስቲያናት ቅዳሴ እትናቴዎስን ነው የሚቀደሰው፤ እንዴት ያለ ግሩም ቅዳሴ ነው/// በነገራችን ላይ አቡነ አትናቴዎስ የመጀመሪያውን የኢትዮጰያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃንን ቀብቶ የሾመ አባት ነው፤ይህ ታሪክ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደረጃ የታሪክ ትምህርት ካሪኩለም ውስጥ የተካተተ ነው። አቡነ አትናቴዎስ 318ቱ ሊቃውን በኒቂያ ጉባዬ አርዮስን ተከራክረው ሲረቱ አፈጉባዬ የነበረ አባት ነው፤ ልክ እንደ ዲዮስቆሮስ በደሴተ ጋግራን ለሰባት ዓመት በግዞት ኖሯል፤ይህን አባት የማይጠቅሰው ሊቅ የለም፤ ሃይማኖተ አበው ላይ በስፋት ይገኛል፤ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ለ 46 ዓመት ህዝቡን በፍቅር ካገለገለ በኃላ ግንቦት 7 ቀን በክብር አርፏል፤ በረከቱ ይደርብን።

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ልደታ ለማርያም


ጴጥርቃ እና ቴክታ የሚባሉ ሰዎች በኢየሩሳሌም በአንድነት ተጋብተው ይኖሩ ነበር:እነዚህም በእግዚአብሄር የሚያምኑ የተወደዱ ጻድቃን ደግ ሰዎች ነበሩ:እነዚህም ሰዎች በእግዚአብሄርም በሰውም ዘንድ የበቁ ባለጸጎች ነበሩ:ነገር ግን የሚወርሳቸው ልጅ አልነበራቸውምና መካን ነበሩ:አንድ ቀን ጴጥርቃም ቴክታን እህቴ ሆይ ይህን ሁሉ የሰበሰብነውን ገንዘባችንን ምን እናደርገዋለን ልጅ የለን የሚወርሰን:አንቺም መካን ነሽ እኔም ካንቺ በቀር ሌላ ሴት አላውቅም አላት:እርሱአም ወንድሜ ሆይ አምላከ እስራኤል ለኔ ልጅ ቢነሳኝ አንተም እንደኔው ሆነህ ትቀራለህን? ከሌላ ደርሰህ ውለድ እንጂ ብላ ብታሰናብተው እንደዚ ያለ ነገር እንኩአንስ ላደርገው በልቦናዬ እንዳላስበው አምላከ እስራኤል ያውቅብኛል አላት:እሱአም አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን የሚያውቅ የለም:ትላንትና ማታ በህልሜ ነጭ ጥጃ ከማህጸኔ ስትወጣ ያችም ነጭ ጥጃ ሌላ ነጭ ጥጃ ስትወልድ እንዲሁ እስከ 7ት ትውልድ ሲዋለድ ሰባተኛይቱ ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃዋም ፀሃይን ስትወልድ አየሁ አለችው::
እርሱም በጠዋት ከህልም ፈቺ ዘንድ ሂዶ የነገረችውን ሁሉ ነገረው:ያም ህልም ፈቺ እግዚአብሄር በምህረቱ አይቱአቹአል በሳህሉ መግቡአችሁአል 7 አንስት ጥጆች መውለዳቹ 7 ሴቶች ልጆች እና የልጅ ልጆች ትወልዳላቹ ከቤታቹ ሰባተኛይቱ ጨረቃ መውለዱአ ከሰው የበለጠች ከመላእክትም የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላቹ የፀሃይ ነገር ግን አልታወቀኝም አለው:እርሱም የነገረውን ሁሉ ሄዶ ነገራት እርሱአም እንጃ አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን ማን ያውቃል ብላ ዝም አለች:ከዛም ፀንሳ በ9 ወሩአ ሴት ልጅ ወለደች:ስሙአንም ሄሜን ብለው አወጡላት:ሄሜንም አድጋ ለአካለ መጠን ስደርስ አጋብተዋት ሴት ልጅ ወለደች በስምንተኛ ቀኑአም ደርዲ ብለው ስም አወጡላት:ደርዲም አድጋ እንዲሁ ሴት ወለደች እና ቶና አለቻት:ቶናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሲካር አለቻት;ሲካርም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሴትና አለቻት:ሴትናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሄርሜላ አለቻት:ሄርሜላም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ንጽህት ቅድስት ክብርት የምትሆን እመቤታችንን የምትወልደውን ሃናን ወለደች::
ከጴጥርቃና ከቴክታ የተወለዱ 67 ወንዶች ልጆች አሉ የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ትውልድ ለመቁጠር ትንቢት አልተነገረላቸውም ሱባኤ አልተቆተረላቸውምና አልተፃፈም:ይህቺም ሃና በስራት በቅጣት አደገች:ለአእምሮ ስትበቃ አካለ መጠን ስደርስ ከቤተ መንግስት ወገን ከነቅዱስ ዳዊት ወገን ከሆነው(መጽሃፍ ቅዱስ ይገልጸዋል) ከቅዱስ እያቄም ጋር አጋቡአት::እነዚህ ቅዱሳን እያቄም እና ሃና በአንድነት ተጋብተው ሲኖሩ ልጅ አጡ:ከእለታት አንድ ቀን ወደ ቤተ እግዚአብሄር ሂደው ሲፀልዩ ሲያዝኑ ዋሉ:ሃዘናቸው እንዴትስ ነው ቢሉ:እያቄም:-"አቤቱ ጌታዬ ያባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለው አትጣለኝ:አትናቀኝ:ፀሎተን ስማኝ ፈቃዴን ፈጽምልኝ:ለአይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የሚሆን የተባረከ ወንድ ልጅ ስጠኝ" ብሎ ሲለምን ዋለ:ሃናም በበኩሉአ "አቤቱ ጌታዬ የአባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለው:ስማኝ ለአይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የምትሆነኝ የተባረከች ሴት ልጅ የማህፀኔን ፍሬ ስጠኝ" ብላ ስትለምን ዋለች: እንዲ ብለው ስይዝኑ ሲጸልዩ ውለው ርግብ ከልጆቹአ ጋር ስትጫወት አይታ አቤቱ ጌታዬ ለዚች ግእዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሳኅኝ ብላ ምርር ብላ አለቀሰች:እንዲ ብለው ሲያዝኑ ሲፀልዩ ውለው ከዘካርያስ ከሊቀ ካህናቱ ሄደው አቤቱ ጌታችን ሆይ ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተ እግዚአብሄርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን:ሴት ልጅም ብንወልድ ማይ ቀድታ መሶብ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን ብለው ስለት ገቡ::
ዘካርያስም እግዚአብሄር ጸሎታችሁን ይስማላቹ ስእለታችሁን ይቀበልላቹ ጻህቀ ልቦናችሁን ይፈጽምላቹ ብሎ አሳረገላቸው:
ከዚያም በሁአላ ቅድስት ሃና እና ቅዱስ እያቄም እለቱን ራእይ አይተው ነገር አግንተው አደሩ:ራእዩም እንዴት ነው ቢሉ ኢያቄም 7ቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ አላት:ወፍ የተባለው ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:ነጭነቱ ንጽሃ ባህሪው ነው:ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ ማለቱ:የኢያቄምን ባህርይ ባህርይ እንዳደረገው እወቅ ሲል ነው:7ቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ልዩ ልዩ ባህሪው:ምልአቱ:ስፍሃቱ:ርቀቱ:ልእልናው:ዕበዩ መንግስቱ ናቸው:ሃናም እኔም አየሁ አለችው:ምን አየሽ ቢላት:ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማህጸኔ ስትተኛ አየሁ አለችው::ርግብ የተባለች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት:ነጭነቱአ ንጽህናዋ:ቅድስናዋ ድንግልናዋ ነው:ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማህጸኔ ስትተኛ አየሁ ማለቱአ ብስራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን መፀነሱአ ነው:ይህንኑም ራእይ ያዩት ሃምሌ 30 ዕለት ነው::
እነሱም እንዲ ያለ ራዕይ ካየን:ነገር ካገኘን ብለው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም:ፈቃደ እግዚአብሄር ቢሆን ብለው አዳምንና ሄዋንን ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት ብሎ ያበሰረ አምላክ ለኛስ ይልክልን የለምን? ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ 7 ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ:ነሃሴ በባተ በሰባተኛው ቀን ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ዓለሙ ሁሉ ተሰብስቦ ቢመዘን አንድ የራሱአን ፀጉር የማያህል ደግ ፍጥረት ትወልዳላቹህና ዛሬ በሩካቤ ስጋ ተገናኙ ብሎአቹሃል ጌታ ብሎ መልአኩ ለሃና ነገራት በፈቃደ እግዚአብሄር በብስራተ መልአክ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም እሁድ እለት ተፀነሰች(በኦሪት ስርአት እሁድ ዕለት ባል እና ሚስት መገናኘት ልማድ ነበርና):እመቤታችን የተፀነሰች ዕለት አይሁድ ቀንተው ተነሱባቸው ቅናቱ እንዴት ነው ቢሉ:ሳሚናስ የሚባል የጦሊቅ ልጅ ከኤዶቅ ካጎቱ ቤት ሄዶ ሞተ እነርሱም እንቀብራለን ብለው ባልጋ ይዘው ሲሄዱ ከመንገድ አሳረፉት:የሃናም የአጎቱአ ልጅ ነበርና ለማልቀስ ብትደርስ ዘመዶቹአ ሁሉ ተሰብስበው ሲላቀሱ ቆዩአት:እርሱአም አብራ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ብድግ ብሎ ተነስቶ ስብሃት ለኪ ማርያም እሙ ለፀሃየ ጽድቅ ለአብ ሙሽራው ለወልድ ወላዲቱ ለመንፈስቅዱስ ጽርሃ ቤቱ ተፈስሂ ደስ ይበልሽ ብሎ ሰገደላት:አይሁድ ከዛ ነበሩና ምነው ሳሚናስ ምን አየህ? ምን ትላለህ? ቢሉት ከዚች ከሃና ማህፀን የምትወለደው ህፃን ሰማይ ምድርን:እመቅ አየርን የፈጠረ አምላክን ትወልዳለች እያሉ መላእክት ሁሉ ሲያመሰግኑአት ሰማሁአቸው እኔንም ያነሳችኝ የፈወሰችኝ ያዳነችኝ እርሱአ ናት አላቸው በል ተወው ሰማንህ ብለው ቅናት ጀመሩ::
""እመቤታችን እግዝትእነ ማርያም በተፀነሰች በ9 ወር ከአምስት ቀን የግንቦት መባቻ ዕለት ግንቦት 1 ተወለደች::""
እመቤታችን እግዝትእነ ማርያም የተወለደችበት እለት በአባት እናቱአ ቤት ፍስሃ ደስታ ተደረገበት ቤቱንም ብርሃን መላው በስምንተኛውም ቀን ""ማርያም"" ብለው አወጡላት::ስለምን ማርያም ብለው አወጡላት ቢሉ:እነሆ በዚ አለም ከሚመገቡት ሁሉ ምግብ ለአፍ የሚጥም ለልብ የሚመጥን "ማር" ነው:በገነትም በህይወት የተዘጋጁ ጻድቃን ቅዱሳን "ያም" የሚባል ምግብ አላቸው ::ከዚ ሁሉ የበለጥሽ የከበርሽ ነሽ ሲሉ ስለዚህ "ማርያም" ብለው አወጡላት::የእመቤታችን ማርያም ስም ተነቦ ሳይተረጎም ይቀር ዘንድ አይገባምና:-""ማ"" ማለት ማህደረ መለኮት: ""ር"" ማለት ርግብየ ይቤላ: ""ያ"" ማለት ያንቀዓዱ ኃቤኪ ኩሉ ፍጥረት:""ም"" ማለት ምስሃል ወምስጋድ ወምስትሥራየ ኃጥያት ማለት ነው::አንድም "ማርያም" ማለት ልዩ ከጣዖት:ክብርት እምፍጥረታት:ንጽህት እምሃጥያት:መልክ ከደም ግባት የተሰጣት ማለት ነው:ዳግመኛም "ማርያም" ማለት ተፈስሂ ቤተ ይሁዳ ወተሃሠዪ ቤተ እስራኤል ማለት ነው::
አንድም "ማርያም" ማለት መርህ ለመንግስተ ሰማያት ማለት ነው:ይህስ እንዴት ነው ቢሉ:እነሆ ዛሬ በዚህ አለም ለዕውር መሪ በትር እንዲሰጡት ሁሉ እርሱአም በፍቅሩአ:በጣዕመ ፍቅሩአ የሰውን ሁሉ ኃጥያት:ክፋት ፍቃ ከልጁአ ከወዳጁአ አስታርቃ ከገሃነመ እሳት አውጥታ መንግስተ ሰማያት የምታስገባ ስለሆነች ስለዚህ መርህ ለመንግስተ ሰማያት አሉአት::አንድም ማርያም ማለት ሰረገላ ፀሃይ ማለት ነው:አንድም ማርያም ማለት ተላኪተ እግዚአብሄር ወሰብእ ማለት ነው:አንድም ማርያም ማለት ውብህት(ስጥውት) ማለት ነው::
በግንቦት አንድ ቀን እመቤታችን አለምን ልታስምር ከቅድስት ሃና እና ከቅዱስ እያቄም በብዙ ልመና ተገኘች:: 
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅሩአ ጣዕሙአ በረከቱአ ረድኤቱአ አማላጅነቱአ በእውነት በኛ አማላጅነቱአን በምናምን ልጆቹአ ላይ ይደርብን::

https://www.facebook.com/photo.php?fbid=292837507541054&set=a.117306178427522.24396.117298008428339&type=1&theater

LIKE OUR PAGE >>>

ትንሳኤ ክርስቶስ


ትንሳኤ ማለት ተንሥአ ካለው የግዕዝ ግሥ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም መነሣት አነሣሥ ማለት ነው ።እስራኤል ዘስጋ ያከብሩት የነበረው በዓለ ፋሲካ ከባርነት ቀንበር ወደ ነጻነት የተላለፉበት ከኀዘን ወደ ደስታ የተሸጋገሩበት በዓል ነበር ።
የሐዲስ ኪዳን በዓለ ትንሣኤ ግን እሥራኤል ዘነፍስ ወደ ከኃጢአት ጽድቅ የተመለስንበት ከሐሳር ወደ ክብር ከአሮጌው ወደ ሐዲስ ሕይወት የተሸጋገርንበት መንፈሳዊ የነጻነትበዓል ነው ።ፋሲካ በዐረብኛ ፓስኻ ማለት ሲሆን ትርጉሙም ማዕዶት መሸጋገሪያ ማለትነው ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በቀደምት ነቢያት የተነገሩና የተጻፉ አንቀጾች ብዙ ናቸው፡፡ የሞቱና የትንሣኤ ምሥጢር በቅዱሳን መጻሕፍት ሰፊ ቦታ ያለው ነው፡፡ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚነገረው ሞትና ትንሣኤ ከቅርቡ /ከመስቀሉ አካባቢ/ በመነሣት እሱ ራሱ መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥርዓተ ቊርባንን በሠራበት ምሽት የሞቱንና ትንሣኤውን ነገር አንሥቶ ለደቀ መዛሙርቱ በሰፊው ገልጿል፡፡ “በዚች ሌሊት ሁላችሁ ትክዱኛለችሁ መጽሐፍ እረኛው ይመታል የመንጋው በጎች ይበተናሉ ያለው ይፈጸማል” ብሎ ነግሮአቸዋል፡፡ ከዚህም ቀደም ብሎ በጉባኤው ይሰበሰብ ለነበረው ሕዝብ ዮናስ በከርሠ አንበሪ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት እንደኖረ ወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ያድራል፡፡ ነገር ግን ወደገሊላ እቀድማችኋለሁ እያለ ይነግራቸው፥ ያስተምራቸው ነበር፡፡ ማቴ ፲፪፥፵፣ ፳፯፥፴፩

መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሱ በተጻፈው መሠረት የመስቀልን ፀዋትወ መከራ ተቀብሎ በመስቀል ላይ ሞቶ፥ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሙታንን በሞቱ ሕያዋን ያደርጋቸው ዘንድ ሞተ፡፡ በዕለተ ዓርብ የፈጠረውን አዳም በፈጸመው በደል ከተፈረደበት የሞት ፍርድ ነፃ ይሆን ዘንድ፥ በባሕርዩ ሞት የሌለበት አምላክ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ ዋለ፡፡ ወዳጆቹ የአርማትያሱ ዮሴፍና፥ አስቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታ የሄደው ኒቆዲሞስ በመስቀል ላይ የዋለውን ሥጋውን አውርደው፥ ለመቅበር፤ ከገዥው ከጲላጦስ ለምነው እንዲቀብሩ ተፈቅደላቸው፡፡ ከምሽትም ከመስቀሉ አወረዱት እንደቤተ አይሁድ የአቀባበር ሥርዓትና ልማድ የደቀቀና መዓዛው የጣፈጠ ሽቱ አዘጋጅተው፥ ከጥሩ ሐር በተሠራ በፍታ ገንዘው ዮሴፍ ለራሱ አስወቅሮ ባሳነፀው አዲስ መቃብር ቀበሩት፡፡ታላቅ ድንጋይም አገላብጠው ገጠሙት ማቴ ፳፯፥፶፯‐፶፰፣ ዮሐ፲፱፥፴፰‐፵፪ ይህ ሁሉ ለአይሁድ ሊቃናትና ሕዝብ ደስ የሚያሰኝ አልበረም፡፡ ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚደረገው ጥንቃቄና የሚሰጠው ክብር ሁሉ፥ በነሱ ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም፡፡ 
“ያ በሕይወተ ሥጋ ሳለ በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ ብሏልና ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት ሰርቀው፥ ወስደው ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ብለው ሕዝቡን እንዳያስቱ መቃብሩ ይጠበቅ” በማለት ወስነው ነበር፡፡ በእያንዳንዱ አራት አባል የሚገኝበት በሦስት ፈረቃ የሚጠብቅ የጭፍራ ቡድን ተመድቦ መቃብሩን በንቃትና በጥንቃቄ እንዲጠብቅ ተደርጓል፡፡ ባለሥልጣኖችም ጭፍራው ባለበት መቃብሩን አስቆልፈው በየቀለበታቸው (ማኅተማቸው) አትመውት ነበር፡፡ ማቴ ፳፯፥፷፪-፷፮
ይህ ሁሉ በሚፈጸምበት ዕለትና ጊዜ እነማርያም መግደላዊት፣ ማርያም ባወፍልያና እና ሰሎሜ ከእግረ መስቀሉ ሳይለዩ ከመቃብሩ ፊት ለፊት ቆመው በኀዘን፣ በተሰበረ መንፈስ የነገሩን ፍጻሜ የሚመለከቱ የዓይን ምስክሮች ነበሩ፡፡ ማቴ ፳፯፥፷፩ ይሁን እንጂ ሰውን ለመዳን በፈቃዱ ባደረገው የቸርነት ሥራ፥ በሥጋ ቢሞትም በባሕርዩ ሞት የሌለበትን ጌታ ሞትና መቃብር ይዘው ሊያስቀሩት የማይቻላቸው በመሆኑ፤ ኃጢአትን፣ ሞትንና መቃብርን ደምስሶ፥ መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ፣ ሳይል በሦስተኛው ቀን በሌሊተ እሑድ ከሞት ተነሥቷል፡፡ በመቃብሩ ላይ ተገጥሞ የነበረው ታላቅ ድንጋይ ተገለባብጦ የተጠቀለለበት የከፈን ጨርቅ በአፈ መቃብሩ ተቀምጦ ተገኝቷል፡፡ የአይሁድ ጎመድ ሁሉ አልነበረም፡፡ ለጥበቃ ተመርጠው ልዩ መመሪያና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአቸው የነበሩ ጭፍሮችም ራሳቸውን እንኳ መጠበቅ ተስኗአቸው በያሉበት ወድቀው እንደ በድን ሆነው ነበር፡፡ ትንሣኤውን ለማየት ወደ መቃብሩ ሲመላለሱ ያነጉት ቅዱሳት አንስት ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን ለማየት ቀዳሚ ዕድል ነበራቸው፡፡ አስቀድማ ለማየት የበቃችው ማርያም መግደላዊት መሆኗን ቅዱስ ወንጌል አስቀምጦታል፡፡ ከሷ በማስከተል፥ ሁሉም ሴቶች አይተዋል፡፡ 
ጌታችን በተነሣ ጊዜ፥ መልአኩ እንደ ፀሐይ በሚያበራ ልብስ እንደ በረዶ በነጣ ግርማ ርእየቱ በሚያሰፈራ ሁኔታ ተገልጦ ነበር፡፡ ሴቶቹንም “አይዞአችሁ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ ዐውቃለሁ፤ እሱ ከዚህ የለም እንሣለሁ እንዳለ ተነሥቷል፡፡ ነገር ግን ኑ የተቀበረበትን ቦታ እዩ ካያችሁም በኋላ ፈጥናችሁ ሄዳችሁ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው በገሊላ ይቀድማች ኋል (መታየትን ይጀምርላችኋል) በገሊላ ታዩታላችሁ” ብሎአቸው፥ ወደ መቃብሩ እየመራ ወሰዳቸው፡፡ ሴቶችም ፍርሃትና ድንጋጤ በተቀላቀለበት የደስታ መንፈስ ተውጠው ወደ መቃብሩ ሄዱ፡፡ ፍርሃት የእግዚአብሔርን መልአክ ማየታቸው፤ ደስታው ደግሞ፥ ትንሣኤውን መስማታቸው ነው፡፡ በደስታ ተሞልተው ዜናውን ለደቀ መዛሙርቱ ነግረው፥ እየተቻኮሉ ሲሄዱ ጌታችንን በመንገድ ተገለጠላቸው፡፡ 

“እንዴት ሰነበታችሁ! አስታረቅኋችሁ” አላቸው፡፡ ቀርበውም ሰገዱለት፤ እሱም አይዞአችሁ አትፍሩ፤ ሂዱ ለወንድሞቻችሁ ገሊላ ይሂዱ ዘንድ ንገሩአቸው በዚያ ያዩኛል” አላቸው፡፡ ዐሥራ አንዱ ሐዋርያትም ዜናውን ሰምተው ወደተባሉበት ቦታ ወደ ገሊላ ሄዱ፡፡ በዚያም ጌታችንን ከሙታን ተነሥቶ አዩት፤ ሰገዱለትም፡፡ ማቴ ፳፰፣ ማር ፲፮፡፩‐፲፪፣ ሉቃ ፳፥፲፪ ለፍቅሩ ይሳሱ፥ ይናደዱ የነበሩ ጴጥሮስና ዮሐንሰም በጊዜው ወደ መቃብሩ ሄደው መነሣቱን አረጋገጡ፡፡ ዮሐ፳፥፩‐፲፩፣ ፲፰

የክርስቶስ ትንሣኤ በስሙ ላመኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ትንሣኤ ነው፡፡ ክርስቶስ ለሙታን ሁሉ በኲር ሆኖ ተነሥቶአል፡፡ የሙታንን ሁሉ መነሣት የሚያረጋግጥልን የጌታ ትንሣኤ ነው፡፡ የክርስቶስም ትንሣኤ መርገመ ሥጋ፥ መርገመ ነፍስ፤ ሞተ ሥጋ፥ ሞተ ነፍስ የተሻረበት ርደተ ገሃነም ጠፍቶ፥ በአዳም የተፈረደው ፍርድ ሁሉ ተደምስሶ፤ ፍጹም ነፃነት፣ የማይለወጥ ደስታ፣ የተገኝበት ስለሆነ ፋሲካ ይባላል፡፡ ፋሲካ ደስታ ነው እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነፃ የወጡበትን ቀን ፋሲካ ብለውታል፡፡ የእርቅ፣ የሰላም፣ የድኅነት ቀን ነው ከሞት ከመነሣት ከመቃብር ጨለማ ከመውጣት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ከመላቀቅ፥ ከሲኦል እስራት ከመፈታት የሚበልጥ ምን ደስታ ሊኖር ይችላል?
የክርስቶስ ትንሣኤ እግዚአብሔር እኛን ምን ያህል እንደ ወደደን የምናስተውልበት፣ የፍቅሩን ጥልቀት፤ የቸርነቱን ስፋት የምናደንቅበት፤ የነፍሳችን የዕረፍት ቀን ነው፡፡ በሰው ዘንድ በቃል ሲነገር በተግባር ሲፈጸም የሚታየው ፍቅር ዘመድ ወዳጅ የሚለይበት ሰው ከሰው የሚዳላበት፤ ባለ ካባ ከባለ ካባ፣ ባለዳባ ከበለዳባ የሚበልጥበት፤ የሚወደውን የሚወዱበት፤ የሚጠላውን የሚጠሉበት ነው፡፡ ለሚጠሉት ይቅርና ለሚወዱት ተላልፎ የሚሞቱበት ፍጹም ፍቅር በዓለማችን አይታይም፡፡ 
መድኃኔዓለም ክርስቶስ እኛን የወደደበት ሕይወቱን እስከመስጠት ደርሶ ቤዛ የሆነበትን ምሥጢር የሰው ሕሊና መርምሮ ሊደርስበት የሚችል አይደለም፡፡ ተነጻጻሪ ተወዳዳሪ አቻ ምስያ የሌለው ልዩ ነው፡፡ ከቀደምት አበው እነ አብርሃም ልጆቻቸውን በቁርጥ ሕሊና ለመሥዋዕት አቅርበዋል፡፡ እነ ሙሴ እነ ዳዊት ይመሩት ይጠብቁት ለነበረው ሕዝብ ተላልፈን እንሙት እንቀጣ የሕዝቡን ቅጣት እንቀበል ብለው እንደነበረ ተጽፎአል፡፡ ግን በቅርብ ለነበረ፣እንዲያስተዳድሩ ለተሾሙለት ለተወሰነ ሕዝብና ለወገናቸው ብቻ ነበር፡፡ ሁሉን የሚያጠቃልል ሁሉን የሚያድን አልነበረም፡፡ 

መድኃኒታችንን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በመስቀል ላይ መከራ ተቀብሎ የሞተው፥ ለመላው የሰው ዘር ለአዳም ልጆች ሁሉ ነው፡፡ ቤተሰብና ዘመድ ወዳጅና ጠላት ወንዝና አካባቢ የሚለው አልነበረም፡፡ ከሰው አስተሳሰብ ሚዛንና ግምት የራቀ የጠለቀ ነው፡፡ የወደደን መከራ የተቀበለው እኛ ስለወደድነው አልነበረም፡፡ እሱ ስለ ወደደን ብቻ ነው፡፡ ስንኳንስ ቀድሞ ዛሬም ያደረገልንንና ያደለንን አስበን፥ ፍቅሩን ተገንዝበን፥ ለሰው በጎ ማድረግ፤ በፍቅሩ መመላለስ እጅግ ያዳግተናል፡፡ ከሁሉም የሚረቀውና የሚደንቀው ያጠፋን የበደልን፣ በጥፋታችን ሞትን በራሳችን ላይ ያመጣን እኛ ስንሆን፥ እሱ ስለኛ በደል ተላልፎ በእኛ የተፈረደውን የሞት ፍርድ ተቀብሎ መሞቱ ይደነቃል፡፡ ለዚህም አንክሮ ይገባል፡፡ 
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ርእዩ መጠነ ዘአፍቀረነ እግዚአብ ሔር … ወሶበ እንዘ ፀሩ ንሕነ ተሣሃለነ በሞተ ወልዱ እግዚአ ብሔር ምን ያህል እንደወደደን አስተውሉ ጠላቶቹ ስንሆን በልጁ ሞት ይቅር አለን” ብሎ እንዳስተማረው ስንኳን ተላልፎ እስከመሞት የሚያደርስ ፍቅርና ከፍርድ የሚያድን ምንም መልካም ሥራ ሳይኖረን፤ በሱ ፍቅር የተደረገልንን ቸርነት የምናስብበት የነፃነት የምስጋና ዕለት ነው፡፡ ሮሜ ፭፥፮‐፲በልጁ ሞት ስለካሰልን ይቅርታን አገኝን፤ በአንድ አዳም በደል ምክንያት ኃጢኣት ወደ ዓለም እንደ መጣች፤ በዚችም ኃጢኣት ምክንያት፥ በሰው ሁሉ ሞት እንደተፈረደበት፤ ሰውን ሁሉ በደለኛ፣ ኃጢአተኛ፣ አሰኝቸው፡፡ በአዳም ኃጢአት ምክንያት የመጣ ሞት ከአዳም እስከ ክርስቶስ የነበሩትን የበደሉትንና ያልበደሉትን ሁሉ ገዛቸው፡፡ ታላቁ ሙሴ እንኳን ሌላውን ሲያድን ራሳቸውንም ከሞት ማዳን ስላልተቻላቸው ለሞት ተገዝተዋል፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር የጸጋው ስጦታ በኃጢአታችን ልክ የተደረገብን አይደለም፡፡ ራሱን ቤዛ አድርጎ ካሰልን፤ ከዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰጠን ጸጋ በጥምቀት፣ በሃብት፣ በልጅነት ለሰው ሁሉ ሕይወት በዛለት፡፡ ሮሜ ፭፥፲፮‐፲፰ የተነሣውን ክርስቶስን ሐዋርያት አይተውታል ገጽ በገጽ ዓይን በዓይን ፊት ለፊት ተያይተዋል፡፡ ሰግደውለታል፤ አመስግነውታል፤ ደስታቸው ፍጹም ሆኖላቸዋል፡፡ “… እናንተ አሁን ታዝናላችሁ ነገር ግን እንደ ገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም” ያለው የተፈጽሞላቸዋል፡፡ ዮሐ ፲፮፥፳፪ ለትምህርታቸው መሠረት ለስብከታቸው መነሻ የሆነው የጌታ ትንሣኤ ነው ምስክርነታቸውም የጸናው በትንሣኤ ነው፡፡ የተልእኳቸው ዋነኛ ዓላማ ሞቱንና ትንሣኤውን በመመስከር ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ሐዋ ፩፥፳፣ ሐዋ ፪፡፴፪፣ ሐዋ ፬፡፳
ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ በተለያዩ ቦታዎችና ጊዜያት እየተገለጠ ታይቶአል፡፡ እስከዓረገበት ዓረባኛው ቀን ድረስ ከሐዋርያት ብዙ አልተለየም፡ ከዚህም ሁሉ ጋር በሐዋርያት ትምህርትና ሥርዓተ ጸሎት አካባቢ የነበሩ ሳይቀሩ ብዙዎች አይተውታል፡፡ ከሁሉም በቀዳሚነት ማርያም መግደላዊት ዮሐ ፳፥፲፬‐፲፰ በመቃብሩ አካባቢ ነበሩ እነማርያም ባውፍልያ ማቴ ፳፰፥፱ ወደ ኤማሁስ ይጓዙ የነበሩ ሁለት ደቀመዛሙርት ሉቃ ፳፬፥፲፫‐፴፩ ስምኦን ጴጥሮስ ሉቃ ፳፬፥፴፬፣፩ቆሮ ፲፭፥፭ አሥሩ ደቀመዛሙርት ዮሐ ፳፥፲፱ አሥራ አንዱ ሐዋርት ዮሐ ፳፥፳፮ ከዳግም ትንሣኤ /ከሁለተኛው ሰንበት/ በኋላ ሰባቱ ደቀመዛሙርት ዮሐ፳፩፥፩‐፳፪ በገሊላ አሥራ አንዱ ሐዋርት ማቴ ፳፰፥፲፮ ማትያስ ባለበት አሥራ አንዱ ፩ቆሮ ፲፭፥፭ ሐዋ ፩፳፥፮ ከአምስት ጀምሮ (፭፻) የሚበዙ ወንድሞች ፩ቆሮ ፲፭፥፯ሐዋርያው ያዕቆብ ፩ቆሮ ፲፭፥፯-፲፪ ሁሉም ሐዋርያት በየጊዜውና በየቦታው አይተውታል፡፡ ማር ፲፮፥፲፱፣ ሉቃ ፳፬፥፶፣ ሐዋ ፩፥፫‐፲፪፣ ቁ ፳፮ በመጨረሻም ለቅዱስ ጳውሎስ ተገልጦለታል፡፡ ፩ ቆሮ ፲፭፥፰ 

እንግዲህ ክርስቶስን የምናገኝው እሱን በማመን ጸንተን፤ በፍቅሩ መስለነው በፈለገነው መጠን ስለሆነ፤ በፍጹም ፍቅሩ በሰጠን የልጅነት ጸጋ የክብሩ ወራሾች ለመሆን እንድንበቃ የትንሣኤውን ብርሃን በየልባችን ይሳልብን! አሜን፡፡

LIKE OUR PAGE >>>