Tuesday, November 5, 2013

ጥቅምት 27 እንኳን አደረሳችሁ

እንኳን ለመድኃኒዓለም ዓመታዊ ክብረ በዓል ጥንተ ስቅለት፣ ለአቡነ መብዓ ጽዮን፣ እንዲሁም ለአባ ጽጌ ድንግል በዓለ እረፍታቸው አደረሳችሁ አደረሰን አደረሳችሁ አሜን!!!

ጥቅምት 27
በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ መብአ ጽዮን የእረፍት ቀናቸው ነው፤ ትውልዳቸው ሸዋ ትጉለት ውስጥ ነው እመቤታችን ያወጣችላቸው ስም ተክለ ማርያም ነው፤እኚህ ጻድቅ በጣም የሚታወቁበት ተጋድሎ አላቸው፤ ይህም አርብ አርብ ቀን የጌታችንን ሞቱን ለማሰብ ትልቅ ድንጋይ በጀርባቸው አዝለው እልፍ እልፍ እየሰገዱ ማታ ላይ ኮሶ ይጠጡ ነበር፤ ሀሞት መጠጣቱን ለማሰብ፤ ከጽድቃቸው ብዛት የተነሳ መቋሚያቸውን ቢተክሉት ሎሚና ትርንጎ አፈርቷል፤ጻደቁ የእረፍት ቀናቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጾ በርካታ ቃለ ኪዳን ገብቶላቸዋል፤ የእረፍታቸውን ቀን በእረፍት ቀኑ አድርጎላቸዋል፤ ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ቤተክርስቲያን የመድሐኒያለምን በዓል በደማቁ ታከብራለች፤ ይህም የለውጥ በዓል ነው፤ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው ስጋውን የቆረሰው አንዴ ብቻ ነው እርሱም መጋቢት 27 ቀን፤ ይህ ግን በአብይ ጾም ስለሚውል በአብይ ጾም ሀዘን እንጂ ደስታ ስለሌለ በዓል ማክበርም ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት 27 ተዛውሮ ደስ ብሎን ከድሆች ጋር እንድናከብረው ቤተክርስቲያ ስርዓት ሰርታለች፤ 
አቡነ መብዓ ጽዮን በ15ኛው መቶክፍለ ዘመን ልጅ በማጣታችው በጾምና በፀሎት ፈጣሪአቸውን ከሚለምኑ ባልና ሚስት ተወለዱ። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የዕለተ ዓርቡን መከራህን አሳየኝ ስለራሴ ፈጽሞ አለቅስ ዘንድ ብለው በጸለዩ ጊዜ መከራ መስቀሉን ለማየት ትፈቅዳለህን?ብሎ ጠየቃቸው።ጻድቁ አባ መባዓ ጽዬንም አዎ አይ ዘንድ እወዳለሁ ሲሉ ለጌታቸው መለሱለት።ያን ግዜም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕፅ መስቀል ላይም እጆቹና አወግሮቹ ተቸንክረውና ተዘርግተው ታዩ በራሱ ላይም የእሾህ አክሊል ደፍቶ ነበር።እንዲህ ሆኖ በሮም አደባባይ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንደታየው ታያቸው። የጌታን ሕማማተ መስቀል እያሰቡ ዘወትር ስለሚያነቡ ዓይኖቻቸው ጠፍተው ነበር።ነገር ግን እመብዙሀን የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ወደኝህ ጻድቅ አባት በዓት የብረሃን ጽዋዕ ይዛ መጥታ ዓይኖቻቸውን ቀብታ አድናቸዋለች።ከዚህ የተነሳ በትረ ማርያም እየተባሉ ይጠሩ ነበር።የጻድቁ መታሰብያ በዓል በየዓመቱ ጥቅምት 27 ቀን እና ከመድሃኔዓለም የስቅለት በዓል ጋር ይከበራል።ጥቅምት 27 ቀን ለወዳጆቹ እውነተኛውን ዋጋ የሚከፍል መድሃኔዓለም ክርስቶስ ለጻድቁ መብዓ ጽዬን ብዙ ቃል ኪዳን የገባበት ቀን ነው። ነው።†♥†አባ ጽጌ ድንግል†♥†
ሀገራቸው ወሎ ቦረና ሲሆን ደራሲና ማህሌታዊ ናቸው። ጻድቁ አባታችን ማህሌተ ጽጌን የደረሱ ሲሆን እንጀራ ሳይበሉ ባቄላ እየበሉ ውሃ እየጠጡ 9 ዓመት የቆዩ ትልቅ አባት አባት ሲሆኑ በስማቸው የተሰራ የአለት ፍልፍል የተሰራ ከወቅር የታነጸ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ከጋስጫ አጠገብ አላቸው። ቤተ ክርስቲያናቸው በረሃ ውስጥ ነው ያለው። ድሮ ጧት አንድ በ6 ሰዓት አንድ ማታ አንድ በድምሩ በ3 መነኮሳት ይታጠን ነበር። ዛሬ ግን ማዕጠንትም ቅዳሴም የለም። ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ 4 ሰዓት መንገድ ተሂዶ የአባ ጽጌ ድንግል ቤተ ክርስቲያን ይገኛል። መቃብራቸውም በዚሁ ቦታ እራሳቸው ባነጹት ነው ያለው። ዛሬ መነኮሳቱ ትተውት ከተማ ስለገቡ ተዘግቶ ነው የሚኖረው እጅግ በጣም ያሳዝናል። በሳምንት ብቻ አንድ ጊዜ ይታጠናል። ጻድቁ እመቤታችንን ስለሚወዱ ማህሌተ ጽጌን ደረሱ። ሌላም አስደናቂ አስደናቂ ድርሰቶችን ደርሰዋል። ገድልም አላቸው። ታቦትም በስማቸው ተቀርጿል። ቤተ ክርስቲያንም ከአለት የተወቀረ አላቸው። ጻድቁ አባታችን በብዙ ተጋድሎም ዛሬ ማለትም ጥቅምተ 27 ቀን አርፈዋል። በዚህ በአባ ጽጌ ገዳም ታላላቅ ታላላቅ የሆኑ የብራና መጽሐፍቶች ከ130 በላይ ይገኛሉ። በሐረግ ያሸበረቁ ናቸው። ነጮችና የእጅ ባለሙያዎች ያልደረሱባቸው ጠባቂዎቹ ይመሰገናሉ። የአባቶቻችን በረከት በሁላችን ላይ ይደር። የመድሃኔ አለም ቸርነቱ ምህረቱ በእኛ ላይ ይደር
አሜን!!

LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

2 comments:

  1. እግዚያብሔር አምላክ ያበረከታቸውን ያሳድርብን በቸርነቱ ይጎብኘን በቃል ኪዳናቸውም ይጎብኘን።

    ReplyDelete