Wednesday, June 19, 2019

ሰኔ 13 እና 14


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን

<3 ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)

ሰኔ 13 እና 14

+ ከታላቁ ጻድቅ ከቅዱስ ኤጲፋንዮስ ጋር በታናሽነቱ በአባ ኤስድሮስ ገዳም መንኩሶ በታላቅ ተጋድሎ የኖረው የኢየሩሳሌሙ ቅዱስ አባ ዮሐንስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ዮሐንስም በሹመቱ ሳለ ገንዘብን በመውደድ ጌታችንን ቢያሳዝነው ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዐይኖቹን አሳውሮ በኋላም እንደገና መልሶ አንድ ዐይኑን በማብራት በተአምራት ወደ ንስሓ የመለሰው ነው፡፡

+ ዳግመኛም በዚኽች ዕለት የሄኖስ ልጅ ቃይናን የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ቃይናንም 170 ዓመት ኖሮ መላልዔልን ወደለደው፡፡ መላልዔልንም ከወለደው በኋላ 740 ዓመት ኖረ፡፡ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ፡፡ የቃይናንም መላ ዘመኑ 910 ዓመት ሲሆነው በዚህች ዕለት ዐረፈ፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡

+ + + + +
አቡነ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም፡- ይኸውም ቅዱስ የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ሲሆን ከታላቁ ጻድቅ ከአቡነ ኤጲፋንዮስ ጋር በታናሽነቱ በአባ ኤስድሮስ ገዳም መንኩሶ በታላቅ ተጋድሎ ይኖር የነበረ ነው፡፡ የእርሱም ደግነቱ፣ ትሩፋቱ፣ ቅድስናውና ታላቅ ተጋድሎው በቦታው ሁሉ ተሰማ፡፡ ከዚህም በኋላ አቡነ ኤጲፋንዮስን በቆጵሮስ ሀገር ኤጲስቆጶስ አድርገው ሲሾሙት አቡነ ዮሐንስን ደግሞ የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ አድገው ሾሙት፡፡

አቡነ ዮሐንስም በሹመት በነበረ ጊዜ ሰይጣን በገንዘብ ፍቅርና በዚህ ዓለም ክብር አሳተው፡፡ የቀድሞ ግብሩን እረስቶ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች የማይራራ ሆነና ቁራሽ እንጀራን እንኳን የማይሰጣቸው ሆነ፡፡ ይልቁንም ለራሱ ብዙ ገንዘብ ሰብስቦ ለማዕዱ የሚመገብበትን የወርቅና የብር ሣህን አሠራና በድሎት የሚኖር ሆነ፡፡
አቡነ ኤጲፋንዮስም ይህን በሰማ ጊዜ የአቡነ ዮሐንስን የቀድሞውን ተጋድሎውንና የዓለም መናኒነቱን፣ ፍቅሩንም አስታውሶ እጅግ አዘነ፡፡ እርሱም ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ መንፈሳዊ ወንድሙና ወዳጁ ነበር፡፡ ስለዚህም ብፁዕ ኤጲፋንዮስ ከቆጵሮስ ተነሥቶ ወደ ኢየሩሰሌም ወደ አቡነ ዮሐንስ መጣ፡፡ ከስሕተቱ ይመልሰውና በጥበብ ያድነው ዘንድ አስቦ የጌታችን መቃብር ባለበት ቤተ መቅደስ ለመስገድ እንደመጣ ነገረው፡፡ በተገናኙም ጊዜ አቡነ ዮሐንስ አቡነ ኤጲፋንዮስን ወደ ቤቱ አስገብቶ ማዕድ አዘጋጀለት፡፡ በማዕዱም ላይ በወርቅና በብር ያሠራቸውን ሣህኖቹን አስቀመጠ፡፡ አቡነ ኤጲፋንዮስ ከእርሱ ዘንድ ወጥቶ ወደ አንዱ ገዳም ሄዶ አደረ፡፡ ወደ አቡነ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ መልእክት ላከ፡- ‹‹ወንድሜ ሆይ ከቆጵሮስ ሀገር ሽማግሎችና የሕዝቡ መምህራን ወደ እኔ መጥተዋልና በእነርሱ ፊት ታከብረኝ ዘንድ ከወርቅና ከብር ያሠራሃቸውን የማዕድ ዕቃዎችህን ይመገቡባቸው ዘንድ እንድትክልኝ›› ብሎ መልእክት ላከበት፡፡ አቡነ ዮሐንስም የከበሩ ዕቃዎቹን ላከለት፡፡

አቡነ ኤጲፋንዮስም የከበሩ የማዕድ ዕቃዎቹን ወስዶ ሸጣቸውና ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች መጸወተው፡፡ ሁለቱም በተገናኙ ጊዜ አቡነ ዮሐንስ ‹‹የላኩልህን የከበሩ የማዕድ ዕቃዎቼን መልስልኝ›› አለው፡፡ አቡነ ኤጲፋንዮስም ‹‹እሺ›› አለው፡፡ በሌላ ጊዜም እስከ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ ጠየቀው፡፡ በአንዲት ዕለትም የጌታችን መቃብር ካለበት ቤተ መቅደስ ሲወጣ አግኝቶ ያዘውና ‹‹ንብረቶቼን ካልሰጠኸኝ›› ብሎ ያዘው፡፡ አቡነ ኤጲፋንዮስም ወደ ጌታችን ቢጸልይ የአቡነ ዮሐንስ ሁለት ዐይኖቹ ወዲያው ታወሩ፡፡ እርሱም እጅግ ደንግጦ ይቅር ይለው ዘንድ አቡነ ኤጲፋንዮስን ለመነው፡፡ አቡነ ኤጲፋንዮስም የእውነት መጸጸቱን አይቶ አንዲቱን ዐይኑን አበራለት፡፡ እንዲህም አለው፡- ‹‹ነፍስህን ታስብ ዘንድ አንዲቷን ዐይንህን ዕውር እንደሆነች ትቀር ዘንድ ጌታችን ትቶልሃል›› ብሎ ገሠጸው፡፡ ‹‹እነሆ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቀድሞ ድካምህንና ተጋድሎን አስቦ እራርቶልሃልና ከስሕተትህም አድኖሃል›› አለው፡፡
ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ አቡነ ዮሐንስ ከእንቅልፉ እንደነቃ ሆኖ የቀድሞ መልካም ሥራውንም መሥራት ጀመረ፡፡ ምንም ሳያስቀር ጥሪቱን ሁሉ አውጥቶ በመሸጥ መጸወተው፡፡ ተጋድሎውንም እንደበፊቱ በጽኑ ጀመረ፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን የመፈወስ ሀብት ሰጠው፡፡ ብዙ አስገራሚ ተአምራትን እያደረገ ወንጌልን እየሰበከ ብዙ ካገለገለና ጌታችንም ታላቅ ቃልኪዳን ከገባለት በኋላ በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፈ፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + +

ሰኔ 14-የከበሩ ቅዱሳን አክራ፣ ዮሐንስ፣ አብጥልማ እና ፊሊጶስ በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡ እነዚህም አራት የከበሩ ቅዱሳን በጌታችን ስም ሰማዕት ይሆኑ ዘንድ በምክር ተስማሙ፡፡ አክራና ፊሊጶስ ወንድማማቾች ሲሆኑ እነርሱም የከበሩ ባለጸጎች ናቸው፡፡ ዮሐንስና አብጥልማ ግን የከበሩ ቀሳውስት ናቸው፡፡ አራቱም ሰማዕት ይሆኑ ዘንድ ከተስማሙ በኋላ ቀርጥስ ወደሚባል አገር ሄደው በከሃዲው መኮንንነ ፊት ቆመው የጌታችንን አምላክነት መሰከሩ፡፡ መኮንኑም በቀስት እንዲነድፏቸው አዘዘ፡፡ ነገር ግን ቀስቶቹ ሳይነኳቸው ቀሩ፡፡
ዳግመኛም በእቶን እሳት ውስጥ ጨመሯቸው፣ ጌታችንም መልአኩን ልኮ አዳናቸው፡፡ ከዚህም በኋላ በፈረሶች ጅራት ላይ አሥረው ከቀርጥስ እስከ ይምንሑር አገር ድረስ ጎተቷቸው፡፡ አሁንም ጌታችን ፈውሳቸውና ምንም ጉዳት እንዳላገኛቸው ሆኑ፡፡ ከዚህም በኋላ መኮንኑ ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ ራስ ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጧቸው አዘዘ፡፡ እንደትእዛዙም ከይምንሑር ከተማ አውጥተው በሰይፍ አንገታቸውን ቆረጧቸውና የሰማዕትነታቸው ፍጻሜ ሆነ፡፡ እነርሱም የክብርን አክሊል ተቀዳጁ፡፡
ፃ ከምትባል አገር ሰዎቸ መጥተው የቅዱስ አክራን ሥጋ ወሰዱ፡፡ ከይምንሑር ከተማ የመጡ ሰዎች ደግሞ የቅዱስ ፊሊጶስን፣ የቅዱስ ዮሐንስንና የቅዱስ አብጥልማ ሥጋቸውን ወስደው ለሁሉም የተዋቡ አብያተ ክርስቲያናትን ሠርተውላቸው የሰማዕታትን ሥጋቸውን በውስጣቸው አኖሩ፡፡ ከቅዱሳኑም ሥጋ አስገራሚ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/tewadhdohaimanotachin
https://ttewahdo.blogspot.com/

Sene 12- Enkwan Aderesachu

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን






ሰኔ 12-ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የሚበር ንሥረ አርያም የሚባል ውዳሴው እንደ ማር የጣፈጠ ንዑድ ክቡር የሆነ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል አፎምያን ያዳነበት ዕለት ነው፡፡ ዳገመኛም ይኽች ዕለት የባሕራንን የሞት ደብዳቤ ቀዶ እርሱን ለታላቅ ክብር ያበቃባት ዕለት ናት፡፡


+ ዳግመኛም ቅዱስ እለእስክንድሮስ አንድን ቤተ ጣዖት አፍርሶ ከቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ ታቦተ ሚካኤልን አግብቶ በዓሉን በደስታ በሐሴት ያከበረባት ዕለት ናት፡፡


+ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶ ሰባቱ ሰማያትን ካያሳየውና በጌታችን ፊት አቅርቦት ካስባረከው በኋላ ጌታችንም በቅዱስ ቃሉ ‹‹ሕዝቦቼ የመከራና የሥቃዬን ቦታ ለማየት ኢየሩሳሌም በመሄድ በመንገድ እየቀሩ ስለሆነ አሁን ግን አንተ በሀገረ ሮሀ ኢየሩሳሌምን ትሠራለህ›› በማለት የቤተ መቅደሶቹን አሠራር በዝርዝር የነገረው ጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ላሊበላ ዕረፍቱ ነው፡፡


+ ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ የክርስትና ጥምቀትን ያጠመቀው በኋላም ዲቁናና ቅስና የሾመው የከበረ አባ ዮስጦስ ዕረፍቱ ነው፡፡ እርሱም በቅዱስ ማርቆስ መንበር ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት 6ኛ ሆነ፡፡


+ + + + +


ሚካኤል ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ሚ-መኑ' ካ-ከመ' ኤል- አምላክ ማለት ሲሆን በአንድነት ሲነበብ መኑ ከመ አምላክ (እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው) ማለት ነው፡፡ አንድም ለእግዚአብሔር አሸናፊ ድል አድራጊ የቸርነትና የርህራሄ መገኛ መዝገብ ማለት ነው፡፡


ይህ ታላቅ መልአክ ዮሐንስ ወንጌላዊ በራዕዩ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ›› ብሎ ከተናገረላቸው መላእክት ውስጥ የሚመደብ ሲሆን የሰባቱም ሊቃነ መላእክት አለቃ እንዲሆን እግዚአብሔር መርጦ ሹሞታል፡፡ ይህ ታላቅ መልአክ ያደረጋቸው የሠራቸው እጅግ ብዙ የሆኑ ተአምራት አሉት፡፡ ስለዚህ ስለ ታላቁ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ክብር፤ ጠባቂነትና አማላጅነት ከአባቶቻቸው የተማሩትን በኑሮአቸው ያዩትን አባቶቻችን ጽፈዋል፡፡ ስለ ቅዱስ ሚካኤል ከጻፉት አባቶች መካከል የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል፡- ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ኤዎስጣቴዎስ ዘአንፆኪያ፣ ቅዱስ መቃርዮስ፣ ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እና የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አባዲማቴዎስ ናቸው፡፡ እኛም የአባቶቻችንን አንደበት አንደበታችን አድርገን በኅዳር 12 ክቡር ገናና የሆነ ቅዱስ ሚካኤል ካደረጋቸውና ከሠራቸው ብዙ ተአምራት ውስጥ የተወሰኑትን በመልአኩ ተረዳኢነት እንዲህ ብለን እንናገራለን አንጽፋለን፡፡


ጥንተ ነገሩ እንዲህ ነው፡- ንግስት ክሌዎፓትራ ‹‹ሳተርን›› ለሚባለው ጣዖት የሠራችው ቤተ ጣዖት በእስክንድርያ ነበር፡፡ ይህ ቤተ ጣዖት እስከ እስክንድርያው ፓትርያርክ እለ እስክንድሮስ /312 - 326/ ዘመን ድረስ ነበር፡፡ እለ እስክንድሮስ ሊያጠፋው ሲነሣ ሕዝቡ ከልቡ ገና የአምልኮ ጣዖት ስላልጣፋ "18 ፓትርያርኮች ያልነኩትን አንተ ለምን ታፈርስብናለህ?" ብለው ተቃወሙት፡፡ እለ እስክንድሮስም ሕዝቡን መክሮና አስተምሮ የሳተርን በዓል ይውልበት በነበረው ዕለት የቅዱስ ሚካኤልን በዓል እንዲያከብሩ አውጆ ቤተ ጣዖቱንም በቅዱስ ሚካኤል ስም ሰይሞ ቤተክርስቲያን አደረገው፡፡
ሕዝቡ በየዓመቱ መሥዋዕት እየሠው ተረፈ መሥዋዕቱን እየተመገቡ እየዘፈኑ እያጨበጨቡ ያከብሩ ነበር፡፡ ታላቁ ጻድቅ ንጉሥ ቁስጠንጢኖስ "አብያተ ጣዖታት ይዘጉ አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ" ብሎ ካወጀ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት እለ እስክንድሮስ ቤተ ጣዖቱን አፍርሶ ከቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ ታቦተ ሚካኤልን አግብቶ በዓሉን በደስታ በሐሴት አሳለፉት፡፡ እለ እስክንድሮስም ሕዝቡን የጣዖቱን በዓል ተው "ይህን የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል አክብሩ" ብሎ በየዓመቱ በዚህ ቀን በዓል እንዲሆን ሥርዓት ሠራላቸው፡፡ ይህንንም የቅዱስ ሚካኤልን በዓል ከሚያከብሩ ምእመናንን አንዱ የባሕራን አባት ነበር፡፡

እርሱም እግዚአብሔርን እጅግ አድርጐ የሚፈራ ወር በገባ በየዐሥራ ሁለቱ ቀን የቅዱስ ሚካኤልን ዝክሩን የሚዘክርና ይልቁንም በኅዳር ዓሥራ ሁለትና በሰኔ ዓሥራ ሁለት ቀን በታላቅ ክብር የሚያከብር አንድ ሰው ነበር። ለዚህ እግዚአብሔርን ለሚፈራ ሰውም ርኅራኄ የሌለው በእርሱም ላይ ጥላቻ ያደረበት አንድ በለጸጋ ጐረቤት ነበረው፡፡ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል በሚያከብርበት ጊዜ ሁሉ ይዘብትበት ይሳለቅበት ነበር። ይህ እግዚአብሔርን ለሚፈራ ሰውዬ በዚህ ዓይነት በጐ ሥራ ብዙ ጊዜ ከኖረ በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም ያርፍ ዘንድ የሞቱ ጊዜ ቀረበ። ሚስቱንም ጠርቶ "በጐ ስራ ከመሥራት ለድኃ ከመመጽወት ቸል አትበይ የቅዱስ ሚካኤልንም በዓል በየወሩ ከማክበር አትቦዝኝ ይልቁንም በኅዳር ዓሥራ ሁለትና በሰኔ ዓሥራ ሁለት ቀን ከፍ ባለ ሥነ ሥርዓት እንድታከብሪ አደራ እልሻለው" አላት፡፡ በሚሞትበትም ጊዜ ሚስቱ ፀንሳ ነበር። ይህም ደገኛ ሰው በሰላም ዐረፈና ፍጹም መንግሥተ ሰማያትን ወረሰ። 

ከዚህም በኋላ ሚስቱ የመውለጃዋ ጊዜ ተቃርቦ ነበርና ምጥ ይዟት በታላቅ ጭንቅ ላይ እንዳለች "አንተ የእግዚአብሔር መልአክ ሆይ በእኔ ላይ ይቅርታን አውርድ ከዝህ ከደረሰብኝም ጭንቅ ይገላግለኝ ዘንድ ስለኔ እግዚአብሔርን ለምንልኝ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ባለሟልነት ተሰጥቶሃልና" እያለች ለመነች። ይህንንም በምትልበት ጊዜ ያለችበት ቤት በብርሃን ተመላ ከጭንቋም ዳነችና መልኩ በጣም ያማረ ልጅ ወለደች። የእግዚአብሔር መልእክተኛ ቅዱስ ሚካኤልም ከሰማይ ወርዶ ያን ሕፃን ባረከውና "ቸርነት ርኅራኄ የሌለውን የዚህን ባለጸጋ ገንዘብና ሀብት እርሻውንም ሁሉ ይህ ሕፃን እንዲወርስ እግዚአብሔር አዟል" አለ። ያን ጊዜ ያ ባለጸጋ በሴትዮዋ ቤት መስኮት አጠገብ ሆኖ ሁኔታውን ሁሉ ይመለከት ነበርና ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ልቡ በታላቅ ኅዘን ተነካ፤ ሕፃኑንም የሚገድልበትን ምክንያት ይፈልግ ጀመር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በቅዱስ ሚካኤል ጸሎት ብላቴናውን ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቀው ነበር።

 ብላቴናውም ዓሥር ዓመት በሆነው ጊዜ እናቱ በጣም ችግር ፀናባት፡፡ በዚህን ጊዜ እምነት የጐደለው ያ ባለጸጋ "አንቺ ችግረኛ ስለሆንሽ ይላከኝ ያገለግለኝ ዘንድ ልጅሽን ስጭኝና ምግቡንና ልብሱን ምንም ሳላጐድል ተንከባክቤ አኖረዋለው ለአንቺም ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሻለው" አላት። ይህንንም ባላት ጊዜ ስለ ችግሯ በጣም በመደሰት ልጅዋን ሰጠችውና ሃያውን ወቄት ወርቅ ተቀበለች፡፡ ብላቴናውንም በወሰደ ጊዜ እንግዲህ ሃሳቤ ሁሉ ዛሬ ተፈጸመልኝ እያለ በጣም ደስታ ተሰማው፡፡ ከዚህ በኋላ በልጅ ቁመት ልክ ሳጥን አሠርቶ ሕፃኑን በሣጥኑ ውስጥ አግብቶ በላዩ ላይ ቆለፈበትና ሣጥኑን ወስዶ ከባሕር ጨመረው፤ እንዲሁም የሣጥኑን ቁልፍ መክፈቻ አብሮ ወረወረው። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ያ ሣጥን ሳይሰጥም በባሕሩ ላይ እየተንሳፈፈ ከዚያች አገር ርቃ ወደምትገኝ የባሕር ወደብ ደረሰ።
በባሕሩ አካባቢ በጎቹን አሰማርቶ የሚጠብቅ አንድ ሰው ነበርና ያንን ሣጥን ባየው ጊዜ ከባሕሩ አወጣውና ወደ ቤቱ ወሰደው። እቤቱም በደረሰ ጊዜ "ይህን ሣጥን በምን እከፍተዋለሁ?" እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ ተመልሶ ወደ ባሕሩ ይሄድ ዘንድ እግዚአብሔር አሳሰበው፤ በሄደም ጊዜ አንድ ዓሣ የሚያጠምድ ሰው አገኘና ዓሣ አጥማጁን "በኔ ስም መረብህን ወደ በሕር ጣልና የተሠገረው ዓሣ ለኔ ይሆናል ዋጋውን ግን እከፍልሃለው" አለው፡፡ ዓሣ አሥጋሪውም እንደ ተነጋገሩት መረብን ከባሕር ቢጥል ታላቅ ዓሣ ተያዘና ለሰውየው ሰጥቶት ዋጋውን ተቀበለ። እሱም ያንን ዓሣ ከቤተሰቦቹ ጋር ጠብሶ ይበላ ዘንድ በችኮላ ወደ ቤቱ ሄደና ያሣውን ሆድ ቢሰነጥቀው የዚያን የሣጥን ቁልፍ መክፈቻ አገኘ፡፡ በዚያን ጊዜ ይህ መክፈቻ የዚህ ሣጥን ቁልፍ መክፈቻ መሆን አለበት ሲል አሰበና ቁልፉን ለመክፈት ቢሞክር ወለል ብሎ ተከፈተ። በዚህም እየተደነቀ ሳለ ሣጥኑን ቢከፍተው ያ ባለ ፀጋ ሊገድለው ያሰበውን ሕፃን በሣጥኑ ውስጥ አገኘው። ባየውም ጊዜ እጅግ ተደስቶ በባሕር ውስጥ ስላገኘው ስሙን "ባሕራን" ብሎ ሰየመውና እንደ ልጁ አድርጐ ይንከባከበው ዘንድ ወሰነ፡፡
ከባሕራን ሀገር የበግ ጠባቂው አገር የዓሥር ቀን ጐዳና የሚያስኬድ ርቀት ነበረው። ከብዙ ዓመታት በኋላ ያ ባለ ጸጋ ሰው ለንግድ ከሀገሩ ወጣ፡፡ በጉዞውም ላይ ሳለ ፀሐይ ስትገባ ከዚያ የበግ ጠባቂው ዘንድ ደረሰ። በግ ጠባቂውንም "ወንድሜ ሆይ ባንተ ዘንድ የማድርበት ቢኖር ታሳድረኝ ዘንድ እለምንሃለው፣ ኪራዩንም እከፍልሃለው" ብሎ ጠየቀውና ያ በግ ጠባቂ ወደ ቤቱ አስገባው። ባለጸጋውም ገብቶ ጥቂት ካረፈ በኋላ በግ ጠባቂው ያን ብላቴና ባሕራን ብሎ ሲጠራው በሰማ ጊዜ "ልጅህ ነውን?" ብሎ ጠየቀው። በግ ጠባቂውም "አዎን ይህ አሁን ጐልማሳ ሆኖ የምታየው ወጣት ገና ሕፃን ሆኖ ሳለ በሣጥን ተከቶ ከባሕር ውስጥ ተጥሎ አግኝቼው ወስጄ አሳድጌዋለሁና ልጄ ነው" አለው። ባለጸጋውም በባሕር ውስጥ የጣለው ሕፃን መሆኑንም ስላወቀ ይህንን ነገር በሰማ ጊዜ ፈጽሞ ደነገጠ፤ ይገድለውም ዘንድ ፈለገ፡፡
በበነጋውም መንገዱን ለመሄድ ሲዘጋጅ ልዩ ልዩ ምክንያት (ሰይጣናዊ ሃሳብ) በመፍጠር በግ ጠባቂውን "ወንድሜ ሆይ አንድ የማስቸግርህ ጉዳይ አለኝ ይኸውም በቤቴ የረሳሁት ነገር ስላለ ዕገሊት ወደ ምትባል ሀገር ሄዶ መልእክት ያደርስልኝ ዘንድ ይህን ብላቴና እንድትሰጠኝ ነው የድካሙንም ዋጋ ሃያ ወቄት ወርቅ እከፍላለሁ" አለው።
ያም በግ ጠባቂ ስለ ወርቁ ስጦታ ደስ በመሰኘት ያን ጐልማሳ ጠርቶ "ልጄ ባሕራን ሆይ ይህ ክቡር ሰው ለሥራ ጉዳይ ወደ ቤቱ ሊልክህ ይፈልጋልና መልእክቱን አድርስለት እግዚአብሔር በሰላም ያግባህ" ሲል ጠየቀው፡፡ ልጁም "እሺ መልካም ነው አባቴ ሆይ ያዘዝከኝን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁ ነኝ" አለው። ከዚህም በኋላ ያ ባለጸጋ "ይህችን የመልእክት ደብዳቤ ይዞ ወደ አንተ የመጣውን ስሙ ባሕራን የተባለውን መልእክቷ በደረሰችህ ጊዜ ፈጥነህ ግደለው ገድለህም ሬሣውን ከጉድጓድ ጣለው እኔ በሰላም ተመልሼ እስክመጣ ድረስ ማንም ማን ይህን ምሥጢር አይወቅ" የሚል ጽሑፍ ለሹሙ ጽፎ አዘጋጀ፡፡ እንዲሁም በሹሙና በእርሱ መካከል የሚተዋወቁበትን ማኅተም በደብዳቤው ላይ አትሞ ለባሕራን ሰጠው፡፡ ለመንገዱም የሚሆነው ስንቅ ሰጥቶ ላከው።

ባሕራንም መልእክቱን ለማድረስ ዘጠኝ ቀን ተጉዞ የአንድ ቀን ጎዳና ሲቀረው እነሆ ክቡር የሚሆን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በንጉስ ጭፍራ አምሳል በፈረስ ተቀምጦ ወደሱ ደረሰና ወዴት እንደሚሄድ ጠየቀው፡፡
ባሕራንም "ከአንድ ባለጸጋ ሰው የተጻፈ ደብዳቤ ይዤ እርሱን ለማድረስ ዕገሊት ወደምትባል አገር እሄዳለሁ" አለው። ንዑድ ክቡር የሚሆን ቅዱስ ሚካኤልም "እስኪ የመልእክቱን ደብዳቤ አሳየኝ?" አለው፡፡ ባሕራንም "ጌታዬ ለማንም አታሳይ ብሎኛል" አለው፡፡ መልአኩም "እሺ ያም ባይሆን እንደተጠቀለለ አሳየኝ" አለው፡፡ ባሕራንም አሳየው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም በሞቱ ደብዳቤ ላይ እፍ ቢልበት የሞቱን ትእዛዝ አጥፍቶ የሕይወት ትዕዛዝ ጽፎበታል፡፡ በደብዳቤው ላይ የተጻፈውን የሞት መልእክት ደምስሶ "ከእኔ ከባለጸጋ ዕገሌ የተጻፈ" ይልና "ይህን መልእክት ይዞ ለመጣሰው ዕገሊት የምት ባለዋን ልጄን አጋቡት (ዳሩለት) በዱር የተሰማራውን ከብቴን በቤት ያለውን ሀብቴን በጠቅላላው የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረቴን በሙሉ አውርሼዋለሁና እኔ እስክመጣ ድረስ አትጠብቁ በሄድኩበት ሀገር የምቆይበት ጉዳይ አለኝና፤ በቤቴና በንብረቴ ላይ ሙሉ ሥልጣን ሰጥቼዋለሁና የወደደውን ያደርግ ዘንድ አትከልክሉት ስለዚህም በእኔና በአንተ መካከል የምንተዋወቅበትን ምልክት አድርጌበታለሁ" የሚል ጽሑፍ ጽፎ ሰጠውና "እንግዲህ ወደ ባለጸጋው ቤት ሂድና ይህን መልእክት አድርስ ነገሩ እንዳይገለጽብህ ከእኔ ጋር መገናኘታችንንና የመልእክቱን ጽሑፍ እንደለወጥኩልህ ለማንም አትንገር" ሲል አስጠነቀቀው፡፡ ባሕራንም "እሺ ጌታዬ እንዳዘዝከኝ አደርጋለሁ" ብሎ ጉዞውን ቀጠለና የዚያን የባለፀጋ ቤት እየጠየቀ ከደረሰበት በኋላ ደብዳቤውን ለሹሙ ሰጠው።


ያም ሹም ደብዳቤውን ተቀብሎ ሲያነብ የታተመበት ማኅተም ዕውነተኛ መሆኑን ከአረጋገጠ በኋላ እግዚአብሔር እንዳዘዘው በቤተ ክርስቲያን ደንብ የባለጸጋውን ልጅ በተክሊል አጋባው፣ የሠርጉንም በዓል እስከ ዐርባ ቀን ድረስ በታላቅ ደስታ አከበሩ። ከሠርጉም በዓል ፍጻሜ በኋላ ያ ባለጸጋ ሰው ከሄደበት አገር ወደ ሀገሩ ተመልሶ ገባና በቤቱ አካባቢ ሲደርስ የደስታና የዘፈን ድምፅ ስለሰማ "ይህ የምሰማው ድምፅ ምንድነው?" ሲል ጠየቀ፡፡ ሰዎቹም "ባሕራን የተባለ ጐበዝ ካንተ ዘንድ ልጄን ዳሩለት የሚል ትእዛዝ አምጥቶ ልጅህን አግብቶ በሠርጉ ምክንያት ይዘፍናሉ ይደሰታሉ እነሆ እየበሉና እየጠጡ በቀንና በሌሊት እየዘፈኑ ሲደሰቱ ዐርባ ቀን ሆኗቸዋል በመልእክትህም እንዳዘዝከው ገንዘብህን የወንድና የሴት ባሮችህን በጠቅላላው የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረትህን ሁሉ በሙሉ አስረክበውታል" አሉት።
ያም ባለጸጋ ያህን ቃል በሰማ ጊዜ ከድንጋጤው የተነሳ በታላቅ ቃል በመጮኽ ከመሬት ላይ ተከስክሶ ሞተና ነፍሱን አጋንንት ተረክበው ወደ ሲኦል አወረዷት። ከዚህም በኋላ ባሕራን የተባለ ያ ጐልማሳ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል በየወሩ እያከበረ ዝክሩን እየዘከረ ይኖር ጀመር። በዚያን ጊዜ በጉዞ ላይ ሳለ ተገልጾለት የሞቱን መልእክት ወደ ሕይወት የለወጠለት ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነም አወቀ ተረዳ። ንዑድ ክቡር የሚሆን የመላእክት ሁሉ አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ያደረገው ተአምር ሊቆጥሩት የማይቻል ብዙ ስለሆነ በኛም ላይ ኃይለ ረድኤቱ አድሮብን ይኑር እስከ ዘላለሙ ድረስ አሜን።
+ + +

ቅድስት አፎምያ፡- ቅድስት አፎምያ ሀገሯ ኪልቅያ ነው፡፡ ባለቤቷ አስተራኒቆስ መስፍነ ኪልቅያ ነበረ፡፡ እርሷም በትዳር በነበረችባቸው ዘመናት እግዚአብሔርን ከሚወድ ባለቤቷ ጋር እግዚአብሔርን ስታገለግለው የኖረች ሴት ደገኛ ሴት ናት፡፡ በየወሩ በ29 ቀን የጌታችንን የልደቱን፣ ወር በገባ በ21 የእመቤታችንንና ወር በገባ በ12 የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያደረጉ ነዳያንን ይጎበኙ ነበር፡፡

ባለቤቷ አስተራኒቆስ ከዚህ ዓለም የሚያርፍበት ጊዜ እንደደረሰ ባወቀ ጊዜ ይሰጡት የነበረውን ምጽዋት እና የሦስቱን በዓላት መታሰቢያ ማድረግ እንዳታስታጉል ከአደራ ጋር አዘዛት፡፡ እርሷም የመልአኩን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ያሥልላት ዘንድ ባለቤቷን ጠይቃ አሠርቶ ሰጣት፡፡ በከበረ ቦታም አኖረችው፡፡ ባሏ ካረፈ በኋላ ያዘዛትን መንፈሳዊ ሥራ ከወትሮው አስበልጣ መሥራት ቀጠለች፡፡ ባሏም ታሞ ሞቶ ከሀብቷ ከንብረቷ እየሰጠች እየመጸወተች በጾም በጸሎት ተወስና ትኖር ነበር፡፡ ሰይጣን ለምቀኝነት አያርፍምና ደግ መነኩሴ መስሎ አጋንንትን መነኮሳይያት አስመስሎ መጥቶ ከደጅ ሆኖ አስጠራት፡፡ እርሷም "ከቤት ገብታችሁ በቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ፊት ጸልዩልኝ" አለቻቸው፡፡ ሰይጣናቱም "እኛማ በነግህ ጸልየናል?" አሏት፡፡ ቀጥሎም ሰይጣን "...እንደው አንቺ ግን ይህ ሁሉ ጾም ጸሎት ምን ያደርገልሻል? ሀብትሽን ሰጥተሸ መጨረስሽስ ስለምንድን ነው? በዚያ ላይ አንቺ ስትደክሚ የሚደግፍሽ ስታረጂ የሚጦርሽ ልጅ የለሽም ሁለተኛ ማግባት ኃጢአት መስሎሻልን? እነ አብርሃም እነ ዳዊ ከብዙ ሴቶች ብዙ ልጆች ወልደው የለምን? አሁንም ቤት ሰሪ ጎመን ዘሪ ልጅ ያስፈልግሻልና ባል አግቢ፣ እሺ በይኝ" አላት፡፡

 ቅድስት አፎምያም "አባ ቆብህ መልካም ነበር ንግግርህ ግን ክፉ ነው፣ አትጹሚ አትጸልዩ ያልከኝ ጌታ ምጽዋት አበድር እመስዋዕት ብሎ የለምን? ሁለተኛ ባል አግቢ ማለትንስ ከምን አገኘኸው? እርግቦች እንኳ ባሎቻቸው ከሞቱባቸው ከሌላ ወንድ አይቀርቡም ታዲያ ጥንቱን በንጽሕና ሊኖር የተፈጠረ ሰው ሁለተኛ አላገባም ቢል ዕዳ ፍዳ ሊሆንበት ነውን?" ብላ ሞገተችው፡፡

 የሰው ልጆች ጠላት የሆነው ሰይጣንም በመልካም አገልግሎት ስትበረታ አይቷታልና ዝም ብሎ ሊተዋት አልወደደም፡፡ ከላይ እንዳየነው በመጀመሪያ ባል ሳታገባ ማገልገሏን ትታ ሌላ ባል አግብታ ልጅ ወልዳ እንድትኖር በብዙ ማባበል ጠየቃት፡፡ ባሏ መንግሥተ ሰማያትን ስለወረሰ ምንም ምጽዋት እንደማይሻ አስመስሎ ነገራት፡፡ ቅድስት አፎምያ ግን ዳግመኛ ትዳር ላለመመሥረት ቃል ኪዳን እንደገባች ርግብንና ዖፈ መንጢጥን አብነት አድርጋ እነርሱ እንኳ በሕይወት ዘመናቸው ከአንድ ባል ውጪ ሌላ ባል እንደማያውቁ በመጥቀስ አሳቡን እንደማትቀበለው ገለጸችለት፡፡ ሰይጣንም አስመሳይ መሆኑ አላዋጣ ሲለው ማንነቱን ቀይሮ ሊያንቃት ቢሞክር የእግዚአብሔርንና የቅዱስ ሚካኤልን ስም ጠርታ አባረረችው፡፡ እርሱም ተመልሶ መጥቶ እንደሚያጠፋት ዝቶባት እንደአቧራ በኖ እንደ ጢስም ተኖ ጠፋ፡፡
በሰኔ 12 ቀን የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያዘጋጀች ሳለች ሰይጣን ብርሃናዊ መልአክ መስሎ መጣ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነ ገልጾ የመጀመሪያውን የመሰለ ከንቱ ምክሩን አሰማምሮ አቀረበላት፡፡ አሳቡንም የእግዚአብሔር ፈቃድና አሳብ እንደሆነ አድርጎ ለማሳመን ሞከረ፡፡ ሰይጣን አስቀድሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በገዳመ ቆሮንቶስ መጻሕፍትን እየጠቀሰ እንደተፈታተነው ሁሉ ቅድስት አፎምያንም ለማሳመንም አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን፣ ዳዊትን የመሳሰሉ ደጋግ አባቶችን ታሪክ እየጠቀሰ ወደ ትዳር እንድትገባ ደጋግሞ ወተወታት፡፡ ቅድስት አፎምያም በእግዚአብሔር ኃይል ጸንታ በቅዱስ ሚካኤልም ተራዳኢነት ታምና "የእግዚአብሔር መልአክ ከሆንክ መንፈሳዊ ማረጋገጫህ የሆነው የመስቀል ምልክት የታለ?" በማለት በምድራዊ ንጉሥና በጭፍራው መካከል የሚኖርን የጋራ መግባቢያ መንገድ ዋቢ አድርጋ ጠየቀችው፡፡ ለጊዜው "በእኛ በመላእክት ዘንድ እንዲህ አይደለም" ብሎ ሊሸነግላትና አቋሟን ሊያስቀይራት ሞከረ፡፡ ከቤቷ ያለ የቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ላይ ያለውን ምልክት አብራርታ የእርሱ ግን ከዛ ጋር አንድነት እንደሌለው አረጋገጠችበት፡፡ በመቀጠልም ከቤቷ ላለው ለቅዱስ ሚካኤል ሥዕል እጅ እንዲነሣ ጠየቀችው፡፡ በዚህ ጊዜ መልኩ ወደ ትክክለኛ ሰይጣናዊ ማንነቱ ተለወጠና ጨለማ ለብሶ እየዛተ አነቃት፡፡ ቅድስት አፎምያም የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልን "ድረስልኝ" እያለች በጠራችው ጊዜ መልአኩም ፈጥኖ በመድረስ ከሰይጣን እጅ አዳናት፡፡

 የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ለሰይጣኑ ተገቢውን ቅጣት ሰጥቶ ቅድስት አፎምያን ባረካት፡፡ የዕረፍት ቀኗ በዚህ ቀን መሆኑን ነግሮ ቤቷን እንድታዘጋጅ አዘዛት፡፡ የበዓሉን ዝግጅት አከናውና ሥጋ ወደሙን ተቀብላ ኤጲስ ቆጶሱንና ካህናቱን እንደየመዓርጋቸው ጠርታ በቤቷ አክብራ ተቀበለቻቸው፡፡ ለነዳያንና ለጾም አዳሪዎች በኤጲስ ቆጶሱና በካህናቱ እጅ ገንዘቧን መጽውታ መንገዷን አሳመረች፡፡ ስለ ኃጢአቷ እንዲጸልዩላት ተማፅና በፊታቸው ተንበርክካ ጸለየች፡፡ ባሏ ያሠራላትን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል አቅፋ ስማ ከተማጸነች በኋላ ሰኔ 12 ቀን በሰላም ዐረፈች፡፡ ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ በጸሎቷ ይማረን!


እጅግ አስገራሚው የቅዱስ ላሊበላ ሙሉ ገድል በክፍል ኹለት ይቀጥላል....


+ + + + + 

ጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ላሊበላ፡- ቅዱስ ላሊበላ ጌታችን የጠጣውን መራራ ሐሞት በማሰብ ሁልጊዜ ዓርብ ዓርብ ኮሶ ይጠጣ ነበር፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ላሊበላን ኢየሩሳሌም ወስዶት በዚያ ያሉ ቅዱሳን መካናትን ሁሉ አሳይቶ አሳልሞታል፡፡ ወደ ሰማይም ነጥቆ ወስዶ ሰባቱ ሰማያትን ያሳየው ሲሆን በጌታችን ፊትም አቅርቦት አስባርኮታል፡፡ ጌታችንም ‹‹ሕዝቦቼ የመከራና የሥቃዬን ቦታ ለማየት ኢየሩሳሌም በመሔድ በመንገድ እየቀሩ ስለሆነ አሁን ግን አንተ በሀገረ ሮሀ ኢየሩሳሌምን ትሠራለህ›› በማለት የቤተ መቅደሶቹን አሠራር በዝርዝር ነግሮታል፡፡ ከነገሠም በኋላ ሱባኤ ገብቶ ቤተመቅደስ የሚሠራበትን ቦታ በጸሎት ሲጠይቅ ዛሬ ቤተ ማርያም ካለችበት ቦታ ላይ የብርሃን አምደ ወርቅ ተተክሎ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ስላየ ቦታው እግዚአብሔር የፈቀደው መሆኑን አውቆ ሥራውን ጀመረ፡፡ ጌታችን ቀድሞ ‹‹እኔ ራሴ ነኝ እንጂ ቤተ መቅደሶቹን የምትሠራቸው አንተ አይደለህም፣ ነገር ግን በአንተ ስም እንዲጠራ ስለፈቀድኩ ሄደህ ሥራ›› ብሎ እንዳዘዘው ቅዱስ ገድሉ ይናገራል፡፡ ላሊበላ ዓሥሩን ቤተመቅደሶች ሲሠራ እርሱ አንድ ስንዝር ሠርቶ እንደሆነ ሌሊቱን ዓሥር ስንዝር ሆኖ ያገኘው ነበር፡፡ ቀንም ሲሠራ ቅዱሳን መላእክት በማይታወቁ ሰዎች አምሳል ሆነው ይራዱት ነበር፡፡ በመጨረሻም ጌታችን በገሃድ ተገልጦለት በቦታው ላይ እጅግ አስገራሚ ቃልኪዳኖችን ሰጥቶታል፡፡
ከ10ኛው እስከ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (920-1253 ዓ.ም ድረስ) በላስታ ቡግና ምድር የነገሡ የላስታ ቡግና ተወላጅ የሆኑ የኢትዮጵያ ቅዱሳን ነገሥታት የንግሥናቸው መጠሪያ ‹‹የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት›› ወይም ‹‹የላስታ መንግሥት›› በመባል ይታወቃል፡፡

  የላስታ ነገሥታት የዘር ሀረጋቸው ከንጉሥ ሰሎሞን ዘር ሲያያዝ የመጣ ነው፡፡ ከላስታ (ከዛጉዌ) ነገሥታት መካከል ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ገብረ ማርያም፣ ቅዱስ ላሊበላና ቅዱስ ነአኵቶለአብ እነዚህ አራቱ ነገሥታት እንደ መልከጼዴቅ (ዘፍ 14፡18) ክህነትን ከንግሥና፣ ቅድስናን ከንጽሕና ጋር አንድ አድርገው በመያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅድስና አገልግለው አልፈዋል፡፡ በንግሥናቸው ሀገራችንን በመልካም ሥራና በቅድስና ከማስተዳደራቸው በተጨማሪ ቅዱሳን ጻድቃን ሆነው እግዚአብሔርን በብዙ ድካም በመልካም ተጋድሎአቸው ያገለገሉና አገልግሎታቸውም ሆነ ቅድስናቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ስለተመሰከረላቸው ጌታችን የሰጣቸውን ቃልኪዳን መሠረት በማድረግ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን የቅድስና ማዕረግ ሰጥታ፣ በስማቸው ቤተክርስቲያን አንጻ፣ ጽላት ቀርፃ በዓላቸውን እያከበረች መታሰቢያቸው ተጠብቆ ለዘለዓለም እንዲኖር አድርጋለች፡፡


እኛ ኢትዮጵያውያን የቅዱስ ላሊበላን እጅግ ድንቅ የሆኑ ሥራዎቹን ዓለም ከሚመለከትበት የተለየ መንፈሳዊ ዐይን ሊኖረን ይገባል፡፡ ስለዚህም የቅዱስ ላሊበላን የቅድስና ሕይወትና ከእግዚአብሔር ጋር ስለነበረው ግንኙነት ገድለ ቅዱስ ላሊበላን መነሻ በማድረግ ብዙ ነገሮችን ቀጥሎ እናያለን፡-

1. ቅዱስ ላሊበላ ከአባቱ ዣን ስዩምና ከእናቱ ኪርወርና ጌታችን በተወለደበት ዕለት ታኅሣሥ 29 ቀን 1101 ዓ.ም በላስታ ቡግና ወረዳ ልዩ ስሟ ሮሀ በተባለችው ሥፍራ ተወለደ፡፡ የልደቱን ነገር አስቀድሞ ቅዱስ ሚካኤል ለእናቱ ነግሯት ነበርና በተወለደ ጊዜ ብዙ ነጫጭ ንቦች መጥተው በሰውነቱ ላይ አርፈው እንደ ማር እየላሱት ስለታዩ እናቱ ‹‹ልጄን ንብ ዘበኛ ሆኖ ይጠብቅልኛል›› ስትል ስሙን ‹‹ላል ይበላል›› ብላዋለች፡፡ ላል በአገውኛ ንብ ማለት ነው፡፡ በጊዜ ብዛት በተለምዶ ነው ‹‹ላሊበላ›› ተብሎ መጠራት የተጀመረው፡፡ ንቦቹ ግን ሥጋዊ ንቦች ሳይሆኑ በንብ የተመሰሉ መላእክት ናቸው፡፡ ንጉሥ መሆኑን እያመለከቱ የሃይማኖትና የምግባር ማር ከእርሱ ይቀዳል ሲሉ በንብ ሠራዊት ተመስለው ሰውነቱን ላሱት፡፡ እንደ ዮሐንስና እንደ ኤርምያስም በእናቱ ማኅፀን ሳለ ነው መንፈስ ቅዱስ የሞላበት፡፡
ከዚህ ቀጥሎ በገድሉ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ አስደናቂ ነገሮችን እናያለን፡፡ 

2. ቅዱስ ላሊበላ ያነጻቸውን አብያተ ክርስቲያናት መመልከት ያለብን በቅርስነታቸውና በቱሪስት መስህብነታቸው ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የተገኙ ብቸኛ መንፈሳዊ ሀብቶቻችን መሆናቸውን ነው፡- ስለ ቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ከማንሳታችን በፊት በመጀመሪያ እውነተኛ የሕይወት ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን መመልከት የግድ ያስፈልጋል፡፡ ቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ቀድሞ በሕገ ልቡና ከዚያም በሕገ ኦሪት እግዚአብሔርን ስታመልክ ኖራለች፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ሐዋርያቱ እንኳን ለስብከት ከኢየሩሳሌም ሳይወጡ ነው በ34 ዓ.ም በራሷ ሐዋርያ በጃንደረባው ባኮስ አማካኝነት በክርስቶስ ማመንንና ጥምቀትን ወደ ሀገሯ ያመጣችው፡፡ የዚህ ደግሞ ምስክሩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ 1ኛ ነገ 10፡1-13፣ ሐዋ 8፡26-40፡፡ በዚህ መረጃ መሠረት ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ እስከ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ወደ ኢየሩሳሌም እየሔዱ ሃይማኖታዊ ጉዞ ያድርጉ ነበር፡፡

ከ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ግን ከኢትዮጵያ ተነስቶ በሱዳን በግብፅ አድርጎ ወደ ኢየሩሳሌም በእግርና በእንስሳት ጉዞ ለማድረግ የመንገዱ አድካሚነትና በረሃማነት የሚባክነው ጊዜ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ተሻግሮም እስከ ግብፅና ሱዳን ድረስ የእስልምና ሃይማኖት ስለተጠናከረ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ወደ ኢየሩሳሌም ለመጓዝ አስቸጋሪ ስለሆነባቸው ለሃይማኖታዊ አምልኮና ስግደት ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርጉት ጉዞ ተቋረጠ፡፡ ይህ ሁኔታም ሲያያዝ እስከ ቅዱስ ላሊበላ ዘመን ደርሷል፡፡

ቅዱስ ላሊበላም የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ወደ ኢየሩሳሌም ያደርጉት የነበረው ጉዞ በመቋረጡ በእጅጉ እያዘነ ተግቶ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር፡፡ የኢየሩሳሌምንም አምሳያ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናትን በሀገሩ ለመሥራት ይመኝ ነበር፡፡ ጥቂት ነገር ሲለምኑት አብዝቶ መስጠት ለእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነውና ላሊበላ ምድራዊ ኢየሩሳሌምን በሀገሩ ለመሥራት ሲያስብ ልዑል እግዚአብሔር በጥበቡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ (2ኛ ቆሮ 12፡1-7) ወደ ሰማይ አሳርጎት ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን አሳይቶታል፡፡ ጌታችንም ‹‹ሕዝቦቼ የመከራና የስቃዬን ቦታ ለማየት ኢየሩሳሌም በመሄድ በመንገድ እየቀሩ ስለሆነ አሁን ግን አንተ በሀገረ ሮሐ ኢየሩሳሌምን ትሠራለህ›› በማለት የቤተ መቅደሶቹን አሠራር ሁሉ በዝርዝር ነግሮታል፡፡ በሰማያዊት ኢየሩሳሌምም ምሳሌ በሀገሩ ላይ ወጥ ከሆኑ የዓለት ድንጋዮች መላእክት እየተራዱት ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያንጽ ነግሮታል፡፡

 3. ጠላት ለክፉ ያሰበውን እግዚአብሔር ለበጎ ያደርገዋል፡- ወደኋላ ተመልሰን የቅዱስ ላሊበላን የልጅነት ሕይወቱን እናንሳ፡- ቅዱስ ላሊበላ እናትና አባቱ ከሞቱበት በኋላ ወደ ጎጃም በመሄድ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን፣ ብሉይና ሐዲስን በደንብ ተምሮ ከጨረሰ በኋላ ወደ ደብረ ሮሐ ተመልሶ መጥቶ ነግሦ ከነበረው ከወንድሙ ከገብረ ማርያም ዘንድ ተቀመጠ፡፡ ‹‹ከገብረ ማርያም ቀጥሎ የሚነግሠው ላሊበላ ነው›› ተብሎ ትንቢት ስለተነገረ ሊያጠፋው ምክንያት ይፈልግበት ነበር፡፡ ለዐፄ ገብረ ማርያም በእናትም በአባትም እኅት የምትሆነው ለላሊበላ ግን በአባት ብቻ እኅት የሆነችው ዮዲት ላሊበላን ለመግደል በማሰብ ቀን ከሌሊት አጋጣሚን ትጠብቅ ነበር፡፡ ቅዱስ ላሊበላም ጌታችን መራራ ሐሞት መጠጣቱንም እያሰበ ሁልጊዜ ዓርብ ዓርብ ከጾምና ጸሎት በኋላ መራራ ኮሶ ይጠጣ ነበርና ይህን አጋጣሚ በመጠቀም አንድ ቀን እንደጠማው አውቃ በጠላ ውስጥ መርዝ ጨምራ ሰጠችው፤ ቅዱስ ላሊበላም መርዝ የተቀላቀለበትን ጠላ ጠጣው፡፡ እርሱ ከመጠጣቱ በፊት ያገለግለው የነበረው ዲያቆን ቀምሶት ወዲያው ሲሞት አየ፡፡ ዲያቆኑ ያስመለሰውን የጠጣው ውሻም ወዲያው ሞተ፡፡ ቅዱስ ላሊበላም ይህን ሲመለከት በሐዘንና በፍጹም ፍቅር ሆኖ ‹‹አገልጋዬ ለእኔ የተዘጋጀውን መርዝ ጠጥቶ እንደሞተ ሁሉ እኔም መሞት ይገባኛል›› በማለት ያን መርዝ ስለወዳጁ ፍቅር ሲል ጠጥቶ ለመሞት ቆረጠና ጠጣው፡፡ ጌታችን በወንጌሉ ስለራሱ ‹‹ስለ በጐቹ ቤዛ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ የሚሠጥ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም›› (ዮሐ 15፡13) ብሎ የተናገረውን ቃል ቅዱስ ላሊበላም ስለ ወዳጁ ሞት ሲል ራሱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ፡፡ ነገር ግን መርዙ እንኳን ሊጎዳው ይቅርና በሆዱ ውስጥ ከልጅነቱ ጀምሮ የነበረበትን የሆድ ሕመም ነቅሎ አወጣለት፡፡ በዚህም ጌታችን በወንጌሉ ‹‹የሚገድል መርዝም ብትጠጡ ምንም አትሆኑም›› (ማር 16፡18) ያለው ቃል ተፈጽሞለታል፡፡ መርዙ ለበጐ ሆኖለት ከሆዱም ውስጥ የነበረው ጥፍሮች ያሉት አውሬ መሰል ፍጡር ወጣለትና የሆድ ሕማሙ ፈጽሞ ተወው፡፡ ያን ጊዜም ቅዱስ ላሊበላ በወቅቱ ለሦስት ቀንም ያህል እንደሞተ ሆኖ የቆየ ቢመስልም ቅዱስ ገብርኤል ግን በመንፈስ ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶ ሰባቱ ሰማያትን ያሳየው ሲሆን በጌታችን ፊትም አቅርቦት አስባርኮታል፡፡ ጌታችንም ቅብዓ መንግሥት ቀብቶት ትልቅ ቃልኪዳን ሰጥቶታል፡፡ 

ጻዲቁ ንጉሥ ቅዱስ ላሊበላ ቅድስናን ከንግሥና፣ ክህነትን ከንጽሕና፣ ጥበብ መንፈሳዊን ከጥበብ ሥጋዊ ጋር አንድ አድርጐ አስተባብሮ የያዘ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ፣ ቅዱሳን መላእክትም ይራዱት እንደነበርና ጌታችንም ትልቅ ቃልኪዳን እንደሰጠው ከቅዱስ ገድሉ ላይ እናገኛለን፡፡ ከጌታችን ዘንድ የተሰጠውንም ቃልኪዳን በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ በዚህም መሠረት፡- 

1ኛ. መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ላሊበላን እየመራው ከላስታ ወደ አክሱም ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም አድርሶ በዚያ የሚገኙትን ቅዱሳት መካናት ሁሉንም ካሳየው በኋላ ‹‹ወደ ሀገርህ ሮሐ ተመልሰህ በእነዚህ ምሳሌ ታንጻለህ›› ብሎታል፡፡ ወደ ሀገሩም ተመልሶ በአሽተን ማርያም ተራራ ላይ ሱባኤ ይዞ በጾም ጸሎት ተወስኖ ሳለ እግዚአብሔር የሚሠራቸውን መቅደሶች በግልጽ በራእይ አሳይቶታል፡፡ 

2ኛ. ከላይ እንዳየነው ለሞት ተብሎ የተሰጠው መርዝ ለሕይወት ሆኖለት በመሬት ላይ ወድቆ ሳለ በነፍስ መልአክ ነጥቆት እስከ ሰባተኛው ሰማይ ጽርሐ አርያም ድረስ ደርሶ በጌታ ፊት ቀርቦ ከጌታ ዘንድ ‹‹እኔ አከበርኩህ ቃሌ አይታበይም፣ ከአንድ ቋጥኝ እነዚያን በራእይ ያሳየሁህን አብያተ ክርስቲያናት ታንጻለህ›› የሚል ቃልኪዳን ተቀብሏል፡፡



 3ኛ. ከኢየሩሳሌምም ተመልሶ የንግሥናውን ዙፋን ከቅዱስ ገብረ ማርያም ከተረከበ በኋላ በተሰጠው መንፈሳዊ ሀብትና ባየው ራእይ መሠረት አብያተ ክርስቲያናቱን አንጾ ከጨረሰ በኋላ በቀኝና በግራው ዓሥር ዓሥር ኪሎ የሚመዝን የዓለት ድንጋይ ተሸክሞ ለ7 ዓመት ሲጾም ሲጸልይ ጌታችን ተገልጦለት ‹‹…ያነጽካቸውን ቤተ መቅደሶች የተሳለመውን ኢየሩሳሌምን እንደተሳለመ አድርግለታለሁ›› የሚለውን የመጨረሻውን ቃልኪዳን ሰጥቶታል፡፡ (ይህን ቃልኪዳኑን መጨረሻ ላይ በዝርዝር እናየዋለን) እነዚህን ሦስት ዋና ዋና ቃልኪዳኖቹን በቅድሚያ ማንሳት የፈለኩበት ምክንያት ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ስለ ቅዱስ ላሊበላ ድንቅ ሥራዎች ከማሰባችንም ሆነ ከመናገችን በፊት በቅድሚያ ስለ ራሱ ስለ ቅዱስ ላሊበላ የቅድስና ሕይወቱና ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት ማወቁ የግድ አስፈላጊ መሆኑን ለመጠቆም ነው፡፡ አሁን አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሆን ተብሎ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቶቹ በቱሪስት መስህብነታቸው ብቻ እየታዩ የቅድስና ታሪካችንም እየተጨፈለቀና መንፈሳዊ እሴቶቻችንንም ለማጥፋትም ጥረት እየተደረገ ስለሆነ እውነተኛውን ነገር በደንብ ማወቅና በእጅጉ መጠንቀቅ ስላለብን ነው ይህን የማነሳው፡፡ ስለዚህ የቅዱስ ላለበላን የቅድስና ሕይወትና ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት ስንረዳ እነዚያ እጅግ ድንቅ የሆኑ ሥራዎቹ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና በሰማያውያን መላእክት እርዳታ የተሠሩ መሆናቸውን እንረዳለን፤ እግዚአብሔርም ለእኛ የሰጠንን ድንቅ የምሕረትና የቃልኪዳን ስጦታዎቻችን መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ ያንጊዜም ውቅር አብያተ ክርስቲያናቶቹን ዓለም ከሚመለከትበት የተለየ መንፈሳዊ ዐይን ይኖረናል፡፡ የቃልኪዳኑም ተጠቃሚዎች ለመሆን መንፈሳችን ይነሳሳል፡፡ በዚህ ደግሞ አሁን ያለውም ሆነ ወደፊት የሚመጣው ትውልድ ታሪኩን ከማጉደፍና ከጥፋት ይጠበቃል፣ አኩሪ ታሪኩንም ጠንቅቆ ለማወቅ መንፈሳዊ ቅናትም ስለሚያድርበት ራሱንም ከውጪው የባሕል ወረራና ጥቃት ይጠብቃል፡፡ በሀገራችን ያሉትን እጅግ ጥልቅ የሆኑ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ምሥጢሮችን ጠንቅቀው የተረዱት እነ ፕሮፌሰር ፓንክረስት ‹‹ክርስቶስ ከነጮች ይልቅ ለኢትዮጵያውያን ቅርበት አለው›› በማለት ምስክርነታቸውን እየሰጡ ባለበት ወቅት የዘመኑ የሀገራችን ወጣት ማንነቱን ጠንቅቆ ቢያውቀው ኖሮ የእነርሱን (የነጮቹን) ባሕል ለመከተል ባልዳዳው ከዘመናዊ ባርነትም ራሱን በጠበቀ ነበር፡፡


4.መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለቅዱስ ላሊበላ ስለ ቤተመቅደሶቹ አሠራር በዝርዝር እንዳስረዳው፡- በተራ ቁጥር ሁለት ላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በቅዱስ ገድሉ ላይ ከገጽ 117-127 ድረስ በጣም በስፋትና በዝርዝር እንደተጠቀሰው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ላሊበላን እስከ ሰባተኛው ሰማይ ድረስ በመላእክት ተነጥቆ በፊቱ እንዲቆም ካደረገው በኋላ ቤተ መቅደሶቹን እንዴት እንደሚያንጽ ቃል በቃል ነግሮታል፡፡ እግዚአብሔር ለኖህ መርከቡን እንዴት እንደሚሠራ ከነልኬቱ ጭምር በዝርዝር እንደነገረው ሁሉ ለቅዱስ ላሊበላም ዝርዝር ሁኔታዎችን ጭምር እንዲህ በማለት ትእዛዝ ሰጥቶታል፡- ‹‹መልአኩም ክብሩ ከሰማያት ሁሉ ክብር ወደሚበልጥ ወደ ሰባተኛው ሰማይ አደረሰው፣ ቅዱስ ላሊበላም ይህንን አይቶ በግንባሩ ተደፋ፣ ከኪሩቤል ዘንድ ይነሳ የሚል ቃል ተሰማና አንዱ ሱራፌል መጥቶ አነሣው፡፡ ልቡንም አጽንቶ አቆመው…እግዚአብሔርም ተናገረው፡- ‹በምድር ላይ ቤተመቅደስ ትሠራልኝ ዘንድ የማሳይህን አስተውል፤ እዝነ ልቡናህንም ግለጥ፡፡ ከሰው ጋር ስለምኖር በሰማያት የምትኖር አባታችን እያሉ ከሚጠሩኝ በሃይማኖት ከተጐናፀፈኝ ስሜን ከሚያመሰግኑ ከመረጥኳቸው ከሕዝብ አንደበት በምመሰገንበት ገንዘብ እኔ ፈጥሬያቸዋለሁና፡፡

ከመጀመሪያይቱ ድንኳን ውስጥ በተሣለው ላይ ምስላቸው የተሠራ ከሚንቀሳቀሱ ከኪሩቤል አምሳል ለሙሴ እንደተናገርኩት አይደለም፡፡ ወዳጄ ሙሴ የመጀመሪያይቱን ድንኳን አርአያ በደብረ ሲና እንዳሳየሁት ድንኳንን እንደሠራ ሁሉ እንደሁ አንተም እንዳሳየሁህ ትሠራ ዘንድ ዕወቅ፣ አስተውል፣ ተጠንቀቅም፡፡ የማሳይህ ግን ለሙሴ እንዳሳየሁት አይደለም፤ መቅደሴን የምትሠራልኝም ሙሴ እንደሠራው አይደለም፤ ሙሴስ ከተፈተለ ልብስና ከእንጨት ድንኳን ሠራ፤ አንተ ግን ለምሰሶውም ሆነ ለመቀኑ ለመድረኩ እንጨትን የምትፈልግ አይደለህም፤ ለጠፈራቸው መማገሪያ ገመድ የምትሻ አይደለህም፣ እንጨትንም ለማገር፣ ለምሰሶዋቸውም ገበታ፣ ለዙሪያቸውም ለማያያዣ ጭቃን የምትፈልግ አይደለህም፡፡ የቤተመቅደሶችን ፈቃድ ሁሉ ከአንድ ቋጥኝ ድንጋይ ትፈጽማለህና፡፡ የማሳይህ እኚህ የቤተ መቅደሶች አኗኗር ከምድር ልብ ውስጥ እስከዛሬ አለ፡፡ ከአሁን ጀምሮ በእጅህ እስኪገለጡም ድረስ በምድር ልብ ይኖራሉ፡፡ በሰው ልጅ ጥበብ ያይደለ በእኔ ሥልጣን ከምድር ልብ ውስጥ ታወጣቸው ዘንድ መረጥሁህ፡፡ ሕዝቦቼ ተወልጄ አድጌ ሞቼ ተቀብሬ ከሞትም የተነሳሁባትን ሀገር ለማየት ኢየሩሳሌም በመሄድ ግማሹም በበረሃ ይቀር ነበር አሁን ግን አንተ ኢየሩሳሌምን በሀገርህ ትሠራለህ፡፡ በማንም እጅ ዳግመኛ ሊሠሩ የማይችሉ ቤተ መቅደሶቼን እንዳሳየሁህ ትሠራለህ፡፡ አንተም እንዳሳየሁህ በልብህ ውስጥ አኑራቸው፡፡ ስትሠራቸውም እየልካቸው ይሁን፤ ከእርዝመታቸውም በላይ ቢሆን፣ ከወርዳቸውም በላይ ቢሆን፣ በመወጣጫቸውም ላይ ቢሆን አንዳች እንዳትጨምር፡፡ ያሳየሁህ እሊህ ዐሥሩ መቅደሶች ከአንዲት ቋጥኝ ድንጋይ ሲወጡ አይተሃልና….› እያለ ጌታችን ሲነግረው ጻዲቁ ንጉሥ “ይህ እንዴት ይሆናል?” በማለት ይጠይቃል፡፡ ጌታም እውነት እልሃለሁ እነዚህ ያሳየሁህ መቅደሶች በሰው ኃይል የሚሠሩ ሆነው አይደለም፤ ጀማሪያቸው ሠሪያቸውና ፈጻሚያቸው እኔ ነኝ ነገር ግን ኃይሌ በአንተ እጅ እንዲገለጽ ለምክንያት ተልከሃል፤ አንተ አነጽካቸው እየተባለ እስከ ዕለተ ምፅዓት ድረስ ስምህ ይጠራባቸዋል…›› እያለ ይቀጥላል የቅዱስ ላሊበላ ገድል፡፡ ቤተ መቅደሶቹንም ለመሥራት ቦታውን ያውቅ ዘንድ ሱባኤ ገብቶ ሳለ ዛሬ ቤተ ማርያም ካለችበት ቦታ ላይ ቅዱሳን መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ታይተውት በቦታው ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መቅደሱን መሥራት ጀመረ፡፡ ዓሥሩን ቤተ መቅደሶች ሲሠራ እርሱ አንድ ክንድ ሠርቶ እንደሆነ ሌሊቱን አድሮ በቀጣዩ ቀን አሥር ክንድ ሆኖ ያገኘው ነበር፣ ቀንም በማይታወቁ ሰዎች አምሳል እየተገለጡ መላእክት ይራዱት ነበር፡፡

5. አንዳንድ ነገሮች ስለ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፡- ቅዱስ ላሊበላ ዓሥሩም ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በጣም በሚያስገርም ሁኔታ በውስጥና በውጭ ያሉት ብዙ ቅርጾች ነገረ ድኅነትን በምሳሌ እንዲወክሉ አድርጎ ነው ያነጻቸው፡፡ የክርስቶስን መከራና በእርሱም የተገኘውን ፍጹም ዘላለማዊ ድኅነት በእያንዳንዱ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዴት አድርጎ በምሳሌ እንዳስቀመጠው እጅግ አስገራሚ ነው፡፡

በላስታ ቅዱስ ላሊበላና አካባቢው የሚገኙ ሌሎች አስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፡- ከአሥሩ የቅዱስ ላሊበላ አስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ የቅዱስ ነአኵቶለአብና የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም አሸተን ማርያም በዋናነት ሕዝበ ክርስቲያኑ የሚጐበኛቸው ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ በላሊበላና አካባቢው ግን እጅግ ጥንታዊና አስደናቂ የሆኑ በጣም በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ሣርዝና ሚካኤል፣ ብልባላ ቂርቆስ፣ ብልባላ ጊዮርጊስ፣ አርባዕቱ እንስሳ፣ ትርኩዛ ኪዳነምሕረት፣ ገነተ ማርያም፣ ቀንቀኒት ሚካኤል እነዚህ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሲሆኑ እንዲሁም ዋልድቢት ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም፣ አቡነ ዮሴፍ ገዳም፣ ገብረ ክርስቶስ ዋሻ ቤተክርስቲያን፣ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን፣ ቀደሊት ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ እመኪና መድኃኔዓለምና እመኪና ልደታ፣ ማውሬ እስጢፋኖስ፣ የቅዱስ ገብረ ማርያም ቤተክርስቲያን፣ ማይ ማርያም ቤተክርስቲያን፣ ተከዜ ኪዳነምሕረትና መድኃኔዓለም አንድነት ገዳም ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ ከ485-536 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በዐፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት የታነጹ ናቸው፡፡ ሌሎቹንና በሰሜን ላስታ ያሉትን ደግሞ እነ ላሊበላና ይምርሃነ ክርስቶስ አንጸዋቸዋል፡፡

ቅዱስ ላሊበላ እኛ ከምናውቃቸው ከድንቅ ሥነ ሕንፃዎቹ ሥራ በተጨማሪ ከሺህ ዓመታት በፊት በሥዕል፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሃይማኖት፣ በኢኮኖሚ፣ በውጭ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙትና በመሳሰሉት ሁሉ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ከሺህ ዓመታት በፊት አዳራሾችን፣ ፎቆችን፣ የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያዎችን፣ የእንግዳ መቀበያዎችን፣ የሕፃናት ማሳደጊያዎችን፣ የሕሙማን መፈወሻዎችን፣ የሕንፃ መሳሪያዎችን፣ የትምህርት ማዕከሎችን፣ የመደጎሻ ቦታዎችን ያቋቋመ መሆኑን የብራና ገድሉ እንደሚናገር የደብሩ አባቶች ይገልጣሉ፡፡ ወደፊት ተርጎመው እንሚያቀርቡልን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ከዚህ በተጨማሪ የግእዝ ቋንቋን በጽሑፍ አበልፅጎ ያቆየ ባለውለታ ነው፡፡ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ውጭ ሌሎችንም በርካታ ቤተ መቅደሶች ሠርቷል፤ ከሀገራቸንም አልፎ በሱማሌ ሞቃዲሾ ላይ መቅደሰ ማርያም የተባለች ቤተክርስቲያን ሠርቷል፡፡ ክርስትናን ከግብፅ ምድር ጨርሰው ለማጥፋት ተንባላት በተነሡ ጊዜ ዓባይን ሊያግድባቸው ሲነሣ በብዙ ምልጃና ልመና ስለማራቸው በሀገሪቱ ውስጥ ክርስትና እስካሁን እንዲቆይ የራሱን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ ቅዱስ ላሊበላ ነቢይም ሆኖ፣ ሐዋርያም፣ ጻዲቅም፣ ሰማዕትም ሆኖ ጥበብ መንፈሳዊንና ጥበብ ሥጋዊን ከእግዚአብሔር ተሰጥቶት ንግሥናንና ክህነትን፣ ቅድስናንና ንጽሕናን በሚገባ አስተባብሮ በማያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅንነት ሲያገለግል ኖሮ ሰኔ 12 ቀን 1197 ዓ.ም ከፈጣሪው ታላቅ ቃልኪዳን ተቀብሎ በዝማሬ መላእክት፣ በመዝሙረ ዳዊት ቅድስት ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ ሰማያዊ ክብርን ወርሷል፡፡ ክቡር ሥጋውም ራሱ ባነጸው ቤተ ሚካኤል መቅደስ ሥር በክብር ዐርፏል፡፡

6.መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለቅዱስ ላሊበላ የገባለት ልዩ ቃልኪዳን፡-

 6.1. ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶት በዙፋኑ ፊት የሰጠው ቃልኪዳን፡- ‹‹ዛሬ በዚህች ቀን ከአንተ ጋር እነሆ ኪዳኔን አጸናሁ፡፡ በጸሎትህ ኃይል ታምኖ በውስጣቸው የሚያመሰግን ትሠራቸው ዘንድ ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የደረሰ ሁሉ አንተን አስቦ ‹አቤቱ ፈጽመህ ይቅር በለኝ› የሚለኝ፣ ‹ይህን የሚያስደንቅ ሥራ በእጁ ስለገለጥክለት ስለ ባሪያህ ስለ ቅዱስ ላሊበላ ብለህ ይቅር በለኝ› እያለ የሚጸልየውን በዚያ ጊዜ እኔ ጸሎቱን እሰማዋለሁ፡፡ ከሕፃንነቱ ጀምሮ የሠራውን ኃጢአት ሁሉ አስተሠርይለታለሁ፤ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ እንደ እንደተወለደባት ቀን የነፃ አደርገዋለሁ፡፡ የዕዳ ደብዳቤውንም በእጅህ ትቀደው ዘንድ ለአንተ እሠጥሃለሁ፤ ዕድሜውንም በምድር ላይ አረዝምለታለሁ፤ ቤቱንና ንብረቱን ሁሉ እባርክለታለሁ፤ በተንኮል የሚከራከረው ቢኖር ድል እንዳይነሣው አሠለጥነዋለሁ፤ እግሮቹ እየተመላለሰ ወደ ቤተክርስቲያን የገሠገሠ ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት በኤዶም ገነት ውስጥ እንዲመላለስ አደርገዋለሁ፤ መባዕ የሚያገባ ሁሉ ጥቂትም ቢሆን ብዙም ቢሆን በእጅህ ከምሠራው ከቤተ መቅደሴ የሚያመጣውን መባዕ ሁሉ ቀኝ እጄን ዘርግቼ ከእጁ ፈጽሜ እቀበለዋለሁ፡፡ ከዕጣንም ወገን በየአይነቱ ያገባ ቢኖር እንደሰው ልማድ ሥጋዬን እንደቀባበት እንደ ኒቆዲሞስ ሽቱ እቀበለዋለሁ፣ በቢታንያ እንደቀባችኝ እንደ ማርያም እንተ ዕፍረት ሽቱ መዓዛውን አሸትለታለሁ፤ ስለ ማርያም እንተ ዕፍረት እስከ ዓለም ዳርቻ ሁሉ የመንግሥቴ ወንጌል በተሰበከበት ስሟን ይጠሩ ዘንድ እንዳዘዝኩ ሁሉ ትጉሃን በሚሆኑ በሰማያውያን መላእክት ከተሞች ስሙን ይጠሩት ዘንድ አዛለሁ፡፡ ለመብራት የሚሆን ዘይት ቢያገባ በይቅርታዬ ዘይትነት ራሱን አወዛዋለሁ፣ ሰውነቱ ለዘለዓለሙ አይሻክርም፣ ከፊቱም የብርሃን መብራት አይጠፋም፡፡ ወደ ሠርግ ቤት ከሚገቡ መብራታቸው ካልጠፋባቸው ከልባሞች ደናግል ጋር በመጣሁ ጊዜ በደስታ ይቀበለኛል፡፡››
6.2. በኢየሩሳሌም ሳለ ጌታችን የስቅለቱን መከራ በራእይ ካሳየው በኋላ የሰጠው ቃልኪዳን፡- ‹‹ለሌሎቹ ጻድቃን ከዚህ ዓለም በሞት በሚለዩበት ወቅት በፍጹም ልቡናቸው እንደሚገባ ያገለገሉኝን ዋጋቸውን ሰጠኋቸው፣ ለአንተ ግን በሞት የምትለይበት ጊዜ ሳይደርስ በሕይወትህ ሳለህ ኪዳንን ሰጠሁህ፡፡ ማደሪያህ ከጳውሎስና ከጴጥሮስ ጋር ይሆናል፡፡ አቀማመጥህ በቀኜ ነው፣ ደቀ መዛሙርቴን በ12 ወንበር ተቀምጣችሁ በ12ቱ ነገደ እስራኤል ትፈርዳላችሁ እንዳልኳቸው አንተም ወንበርህ ከወንበራቸው አያንስም፤ ብርሃንህ ከብርሃናቸው፣ ክብርህ ከክብራቸው አያንስም፤ ኪዳንህም ከሰጠኋቸው ኪዳን አያንስም፤ ርስትህ ዕድል ፈንታህ ከእነርሱ ጋር ነው፡፡ የሰጠሁህን ቃልኪዳንና ገድልህን የሚያቃልል ሁሉ ዕድል ፈንታው ከአንተ ጋር አይሁን፣ ርስት ጉልቱም ከአንተ ርስት ጉልት አይገኝም፤ የጸናሁልህን ቃልኪዳን የማያምን ያ ሰው እኔን ክርስቶስን እግዚአብሔር አይደለም እሩቅ ብእሲ ነው እንጂ እንደሚለኝ ሰው ይሁን፡፡ መጽሐፍህን ሰምቶ የተቀበለ ሁሉ የመንግሥቴን ወንጌል እንደተቀበለ ይሁን፤ አንተን ያከበረ እኔን እንዳከበረ ይሁን፡፡ ደቀ መዛሙርቴን እናንተን የሰማ እኔን የሰማ ነው፣ እናንተን የካደ እኔን የካደ ነው እንዳልኳቸው አሁንም አንተን የሰማ ቃልኪዳንህንም ያመነ እኔን ጌታህን የሰማ ነው እልሃለሁ፡፡ መከራህንና ቃልኪዳንህን የካደ ሰው ቢኖር እኔ በምድር የተቀበልኩትን መከራ እንደ ካደ ሰው ነው፡፡ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በጸሎትህ ኃይል የታመኑ ሁሉ ማደሪያቸው ከአንተ ጋር ይሁን፤ ለቤተክርስቲያኖችህ አምኃ የሰጠ ቢኖር እንደ ደሜ ፍሳሽ እንደ ሥጋዬ ቁራሽ አድርጌ እቀበለዋለሁ፡፡››
3.ቤተ መቅደሶቹን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ ጌታችን የሰጠው ቃልኪዳን፡- ቅዱስ ላሊበላ ጌታችን ባሳየውና ባዘዘው መሠረት አብያተ ክርስቲያናቱን አንጾ ከጨረሰ በኋላ በቀኝና በግራው ዓሥር ዓሥር ኪሎ የሚመዝን የዓለት ድንጋይ ተሸክሞ ለ7 ዓመት ሲጾም ሲጸልይ ከኖረ በኋላ ጌታችን ተገልጦለት በፊት የገባለትን ቃልኪዳን በዚህም ጊዜ በድጋሚ አረጋግጦለታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹…ወደ ደጅህ የመጡት ሁሉ አስራት ይሁኑልህ፣ አንተ ከገባህበትም ይግቡ፣ አንተንም ከ12ቱ ሐዋርያት ጋር በፍርድ ቀን 13ኛ አደርግሃለሁ፡፡ ያነጽካቸውን ቤተ መቅደሶች የተሳለመውን ኢየሩሳሌምን እንደተሳለመ አደርግለታለሁ፤ መታሰቢያህን ያደረገውን፣ ገድልህን የጻፈውን ያጻፈውን፣ በዚህ ቦታ ላይ መጥቶ አማልደኝ ያለውን፣ በአማላጅነትህ የተማጸነውን ሁሉ እስከ 15 ትውልድ ምሬልሃለሁ›› ብሎ የመጨረሻውን ቃልኪዳን ሰጥቶታል፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! እኛንም በአማላጅነታቸው የምንታመን ሁላችንንየመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤልን እና የቅዱስ ላሊበላን በረከታቸውን ያድለን በጸሎታቸው ይማረን አሜን!!!


 (ምንጭ፡- ገድለ ቅዱስ ላሊበላ፡- የቅዱስ ላሊበላ ደብር በ2003 ዓ.ም ያሳተመው፣ ስንክሳር ዘወርሃ ሰኔ፣ ድርሳነ ሚካኤል ዘወርሃ ሰኔ)