Wednesday, January 23, 2019

ጥር 15 - ወበዛቲ ዕለት

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈሰ ቅዱስ ስም አሜን
 ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it) 
ጥር 15-በሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወሩ የከበረች ወንጌልን ሰብኮ ጣዖት አምላኪዎችን በተአምራቱ ያሳመነውና ብዙ አሰቃቂ መከራዎችን የተቀበለው ሕፃኑ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ማኅበርተኞቹ የሆኑ ዓሥራ አንድ ሺህ አራት ሰዎችም አብረው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ 
+ በግራኝ ዘመን ከአንድ ቤተ ክርስቲያን ጋር በእሳት ተቃጥሎ በሰማዕትነት ያረፈው አቡነ ቄርሎስ ዕረፍቱ ነው፡፡
+ የሶርያ ክርስቲያኖች በዚህች ዕለት በዓሉን በድምቀት የሚያከብሩለት የኑሲሱ አቡነ ጎርጎሪዮስ መታሰቢያ በዓሉ ነው፡፡ 
+ ነቢዩ ቅዱስ አብድዩ ዕረፍቱ ነው፡፡
አቡነ ቄርሎስ ኢትዮጵያዊ፡- አባታቸው ሳይንቱ እናታቸው ወለቃት ሲባሉ የመጀመሪያ ስማቸው መብዓ ሥላሴ ነው፡፡ በባሕታዊነታቸው መላ ገዳማቱ ሁሉ ያደንቋቸው የነበሩ ሲሆን እንደ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ 60 አንበሶችና 60 ነብሮች የተሰጣቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ጻድቁ በክፉው ግራኝ ዘመን ከአንዲት ቤተ ክርስቲያን ጋር አብረው ተቃጥለው ነው በሰማዕትነት ያረፉት፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!


+++
ነቢዩ ቅዱስ አብድዩ፡- የስሙ ትርጓሜ ‹‹የእግዚአብሔር አገልጋይ›› ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ 1ኛ ነገ 18፡3 ላይ ‹‹አብደዩ እግዚአብሔርን እጅግ ይፈራ ነበር›› ተብሎ የተነገረለት እውነትም ‹‹የእግዚአብሔር አገልጋይ›› የሆነ የነቢዩ ኤልያስ ደቀመዝሙር የነበረ ታላቅ ነቢይ ነው፡፡ ይህም ቅዱስ ነቢይ ከጠረፍ በረሃ አቅራቢያ ካለች ሱሳም በምትባል አገር ካሉ ሰዎች ወገን ነው፡፡ አባቱ ሐናንያ ይባላል፡፡ ለነቢዩ ኤልያስ ደቀ መዝሙሩ ሆኖ በንጉሡ በአክዓብምና በንግሥቲቱ በኤልዛቤል ምክንያት በእርሱ ላይ የመጣውን መከራ ሁሉ ታግሷል፡፡ ታላቁ ነቢይ ኤልያስ ከእነ ኤልዛቤል ሸሽቶ ወደ ተራራ ላይ ወጥቶ በዋሻ ተሸሽጎ ምግቡን አሞራ እያመጣለት በኖረበት ጊዜ እንኳን ነቢዩ አብድዩ ግን ብቻውን የእግዚአብሔርን ነቢያት ይንከባከብ ነበር፡፡ አብድዩ የንጉሥ አክዓብ የቤቱን አዛዥ የነበረ ቢሆንም ንግሥት ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ አብድዩ መቶውን ነቢያት ወስዶ ሃምሳ ሃምሳውን በዋሻ ውስጥ ሸሽጎ እንጀራና ውኃ ይመግባቸው የነበረ ታላቅ ባለውለታ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ታሪኩ እንዲህ ተብሎ ነው የተጻፈው፡-
‹‹ከብዙ ቀንም በኋላ በሦስተኛው ዓመት ‹‹ሂድ ለአክዓብ ተገለጥ፥ በምድር ላይም ዝናብ እሰጣለሁ›› የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ፡፡ ኤልያስም ለአክዓብ ይገለጥ ዘንድ ሄደ፤ በሰማርያም ራብ ጸንቶ ነበር፡፡ አክዓብም የቤቱን አዛዥ አብድዩን ጠራ፤ አብድዩ እግዚአብሔርን እጅግ ይፈራ ነበር፡፡ ኤልዛቤልም የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ እርሱ መቶውን ነቢያት ወስዶ አምሳ አምሳውን በዋሻ ውስጥ ሸሽጎ እንጀራና ውኃ ይመግባቸው ነበር፡፡ አክዓብም አብድዩን ‹‹በአገሩ መካከል ወደ ውኃው ምንጭ ሁሉና ወደ ወንዝ ሁሉ ሂድ፤ እንስሶችም ሁሉ እንዳይጠፉ ፈረሶችንና በቅሎችን የምናድንበት ሣር ምናልባት እናገኛለን›› አለው፡፡ ሁለቱም የሚመለሱበትን አገር ተካፈሉ፤ አክዓብም ለብቻው በአንድ መንገድ አብድዩም ለብቻው በሌላ መንገድ ሄዱ፡፡
አብድዩም በመንገድ ሲሄድ እነሆ ኤልያስ ተገናኘው፤ አብድዩም አወቀው፣ በግምባሩም ተደፍቶ ‹‹ጌታዬ ሆይ! ኤልያስ አንተ ነህን? አለ፡፡ ኤልያስም ‹‹እኔ ነኝ ሄደህ ለጌታህ ‹ኤልያስ ተገኝቶአል› በል›› አለው፡፡ አብድዩም ‹‹እኔን ባሪያህን እንዲገድል በአክዓብ እጅ አሳልፈህ ትሰጠኝ ዘንድ ምን ኃጢአት አድርጌአለሁ? አምላክህ ሕያው እግዚአብሔርን! ጌታዬ ይፈልግህ ዘንድ ያልላከበት ሕዝብ ወይም መንግሥት የለም፤ ሁሉም ‹‹በዚህ የለም›› ባሉ ጊዜ አንተን እንዳላገኙ መንግሥቱንና ሕዝቡን አምሎአቸው ነበር፡፡ አሁንም እነሆ ‹ሂድ ኤልያስ ተገኘ ብለህ ለጌታህ ንገር› ትለኛለህ፡፡ እኔም ከአንተ ጥቂት ራቅ ስል የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወደማላውቀው ስፍራ ይወስድሃል፤ እኔም ገብቼ ለአክዓብ ስናገር ባያገኝህ ይገድለኛል፤ እኔም ባሪያህ ከትንሽነቴ ጀምሬ እግዚአብሔርን እፈራ ነበር፡፡ ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ መቶውን የእግዚአብሔር ነቢያት ወስጄ አምሳ አምሳውንም በዋሻ ውስጥ ሸሽጌ እንጀራና ውኃ የመገብኋቸው ነበር፡፡ ይህ ያደርግሁት ነገር በውኑ ለጌታዬ አልታወቀህምን? አሁንም ‹ሄደህ ኤልያስ ተገኘ ብለህ ለጌታህ ንገር ትላለህ› እርሱም ይገድለኛል›› አለው፡፡
ኤልያስም ‹‹በፊቱ የቆምሁት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔ ዛሬ ለእርሱ እገለጣለሁ›› አለ፡፡ አብድዩም አክዓብን ሊገናኘው ሄደ፣ ነገረውም፤ አክዓብም ኤልያስን ሊገናኘው መጣ፡፡ አክዓብም ኤልያስን ባየው ጊዜ ‹‹እስራኤልን የምትገለባብጥ አንተ ነህን?›› አለው፡፡ ኤልያስም ‹‹እስራኤልን የምትገለባብጡ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ በኣሊምን የተከተላችሁ፣ አንተና የአባትህ ቤት ናችሁ እንጂ እኔ አይደለሁም›› አለው፡፡ 1ኛ ነገ 18፡1-20፡፡
ቅዱስ አብድዩ የንጉሥ አክዓብ የቤቱን አዛዥነቱን ትቶ የኤልያስ ቀደ መዝሙሩ ሆኖ በነቢይነት እግዚአብሔርን ሲያገለግል ኖረ፡፡ በንጉሥ ኢዮሳፍጥ ዘመንም ትንቢትን ተናገረ፡፡ እግዚአብሔርም ስለ ትንሣኤና ስለ ፍርድ ቀን በቃሉ ነገረው፡፡ ሁለተኛም ከእስራኤል ልጆች የሚሆነውን ከአሕዛብም ለቀሩት አጸናቸው፣ አብዝቶ መከራቸው፣ ገሠጻቸውም፡፡ የትንቢቱም ወራት ሲፈጸም በዚህች ዕለት በሰላም በፍቅር አንድነት ዐርፏል፡፡ የትንቢቱም ወራት ሃያ ዓመት ነው፡፡ ይኸውም ከጌታችን ሥጋዌ በፊት በ900 ዓመት ነው፡፡
+ + +
ዳግመኛም በዚህች ዕለት የሶርያ ክርስቲያኖች የኑሲሱን የአቡነ ጎርጎሪዮስን የዕረፍቱን በዓል በደማቅ ሁኔታ ያከበራሉ፡፡ በእኛ አቆጣጠር ግን ዕረፍቱ ጥር 21 ቀን ነው፡፡ (የጥር ሃያ አንዱን ይመለከቷል፡፡)
+ + +
ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ፡- ሦስት ዓመት እንኳን ሳይሞላው በሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወሩ ታላቅ ሰማዕትነትን የተቀበለው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ አባቱ ቆዝሞስ (ስምዖን) እናቱ ኢየሉጣ ይባላሉ፡፡ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ በኅዳር 15 ቀን የተወለደ ሲሆን ሀገሩ በታችኛው እስያ ልዩ ስሙ ሀንጌቤን ይባላል፡፡ ዘመኑ ዘመነ ሰማዕታት ነበርና መምለኬ ጣዖት የሆነው ንጉሥ እስክንድሮስ ቅድስት ኢየሉጣን ‹‹ለጣዖቴ ስገጂ›› ብሎ አስገደዳት፡፡ እርሷም ‹‹ሕፃኑ ልጄ መጥቶ ይመስክር›› ብላ ስትናገር ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ተጠራና ተጠየቀ፡፡ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስም ‹‹ለጣዖት አንሰግድም፣ ዘላለማዊ የሆነ የማይሻር አምላክ ስላለ ለእርሱ ነው የምንሰግደው›› ብሎ የአምላኩን ክብር በሕፃን አንደበቱ መሰከረ፡፡ ሕፃኑም ይህንን በመሰከረ ጊዜ ዕድሜው ገና ሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወሩ ነበር፡፡
ነቢዩ ቅዱስ ዳዊትም ‹‹ከልጆችና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ›› ሲል እንደተናገረ (መዝ 10፡2፣ 118፡130) መድኃኔዓለም ክርስቶስም በቅዱስ ወንጌሉ ላይ ‹‹አባት ሆይ፣ የሰማይና የምድር ጌታ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ›› ያለውን ቃል በሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ሕይወት ተግባራዊ ሆኖ አይተነዋል፡፡ ማቴ 11፡27፡፡ በነቢዩም ትንቢት መሠረት በበዓለ ሆሣዕና ዕለት በእናታቸው እቅፍና ጀርባ ላይ የነበሩ እምቦቀቅላ ጨቅላ ሕፃናት ‹‹ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው›› በማለት ጌታችንን አመስግነውታል፡፡
እንደዚሁ ሁሉ ቅዱስ ቂርቆስም በከሃዲው ንጉሥ ፊት የጌታችንን ክብር በመሰከረ ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተቆጥቶ 40 ጋን ውኃ የሚይዝ በርሜል አስጥዶ 40 ቀን ሙሉ እሳት አስነድዶ ቅንጭብ፣ ዘይት፣ ዝፍጥና ሌላም በእጅጉ የሚጎዱ ነገሮችን በውስጡ ጨምሮ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱን ቅድስት ኢየሉጣን ወደዚያ እቶኑ እሳት እንዲከቷቸው አዘዘ፡፡ ንጉሡ እስክንድሮስ ጭፍሮቹን "ሰም፣ ጨው፣ ባሩድ፣ሙጫ፣ እርሳስ፣ ብረትን፣ ቅንጭብ፣ ቁልቋል ጨምሩበት" ብሎ አዘዛቸው፡፡ ጭፍሮችም ያዘዛቸውን ከፈጸሙ በኀላ መጥተው "ያዘዝከንን ሁሉ ጨምረንበት ነዶ ፈልቷል" አሉት፡፡ "ድምፁም እንደ ነጎድጓድ ይሰማል፤ ወላፈኑም እንደ ፀሐይ ያንፀባርቃል፡፡ የፍላቱም ኃይል 14 ክንድ ያህል እየዘለለ ይወጣል፡፡ በውስጡ የሚጣሉትን ሰዎች እዘዝ" አሉት፡፡ ያንጊዜም ህፃን ቂርቆስንና እናቱን ኢየሉጣን ይዘው ከእስር ቤት አወጧቸው፡፡ በክርስቶስ ስም ስላመኑ በእስር ቤት አግብተው አስረዋቸው ነበርና ፍላቱ ወደ ላይ በሚዘል በብረት ጋን ውስጥ ለመጨመር ሲወስዷቸው በዚያን ጊዜም እልፍ ከአንድ ሺህ አራት መቶ ሰዎች እንዲወጡና በፈላው የብረት ጋን ውስጥ የቅዱሳንን አሟሟት እንዲያዩ ሹሙ አዘዘ፡፡ ቅድስት ኢየሉጣም የፍላቱን ግርማ ባየች ጊዜ ተሸበረች፡፡ ተጠብቆላት ያለውንም ዋጋ ትታ ልትክድ ፈለገች፡፡ ቅዱስ ቂርቆስም ይህን ባወቀ ጊዜ "እናቴ ሆይ ከብረት ጋን ግርማ የተነሳ አትፍሪ፤ ድንጋፄም አይደርብሽ" እያለ ከብሉይና ከሐዲስ እየጠቀሰ እንድትጸና አስተማራት፡፡
"ነገር ግን እናቴ ሆይ አናንያንና አዘርያን፣ ሚሳኤልንም እግዚአብሔር ከዕቶን እሳት እንዳወጣቸው እወቂ፤ እኛንም ከዚህ ከብረት ጋን ውስጥ ሊያድነን ይችላል፡፡ እናት ሆይ ከሚያልፈው ከዚህ ዓለም ጭንቅ ልታመልጭ በሚያልፈው በዘለዓለም እሳት ልትቀጭ ትሻለች፡፡ እናት ሆይ ይህን አትሺ፤ ይቅርብሽ አሁን እግዚአብሔር በመካከላችን አለና ይረዳናል፡፡ ሶስናን ከሀጢያተኞች እጅ ያዳናት እኛንም ከብረት ጋን ያድነናል፡፡ ዳንኤልን ከአንበሶች አፍ ያዳነ እርሱ ያድነናል፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ብረት ጋን ውስጥ ግዳጃችን ልንፈፅም ፈቅዶም እንደሆነ የኢዮብን ነፃነት (ትእግስት) ልናገኝ ይገባናል፡፡ እርሱ ልጆቹንና ሚስቱን ያገኘው ገንዘብ ሁሉ አጥቶ በመጨረሻው ሰውነቱን አጥቶ ነበርና ምንም ምንም የቀረበለት አልነበረምና እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ ከማለት በቀር ያለው ነገር የለም እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔርም ወሰደ አለ፡፡ የእግዚአብሔር ስሙ ለዘለዓለም ይመስገን አለ፡፡ እኛም ይህንን መከራ ልንታገስና የተጠበቀልንን ልንከተል ይገባናል..." እያለ አብዝቶ መከራት፡፡ ነገርግን በዚህም ምክር እናቱን መመለስና ለሰማዕትነት ማዘጋቸት አልቻለም፡፡ ከዚህ በኋላ ቂርቆስ ዓይኖቹን ወደሰማይ አቅንቶ መጸለይ ጀመረ፡፡ "እግዚአብሔር ሆይ ይህች ባርያህ ከምትክድ ከህይወት መፅሐፍ እኔን ፋቀኝ አለ፡፡ አቤቱ ይህነን ነገር ልታደርግ አይገባህም፤ አቤቱ እርሻውን ልታቃጥል ፍሬውንም ልትባርክ ትወዳለህን፡፡ አቤቱ እንጨቱን ቁረጡና አንድዱት ቅጠሉን ጠብቁ ብለህ ልታዝ አይገባህም፡፡ እንጨቱንም ቅጠሉንም ጠብቁ ብለህ እዘዝ እንጂ ይህ አይገባህም ያመነብህ ሁሉ ይህን ያየ ዘንድ፡፡ ማዳን የሚችል አምላክ ኑሮአቸው ቢሆን ከዚህ ከእሳት ባልሸሹም ነበር ብሎ እንዳይጠራጠር፡፡ ዲያብሎስ ከባለስልጣኑ ይልቅ እኔ በረታሁ ቅዱሳኑም ድል ነሳኋቸው ብሎ እንዳይመካ፣ ከመንጋውም አንድ በግ ቀማሁ እንዳይል አቤቱ የኃይል መንፈስ ለእናቴ ስጣት አበርታት..." ብሎ ጸለየ፡፡ በዚያን ጊዜ ዲያብሎስ ከእርሷ ሸሽቶ ሄደ፡፡ ከዚህ በኋላ ቅድስት እናቱ እንዲህ አለች፡- በመንግስተ ሰማያት አባት የሆንከኝ ልጄ ሆይ ጌታህ ኃይል ስጠኝ፡፡ የሚጠብቀንን ገድላችንን እንፈፅምና ድል እንነሣ" አለችው፡፡ የብረት ጋኑን ሲነድ ሳየው በምንጭ ላይ በዝቶ እንደሚወርድ ጠል ሁኖ አየዋለሁና፡፡ ቅዱሳንም ይህንን ሲነጋገሩ አንስተው ከብረት ጋኑ ውስጥ ጨመሯቸው፡፡ በውስጡም አንገትን የሚቆለምም ልብን የሚያጣምም ሆድን የሚሰነጥቅ ሥርንም የሚበጥስ መሣሪያ ነበረበት፡፡ ወዲያውም የራማው ልዑል ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ገብርኤል እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥኖ ከሰማይ ወረደና የብረት ጋኑን እሳት ፈጽሞ አበረደው፡፡ ከቅዱሳንም አንዱን እንኳን ሳይነካው የብረት ጋን ማቃጠሉና መፍላቱ ፀጥ አለ፡፡ እንደ ውኃም ሆነ፡፡
ንጉሡም እሳቱ እንዳልጎዳቸው ሲያውቅ ከዚያ አውጥቶ በሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ አፍና አፍንጫ መርዝ ከተተበት፣ ነገር ግን መርዙ ምንም አልጎዳውም እንዳውም ምግብ ሆነው፡፡ ዳግመኛም ጨውና በርበሬ በዐይኑ አነደደበት፡፡ አሁንም ምንም አልነካውም፡፡ ከዚህም በኀላ ሹም እስክድሮስም አስራ አራት የተሳሉና የጋሉ ብረቶች ያመጡ ዘንድ ዳግመኛ አዘዘ፡፡ ሰባቱን በእናቱ አካል ሰባቱን በሱ አካል ውስጥ ይተክሉ ዘንድ ከነዚሁም ሁለቱን በጆሮዎቹ ሁለቱን በዓይኖቹ ሁለቱን በአፍንጫዎቹ አንዱን በልቡ ይተክሉ ዘንድ አዘዘ፡፡በሕፃኑም ላይ ሹሙ እንዳዘዘው አደረጉበት፡፡ አሁንም ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደና ፈወሳቸው፡፡
ዳግመኛም የሕጻኑን እራስ ከነቆዳው ገፈው በእሳት ውስጥ ይጨምሩ አንድ ሹም አዘዘ፡፡ እንዲሁም አደረጉበት፡፡ ዳግመኛም ቅዱስ ገብርኤል እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥኖ መጥቶ ይህንን መከራ ከሕፃኑ አራቀለት፡፡ ዳግመኛም ሹሙ በመቃን ውስጥ ጨመረው በገመድ እንዲሰቅሉት አዘዘ፡፡ ከዚህም መከራ መልአኩ አዳነው፡፡ ሐምሌ 19 ቀን በዓሉን በታላቅ ድምቀት የምናከብረው ይህንን ሁሉ የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤልን ተራዳኢነት በማሰብ ነው፡፡
ንጉሡም በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በብዙ ጭንቅና ሥቃይ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣን ለ3 ዓመታት አሠቃያቸው፡፡ እነርሱም መከራን እየተቀበሉ በከሀዲው ንጉሥ ፊት የአምላካቸውን ስም እየጠሩ መሰከሩ፡፡ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና ክብሩን ይመሰክሩለት ዘንድ የቢታንያን ድንጋዮችና የበለዓምን አህያ አንደበት ከፍቶ ያናገረ አምላክ ሦስት ዓመት እንኳን ባለሞላው በሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወር ሕፃን ልጅ ላይ አድሮ በወቅቱ የነበሩ ዓላውያን ነገሥታት ክብሩን እንዲያውቁ አደረገ፡፡
ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ሄሮድስ ላስፈጃቸው 144,000 የቤቴልሔም ሕፃናት አለቃቸው ነው፡፡ ይህስ እንደምን ነው ቢሉ ሄሮድስ ያስፈጃቸው እነኚያ እልፍ የቤቴልሔም ሕፃናት የተገደሉት ጌታችንን ለማግኘት በተደረገው ፍለጋ ምክንያት ስለሆነ ቅዱስ ቂርቆስን በመሞት ይተካከሉታል እርሱ ግን የአምላኩን ስምና ክብር በማስተማርና በመመስከር ሰማዕትነትን ስለተቀበለ በዚህ ይበልጣቸዋልና ለእነኚያ እልፍ የቤቴልሔም ሕፃናት አለቃ አድርጎ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሾሞታል፡፡ ቅዱስ ገድሉም እንደሚናገረው ‹‹መንገድ ጠራጊ ከተባለ ከዮሐንስ መጥምቅ በቀር ሴቶች ከወለዱዋቸው እንደ አንተ ያለ አልተገኘም›› በማለት ጌታችን በማይታበል ቅዱስ ቃሉ ታላቅ የሆነ ቃልኪዳኑን በመሐላ አጽንቶለታል፡፡ በመጨረሻም ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ተጋድሎውን ፈጽሞ ጥር 15 ቀን በ3 ዓመት ከ1 ወር ከ3 ቀኑ አንገቱን በሰይፍ ተቆርጦ ሰማዕትነትን ተቀብሏል፡፡ ሲሰየፍም ከአንገቱም ደም፣ ውኃና ወተት የወጣ ሲሆን ሦስት አክሊላትም ወርደውለታል፡፡ ጌታችንም የመከራውን ጽናት የትዕግስቱን ብዛት አይቶ ከመከራ ሊያሳርፈው ፈቀደና ተገልጾለት ‹‹ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ቂርቆስ›› አለው፡፡ ‹‹ሰላም ላንተ ይሁን፤ የመከራህን ጽናት፣ የትዕግስትህን ብዛት አይቼ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍህ መጣሁ›› ብሎ ብዙ ቃልኪዳን ሰጠው፡፡ ‹‹…ስምህ በተጠራበት፣ ቤተመቅደስህ በታነጸበት፣ ስዕልህ ባለበት ቦታ ሁሉ የሕፃናት እልቂት፣ የከብት በሽታ፣ የእህል እጦት ርሀብ፣ ቸነፈር አይደርስም›› የሚል አስደናቂ ቃልኪዳንም ገብቶለታል፡፡ ሕፃኑም በምድር ላይ አልተቀበረም ይልቁንም ጌታችን በኤልያስ ሰረገላ ሥጋውን አሳርጎለታል፡፡ እናቱ ቅድስት ኢየሉጣም በጥር 16 ቀን ሰማዕትቷን በክብር ፈጽማለች፡፡ የቅዱስ ቂርቆስ ማኅበርተኞች የሆኑ ዓሥራ አንድ ሺህ አራት ሰዎች የጌታችንን ክብር እየመሰከሩ በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡
የቅዱስ ቂርቆስና ማኅበርተኞች የሆኑ የቅዱሳን ሰማዕታት ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!
ዳግመኛም ጥር 14 ቀን እነዚኽ ታላላቅ ቅዱሳን በዓመታዊ በዓላቸው ታስበው ውለዋል፡-
+ የዚህን ዓለም ሹመት ለመሾም ወደ ንጉሡ እየሄደ ሳለ ማዕበል የተፋው አንድ በድን ቢያገኝ በዚያው የዓለምን ኃላፊነትና የእርሱንም መሞት አስቦ የመነኮሰውና የሴትንም ፊት እንዳያይ ቃል ገብቶ በታላቅ ተጋድሎ የኖረው አቡነ አርከሌድስ ዕረፍቱ ነው፡፡ 
+ በ12 ዓመቷ ከከሃድያንን ነገሥታት ጋር ስለ እምነቷ ተጋድላ በሰማዕትነት ያረፈችው ቅድስት ምህራኤል ዕረፍቷ ነው፡፡ + መቋሚያቸው በሰው አንደበት የምትናገረውና የወይራ ዛፍ እንደተደገፉ ሳይንቀሳቀሱ 40 ዓመት ሙሉ የጸለዩት ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ አካለ ክርስቶስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ 
+ ዐፅማቸው ደብረ ዳሞ ያረፈው የወሎው አቡነ ዘድንግል ዕረፍታቸው ነው፡፡ 
+ ዐፅማቸው ዋልድባ ዳልሻ የሚገኘው የትግራይ ተወላጁ አቡነ ምሥራቃዊ ልደታቸው ነው፡፡ 
+ ቅዱስ መክሲሞስ በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡ 
+ ቅድስት እምራይስ በሰማዕትነት ዐረፈች፡፡ 
+ ከተሰዓቱ ቅዱሳን ውስጥ አንዱና ዋነኛው የሆኑት ጻድቁ አቡነ አረጋዊ ልደታቸው ነው፡፡
ሰማዕቷ ቅድስት ምህራኤል፡- ይህችውም የከበረችና የተመሰገነች ቅድስት ምህራኤል ጠምዋህ ከሚባል አገር የተገኘች ታላቅ ሰማዕት ናት፡፡ ወላጆቿ ካህኑ አባቷ ዮሐንስና እናቷ ኢላርያ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ደገኞች ናቸውና እርሷንም በሃይማኖት በምግባር ኮትኩተው አሳደጓት፡፡ መጀመሪያውንም ልጅ ስላልነበራቸው በስዕለት ከብዙ ዘመን በኋላ ነው ያገኟት፡፡ ስዕለታቸውም ደርሶላቸው ቅድስት ምህራኤልን ከወለዷት በኋላ ፈሪሃ እግዚአብሔርንና የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያስተማሩ አሳደጓት፡፡
ቅድስት ምህራኤልም 12 ዓመት በሆናት ጊዜ በላይዋ ባደረ በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን መሥራት ጀመረች፡፡ ከሃዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ በነገሠና አምልኮተ ጣዖትን በአዋጅ ባወጀ ጊዜ ቅድስት ምህራኤል ስለ ጌታችን አምላክነት መስክራ ሰማዕት መሆንን ተመኘች፡፡ ከዚህም በኋላ በቁርጥ ሀሳብ ተነሥታ ወደ ባሕር ዳርቻ በመሄድ በመርከብ ተሳፍራ ሄዳ ስሙ ፍልፍልያኖስ የሚባለው የዲዮቅልጥያኖስ መኮንን ዘንድ ደረሰች፡፡ በመርከብም ስትጓዝ ሌሎች ስለ ቀናች እምነታቸው ሰማዕትነትን ለመቀበል የተዘጋጁ ሰማዕታትን አግኝታ ከእነርሱ ጋር ነበረች፡፡ በመኮንኑም ፊት ቆማ እውነተኛውና ሊመለክ የሚገባው አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑን መሰከረች፡፡ መኮንኑም ስለ ታናሽነቷ ራርቶላት ከሌሎቹ ለይቶ ሊተዋት ወደደ፡፡ ነገር ግን ቅድስት ምህራኤል መኮንኑ እንደተዋት ዐውቃ የተመኘችውን ሰማዕትነት ሊያስቀርባት መሆኑን ባየች ጊዜ ዳግመኛ መኮንኑንና የረከሱ አማልክቶቹን በድፍረት ረገመችበት፡፡
ከዚህም በኋላ መኮንኑ በጣም ተቆጥቶ ጽኑ በሆኑ የተለያዩ ሥቃዮች አሠቃያት፡፡ ከቀናች ሃይማኖቷም ሸንግሎ ይመልሳት ዘንድ እንዳልተቻለው ሲያውቅ መርዛማ እባቦች፣ ጊንጦችና እፉኝቶች ወዳሉበት ጉድጓት ጣላት፡፡ ከቅድስት ምህራኤልም ጋራ ሌሎች ብዙ ሰማዕታት አብረው ተጣሉ፡፡ በዚህም ጊዜ የታዘዘ የእግዚአብሔር መልአክ ለቅድስት ምህራኤል ተገለጸላትና ከጌታችን ዘንድ የተሰጣትን ቃልኪዳን አስረከባት፡፡ ከዚህም በኋላ ነፍሷን ለእግዚአብሔር አሳልፋ ሰጥታ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለች፡፡ ምእመናንም የከበረ ሥጋዋን መርዛማ እባቦችና ጊንጦች ካሉበት ቦታ አውጥተው በክብር ቀበሯት፡፡ በኋላም ወላጆቿ ልጃቸው ቅድስት ምህራኤል ስለ እምነቷ መስክራ በክብር ሰማዕት መሆኗን በሰሙ ጊዜ ከብዙ የሀገራቸው ሕዝብ ጋር መጥተው የከበረ ሥጋዋን አፍልሰው ወደ አገራቸው ወሰዱት፡፡ ያመረች ቤተ ክርስቲያንም ሠርተው ሥጋውን በውስጧ ባኖሩ ጊዜ ከሰማዕቷ ቅዱስ ሥጋ ብዙ አስገራሚ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡
+ + +
አቡነ አርከሌድስ ግብፃዊ፡- በትውልዱ ከሮሜ ሀገር ከታላላቅ ወገኖች ነው፡፡ አባቱ ዮሐንስ እናቱ ሰንደሊቃ ሲባሉ ሁለቱም የእግዚአብሔርን ሕግ የሚጠብቁ እውነተኞች ነበሩ፡፡ ቅዱስ አርከሌድስም ዕድሜው 12 ዓመት በሆነው ጊዜ አባቱ ዮሐንስ ሞተ፡፡ በኋላም እናቱ ግን ሚስት ልታጋባው አሰበች እርሱ ግን ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ አባቱ በሕይወት ሳለ ንጉሡ የሾመው ነበርና እናቱ አሁንም ወደ ንጉሡ ሄዶ የአባቱን ሹመት ይቀበል ዘንድ አርከሌድስን መከረችው፡፡ ለንጉሡ የሚሰጥ እጅ መንሻንና አገልጋዮችን አድርጋ ብዙ ገንዘብ አስይዛ ላከችው፡፡ እርሱም በመርከብም ተጭኖ ሲሄድ ታላቅ ንፋስ ተነሣና ማዕበሉ አየለባቸው፡፡ መርከቡም ተሰበረ፡፡
ቅዱስ አርከሌድም አንዲት የመርከብ ስባሪ ሠሌዳ ላይ ተንጠልጥሎ ወደ የብስ ደረሰ፡፡ ከባህሩ ሲወጣ ማዕበል የተፋው አንድ በድን አገኘና ተቀምጦ ስለ በድኑ አለቀሰ፡፡ የዓለምን ኃላፊነትና እርሱም ከሞተ በኋላ አፈርነቱን አሰበ፣ ነፍሱንም ገሠጻት፡፡ ወደ ቀና መንገድ ይመራውም ዘንድ ወደ ጌታችን ለመነ፡፡ ረጅም መንገድ ተጓዘና ሶርያ ውስጥ በቅዱስ ሮማኖስ ስም ወደተሠራች አንድ ተራራማ ገዳም ደረሰ፡፡ ከገንዘቡም ከእርሱ ጋር የቀረውን ሁለት መቶ የወርቅ ዲናር ለአበ ምኔቱ ሰጠው፡፡ እንዲያመነኩሰውም ጠየቀው፡፡ መጀመሪያውኑ አርኬሌድስ ከመምጣቱ በፊት ለአበምኔቱ መንፈስ ቅዱስ የመምጣቱን ነገር አስረድቶት ነበርና እርሱ በደረሰ ጊዜ ደስ አለው፡፡ መነኮሳቱም ሁሉ ከጸለዩለት በኋላ አመነኮሰው፡፡
ከዚህም በኋላ የከበረ አርከሌድስ ጽኑ ተጋድሎ መጋደል ጀመረ፡፡ ሲጸልይ ይውላል ሲጸልይ ያድራል፤ ሁልጊዜ በየሰባቱ ቀን የሚጾም ሆነ፡፡ እግዚአብሔርም ሀብተ ፈውስን ሰጥቶት ብዙ ሕመምተኞችን ፈወሳቸው፡፡ ከዚህም በኋላ የሴቶችን ፊት ከቶ እንዳያይ ከጌታችን ጋር ቃል ገባ፡፡ ። እናቱም ለ12 ዓመት ያህል የልጇን ወሬ ምንም ስላልሰማች በእርሱ የሆነውን አላወቀችም ነበርና የሞተም ስለመሰላት እጅግ አዘነች፡፡ የእንግዶችና የመጻተኞች መቀበያ የሚሆን ቤት ሠርታ የመንገደኞች ማደርያ አደረገችው፡፡ በአንዲት ዕለት ያሳደረቻቸው እንግዶች የቅዱስ አርከሌድስን ዜና ሲናገሩ ሰማቻቸው፡፡ እንግዶቹም ስለ ቅድስናው፣ ስለ ተጋድሎው የሚያሳያቸውን ምልክቶችና ተአምራቶቹን፣ የመልኩንም ደም ግባት ሲነጋገሩ ሰምታ ልጇ እንደሆነ ዐወቀች፡፡
መንገደኞቹንም ስለ ሥራው ጠየቀቻቸውና ሥራውን ሁሉ ነገሯት፡፡ ልጇ በሕይወት እንዳለና ሕያው እንደሆነ ተረዳች፡፡ በዚያን ጊዜ ተነሥታ ወደ ከበረ ሮማኖስ ገዳም ሄደች፡፡ ወደ ልጇዋ ወደ ቅዱስ አርከሌድስ ‹‹እነሆ ፊትህን አይ ዘንድ ወድጄ እኔ እናትህ መጥቻለሁ›› ብላ መልእክት ላከች፡፡ ልጇ ቅዱስ አርከሌድም ‹‹ከቶ የሴቶችን ፊት እንዳላይ ከክብር ባለቤት ከጌታዬ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ቃል ገብቻለሁና ቃልኪዳኔን ማፍረስ አይቻለኝም›› ብሎ መልሶ ወደእርሷ ላከ፡፡ እናቱም ‹‹ፊትህን ካላሳየኸኝ እኔ ወደ ዱር እሄዳለሁ፣ አራዊትም ይበሉኛል›› ብላ ላከችበት፡፡ ቅዱስ አርከሌድስም እናቱ ካላየችው እንደማትተወው እርሱም ለእግዚአብሔር የገባውን ቃልኪዳን ማፍረስ እንደማይቻለው ባወቀ ጊዜ ነፍሱን እንዲወስዳት ወደ ጌታችን ለመነ፡፡ ከዚህም በኋላ የበሩን ጠባቂ ‹‹እናቴን ወደእኔ ትገባ ዘንድ ፍቀድላት›› አለው፡፡ እናቱም ወደ ውስጥ በገባች ጊዜ ልጇን ቅዱስ አርከሌድስን ሙቶ አገኘችውና በታላቅ ድምፅ በመጮህ አለቀሰች፡፡ የእርሷንም ነፍስ ይወስድ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ለመነች፡፡ ጌታችንም ልመናዋን ተቀብሎ ነፍሷን ወሰደ፡፡
እናትና ልጅም በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ካረፉ በኋላ የሁለቱን ሥጋቸውን ለይተው ሊቀብሯቸው ሲሉ የቅዱስ አርከሌደስ በድን በሰው አንደበት መናገር ጀመረ፡፡ ‹‹የእናቴን ሥጋ ከሥጋዬ አትለዩ በሕይወቷ ሳለች ታየኝ ዘንድ ልቧን ደስ አላሰኘሁምና›› የሚል ቃል ከአርከሌድስ በድን ወጣ፡፡ ይህንንም ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ አድንቀው እግዚአብሔርን ካመሰገኑት በኋላ ሁለቱንም በአንድ መቃብር ውስጥ ቀበሯቸው፡፡ ጌታችንም በቅዱስ አርከሌድና በእናቱ ሥጋ ላይ ታላቅ ፈውስን ገለጠና አስገራሚ ተአምራት መታየት ጀመሩ፡፡ በሞት ካረፈ በኋላ በድኑ አፍ አውጥታ የተናገረች ይህ ታላቅ ጻድቅ በስሙ የተሰየመው ትልቅ ገዳም ትግራይ ተንቤን ሀገረ ሰላም ይገኛል፡፡
+ + +
ቅድስት እምራይስ፡- ይኽችውም ቅድስት ከከበሩ ደገኛ ክርስቲያኖች የተወለደች ናት፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔርንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እየተማረች አደገች፡፡ በአንዲትም ዕለት ውኃ ልትቀዳ ወደ ወንዝ ወርዳ ሳለ ተይዘው ስለ ክርስቶስ ታስረው የሚሠቃዩ ሰማዕታትን አየች፡፡ እነርሱም ጳጳሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት ናቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ቅድስት እምራይስ ወደ መኮንኑ ጭፍራ ዘንድ ቀርባ ‹‹እኔም በእነዚህ ቅዱሳን አምላክ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የማምን ክርስቲያን ነኝና ስሜን ከስማቸው ጋር ጽፈህ ወደ ሰማዕትነት አደባባይ አድርሰኝ›› አለቸው፡፡ እርሱም ስሟን ከሰማዕታቱ ስም ጋራ ጽፎ አብሮ አሰራትና በከሃዲው መኮንን ቁልቁልያስ ፊት አቆማት፡፡ መኮንኑም ለጣዖታቱ እንድትሰግድ በብዙ የስንገላ ቃላት አባበላት ነገር ግን ቅድስት እምራይስ የጌታችንን አምላክነት እየመሰከረች የመኮንኑን ጣዖታት ረገመችበት፡፡ መኮንኑም እጅግ ተቆጥቶ አንገቷን በሰይፍ አስረጠውና ሰማዕትነቷን በድል ፈጽማ የክብር አክሊልን ተቀዳጀች፡፡
+ + +
ዳግመኛም በዚህች ዕለት የከበረ ሕፃን የቅዱስ ቂርቆስ ማኅበርተኞች የሆኑ አራት ሺህ ሠላሳ አራት ሰዎች በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ ዜና ገድላቸው ከአባታቸው ከሕፃኑ ከቅዱስ ቂርቆስ ዕረፍት ጋር ጥር 15 ተጽፏል፡፡
የእጅግ የከበረ የቅዱስ ዱማቴዎስ ወንድም ቅዱስ መክሲሞስም ዕረፍቱ በዚሁ ዕለት ነው ነገር ግን ገድሉን በዚሁ ወር በ17 ከወንድሙ ታሪክ ጋር እንጽፈዋለን፡፡
የቅዱሳን ሰማዕታት ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!
 

No comments:

Post a Comment