Sunday, April 24, 2022

ትንሣኤ ዘክርስቶስ - የክርስቶስ ትንሳኤ

❤ ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it) ❤

ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት በመቃብር፤
ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት የሞላው እንዴት ነው?፤
እንዴት ተነሣ?
ለምን በአዲስ መቃብር ተቀበረ?
እንዴት በዝግ መቃብር ተነሣ?
መቃብሩን ማን ከፈተው?
(መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው/ PDF):- ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድኅነተዓለምን በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ በአካለ ሥጋ ወደመቃብር ወረደ÷ ይኸውም በመቃብር ፈርሶ በስብሶመቅረትን ሊያስቀርልን ነው፡፡ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወረደ÷ ይኸውም በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ነፃነትንይሰብክላቸው ዘንድ ነው፡፡ መለኮት፥ በተዋሕዶ፥ ከሥጋም ከነፍስም ጋር ነበረ፡፡ ለዚህ ነው፥ መቃብር ሥጋንሊያስቀረው ያልቻለው፤ ሲኦልም ነፍስን ማስቀረት አልተቻለውም፡፡
ቅዱስ ዳዊት፡- « ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተዋትም» ያለው ይኽንን ታላቅምሥጢር በትንቢት ቃል ሲናገር ነው፡፡ መዝ ፲፭÷፲፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፡- «ክርስቶስ ደግሞ ወደእግዚአብሔር (ወደ አብ÷ ወደ ራሱና ወደ መንፈስ ቅዱስ) እንዲያቀርበን፥ እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜበኃጢአት ምክንያት (ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ተላልፎ በመሰጠት) ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ (በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋውለየ)÷ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ÷ (ያን ሥጋ ነፍስ እንድተለየችው መለኰት አልተለየውም)÷ በእርሱም ደግሞ (መለኰትበተዋሐዳት ነፍስ) ሄዶ በወኅኒ ለነበሩት ነፍሳት ሰበከላቸው፤» ብሏል።
ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት በመቃብር፤
ጌታችን በከርሰ መቃብር የቆየው ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ነው፡፡ «ሥጋዬ ደግሞ በተስፋ ታድራለች፤»የሚለው ቃለ ትንቢት የሚያረጋግጥልን ይኽንኑ ነው፡፡ መዝ ፲፭፥፱፡፡ ምሥጢራዊ ትርጉሙም «ወደ መቃብር የወረደሥጋዬ በተስፋ ትንሣኤ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በመቃብር አደረ፤» ማለት ነው፡፡ ተስፋ ትንሣኤውም በተዋሕዶከሥጋ ጋር ወደ መቃብር የወረደ መለኰት ነው፡፡ ነቢዩ ሆሴዕም፡- «ኑ÷ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱሰብሮናልና÷ (በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስን ጨምሮ የፈረደብን እርሱ ነው)÷ እርሱም ይፈውሰናል፤ (መርገመ ሥጋንመርገመ ነፍስን አስወግዶ ከሞት ወደ ሕይወት ያሸጋግረናል)፤ እርሱ መትቶናል÷ እርሱም ይጠግነናል፡፡ ከሁለት ቀንበኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፡፡» በማለት ትንሣኤ ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን መሆኑን አረጋግጧል፡፡ሆሴ ፮÷፲፪፡፡ ይልቁንም ጌታችን ራሱ በመዋዕለ ሥጋዌው፡- ከሽማግሌዎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራይቀበልና ይገደል ዘንድ፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀመዛሙርቱ በግልጥ ነግሯቸዋል፡፡ ማቴ፲፮÷፳፩፡፡ በገሊላም ሲመላለሱ፡- «ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው÷ይገድሉትማል÷ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤» ብሏቸዋል፡፡ ማቴ ፲፯÷፳፡፡ ጻፎችና ፈሪሳውያንም ምልክት በጠየቁትጊዜ፡- «ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል÷ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በዓሣአንበሪ ሆድ፥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ÷ እንዲሁ የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) በምድር ልብሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡» ብሏቸዋል፡፡ ማቴ ፲፪፥፴፰-፵።
ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት የሞላው እንዴት ነው?፤
ጌታ በከርሰ መቃብር የቆየው ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ነው፡፡ ይኽንንም ለመረዳት ዕብራውያን ዕለታትንእንዴት እንደሚቆጥሩ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እኛ በሀገራችን የሌሊቱን ሰዓት መቁጠር የምንጀምረው ከዋዜማው ከምሽቱአንድ ሰዓት ነው÷ የቀኑን ሰዓት መቁጠር የምንጀምረው ደግሞ ከማለዳው አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ የሌሊቱ ሰዓትየሚያ ልቀው ከማለዳው አሥራ ሁለት ሰዓት ሲሆን፥ የቀኑ ደግሞ ከምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ሲሆን ነው፡፡ የቀኑምየሌሊቱም ሰ ዓት ተደምሮ ሃያ አራት ሰዓት ይሆናል፡፡ ሁሉም ሰዓት ዕለቱን ይወክላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው እሑድዕለት ከሃያ አራቱ ሰዓ ት በአንዱ ቢወለድ እሑድ ተወለደ ይባላል÷ ቢሞትም እሑድ ሞተ ይባላል፡፡ ዕለቱበሚጀምርበትም ሰዓት ሆነ፥ በሚያልቅ በት ሰዓት፥ ድርጊቱ ቢፈጸም ያ ሰዓት እንደ አንድ መዓልትና እንደ አንድ ሌሊትይቆጠራል፡፡ አውሮፓውያን አንድ ብለው ሰዓት መቁጠር የሚጀምሩት በእኛ አቆጣጠር ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ነው፡፡እስከ ሃያ አራት ይቆጥሩና በእኛ አቆጣጠር ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሲሆን ይጨርሳሉ፡፡ ሃያ አራት ሰዓት ሲሆን ዜሮይሉና እንደገና አንድ ብለው መቁጠር ይጀምራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ከሌሊት እስከ ሌሊት ይቆጥራሉ፡፡ አሜሪካውያንደግሞ በእኛ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን አንድ ብለው ይጀምሩና በእኛ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ሲሆን አሥራ ሁለት ብለውይጨርሳሉ፡፡ ከዚያም በእኛ አቆጣጠር ከቀኑ ሰባት ሰዓት እንደገና አንድ ብለው ይጀምሩና በእኛ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓትሲሆን አሥራ ሁለት ብለው ይጨርሳሉ፡፡
ዕብራውያን ግን ዕለትን መቁጠር የሚጀምሩት ከዋዜማው ማለትም በአውሮፓውያን ከአሥራ ሰባት ሰዓት÷በአሜሪካውያን ከአምስት ሰዓት (P.M.) ÷ በእኛ ደግሞ ከምሽቱ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ከዚህ ሰዓት ጀምሮእስከ ቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ድረስ ሃያ አራት ሰዓት ቆጥረው አንድ ቀን ይላሉ፡፡ ከላይ እንደተገለጠው እያንዳንዱ ሰዓትየዕለቱን መዓልትና ሌሊት ይወክላል፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ከመስቀል ወርዶ የተቀበረው ዓርብ ቅዳሜ ከመግባቱበፊት ነው፡፡ ዓርብ ዕለቱ የሚጀምረው ከዋዜማው ሐሙስ በእኛ አቆጣጠር ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ስለዚህ ጌታ የተቀበረው በዓርብ ሃያ አራት ሰዓት ክልል ውስጥ በመሆኑ እንደ አንድ መዓልትና ሌሊት ይቆጠራል፡፡ሁለተኛው ደግሞ ዓርብ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ቀን አሥራ አንድ ሰዓት ያለው ነው፡፡ ሦስተኛውደግሞ ቅዳሜ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ እሑድ ቀን አሥራ አንድ ሰዓት ያለው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የሰኞምሽት ይገባል፡፡ ጌታ የተነሣው በሦስተኛው ቀን እሑድ መንፈቀ ሌሊት ነው።
እንዴት ተነሣ?
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው በታላቅ ኃይልና ሥልጣንነው፡፡ ይህ ኃይልና ሥልጣን የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ ይኽንንም፡- «ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ (ሰውነቴን ከሞት አነሣትዘንድ) አኖራለሁና (በፈቃዴ እሞታለሁና)፤ ስለዚህ አብ ይወደኛል፡፡ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ (ነፍሴን በፈቃዴከሥጋዬ ለይቼ በገነት÷ ሥጋዬንም በመቃብር አኖራቸዋለሁ እንጂ) ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ (ያለ እኔ ፈቃድየሚፈጸም ምንም ነገር የለም)፡፡ ላኖራት (ነፍሴን በገነት÷ ሥጋዬን በመቃብር ላኖራቸው) ሥልጣን አለኝ፤ ደግሞምላነሣት (ነፍሴን ከሥጋዬ አዋሕጄ ላነሣት) ሥልጣን አለኝ፡፡» በማለት አስቀድሞ ተናግሮታል፡፡ ዮሐ ፲÷፲፯-፲፰፡፡ ነቢዩኢሳይያስ፡- «ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት÷ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚልበግ እንዲሁ አፉን አልከፈ ተም፡፡» በማለት መናገሩ ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ እንደሚሞት የሚያጠይቅ ትንቢትነበር፡፡ ኢሳ ፶፫፥፯፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ከዚህ የሚመሳሰል ቃል ተናግሯል፡፡ ፩ኛጴጥ ፪÷፳፴፡፡ በዚህ ዓይነትነቢያትም ሐዋርያትም የተናገሩለት ኢየሱስ ክርስቶስ በኃይሉ በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጐ÷ ሙስና መቃብርንአጥፍቶ ተነሥቷል፡፡ እርሱ የትንሣኤና የሕይወት ባለቤት ነውና፡፡ ዮሐ ፲፩÷፳፭፡፡
ይህ እንዲህ ከሆነ÷ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፡- «የሕይወትን ራስ ገደላችሁት፤» በማለት አይሁድንከወቀሳቸው በኋላ፡- «እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፤» ለምን አለ? የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፡፡ይኽንን ኃይለ ቃል በመያዝ «አብ አስነሣው እንጂ በራሱ አልተነሣም፤» የሚሉ አሉና፡፡ እነዚህም ትርጓሜውን ያልተረዱምሥጢሩን ያላስተዋሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ሐዋርያው «እግዚአብሔር አስነሣው፤» ያለው «እግዚአብሔር» የሚለው ስምየሦስቱም መጠሪያ እንጂ የአብ ብቻ አለመሆኑን ስለሚያውቅ ነው፡፡ ምክንያቱም፦ ወልድም እግዚአብሔር ተብሎይጠራል፡፡ ዮሐ ፩÷፩ ፣ የሐዋ ፳÷፳፰፡፡ መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል፡፡ ዮሐ ፩÷፪፡፡ ስለዚህ፦ሥላሴ በፈቃድ አንድ በመሆናቸው፥ «አንዲት በሆነች በአብ በራሱና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና ሥልጣን ተነሣ፤አንድም፦ ወደ መቃብር የወረደ ሥጋ፥ መለኰት የተዋሐደው ስለሆነ ተነሣ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በመሆኑተነሣ፤» ተብሎ ይተረጐማል፥ ይታመናል፡፡ ትንቢተ ነቢያትም የሚያረጋግጥልን ይኽንኑ ነው፡፡ «እግዚአብሔርምከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ÷ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው፤ ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፤» ይላል።መዝ ፸፯፥፷፭።
ለምን በአዲስ መቃብር ተቀበረ?
በእስራኤል ባሕል፥ የአባቶቻቸው አፅም ካረፈበት መቃብር፥ የመቀበር ልማድ አላቸው፡፡ ዮሴፍ በግብፅየእስራ ኤልን ልጆች፡- «እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ፤» ብሎያማላቸው፥ የአባቶቹ የአብርሃም እና የይስሐቅ የያዕቆብም አፅም ካረፈበት ለመቀበር ፈልጐ ነው፡፡ ዘፍ. ፶÷፳፭፡፡በቤቴል የነበረውም ሽማግሌ ነቢ ይ፡- «በሞትሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ አጥንቶቼንምበአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ፤» ብሏል ፡፡ ፩ኛነገ ፲፫÷፴፩፡፡ ጌታችን የተቀበረው እንደ እስራኤል ባሕል የቅዱሳን አፅምካረፈበት ሳይሆን ማንም ካልተቀበረበት ከአዲስ መቃብር ነው፡፡ ይኸውም ዮሴፍ ለራሱ ያዘጋጀው ነው፡፡ «ዮሴፍምሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው÷ ከዓለት በወቀረ ው በአዲሱ መቃብርም አኖረው÷ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅድንጋይ አንከባሎ ሄደ፤» ይላል ማቴ ፳፯÷፶፱፡፡ ይህም የሆነው እርሱ ባወቀ በርሱ ጥበብ ነው፡፡ እንዲህም በማድረጉአይሁድ ለትንሣኤው ምክንያት እንዳያበጁለት አድርጓቸዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን እንደተጻፈው፥ ከነቢዩ ከኤልሳዕ መቃብርተቀብሮ የነበረው ሰው፥ የነቢዩ አጥንት በነካው ጊዜ፥ በተአምር ተነሥቷል። ፪ኛነገ ፲፫÷፳፡፡ እንግዲህ ጌታችንም፥ከአንዱ ቅዱስ መቃብር ተቀብሮ ቢሆን ኖሮ፥ ሞትን ድል አድርጐ በሚነሣበት ጊዜ «በራሱ አልተነሣም፥ የቅዱሱ አፅምነው ያስነሣው፤» ባሉት ነበር፡፡ ይኸንን ምክንያት ለማጥፋት ነው፥ በአዲስ መቃብር የተቀበረው።
እንዴት በዝግ መቃብር ተነሣ?
ጌታችንን ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ገንዘው ከቀበሩት በኋላ፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተመልሰው፡- « ጌታ ሆይ÷ ያ ሰው (ክርስቶስ)፥ ገና በሕይወቱ ሳለ፥ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ፥ እንዳለ ትዝ አለን፡፡ እንግዲህደቀመዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ÷ የኋለኛይቱ ስሕተትከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት፡፡ ጲላጦስም፡-ጠባቆች አሉአችሁ፥ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ፤» አላቸው፡፡ እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመውመቃብሩን አስጠበቁ፡፡» ማቴ ፳፯፥ ፷፫÷፷፮፡፡ በታላቅ ድንጋይ የተገጠመው መቃብር፥ ድንጋዩ እንደታተመ፥ ክርስቶስሞትን ድል አድርጐ ተነሥቷል፡፡ ይኸውም፦ ምንም የማያግደው መለኰት በተዋሕዶ ከሥጋ ጋር በመቃብር ስለነበረነው፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረው፥ በተዋሕዶ፥ የቃል ገንዘብ ለሥጋ፥ የሥጋም ገንዘብ ለቃል በመሆኑ ነው፡፡ለምሳሌ፦ አይሁድ ብዙ ጊዜ በድንጋይ ቀጥቅጠው ሊገድሉት ሲፈልጉ፥ እያዩት ይሰወርባቸው ከእጃቸውም ይወጣነበር፡፡ በመካከላቸው አልፎ ሲወጣ አያዩትም ነበር፡፡ ዮሐ ፰÷፶፱፤ ፲፥፴፱፡፡ ይህም የሆነው፥ እንደ ነፍስና ሥጋተዋሕዶ፥ መለኰት ሥጋን በመዋሐዱ ነው፡፡ ከትንሣኤው በኋላም ከአንዴም ሁለት ጊዜ ከተዘጋ ቤት በሩ ሳይከፈትየገባው ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ ፳÷፲፱፤ ፳፮፡፡ በልደቱም ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልናእንደታተመች የተወለደው ለዚህ ነው፡፡ ኢሳ ፯÷፲፬፡፡ ማቴ ፩÷ ፳-፳፫ ፣ ሉቃ ፪÷፮-፯፡
መቃብሩን ማን ከፈተው?
ጌታችን የተነሣው መግነዝ ፍቱልኝ፥ መቃብሩን ክፈቱልኝ ሳይል ከሆነ፥ «መቃብሩን ማን ከፈተው?ለምንስ ተከ ፈተ?» የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፤ በወንጌል እንደተጻፈው፥ የአይሁድ ሰንበት ቅዳሜ ካለፈ በኋላ፥እሑድ በማለዳ፥ ፀሐይ ሲወጣ፥ መግደላዊት ማርያም÷ የያዕቆብም እናት ማርያም ሶሎሜም ሽቱ ሊቀቡት ወደ መቃብሩመጥተው ነበር፡፡ ትልቁ ጭንቀታቸው «ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል?» የሚል ነበር÷ ድንጋዩ እጅግትልቅ ነበርና፤ አሻቅበውም አይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደነበር ተመለከቱ፡፡ ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስየተጐናጸፈ ጐልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ፡፡ በጐልማሳ አምሳል የተገለጠላቸው የጌታ መልአክ ነው፡፡እርሱ ግን፡- «አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ አውቃለሁ፤ ተንሥቷል በዚህ የለም፡፡»አላቸው፡፡ ማር ፲፮÷፩-፮፡፡ ጌታችን በዝግ መቃብር ከተነሣ በኋላ ባዶ የነበረውን መቃብር የከፈተው ይህ የጌታ መልአክነው፡፡ የከፈተበትም ምክንያት በእምነት የመጡ እነዚህ ሴቶች ያልተነሣ መስሏቸው ዘወትር በመመላለስ እንዳይቸገሩነው፡፡ አንድም ትንሣኤውን እንዳይጠራጠሩ ነው፡፡ በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልም «በሰንበትም መጨረሻ የመጀመሪያውቀን ሲነጋ፥ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ፡፡ እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይስለወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ፡፡ መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱምእንደ በረዶ ነጭ ነበረ፡፡ ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ፡፡ እንደ ሞቱም ሆኑ፡፡ መልአኩም መልሶሴቶቹን አላቸው፥ እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና፤ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህየለም፤» የሚል ተጽፏል፡፡ ማቴ ፳፰÷፩-፮፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በእርግጠኝነት ትንሣኤውን ያመኑት መልአኩ ወደ ከፈተውመቃብር ገብተው መግነዙን ካዩ በኋላ ነው። ዮሐ ፳፥፯።
በኲረ ትንሣኤ፤
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለባሕርይ አባቱ፥ ለአብ ለእናቱ ለድንግል ማርያምምየበኵር ልጅ ነው፡፡ ዕብ ፩÷፮፣ ሉቃ ፪÷፯፡፡ ለበጎ ነገርም ሁሉ በኵር በመሆኑ የትንሣኤያችንም በኵር እርሱ ነው፡፡ «አሁንግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኵራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል፡፡ ሞት በሰው (በቀዳማዊ አዳም) በኵል ስለመጣ፥ ትንሣኤሙታን በሰው (በተዋሕዶ ሰው በመሆኑ ዳግማዊ አዳም በተባለ በክርስቶስ) በኩል ሆኗልና፡፡ ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱእንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኵራትነው፤» ይላል፡፡ ፩ኛቆሮ ፲፭÷፳-፳፫፡፡ በተጨማሪም፡- «በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥሯልና፥ ከፍጥረትሁሉ በፊት በኵር ነው፡፡ (ከፍጥረታት በፊት የነበረ÷ የፍጥረታት አለቃ÷ የፈጠረውን ፍጥረት የሚገዛ ነው)፤ ሁሉበእርሱና ለእርሱ ተፈጥሯል ፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፤ (ለዘመኑ ጥንት የሌለው ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋርበአንድነት በህልውና የነበረ ነው)፤ ሁሉም በእርሱ ተጋጥሟል፡፡ እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርሰቲያን ራስ ነው፤እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው፡፡» የሚል አለ፡፡ ቈላ ፩÷፲፮-፲፰፡፡ ቅዱስዮሐንስም፡- «ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም÷ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት÷ ከታመነውም ምስክርከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን፤» ብሏል። ራእ ፩፥፭።
በብሉይ ኪዳን እነ ኤልያስ÷ እነ ኤልሳዕ ሙት አስነሥተዋል፡፡ ፩ኛነገ ፲፯፥፳፪ ፣ ፪ኛነገ ፬÷፴፪-፴፰፡፡ በአዲስኪዳንም ራሱ ባለቤቱ የመኰንኑን ልጅ ÷ የመበለቲቱን ልጅ÷ አልዓዛርንም ከሞት አንሥቷቸዋል፡፡ ማቴ ፱÷፳፭፣ ሉቃ፯÷፲፭ ፣ ዮሐ ፲፩÷፵፬፡፡ ነፍሱን በመስቀል ላይ በፈቃዱ አሳልፎ በሰጠም ጊዜ አያሌ ሙታን ከእግረ መስቀሉተነሥተዋል፡፡ ማቴ ፳፯÷፶፫፡፡ እነዚህ ሁሉ በኵረ ትንሣኤ አልተባሉም፡፡ ምክንያቱም፦ አንደኛ፥ በራሳቸው ኃይልየተነሡ አይደሉም፡፡ ሁለተኛ፥ ለተወሰነ ጊዜ ከኖሩ በኋላ ተመልሰው ሞተው ትንሣኤ ዘጉባኤን የሚጠብቁ ሆነዋል፡፡ሦስተኛ፥ ፍጡራን ናቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የባሕርይ አምላክ በመሆኑ በራሱ ኃይልና ሥልጣን ተነሥቷል፡፡ዳግመኛም አይሞትም፡፡ ይኽንንም፡- «ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደፊት እንዳይሞት፥ ሞትም ወደፊት እንዳይገዛውእናውቃለንና ÷ መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቷልና፡፡» በማለት ሐዋርያው ገልጦታል፡፡ ሮሜ ፮÷፱፡፡ጌታችንም፡- «ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያውነኝ፤» ብሏል። ራእ ፩፥፲፰።
ከትንሣኤው በኋላ ለምን ተመገበ?
ጌታችን በተዘጋ ቤት ገብቶ ለደቀ መዛሙርቱ በተገለጠ ጊዜ፥ መንፈስ የሚያዩ መስሏቸው ኅሊናቸው ደንግጦ÷ልባቸውም ፈርቶ ነበር፡፡ እርሱም፡- «ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደሆንሁእጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት÷ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና፥ እኔን ዳስሳችሁ እዩ፤» ካላቸው በኋላእጆቹንና እግሮቹን አሳይቷቸዋል። እነርሱም ከደስታ የተነሣ ገና ስላላመኑ ሲደነቁ ሳሉ፡- «በዚህ አንዳች የሚበላአላችሁን?» አላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ ከማር ወለላም ሰጡት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በላ፥ይላል። ሉቃ ፳፬÷፴፮ -፵፫። ለሦስተኛ ጊዜ በጥብርያዶስ በተገለጠላቸውም ጊዜ አብሯቸው ተመግቧል፡፡ ዮሐ ፳፩÷፱-፲፬። ይኽንንም ያደረገው ከትንሣኤ በኋላ መብላት መጠጣት ኖሮ አይደለም፡፡ አለማመናቸውን ለመርዳት ነው፡፡ደቀመዛሙርቱ በተዋሐደው ሥጋ ለመነሣቱ እርግጠኞች እንዲሆኑ ነው፡፡ ከወንጌሉ እንደምንረዳው ደቀመዛሙርቱይበልጥ እርግጠኞች የሆኑት ስላዩት ሳይሆን፥ ያቀረቡለትን በመብላቱና በመጠጣቱ ነውና፡፡
ለምን አትንኪኝ አላት?
መግደላዊት ማርያም ገና ሰማይና ምድሩ ሳይላቀቅ፥ በማለዳ፥ ሽቱ ልትቀባው ከመቃብሩ አጠገብ ተገኝታነበር። እንደደረሰችም ድንጋዩ ከመቃብሩ አፍ ተፈንቅሎ አየች። ይህች ሴት በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ ከባለቤቱብትሰማም፥ « እንደተናገረ ተነሥቶ ነው፤» ብላ አላመነችም። ላለማመኗም ምክንያት የሆነው፥ «እኛ ተኝተን ሳለንደቀመዛሙርቱ በሌሊት ሰረቁት፤» የሚለው የጭፍሮች ወሬ ነው። ጭፍሮቹ እውነትን በሐሰት ለውጠው ይኽንንያወሩት፥ በገንዘብ ተደልለው ነው፡፡ ማቴ ፳፰÷፲፩-፲፭፡፡ ለዚህ ነው ወደ ደቀመዛሙርቱ ሄዳ፡- «ጌታን ከመቃብርወስደውታል፥ ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም፤» ያለቻቸው፡፡ ዮሐ ፳÷፪፡፡ ከመቃብሩ ራስጌና ግርጌ ሁለት መላእክትተገልጠውላት፡- «አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ?» ባሏት ጊዜም፥ «ጌታዬን ወስደውታል፥ ወዴትም እንዳኖሩትአላውቅም፤» ብላቸዋለች፡፡ ዮሐ ፳÷፲፫፡፡ በመጨረሻም ጌታ ራሱ ተገልጦላት፡- «አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስትፈልጊያለሽ?» ሲላት አላወቀችውም፡፡ ለዚህ ነው፥ አትክልት ጠባቂ መስሏት፡- «ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸውእንደሆንህ፥ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ፥ እኔም ወስጄ ሽቱ እንድቀባው፤» ያለችው፡፡ ዮሐ. ፳÷፲፭፡፡ በዚህን ጊዜ፥«ማርያም»፥ ብሎ በስሟ ቢጠራት በድምፁ አወቀችውና «ረቡኒ ( መምሕር ሆይ)» አለችው፡፡ መልኩን አይታ፥ ድምፁንሰምታ÷ ትንሣኤውን አረጋግጣ፥ «አምላኬ» አላላችውም፡፡ ስለዚህ «ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ አትንኪኝ፥ ነገር ግንወደ ወንድሞቼ (ወደ ደቀመዛሙርቴ) ሄደሽ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ÷ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አርጋለሁብሏል፥ ብለሽ ንገሪያቸው፤» አላት፡፡ እንዲህም ማለቱ የእርሱ የእግዚአብሔር ልጅ መባልና የእነርሱ የእግዚአብሔርልጆች መባል ፍጹም የተለያየ በመሆኑ ነው፡፡ እርሱ፥ «አባቴ» ቢል የባሕርይ ልጅ በመሆኑ ነው፡፡ እነርሱ ግን የጸጋልጆች ናቸው፡፡ እርሱ፥ «አምላኬ» ቢል ስለተዋሐደው ሥጋ ነው፡፡ የተዋሐደው የፈጠረውን ሥጋ ነውና ፡፡ እነርሱ ግን«አምላካችሁ» ቢባሉ ፍጡራን ስለሆኑ ነው፡፡ በዚህም እርሱ ፈጣሪ እነርሱ ፍጡራን መሆናቸውን አስረግጦ ተናግሯል፡፡ቶማስን ግን፡- «ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው ፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህአትሁን፤» ብሎታል፡፡ ዮሐ ፳፥፳፯ ፡፡ ምክንያቱም አይቶ፥ ዳስሶ፥ «ጌታዬ አምላኬም» ብሎ የሚያምን ነውና፡፡ አንድምሥጋውንና ደሙን ለመዳሰስ÷ ለመፈተት፥ የተጠራ የተመረጠም ካህን ነውና፡፡
ተስፋ ትንሣኤ፤
በብሉይ ኪዳን ዘመን ሁሉም በአዳም ኃጢአት ምክንያት እየተኰነኑ በሞተ ነፍስ ተይዘው ወደ ሲኦል ይወርዱነበር ። ፩ኛ ቆሮ ፲፭ ÷፳፪፡፡ «ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ ከአዳም ጀምሮ እስከሙሴ ( እስከ ክርስቶስ) ድረስ ሞት ነገሠ፤» የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ሮሜ ፭÷፲፬፡፡ ከዚህ የተነሣ እነ አብርሃም እንኳሳይቀሩ የወረዱት ወደ ሲኦል ነው፡፡ እነ ኢሳይያስ፡- «ጽድቃችንም ሁሉ እንደመርገም ጨርቅ ነው፤» ያሉት ለዚህ ነው፡፡ኢሳ ፷፬ ÷፮፡፡ እነ ኤርምያስም፡- «ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም፥ ስንዴን ዘሩ እሾህንም አጨዱ፡፡» ብለዋል፡፡ ኤር፲፪÷፲፫። በዚህ ምክንያት የብሉይ ኪዳን፥ ዘመን ዘመነ ፍዳ÷ ዘመነ ኵነ ÷ ዘመነ ጽልመት ተብሏል፡፡ በዚህ ዘመን እነቅዱስ ዳዊት፡- «አንሥእ ኃይለከ÷ ወነዓ አድኅነነ፤ ኃይልህን አንሣ÷ እኛንም ለማዳን ና ፤ (በሥጋ ተገልጸህ÷ ሰው ሁነህአድነን)፤» እያሉ ወልድን ተማጽነዋል፡፡ መዝ 79÷ 2 ፡፡ «ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ፤ ብርሃንህንና እውነትህን ላክልን፤(ብርሃን ወልድን÷ እውነት መንፈስ ቅዱስን ላክልን) ፤ እነርሱ ይምሩን÷ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ÷ (ወደገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት) ይውሰዱን »፤ እያሉም አብን ተማጽነዋል፡፡ መዝ ፵÷፫፡፡ ይህም የሚያመለክተው በዚያበጨለማ ዘመን ሆነው ተስፋቸው የክርስቶስ ትንሣኤ እንደነበረ ነው፡፡ በሞት አጠገብ ሕይወት÷ በመቃብር አጠገብትንሣኤ እንዳለ ተስፋ እንዲያደርጉ የሚያደርጋቸው የክርስቶስ ትንሣኤ ነውና፡፡ ያንጊዜ ከሲኦል እንደሚወጡ፥የተዘጋች ገነትም እንደምትከፈትላቸው ያውቃሉና፡፡
የክርስቶስ ትንሣኤ የአዳም ልጆች በጠቅላላ ትንሣኤ ዘጉባኤን በተስፋ እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል፡፡ ይህምተስፋ ሃይማኖት እንዲይዙ÷ ምግባር እንዲሠሩ አጽንቷቸዋል፡፡ ምድራዊውን እንዲንቁ፥ ሰማያዊውን እንዲናፍቁአድርጓቸዋል፡፡ « ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን፡፡» ይላል፡፡ ፪ኛ ጴጥ፫÷፲፫፡፡ ቅዱሳን በሃይማኖት አይተዋታል፡፡ «አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ÷ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱምድር አልፈዋልና÷ ባሕርም ወደፊት የለም፡፡ ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ፡፡» ይላል፡፡ ራእ ፳፩÷፫፡፡ እግዚአብሔርም፡- «እነሆ÷ አዲስሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፥ የቀደሙትም አይታሰቡም÷ ወደ ልብም አይገቡም፡፡ ነገር ግን በፈጠርሁት ደስይበላችሁ፥ ለዘላለምም ሐሴት አድርጉ፤ እነሆ÷ ኢየሩሳሌምን ለሐሴት÷ ሕዝቧንም ለደስታ እፈጥራለሁና፡፡» ብሏል፡፡ኢሳ ፷፭፥፲፯።
ሙታን እንዴት ይነሣሉ?
እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው የሚያንቀላፋና የሚነቃ አድርጐ ፈጥሮታል፡፡ ማንቀላፋቱ የሞት፥መንቃቱ ደግሞ የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ አቤል ከሞተ በኋላ በደሙ መናገሩም የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ ፬÷፲፡፡የሄኖክም ከዓይነ ሞት ተሰውሮ በእግዚአብሔር መወሰድ የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ ፭÷፳፬፡፡ ፍጥረታት በጠቅላላምትንሣኤን የሚሰብኩ ናቸው፡፡ የፀሐይ መውጣት የመወለድ÷ የፀሐይ መጥለቅ የመሞት÷ ከጠለቀች በኋላም እንደገናመውጣት የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙታን እንደሚነሡ በቃልም በተግባርም አስተምሯል፡፡በቃል ፡- «በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ÷ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ፡፡» ሲል አስተምሯል፡፡ ዮሐ ፭÷፳፱፡፡ በተግባርም የአራትቀን ሬሳ አልዓዛርን አስነሥቷል፡፡ ዮሐ ፲፩÷፵፫፡፡ ቅዱሳን ነቢያት፡- እነ ኢሳይያስ «ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፥ ሬሳዎችምይነሣሉ፡፡» ብለዋል። ኢሳ ፳፮÷፲፱፡፡ እነ ዳንኤልም፡- «በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች (ሁሉም) ይነቃሉ፤እኵሌቶችም ወደ ዘላለም ሕይወት÷ እኵሌቶችም ወደ እፍረትና ዘላለም ጉስቊልና፡፡» ብለዋል፡፡ ዳን ፲፪÷፪፡፡ በተለይምለነቢዩ ለሕዝቅኤል፥ እግዚ አብሔር፦ በአፅም የተሞላ ታላቅ ሸለቆ ካሳየው በኋላ፥ «እነዚህ የደረቁ አጥንቶች ተመልሰውበሕይወት የሚኖሩ ይመስ ልሃልን?» ሲል ጠይቆታል፡፡ ሕዝቅኤልም፡- «እግዚአብሔር ሆይ÷ አንተ ታውቃለህ፤» የሚልመልስ ሰጥቶቷል፡፡ በመጨ ረሻም እነዚህ ሁሉ ሕይወት ዘርተው ሲነሡ አይቷል፡፡ ይኸንንም፡- «እንዳዘዘኝም ትንቢትተናገርሁ÷ ትንፋሽም ገባባቸው፥ ሕያዋንም ሆኑ÷ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ፡፡» በማለትገልጦታል፡፡ ሕዝ ፴፯፥፩-፲፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሙታን ትንሣኤ በሚገባ ቋንቋ አብራርቶ በምሳሌ ሲያስተምር «ነገር ግን ሰው፥ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል፡፡» ብሎ ከጠየቀ በኋላ፥ «አንተ ሞኝአንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፡፡» ብሏል፡፡ ከዚህም አያይዞ «የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው፡፡በመበስበስ ይዘራል÷ ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል÷ በኃይል ይነሣል፤ፍጥረታዊ አካል ይዘራል÷ መንፈሳዊ አካል ይነሣል ፤ ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ፡፡ እንዲሁደግሞ፡- ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም (ክርስቶስ) ሕይወትን የሚሰጥመንፈስ ሆነ፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም።የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው። ሁለተኛው ሰው ( ክርስቶስ ) ከሰማይ ነው፡፡ መሬታዊው እንደሆነመሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲህ ናቸው÷ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው ፡፡የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን፡፡» ብሏል። ፩ኛቆሮ ፲፭÷፴፭-፵፱፡፡ በፊልጵስዩስ መልእክቱም፡- «ክቡር ሥጋውን እንደሚስል የተዋረ ደውን ሥጋችንን ይለውጣል፡፡» ብሏል፡፡ ፊል፫÷፳፩። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም፡- «እርሱን እንድንመስል እናውቃለን፤» ብሏል፡፡ ፩ኛ ዮሐ ፫÷፪።
የትንሣኤ ጸጋ፤
በክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘነው ጸጋ ታላቅ ነው። ከጨለማ ወደ ብርሃን ወጥተናል÷ ከሞት ወደ ሕይወትተሸጋግረናል ። ሙታን የነበርን ሕያዋን÷ ምድራውያን የነበርን ሰማያውያን÷ ሥጋውያን የነበርን መንፈሳውያን ሆነናል፡፡«ሞት ሆይ÷ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ÷ ድል መንሣትህ የት አለ?» የምንል ሆነናል፡፡ ሆሴ ፲፫÷፲፬ ፣ ፩ኛቆሮ፲÷፶፭፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ «እኛ አገራችን በሰማይ ነውና÷ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታንኢየሱስ ክርስቶስን እንጠ ባበቃለን፤ እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር ክቡር ሥጋውንእንዲመስል የተዋረደውን ሥጋች ንን ይለውጣል፡፡» የምንል ሆነናል፤ ፊል ፫፥ ፳-፳፩፡፡ ናፍቆታችን ሁሉ በትንሣኤያገኘነውን ጸጋ እውን ማድረግ ነው፡፡ «ድንኳን የሚሆነው ምድራዊው መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና፡፡ በዚህ ውስጥ በእውነትእንቃትታለንና÷ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድን ለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም፡፡»ይላል፡፡ ፪ኛቆሮ ፭፥፩-፪፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፡- «ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋናለማይጠፋ÷ እድፈትም ለሌለበት÷ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስክርስቶስ አባት ይባረክ» ብሏል፡፡ ፩ኛጴጥ ፩÷፫፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም፡- «በሚመጡ ዘመ ናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳ የን ዘንድ ከእርሱ ጋር አስነ ሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስምበሰማያዊው ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።» ብሏል። ኤፌ፪÷፮-፯።
የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን፡፡
Other materials to refer

Monday, April 18, 2022

ሰሙነ_ሕማማት

 ሰሙነ_ሕማማት


#ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ሰሙነ ሕማማት የጾመ ሁዳዴ የመጨረሻው ሳምንት፤ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም የሚታሰብበት፤ ካህናትና ምእመናን በአጸደ ቤተክርስቲያን ተሰብስበው የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ የሚያዜሙበት፤ ግብረ ሕማም በመባል የሚታወቀውን መጽፍ የሚያነቡበትና የሚሰሙበት፤ በነግህ፣ በሠልስት፣ በስድስት፣ በተሰዓት /ዘጠኝ /ሰዓት፣ በሰርክ /በዐስራ አንድ/ ሰዓት እየመላለሱ የሚሰግዱበትና የሚጸለዩበት ልዩ ሳምንት ነው ከሆሳዕና ማግስት እስከ ትንሳኤ።

በዚህ ሳምንት በተለይ ካህናት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ ምክንያቱም ጌታችን የደረሰበትን መከራና ስቃይ እንዲሁም የሰው ልጅ ፭ ሺ ፭ መቶ ዘመን በጨለማ ግዞት ይኖር እንደነበር ለማዘከርም ጭምር ነው። የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራና ሕማም በጽኑ እንድናስበው ያስተማሩን ሐዋርያት ናቸው። ለእነርሱም የነገራቸው ደግሞ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ሰሙነ ሕማማት የጌታችንን ሕማማት ከማሰብ ጋር በየዕለቱ በርካታ ድርጊቶች መፈጸማቸውን የምናስታውስበት ሳምንት ነው፦

#ሰኞ
#መርገመ_በለስ_የተፈጸመበት_ሰኞ_ይባላል
በዚህ ዕለት ጌታችን ከቢታኒያ ሲወጣ ተራበ ቅጠል ያለባትን በለስ ተመልክቶ ወደ በለሲቱ ቢቀርብ ከቅጠል በቀር ምንም ነገር ባለማግኘቱ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ምንም ካንቺ ፍሬ አይበላ” ማር ፲፩፥፲፬ በማለት ስለረገማት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል።

#አንጽሖተ_ቤተ_መቅደስ_ይባላል፡-
ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሄዶ በቤተመቅደሱ የሚሸጡትን እና የሚለውጡትን “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” ማቴ ፳፩፥፲፫ በማለት ከቤተመቅደስ ገርፎ አስወጥቷቸዋልና።

#ማክሰኞ
#የጥያቄ_ቀን_ይባላል
ሰኞ ዕለት በቤተመቅደስ ሲሸጡ እና ሲለውጡ የነበሩትን ሁሉ እየገረፈ በማባረሩ ምክንያት ለሰው ልጅ ሹመትንና ስልጣንን የሰጠ ጌታ “በምን ስልጣን ይህንን ታደርጋለህ?” ማቴ ፳፩፥ ፳፫ ተብሎ በፈሪሳውያን ተጠይቋልና የጥያቄ ቀን ይባላል።

#የትምህርት_ቀን_ይባላል፡-
በዚህ ዕለት በቤተመቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረም የትምህርት ቀን ይባላል። ሉቃ ፳፩ ፥፳፰ ፣ ማር ፲፪፥፪።

#ረቡዕ
#ምክረ_አይሁድ_ይባላል
ረቡዕ እለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የመከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉበት ቀን በመሆኑ ምክረ አይሁድ ይባላል። ወቅቱ የፋሲካን በዓል የሚያከብሩበት ቀን በመሆኑ እና ብዙ ህዝብም ጌታን ይከተለው ስለነበር ሁከት እንዳይነሳ ስጋት ነበራቸው ። ነገር ግን ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ስለነገራቸው ሉቃ ፳፪፥፩-፮ ጭንቀታቸው ተወግዶ በጌታ መያዝ ተስማምተዋል።

#የመልካም_መዓዛ_ቀንም_ይባላል፡-
ጌታችን በዚህ ዕለት በለምጻሙ በሰምዖን ቤት ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት/ባለሽቶዋ ማርያም/ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ የአልባጥሮስ ሽቱ አምጥታ በራሱ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባቸው ማቴ ፳፮፥፮-፯ የመዓዛ ቀን ይባላል።

#የእንባ_ቀን_ይባላል፡-
ባለሽቱዋ ሴት (ማርያም እንተ እፍረት) ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት እየለመነች በእግሩ ስር ተደፍታ በእንባዋ እግሩን አርሳለችና ማር ፲፬፥፱ የእንባ ቀን ይባላል።

#ሐሙስ
#ጸሎተ_ሐሙስ_ይባላል
ጌታችን ለአይሁድ ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሲጸልይ በማደሩ ማቴ ፳፮፥፴፮ ጸሎተ ሐሙስ ይባላል።ጌታችን የደቀመዛሙርቱን እግር በፍጹም ትህትና ዝቅ ብሎ ያጠበበት ዕለት በመሆኑም ዮሐ ፲፫፥፫-፲፩ ሕጽበተ ሐሙስ ይባላል።

#የምስጢር_ቀን_ይባላል፡-
ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ የቅዱስ ቁርባን ምስጢር ማቴ፳፮፥፳፮-፳፱ በዚህ ዕለት ተፈጽሟልና የምስጢር ቀን ይባላል።

#የሐዲስ_ኪዳን_ሐሙስ_ይባላል፡-
መሥዋዕተ ኦሪት /በእንስሳት ደም የሚቀርብ መሥዋዕት/ቀርቶ ለአለም ድኅነት ራሱን ያቀረበበት ቀን በመሆኑ ሉቃ ፳፪፥፳ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል።

#የነጻነት_ሐሙስ_ይባላል፡-
ለኃጢአትና ለዲያቢሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱን እንዲሁም የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነም ዮሐ ፲፭፥ ፲፭ የነጻነት ሐሙስ ይባላል።

#ዓርብ
#የስቅለት_ዓርብ_ይባላል
ጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የዋለበት ዕለት ነውና ማቴ ፳፯፥፴፭ የስቅለት ዓርብ ይባላል።

መልካሙ_ዓርብ_ይባላል፡-
ከጌታ ስቅለት በፊት በተለይም በሮማውያን ህግ የወንጀለኛ መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል ጌታችን በደሙ ቀድሶ የምህረት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያቢሎስ ድል መንሻ ስላደረገው፤ በሞቱ መልካሙን ሕይወት ስላገኘን መልካሙ ዓርብ ይባላል።

🌱ቅዳሜ
🌱🌿ቀዳም_ስዑር_ትባላለች ፦
ይህች እለት ከድሮ በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረች ቅዳሜ ይባላል።

🌱🌿ለምለም_ቅዳሜ_ይባላል፡-
ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት በመሆኑም ለምለም ቅዳሜ ይባላል። ምዕመናንም ይህንን ለምለም ቀጤማ እስከ ትንሣኤ ለሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል።

🌱🌿ቅዱስ_ቅዳሜ_ይባላል፡-
ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ያረፈበት ቀን ሲሆን በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ስራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ በነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዶ ሲኦልን በርብሮ ባዶዋን ሲያስቀራት በዚያ የነበሩትን ነፍሳት የዘላለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል።

(ስምዐ ጽድቅ መጋቢት ፳፻፪ ዓ.ም)

Wednesday, February 23, 2022

💚 💛❤️ ማንኛውንም ሥዕላት/ቅዱሳን ሥዕላት ለገዳማት፡ ለቤተክርስትያናት ለወዳጅ ለዘመድ ማሠራት ከፈለጉ 💚 💛❤️

 

🖌🖌🖌✏️✏️✏️ ማንኛውንም ሥዕላት/ቅዱሳን ሥዕላት ለገዳማት፡ ለቤተክርስትያናት ለወዳጅ ለዘመድ ማሠራት ከፈለጉ ከታች ያለውን አድራሻ ይጠቀሙ። ሠዓሊ ጊጋር
ማንኛውንም የሥዕል ዓይነት ለማሠራት ስትፈልጉ ከሥር ያለውን አድራሻ መጠቀም ትችላላችሁ።🧡💛💙💜🖤🤍🤎💚
👇👇👇👇👇👇👇👇
አድራሻ
#ስልክ: 0911169870 ,0943800478
#ቴሌግራም -- @gigarn , @gigarmarshet
#ኢ-ሜይል-- negussegigar@gmail.com










ተዋህዶ-ሀይማኖታችን: ኪዳነ ምህረት (የካቲት 16)

ተዋህዶ-ሀይማኖታችን: ኪዳነ ምህረት (የካቲት 16): ኪዳነ ምህረት ማለት የምህረት መሐላ ማለት ነው፡፡ ከ 33 ቱ በዓላተ እግዝእትነ ድንግል ማርያም አንዱ ነው፡፡ እመቤታችንም ከጌታችን መቃብር እየሄደች በምትለምንበት ጊዜ አይሁ...



Monday, January 31, 2022

ጥር 18 - ወበዛቲ ዕለት

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈሰ ቅዱስ ስም አሜን

ጥር 18-ፀሐይ ዘልዳ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዐፅሙ ተቃጥሎ አጥንቱ ተፈጭቶ በደብረ ይድራስ ተራራ ላይ የተበተነበት ዕለት ነው፡፡



+ በ34 ዓ.ም ጥምቀትን ያመጣልን ለሀገራችንም ሆነ ለአፍሪካ የመጀመሪያ ሐዋርያችን የሆነው ቅዱስ አቤላክ (ባኮስ) በዚህች ዕለት በሰሜን ተራራዎች ላይ ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት ቦታ ተሰወረ፡፡ እርሱም በጌታችን የተመረጡ የከበሩ ሐዋርያት እንኳን ወንጌልን በዓለም ለመስበክ ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት ወቅት ወደ አፍሪካ መጥቶ ወንጌልን የሰበከ ነው፡፡
+ ለቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ መምህሩ የሆኑት አባ ያዕቆብ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+ ጌታችን ከሞት ያስነሣው የቅዱስ አልዓዛር እኅቶች ማርያምና ማርታ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡
አባ ያዕቆብ፡- በገድል ተጠምደው የኖሩ እጅግ የከበሩ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉት ንጽቢን በምትባል ከተማ ቢሆንም ሶርያዊ ተብለው ይጠራሉ፡፡ የሀገረ ንጽኒቢን ኤጲስ ቆጶስ ሲሆኑ የእመቤታችንን ውዳሴ ለደረሰው ታላቅ አባት ለቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ መምህሩ ናቸው፡፡ ይህ ታላቅ አባት ከልጅነታቸው ጀምሮ ዓለምን ንቀው በመንኩስና መኖርን መርጠው መንኩሰዋል፡፡ በጠጉር ከተሠራ ማቅ በቀር ሌላ ልብስ ለብሰው አያውቁም፡፡ በቀን በሌሊት፣ በበጋ ሐሩርም ይሁን በክረምት ቁር ቢሆን ይህንን ልብሳቸውን አውልቀውት አያውቁም፡፡ ምግብም ከቅጠላ ቅጠል ውጭ ተመግበው አያወቁም፡፡ የሚጠጡትም የዝናብ ውኃ ብቻ ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ ሀብተ ትንቢትና ሀብተ ፈውስ ተሰጥቷቸው እጅግ አስገራሚ የሆኑ ተአምራትን ያደርጉ ጀመር፡፡ በአንዲት ዕለት ሴቶች በውኃ ምንጭ ላይ እርቃናቸውን ያለ ማፈር ሲጫወቱና ሲሳለቁ አይተው የውኃውን ምንጭ ወዲያው እንዲደርቅ አድርገውታል፡፡ የሴቶቹንም የራሳቸውን ጸጉር በተአምራት ነጭ ሽበት አደረጉባቸው፡፡ ሴቶቹም ተጸጽተው በአባታችን እግር ሥር ወድቀው በለመኗቸው ጊዜ የውኃውን ምንጭ መልሰው አፈለቁላቸው፡፡ እንዳይታበዩ ሲሉ ግን የራሳቸውን ጸጉር ለምልክት ነጭ አድርገው ተውላቸው፡፡ ትሩፋታቸውና ዜናቸው በበየቦታው በተሰማ ጊዜ አቡነ ያዕቆብን በንጽቢን ሀገር ላይ ኤጲስ ቆጶስነት ሾሟቸው፡፡
ጻድቁ ንጉሥ ታላቁ ቈስጠንጢኖስ 318ቱን የከበሩ አባቶች በኒቅያ እንዲሰበሰቡ ሲያደርግ ገድላኛ የሆኑት ይህ ታላቅ አባትም አንዱ ነበሩ፡፡ በጉባኤውም መካከል ሙት አስነሥተው እንዲመሰክር አድርገውታል፡፡ እርሳቸውም አርዮስን አስተምረው መክረው እምቢ ቢላቸው ረግመው አውግዘውታል፡፡ የፋርስ ንጉሥ መጥቶ ሀገረ ንጽቢን ሊወር አስቦ በከበባት ጊዜ አቡነ ያዕቆብ በጸሎታቸው የጭጋግ ደመና በሠራዊቱ ላይ አመጡባቸው፡፡ ተናዳፊ ትንኞችም ፈረሶቻቸውንና ወታደሮቻቸውን ሁሉ ነደፏቸው፡፡ ፈረሶቹም ማሠሪያቸውን እየበጠሱ ፈርጥተው ጠፉ፡፡ ንጉሡም ይህን ተአምር አይቶ እጅግ ፈርቶ ወደ ኋላው ተመልሶ ሄዷል፡፡ ጻድቁ ሕዝበ ክርስቲያኑንና ሀገራቸውን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በጽድቅ ሲያገለግሉ ኖረው በሰላም ዐርፈዋል፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!
+ + +
ስብረተ ዐፅሙ ለሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ፡- ከሃዲው ንጉሥ ዱድያኖስ እጅግ አሠቃቂ በሆኑ ብዙ መከራዎች እያሠቃየ ሦስት ጊዜም ቢገድለው ጌታችን ግን ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሞት እያስነሣው ከሃድያንን ያሳፍራቸው ነበር፡፡ ንጉሥ ዱድያኖስ የሚያደርገው ቢያጣ ጭፍሮቹን ‹‹በመንኰራኩር ፈጭታችሁ አጥንቱን ደብረ ይድራስ ተራራ ላይ ወስዳችሁ ዝሩት›› ብሎ አዘዛቸው፡፡ ጭፍሮቹም የቅዱስ ጊዮርጊስን ሥጋ በመንኰራኩር ፈጭተው ወስደው በተራራው ላይ ቢረጩት ሥጋው ያረፈበት ሳር፣ ቅጠሉ፣ ደንጊያው፣ እንጨቱ ሁሉ ‹‹ጊዮርጊስ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር፣ ጊዮርጊስ ሰማዕቱ ለእግዚአብሔር›› እያሉ አመስግነዋል፡፡ አሁንም ጌታችን ለሦስተኛ ጊዜ ከሞት አስነሣውና ሥጋውን ፈጭተው በተራራም ላይ ሥጋውን በትነውት ወደ ንጉሡ የሚመለሱትን ወታደሮች በመንገድ ከኋላቸው ሄዶ ደረሰባቸውና ‹‹ቆዩኝ ጠብቁኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም እጅግ ደንግጠው ይህ እንዴት እንደሆነ ሲጠይቁት ‹‹አምላኬ ከሞት አዳነኝ›› አላቸው፡፡ ጭፍሮቹም እጅግ ደንግጠው ከእግሩ ስር ወድቀው ‹‹ይቅር በለን›› ብለው በአምላኩ እንደሚያምኑ መሰከሩለት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ከመሬት ላይ ውሃ አመንጭቶ በጸሎት ጌታችንን ቢጠይቅ ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ አጥምቋቸዋል፡፡ እነርሱም በንጉሣቸው ፊት ሄደው ስለጌታችን በመመስከር በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዐፅሙ ተቃጥሎ አጥንቱ ተፈጭቶ በደብረ ይድራስ ተራራ ላይ የተበተነው በዚህች ዕለት ነው፡፡

የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
የመጀመሪያው የአፍሪካ ሐዋርያ ቅዱስ አቤላክ (ባኮስ)፡- ይኽም ጃንደረባ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ንግሥት የሆነችው የህንደኬ የገንዘቧ ሁሉ ኃላፊና አዛዥ የነበረ ነው፡፡ ከአባቱ እብነ መላክ ከእናቱ ስሂነ ሕይወት ታኅሣሥ 29 ቀን ተወለደ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ለበዓለ ፋሲካ በቤተ መቅደስ ይሰግዱ እንደነበረው ሁሉ ይኽም ጃንደረባ ከ4 ሺህ ማይልስ በላይ ተጉዞ ኢየሩሳሌምን ተሳልሞ በመለስ ላይ ነበረ፡፡ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ በተለይም ስለ ጌታችን መከራ መስቀል በዝርዝር የሚናገረውን ክፍል 53ኛውን ምዕራፍ ያነብ ነበር ነገር ግን ጃንደረባው ስለማን እንደሚናገር አልገባውም ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር በአካባቢው ወንጌልን ይሰብክ የነበረውን ሐዋርያውን ቅዱስ ፊሊጶስን ላከለት፡፡ እርሱም ጃንደረባው ያነበው የነበረውን መጽሐፍ ተረጎመለት፣ የከበረች ወንጌልን ሰበከለት፣ በመጨረሻም አጠመቀው፡፡ ሐዋርያው ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በጃንደረባው ላይ ወረደ፡፡ ሐዋ 8፡26-40፡፡ ይህን ለእኛ ለኢትዮጵያውን እጅግ የሚያኮራን ታሪካችን ነው፡፡ ዛሬ በእጃችን ላይ በመገኘው መጽሐፍ ውስጥ ባይኖርም በቆዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች ላይ ግን ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ ጃንደረባውን ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በኢትዮጵያው ጃንደረባ ላይ እንደወረደ ተጽፏል፡፡ (ዝኒ ከማሁ ገጽ 87፣ v.39.cord.alexand. in bible reg. angl-alique plures codd.mss)
ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ጃንደረባውን ያጠመቀበት ወንዝ ‹‹ቤተ ሳሮን›› በተባለችውና እስከዛሬም ድረስ ከኢየሩሳሌም 20 ማይልስ ርቀት በምትገኘው መንደር በኬብሮን መካከል ባለው ኮረብታ ሥር የሚመነጭ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ጸሐፊ የሆነው ሊቁ ቅዱስ ጀሮም ጃንደረባውን ‹‹የኢትዮጵያውያን ሐዋርያ›› በማለት ይጠራዋል፡፡ በሰፊው ለኢትዮጵያውያን ወንጌልን የሰበከ እርሱ ነውና፡፡ ጌታችን የመረጣቸው የከበሩ ሐዋርያት እንኳን ወንጌልን በዓለም ለመስበክ ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት ወቅት በ34 ዓ.ም ነው ቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ በክርስቶስ አምና ወንጌልን የተቀበለችው፡፡ በምድሪቱም ላይ ወንጌል መነገር የጀመረው ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡
እንሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከኢየሩሳሌም ወንጌልን ተምሮና ተጠምቆ ወደ አክሱም እንደተመለሰ በመጀመሪያ ያጠመቀው ንግሥቲቷን ሕንደኬን ነው፡፡ ከእርሷም በኋላ መኳንንቱና መሳፍንቱ ሁሉ አምነው በባኮስ እጅ ተጠመቁ፡፡ ይኸውም በ34 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚህም በኋላ ባኮስ እስከ ኑብያ ድረስ ሄዶ ወንጌልን ሰብኮ ብዙዎችን አሳምኖ አጥምቋል፡፡ በዚህም ጊዜ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በባኮስ እየተሰጠ የነበረውን የወንጌል ብርሃን የበለጠ እንዲበራ አድርጓል፡፡ ከጃንደረባውም ጋር ሆነው በብዙ ቦታዎች አብረው ወንጌልን ሰብከው አምልኮተ ጣዖትን አጥፍተዋል፡፡
ከዚህም በኋላ ባኮስ ወደ የመን በመሄድ በዚያም ክርስትናን በማስተማር ብዙዎችን አሳምኖ ካጠመቀ በኋላ ወደ ፐርሺያ ከዚያም ወደ ሕንድ በመሄድ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሟል፡፡ በመጨረሻም ጥንት ታፕሮባና (taprobana) ዛሬ ሲሎን በምትባለው ደሴት ወንጌልን በማስተማር ላይ እያለ በሰማዕትነት እንዳረፈ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ (lives of the most eminent fathers of the church, page 87) በሌላም በኩል ሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከመጠመቁ በፊት 35 ዓመት ከተጠመቀ በኋላ ደግሞ 41 ዓመት ኖሮ በኢየሩሳሌምም 3 ዓመት ተቀምጦ ወንጌልን ዞሮ ካስተማረ በኋላ በመጨረሻ በ79 ዓመቱ ጥር 18 ቀን በሰሜን ተራራዎች ላይ ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት ቦታ እንደተሰወረ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ጽፈዋል፡፡

የቅዱስ አቤላክ (ባኮስ) ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!




Like
Comment
Share