Tuesday, November 26, 2013

ህዳር 18

ህዳር 18

በዚህች ቀን ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ሐዋርያው ፊሊጶስ አረፈ፤ ጥቅምት 14 ቀን መታሰቢያውን የምናከብርለት ኢትዮጰያዊውን ጀንደረባ ያጠመቀውን ዲያቆኑ ፊሊጶስ ነው ይህ የዛሬው ግን ቁጥሩ 12 ሐዋርያት ነው ዮሐ 144 በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና። ተከተለኝ አለው።ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ ይላል። ሐዋርያት ዓለምን ዞረው ለማስተማር ዕጣ ሲያወጡ ለፊሊጶስ ከወርቅ የተሰራ ኦሞራ የሚያመልኩ ሰዎች ያሉበት አገር ደረሰው ገድለ ሐዋርያት ላይ አፍራቅያ ይለዋል የአገሩን ስም ቱርክ አካባቢ የሚገኝ ነው፤ ወደ ከተማው ግብቶ ወንጌለ መንግስተ ሰማያትን ሰበከ ብዙዎችንም አሳመነ አጠመቃቸው፤ አቆረባቸውም፤ ቤተክርስቲያን ሰራላቸው፤ ካህንና ዲያቆንም ሾመላቸው፤ ነገር ግን ጥቅማቸው የጎደለባቸው የጣኦት ካህናት ከንጉሱ ጋር ነገር ሰርተው አጣሉት፤ አስረው ደበደቡት፤ ሰቅለውም ገደሉት ይህም የሆነው በዛሬዋ ቀን፤ የሐዋርያው በረከት ይደርብን፤

Sunday, November 24, 2013

የገና ጾም - ጾመ ነቢያት


እንኳን ለጾመ ነቢያት በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ

ነቢያት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ፣ ወደ ግብፅ ስለ መሰደድ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለመጠመቅ፣ በትምህርተ ወንጌል ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ጸዋትወ መከራ ስለመቀበሉና ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ትንሣኤው፣ ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረው አላቆሙም፤ ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢት ፍፃሜ እንዲያደርሳቸው ፈጣሪያቸውን ተማፀኑትም እንጂ፡፡ በየዘመናቸው «አንሥእ ኃይለከ፣ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሳ እጅህንም ላክ» እያሉ ጮኹ፡፡ በጾምና በጸሎት ተወስነውም ሰው የሚሆንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት ቆጠሩ፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ሥጋዌው ትንቢት በተናገረ በ446 ዓመት ጌታችን ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆኗል፡፡

ነቢያት ተስፋው በዘመናቸው ተፈጽሞ በዓይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም እግዚአብሔር «የማያደርገውን አይናገር የተናገረውን አያስቀር» ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ፡፡ለዘመነ ሥጋዌ ቅርብ የነበሩት እነ ኢሳይያስ ጾሙ እንዴት መፈጸም እንዳለበትተናግረዋልም፡፡ ኢሳ 58-1፡፡

በመሆኑም በጌታ ልደት ትንቢተ ነቢያት ስለ ተፈጸመበት ይህጾም «የነቢያት ጾም» ይባላል፡፡ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት የሰውልጆች ተስፋ የተመሰከረበት የምሥራቹ የተነገረበት ስለሆነም «ጾመ ስብከት» ይባላል፡፡

ሰው በኃጢአት ቢወድቅም ፈጣሪው ሊያነሳው፤ ቢጠፋ ሊፈልገው እንደሚመጣ በተስፋ ሲጠብቀው ወልደ አምላክ ሰው መሆኑ የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ አዳም የልደቱን ነገር በትንቢት መነፅርነት ሲመለከተው /በነቢያቱ ትምህርትና ስብከት/፣ በሚኖርበት ዓመተ ፍዳ የምሥጢረ ሥጋዌ ብርሃን ከሩቅ ሲመለከተው ኖረ፡፡ ምሥጢረ ሥጋዌን በትንቢት መነፅርነት ማየቱም መከራውን እንዲቋቋመው የተስፋ ስንቅ ሆነው፡፡
ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር በጸጋ እንደተወለዱ በማመን ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር ከሚገልጡባቸው ነገሮች አንዱ ጾም ነው፡፡ ጾም የፍቅር ስጦታ ከመሆኑ በተጨማሪ ታዛዥነትንና የገቡትን ቃል ኪዳን ጠባቂነትንም ማሳያ ነው፡፡ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ ተፈጥሯአል፡፡ ኃጢአት ሠርቶ የእግዚአብሔር አርአያነቱን ቢያጠፋውም እግዚአብሔር ግን በአርአያው ሲፈጥረው ምን ያህል እንደሚወደው ማረጋገጫ ስለነበር በኃጢአት ሲወድቅም እንደወጣ ይቅር ሳይል ሊፈልገው መጣ፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሊፈልግ የመምጣቱ ተስፋ የተነገረበትንና ሱባኤ የተቆጠረበትን ዕለት ለማየት በመናፈቅ ከቀረበው መሥዋዕት አንዱ ጾም ነበር፡፡

ጾም ሰው ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር እና ታዛዥነት መግለጫና ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን ሲወድቁ መነሻ ከብልየት (እርጅና )መታደሻ፥ ከኃጢአት ቆሻሻ መታጠቢያ /ከንስሓ ጋር አብሮ ሲፈጸም/ ሳሙናም ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በሲና ተራራ ላይ እግዚአብሔር ወደ ነበረበት ጨለማ የገባው፣ አስፈሪውን መብረቅና ነጐድጓድ የተቋቁመው፣ ጨለማውን አልፎ የሰው ልጅ ያልሠራትን ሰማያዊ መቅደስ የተመለከተውና ወደ ዓለቱ ድንጋይ የቀረበው ራሱን ለእግዚአብሔር በጾም በመቀደስ ጭምር ነው፡፡ /የወገን ፍቅርና ለእግዚአብሔር ታዛዥነቱ እንዳለ ሆኖ/፡፡

ጾም እነዚህንና መሰል መንፈሳዊ በረከትን ስለሚያስገኝ ክርስቲያኖች ይመጣላቸው ዘንድ ይናፍቁታል፡፡ ከእነዚህ የሚናፈቁ አጽዋማት መካከል አንዱ ጾመ ነቢያት ነው፡፡ ጾመ ነቢያት የሚባለው ጾመ ገና፣ ጾመ ማርያም፣ ጾመ አዳም፣ ጾመ ፊልጶስ ተብሎ ይጠራል፡፡
ጾመ ነቢያትም ሆነ ሌሎች አጽዋማት ሲደርሱ ክርስቲያኖች የሚደሰቱት ጾም የሥጋ ፈቃድ እንዳይሰለጥንባቸው፣ ቁስለ ሥጋን በማከም፣ ቁስለ ነፍስን ስለሚፈውስላቸው ነው፡፡ ጾም የቁስል መፈወሻ ኃይለ መዊዕም(ድል ማድረጊያ) ይሆናል፡፡ ከሥጋም ከመንፈስም ተቆራኝቶ ሰውን ወደ ጥፋት የሚወስድን ክፉ መንፈስ ለማራቅም ይጠቅማል፡፡
ጾም የሥጋን ምኞት እስከመሻቱ ቆርጦ የሚጥል፣ ለመንፈስ ልዕልና የሚያበቃውን መሳሪያ የሚያስታጥቅ ነው፡፡ ክርስቲያን ይህን መሰል መንፈሳዊ የጦር እቃ እንዳይለየው አጥብቆ ይለምናል፡፡ የጦር ልምድ እንደሌለው ወታደር ጠላቱን የሚቋቋምበት የጦር ትጥቅ ሳይዝ አውላላ ሜዳ ላይ ባዶውን አይቆምም፡፡ መንፈሳዊ ውጊያን በሥጋዊ ጥበብ ማሸነፍ ስለማንችል ነው አበው ፍቅረ አጽዋማትን በአስተምህሮአቸውና በሕይወታቸው የሰበኩልን፡፡
ጾም እነዚህንና መሰል መንፈሳዊ በረከትን ስለሚያስገኝ ክርስቲያኖች ይመጣላቸው ዘንድ ይናፍቁታል፡፡ ከእነዚህ የሚናፈቁ አጽዋማት መካከል አንዱ ጾመ ነቢያት ነው፡፡ ጾመ ነቢያት የሚባለው ጾመ ገና፣ ጾመ ማርያም፣ ጾመ አዳም፣ ጾመ ፊልጶስ ተብሎ እንደሚጠራ መምህር ቃኘው ወልዴ ጾምና ምጽዋት በተሰኘው መጽሐፋቸው ገልጠውታል፡፡
ጾመ ነቢያት ለአዳም የተነገረው ትንቢት፣ የሚጠበቀው ሱባኤ እንደደረሰ የሚያበስር በመሆኑ ጾመ አዳም ይባላል፡፡ አዳም ቢበድልም ንስሐ ገብቶ በማልቀሱ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሀለሁ ብሎ የተነገረው ተስፋ መድረሱን፣ ምሥጢረ ሥጋዌ እውን ሊሆን መቃረቡን የሚያስረዳ ጾም ነው፡፡

ነቢያትም የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር ተገለጦ ስለታያቸው፣ ክርስቶስ ለሰው ልጅ የሚከፍለውን የፍቅር ዋጋ በትንቢት ተመልክተው ጾመውታልና ጾመ ነቢያት ይባላል፡፡ ይህ ጾም የራቀውን አቅርቦ፣ የረቀቀውን አጉልቶ ስላሳያቸው እስከሞት ድረስ ቢደበደቡም፣ ከመከራው ጽንአት የተነሣ ዋሻ ለዋሻ፣ ፍርኩታ ለፍርኩታ ቢንከራተቱም፣ የፍየል ሌጦ ለብሰው ቢዞሩም የተስፋው ቃል ሁሉን አስረስቶአቸው ከትንቢቱ ባለቤት ጋር በመንፈስ ተዋሕደው አልፈዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሐዋርያት ምን ሠርተን የክርስቶስን ልደት እንቀበለው ብለው ስለጾሙት ጾመ ሐዋርያት ተብሎ ይጠራል፡፡
ጾመ ነቢያት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ወልደ አብን ፀንሼ ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ በማለት ጾማዋለችና ጾመ ማርያም ይባላል፡፡ ይህን ያለችው በመደነቅ፣ አንድም በትሕትና አንድም ቀደምት አባቶቿ ነቢያት ሲጾሙት አይታ ጾማዋለች፡፡ እንዴት ፀንሼ እወልደዋለሁ ማለት ጥርጥር ሳይሆን ተደሞ፣ መደነቅ የነገረ ልደቱን አይመረመሬነት ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትሕትና ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ቅድስናዋን አይቶ በብስራተ መልአክ አማካኝነት ክርስቶስን እንደምትወልድ ቢነግራትም የትሕትና እናት ናትና ምን ሠርቼ የሰማይና ምድርን ፈጣሪ እችለዋለሁ ስትል ጾማዋለች፡፡
ይህ ጾም ጾመ ፊልጶስም ይባላል፡፡ ሐዋርያው ፊልጶስ በአረማውያን ዘንድ ገብቶ ሲያስተምር በሰማዕትነት ሲሞት አስከሬኑ ከደቀመዛሙርቱ ስለተሰወረ እግዚአብሔር የተሰወረውን የመምህራቸውን አስከሬን እንዲገልጽላቸው ከኅዳር አስራ ስድስት ጀምረው ሲጾሙ በሦስተኛው ቀን የመምህራቸው አስከሬን ቢመልስላቸውም ጾሙን ግን እስከ ልደት ቀጥለዋል፡፡ ጾምን ትእዛዝ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የፍቅርና የበረከት ምንጭ በመሆኑ ጭምር ደስ እያለን ብንጾመው የቅዱሳኑ በረከት ያድርብናል፡፡

ጾሙን ጾመ ሥርየት ፤ ጾመ መድኃኒት ያድርግልን ፤
ለብርሃነ ልደቱ በሰላም እና በጤና ያድርሰን ፤
ጾመን ለማበርከት ያብቃን - አሜን ፡፡


https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ህዳር 15


ህዳር 15
መንፈቀ ህዳር የጾመ ስብከት መጀመሪያው ነው፤ ጾመ አዳም፤ ጾመ ነቢያትም ይለዋል የአዳም ተስፋ የነቢያት ትንቢት ተፈጽሞበታልና፤ ይህንን ጾም እመቤታችን ሰማይና ምድር የማይወስኑትን በሆዴ ተሸክሜ ምን ሰርቼ እወልደዋለሁ ስትል ጾማዋለች፤ሐዋርያትም ትንሳኤውን አብይ ጾምን ጾመን እናከብራለን ልደቱን ምን ሰርተን እናክብር ሲሉ ጾመውታል፤
ህዳር 15 በዚህች ቀን ቅዱስ ሚናስ አረፈ፤ ይህ አባት የአገር ገዢ ልጅ ነው፤ አባቱ በ 12 ዓመቱ ሞተ ከ 3 ዓመት በኃላ እናቱም አረፈች፤ ብቻውን ቀረ፤ መኳንንቱ አባቱን በጣም ይወዱት ነበርና በአባቱ ፋንታ ምስፍና ሾሙት፤ ግን ብዙም አልቆየም ዲዮቅልጥያኖስ “አብያተክርስቲያና...ት ይዘጉ አብያተ ጣኦታት ይከፈቱ በክርስቶስ የሚያምኑ በሰይፍ ይታረዱ” ሲል አዋጃ ነገረ፤ብዙዎች በሰማዕትነት ሞቱ ቀዱስ ሚናስ ግን ሹመቱን ትቶ ወደ ገዳም ገባ በተጋድሎም ኖረ ከእለታት በአንዱ ቀን ሰማይ ተከፍቶ ሰማዕታት የብርሃን አክሊል ሲቀዳጁ አየ፤አልዋለም አላደረም ወደ ከተማ ተመለሰ የክርስቶስ ባሪያ ነኝ ሲል ድምጹን አሰምቶ ተናገረ፤ አገሬው በጣም ይወደው ነበርና እንዳይሞትባቸው ፈርተው እባክህን ዝም በል አሉት፤ መኮንኑም ሊሸነግለው ሞከር ቅዱስ ሚናስ ግን እምቢኝ አለ ከዚህ በኃላ ልዩ ልዩ ጸዋትኦ መከራ አደረሱበት በመጨረሻም በዛሬዋም ቀን አንገቱን ቆርጠው ገደሉት የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ፤ ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከሰማዕቱ በረከት ያድለን።
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

መዝሙርየመናፍቃንን መዝሙር መስማት.......... ዲያቆን ህብረት የሺጥላ
(ከሕይወተ ወራዙት መፅሀፍ ላይ የተወሰደ)

• ዘፈን መስማት ኃጢአት ነው የመናፍቃንን «መዝሙር›› መስማት ግን ዓመፅና ክህደት ነው፡፡ ኃጢአት የምግባር ሕፀፅ ሲሆን ዓመፅ ደግሞ የሃይማኖት ሕፀፅ ነው፡፡ የቱ የሚከፋ ይመስልሃል?
• «የመናፍቃንን መጽሐፍ ከመመልከት ተከልከል››ማር ይስሐቅ ::
• «ዑቅ ከመኢትቅረብ ኀቤሃ - ወደ እርሷ ከመቅረብና ገልጾ ከማየት እንኳን ተጠንቀቅ›› ይላል፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዳ መንፈሰ ጽርፈት / የስድብ መንፈስ/ እንዳያድርብህ ነው ይላል፡፡ በእርግጥ ይህ ቃል የተነገረው የመናፍቃንን መጽሐፍ ስለማንበብ ነው፡፡ ማር ይሥሐቅ ከላይ እንዳስጠነቀቀን የመናፍቃንን መጽሐፍ ማንበብ ክፉ ነገር ነው፡፡ መጽሐፋቸውን ከማንበብ በላይ በዘፈን ዜማ የወዛ «መዝሙራቸውን መስማት›› እጅግ አይከፋምን? ስለዚህ እንደ መጽሐፋቸው ሁሉ «መዝሙራቸውንም›› መስማት ይከለክለናል፡፡
• እነርሱ «የምስጋና መዝሙር›› ቢሏቸውም አስተውሎ ለሰማቸው ፉከራና ሽለላዎች ናቸው፡፡
• የመዝሙሮቻቸው የጌታችንና የመድሐኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስሙን ሲያነሡ ልክ ባልጀራቸውን እንደሚጠሩ ያህል በድፍረት መሆኑ ደግሞ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ታዲያ አንተ መዝሙራቸውን እየሰማህ ከእነርሱ ጋር «ኢየሱስ ጓዴ›› ለማለት ልብህ ይከጅላልን?
‹‹ይህ ነው ምስጋናቸው›› ይመልከቱት
ዘፈን መስማትና ዘፋኝነት ለመናፍቃን መዝሙር ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ ምክንያቱም የመናፍቃን መዝሙር ከሚያስጨፍር ዘፈን አይለይምና፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ኦርቶዶክሳዊያን ወጣቶች ለመናፍቃን መዝሙር የቀረበ አመለካከት እንዲኖራቸው ያደረገው በውስጣቸው ያለው የዘፈን እርሾ ነው፡፡ ብዙ ዘፋኞች ወደ መናፍቅነት እንዲሄዱና በዚያም «ዘማሪ›› እስከመባል መድረሳቸው በዚህ ውጤት ነው፡፡
የተዘረዘሩትን ጉዳቶች ጨምሮ ለከፍተኛ ጉዳት ያጋልጣል፡፡ ብዙ እጥፍ ይከፋል፡፡ ዘፈን መስማት ኃጢአት ነው የመናፍቃንን «መዝሙር›› መስማት ግን ዓመፅና ክህደት ነው፡፡ ኃጢአት የምግባር ሕፀፅ ሲሆን ዓመፅ ደግሞ የሃይማኖት ሕፀፅ ነው፡፡ የቱ የሚከፋ ይመስልሃል?
ከባሕር ማዶ ያሉ በርካታ ዘፋኞች ታሪክ ሲጠናና ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው የሚናገሩት «የቤተ ክርስቲያን ዘማሪ›› እንደነበሩ ነው፡፡ አብዛኞቹ ለዘፋኝነታቸው መነሻ የሆናቸው «መዝሙር›› እንደሆነ አበክረው ይገልጻሉ፡፡
የእነዚህ ዘፋኞች ገለጻ የሚያመለክተው የ«መዝሙር›› ተብዬው ዜማና መሣሪያቸው ከዘፈን ዜማና መሣሪያ ጋር ምንም ልዩነት ስለሌለው ወደ ዘፈን እንደተሳቡ ነው፡፡ ሰይጣን ሰዎችን በለመዱት መሳብ ሥራው ነውና፡፡ የሰው ልብ ማረፊያ ይሻል፡፡ የሰው ልብ ሌላ ለመያዝ ካለሆነ በቀር የያዘውን ለቆ በባዶ መቀመጥ አይሆንለትም፡፡ ይህን የሚያውቅ ሰይጣን መዝሙርን ሲያስለቅቅ ዘፈንን ያስጨብጣል፡፡
ለፈጣሪ ክብር ምሰጋና ይግባውና እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ባሕር ማዶ ሰዎች የመዝሙርና የዘፈን ልዩነት ጠፍቶን ግራ እንድንገባ የሚያደረግ ችግር የለብንም፡፡ ምክንያቱም የመዝሙራችን ዜማ ከዘፈንም ሆነ ከመናፍቃን መዝሙር ዜማ የተለየ ሲሆን የመዝሙር መሣሪያችን ደግሞ ከዘፈንና ከመናፍቃን የመዝሙር መሣሪያ በእጅጉ ይለያልና፡፡
ሆኖም እንደ ባሕር ማዶ ዘፋኞች ሁሉ በኛ አገርም ያሉ በርካታ አዝማሪዎችና ዘፋኞች «ዘማሪ ነበርኩ፣ መነሻዬ የቤተክርስቲያን መዝሙር ነው፡፡›› ሲሉ ይደመጣል፡፡ በእርግጥ ከዘማሪነት እስከ ድቁናና ምርግትና/መሪጌትነት/ ማዕረግ የደረሱ በርካታ ሰዎች ወደ ዘፋኝነት ያዘነበሉና የሄዱ እንዳሉ ይታመናል፡፡ ጥቂቶች ግን ዘፈኖቻቸውን ከሚያዳምጡላቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የቤተ ክርስቱያን ሰዎች ናቸው ብለው ስለሚያምኑ ተቀባይነትን እንደሚያገኙ አስበው «ዘማሪ ነበርኩ›› እያሉ ይዋሻሉ፡፡
ቤተክርስቲያን የመናፍቃንን «መዝሙር›› እንዳይሰሙ ልጆቿን የምታስተምረው የዜማ ዕቃዎቿ ከመናፍቃን የመዝሙር መሣሪያዎች ልዩ ስለሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ አንዱ ቢሆንም ዋናው ግን መናፍቃን የሚምሩትና የሚሠውት ለአጋንንት ስለሆነ ነው፡፡
ክስርቲያኖች ደግሞ የአጋንንትንና የጌታን ጽዋ መጠጣት አይችሉም፡፡ መዝሙር መሥዋዕት መሆኑን አታውቅምን? ወይስ በእስራኤል ዘሥጋ ዙሪያ የነበሩ አሕዛብ ክርስቲያኖችን ከብበው ለሚኖሩ መናፍቃን ምሳሌ መሆናቸውን ትጠራጠራለህ? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እስራኤል ዘሥጋ ከአሕዛብ ጋር ሊኖራቸው የሚገባውን ጠንቃቃ ግንኙነት ለክርስቲያኖች ሁሉ ትምህርት እንደሆነ አድርጎ አስፍሮታል፡፡/1ቆሮ 10÷18-22/
ብዙ ሰዎች «ዘፈን ከመስማት አይሻልምን?›› እያሉ የመናፍቃንን መዝሙር ለማስማት ይከጅላሉ፡፡ ሐዋርያው «አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት›› ሲል በተናገረው ቃል ታምናለህ? /ኤፌ4÷5/ እንግዲያውስ የመናፍቃንን ስብከትና መዝሙር ከመስማት ተከልከል፡፡
በአንዲት ሃይማኖት ስታምን መናፍቃን ሁሉ «በስሜ ይመጣሉ›› ተብሎ በትንቢት እንደተነገረባቸው ምንም እንኳን ስመ ክርስቶስን እየጠሩና «ክርስቲያኖች ነን›› እያሉ ቢመጡም ሁሉም «ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች›› መሆናቸውን ትረዳለህ፡፡ /2ቆሮ11÷13/ዋናው ግን ትክክለኛዋ ሃይማኖት አንዲት ብቻ መሆኗን እርሷም ርትዕት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መሆኗን ማመንህ ነው፡፡
እስራኤላውያን በዘመናቸው በዙሪያቸው ባሉ የአሕዛብ አምላክ ስም እንዳይምሉና እንደ አሕዛብም እንዳይዘፍኑ፣ በአጠቃላይ የጣዖት ስም እንዳይጠሩና ከአፋቸውም እንዳይሰማ ታዘው ነበር፡፡ ትእዛዙም «የሌሎችንም አማልክት ሰም አትጥሩ÷ከአፋችሁም አይሰማ፡፡›› የሚል ነበር፡፡ /ዘጸ23÷13/ በዘመነ ኦሪት እግዚአብሐርን ያመልኩ የነበሩ እስራኤል ዘሥጋ የክርስቲያኖች /የእስራኤል ዘነፍስ/ ምሳሌ ነበሩ፡፡ በዙሪያቸው የሚገኙ ጣዖት አምላኪዎች አሕዛብ ደግሞ ዛሬ በክርስቲያኖች ዙሪያ ለሚገኙ መናፍቃንና አረማዊያን በሙሉ ምሳሌ ናቸው፡፡
ልዩነቱ የዛሬዎቹ መናፍቃን ክርስቲያኖች የያዙትን መጽሐፍ አንግበውና ስመ ክርስቶስን እየጠሩ መምጣታቸው ብቻ ነው፡፡ «ይህም ድንቅ አይደለም ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እስኪመስለ ድረስ ራሱን ይለውጣለና፡፡ እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውም ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፡፡´/2ቆሮ11፡14-15/ ስለዚህ እስራኤል «የሌሎችን አማልክት ስም›› እንዳይጠሩ የሚያስጠነቅቀው ቃል ከክርስቲያንነት አንጻር ስንመለከተው የመናፍቃንን መዝሙር መስማትና ስመ አምላካቸውንም አስመስሎ መጥራት እንደማይገባ ያስተምረናል፡፡ ስመ ክርስቶስ አንድ ቢሆንም በዚህ ስም ውስጥ የሚወከሉና በእምነት ሊቀበሏቸው የሚገቡ በርካታ ቁም ነገሮች አሉ፡፡ በእነዚያ ላይ የሚፈጠር ልዩነት በበዛ ቁጥር የስሙ ውክልናም እንደዚሁ ይበዛል፡፡
በመሆኑም መናፍቃን በክርስቶስ ላይ ያላቸው እምነት እንደ ኦርቶዶክሳዊያን እስካልሆነ ድረስ እነርሱ ክርስቶስ ብለው በሚጠሩበት ጊዜ ይህ ስም ያለው ውክልና ኦርቶዶክሳውያን ሲጠሩት ከሚኖረው ውክልና በእጅጉ ይለያል፡፡ ታዲያ የስሞች መመሳሰል ስላለ ብቻ የመናፍቃንን መዝሙር ስለ እግዚአብሔር እንደተዘመረ አድርጎ መቀበል እንዴት ይቻላል?
ቅዱስ ጳውሎስ አንድ ሰው ወንጌል ጨብጦና ስመ ክርስቶስን እየጠራ ቢመጣም ስለክርስቶስ የሚናረው የወንጌልን ቃል አጣሞ ሐዋርያት ካስተማሩት ትምህርት የተለየ ከሆነ ያ ሰው ክርስቶስን ሳይሆን «ሌላ ክርስቶስ›› ን እየሰበከ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ያ ሰው የያዘውንም ወንጌል ሌላ ወንጌል ነው ይለናል፡፡ እንዲህ ሲል «የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ÷ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈሰ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ÷ በመልካም ትታገሡታላችሁ?›› /2ቆሮ11÷4ገላ1÷6-9/
ብዙ ነገሮች ተመሳሳይ መስለው ግራ ቢገባህም መናፍቃን የሚያመልኩት ኢየሱስ ኦርቶዶክሳዊያን ከሚያመልኩት ኢየሱስ የተለየ መሆኑን ከላይ በሰፈረው የሐዋርያው ቃል አስተውል፡፡ ይህን ስትረዳ የመናፍቃንን መዝሙር መዘመርና መስማት ምን ያህል ለሰይጣን መገዛትና ስሕተት መሆኑን ትረዳለህ፡፡
ይህን ጠንቅቀው የተረዱ አባቶቻችን ሰለስቱ ምዕትም እንደ ሐዋርያት ሁሉ «ከአርሲሳን ጋር አትጽልይ፡፡ እኒህም መናፍቃን ናቸው፡፡ ከአሕዛብም ጋር ቢሆን፡፡›› ብለዋል፡፡ /ሃይአበ ዘሠልስቱ ምዕት/ መዝሙር ጸሎት መሆኑ ይጠፋሃል? ወይስ ለአባቶችህ ትምህርትና ምክር ግድ የለህም? መዝሙር ጸሎት እስከሆነ ድረስ ከመናፍቃን ጋር አትጸልይ ማለት መዝሙራቸውን አትስማ ማለት ነው ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡
ማር ይስሐቅም «የመናፍቃንን መጽሐፍ ከመመልከት ተከልከል›› ይላል፡፡ እንዲያውም ጠንከር አድርጎ «ዑቅ ከመኢትቅረብ ኀቤሃ - ወደ እርሷ ከመቅረብና ገልጾ ከማየት እንኳን ተጠንቀቅ›› ይላል፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዳ መንፈሰ ጽርፈት / የስድብ መንፈስ/ እንዳያድርብህ ነው ይላል፡፡ በእርግጥ ይህ ቃል የተነገረው የመናፍቃንን መጽሐፍ ስለ ማንበብ ነው፡፡ ማር ይሥሐቅ ከላይ እንዳስጠነቀቀን የመናፍቃንን መጽሐፍ ማንበብ ክፉ ነገር ነው፡፡ መጽሐፋቸውን ከማንበብ በላይ በዘፈን ዜማ የወዛ መዝሙራቸውን መስማት እጅግ አይከፋምን? ስለዚህ እንደ መጽሐፋቸው ሁሉ መዝሙራቸውንም መስማት ይከለከላል፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ ‹‹የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን፡፡የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ አገር እንዴት እንዘምራለን?›› የሚል አስደናቂ ቃል ተጽፎ ይገኛል፡፡ ይህን ቃል ቅዱስ ዳዊት ወደ ባቢሎን ተሰደው ስለነበሩ እስራኤላዊያን በትንቢት መልክ ተናግሮታል፡፡ በዚህ ዓረፍተ ነገር ውስጥ እስራኤላዊያን «የአግዚአብሔርን ዝማሬ›› በባዕድ አገር እንደማይዘምሩ አረጋግጠዋል፡፡ /መዝ 136÷3-4/
አንተስ ብትሆን? የእግዚአብሔርን ዝማሬ በዘባቾች መኻል ትዘምር ነበርን? አቋምህ እንደ እስራኤላዊያን «አልዘምርም ነበር›› የሚል ከሆነ የራስህን ለእነርሱ አለዘምርም ማለትህ መልካም ነው፡፡ የእነርሱን ዘፈንንና የአምልኮታቸውን መዝሙር ዝፈን ወይም ዘምር ቢሉህስ ታደርገዋለህ? አላደርገውም እንደምትል አይጠረጠርም፡፡ እንዲህ ከሆነ በዙሪያህ ያሉ መናፍቃንና አህዛብ ያንተን ባትዘምርልንም እኛ ስንዘምር ተቀብለን ወይም ስማን ሲሉህ ለምን እሺ ትላቸዋለህ? በሌላ አቅጣጫ ላየው ሰው የነቢዩ የዳዊት ቃል የመናፍቃንን መዝሙር ክርስቲያኖች መስማት እንደሌለባቸው ያስረዳል፡፡
የመናፍቃን መዝሙር ፍጹም ሥጋዊ ነው፡፡ ይህም በዜማውና በማጀቢያ መሣሪያው ብቻ አይምሰልህ፡፡መልእክቱንም ብትመረምረ አንድም ቦታ ኃጢአተኛነትህን እንድትመረምር የሚያደርግ የጸጸትና የንስሐ ቃል አታገኝበትም፡፡ የምትሰማው ሁሉ ስለ ፈውስ፣ ስለማግኘት፣ ስለ ብልጽግና፣ ስለ ክብር፣ ጠላትን ድል ስለማድረግና ስለ መሳሰሉት ሥጋዊ ነገሮች ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ነጥቦች በይዘታቸው መንፈሳዊ ናቸውን? ሰማያዊ ነገርንስ ያሳስባሉን? እነዚህ ሁሉ ምንም እንኳን እነርሱ «የምስጋና መዝሙር›› ቢሏቸውም አስተውሎ ለሰማቸው ፉከራና ሽለላዎች ናቸው፡፡
በተጨማሪም ከላይ ሐዋርያው መናፍቃን የሚያመልኩት ኢየሱስ «ሌላ ኢየሱስ ነው›› በማለት ያስረዳን እንደተጠበቀ ሆኖ በየመዝሙሮቻቸው የጌታችንና የመድሐኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስሙን ሲያነሡ ልክ ባልጀራቸውን እንደሚጠሩ ያህል በድፍረት መሆኑ ደግሞ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ታዲያ አንተ መዝሙራቸውን እየሰማህ ከእነርሱ ጋር «ኢየሱስ ጓዴ›› ለማለት ልብህ ይከጅላልን? በዚሁ ላይ መናፍቃን ቅዱሳንና መላእክትን ማቃለላቸው ሳያንሳቸው የባሕርይ አምላክ ክርስቶስን ለማኝና አማላጅ በማድረግ በየመዝሙሮቻቸው በፍጡራን ቦታ ያስቀምጡታል፡፡ ለክርስቲያኖች ይህን የመሰለውን የመናፍቃን መዝሙር ሁሉ መስማት እጅግ አያሳፍርምን?
መናፍቃን እምነታቸውን በመዘሙሮቻቸው ስለሚያንጸባርቁ ያንን ለመስማት መቅረብህ እምነታቸውንም እንደመቀበል ይቆጠርብሃል፡፡ በነገረ ሃይማኖት «ለማስማት መቅረብ›› ብቻ ራሱ እንደመታዘዝና አምኖ እንደመቀበል ይቆጠራልና፡፡ ለምሳሌ፣- መልካሙን ትምህርት ለመስማት ወደ ቤተ ክርስቲያን ብትገሰግስ መሥዋዕት ከማቅረብ በላይ ሆኖ ይቆጠርልሃል፡፡ «ለማስማት መቅረብ ከሰነፎች መሥዋዕት ይሻላል›› ተብሏልና፡፡/ መክ5÷1/

https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ቅዱስ ሩፋኤል


ከከበሩት ከ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝ ::
ጦቢት 12 : 13
እንግዲህ ከባህሪው ቅድስና ፍጥረቱን በጸጋ ቅድስና መርጦ የሚለይ እግዚአብሔር አክብሮ እንዲህ ያለ ሰማያዊ ፀጋ ከሰጣቸው ቅዱሳን መላእክት መካከል በስልጣኑ ሊቀመናብርት (የመናብርት አለቃ) የሆነ በሹመት ፈታሔ ማኅጸን (ማሕጸን የሚፈታ) ከሳቴ እውራን (የእውራንን ዓይን የሚያበራ) ሰዳዴ አጋንንት (አጋንንትን የሚያባርር) ፈዋሴ ዱያን (ድውያንን የሚፈውስ)፣ አቃቤ ኆኅት (የምህረትን ደጁ የሚጠብቅ) ተብሎ የተገለጠ ከሊቃነ መላእክቱ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ተከትሎ የሚነሳ መልአክ ራሱን እንዲህ በማለት ገለጠ « የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነት ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ» (ጦቢ.12÷15)
ይህ የከበረ ታላቅ መልአክ ሰሙ የእብራይስጥ ሁለት ቃላት ጥምረት ውጤት ነው፡፡ ሩፋ ማለት ጤና፣ ፈውስ፣ መድኃኒት ማለት ሲሆን ኤል ሚለው በሌሎቹም መላእክት ስም ላይ የሚቀጠል ስመ አምላክ ነው ይህም « መልአኬን በፊትህ እሰዳለሁ….. ስሜ በእርሱ ስለሆነ . አታስመርሩት» (ዘጸ.23÷20-22) እዳለው ነው፡፡
ታዲያ ሩፋኤል የሚለው በጥምረት ከአምላክ ለሰዎች የተሰጠ ፈውስ የሚለውን ይተካል «በሰው ቁስል የተሾመ ከከበሩ ከመላእክት አንዱ ሩፋኤል ነው፡» (ሄኖ.6÷3)
ይህ መልአክ እንደሌሎቹ ሊቃነ መላእክት ሁሉ የሰው ልጆችን ይጠብቃቸዋል(ዳን.4÷13 ዘጸ. 23÷20 መዝ. 90÷11-13 )
ያማልዳል፣ ከፈጣሪ ያስታርቃቸዋል፡፡(ዘካ.1÷12)
በፈሪሀ እግዚአቤሔር እና በአክብሮተ መላእክት ያሉትን ድናቸዋል (ዘፍ.49÷15 መዝ.3÷37)
« እግዚአብሔር ሃይሉን የሚገልጥበትን ቅጣቱን ሊያሳይ ቢወድ አስቀድሞ መርጦ በወደዳቸው ለይቅርታ የተዘጋጁ የይቅርታ መላእክትን ያመጣል» (ሮሜ.9÷22)
ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀመናብርትን ድንቅ ገቢር ተአምራቱን ያዩ ምዕመናን

……የወላድ ማኅፀን እንዲፈታ
ስለተሸመ ከጌታ
አዋላጅ ብትኖር ባትኖርም
ሐኪም ሩፋኤል አይታጣም
በምጥ ጊዜ ሲጨነቁ የባላገር ሴቶች ሁሉ
የመልአኩን መልክ አንግተው ማርያም ማርያም ይላሉ
ማየጸሎቱን ጠጥተው ቶሎ ፈጥነው ይወልዳሉ ……
እያሉ ደጅ ጠንተው ይማጸኑታል፡፡

ዜና ግብሩን ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ከተናገረለት በመነሳት በቅዱሳን ላይ ድንቅ የሆነ እግዚአብሔር በመልአኩ አድሮ ያደረጋቸውን ተግባራት አበው የበረከት ምንጭ በሆነ ድርሳኑ ላይ አኑረው የበረከቱ ተካፋይ እንድንሆን ሰጥተውናል፡፡ በጉልህ ሠፍረው ከምናገኛቸው ብዙ ድንቅ ሥራዎች መሀል ጥቂቶቹን እነሆ
~~~> በሥነ-ስዕሉ የተማጸኑ፣ በምልጃው ታምነው የጸኑ ቴዎዶስዮስንና ዲዮናስዮስን በገሃድ ተገልጾ ለንግስናና ለጵጵስና ክብር አብቅቷቸዋል፡፡
~~~> የንጉስ ቴዎዶስዮስ ልጅም ጻድቁ አኖሬዋስም በፈጣሪው ህግ እየተመራ የሊቀ መናብርቱን መታሰቢያ ቤተ መቅደስ አሳንጾ ሲያስመርቅ ለበለጠ ክብር ልቡን አነቃቅቶ ለታናሽ ወንድሙ ለአርቃዴዋስ የነጋሢነት ስልጣኑን ትቶ መንኖ በስውርና በጽሙና እዲኖር ረድቶታል፡፡
~~~> በሊቀጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን አባቶች ለሊቀመናብርቱ ክብር በአሣ አንበሪ ጀርባ ላይ ያሳነጹትን መታሰቢያ ቤተ መቅደስ በወደቡ አጠገብ በእስክንድሪያ ሳለች ጠላት ዲያቢሎስ አነዋውጾ ለምስጋና የታደሙትን ምዕመናን ሊያጠፉ አሣ አንበሪውን ቢያውከው ወደ ሊቀመናብርቱ ተማጽነው እርዳን ቢሉ ፈጥኖ ደርሶ በበትረ መስቀሉ (ዘንጉ) ገሥጾ ከጥፋት ታድጓቸዋል፡፡
በቅዱስ መጽሐፍም እንደተገለጠው
~~~> ሣራ ወለተ ራጉኤልን አስማንድዮስ ከተባለው የጭን ጋንኤን ሲታደጋት የጦቢያን አባት የጦቢትን ዓይን አበራለት (መጽሐፍ ጦቢት)
ከዚህም አልፎ የይስሐቅን እናት ሣራን፣ የሶምሶንን እናት (እንትኩይን) ምክነታቸውን የቆረጠ ወልዶ ለመሳም ያበቃቸው ይኸው ፈታሔማኅጸን የልዑል እግዚአብሔር መልአክተኛ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ከመልአኩ ከቅዱስ ሩፋኤል ረድኤት ያሳድርብን አሜን !!!

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

Thursday, November 21, 2013

╬ ╬ ╬ በዓለ ሲመቱ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ╬ ╬ ╬

ህዳር 12

በዚህች ቀን የሰማይ ሰራዊት ሁሉ አለቃቸው መልአከ ምክሩ የምክሩ አበጋዝ ይለዋል የቅድስት ስላሴ መንጦላእትን የሚከፍትና የሚዘጋ ለፍጥረት ሁሉ የሚማልድ የገናናው ቅዱስ ሚካኤል የተሾመበት ቀን ነው። በህዳር ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ቤተ ክርስቲያናችን የታላቁ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን በዓለ ሲመት በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን አስተምህሮ ህዳር 12 ቀን ታላቁ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል በኢዮር ባለችው በአራተኛይቷ ከተማ በሚኖሩት ኃይላት እና በአሥሩ ነገደ መላእክት ላይ አለቃ ሆኖ የተሾመበት ቀን ነው፡፡እግዚአብሔር ሳጥናኤልን በትዕቢቱ ምክንያት ከሥልጣኑ ገፍፎ ወደ ምድር ሲጥለው ቅዱስ ሚካኤል በእርሱ ቦታ በዐሥሩ ከተማ በመቶውም ነገደ መላእክት ላይ ተሹሟል፡፡(ይህን ሁለተኛውን ሹመት ያገኘው በሚያዚያ 2 እንደሆነ አክሲማሮስ በሚባለው የቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ አናገኛለን፡፡)
የቅዱስ ሚካኤል ሹመት በነገደ መላእክት ላይ ብቻ ግን አይደለም ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይም ጭምር ነው ፡፡ ይህም እንደሆነ እንድንረዳ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባለውን እስራኤል ዘሥጋን ሲራዳና ሲጠብቅ እንደነበረ ተጽፎልን እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለኢያሱ በኢያሪኮ ምድረ በዳ እንደተገለጠለት “… ዐይኑን አንሥቶ ተመለከተ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ ሰው በፊቱ ቆመ፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ? አለው፡፡ እርሱም “እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁንም ወደ አንተ መጥቼአለሁ” (ኢያ.5፡13) ይለናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ስለ ቅዱስ ሚካኤል እንዲህ አለ "በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱም ዘንዶውን ተዋጉት፥ ዘንዶውም አልቻላቸውም፥ ከዚያም በኋላ በሰማይ ቦታ አልተገኘለትም። ራእ 12፤7 ነብዩ ዳንኤልም እንዲህ አለ "በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል" ዳን ፲፪፥፩። አዲስ አበባ ውስጥ ከተተከሉት አብያተክርስቲያናት ቀዳሚው ሾላ የሚገኘው የካ ሚካኤል ነው፤ የተተከለው በ 4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአብርሃና አጽብሃ ሲሆን ታቦቱ የመጣው ከታቦተ ጽዮን ጋር አብሮ ነው፤ ለዚህም ይመስላል አንዳንድ ምዕመናን አጥቢያቸው የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን እያለ የካ ሚካኤል ድረስ ሄደው የሚያነግሱት፤ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

Tuesday, November 19, 2013

ህዳር 11ህዳር 11

በዚህች ቀን የእመቤታችን እናት ቅድስት ሐና አረፈች፤ የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ቴክታ በጥሪቃ ይባላሉ፤ ይህ ቀራቸው የማይባሉ ባለጸጎች ነበሩ፤ ብዕላቸውም የወርቅ፣ የብር፣ የፈረስ፣ የበቅሎ፣ የሴት ባሪያ፣ የወንድ ባሪያ ነው፡፡ ከወርቁ ብዛት የተነሣ እንደ አምባር እንደ ቀለበት እያሠሩ፤ ከበሬው ከላሙ ቀንድ ያደርጉት ነበር፡፡ ይህን ያህል አቅርንተ ወርቅ፤ ይህን ያህል አቃርንተ ብሩር ተብሎ ይቈጠር ነበር እንጂ፤ የቀረው አይቈጠርም ነበር፡፡ ከዕለታት ባንደኛው በጥሪቃ ከቤተ መዛግብት ገብቶ የገንዘቡን ብዛት አይቶ፤ “ቴከታ እኔ መካን፤ አንቺ መካን ይህ ሁሉ ገንዘብ ለማን ይሆናል?” አላት “እግዚአብሔር እንጂ ከኔ ባይሰጥህ ወይ ከሌላ ይሰጥህ ይሆናል፤ አግብተህ አትወልድምን?” አለችው፡፡ “ይህንስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃል” አላት፤ በዚህ ጊዜ አዘኑ፤ ወዲያው ራእይ አይተዋል፤ ነጭ እንቦሳ ከበረታቸው ስታወጣ፣ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ስታደርስ ስድስተኛይቱ ጨረቃን፣ ጨረቃ ፀሐይን ስትወልድ አይተው፥ በሀገራቸው መፈክረ ሕልም /ሕልም ተርጓሚ/ አለና ሂደው ነገሩት፤ “ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ፤ ጨረቃይቱ ከፍጡራን በላይ የምትሆን ልጅ ትወልዳላችሁ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም እንደ ነቢይ እንደ ንጉሥ ያለ ይሆናል” አላቸው፡፡ እነርሱም “ጊዜ ይተርጉመው” ብለውት ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ፀነሰች፤ ወለደች ስሟን ሄኤማን አለቻት፤ ሄኤማን ማለት ረካብኩ ስእለትየ ረከብኩ ተምኔትየ /የፈለግሁትን የለመንኩትን አገኘሁ/ ማለት ነው፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፣ ቶና ሲካርን፣ ሲካር ሄርሜላን፣ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና አካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት:: እያቄምና ሐና ደጋግ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም ነበሩ በንጽህና በቅድስና የሚኖሩ ልጅ ግን አልነበራቸውም ህዝቡም ቅድስት ሐናን ይህቺ የበቅሎ ዘመድ ቢወልዷት እንጂ የማትወልድ፤ እግዚያብሔር እኮ ያደረቃት በኃጢያቷ ነው እያሉ ይዘልፏት ነበር ወደ ቤተ እግዚያብሔር መባ ይዘው ሲሄዱ አይቀበአለቸውም ነበር፤ በዚህም ሲያዝኑ ኖሩ ልጅ እንዲሰጣቸውም እግዚያብሔርን ዘወትር ይለምኑት ነበር፤ በኃላም እግዚያብሔር ጎበኛቸው ነሐሴ በባተ በ 7ኛው ቀን ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ዓለሙ ሁሉ ተሰብስቦ ቢመዘን አንድ የራሷን ጸጉር የማያ...ህል ደግ ፍጥረት ተወልዳለችሁ ብሎ ቅዱስ ገብርኤል አበሰራቸው፤ ሐና ጸነሰች ይህም በአገሬው ታወቀ ሊጠይቋት የሚመጡ ማህጸኗን እየዳሰሱ ይፈወሱ ነበር፤ አይናቸው የበራላቸውም ነበሩ፤ ግንቦት 1 ቀን ሊባኖስ ተራራ ላይ በነብያት ብዙ የተባለላት የድህነታችን መጀመሪያ የንጽህናችንም መሰረት የሆነችውን እመቤታችንን ወለደች፤ቅድስት ሐና በቅድስና በንጽህና ኖራ በዛሬዋ ዕለት አረፈች፤ይህች ቅድስት እናት ኢትዮጰያ ውስጥ በስሟ በርካታ ቤተክርስቲያን አላት አዲስ አበባ ውስጥ ቀደምቱ ኮተቤ የሚገኘው ኢያቄም ወሐና ነው በዛሬዋ እለት በደማቁ ተከብሮ ይውላል። በረከቷን ያድለን።
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ህዳር 8

ህዳር 8
በዚህች ቀን የቅድስት ስላሴን ዙፋን የሚሸከሙት አራቱ እንስሶች ክብረ በዓላቸው ነው፤ አርበአቱ እንስሳ ይላቸዋል ግዕዙ፤ በመዲናችን አዲስ አበባ አራት ኪሎ ቅዱስ በዓለ ወልደ ቤተክርስቲያን ታቦታቸው አለ በዛሬዋ ቀን ተዘክረው ይውላሉ፤ አርብአቱ እንስሳ መላአክት ናቸው የሰው ፊት የአንበሳ ፊት የንስር ፊትና የእንስሳ ፊት አላቸው፤ የሰው ፊት ያለው ለሰው ዘር የአንበሳ መልክ ያለው ለአራዊት የንስር መልክ ያለው ለአዕዋፍ የእንስሳ መልክ ያለው ለእንስሳት ይጸልያሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለእነርሱ እንዲህ ሰል መሰከረ ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁ...ት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር።አንዱም ለአንዱ። ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር። የመድረኩም መሠረት ከጭዋኺው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ፥ ቤቱንም ጢስ ሞላበት። እኔም። ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ፥ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዓይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ! አልሁ። ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፥ በእጁም ከመሠዊያው በጕጠት የወሰደው ፍም ነበረ። አፌንም ዳሰሰበትና። እነሆ፥ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢአትህም ተሰረየልህ አለኝ። ኢሳ 6፤1 ራዕ 5፤14 ፤3 በረከታቸውን ያድለን
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ህዳር 7

ህዳር 7 

በዚህች ቀን የፋርስና የልዳ ፀሐይ የተርሴስና የቤሩት ኮከብ የባህርና የየብሰ ብርሃን የጌታችን የመድሐኒታችን የእየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ምስክር የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት ቀን ነው፤ ይህንንም ቀን በመላ ኢትዮጰያ በተለይም በመዲናችን የሚገኘው አንጋፋው ገነተ ጽጌ አራዳ ጊዮርጊስ ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቁ ይከበራል። ታሪኩ በአጭሩ እንዲህ ነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሚያዚያ 23 ቀን በሰማዕትነት ከሞተ በኃላ አጋልጋዮቹ እጅግ የከበሩ ልብሶችና ያማሩ ሽቶዎች አዘጋጁ በከበረ አገናነዝም ገነዙት በመርከብም ጭነው ወደ ትውልድ አገሩ ልዳ አመጡት ነገር ግን ቤተሰቦቹ በሙሉ ማለትም አባቱ ዘሮንቶስ እናቱ ቴዎብስታ እህቶቹ ማርታና እስያ እንዲሁም አጭተውለት የነበረች እጮኛው ሁሉም ሞተው አገኙዋቸው፤ እንድርያስ የሚባል አጎት ነበረው ስጋውን ተቀበላቸው አገሬው ተሰበሰበ የእየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳስ አባ ቴዎድሮስ ተጠርቶ መጣ ቤተክርስቲያኑን አነጹለት ስጋውንም በዚያ በክብር አኖሩት፤ በዚህች ቀን እጅግ ብዙ የሆነ ድንቅ ታአምራትና ታላላቅ ኃይላት ተደረጉ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤተክርስቲያን ይህንን ቀን ታከብረዋለች። ታሪክ ብልሁ ንጉሳችን እምዬ ምኒሊክ አራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንን ሲሰሩ ከዚሁ ከልዳ የቅዱስ ጊዮርጊስ መቃብር ካለበት አፈሩን በመርከብ ከዚያም በበቅሎ አስጭነው አምጥተው ለቤተክርስቲያኑ መሰረት አድርገውታል ቅጥሩን ዙርያውንም ነስንሰውታል ይላል። ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚከበርባቸው ሚያዚያ 23 እረፍቱ ህዳር 7 ቅዳሴ ቤቱ ጥር 23 ዝርዎተ አጽሙ ናቸው፤ በረከቱን ያድለን። ምንጭ ገድለ ጊዮርጊስ ምዕራፍ 9
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ቁስቋም - ህዳር 6

እንኳን እመቤታችን ከስደት ተመልሳ ቁስቋም የገባችበት በዓል ቀን በሰላም አደረሳችሁ

ህዳር 6
በዚህች ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ አንዲሁም ከዮሴፍና ሶሎሜ ጋር 3 ዓመት ከ 6 ወር በስደት ከተንገላታች በኋላ ወደ አገራቸው የተመለሱበት ቀን ነው፤ ከግብጽ ሲመለሱ ጌታችን በእመቤታችን ጀረባ ላይ ሆኖ እነዚያ እውራንን ባበሩ ጣቶቹ ወደ ኢትዮጵያ ይጠቁም ያመለክት ነበር፤ እመቤታችንም ልጄ ሆይ ለምንድነው ጣትህን የምታመለክተው ብትለው "ያቺ የተባረከች አገር ናት እኔን የሚያመልኩ አንቺን የሚማልዱ በፍቅርሽ የነደዱ ቅዱሳን መነኮሳት የሚፈልቁባት አገር ናት፤ ያንቺ ዘመዶች ሰቅለው ይገድሉኛል በዚህች አገር ያሉ ግን ሳይዩኝ ያመኑኛል፤ አስራት በኩራትሽ ትሁን ብሎ ሰጥቷታል፡፡ በኪደተ እግራቸውም ጣና ሐይቅን፤ ዋልድባንና ሌሎችንም ቦታዎች ዞረው እንደባረኩ ድርሳነ ኡራኤልና ተአምረ ማርያም ላይ በስፋት ተጽፏል፡፡ እመቤታችንን ከሐና ማህጸን ፈጥሮ ከፍጥረተ ዓለም ለይቶ ከሁሉ አልቆ የእናት አማላጅ ትሁናችሁ ብሎ የሰጠን እግዚአብሔር ይመስገን። ዳግመኛም በዛሬዋ ቀን በኢትዮጵያ ምድር ታላቅ አምድ ወደቀ ይህም የመናገሻው ባህታዊ አባ ኤልያስ ነው፤ በ 400 ዓመት እድሜው ህዳር 6 1874 ዓ/ም አረፈ፤ በአጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ማለት ነው፤ የቅርብ ጊዜ ነው፤ ይህ አባት በግራኝ መሐመድ ወረራ ጊዜ የነበረ ነው፤ በዚያን ጊዜ በተለይ ኦሮሞዎች "አያና ውቃቢ" እያሉ በጣም ያከብሩት ነበር፤ ከመናገሻ እንጦጦ ኪዳነምሕረት እየተመላለሰ ሱባኤ እየገባ ጸሎት ያደርግ ነበር፤ በዛሬዋ ቀን ይህ አባት ሲሞት በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ከዋክብት ሲበታተኑ ሲራወጡ ታየ የተጉለቱ አባ በላይነህም ይህንን ምልክት አይቶ የአባ ኤልያስን መሞት ተረዱ ወደ መናገሻ ቢመጡ ሞቶ ተቀብሮ አገኙት፤ጎንደር ላይም በተመሳሳይ ከዋክብት ሲበታተኑ እነ አለቃ ወልደ ቂርቆስ በአይኔ አየሁ ሲሉ መስክረዋል ይላል መርስሄ ሐዘን ''ትዝታዬ ስለራሴ የማስታውሰው" በሚለው መጽሐፋቸው የከተቡልን። የሚገርመው ይህ አባት ከቤተመንግስት ወገን ሲሆን ተድላ ደስታን ንቆ 400 ዓመት በቅድስና በተጋድሎ የኖረ መናገሻንና እንጦጦ ኪደነምሕረትን በጸሎቱ የባረከ ይህንን የመሰለ ቅዱስ አለመዘከሩ ታሪኩ አለመጻፉ የታሪክ ጸሐፍት ወዴት አሉ ሊቃውንቱስ ወዴት ተደበቁ ያሰኛል፤ ከእመቤታችንንና ከመናገሻው አባ ኤልያስ በረከት ያሳትፈን። አሜን !!!

LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

Monday, November 11, 2013

ህዳር 3


ህዳር 3
በዚህች ቀን ጻድቁ ንጉስ ነአኩቶ ለአብ አረፈ፤ ይህ ጻድቅ የቅዱስ ላሊበላ የወንድም ልጅ ነው አባቱ ሐርበይ እናቱ መርኬዛ ይባላሉ፤ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ክህነትን ከንግስና ይዘው ኢትዮጰያን ከመሩ አራቱ የዛጌ ነገስታት አንዱ ነው፤ ቤተክርስቲያን ለነዚህ አራት ነገስታት ጽላት ቀርጻላቸው ቤተክርስቲያን አንጻላቸው የቅድስና ስም ሰጥታቸው ታከብራቸዋለች፤ ይምርሃነ ክርስቶስ፤ላሊበላ ነአኩቶ ለአብና ገብረ ማርያም ፤ ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በነገሰበት 40 ዓመት ሙሉ አርብ አርብ ቀን የጌታን ህማም እያሰበ በዘውዱ ፋንታ የእሾህ አክሊል ደፍቶ፤5 ጦር ዙሪያውን ተክሎ እየደማ እያለቀሰ ሲጸልይ ሲሰግድ ይውል ነበር፤ከእለታት በአንዱ ቀን ጌታችን ተገለጸለት እንዲህም አለው ወዳጄ ነአኩቶ ለአብ እኔ ለዓለም ደሜን ያፈሰስኩት አንድ ቀን ነው፤ አንተ ግን 40 ዓመት ሙሉ ደምህንንና እንባህን ስታፈስ ኖርክ ይበቃሃል አሁን ወደ እኔ ልወስድህ ነው ይለዋል፤ነአኩቶ ለአብም ጌታችንን “ጌታዬ ሆይ እዚህ ቦታ እኔን ብለው የሚመጡ ወገኖቼን ማርልኝ ይለዋል” ጌታም እውነት እልሃለው ቦታህን ባይረግጥ ዝክርህን ባያዘክር እንኳን ዝናህን ሰምቶ ያሰበህን ኃጢያቱ ምን ቢበዛ እምርልሃለው፤ ዳግመኛም እልሃለው 40 ዓመት ሙሉ እንባህን ያፈሰስክባት ይህች ድንጋይ እስከ እለተ ምጽአት እያነባች ትኖራለች ከዚህ ለሚጠጡ ለሚጠመቁ ድህነት ይሁናቸው ብሎታል፤ ዛሬም ድረስ የነአኩቶ ለአብ ቤተክርስቲያኑ ባለበት ከጣራው ስር ጻበሉ እየቆየ ጠብ ጠብ ይላል፤ክረምት ከበጋ እይለይም እንዲያውም በበጋ መጠኑ ይጨምራል ይህ ጸበል እጅግ መድሐኒት ነው፡፡ ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አሸተን ማርያምን አንጾ ከጨረሰ በኃላ ማዕጠንት ይዞ ቤተክርስቲያኑን ሲያጥን ብዙ ቅዱሳን እጣኑን አሽትተው ቤተክርስቲያን ውስጥ ጥቅጥቅ ብለው ቆሙ፤ እናንተ ደግሞ እንዴት መጣችሁ አላቸው እነርሱም እጣኑን አሽትተን መጣን አሉት በዚህም የተነሳ “አሸተን ማርያም ” ተብላለች፤ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በ70 ዓመቱ ህዳር 3 ቀን እንደነ ሄኖክ ተሰውሯል። በረከቱ ይደርብን፡፡ ምንጭ የይምርሃነ ክርስቶስና የነአኩቶ ለአብ ገድል
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ህዳር 1

ህዳር
እነሆ የተባረከ የህዳር ወር ባተ፤ ይህ ወር ቀኑ 10 ሰዓት ነው ሌሊቱ 14 ሰዓት፤ ቀኑ አጭር ነው ቶሎ ይመሻል፤ ሌሊቱ ደግሞ ረጅም ነው ቶሎ አይነጋም፤ ይህንንም ለማረጋገጥ ማታ 12 ሰዓት ላይ ሰዓትን መመልከት ነው በጣም ይጨላልማል፤ ታህሳስ ላይ ከዚህም ይጨምራል ቀኑ 9 ሰዓት ሌሊቱ 15 ሰዓት ይሆናል፤ ለዚህም ነው የገና ጀምበር የሚባለው፤ ህዳር 1 በዚህች ቀን በከሃዲው ንጉስ በዳኬዎስ ዘመን አራቱ ቅዱሳን በሰማዕትነት አረፈፉ፤ የእነዚህም ስማቸው መክሲሞስ፤ፍሊጶስ፤ፊቅጦርና፤ማንፍዮስ ነው፤ ንጉሱ ላቆመው ምስል አንሰግድም ጌታ አንዱ እግዚያብሔር ብቻ ነው ብለው ጮኹ ይላል፤ ንጉሱ ይህን ሰምቶ ተቆጣ በጅራፍ ገረፋቸው፤ በጋለ የብረት በትር ደበደቸው፤በበርኖስ እላቂ ጨርቅ ቆምጣጣና ጨው ነክረው ቁስላቸውን አሿቸው ይህንን ሁሉ ታገሱ በመጨረሻ በሰይፍ ትንሽ ትንሽ አካላቸውን እየቆራረጡ ገደሏቸወው፤ እነርሱም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ፤ በጸሎታቸው የሚገኝ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን።

LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥቅምት 30

እንኳን ለቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ ዓመተ ክብሩ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ አሜን።
ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ

ጥቅምት 30 ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ የተወለደበት ቀን ነው፤ በመዲናችን አዲስ አበባ ጨምሮ በስሙ በታነጹለት አብያተ ክርስቲያናት ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፤ ሚያዚያ 30 እረፍቱ ነው። ቅዱስ ማርቆስ ቁጥሩ ከ 72ቱ አርድእት ነው፤ የእናቱ ስም ማርያም ይባላል ቁጥሯ ከ 36ቱ ቅዱሳት አንስት ነው፤ በ 50ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደላቸው በዚህች ቅድስት እናት ቤት ሆነው ሲጸልዩ ነው፤ ሐዋ 2፤1 12፤12 ፤ ይህ ሐዋርያ ወንጌሉን የጻፈው ጌታ ባረገ በ 11ኛ ዓመት በሮማይስጥ ቋንቋ ሮም ላይ ሆኖ ነው፤ ምንም እንኳን ቅዱስ ጴጥሮስንና ቅዱስ ጳውሎስን ተከትሎ በተለያዩ ቦታዎች ወንጌልን ቢሰብክም በዋናነት ግብጽ በመዘዋወር ጣኦታት አፈራርሷል፤ ወልድ ዋህድ ብላ እንድትጸናም አድርጓል፤ ኢትዮጵያም ድረስ መጥቶ ወንጌልን ሰብኳል፤ መንበረ ጰጰስናው ግብጽ እስክንድርያ ነው፤ ኢትዮጵያ በዚህ በማርቆስ መንበር የተሾሙ 111 ጳጳሳትን ከግብጽ ስታስመጣ ኖራለች፤ እስክንድርያ እናቴ ማርቆስ አባቴ የምትለውም ለዚህ ነው፤ ቅዱስ ማርቆስን ሚያዚያ 30 ቀን ጣኦት አምላኪዎች በበሬ አስጎትተው ገድለውታል። ስለ ደብረ ማርቆስ ከተማ ጥቂት ልበል ከአባቶች የሰማሁት ነው፤ በዚህች ከተማ የነበሩት ጳጳስ የቅዱስ ማርቆስን ቤተክርስቲያን ከነጹ በኃላ ታቦተ ህጉን ለማስገባት አገሬው ይሰበሰባል፤ እናም ሽማግሌዎች ተነስተው ጳጳሱን ይመርቃሉ እንዲህ ብለው አባታችን ይህንን ደብር እንደሰሩልን እርሶንም እግዚያብሔር ይደብሮት ብለው መረቁ በዚህን ጊዜ በዙሪያው የነበሩት ጎረምሶች ከት ብለው ሳቁ፤ ግን ምን አሳቃቸው እግዚያብሔር ይደብሮት ማለት እኮ ታላቅ ሰው ያድርጎት ማለታቸው ነው ደብር ማለት ተራራ ማለትም አይደል። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

Tuesday, November 5, 2013

ጥቅምት 27 እንኳን አደረሳችሁ

እንኳን ለመድኃኒዓለም ዓመታዊ ክብረ በዓል ጥንተ ስቅለት፣ ለአቡነ መብዓ ጽዮን፣ እንዲሁም ለአባ ጽጌ ድንግል በዓለ እረፍታቸው አደረሳችሁ አደረሰን አደረሳችሁ አሜን!!!

ጥቅምት 27
በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ መብአ ጽዮን የእረፍት ቀናቸው ነው፤ ትውልዳቸው ሸዋ ትጉለት ውስጥ ነው እመቤታችን ያወጣችላቸው ስም ተክለ ማርያም ነው፤እኚህ ጻድቅ በጣም የሚታወቁበት ተጋድሎ አላቸው፤ ይህም አርብ አርብ ቀን የጌታችንን ሞቱን ለማሰብ ትልቅ ድንጋይ በጀርባቸው አዝለው እልፍ እልፍ እየሰገዱ ማታ ላይ ኮሶ ይጠጡ ነበር፤ ሀሞት መጠጣቱን ለማሰብ፤ ከጽድቃቸው ብዛት የተነሳ መቋሚያቸውን ቢተክሉት ሎሚና ትርንጎ አፈርቷል፤ጻደቁ የእረፍት ቀናቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጾ በርካታ ቃለ ኪዳን ገብቶላቸዋል፤ የእረፍታቸውን ቀን በእረፍት ቀኑ አድርጎላቸዋል፤ ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ቤተክርስቲያን የመድሐኒያለምን በዓል በደማቁ ታከብራለች፤ ይህም የለውጥ በዓል ነው፤ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው ስጋውን የቆረሰው አንዴ ብቻ ነው እርሱም መጋቢት 27 ቀን፤ ይህ ግን በአብይ ጾም ስለሚውል በአብይ ጾም ሀዘን እንጂ ደስታ ስለሌለ በዓል ማክበርም ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት 27 ተዛውሮ ደስ ብሎን ከድሆች ጋር እንድናከብረው ቤተክርስቲያ ስርዓት ሰርታለች፤ 
አቡነ መብዓ ጽዮን በ15ኛው መቶክፍለ ዘመን ልጅ በማጣታችው በጾምና በፀሎት ፈጣሪአቸውን ከሚለምኑ ባልና ሚስት ተወለዱ። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የዕለተ ዓርቡን መከራህን አሳየኝ ስለራሴ ፈጽሞ አለቅስ ዘንድ ብለው በጸለዩ ጊዜ መከራ መስቀሉን ለማየት ትፈቅዳለህን?ብሎ ጠየቃቸው።ጻድቁ አባ መባዓ ጽዬንም አዎ አይ ዘንድ እወዳለሁ ሲሉ ለጌታቸው መለሱለት።ያን ግዜም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕፅ መስቀል ላይም እጆቹና አወግሮቹ ተቸንክረውና ተዘርግተው ታዩ በራሱ ላይም የእሾህ አክሊል ደፍቶ ነበር።እንዲህ ሆኖ በሮም አደባባይ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንደታየው ታያቸው። የጌታን ሕማማተ መስቀል እያሰቡ ዘወትር ስለሚያነቡ ዓይኖቻቸው ጠፍተው ነበር።ነገር ግን እመብዙሀን የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ወደኝህ ጻድቅ አባት በዓት የብረሃን ጽዋዕ ይዛ መጥታ ዓይኖቻቸውን ቀብታ አድናቸዋለች።ከዚህ የተነሳ በትረ ማርያም እየተባሉ ይጠሩ ነበር።የጻድቁ መታሰብያ በዓል በየዓመቱ ጥቅምት 27 ቀን እና ከመድሃኔዓለም የስቅለት በዓል ጋር ይከበራል።ጥቅምት 27 ቀን ለወዳጆቹ እውነተኛውን ዋጋ የሚከፍል መድሃኔዓለም ክርስቶስ ለጻድቁ መብዓ ጽዬን ብዙ ቃል ኪዳን የገባበት ቀን ነው። ነው።†♥†አባ ጽጌ ድንግል†♥†
ሀገራቸው ወሎ ቦረና ሲሆን ደራሲና ማህሌታዊ ናቸው። ጻድቁ አባታችን ማህሌተ ጽጌን የደረሱ ሲሆን እንጀራ ሳይበሉ ባቄላ እየበሉ ውሃ እየጠጡ 9 ዓመት የቆዩ ትልቅ አባት አባት ሲሆኑ በስማቸው የተሰራ የአለት ፍልፍል የተሰራ ከወቅር የታነጸ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ከጋስጫ አጠገብ አላቸው። ቤተ ክርስቲያናቸው በረሃ ውስጥ ነው ያለው። ድሮ ጧት አንድ በ6 ሰዓት አንድ ማታ አንድ በድምሩ በ3 መነኮሳት ይታጠን ነበር። ዛሬ ግን ማዕጠንትም ቅዳሴም የለም። ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ 4 ሰዓት መንገድ ተሂዶ የአባ ጽጌ ድንግል ቤተ ክርስቲያን ይገኛል። መቃብራቸውም በዚሁ ቦታ እራሳቸው ባነጹት ነው ያለው። ዛሬ መነኮሳቱ ትተውት ከተማ ስለገቡ ተዘግቶ ነው የሚኖረው እጅግ በጣም ያሳዝናል። በሳምንት ብቻ አንድ ጊዜ ይታጠናል። ጻድቁ እመቤታችንን ስለሚወዱ ማህሌተ ጽጌን ደረሱ። ሌላም አስደናቂ አስደናቂ ድርሰቶችን ደርሰዋል። ገድልም አላቸው። ታቦትም በስማቸው ተቀርጿል። ቤተ ክርስቲያንም ከአለት የተወቀረ አላቸው። ጻድቁ አባታችን በብዙ ተጋድሎም ዛሬ ማለትም ጥቅምተ 27 ቀን አርፈዋል። በዚህ በአባ ጽጌ ገዳም ታላላቅ ታላላቅ የሆኑ የብራና መጽሐፍቶች ከ130 በላይ ይገኛሉ። በሐረግ ያሸበረቁ ናቸው። ነጮችና የእጅ ባለሙያዎች ያልደረሱባቸው ጠባቂዎቹ ይመሰገናሉ። የአባቶቻችን በረከት በሁላችን ላይ ይደር። የመድሃኔ አለም ቸርነቱ ምህረቱ በእኛ ላይ ይደር
አሜን!!

LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥቅምት 25

ጥቅምት 25
በዚህች ቀን አቡነ አቢብ አረፈ፤ሮማዊ ነው፤ጻድቅ ወሰማእት ይለዋል እንደ ሰማእታት ተጋድሏል እንደ ጻድቃንም በገዳም ኖሯል፤ ወላጆቹ በህጻንነቱ ሞቱበት፤እድሜው አስር ዓመት ሲሆን ለጣኦት መስገድን የሚያዝ መኮንን መጣ፤ አቡነ አቢብም መኮንኑ ፊት ቆሞ ጣኦቶቹን ረገመበት፤የአካሉን ትንሽነት አይቶ መኮንኑ ተደነቀ ይላል፤ ግን ከማሰቃየት ወደ ኃላ አላለም በመንገድ እስጎተተው፤አስገረፈው፤ስጋውን ሰነጣጠቀው እጅና እግሩን በመጋዝ አስቆረጠው፤ልዩ ልዩ ጸዋትኦ መከራ አደረሰበት ሚያዚያ 18 ቀን አንገቱን በሰይፍ ቆርጦ ገደለው፤ ቅዱስ ሚካኤል ከሞት አስነሳው፤ወደ አንድ ገዳምም ወሰደው፤ መስቀልና አስኬማ ሰጥቶ በዚያው ገዳም እንዲጋደል አዘዘው፤ለ 42 ዓመት እህል ውሃ ሳይቀምስ በተጋድሎ ኖረ፤ የእረፍቱ ቀን ሲደርስ ጌታችን እልፍ አእላፍ መላእክትንና ቅዱሳንን አስከትሎ ተገለጸለት ፤ ስምህን የሚጠራ መታሰቢያህን የሚያደርገውን እኔ ኃጢያቱን ይቅር እለዋለሁ ብሎ ብዙ ቃል ኪዳን ገባላት፤ ማቴ 10፤41 በዛሬዋ ቀንም በመላእክት ዝማሬ ነፍሱ ከስጋው ተለይታለች፤ ከአቡነ አቢብና ከሰማእቱ መርቆርዮስ በረከት ያሳትፈን፤
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥቅምት 23

ጥቅምት 23
በዚህች ቀን የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አባ ዮሴፍ አረፈ፤ ይህ አባት ከደጋግ ክርሰቲያኖች ወገን ነው፤ ወላጆቹ በመልካም አስተዳደግ አሳደጉት፤ ዲቁናን ቅስናን ተቀበላ በ 20 ዓመቱ መነኮሰ ገዳመ አስቄጥስ ገብቶ ለ 39 ዓመት በተጋድሎ ኖረ። ከዚህ በኃላ እንዲህ ሆነ 51ኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ሲሞት አባቶች ማንን እንሹም ብለው አሰቡ፤ አባ ዮሴፍንም ለመሾም ከእግዚያብሔር ምልክትን አገኙ ወደ ገዳሙ ሄደው ተገናኙት፤ በመልካም መስተንግዶ በበዓቱ አስተናገዳቸው፤ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ አድርገን ልንሾምህ ነው ይሉታል፤ እኔ ኃጢያተኛ ነኝ አይሆንም ይላቸዋል፤ ስንክሳሩ እንደሚለው በግድ አስረው ወደ እስክንድርያ ወሰዱት 52ኛ ሊቀ ጳጳስም አድርገው ሾሙት ይላል፤ የሚገርም ነው የዚህ ዘመን ፍጹም ተቃራኒ ማለትም አይደል ባልንጀራን እስር ቤት ከቶ እኔ ልሾም እኔ ልሾም የምንል ትውልዶች የበቀልንበት ዘመን፤ አባ ዮሴፍ አስረው እንደሾሙት እርሱም በእግዚያብሔርና በሰው ፍቅር ታስሮ ለ 19 ዓመት መንጋውን ተግቶ ጠበቀ ድሆችን እረዳ፤ ሀይማኖቱን አጸና በ 78 ዓመቱ በዛሬዋ ቀን አረፈ። ከቅዱስ ጊዮርጊስና ከአባ ዮሴፍ በረከት ያሳትፈን።
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl