Tuesday, December 5, 2017

ወበዛቲ ዕለት... ኅዳር ፳፮


እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን ኢየሱስ ሞዐ ወአቡነ ሃብተ ማርያም እና ለናግራን ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
<3 ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it) <3
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ <3

እግዚአብሔር በአሥራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እነ አቡነ ኢየሱስ ሞዐን ባያስነሳ ኑሮ ምናልባትም ዛሬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በምናያት መንገድ ላናገኛት እንችል ነበር። እውነተኛ አባቶቻችን ፈጽሞ ከሚቆረቁራቸው ነገር አንዱ የጻድቅና ሐዋርያዊ አባት አቡነ ኢየሱስ ሞዐ መዘንጋት ነው።

እርሳቸው ፍሬ ሃይማኖት ሆነው ከጽድቅ ፍሬአቸው አዕላፍ ቅዱሳንን ወልደው ሃገራችን በወንጌል ትምህርትና በገዳማዊ ሕይወት እንድታሸበርቅ አድርገዋል። እስኪ በዕለተ ዕረፍታቸው ስለ ጻድቁ ጥቂት ነገሮችን እናንሳ።

አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ የተወለዱት ጐንደር የድሮው ስማዳ (ዳኅና) አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው ዘክርስቶስና እግዚእ ክብራ ይባላሉ። የተወለዱት በ፲፪፻፲ ዓ/ም ነው። ነገር ግን አንዳንድ ምንጮች በ፲፩፻፺፮ ዓ/ም ያደርጉታል።

ጻድቁ ከክርስቲያን ወላጆቻቸው ጋር እንደሚገባ አድገዋል። በልጅነታቸው በብዛት ወላጆቻቸውን ያግዙ ነበር። በትርፍ ጊዜአቸው ደግሞ ትምሕርተ ሃይማኖትንና ሥርዓቱን ያጠኑ ነበር። በ፲፪፻፵ ዓ/ም ግን (ማለትም ሠላሳ ዓመት ሲሞላቸው) ይህቺን ዓለም ይተዋት ዘንድ አሰቡ።

አስበውም አልቀሩ ፈጣሪን እየለመኑ ደብረ ዳሕሞ ገቡ። በወቅቱ ዳሞ የትምህርትና የምናኔ ማዕከል ከመሆኑ ባሻገር የአቡነ አረጋዊ አምስተኛ የቆብ ልጅ ካልዕ ዮሐኒ ነበሩና የእርሳቸው ደቀ መዝሙር ሆኑ።

አቡነ ኢየሱስ ሞዐ በደብረ ዳሞ በነበራቸው ቆይታ ቀን ቀን ሲታዘዙ፣ ሲፈጩ፣ ውኃ ሲቀዱ ውለው ሌሊት እኩሉን በጸሎት በስግደትና የቀረውን ሰዓት ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመገልበጥ አሳለፉ።

በመጨረሻም ልብሰ ምንኩስናን ለበሱ። ይህን ጊዜ ሠላሳ ሰባት ዓመታቸው ሲሆን ዘመኑም ፲፪፻፵፯ ዓ/ም ነው። ወዲያውም በዳሞ ሳሉ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦ "ወደ ወሎ ሐይቅ ሒድ፤ ብዙ የምትሠራው አለና።" አላቸው።

በአንዴም ከዳሞ (ትግራይ) ነጥቆ ሐይቅ እስጢፋኖስ (ወሎ) አደረሳቸው። በዚያም ለሰባት ዓመታት በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ መቅደስ በተጋድሎ፣ በስብከተ ወንጌል፣ በማዕጠንትና ሐይቁ ውስጥ ሰጥሞ በመጸለይ ኖሩ።

ቅድስናቸውን የተመለከቱ አበውም በግድ አበ ምኔት አድርገው ሾሟቸው። ይህ ነው እንግዲህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ትልቁ መሠረት የተጣለበት አጋጣሚ።
ነገሩ እንዲህ ነው፦
ስም አጠራሯ የከፋ ዮዲት ጉዲት ለአርባ ዓመታት ሃገሪቱን እንዳልነበረች ብታደርጋት ክርስትና ተዳከመ፤ ባዕድ አምልኮም ነገሠ። አቡነ ኢየሱስ ሞዐ (ትርጉሙ ኢየሱስ ክርስቶስ አሸነፈ ማለት ነው።) ደግሞ ሃይማኖታቸው የቀና ከስምንት መቶ በላይ ክርስቲያኖችን ሰበሰቡ።

በሃገሪቱ ትልቅና የመጀመሪያው ሊባል የሚችል ቤተ መጻሕፍት አደራጁ። እነዚያን አርድእት በቅድስናና በትምህርት አብስለው አመነኮሱና "ሒዱ! ሃገሪቱን ታበሩ ዘንድ ተጋደሉ።" ብለው አሰናበቷቸው።

ከእነዚህ መካከልም ታላላቁን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን፣ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልን እና የኋላውን ፍሬ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫን መጥቀስ እንችላለን። በዚህም ምክንያት ጻድቁ "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን - አእላፍ ቅዱሳንን የወለደ" ሲባሉ ይኖራሉ።

ጻድቁ ከዚህ በተጨማሪ የወቅቱን ንጉሥ አፄ ይኩኖ አምላክን በማስተማር ለሃገርና ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ ሰው አድርገዋል። በግላቸው ሐይቅ ውስጥ ገብተው ሲጸልዩ የብርሃን ምሰሶ ይወርድላቸው ነበር። ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምንም ከጠፋ ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ አቅንተዋል።

እንዲህ ለቤተ ክርስቲያን ሲተጉ በተለይ በአበ ምኔትነት በቆዩባቸው አርባ አምስት ዓመታት ለዓይናቸው እንቅልፍን አላስመኙትም። ጐድናቸውም ከመኝታ ጋር ተገናኝቶ አያውቅም።
"እንዘ የኀሊ ዘበሰማያት ዐስቦ
መጠነ ዓመታት ሃምሳ ኢሰከበ በገቦ።" እንዲል።

ከዚህ በኋላ የሚያርፉበት ዕለት ቢደርስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወርዶ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። በተወለዱ በሰማንያ ሁለት ዓመታቸው (በሰማንያ ስድስት ዓመታቸው የሚልም አለ።) በ፲፪፻፹፪ ዓ/ም በዕለተ ሰንበት ዐርፈው ተቀብረዋል።
ጻድቁ ስም አጠራራቸው እጅግ የከበረ ነው!

<3 አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ <3

እኒህ ጻድቅ ደግሞ የሃገራችን ኮከበ ገዳም ናቸው። "ጽድቅና ትሩፋት እንደ ሃብተ ማርያም" እንዲሉ አበው። ባሕር ከሆነ ጣዕመ ሕይወታቸው ጥቂቱን ለበረከት እንካፈል።

ጻድቁ መካነ ሙላዳቸው ሽዋ (የራውዕይ) ውስጥ ሲሆን አባታቸው ፍሬ ቡሩክ እናታቸው ደግሞ ቅድስት ዮስቴና ትባላለች። በተለይ ቅድስት ዮስቴና እጅግ ደመ ግቡ፣ ምጽዋትን ወዳጅ፣ ቡርክት ሴት ነበረች። እንዲያውም ከጻድቁ መወለድ በፊት መንና ጭው ካለ በርሃ ገብታ ነበር።

ግን የበቃ ግኁስ አግኝቷት "ከማኅጸንሽ ደግ የሥላሴ ባርያ አለና ተመለሽ።" ብሏት እንደ ገና ተመልሳለች። ጻድቁን ወልዳ አሳድጋም እንደ ገና መንና በተጋድሎ ኑራ ሰባት አክሊላትን ተቀብላ ዐርፋለች።

ወደ ጻድቁ ዜና ሕይወት ስንመለስ አቡነ ሃብተ ማርያም ገና ሕፃን እያሉ ከእናታቸው ጋር ቆመው ሲያስቀድሱ "እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ" ሲባል ይሰማሉ። ይህችን ጸሎት በሕፃን አንደበታቸው ይዘው ሌሊት ሌሊት እየተነሱ "ማረን እባክህን?" እያሉ ይሰግዱ ነበር።

የአምስት ዓመት ሕፃን እንዲህ ሲያደርግ ማየቱ በእውነት ይደንቃል። ትንሽ ከፍ ብለው በእረኝነት ሳሉም ፍጹም ተሐራሚና ጸዋሚ ነበሩ። ጸጋው ስለ በዛላቸውም ልጅ ሆነው ብዙ ተአምራትን ሰርተዋል። የፈጣሪውን ስም ያቃለለውን አንድ እረኛም በዓየር ላይ ሰቅለው አውለውታል።

ከዚያ ግን ለአካለ መጠን ሲደርሱ ወደ ትምህርት ቤት ገብተው መጻሕፍትን አጥንተው መንነዋል። በአባ መልከ ጼዴቅ እጅ ከመነኮሱ በኋላ የሠሩትን ትሩፋትና የነበራቸውን ተጋድሎ ግን የኔ ብጤ ደካማ ሰው ሊዘረዝረው አይችልም።
ባሕር ውስጥ ሰጥመው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ።
በየቀኑ አራቱን ወንጌልና መቶ ሃምሳውን መዝሙረ ዳዊት ይጸልያሉ። (መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ታላቅ ጸሎት ነው።)
በአርባ ቀናት ቀጥሎም በሰማንያ ቀን አንዴ ብቻ ይመገባሉ።
ምግባቸው ደግሞ ሣርና ቅጠል ብቻ ነው።
በየዕለቱ ያለ ማስታጐል ማዕጠንት ያሳርጋሉ። (ካህን ናቸውና)
ዘወትር በንጽሕና ቅዱስ ሥጋውን ይበላሉ፤ ክቡር ደሙን ይጠጣሉ።
በፍጹም በልባቸው ውስጥ ቂምን፣ መከፋትን አላሳደሩም።

በእነዚህና በሌሎች ትሩፋቶቻቸው ደስ የተሰኘ ጌታም ለጻድቁ የእሳትና የብርሃን ሠረገላን ሰጥቷቸው በዚያ እየበረሩ ኢየሩሳሌም ይሔዱ ነበር። ከብዙ የተጋድሎ ዘመናት በኋላም የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ አዕላፍ መላእክትን አስከትሎ መጥቶ አላቸው።
"ስለ እኔ ረሃብና ጥምን ስለ ታገስክ፣
ስለ ምናኔህ፣
ስለ ተባረከ ምንኩስናህ፣
ስለ ንጹሕ ድንግልናህ፣
ቂምና በቀልን ስላለመያዝህ፣
ስለ ንጹሕ ክህነትህና ማዕጠንትህ፣
ቅዱስ ወንጌልን በፍቅር ስለ ማንበብህ ሰባት አክሊላትን እሰጥሃለሁ።"

"በሰማይም ከመጥምቁ ዮሐንስ ጐን አምስት መቶ የእንቁ ምሰሶዎች ያሉበትን አዳራሽ ሰጥቼሃለሁ። በስምህ የሚለምኑ፣ በቃል ኪዳንህ የሚማጸኑትንም ሁሉ እንድምርልህ 'አማንየ! በርእስየ!' ብዬሃለሁ።" አላቸው።

ቅዱሳን መላእክትም "ሃብተ ማርያም ወንድማችን" ሲሉ አቀፏቸው። ጌታ ግን በዚያች ሰዓት አንድም ሦስትም ሆኖ ታያቸውና አቅፎ ሦስት ጊዜ ሳማቸው። ከፍቅሩ ጽናትም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች፤ በዝማሬም ወሰዷት።

<3 የናግራን ሰማዕታት <3

በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ናግራን (የአሁኗ የመን) የክርስቲያኖች ሃገር ነበረች። የሳባ ግዛትን የእኛ ነገሥታት ሲተዋት የተተካው ፊንሐስ ደግሞ ጨካኝ አይሁዳዊ ነበርና ናግራንን ሊያጠፋት ተመኘ። ቀጥሎም "ሃገራችሁን ልጐብኝ።" ብሎ በማታለል ገባ።

ወዲያውም ሕዝቡንና ካህናትን ሰብስቦ "ክርስቶስን ካዱ።" አላቸው። ጽኑ ክርስቲያኖች ግን "አይደረግም!" አሉት። እርሱም ሊያስፈራራቸው አስቦ አራት ሺህ ያህል ካህናት፣ ዲያቆናትና ምሑራንን ጨፈጨፋቸው።

ይህንን አድርጐ "አሁንሳ?" አላቸው። ሕዝቡ ግን አሁንም "ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን የለም።" አሉት።
(ሮሜ. ፰፥፭)
ጨካኙ ፊንሐስም እንደ ገና ከሕዝቡ መካከል ከአራት ሺህ አንድ መቶ በላይ የሚሆኑትን ጨፈጨፈ።

ታላቁን ቅዱስ ሒሩትንም (የሕዝቡ መሪ ነው።) ብዙ አሰቃይቶ ሰየፈው። ሚስቱን ቅድስት ድማሕንም ሁለት ሴት ልጆቿን ሰይፈው የልጆቿን ደም አጠጧት፤ ከዚያም ሰየፏት። ይህንን የተመለከቱ የናግራን ክርስቲያኖች ግን ስለ መፍራት ፈንታ በፈቃዳቸው እየተሯሯጡ ወደ እሳትና ሰይፍ ተሽቀዳደሙ።

ከተማዋም እየነደደችና ደም እየፈሰሰባት ለአርባ ቀናት ቆየች። ይህንን የሰማው ቅዱሱ አፄ ካሌብም ደርሶ የተረፉትን ሲታደግ ፊንሐስን ከነ ወታደሮቹ አጥፍቶታል።

አምላከ አበው ወሰማዕት ጣዕመ ፍቅራቸውን፣ ክብራቸውን፣ ጸጋ በረከታቸውንም ይክፈለን።

ኅዳር ፳፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፪.አቡነ ሃብተ ማርያም ንጹሕ
፫.ቅድስት ዮስቴና ቡርክት
፬.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
፭.ቅዱስ ሒሩት አረጋዊ
፮.ቅዱሳን ቢላርያኖስ፣ ኪልቅያና ታቱስብያ (ሰማዕታት)
፯.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘደሴተ ሰንሲላ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪.ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

"እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና።ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና። ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል።.....
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ። በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል። አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው። በእርምጃውም አይሰናከልም።"
(መዝ ፴፮፥፳፰-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl