Wednesday, June 12, 2013

ዕርገተ ክርስቶስ

ዐረገ በስብሐት ዐረገ በእልልታ
በስብሐት በእልልታ
ዐረገ ዐረገ በእልልታ
እልእልእልእልእልእልእልእልእልእልልልልል...................
+++ እንኳን ለብርሀነ ዕርገቱ በሰላም አደረሰን +++
 
“አልቦ ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ዘእንበለ ዘወረደ እምሰማይ ወልደ እጓለመሕያው” ዮሐ.3፥13

ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፡፡ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው፡፡ ይህ ኃይለ ቃል ክብር ምስጋና ይግባውና ስለጌታችን፣ አምላካችን፣ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት መውረድ ከድንግል ማርያም መወለድ እና የሰውነቱን ሥራ ጨርሶ በክብር ወደ ሰማይ ማረጉን የሚገልጽ ነው፡፡ እንደሚታወቀው አምላካችን ስለሁለት አቢይ ጉዳዮች ሰው ሆኗል፡፡

ለቤዛነት /ዓለምን ለማዳን/
ለአርአያነት /ምሳሌነት/

የሰውን ልጅ በመውደዱ ልዑል ባሕርዩን ዝቅ አድርጎ ከሰማይ ወረደ ሥጋ ለበሰ በምድር ላይ ተመላለሰ፤ ምድርን በኪደተ እግሩ ቀደሰ፤ ድውያንን ፈወሰ፤ ፍጹም ሰው እንደ መሆኑ ተራበ ፍጹም አምላክ መሆኑንም ያስረዳ ዘንድ አምስት ገበያ ሕዝብ በአምስት እንጀራ በሁለት ዓሣ አጠገበ ማቴ.14፥19 ለእኛ አርአያና ምሳሌ ለመሆን ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ ዮሐ.13፥14 እኛም ፍለጋውን እንከተል ዘንድ “አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ ለቢፅክሙ” እናንተም ለባልንጀሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉ ብሎ አዘዘ፡፡ መምሕረ ትሕትና ነውና በዚህ ዓይነት መልኩ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር በዚህ ዓለም ኖረ ለሐዋርያት ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን አስተማራቸው ትምህርት በሚገባ ከተረዳለት በኋላ ለድኅነተ ዓለም በማዕከለ ምድር በቀራንዮ ተሰቀለ፡፡

“ወገብረ መድኀኒተ በማዕከለ ምድር” እንዲል በምድር መካከል መድኀኒትን አደረገ መዝ.73፥12

“እስመ ኢይደልዎ ለነቢይ መዊት በአፍአ ዘእንበለ በኢየሩሳሌም” ነቢይ በኢየሩሳሌም ነው፡፡ እንጂ በውጭ ሊሞት አይገባውም” ብሎ እንደተናገረ፡፡ ሉቃ.13፥33 በሞቱ ዓለምን አድኖ ሦስት መአልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር አድሮ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ብርሃነ መለኮቱን ገልጾ ተነሣ ነቢያት እንደተናገሩ “እግዚአብሔር ይነሣል ጠላቶቹም ይበተናሉ” መዝ.67፥1 እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁ እግዚአብሔርም /እግዚአብሔርነቴ/ አስነሥቶኛልና ተነሣሁ፡፡ መዝ.3፥5 እግዚአብሔር አሁን እነሣለሁ ይላል መድኀኒትንም አደርጋለሁ በዕለቱም እገለጣለሁ” መዝ.11፥5፡፡

“ሥጋየ ደግሞ በተስፋ /በትንሣኤ/ ታድራለች ነፍሴን በሲዖል /በመቃብር/ አትተዋትምና/ እነሣለሁ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም” መዝ.15፥9 “አቤቱ ንቃ ለምንስ ትተኛለህ ተነሥ ለዘወትርም አትጣለን መዝ.43፥23 እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ መዝ.77፥65 ተብሎ የተተነበየውን ትንቢት ፈጽሞ ተነሣ፡፡ በሞቱ ሞታችንን ሻረልን፤ በመቀበሩም ሙስና መቃብርን አጠፋልን፡፡ “በሞቱ ደምሶ ለሞት” በሞቱ ሞትን አጠፋው” እንዲል መጽሐፈ ኪዳን “ወበተቀብሮተ ሥጋሁ ውስተ መሬት አሰሰለ ሙስና እምውስተ መቃብር ወመልሆ እምሥርዉ ወተርእየ ጽውረ ለተወድዮ ውስተ መቃብር እንዘ ውእቱ ይመልዕ ኲሎ” እንዲል፡፡ ሕንፃ መነኮሳት “እርሱ በሁሉ ምሉዕ ሲሆን በመቃብር ለመቀበር ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ተሸክመውት ታየ፡፡ ከመሬት ውስጥ በመቀበሩም ሙስና መቃብርን አጠፋ ከሥሩም ነቀለው” ከተነሣ በኋላ ትንሣኤውን መጀመሪያ ለማርያም መግደላዊት ገለጸ ማር.16፥9፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ስለ ትንሣኤው ሲመሰክር “ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረም፤ መጽሐፍ እንደሚል፤ በሦስተኛው ቀን ተነሣ፡፡ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፡፡ ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ” 1ቆሮ.15፥3-8 ብሎ ክርስቶስ ትንሣኤውን ለተከታዮቹ በሙሉ የገለጠ መሆኑን መስክሯል፡፡ የሚያምኑ ፈሪሳውያንም ትንሣኤው ምትሐት ነው እንዳይሉ እየታየ እያስተማረ እስከ 40 ቀን ድረስ መቆየቱን ይገልጽልናል በዚህም የአርባ ቀን ከትንሣኤ በኋላ ቆይታው ሦስት ቀን ጉባኤ አድርጎ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል፡፡ “ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነበረ” እንዲል ዮሐ.21፥14 ይህንም ሊቃውንት አባቶቻችን፡-

የትንሣኤ
የአግብኦተ ግብር /ዳግም ትንሣኤ/
የጥብርያዶስ ነው ብለው አስቀምጠውታል በዚህ 40 ቀን ቆይታ መጽሐፈ ኪዳንን የቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ ይሆን ዘንድ ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል፡፡


ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም ዕርገቱን ለመናገር ከሰማየ ሰማያት መውረዱን አስቀድሞ ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ማንም ወደ ሰማይ የወጣ የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው ብሎ ከዕርገቱ በኋላ በየማነ አብ፤ በዝባነ ኪሩብ በአምላክነት ሥልጣን ለመኖር ወደሰማይ የወጣ ከእርሱ በቀር ሌላ እንደሌለ አስረግጦ ነገረን፡፡ ሲጀምር ከሰማይ መውረዱን ማስቀደሙ ወረደ ብሎ ዐረገ ለማለት ይመቻል፡፡ ተጸነሰ ተወለደ ለማለት ጥንቱ ከሰማያት ወረደ ማለት እንደሆነ ሁሉ፤ 'ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤ ተነሣ' ለማለት 'ጥንቱ:- ተጸነሠ፤ ተወለደ፤ አደገ ተመላለሰ ሠላሳ ዓመት ኖረ የሚለው ነው፡፡ ስለሆነም ቅዱስ ዮሐንስ ጠርዝና ጠርዙን ይዞ ተናገረ፡፡ ወረደ ዐረገ የሚሉት ሁለት ቃላት የዓለም ድኅነት መነሻና መድረሻ ናቸው እነዚህን ሁለት ቃላት ስናይ በሁለቱ መካከል የተፈጸሙትን የአምላክ ሥራዎች ልብ ማለት ይገባል፡፡ ቤት በመሠረት ይጀመራል በጣሪያ ይፈጸማል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ይህን የቤዛነት ሥራ ሲያስረዳ በዮሐ.1፥14 “ቃል ሥጋ ኮነ” ቃል ሥጋ ሆነ ብሎ ጀምሯል ይህንም ቃል ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም በማለት ሰው መሆኑን ብቻ ሳይሆን በአርያም የሚኖር መሆኑን አስተማረን፡፡ እንግዲህ ጌታችን ዕርገት እንዲሁ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አለመሆኑን ቀድሞ በነቢያት የተነገረ ኋላም በሐዋርያት የተመሰከረ መሆኑን ማወቅ ያስፈለጋል፡፡

የክርስቶስ ዕርገት በትንቢተ ነቢያት

“አጽነነ ሰማያተ ወወረደ ወቆባር ታሕተ እገሪሁ፡፡ ተፅዕነ ላዕለ ኪሩቤል ወሠረረ፡፡ወሠረረ በክነፈ ነፋስ” ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ ወረደም ጨለማ /ዲያብሎስ/ ከእግሩ በታች ነበር በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ በነፍሳትም ክንፍ በረረ” መዝ.17፥9 “አምላክ በእልልታ እግዚአብሔር በመለከት ድምጽ ዐረገ” መዝ.46፥5 ወደላይ ዐረግህ፥ ምርኮን ማረክህ ፥ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ መዝ.67፥18፡፡

“ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘአርገ ውስተ ሰማያት ሰማይ ዘመንገለ ጽባሕ” በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ መዝ.67፥33፡፡

“በሌሊት ራእይ አየሁ እነሆም የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለው ደረሰ /ወደ አብ/ ወደፊቱም አቀረቡት፡፡ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ሥልጣን ተሰጠው ግዛቱም የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት ነው፡፡ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው” ዳን.7፥13 ከዚህ ላይ ዳንኤል ስለጌታችን ዕርገት የተናገረው ዮሐንስ ከተናገረው ጋር ምንም ልዩነት የለውም ግዛት ሥልጣን የዘለዓለም መንግሥት ተሰጠው በማለት ጌትነቱን አምላክነቱን አጉልቶ ዮሐንስ ከእርሱ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም ያለውን ቀደም ሲል በመንፈስ ረድኤት ጸንቶ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ተናግሮታል ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር እያለ አምላክነቱን ገልጾታል አረገ ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር መሆኑን አጽንዖት ሰጥቶ ነግሮናል ዳዊት እግዚአብሔር ብሎ የገለጸውን ዳንኤልና ዮሐንስ እንደአንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው የሰው ልጅ በማለት ገልጸውታል፡፡ ፍጹም ሰው ሆኖአልና፡፡ ክርስቶስ ራሱም “የሰውን ልጅ ማን ይሉታል” ማቴ.16፥15 በማለት ከጠየቀ በኋላ እነዳንኤል የተናሩት ስለ እርሱ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

የክርስቶስ ዕርገት በትምህርተ ሐዋርያት

“ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ወደ ሰማይ አረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ” ማር.16፥19 “እስከ ቢታንያ አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደኢየሩሳሌም ተመለሱ ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ” ሉቃ.24፥50 “ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ ደመናም ከዐይናቸው ሰውራ ተቀበለችው እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኩር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ እነሆ ነጫጭ ልብስ ለብሰው ሁለት ሰዎች /መላእክት/ በአጠገባቸው ቆሙ ደግሞም የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለምን ቆማችኋል ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት ዳግመኛ ይመጣል አሏቸው” ሐዋ.1፥9-12 በማለት ሐዋርያት የክርስቶስን ዕርገት ከመላእክት ጋር ሆነው እንደተመለከቱ ደስታውን እንደተካፈሉ ቅዱስ ሉቃስ ጽፎልናል፡፡ በትንሣኤው ነጭ ልብስ ለብሰው የታዩ መላእክት የደስታ ዘመን ነው ሲሉ በእርገቱም ነጭ ልብስ ለብሰው የዕርገቱን የምሥራች ለሐዋርያት አብስረዋል፡፡ ጌታችን በዚህ ዓለም ሲመላለስ ሲያስተምር የቅዱሳን መላእክት ምስክርነት አልተለየም በልደቱ “ለዓለም ሁሉ የሚሆን መድኀኒት ተወልዶላችኋል ታላቅ የምሥራችን እንነግራችኋለን” ሲሉ ለእረኞች አብስረዋል፡፡ ሉቃ.2፥10-15 ክርስቶስ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾሞ ዲያብሎስን ድል በነሳ ጊዜ “መላእክትም ያገለግሉት ዘንድ መጡ” ማቴ.4፥11 በትንሣኤውም “እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ክርስቶስ እንድትሹ አውቃለሁ ተነሥቶአል ከዚህ የለም” ማቴ.28፥4-11 ብለው ለሴቶች የትንሣኤውን የምሥራች ነግረዋል በመስቀሉ ስርም ደሙን በብርሃን መነሳንስ ሲቀበሉ ለከ ኃይል እያሉ ሲሰግዱ ችሎታውን ቸርነቱን ሲያደንቁ ብሎ የቤተ መቅደስ መጋረጃ በሰይፋቸው ለሁለት ሲከፍሉ ታይተዋል፡፡ ማቴ.27፥51 ዛሬም በዕለተ ዕርገት በዕለተ ልደት ያመሰገኑት ምሥጋና እያመሰገኑ የምሥራች ለሰው ልጆች ሲነግሩ እርገቱን ከዳግም ምጽአቱ ጋር አስተባብረው ሰብከዋል፡፡ ጌታ ባረገ በ8 ዓመት ያመነው ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያትን መስሎ ስለ ዕርገቱ መስክሯል “በሥጋ የተገለጠ መንፈስ የጸደቀ ለመላእክት የታየ በአሕዛብ የተሰበከ በዓለም የታመነ በክብር ያረገ” 1ጢሞ.3፥16 ልደትን እንደ ዘር ዕርገትን እንደ መከር አድርጎ ገልጾልናል ወርሐ ዘር የመከር ጊዜ ነው፡፡ ገበሬ በጎተራ ያለውን እህል እያወጣ ሲዘራ ከላይ ዝናም ከታች ጭቃውን ታግሶ ነው፡፡ በመከር ጊዜ ያን የዘራውን ምርት በጥፍ ሲያገኝ ደስ ይለዋል መከራውን ይረሳዋል፡፡ ምነው በጨመርኩበት ይላል የክርሰቶስም ልደቱ ስለኛ መከራን ለመቀበል ነውና፥ በሥጋ የተገለጠ ብሎ ትሕትናውን አሳየ፡፡ ዕርገቱን ግን በክብር ያረገ ብሎታል፡፡ ምክንያቱም የሰውነትን ሥራ ፈጽሟልና ድል ነስቶአልና ይህን በሥጋ ዕርገቱን ስናስብ ለምን ዕለቱን ተነሥቶ እለቱን አላረገም ለምንስ እስከ አርባ ቀን በምድር ላይ ቆየ የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ እስከ አርባ ቀን በምድር ላይ የቆየው ትንሣኤው በግልጽ እንዲረዳ ደቀ መዛሙርቱንም መጽሐፈ ኪዳንን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምር ዘንድ ነው፡፡ ሌላው አራት ባሕርየ ሥጋና አምስተኛ ባሕርየ ነፍስ ላለው የሰው ልጅ እንደ ካሰ ለማጠየቅ ነው፡፡ አርባን ለአምስት ቢያካፍሉት ስምንት ስምንት ይደርሳቸዋል፡፡ ይህም ስምተኛው ሺህ ሲፈጽም የዚህ ዓለም ምግብና እንደሚጠናቀቅና፥ ክርስቶስ አራት ባሕርያተ ሥጋ አምስት ባሕርየ ነፍስ ላለው የሰው ልጅ እንደየ ሥራው ለመክፈል መምጣቱን ያስረዳናል፡፡ ከዚህ የሐዋርያት ትምህርት ተነሥተው ሊቃውንት አባቶቻችን ስለ ጌታችን ዕርገት አምልተው አስፍተው አጉልተው ጽፈዋል፡፡

ሠለስቱ ምዕትም /318ቱ ሊቃውንት/ “ሀመ ወሞተ ወተቀብረ ወተንሥአ እሙታን አመ ሣልስት ዕለት አርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ ዳግመ ይመጽዕ በስብሐት ይኰንን ሕያዋነ ወሙታነ” ታመመ ሞተ ተቀበረ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ መንግሠቱም ፍጻሜ የለውም” ጸሎተ ሃይማኖት፡፡

“ወበዝንቱ ዕርገቱ ተጠየቀ እርገቶሙ ለእለ የአምኑ ቦቱ” በእርሱ ዕርገት በእርሱ የሚያምኑ ሰዎች ዕርገት ታወቀ” ስንክሳር ግንቦት 8 “ዐርገ ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን ንጹሐን” የንጹሐን ጻድቃን ዕርገት ያስረዳ ዘንድ ዐረገ” በትንሣኤው ትንሣኤያችን እንደገለጸልን በዕርገቱም እርገታችንን አጸደቀልን ከዚህም የተነሣ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት የሰው ልጆች ዕርገት ገልጾ አስተምሮአል፡፡ “ንህነ ሕያዋን እለ ንተርፍ አመ ምጽአተ እግዚእነ ንትመሰጥ በደመና ምስሌሆሙ ከመ ንትቀበሎ ለእግዚእነ ውስተ አየር” እኛ ሕያዋን ሆንን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉትን አንቀድማቸውም ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክት አለቃ ድምጽ በእግዚአብሔር መለከት ከሰማይ ይወርዳልና በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ጌታን በአየር ለመቀበል ከእርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን እንዲሁም ሁል ጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናልን ስለዚህ እርስ በእርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ” 1ተሰ.4፥15-18 በማለት የክርስቶስ ዕርገት ለምዕመናን ዕርገት መሠረት መሆኑን ገልጾልናል፡፡

ቅዱሳን አረጉ መባላቸውም ከእርሱ ስለሆነ እነኤልያስ ዐረጉ እነ ሄኖክ ከሞት አመለጡ ብለን ብንናገር በእርሱ ኃይል ስለሆነ ቅዱስ ዮሐንስ ከዕርሱ በቀር ከሰማይ የወረደ ወደሰማይ የወጣ የለም ብሎ ሰው መሆኑን አምላክነቱን ነገረን፡፡

በእርግጥም ቅዱሳን ዐረጉ ብንል ድንግል ማርያም ዐረገች ብንል ምዕመናን ያርጋሉ ብንልም ሰዎች ናቸው እንጂ የአምላክነት የፈጣሪነት ባህርይ የላቸውም፡፡ እርሱ ግን ከሰማይ የወረደ በአምልኮነት በየማነ አብ በዘበነ ኪሩብ ለመቀመጥ ያረገ ነው፡፡ የቅዱሳን የዕርገት መሠረትም እርሱ ነው፡፡ ታዲያ ዕርገትን ስናከብር ትሕትናን ማወቅ መተግበር ያስፈልጋል እንደ ሰማይ በትእቢት ከፍ ያለው በትሕናትና ዝቅ ማለት ያስፈልገዋል፡፡ አለዚያ ዕርገትን ማክበር ብቻ በቂ አይደለም፡፡ፈጣሪያችን በሠራልን ቸርነት ተጠቅመን ለሕይወት ዘላለማዊ የሚያበቃንን ሥራ ለመሥራት ያብቃን፡፡

የአምላካችን ቸርነቱ ረድኤቱ አይለየን፡፡
source: http://www.eotc-mkidusan.org/site/
 

No comments:

Post a Comment