Tuesday, November 19, 2013

ህዳር 7

ህዳር 7 

በዚህች ቀን የፋርስና የልዳ ፀሐይ የተርሴስና የቤሩት ኮከብ የባህርና የየብሰ ብርሃን የጌታችን የመድሐኒታችን የእየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ምስክር የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት ቀን ነው፤ ይህንንም ቀን በመላ ኢትዮጰያ በተለይም በመዲናችን የሚገኘው አንጋፋው ገነተ ጽጌ አራዳ ጊዮርጊስ ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቁ ይከበራል። ታሪኩ በአጭሩ እንዲህ ነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሚያዚያ 23 ቀን በሰማዕትነት ከሞተ በኃላ አጋልጋዮቹ እጅግ የከበሩ ልብሶችና ያማሩ ሽቶዎች አዘጋጁ በከበረ አገናነዝም ገነዙት በመርከብም ጭነው ወደ ትውልድ አገሩ ልዳ አመጡት ነገር ግን ቤተሰቦቹ በሙሉ ማለትም አባቱ ዘሮንቶስ እናቱ ቴዎብስታ እህቶቹ ማርታና እስያ እንዲሁም አጭተውለት የነበረች እጮኛው ሁሉም ሞተው አገኙዋቸው፤ እንድርያስ የሚባል አጎት ነበረው ስጋውን ተቀበላቸው አገሬው ተሰበሰበ የእየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳስ አባ ቴዎድሮስ ተጠርቶ መጣ ቤተክርስቲያኑን አነጹለት ስጋውንም በዚያ በክብር አኖሩት፤ በዚህች ቀን እጅግ ብዙ የሆነ ድንቅ ታአምራትና ታላላቅ ኃይላት ተደረጉ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤተክርስቲያን ይህንን ቀን ታከብረዋለች። ታሪክ ብልሁ ንጉሳችን እምዬ ምኒሊክ አራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንን ሲሰሩ ከዚሁ ከልዳ የቅዱስ ጊዮርጊስ መቃብር ካለበት አፈሩን በመርከብ ከዚያም በበቅሎ አስጭነው አምጥተው ለቤተክርስቲያኑ መሰረት አድርገውታል ቅጥሩን ዙርያውንም ነስንሰውታል ይላል። ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚከበርባቸው ሚያዚያ 23 እረፍቱ ህዳር 7 ቅዳሴ ቤቱ ጥር 23 ዝርዎተ አጽሙ ናቸው፤ በረከቱን ያድለን። ምንጭ ገድለ ጊዮርጊስ ምዕራፍ 9
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

No comments:

Post a Comment