Friday, June 21, 2013

ጾመ ሐዋርያት

በየአመቱ በዕለተ ሰኑይ ብቻ (ሰኞ ቀን ብቻ) የሚጀምሩ ሦስት አጽዋማት አሉ፡፡ እነርሱም ዓቢይ ጾም፣ ጾመ ነነዌ እና ጾመ ሐዋርያት ናቸው፡፡ እነዚህ አጽዋማት ምን ጊዜም ቅበላቸው እሁድ ሲሆን የሚገቡት ደግሞ ሰኞ ቀን ነው፡፡ በየትኛውም አመት ይህን ዕለት አይለቁም፡፡
ስለዚህ የ2005 ጾም ሐዋርያት ሰኔ 17 ይገባል፡፡ የጾሙን ታላቅነት ተረድተን እንድንጾመው የትመጣውን፣ ትንቢቱን፣ ምሳሌውንና ምሥጢሩን መረዳት አጋዥ ስለሚሆነን  አምላከ ቅዱሳን ሐዋርያት ክብር ምስጋና ይድረሰው! አሜን!
ጾመ ሐዋርያት በራሳቸው በሐዋርያት የተጀመረ ጾም እንደመሆኑ መጠን በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም ከዛሬ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት ጀመሮ ሲጾም የኖረ ጾም ነው፡፡ ለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የአዋልድ መጻሕፍትና የታሪክ በርካታ ምስክሮች አሉ፡፡  
ጾመ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ዕድሜያቸው ለጾም የደረሱ ምእመናን በሙሉ እንዲጾሙአቸው ካወጀቻቸው ሰባት የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጌታችንና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አንደበት ቀን የተቀጠረለት፣ ትንቢት የተነገረለትና ምሳሌ የተመሰለለት ጾም መሆኑ ከአጽዋማት ሁሉ ለየት ያደርገዋል፡፡
ጌታችን ስለዚህ ጾም ትንቢተ በመናገር፣ ምሳሌ በመመሰል ሰፊ ትምህርት የሰጠው ፈሪሳውያን ወደ እርሱ ቀርበው ‹‹ደቀ መዛሙርትህ የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው›› ብለው በጠየቁት ጊዜ ነው፡፡ እርሱም ሲመልስ እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል በዚያ ጊዜም ይጦማሉ፡፡ በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና  መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡ በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል  የወይን ጠጁም ይፈሳል፡፡ አቁማዳውም ይጠፋል፡፡ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል ሁለቱም ይጠባበቃሉ፡፡›› (ማቴ9.14-17)
በመቀጠል እስከ መጨረሻ የምንመለከተው ከላይ የሰፈረውን የሉቃስ ወንጌል አጭር ገጸ ንባብ ሐሳብ በመሆኑ መለስ እያሉ ታሪኩን ማንበብ ወይም በልብ ከመዘገቡ በኋላ ቀጣዩን ክፍል ማንበብ ምሥጢሩን ለመረዳት ያግዛል፡፡
በዚህ የጌታችን መልስ ውስጥ ‹‹ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል በዚያ ጊዜም ይጦማሉ፡፡›› የሚል ስለ ጾመ ሐዋርያት የተነገረ የትንቢት ቃል እናገኛለን፡፡ ይህ አምላካዊ ቃል ጾሙ ስለሚጀመርበት ወራት ቀጠሮ ይሰጣል፡፡ ያም ጊዜ ሙሽራው ከእነርሱ ከተወሰደ በኋላ ያለው ጊዜ ነው፡፡ ‹‹ሙሽራው ከተወሰደ›› በኋላ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ማለት ሲሆን በቤተ ክርስቲያን ጾመ ሐዋርያት ከዕርገት በኋላ የሚጀምረው በዚህ ቃል ምክንያት ነው፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያላት መሆኗን ያሳያል፡፡
ጾመ ሐዋርያት ከዕርገት በኋላ ለቀናት ያህል ዘግይቶ እንጂ ወዲያው አይጀምርም፡፡ ምክንያቱም የሐዋርያት ሰውነት በአዲስ ሁኔታ ጌታችን ላዘጋጀው የአዲስ ኪዳን ጾም ተመቻችቶ ያልተገኘ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ የሐዋርያት ሰውነት ለጾሙ መዘጋጀት ነበረበት፡፡ ከዚያ በኋላ ሐዋርያት መጾም ጀምረዋል፡፡ ይህም በጌታችንን የመልስ ቃል ውስጥ የተካተተ እንጂ የፈጠራ ድርሰት አይደለም፡፡ ‹‹በአረጀ ልብስ ላይ›› እና ‹‹በአረጀ አቁማዳ›› የሚሉት ሁለት ተከታታይ ምሳሌያዊ ማብራሪያዎች ሐዋርያት ሰውነታቸው በመንፈስ ቅዱስ ከመታደሱ በፊት ጾም መጾም እንደማይጀምሩ ወይም እንደሌለባቸው የሚያስረዱ ምሳሌዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት የተዘጋጀላቸውን ጾም መጾም የጀመሩት ከኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት በኋላ በዐሥረኛው ቀን በወረደ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ የሕይወት ሕድሳት አግኝተው ነው፡፡
ከላይ በተጠቀሰው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ውስጥ ስለ ጾመ ሐዋርያት የቀረቡ ሦስት ዓይነት ምሳሌዎችን እናገኛለን፡፡ ምሳሌዎቹ በምሥጢር የተሞሉ በርካታ መንፈሳዊ መልእክቶችን ያዘሉ ናቸውና ተራ በተራ እንመለከታቸዋለን፡፡
1ኛ. ‹‹ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን?›› የሚለው ዐረፍተ ነገር በገጸ ንባቡ ውስጥ ስለ ሐዋርያት ጾም የተመሰለው የመጀመሪያው ምሳሌ ነው፡፡ ሚዜዎች የተባሉት እንደ መጥምቁ ዮሐንስ መንገድ የሚጠርጉ፣ የሚያስተምሩና ምእመናንን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያቀረቡ ሁሉ ናቸው፡፡ ሙሽሪትን ወደ ሙሽራው መውሰድ የሚዜዎች ሥራ መሆኑ በአይሁድና በኢትዮጵያውያን ባህል ሲሠራበት የኖረ ነው፡፡ ስለዚህ ዋነኞቹ ሚዜዎች ሐዋርያት ናቸው ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን (ምእመናን) ደግሞ መርዓት (ሴት ሙሽራ) ትባላለች፡፡ (2ቆሮ11.2፤ ዮሐ3.29)
‹‹ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን?›› ሲል ሚዜዎች ሙሽራውን ለማስደሰት ሲሉ ምንም የሚያሳዝን ነገር ቢያጋጥማቸውም እንኳን ጨክነው በመቻል ያሳልፉታል እንጂ በሙሽራው ፊት እንደማያዝኑ፤ እንደዚሁም መጾም ተገቢ ነገር ቢሆንም ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር ሳለ መጾም እንደማይገባቸው ነገር ግን ከእነርሱ ተለይቶ ሲያርግ መጾም እንደሚጀምሩ ያስረዳል፡፡
በዚህ ምሳሌያዊ ንባብ ውስጥ ጾም በኀዘን ተመስሏል፡፡ መጾም ተድላነቱ ለነፍስ እንጂ ለሥጋ አይደለምና፡፡ ሥጋ ጾምን እስኪለምድ ድረስ ቅጣት ይሆንበታል፡፡ ስለዚህ በጾም ነፍስ ስትደሰት ሥጋ ግን ያዝናል፡፡ በዚህ ምክንያት ጾም በኀዘን ተመስሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ጾም በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከኀዘን፣ ከዕንባ፣ ከጸጸትና ከንስሐ ጋር ተያይዞ ቀርቧል፡፡ (ኢዩ2.12)
2ኛ. ‹‹በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡›› ይህ ዐረፍተ ነገር ደግሞ ሁለተኛው ምሳሌ ነው፡፡ እራፊ ማለት ቅዳጅ ወይም መጣፊያ ጨርቅ ማለት ነው፡፡ የስፌት ባለሙያ ባረጀ ልብስ ላይ አዲስ ጨርቅ አይጥፍም (አይሰፋም) ወይም አይለጥፍም፡፡ ይህም አንደኛ ግንጥል ጌጥ እንዳይሆን፤ ሁለተኛ ላሮጌ ልብስ ሲባል አዲሱን ማበላሸት እንዳይመጣና አዲሱ ካሮጌው ስለሚበረታ የባሰ እንዳይቦጭቀው በማሰብ ነው፡፡
በምሳሌው መሠረት በጣፊ ወይም በልብስ ሰፊ የተመሰለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በአዲስ እራፊ ጨርቅ ምሳሌነት የተወከለው ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ በአዲስ ኪዳን እንድንጾመው የሠራልን ጾም ነው፡፡ የተቀደደውና መጣፊያ የሚያስፈልገው ልብስ ደግሞ የሐዋርያት ሕይወት ምሳሌ ነው፡፡
እንደ ምሳሌው ሁሉ ሰዎች የክርስቶስ ልብሶች ይባላሉ፡፡ ‹‹አልባሲሁሰ ለክርስቶስ መሃይምናን እሙንቱ›› እንዲል፡፡ ይህም ‹‹የክርስቶስ ልብሶቹ ምእመናን ናቸው፡፡›› ማለት ነው፡፡ ክርስቶስም ለሰዎች ልብሳቸው ነው፡፡ ሐዋርያው ‹‹እናንተ የተጠመቃችሁ ክርስቶስን ለብሳችኋል›› ብሏልና፡፡ (ገላ3.27) ምእመናን የክርስቶስ ልብሶች ናቸው ማለት የክብሩ መገለጫዎች ናቸው ማለት ነው፡፡ ልብስ የክብር መገለጫ ይሆናልና፡፡ እርሱ ደግሞ ለምእመናን ልብስ ነው ማለት ጌጣቸው፣ ነውራቸውን የሚሸፍንላቸውና ክብራቸውም እርሱ ነው ማለት ነው፡፡
ጾም ‹‹እራፊ›› መባሏ ምሥጢር አለው፡፡ ይኸውም እራፊ የተለያየውን እንደሚያቀራርብና አንድ እንደሚያደርግ ጾምም የተለያዩ ፈቃዳት ያሏቸውን ነፍስና ሥጋ አንድ ታደርጋለች፡፡ ከዚህም በላይ ከእግዚአብሔር የተለየውን ሰውም አስታርቃ አንድ ታደርገዋለች፤ ከመንጋውም እንዲቀላቀል ትረዳዋለች፡፡
‹‹በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡›› ማለት አንድ የስፌት ባለሙያ ባረጀ ልብስ ላይ አዲስ እራፊ እንደማይጥፍ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስም የሐዋርያት ሰውነት በኃጢአት ያረጀ ሆኖ ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ሳያድስላቸው አዲስ የሠራውን የአዲስ ኪዳን ጾም ጹሙ ብሎ ሐዋርያትን አያዛቸውም ማለት ነው፡፡ ሰውነታቸው ሲታደስ ያን ጊዜ ግን ይጾማሉ፡፡
ይህ አገላለጥ እግዚአብሔር መንጋዎቹን ያለ አቅማቸው እንዲሸከሙ የማያደርግ አዛኝ ጌታ መሆኑን ያሳያል፡፡ እንዴት ቢባል ሐዋርያትን ሊፈጽሙት በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ እያሉ እንዲጾሙ አላዘዛቸውምና፡፡ ፈጣሪ ለሕዝቡ መቼ ሕግ መስጠት እንዳለበት በሚገባ ያውቃል፡፡ ለእስራኤላውያን በባርነት ሳሉ ዐሥርቱ ትእዛዛትን ያልሰጣቸው ስለዚህ ነው፡፡ ቢሰጣቸውም ሊጠብቁት አይችሉም ነበርና፡፡ በባርነት ያለ ሰው የራሱ ነጻነት እስከሌለው ድረስ የፈቀደውን ማድረግ አይችልም፡፡ በታላላቅ ተአምራት ከባርነት ካወጣቸው በኋላ ግን ሕጉን ሰጣቸው፡፡ ስለዚህ ከክርስቲያን ወገን ማንም ቢሆን ከአቅሙ በላይ የሆነ ነገር ፈጣሪ እንዳዘዘው አያስብ፡፡ የታዘዝነው ሁሉ በዐቅማችን ልክ እንደሆነ እንመን፡፡
3ኛ. ‹‹በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል: የወይን ጠጁም ይፈሳል፡፡ አቁማዳውም ይጠፋል፡፡›› ይህ ስለ ጾመ ሐዋርያት የተመሰለው ሦስተኛውና የመጨረሻው ምሳሌ ነው፡፡
በአረጀ አቁማዳ የተመሰለው ሐዋርያት በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ሳይታደሱ በፊት የነበራቸው ሕይወት ሲሆን፤ በአዲስ ወይን የተመሰለው ደግሞ ጌታችን በወንጌል የመሠረተልን ጾም ነው፡፡ የጾም ሕግን የሰጠን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ደግሞ በጠጅ ጣዩ (በጠማቂው) ተመስሎ ቀርቧል፡፡ አዲስ ጠጅ ባረጀ አቁማዳ እንደማይጣል አምላካችንም ባልታደሰ ሕይወታቸው ሐዋርያትን እንዲጾሙ አላዘዛቸውም፡፡
ቀደም ሲል ጾም ሥጋን ለጊዜው ደስ ባለማሰኘቱ በኀዘን እንደሚመሰል ተመልክተን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በዚህ ምሳሌ ጾም ነፍስን ደስ የሚያሰኝ በመሆኑ በወይን ተመስሎ አገኘነው፡፡ ‹‹ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል›› እንዲል፡፡ (መዝ103.15)
ጠጅ ጣዮች ሲጥሉ (ሲጠምቁ) ተመልክታችሁ ታውቃላችሁ? አስቀድመው ቦታ ያዘጋጁለታል፡፡ እግር እንዳይበዛበትም ጥላ እንዳይወድቅበትም ይጠነቀቃሉ፡፡ እንዳይነፍስበትም ቀን ከሌሊት ይተጉለታል፡፡ በመጨረሻ ሥራው አልቆ ሳለ ጠጁ ከደረቀ (ከጠነከረ) ይላላ ብለው ማር ያልሱታል (ይበርዙታል)፡፡ ከላላ ደግሞ ይድረቅ ብለው ጊዜ ይሰጡታል፡፡
በጠጅ ለተመሰለ ለጾምም በዓይነቱ ተመሳሳይ ከጥቅሙ አኳያ ደግሞ የበለጠ ጥንቃቄ ሊደረግለት ያስፈልጋል፡፡ ለጠጅ ቦታ እንደሚዘጋጅለት ለጾምም ሰውነትን ማዘጋጀትና ጊዜና ዕለት ወስኖ መመደብ በአጠቃላይ ጾምን ማወጅ ይገባል፡፡ ስንዱ እመቤት ቤተ ክርስቲያናችን የአጽዋማት ዐዋጅ ስላላት እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች የዚህ ችግር የለብንም፡፡ ለጠጅ እግር እንዳይበዛበትና ጥላ እንዳይድቅበት እንደሚጠነቀቁለት ጾማችንም በከንቱ ውዳሴ አጋንንት እንዳይገቡበትና ያለ መልካም ሥራ በጾም ብቻ ቀርተን ዋጋው እንዳያንስብን እየተጠነቀቅን መጾም ይገባናል፡፡ ጠጅ ደረቀ ይላላ፤ ላላ ይድረቅ እንደሚባል ጾማችን በሕግ ከተሠራልን በላይ ሰዓቱ እንዳይበዛና ከዓቅማችን በላይ አልፎ ሰውነታችን እንዳይጎዳ፤ እንደዚሁም የአጽዋማትን ሰዓት ሳንጠብቅ ቀርተንም መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዳይላላ ማዕከላዊውን ስፍራ ይዘን በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በጥንቃቄ መጾም እንደሚገባን ይህ ሦስተኛው ምሳሌ ያስረዳናል፡፡
ይህን ትምህርት ጌታችን መድኃኒታች ኢየሱስ ክርስቶስ የሚቋጨው ‹‹አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል ሁለቱም ይጠባበቃሉ፡፡›› በሚለው ኃይለ ቃል ነው፡፡ ዐረፈተ ነገሩ አዲስ የወይን ጠጅ መጣል ያለበት በአዲስ አቁማዳ መሆኑን ይናገራል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት ሕይወታቸው በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከታደሰ በኋላ በአዲሱ አቁማዳቸው አዲሱን ወይን ጣሉ፡፡ ማለትም በአዲስ ሕይወት የአዲስ ኪዳንን ጾም (ጾመ ሐዋርያትን) መጾም ጀመሩ፡፡
አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ሲጣል ያፈነዳዋል፡፡ በአዲስ አቁማዳ ሲጣል ግን ያለፋዋል እንጂ ሊያፈነዳው አይችልም፡፡ ስለዚህ ወይኑም አቁማዳውም አዲስ የሆኑ እንደሆነ አቁማዳው ወይኑን ያፈላዋል፡፡ ወይኑ ደግሞ አቁማዳውን ያለፋዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ሁለቱም ይጠባበቃሉ›› የሚለው ቃል ይፈጸማል፡፡
ጾምና ሰውነት እንደ ወይንና አቁማዳ ናቸው፡፡ ወይንና አቁማዳ እንደሚጠባበቁ (እንደሚጠቃቀሙ) ጾምና ሰውነትም እንዲሁ ናቸው፡፡ ሰው የጾም ሕግን ቢጠብቅ ሕግም እርሱን ትጠብቀዋለች፡፡ ‹‹ይጠባበቃሉ›› የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ይህን የሚያስረዳ ‹‹አኮ ንሕነ ዘነዓቅቦሙ ለሕገጋት አላ እማንቱ ሕገጋት የዓቅቡነ ለዓቂብ ወለተፀውኖ›› የሚል ቃል ይገኛል፡፡ ይህም ‹‹ሕጎችን እኛ አንጠብቃቸውም፡፡ እነርሱ መጠበቅን ይጠብቁናል፤ መጠጊያም ይሆኑናል እንጂ፡፡›› እንደ ማለት ነው፡፡
ወይኑ ቆዳውን ማልፋቱ መልካም ነገር ነው፡፡ የለፋ ቆዳ ብዙ አገልግሎት ስላለው ይፈለጋልና፡፡ ለቀበቶ፣ ለቦርሳ፣ ለጫማና ለልብስ የሚሆነው የለፋ ቆዳ ነው፡፡ የጾምም ጥቅም እዚህ ላይ ነው፡፡ ለልዩ ልዩ አገልግሎትና ጥቅም የሚውል መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖረን ከፈለግን በጾም የለፋ (የደከመ) ሰውነት ያስፈልገናል፡፡ ቆዳን ማልፋት ማዘጋጀት እንጂ ከጥቅም ውጭ ማድረግ አይደለም፡፡ ሰውነትን በጾም ማድከምም ለመንፈሳዊ ሥራ ማዘጋጀት እንጂ እንዳይሠራ ማድረግ እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የታረሰ መሬት ለዘር እንደሚመች በጾም የደከመ ሰውነትም ለመንፈሳዊ ጉዞ ይመቻል፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ (መዝ108.24)
ይህን የመሰለ ምሥጢር ያለውን ጾም ‹‹የሽማግሌዎች ጾም፣ ከጥንት ያልነበረ›› እያሉ በመጽሐፍ እና በቀኖና የሌላ ስም በመስጠት ምእመናን እንዳይጾሙት ማድረግ የዲያብሎስ ትጥቅ የማስፈታት ዘዴ እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
ላለመጾም ምክንያት ከመፍጠር ምክንያት ፈጥሮ መጾም በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ ደሀው ድኅነት ራሱ ጾም ነው ካለ፤ ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ራሱ ጾም ነው ካለ ለመጾም ክርስቲያን መሆን ሳይሆን ሀገር ወይም ዜግነት መቀየር ሊያስፈልግ ነው ማለት ነው? ምእመናን ‹‹ይህ የሽማግሌዎች ጾም ነው›› ካሉ ስለ ጾም ማስተማርና ጾመው ማሳየት የሚጠበቅባቸው ‹‹ሰባክያን›› ደግሞ ‹‹ቃለ እግዚአብሔር ይመትር ነደ እሳት›› እያሉ ጾም ሽሮ ለመብላት ጥቅስ ከጠቀሱ ጾምን በጽሑፍ እንጂ በሥራ ላናውቃት ነው ማለት ነው፡፡
ሐዋርያት እንደታዘዙት ዓለምን ሁሉ ለማስተማር ከመሰማራታቸው በፊት መጀመሪያ ያደረጉት ጾምን ነው፡፡ ሐዋርያት አልጾሙም ማለት ከላይ የተብራራው የኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢትና ምሳሌ ሐሰት ሆነ ማለት ነው፡፡ ቃሉም ተፈጽሟል ሐዋርያትም ጾመዋል፡፡ እኛም ጾሙን ጾመን የምናስበውና የምንሠራው በጎ ሥራ ሁሉ ይከናወንልን ዘንድ ፈጣሪ በረድኤት አይለየን!
ይቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
Source: http://www.eotc-mkidusan.org

No comments:

Post a Comment