Monday, November 11, 2013

ጥቅምት 30

እንኳን ለቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ ዓመተ ክብሩ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ አሜን።
ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ

ጥቅምት 30 ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ የተወለደበት ቀን ነው፤ በመዲናችን አዲስ አበባ ጨምሮ በስሙ በታነጹለት አብያተ ክርስቲያናት ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፤ ሚያዚያ 30 እረፍቱ ነው። ቅዱስ ማርቆስ ቁጥሩ ከ 72ቱ አርድእት ነው፤ የእናቱ ስም ማርያም ይባላል ቁጥሯ ከ 36ቱ ቅዱሳት አንስት ነው፤ በ 50ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደላቸው በዚህች ቅድስት እናት ቤት ሆነው ሲጸልዩ ነው፤ ሐዋ 2፤1 12፤12 ፤ ይህ ሐዋርያ ወንጌሉን የጻፈው ጌታ ባረገ በ 11ኛ ዓመት በሮማይስጥ ቋንቋ ሮም ላይ ሆኖ ነው፤ ምንም እንኳን ቅዱስ ጴጥሮስንና ቅዱስ ጳውሎስን ተከትሎ በተለያዩ ቦታዎች ወንጌልን ቢሰብክም በዋናነት ግብጽ በመዘዋወር ጣኦታት አፈራርሷል፤ ወልድ ዋህድ ብላ እንድትጸናም አድርጓል፤ ኢትዮጵያም ድረስ መጥቶ ወንጌልን ሰብኳል፤ መንበረ ጰጰስናው ግብጽ እስክንድርያ ነው፤ ኢትዮጵያ በዚህ በማርቆስ መንበር የተሾሙ 111 ጳጳሳትን ከግብጽ ስታስመጣ ኖራለች፤ እስክንድርያ እናቴ ማርቆስ አባቴ የምትለውም ለዚህ ነው፤ ቅዱስ ማርቆስን ሚያዚያ 30 ቀን ጣኦት አምላኪዎች በበሬ አስጎትተው ገድለውታል። ስለ ደብረ ማርቆስ ከተማ ጥቂት ልበል ከአባቶች የሰማሁት ነው፤ በዚህች ከተማ የነበሩት ጳጳስ የቅዱስ ማርቆስን ቤተክርስቲያን ከነጹ በኃላ ታቦተ ህጉን ለማስገባት አገሬው ይሰበሰባል፤ እናም ሽማግሌዎች ተነስተው ጳጳሱን ይመርቃሉ እንዲህ ብለው አባታችን ይህንን ደብር እንደሰሩልን እርሶንም እግዚያብሔር ይደብሮት ብለው መረቁ በዚህን ጊዜ በዙሪያው የነበሩት ጎረምሶች ከት ብለው ሳቁ፤ ግን ምን አሳቃቸው እግዚያብሔር ይደብሮት ማለት እኮ ታላቅ ሰው ያድርጎት ማለታቸው ነው ደብር ማለት ተራራ ማለትም አይደል። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

No comments:

Post a Comment