Wednesday, January 30, 2019

ጥር 21-እረፍታ ለእግዚእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈሰ ቅዱስ ስም አሜን 
 ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it) 
ጥር 21-እረፍታ ለእግዚእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ


ከመጽሐፈ ተአምሯ፡- እመቤታችን ከዚህ ዓለም ታልፍ ዘንድ የጸለየችው ጸሎት ይህ ነው፡- ‹‹አቤቱ ቸር ጌታዬ ሆይ! ከዚህ ሑከትና ኀዘን ከመላበት ዓለም ደገኛውን መልአክህን ልከህ ወደኝ› ስትል በጸለየች ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ተገለጸላት፡፡ እንዲህም እያለች ስትጸልይ ሰማይ ተከፈተ፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ወደ እመቤታችን ወርዶ ‹ጸጋን የተመላሽ ሆይ! ደስ ይበልሽ› በማለት የደስታ መልእክት ነገራት፡፡ ዳግመኛም ‹‹እነሆ ጸሎትሽ ከአንቺ ከተወለደው ከእግዚአብሔር ዘንድ ደረሰ፡፡ እንደፈቃድሽ ከዚህ በኃላፊው ዓለም ወደ ዘላለም ሕይወት ትሄጂ ዘንድ ልመናሽ ተሰምቶልሻል›› አላት፡፡ 
እመቤታችንም ይህንን ነገር ከመልአኩ በሰማች ጊዜ ወደ በዓቷ ተመለሰችና ከዚያ የሚያገለግሏትን ደናግል ሰብስባ ‹አይሁድ ሁልጊዜ የልጄን መቃብር ይጠብቃሉና ስለዚህ የእኔን ከዚያ መገኘት አንድ ቀን ይገለጽላቸውና ከዚያ መግባት ይከለክሉኛል ብዬ ፈራሁ፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ራሳችሁን ችላላችሁ በሰላም ትኖራላችሁ እኔ ወደ ቤተልሔም እሄዳለሁና› አለቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ሁሉም በአንድነት ቃላቸውን አስተባብረው ‹ከአንቺ ጋር እንሄዳለን፡፡ ስለ አንቺ እናት አባታችንን፣ እኅት ወንድሞቻችንን ያለንን ሁሉ ትተን ተከትለንሻልና እነሆ አሁንም አንቺ ከሄድሽበት እኛም አብረንሽ እንሄዳለን፣ ባለ ዘመናችን ሁሉ ከአንቺ አንለይም› አሏት፡፡ እመቤታችንም በዚያን ጊዜ ይዛቸው ወደ ቤተልሔም ሄደች፣ በዚያም ተቀመጠች፡፡ እንዲህም ያለቻቸው ስለ አይሁድ ፍራቻ ሳይሆን ከዚህ ከኃላፊው ዓለም በሞት የመለየቷ ጊዜ ስለመድረሱ ነበር፡፡ እናንት የፍቅሯን ፈለግ የተከተላችሁና በፍቅሯ ቀምበር የተጠመዳችሁ የወንጌል ልጆች ሆይ እንግዲህ እመቤታችን በቤተልሔም ተቀምጣ ሳለች መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከዚህ ዓለም በሞት የምትለይበትን ጊዜ በክብር እንደነገራት አስተውሉ፡፡ ልመናዋ ክብሯ ለዘለዓለሙ በዕውነት ይደርብን፡፡ 
እረፍታ ለእግዚእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ፡- በ50 ዓ.ም ገደማ በዕለተ እሑድ ጌታችን እልፍ አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ ‹‹እናቴ ሆይ! ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ›› አላት፡፡ እመቤታችንም ‹‹ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑህን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኔ ተሸክሜ፣ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን?›› አለችው፡፡ ጌታችንም በሲኦል የሚሠቃዩ ነፍሳትን አሳያትና ‹‹እናቴ ሆይ! ሞትሽ ለእኒህ ቤዛ ይሆናቸዋል›› አላት፡፡ ለፍጥረታት ሁሉ እጅግ የምትራራ እመቤታችንም ‹‹እነዚህን ከማርክልኝስ ይሁን ልሙት›› አለችው፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ቅድስት ነፍስዋን ከክብርት ሥጋዋ ለይቶ በዝማሬ መላእክት አሳረጋት፡፡ ደቀመዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ ‹‹እመቤታችሁን ቅበሩ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ይዘዋት ወደ ጌታ ሰማኔ ወሰዷት፡፡ 
አበው ‹‹እመቤታችን ሆይ! ሞትሽ ሠርግን ይመስላል›› እንዳሉት የእመቤታችን እረፍት እንባ መራጨት፣ ጠጉር መንጨት፣ ደረት መድቃት እንዳለበት የሰው ሞት አልነበረም፡፡ ይልቁንም አንደ ሠርግ ቤት ቅዱሳን መላእክት በውዳሴ፤ በማህሌት፣ በዝማሬ፣ በምስጋና ወደ ሰማይ ሸኟት እንጂ፡፡ ቅዱስ ያሬድም ‹‹እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ አለች፤ በዚያም ከልጇ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች›› በማለት ዘምሯል፡፡ የእመቤታችን ሥጋዋ ከጌቴሴማኔ ወደ ገነት መፍለሱን አስቀድሞ አባቷ ቅዱስ ዳዊት በትንቢት ሲናገር ‹‹አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት›› በማለት ተንብዮዋል፡፡ መዝ 131፡8፡፡ ይህም ‹‹ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ›› ሲል ነው፡፡ ይህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚህ ዓለም ከኖረች በኋላ ነብሷ ከሥጋዋ ተለይቶ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ መነሣቷን የሚያመለክት ነው፡፡ ‹‹ታቦት›› ያላትም ማደሪያው ስለሆነች ነው፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን በምሳሌ ሲናገር «ወደጄ ሆይ ተነሺ፣ ውበቴ ሆይ ነይ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ፣ ዝናቡም አልፎ ሄደ፣ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፣ የዜማም ጊዜ ደረሰ፣ የቁርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጎመራ ወይኖችም አበቡ መዐዛቸውንም ሰጡ ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነይ» አለ፡፡ መኃ 2፡10-14፡፡ ይህ ኃይለ ቃል ሲተረጎም በውስጡ ብዙ ምሥጢራዊ ነገሮችን ያያዘ ነው፡፡ «በክረምትና በዝናብ» የተመሰሉ የእመቤታችን መከራዎች ናቸው፡፡ የመከራሽ ጊዜ አልፏል ሲላት «አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ» ማለቱ ከልጅሽ እግር ሥር ቁጭ ብለው ተምረው ወንጌልን የተቀበሉ ሐዋርያት አንቺን በእናትነት የተረከቡ የሐዋርያት ድምፅ ወይም ስብከት በምድር ሁሉ መሰማቱን ያጠይቃል፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን «የዜማ ጊዜ ደረሰ» ያለው የመከሩን ወቅት ነው፡፡ መከር የፍሬ ጊዜ እንደመኖኑ ሐዋርያት የዘሩት ዘር ማለትም ስብከታቸው ፍሬ አፈራና ክርስቲያኖች በዙ፤ «በለሱ ጎመራ» በጎ ምግባር የሌላቸው ሰዎች በሐዋርያት ስብከት ተምረው ምግባር መሥራት ጀመሩ፤ «ወይኖች አብበዋል መዐዛቸውንም ሰጥተዋል» በመላው ዓለም ያሉ ምዕመናን በሃይማኖት ማበብ፣ መዐዛ ምግባራቸውን ማቅረብ መስጠት ጀመሩ በማለት ሊቃውንት አባቶች ምሥጢሩን ያብራሩታል፡፡ በዚህ ትርጓሜ ‹‹ወደጄ ሆይ! ተነሽ›› እያለ የሚናገረው ተወዳጁ ልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ድንግል ማርያምን በመለኮታዊ ስልጣኑ ከሙታን ለይቶ ማስነሣቱን ሲያስረዳን ነው፡፡ 
ስለዚህ ድንቅ ምስጢር ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት›› (መዝ 131፡8) ብሎ የተናገረው ትንቢት በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ፣ በንጽሐ ልቡና የጸናች የእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕረፍትና ትንሳኤ እንዲሁም ፍልሰት (ዕርገት) ከማሳየቱም በተጨማሪ የአምላክ እናት በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት በክብር መኖሯንም በግልጽ ያስረዳል ያስገነዝባል፡፡ ‹‹በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች›› (መዝ 44፡9) የሚለውን የቅዱስ ዳዊት ትንቢታዊ ቃል ሊቃውንት አባቶች በተለይም የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መተርጉማን ‹‹ንግሥተ ሰማይ ወምድር ድንግል ማርያም በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ፣ በንጽሐ ልቡና›› ተሸልማና አጊጣ በሰማያዊው ዓለም በልጇ መንግሥት በክብር መኖሯን የሚያመለክት መሆኑን አስረግጠው አስረድተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ሰማያዊው አባታቸውን እግዚአብሔርን ‹‹አቡነ ዘበሰማያት፤ በሰማያት የምትኖር አባታችን›› እያሉ ዘወትር ሲያመሰግኑ፤ በአንጻሩ ደግሞ መንፈሳዊት እናታቸውን ድንግል ማርያምን ‹‹በሰላመ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ ኦ እግዝእትየ ማርያም ሰላም ለኪ፤ እመቤቴ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እልሻለሁ›› እያሉ ዘወትር ያከብሯታል ያመሰግኗታልም፡፡ ሉቃ 1፡28፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ዘወትር በምንጸልየው የእሑድ የእመቤታችን ውዳሴ ላይ ‹‹ምልዕተ ጸጋ፣ ምልዕተ ክብር፣ ምልዕተ ውዳሴ የሆንሽ ድንግል ሆይ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ትለምኝልኝ ዘንድ ለአንቺ ይገባል፡፡ አንቺ ከሊቃነ ጳጳሳት ትበልጫለሽ፤ ከቅዱሳን ነቢያት፣ ከቅዱሳን ሐዋርያት ከሰብዓ አርድእትም ትበልጫለሽ፡፡ ዳግመኛም ከሱራፌልና ከኪሩቤል ይልቅ የሚበልጥ የመወደድ የመፈራት ግርማ አለሽ፡፡ በእውነት የባሕርያችን መመኪያ አንቺ ነሽ፡፡ ለሰውነታችንም ሕይወትን፣ ድኅነትን የምትለምኚና የምታማልጅን አንቺ ነሽ›› በማለት የእመቤታችን ልዕልናዋን የጸጋዋን ፍጹምነትና የክብሯን ታላቅነት በአጽንኦት ገልጾ መስክሯል፡፡
እመቤታችን በጥር ሃያ አንድ ቀን በታላቅ ክብር ካረፈች በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት በፈቃደ እግዚአብሔር ከያሉበት መጥተው በኢየሩሳሌም ተሰብስበው የፈጣሪያችን እናት ድንግል ማርያምን በጸሎትና በማዕጠንት አክብረው ገንዘው ጥልቅ በሆነ ኃዘን ሊቀብሯት ወደ ጌቴሰማኒ ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና «ቀድሞ ልጇ ሞቶ ተቀብሮ ሳለ ተነሣ እያሉ ሕዝቡን አስኮበለሉ አሁን ደግሞ እናቱን ሞታ ተነሣች እያሉ እንዳያውኩ ሥጋዋን እናቃጥል» በሚል የክፋት ምክር ተነሳሱ፡፡ በተለይም ደግሞ በእመቤታችን ላይ በክፋትና በተንኮል ከተነሳሱት ከእኒህ አይሁድ መካከል ታውፋንያ የተባለው አይሁዳዊ
አማናዊት ታቦተ እግዚአብሔር የሆነችው የድንግል ማርያም ቅዱስ ሥጋ ያረፈበትን አልጋ ለመያዝ እጁን በድፍረት ዘረጋ፡፡ በዚህን ጊዜ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን (2ኛ ሳሙ 6፡6፤ 1ኛ ዜና 13፡7-10) ላይ የአሚናዳብ ልጅ ዖዛ እጁን በታቦተ ጽዮን ላይ በድፍረት በመዘርጋቱ ምክንያት ተቆጥቶ እንደቀጣው ታውፋንያንም ሰማያዊው መልአክ ሰይፍ እጆቹን ቀጣው ቆረጠው፡፡ «እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን የሚዘረጋ ንጹሕ አይሆንም (1ኛ ሳሙ 26፡9) እንደተባለ እጆቹም አልጋው ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ 
ታውፋንያም ስለተቆረጡት እጆቹ ወደ እመቤታችን አምኖ ወደ እርሷ ቢጮህ ቢማጸናት፤ በቅዱስ ጴጥሮስ አማካይኝነት እጆቹን እንደ ቀድሞ ሆነው ድነውለታል፡፡ በጌታችን ትእዛዝ መልአኩ የእመቤታችንን ቅዱስ ሥጋ ከወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ጋር በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር በክብር አኑሮታል፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት ዮሐንስ ከተመለሰ በኋላ ‹‹እመቤታችን እንደምን አለች?›› አሉት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም «ከገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች» አላቸው፡፡ እነርሱም ዮሐንስ ዐይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ፡፡ ጥር አርፋ በነሐሴ ወር ሁለት ሱባኤ ይዘው ሲጨርሱ በነሐሴ 14 መልአኩ ቅዱስ ሥጋዋን ከገነት አምጥቶ ሰጥቷቸው በጸሎትና በምሕላ ቀብረዋታል፡፡ በዚህ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ቶማስ አልነበረም፡፡ በሦስተኛው ቀን እንደ ልጇ ተነሥታ ስታርግ፣ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ ያገኛታል፡፡ በዚህ ጊዜ ትንሣኤዋን ሌሎች ሐዋርያት አይተው፣ ለእርሱ የቀረበት መስሎት አዝኖ ‹‹በፊት የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፤ አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ከደመናው ለመውደቅ ተመኘ፡፡ በዚህ ጊዜ እመቤታችን ቶማስን አጽናናችው፡፡ ከእርሱ በቀር ትንሣኤዋን ሌላ እንዳላየ ነገራው ለምስክር እንዲሆነው ሰበኗን/መግነዝ ሰጥታው ዐረገች፡፡ 
ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ሙስና መቃብር ሳያገኘው መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሥልጣኑ እሑድ በመንፈቀ ሌሊት እንደተነሣ ሁሉ ክብርት እናቱ እመቤታችም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን ማኅደረ መለኮት ናትና ሙስና መቃብር ሳያገኛት መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል የልጇ ሥልጣን ኃይል ሆኗት መነሣቷን ትንሣኤዋ ‹‹እንደ ልጅዋ ትንሣኤ›› ነው ተብሎ ሲከበርላት ይኖራል፡፡ 
ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያት ወዳሉበት ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ እመቤታችንን እኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት፡፡ እርሱም ምስጢሩን ደብቆ ‹‹ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር›› አላቸው፡፡ ሐዋርያትም ‹‹አንተ ተጠራጣሪ ነህ›› ብለው መቃብሩን ሊያሳዩት ሲከፍቱ አጧት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹እመቤታችን ተነሥታ አርጋለች›› ብሎ ሁኔታውን ተረከላቸው፡፡ ‹‹ለምስክር ይሁንህ›› ብላ የሰጠቸውንም ሰበኗን አሳያቸው፡፡ ሐዋርያትም ይህን አይተው ትንሣኤዋን አመኑ። ሰበኗን ቆራርጠው ለበረከት ተከፋፍለው ወደየሃገረ ስብከታቸው ተመልሰዋል፡፡ ዛሬም በመጾር መስቀልና በካህናት እጅ መስቀላቸው ላይ የሚያስሯት ‹‹መሀረብ›› የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፡፡ በዓመቱም ሐዋርያት ‹‹ቶማስ ትንሣኤሽን አይቶ እንዴት እኛ ይቅርብን!›› ብለው ከነሐሴ አንድ ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በነሐሴ 16 ቀንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅዱሳን ሐዋርያትን ወደ ሰማይ አሳርጎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቅዳሴ ቀድሶ አቁርቧቸዋል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም የመቤታችንን ትንሣኤና ዕርገቷን በዓይናቸው አይተውና በሚገባ ተረድተው ዓለምን ዙረው አስተምረዋል፡፡ 
+ + + 
ከመጽሐፈ ስንክሳር፡- እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ከመሞቷ በፊት በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መቃብሩ ቦታ ትጸልይ ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስም ለእመቤታችን ከዚህ ዓለም እንደምትለይ ነገራት፡፡ ጌታችንም በደብረ ዘይት ላሉ ደናግላን ነግሯቸዋልና ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በፍጥነት መጡ፡፡ እርሷም መንፈስ ቅዱስ የነገራትን ለእነርሱ ነገረቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ እመቤታችን እንዲህ ብላ ጸለየች፡- ‹‹ልጄ ወዳጄ፣ ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ልመናየን ተቀብለህ ደቀ መዝሙርህን ዮሐንስን በዚህች ሰዓት አምጣው፤ እንዲሁም ሕያዋን የሆኑትን ሐዋርያትን ሁሉንም ነፍሶቻቸውን የለየሃቸውንም ሁሉ ወደ እኔ አምጣቸው፤ አንተ የሕያዋን አምላክ ነህና ለአንተም ምስጋና ይሁን አሜን›› አለች፡፡ 
በዚያን ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ትዕዛዝ ቅዱስ ዮሐንስን ደመና ተሸክማ ወደ እመቤታችን አደረሰችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በፊቷ ሰገደላትና እንዲህ አላት፡- ‹‹ሰላምታ ይገባሻል፣ ጌታችንን ፈጣሪያችንን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለድሽው ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ ከዚህ ዓለም ተለይተሽ በክብር በምስጋና ወደ ዘለዓለም ሕይወት ትሄጃለሽና፡፡ ይህም ስሙ ክቡር ምስጉን የሆነ ጌታችንና ፈጣሪያችን ድንቅ ድንቅ ተአምራቶችን በአንቺ ላይ ከገለጠ በኋላ ነው›› አላት፡፡ እመቤታችንም ይህን በሰማች ጊዜ እጅግ ደስ አላት እግዚአብሔርንምእንዲህ ብላ አመሰገነችው፡- ‹‹ፈጣሪዬ ጌታዬ ላንተ ምስጋና ይሁን፣ የለመንኩህን ሰጥተኸኛልና፡፡ አሁንም ነብሴን ተቀብለው ወደ ሰማይ ወደ አንተ ሊይሳርጓት ከሚመጡ ቅዱሳን መላእክቶችህ ጋር በመምጣትህ የምለምንህን ሁሉ ስጠኝ›› አለችው፡፡ በዚያም ጊዜ ከሰማይ እንዲህ የሚል ቃል መጣ፡- ‹‹እነሆ አሁን መላእክት ይደርሳሉ፡፡ ሐዋርያትም ሁሉ ከምድር ዳርቻ በደመና ተጭነው ለሰማይና ለምድር ጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ወደሆነች ወደ ቅድስት ድንግል ይደርሳሉ፡፡ ወዲያውም ሁሉም ሐዋርያት የሞቱት ከመቃብራቸው ተነሥተው በሕይወት ያሉትም ሁሉም ወደ እመቤታችን ደርሰው ሰገዱላት፡፡ ‹‹አምላካችን ከአንቺ የተወለደ ጸጋን የተመላሽ ሆይ! ደስ ይበልሽ፣ እርሱ ከዚህ ዓለም ለይቶ ቃል ኪዳን እንደሰጠሽ በክብር በምስጋና ከእርሱ ጋር ያሳርግሻልና›› አሏት፡፡ 
በዚያንም ጊዜ እመቤታችን በዐልጋዋ ላይ ተቀመጠችና ሐዋርያትን እንዲህ አለቻቸው፡- ፈጣሪዬ ፈጣሪያችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እንደሚመጣ እናንተንም እንዳየኋችሁ እንደማየው አሁን ዐወቅሁ፡፡ ከዚህ ከሥጋዬ ወጥቼ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እሄዳለሁ፡፡ ነገር ግን ትነግሩኝ ዘንድ እሻለሁ፣ እኔ ከዚህ ዓለም እንደምለይ ከወዴት ዐወቃችሁ?›› ብላ የጠቀቻቸው፡፡ በመጀመሪያ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚያም ሁሉም ሐዋርያት ‹‹ወደ አንቺ እንመጣ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አዘዘን፣ በደመና ላይም በተጫን ጊዜ እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥነን ደረስን›› አሏት፡፡ 
እመቤታችንም ይህን ነገር ከሐዋርያት በሰማች ጊዜ ድምጿን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፡- ‹‹ጌታዬና ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ክቡር ምስጉን የሆነ ስምህን ፈጽሜ አመሰግናለሁ፣ የእኔን የአገልጋይህን መከራ ተመልክተህ ድንቅ ኃይልን አድርገህልኛልና ከእንግዲህ ወዲያ ትውልድ ሁሉ ያከብሩኛል ያመሰግኑኛል›› አለች፡፡ ጸሎቷንም ስትጨርስ ሐዋርያትን ‹‹ዕጣን አምጥታችሁ በማጠን የጌታዬን የኢየሱስ ክርስቶስን ስሙን ጥሩት›› አለቻቸው፡፡ እነሱም እንዳዘዘቻቸው አደረጉ፡፡ በዚያም ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን እልፍ አእላፍ ቅዱሳን መላእክቱ አጅበው እያመሰገኑት መጣና እመቤታችንን አረጋጋት፡፡ ያዘጋጀላትንም ተድላ ደስታ ነገራት፡፡ በዚያም ጊዜ ድንቆቸ የሆኑ ተአምራት ተደረጉ፡፡ ዓይነ ሥውራን ማየት ቻሉ፣ ደንቆሮች መስማት ቻሉ፣ ዲዳዎች ተናገሩ፣ ለምጻሞች ነጹ፣ ሐንካሶች መሄድ ቻሉ፣ ደዌ ያለበትም ሁሉ ዳነ፡፡ የብርሃን እናቱ ወላዲተ አምላክ እመቤታችን ወደ አለችበት ቤት በቀረቡ ጊዜ ከደዌአቸው ሁሉ ይፈወሳሉና፡፡ 
ከዚህም በኋላ እመቤታችን ተወዳጅ ልጇን ‹‹በአየር ውስጥ ተበትነው ከሚኖሩ ከሚያስነግጡ ግሩማን መላእክት የተነሣ ከእሳት ባሕርም የተነሣ እፈራለሁ›› ባለችው ጊዜ እርሱም ‹‹እናቴ ሆይ ከእነርሱ ለማንም በአንቺ ላይ ሥልጣን የለውም›› አላት፡፡ ከሥጋዋም የምትለይበት ጊዜ ሲደርስ ሐዋርያትንና ደናግል ትባርካቸው ዘንድ እያለቀሱ ለመኗት፡፡ እመቤታችንም እጇን በላያቸው ዘርግታ ባረከቻቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ጌታችን ቅድስት ንጽሕት ነፍሷን ከሥጋዋ ለይቶ በመለኮታዊ እጆቹ ይዞ በብርሃን ልብስ አጎናጽፎ ወደ ከፍተኛ መኖሪያ ከእርሱ ጋር አሳረጋት። ሥጋዋን ግን እንደሚገባ ገንዘው፤ ወደ ጌቴ ሰማኒ ተሸክመው እንዲወስዷ ሐዋርያትን አዘዛቸው፡፡ ነፍሷ ከሥጋዋ ከመውጣቷ በፊት በሰው አንደበት ይህ ነው ተብሎ የማይነገር ብርሃን እያየች ነበር፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችንም ‹‹እንግዲህ ሥጋሽን ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት አፈልሳለሁ፡፡ ዳግመኛም ሥጋሽን ከነፍሽ ጋር አዋሕጄ አስነሥቼ መላእክት በፊትሽ ሆነው በሚያመሰግኑበት አምሳያ በሌለው ተድላ ደስታ ባለበት መኖሪያ አኖርሻለሁ›› አላት፡፡ 
እመቤታችንም እንዲህ አለች፡- ‹‹አቤቱ በረቀቀ ጥበብህ ይህን ሁሉ የሠራህ አመሰግንሃለሁ፤ ሁለተኛም ልመናየን ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ በስሜ ወደ አንተ የሚለምነውን ሁሉ፤ ልመናውን ተቀበለው በመከራም ውስጥ ሁኖ ስሜን ጠርቶ ወደ አንተ የሚለምነውን ከመከራም ሁሉ አድነው፤ በሰማይም በምድርም በሥራው ላይ ሁሉ አንተ ከሃሊ ነህና መታሰቢያየን በውስጧ የሚያደርጉባትን ቦታ ሁሉ ባርክ፣ በእኔ ስም የሚያቀርቡትን የሁሉንም መሥዋዕታቸውን ተቀበል›› አለችው፡፡ ጌታችንም እንዲህ ብሎ መለሰላት፡- ‹‹የለመንሽኝን ሁሉ አደርግልሻለሁ፤ ደስ ይበልሽ፣ ከእኔ ከአባቴ ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ጸጋ ክብር ባለሟልነት ተሰጥቶሻልና ስምሽንም ጠርቶ የሚለምን ሁሉ በዚህ ዓለምም በወዲያኛው ዓለምም ከቶ አይጠፋም›› አላት፡፡ እመቤታችንም በታላቅ ክብር ካረፈች በኋላ ጌታችን እንዳዘዘ ወደ ጌቴ ሰማኒ ሊወስዷት ሐዋርይት ገንዘው ተሸከሟት፡፡ አይሁድም በሰሙ ጊዜ ሥጋዋን ሊይቃጥሉ ወጡ፡፡ ከእርሳቸውም አንዱ ከምድር ይጥላት ዘንድ የእመቤታችንን አልጋዋን ያዘ፡፡ ያን ጊዜም ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ መልአክ እጆቹን በእሳት ሰይፍ ቀጣውና እጆቹ በአልጋው ላይ ጠንጠለጠሉ፡፡ ያን ጊዜ በጌታችን አምኖ ወደ እመቤታችን እያለቀሰ እንዲህ ብሎ ለመነ፡- ‹‹የእውነተኛ አምላክ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እናት ሆይ! አንቺ በእውነት ድንግል ይሆንሽ በእኔ ላይ ይቅርታ ታደርጊ ዘንድ አለምንሻለሁ፡፡›› በሐዋርይትም ልመና እጆቹ ተመልሰው እንደቀድሞው ደኅነኞች ሆኑ፡፡ 
ሐዋርያትም እመቤታችንን በቀብሯት ጊዜ ከዚያ ሶስት ቀን ኖሩ፣ ዕረፍቷም የሆነው እሑድ ቀን ጥር ወር በ21 ቀን ነበረ፡፡ ጌታችንም ብርሃናውያን መላእክትን ላከ፣ እነርሱም ሥጋዋን ከመቃብር ወስደው በገነት ውስጥ በዕፀ ሕይወት ሥር አኖሯት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ግን ያን ጊዜ አልነበረም በደመና ላይ ተጭኖ እርሱ ሲመጣ መላእክት ሲያሳርጓት እመቤታችንን አገኟት፡፡ ቅዱሳን መላእክትም ‹‹ለአምላክ እናት ለእመቤታችን ድንግል ማርይም ና እጅ ንሣ›› አሉት፡፡ እርሱም ሰገደላትና ተሳለማት ከእርሷም ተባረከ፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ሐዋርያት ደረሰ፡፡ እነርሱም እመቤታችንን ማርያምን እንዳረፈችና እንደ ቀበሯት ነገሩት፡፡ ቶማስም ‹‹ሥጋዋን እስከማይ አላምንም›› አላቸው፡፡ ሥጋውንም ያሳዩት ዘንድ ወደ መቃብሯት ባደረሱት ጊዜ በመቃብሩ ውስጥ ሥጋዋን አላገኙም፤ እነርሱም ደንግጠው እያደነቁ ሳለ ያን ጊዜ ቶማስ ከመላእክት ጋር ወደ ሰማይ ስታርግ እመቤታችን እንዳገኛት ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ የእመቤታችንን ዕርገቷን ስላላዩ እጅግ አዘኑ፡፡ ሥጋዋን በምድር ውስጥ ይተው ዘንድ እንዳልወደደ መንፈስ ቅዱስ አስገነዘባቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አንድ ጊዜ ደግሞ እርሷን ያሳያቸው ዘንድ እንዳለው ጌታችን ቃል ኪዳን በማድረግ ተስፋ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም በተስፋ እስከ ነሐሴ 16 በተስፋ ኖሩ፡፡
አምላክን የወለደች ክብርት እመቤታችን ፍቅሯን ጣዕሟን ታሳድርብን!
+ + + 
ዳግመኛም በዚህች ዕለት ጥር 21 
+ እመቤታችን ተገልጣለት ‹‹ዕረፍትህ በዕረፍቴ ቀን ነውና ተዘጋጅ›› ብላ የነገረችው የኑሲሱ አቡነ ጎርጎሪዮስ ዕረፍቱ ነው፡፡ 
+ አርሲ ፈንታሌ ተራራ ላይ ሠሪቲ ለምትባል ጠንቋይ እየተላላኩ ሕዝቡን የሚያስቱና የሚያሰቃዩ አራት መቶ ሰባ ሺህ ሦስት መቶ አጋንንትን በጸሎታቸው እሳት ከሰማይ አውርደው ያቃጠሏቸው የመሐግሉ አቡነ ቀውስጦስ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+ የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ ታላቅ ወንድም የሆኑት ዋሸራን ገዳምን የመሠረቱት በሱባኤ ስለ ዋሸራ ሕዝብ ታላቅ ምሥጢር የተነገራቸው አቡነ ተስፋ ኢየሱስ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+ በሐይቅ ሲያጥኑ የማዕጠንታቸው ሽታ እስከ ጣና ቂርቆስ ድረስ ይሸት ስለነበር ቅዱሳን ሲሸታቸው አባ ኤልያስ ዛሬ ቅዳሴ ገባ ይሏቸው የነበሩትና በሞት ማረፋቸውን የሚያጥንባት ጽንሐቸው አፍ አውጥታ የተናገረችላቸው የመርጦው አቡነ ኤልያስም ዕረፍታቸው ነው፡፡ 
+ የሮሜው አገር ንጉሥ ልጅ የሆነችው ቅድስት ኢላርያ ዕረፍቷ ነው፡፡ 
+ የደብረ ጽላልሽዋ ቅድስት ማርያም ክብራም ዕረፍቷ ነው፡፡ 
+ ነቢዩ ኤርምያስ መታሰቢያ በዓሉ ነው፡፡ 
+ በሰማዕትነት ያረፈ በዋሻ የሚኖር ቅዱስ ኒቆላዎስ መታሰቢያ በዓሉ መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሰዋል፡፡ 
+ በመናፍቁ ንጉሥ በመርቅያን ዘመን መኮንኑ ጳውሎስና ቀሲስ ሲላስ ምስክር ሆነው በዚህች ዕለት ዐርፈዋል፡፡ እነርሱም በእመቤታችን የዕረፍቷ በዓል ዕለት በጌቴሴማኒ ከምእመናን ጋር ሆነው ተሰብስበው ሳሉ ከሃዲው መኮንን መጥቶ በዚያ ካሉት አንድም ሰው ሳያስቀር የገደላቸው መሆኑን ስንክሳሩ በአጭሩ ይጠቅሳቸዋል፡፡ 
አቡነ ተስፋ ኢየሱስ ዘጎጃም፡- የትውልድ ሀገራቸው ጎጃም ሲሆን የታላቁ ጻድቅ የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ ዘግሽ ዓባይ ታላቅ ወንድም ናቸው፡፡ እንደ ወንድማቸው የተወለዱት በመልአክ ብስራት ነው፡፡ አቡነ ተስፋ ኢየሱስን መልአክ እየመራ ወስዶ ጣና ሐይቅ ገዳም አደረሳቸውና በዚያ የቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ሥርዓቷን ሁሉ በሚገባ ተማሩ፡፡ የዋሸራን ገዳም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ከመሠረቱት 300 ቅዱሳን መነኮሳት ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ በ300ው መነኮሳትም ተመርጠው የገዳሟ ባራኪ ሆነው ተሹመው አገልግለዋል፡፡ ሱባኤ ገብተው ስለ ዋሸራ ገዳምና ስለ አካባቢው ሕዝብ ምሥጢር የተገለጠላቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ገዳሟ ፈለፈ ሊቃውንት እንደምትሆን ተገልጦላቸዋል፡፡ ደግመው ሱባኤ ቢገቡ ገዳሟ በስተኋላ እንደምትቀዘቅዝ ተገለጠላቸው፡፡ ለ3ኛም ጊዜ ሱባኤ ቢገቡ ገዳሟ እስከ ዕለተ ምዕዓት ጸንታ እንደምትኖር ተገልጦላቸው በዚህም ደስ ተሰኝተዋል፡፡ ዋሸራ ገዳም በመጀመሪያ በባሐር የተከበበች ብትሆንም አቡነ ተስፋ ኢየሱስ ባሕሩን ቢባርኩት ተስተካክሎ እንደ ጸበል ሆኖላቸዋል፡፡ እመቤታችንም ዕለት ዕለት እየተገለጠችላቸው ትባርካቸው ነበር፡፡ ጻድቁ በተጋድሎ ብዙ ካገለገሉና ከጌታችን ታላቅ ቃል ኪዳን ከተቀበሉ በኋላ ጥር 21 ቀን ዐርፈው በዚያው ተቀብረዋል፡፡ 
ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን፡፡ 
+ + + 
አቡነ ጎርጎሪዮስ ዘኑሲስ፡- ይኸውም የቅዱስ ባስልዮስ ወንድም ነው፡፡ ሀገሩ ቂሳርያ ሲሆን የተሾመው ኑሲስ በተባለች ደሴት ላይ ነው፡፡ መናፍቁ ሰባልዮስ ‹‹አንድ ገጽ›› በማለቱ ሌሎቹ መናፍቃንም መቅዶንዮስና አቡሊናርዮስ ‹‹መንፈስ ቅዱስ ህጹፅ›› እና ‹ወልድ ሥጋ እንጂ ነፍስ አልነሳም› በማለታቸው በ381 ዓ.ም 150ው ሊቃውንት በቍስጥንጥንያ ተሰብስበው መናፍቃኑን ተከራክረው እረተው ሃይማኖትን ሲያጸኑ ከጢሞቲዎስ ጋር አንድ ላይ የጉባኤው አፈ ጉባዔ የነበረው ሊቁ ጎርጎሪዮስ ዘኑሲስ ነበር፡፡ እርሱም በጉባኤው ላይ እነ መቅዶንዮስንና አቡሊናርዮስን ተከራክሮ በመርታት መልስ አሳጥቷቸዋል፡፡ ሃይማኖትንም አጽንቷል፡፡ 
ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ቅዳሴ ሲቀድስ ጌታችን በርግብ አምሳል ሲወርድ ያየው ስለነበር ዘወትር እያለቀሰ ይቀድሳል፡፡ ከተጋድሎውም ጽናት የተነሣ ታማሚ ሆኖ ነበር፡፡ በኤጲስ ቆጶስነት ተሹሞ 33 ዓመት ኖሯል፡፡ ከተጋድሎውም ብዛት ድካም አጋጥሞት ነበርና አንድ ቀን ወንድሙ ባስልዮስ ሊጠይቀው መጣ፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስም እንደልማዱ ሊቀድስ ወደ መሠዊያው በወጣ ጊዜ እመቤታችን ተገለጠችለትና ‹‹ዕረፍትህ በዕረፍቴ ቀን ነውና ዛሬ ወደእኔ ትመጣለህ›› አለችው፡፡ ጎርጎርዮስም የቁርባኑን ቅዳሴ ሲጨርስ ሕዝቡን በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ ለመምከር ተነሣ ነገር ግን ከድካምና ሕመም ብዛት ሰውነቱ መቆም ስላልቻለ ወንደሙን ባስልዮስን ‹‹ዛሬ አንተ አስተምራቸው›› አለው፡፡ ወዲያውም እንደሚያንቀላፋ ሆነና ዐረፍ አለ፡፡ በቀሰቀሱትም ጊዜ በሞት ዐርፎ አገኙት፡፡ ይኸውን ጥር 21 ቀን ነው፡፡ በስሙ የተጠራ አንድ ቅዳሴና ገድለ ዜና አለው፡፡ በትንቢት ተናጋሪነቱ፣ በደራሲነቱና በመምህርነቱ መጽሐፍ ‹‹ጎርጎሪዮስ ዐቃቤ ሥራይ ቁስለ መድኃኒት ዘነፍስ›› ይለዋል፡፡ ከሃዲው ንጉሥ ዑልያኖስ ወንድማማቾቹን ባስልዮስንና ጎርጎርዮስን በጸሎታቸው ሰዓት ደርሶባቸው እነርሱን ገድሎ መሥዋዕታቸውን ሊበላባቸው ሲመጣባቸው የቅዱስ መርቆሬዎስን ሥዕል በጸሎት ቢማጸኑ ሥዕሉ በገዘፈ ሥጋ ሆኖ በተአምራት ዑልያኖስን በጦር ወግቶ ገድሎላቸዋል፡፡
የቅዱስ ጎርጎሪዎስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን፡፡ 
+ + + 
አቡነ ኤልያስ ዘመርጦ፡- ትውልድ ሀገራቸው ጎጃም መርጡ ለማርያም ነው፡፡ አባታቸው መሠረተ ጽዮን መርጡ ለማርያምን በሹመት ብዙ ዘመን አገልግለዋል፡፡ አቡነ ኤልያስ 7 ዓመት ሲሆናቸው ለታላቁ ጻድቅ መቋሚያቸው እንደ ሰው አፍ አውጥታ ለምትናገረው ለአቡነ ተክል አልፋ ሰጧቸው፡፡ አቡነ ተክል አልፋም ብሉያቱን፣ ሐዲሳቱን፣ ቀኖናውንና ዶግማውን ሁሉ በሥርዓት ካስተማሯቸው በኋላ አመንኩሰዋቸዋል፡፡ ጻድቁ ወደ ሐይቅ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ሄደው 14 ዓመት በገዳሙ አገልግለዋል፡፡ 
አቡነ ኤልያስ በሚያጥኑበት ጊዜ የዕጣኑ ሽታ እስከ ጣና ቂርቆስ ድረስ ይሸት ነበርና ቅዱሳን ሲሸታቸው ‹‹ዛሬ አባ ኤልያስ ቅዳሴ ገባ›› ይላሉ፡፡ ጻድቁ ባረፉ ጊዜ በሞት መለየታቸውን ለመነኮሳቱ የተናገረችው ያጥኑባት የነበረችው ጽንሐ ናት፡፡ እንደ ሰው አፍ አውጥታ ‹‹አባታችን ዐረፉ›› ብላ ተናግራለች፡፡ መነኮሳቱም ወስደው በተድባበ ማርያም ቀብረዋቸዋል፡፡ በስማቸው የተቀረጹ ታቦታት በተደባበ ማርያም፣ በቸር ተከል ማርያምና በየህላ ቅዱስ ሚካኤል እንደሚገኝ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ጽፈዋል፡፡
የአቡነ ኤልያስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን፡፡
+ + + 
ቅድስት ማርያም ክብራ ዘጽላልሽ፡- ትውልዷ ሸዋ ደብረ ጽላልሽ ሲሆን በወቅቱ የትልቅ ባለስልጣን የመስፍን ልጅ ነበረች፡፡ ወደ ደብረ በግዕ ገዳም ገብታ መነኮሳቱን በብዙ ድካም ስታገለግል ከኖረች በኋላ በአቡነ ሕፃን ሞዐ እጅ መንኩሳለች፡፡ 
አቡነ ሕፃን ሞዐ ማለት የደብረ በግዕህ ገዳምን የመሠረቱት ታላቅ አባት ሲሆኑ እንደበሬ በመታረስ ሰማዕትነት የተቀበሉ ናቸው፡፡ ጻድቁን ከአንድ በሬ ጋር ጠምደው ቀኑን ሙሉ ሲያርሷቸው በድካም ሆነው በኋይል የተነፈሱበት ቦታ ላይ ምድሪቱ ዛሬም ድረስ እንደእርሳቸው ስትተነፍስ የእስትንፋሷ ድምጹና ሙቀቱ ይሰማል፡፡ ለአስም ሕመም መድኃኒት ነው፡፡ ቦታውም ከደብረ ብርሃን በእግር የሁለት ሰዓት ተኩል መንገድ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን የጻድቁ ቤተ ክርስቲያኑ ከወይንዬ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አጠገብ ይገኛል፡፡ 
ቅድስት ማርያም ክብራ በጻድቁ ሕፃን ሞዐ እጅ ከመነኮሰች በኋላ ወደ አቡነ ዜና ማርቆስ ገዳም ገብታ በታላቅ ተጋድሎ ስትኖር ሰይጣን ብዙ ጊዜ በሰው አምሳል እየተገለጠ በፈተና ሊጥላት ይሞክር ነበር፡፡ የእግዚአብሔርም መልአክ እየተገለጠ ያበረታት ነበር፡፡ እርሷም በበትረ መስቀሏ ሰይጣንን እያሳደደች ታባርረው ነበር፡፡ ረድኤት በረከቷ ይደርብን በጸሎቷ ይማረን፡፡
+ + + 
ቅድስት ኢላርያ፡- ይኽችም ቅድስት የሮሜው አገር ንጉሥ የዘይኑን ልጅ ናት፡፡ እርሱም እግዚአብሔርን የሚወድ ሃይማኖቱ የቀና ነው፡፡ ልጁ ቅድስት ኢላርያንም ፈሪሃ እግዚአብሔርንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እያስተማረ አሳደጋት፡፡ ከሁለት ሴቶቹ ለጆቹ በቀር ወንድ ልጅ የለውም ነበር፡፡ 
ቅድስት ኢላርያም ዕድሜዋ ከፍ ሲል ዓለምን ፍጹም ንቃለችና የምንኩስናን ልብስ የመላእክትንም አስኬማ ትለብስ ዘንድ ወደደች፡፡ ከቤተ መንግሥትም ተደብቃ ወጥታ የወንድ ልብስ በመልበስ ወደ ግብጽ አገር ሄደች፡፡ ወደ አስቄጥስ ገዳምም ገብታ ስሙ አባ ባውሚን የሚባል ፍጹም ሽማግሌ ጻድቅ ሰውን አግኝታ የምንኩስና ሀሳቧን ነገረችው፡፡ እርሷም ሴት እንደሆነች ስትነግረው ምሥጢሯን ጠብቆ ለብቻዋ ከዋሻ ውስጥ አስገባት፡፡ እየጎበኛትም ልትሠራው የሚገባትን ሁሉ ያስተምራት ነበር፡፡ እንዲህም ሆና በዚያ ዋሻ ውስጥ 12 ዓመት ኖረች፡፡ ቅድስት ኢላርያ ፂም ስለሌላት ለአረጋውያን መነኮሳት ጃንደረባ ትመስላቸው ነበር፡፡ በወንድ ስም አጠራርም አባ ኢላርዮን ብለው ይጠሯት ነበር፡፡ 
ከአባቷ ዘንድ ያለችው ታናሽ እኅቷ ርኩስ መንፈስ አደረባትና ብዙ አሠቃያት፡፡ ያድኗትም ዘንድ አባቷ ብዙ በመድከም ገንዘቡን አወጣ ነገር ግን ልትድን አልቻለችም፡፡ መኳንንቶቹም ወደ ግብጽ አስጥስ ገዳም እንዲልካት ለንጉሡ ነገሩት-በዚያ ያሉ መነኮሳት ክብራቸውና ጸጋቸው በሮም አገሮች ሁሉ ታውቋልና፡፡ ንጉሡም የታመመችውን ልጁን ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደ ግብጽ ላካት፡፡ ለመነኮሳቱም ‹‹… ሁለት ሴቶች ልጆችን ወለድኩ ነገር ግን አንደኛዋ ጥላኝ ጠፋች፣ ሁለተኛዋንም ርኩስ መንፈስ ይዞ መጨወቻ አደረገብኝ፡፡ ቅዱሳን አባቶቼ ሆይ ልጄን በጸሎታቸሁ ትፈውሱልኝ ዘንድ ቅድስናችሁን እለምናለሁ›› የምትል ደብዳቤ ጽፎ ላከላቸው፡፡ መነኮሳቱም የንጉሡን ደብዳቤ ካነበቡ በኋላ በልጅቱ ላይ ጸለዩ፡፡ ነገር ግን ያደረባት ርኩስ መንፈስ ሊለቃት አልቻለም፡፡ ከዚህም በኋላ አረጋውያኑ መነኮሳት ጃንደረባ የሚሏትን ኢላርያን ጠርተው ‹‹እግዚአብሔር እስካዳናት ድረስ የንጉሡን ልጅ ወስደህ በላይዋ ላይ ጸልይ›› ብለው ሰጧት፡፡ እርሷም ‹‹ይህ ለእናንተ እንጂ ለእኔ አይቻለኝም›› ብትላቸውም ግድ አሏት፡፡ 
ከዚህም በኋላ ቅድስት ኢላርያ የታመመችውን ልጅ ወደ በዓቷ ወስዳ ጸሎት አደረገችላት፡፡ ሰይጣኑም ወዲያው ጥሏት ሸሸ፡፡ በጥቂት ቀንም ውስጥ ፈጽማ ዳነች፡፡ ቅድስት ኢላርያም እኅቷ እንደሆነች ታውቃለችና አቅፋ ትስማት ነበር ስለ ፍቅሯና ናፍቆቷም ወደ ውጭ እየወጣች ታለቅስ ነበር ነገር ግን ታማ የነበረችው እኅቷ አላወቀቻትም፡፡ ቅድስት ኢላርያም በጸሎቷ ከፈወሰቻ በኋላ ወደ አረጋውያኑ መነኮሳት ወስዳ ‹‹እነሆ በጸሎታች እግዚአብሔር ፈውሷታልና ወደ ንጉሡ አባቷ መልሷት›› ብላ ሰጠቻቸው፡፡ እነርሱም እጅግ ደስ ብሏቸው ወደ አባቷ መለሷት፡፡ ሮሜ አገር በደረሰችም ጊዜ ልጃቸው ስለዳነችላቸው ንጉሡና መኳንንቱ የአገሩም ሰዎች ሁሉ ተደስተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ ከዚህም በኋላ አባቷ በገዳም ስለነበራት ቆይታ ልጁን ጠየቃት፡፡ እርሷም ‹‹ያ በጸሎቱ ያዳነኝ አባ ኢላርዮን የሚባል መነኩሴ አብዝቶ ይወደኛል፤ አቅፎም ይስመኛል›› አለችው፡፡ ንጉሡም ይህንን ሲሰማ ልቡ ታወከና ‹‹መነኩሴ እንዴት ሴትን ለመሳም ይገባዋል/›› አለ፡፡ በዚህም ጊዜ ‹‹በእኔ ላይ ይጸልይ ዘንድ አገሬንም ይባርክ ዘንድ ልጄን ያዳናትን አባ ኢላርዮንን ወደኔ ላኩልኝ›› ብሎ ደብዳቤ ጽፎ ወደ አስቄጥስ ገዳም ላከ፡፡ 
አረጋውያኑም ቅድስት ኢላርያ ጠርተው ወደ ንጉሡ አገር ሄዳ እንድትባርከው አዘዟት፡፡ እርሷም ይተዋት ዘንድ እያለቀሰች ብትለምናቸውም እነርሱ ግን ‹‹ይህ ንጉሥ ክርስቲያኖችን የሚወድ ጻድቅ ነው፣ ቅዱሳት መጻሕፍትም እንደሚያዙን ትእዛዙን መተላለፍ የለብንም›› ብለው አስገድደው ላኳት፡፡ 
ወደ ንጉሡም በደረሰች ጊዜ ሁሉም በክብር ተቀብለው ተሳለሟት፡፡ ንጉሡና ንግሥቲቱም ለብቻቸው ሆነው ወደ ውስጠኛ ክፍል አስገቧትና ንጉሡ እንዲህ ብሎ ጠየቃት፡- ‹‹ልጄን ትስማት እንደነበር በሰማሁ ጊዜ በሀሳቤ ታውኬያለሁ፤ መነኩሴ ሴትን መሳም አይገባውምና ይህን ነገር ትገልጥልኝ ዘንድ እወዳለሁ›› አላት፡፡ የከበረች ቅድስት ኢላርያም በነገርኳችሁ ጊዜ ወደ አስጥስ ገዳም መሄድን ላትከለክሉኝ የከበረ ወንጌልን አምጥታችሁ ማሉልኝ›› አለቻቸው፡፡ እነርሱም ማሉላት፡፡ በዚህም ጊዜ እርሷ ማለት ልጃቸው ኢላርያ መሆኗን ነገረቻቸው፡፡ እንዴት ከቤተ መንግሥት እንደወጣችም አስረዳቻቸውና በአካሏ ላይ ያለውን ምልክት አሳየቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ በቤተ መንግሥቱ ታላቅ ጩኸት ሆነ፡፡ አቅፈውም እየሳሟት አለቀሱ፡፡ ‹‹ከእኛ ዘንድ እንድትሄጂ ከቶ አንተውሽም›› አሏት፡፡ እርሷም ‹‹በከበረ ወንጌል የማላቸሁትን መሐላ አስቡ›› አለቻቸው፡፡ እሺ ብለው ግን እስከ 40 ቀን አብራቸው እንድትቆይ ለመኗት 40 ቀን አብራቸው ቆየች፡፡
ቅድስት ኢላርያም ወደ አስቄጥስ ገዳም ከተመለሰች በኋላ ንጉሡ ዘይኑን ለገዳሙ መነኮሳት ለፍላጎታቸው ይሆን ዘንድ የግብጽን ምድር ግብር እንዲሰጧቸው አዘዘ፡፡ በዚያም ወራት በአባ መቃርስ ገዳም 400 የመነኮሳት ቤቶች ተሠሩ፡፡ በአባ ዮሐንስ ገዳም 700 በአባ ሙሴ ገዳም 300 ቤቶቸ ተሠሩ፡፡ ከዚህም በኋላ ቅድስት ኢላርያ 5 ዓመት ኖራ በሰላም ዐረፈች፡፡ ከዕረፍቷም አስቀድሞ እርሷ ሴት እንደሆነች ያወቀ የለም፡፡ 
የቅድስት ኢላርያ ረድኤት በረከቷ ይደርብን በጸሎቷ ይማረን፡፡
+ + + 
አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል፡- ቅዱሳን አባቶቻችን እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና እነ አቡነ ዜና ማርቆስ ሌሎቹም እነ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣ አቡነ ሕፃን ሞዐ፣ አቡነ አኖሪዮስ(ትልቁ)፣ አቡነ ገላውዲዮስ፣ አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋርና አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል በሥጋም ዘመዳሞች ናቸው፡፡ ይኸውም የመሐግሉ አቡነ ቀውስጦስ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የቅርብ ዘመድ ናቸው፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት እናት እግዚእ ኀረያና የአቡነ ቀውስጦስ እናት እብነ ጽዮን ታላቅና ታናሸ ናችው፡፡ በአባትም በኩል ወረደ ምሕረት ዘካርያስን ወለደ፡፡ ዘካርያስም የእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት የሆኑ 6 ወንድማማች ልጆችን ወለደ፡፡ እነርሱም እንድርያስ፣ አርከሌድስ፣ ዘርዐ አብርሃም፣ ዘርዐ ዮሐንስ ወይም ጸጋ ዘአብ፣ ቀሲስ ዮሐንስና ቀሲስ ዮናስ ናቸው፡፡ እንድርያስም ሳሙኤል ዘወገግን ወለደ፤ አርከሌድስም ሕፃን ሞዐን ወለደ፤ ዘርዐ አብርሃምም ታላቁን አኖርዮስን ወለደ፤ ዘርዐ ዮሐንስ ወይም ጸጋ ዘአብም ተክለ ሃይማኖትን ወለደ፤ ቀሲስ ዮሐንስም ዜና ማርቆስን ወለደ፣ ቀሲስ ዮናስ ደግሞ የፈጠጋሩን ማትያስንና ገላውዲዮስን ወለዳቸው፡፡ ገላውዲዮስም የመሐግሉ ቀውስጦስን ወለደ፡፡
አቡነ ቀውስጦስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሾሙአቸው ከ12ቱ ንብረ ዕድ ወስጥ አንዱ ሲሆኑ ደብረ ሊባኖስንም የሚያጥኑበትም ወር በመጋቢት ወር ነበር። ሕዝቡ አጥብቆ የሚወዳቸውና የሚያከበራቸው አባት ናቸው፡፡
ግብፃዊው አቡነ ያዕቆብ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የደብረ ሊባኖሱን እጨጌ አቡነ ፊልጶስን አስጠርተው፤ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት “ኢትዮጵያ በአንድ ጳጳስ መወሰን የለባትም፡፡ ስለዚህ ዐሥራ ሁለት አበው መርጠን ክርስትና ይስፋፋ” ብለው ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት፤ አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ /ኤጲስ ቆጶስ/፣ አቡነ አኖሬዎስ ዘሞረት፣ አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋር፣ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣ አቡነ አኖሬዎስ ዘወረብ፣ አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ፣ አቡነ ገብረ ክርስቶስ ዘግድም፣ አቡነ መርቆሬዎስ ዘመርሐ ቤቴ፣ አቡነ አድኃኒ ዘዳሞት፣ አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል፣ አቡነ ኢዮስያስ ዘወጅ፣ አቡነ ዮሴፍ ዘእናርያን መርጠው ሀገረ ስብከት ተሰጥቷቸው ለሐዋርያዊ ተልእኮ ተሠማሩ፡፡ ዐሥራ ሁለቱን ንቡራነ ዕድ ለስብከተ ወንጌል በመላዋ አገሪቱ ሲሠማሩ፡፡
ጻድቁ አቡነ ቀውስጦስ አርሲ ፈንታሌ ተራራ ላይ ሠሪቲ ለምትባል ጠንቋይ እየተላላኩ ሕዝቡን የሚያስቱና የሚያሰቃዩ 470300 (አራት መቶ ሰባ ሺህ ሦስት መቶ) አጋንንትን በጸሎታቸው እሳት ከሰማይ አውርደው ተራውንን ደምስሰው አጋንንቱን ያቃጠሉ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ የታናሽ ወንድማቸው የዐፄ ይኩኖ አምላክ ልጅ ዐፄ አምደ ጽዮን በክፉዎች ምክር የአባቱን እቁባት በማግባቱ አቡነ ቀውስጦስ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ሄደው ንጉሡን ስለገሠፁት በግዞት ወስዶ ጎናቸው በጦር ወግቶ ገድሏቸዋል፡፡ ጻድቁ ልደታቸውም ሆነ ዕረፍታቸው ከእመቤታችን ልደትና ዕረፍት ጋር የተባበረላቸው ናቸው፡፡ ግንቦት አንድ ቀን ተወልደው ጥር 21 ቀን ዐርፈዋል፡፡ 
የአቡነ ቀውስጦስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን፡፡
LIKE OUR PAGE https://www.facebook.com/tewadhdohaimanotachin

No comments:

Post a Comment