Sunday, November 24, 2013

የገና ጾም - ጾመ ነቢያት


እንኳን ለጾመ ነቢያት በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ

ነቢያት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ፣ ወደ ግብፅ ስለ መሰደድ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለመጠመቅ፣ በትምህርተ ወንጌል ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ጸዋትወ መከራ ስለመቀበሉና ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ትንሣኤው፣ ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረው አላቆሙም፤ ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢት ፍፃሜ እንዲያደርሳቸው ፈጣሪያቸውን ተማፀኑትም እንጂ፡፡ በየዘመናቸው «አንሥእ ኃይለከ፣ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሳ እጅህንም ላክ» እያሉ ጮኹ፡፡ በጾምና በጸሎት ተወስነውም ሰው የሚሆንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት ቆጠሩ፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ሥጋዌው ትንቢት በተናገረ በ446 ዓመት ጌታችን ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆኗል፡፡

ነቢያት ተስፋው በዘመናቸው ተፈጽሞ በዓይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም እግዚአብሔር «የማያደርገውን አይናገር የተናገረውን አያስቀር» ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ፡፡ለዘመነ ሥጋዌ ቅርብ የነበሩት እነ ኢሳይያስ ጾሙ እንዴት መፈጸም እንዳለበትተናግረዋልም፡፡ ኢሳ 58-1፡፡

በመሆኑም በጌታ ልደት ትንቢተ ነቢያት ስለ ተፈጸመበት ይህጾም «የነቢያት ጾም» ይባላል፡፡ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት የሰውልጆች ተስፋ የተመሰከረበት የምሥራቹ የተነገረበት ስለሆነም «ጾመ ስብከት» ይባላል፡፡

ሰው በኃጢአት ቢወድቅም ፈጣሪው ሊያነሳው፤ ቢጠፋ ሊፈልገው እንደሚመጣ በተስፋ ሲጠብቀው ወልደ አምላክ ሰው መሆኑ የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ አዳም የልደቱን ነገር በትንቢት መነፅርነት ሲመለከተው /በነቢያቱ ትምህርትና ስብከት/፣ በሚኖርበት ዓመተ ፍዳ የምሥጢረ ሥጋዌ ብርሃን ከሩቅ ሲመለከተው ኖረ፡፡ ምሥጢረ ሥጋዌን በትንቢት መነፅርነት ማየቱም መከራውን እንዲቋቋመው የተስፋ ስንቅ ሆነው፡፡
ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር በጸጋ እንደተወለዱ በማመን ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር ከሚገልጡባቸው ነገሮች አንዱ ጾም ነው፡፡ ጾም የፍቅር ስጦታ ከመሆኑ በተጨማሪ ታዛዥነትንና የገቡትን ቃል ኪዳን ጠባቂነትንም ማሳያ ነው፡፡ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ ተፈጥሯአል፡፡ ኃጢአት ሠርቶ የእግዚአብሔር አርአያነቱን ቢያጠፋውም እግዚአብሔር ግን በአርአያው ሲፈጥረው ምን ያህል እንደሚወደው ማረጋገጫ ስለነበር በኃጢአት ሲወድቅም እንደወጣ ይቅር ሳይል ሊፈልገው መጣ፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሊፈልግ የመምጣቱ ተስፋ የተነገረበትንና ሱባኤ የተቆጠረበትን ዕለት ለማየት በመናፈቅ ከቀረበው መሥዋዕት አንዱ ጾም ነበር፡፡

ጾም ሰው ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር እና ታዛዥነት መግለጫና ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን ሲወድቁ መነሻ ከብልየት (እርጅና )መታደሻ፥ ከኃጢአት ቆሻሻ መታጠቢያ /ከንስሓ ጋር አብሮ ሲፈጸም/ ሳሙናም ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በሲና ተራራ ላይ እግዚአብሔር ወደ ነበረበት ጨለማ የገባው፣ አስፈሪውን መብረቅና ነጐድጓድ የተቋቁመው፣ ጨለማውን አልፎ የሰው ልጅ ያልሠራትን ሰማያዊ መቅደስ የተመለከተውና ወደ ዓለቱ ድንጋይ የቀረበው ራሱን ለእግዚአብሔር በጾም በመቀደስ ጭምር ነው፡፡ /የወገን ፍቅርና ለእግዚአብሔር ታዛዥነቱ እንዳለ ሆኖ/፡፡

ጾም እነዚህንና መሰል መንፈሳዊ በረከትን ስለሚያስገኝ ክርስቲያኖች ይመጣላቸው ዘንድ ይናፍቁታል፡፡ ከእነዚህ የሚናፈቁ አጽዋማት መካከል አንዱ ጾመ ነቢያት ነው፡፡ ጾመ ነቢያት የሚባለው ጾመ ገና፣ ጾመ ማርያም፣ ጾመ አዳም፣ ጾመ ፊልጶስ ተብሎ ይጠራል፡፡
ጾመ ነቢያትም ሆነ ሌሎች አጽዋማት ሲደርሱ ክርስቲያኖች የሚደሰቱት ጾም የሥጋ ፈቃድ እንዳይሰለጥንባቸው፣ ቁስለ ሥጋን በማከም፣ ቁስለ ነፍስን ስለሚፈውስላቸው ነው፡፡ ጾም የቁስል መፈወሻ ኃይለ መዊዕም(ድል ማድረጊያ) ይሆናል፡፡ ከሥጋም ከመንፈስም ተቆራኝቶ ሰውን ወደ ጥፋት የሚወስድን ክፉ መንፈስ ለማራቅም ይጠቅማል፡፡
ጾም የሥጋን ምኞት እስከመሻቱ ቆርጦ የሚጥል፣ ለመንፈስ ልዕልና የሚያበቃውን መሳሪያ የሚያስታጥቅ ነው፡፡ ክርስቲያን ይህን መሰል መንፈሳዊ የጦር እቃ እንዳይለየው አጥብቆ ይለምናል፡፡ የጦር ልምድ እንደሌለው ወታደር ጠላቱን የሚቋቋምበት የጦር ትጥቅ ሳይዝ አውላላ ሜዳ ላይ ባዶውን አይቆምም፡፡ መንፈሳዊ ውጊያን በሥጋዊ ጥበብ ማሸነፍ ስለማንችል ነው አበው ፍቅረ አጽዋማትን በአስተምህሮአቸውና በሕይወታቸው የሰበኩልን፡፡
ጾም እነዚህንና መሰል መንፈሳዊ በረከትን ስለሚያስገኝ ክርስቲያኖች ይመጣላቸው ዘንድ ይናፍቁታል፡፡ ከእነዚህ የሚናፈቁ አጽዋማት መካከል አንዱ ጾመ ነቢያት ነው፡፡ ጾመ ነቢያት የሚባለው ጾመ ገና፣ ጾመ ማርያም፣ ጾመ አዳም፣ ጾመ ፊልጶስ ተብሎ እንደሚጠራ መምህር ቃኘው ወልዴ ጾምና ምጽዋት በተሰኘው መጽሐፋቸው ገልጠውታል፡፡
ጾመ ነቢያት ለአዳም የተነገረው ትንቢት፣ የሚጠበቀው ሱባኤ እንደደረሰ የሚያበስር በመሆኑ ጾመ አዳም ይባላል፡፡ አዳም ቢበድልም ንስሐ ገብቶ በማልቀሱ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሀለሁ ብሎ የተነገረው ተስፋ መድረሱን፣ ምሥጢረ ሥጋዌ እውን ሊሆን መቃረቡን የሚያስረዳ ጾም ነው፡፡

ነቢያትም የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር ተገለጦ ስለታያቸው፣ ክርስቶስ ለሰው ልጅ የሚከፍለውን የፍቅር ዋጋ በትንቢት ተመልክተው ጾመውታልና ጾመ ነቢያት ይባላል፡፡ ይህ ጾም የራቀውን አቅርቦ፣ የረቀቀውን አጉልቶ ስላሳያቸው እስከሞት ድረስ ቢደበደቡም፣ ከመከራው ጽንአት የተነሣ ዋሻ ለዋሻ፣ ፍርኩታ ለፍርኩታ ቢንከራተቱም፣ የፍየል ሌጦ ለብሰው ቢዞሩም የተስፋው ቃል ሁሉን አስረስቶአቸው ከትንቢቱ ባለቤት ጋር በመንፈስ ተዋሕደው አልፈዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሐዋርያት ምን ሠርተን የክርስቶስን ልደት እንቀበለው ብለው ስለጾሙት ጾመ ሐዋርያት ተብሎ ይጠራል፡፡
ጾመ ነቢያት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ወልደ አብን ፀንሼ ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ በማለት ጾማዋለችና ጾመ ማርያም ይባላል፡፡ ይህን ያለችው በመደነቅ፣ አንድም በትሕትና አንድም ቀደምት አባቶቿ ነቢያት ሲጾሙት አይታ ጾማዋለች፡፡ እንዴት ፀንሼ እወልደዋለሁ ማለት ጥርጥር ሳይሆን ተደሞ፣ መደነቅ የነገረ ልደቱን አይመረመሬነት ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትሕትና ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ቅድስናዋን አይቶ በብስራተ መልአክ አማካኝነት ክርስቶስን እንደምትወልድ ቢነግራትም የትሕትና እናት ናትና ምን ሠርቼ የሰማይና ምድርን ፈጣሪ እችለዋለሁ ስትል ጾማዋለች፡፡
ይህ ጾም ጾመ ፊልጶስም ይባላል፡፡ ሐዋርያው ፊልጶስ በአረማውያን ዘንድ ገብቶ ሲያስተምር በሰማዕትነት ሲሞት አስከሬኑ ከደቀመዛሙርቱ ስለተሰወረ እግዚአብሔር የተሰወረውን የመምህራቸውን አስከሬን እንዲገልጽላቸው ከኅዳር አስራ ስድስት ጀምረው ሲጾሙ በሦስተኛው ቀን የመምህራቸው አስከሬን ቢመልስላቸውም ጾሙን ግን እስከ ልደት ቀጥለዋል፡፡ ጾምን ትእዛዝ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የፍቅርና የበረከት ምንጭ በመሆኑ ጭምር ደስ እያለን ብንጾመው የቅዱሳኑ በረከት ያድርብናል፡፡

ጾሙን ጾመ ሥርየት ፤ ጾመ መድኃኒት ያድርግልን ፤
ለብርሃነ ልደቱ በሰላም እና በጤና ያድርሰን ፤
ጾመን ለማበርከት ያብቃን - አሜን ፡፡


https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

No comments:

Post a Comment