Wednesday, January 30, 2019

ጥር 22-ወበዛቲ ዕለት

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
 ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it) 


ጥር 22-ዓለሙ ሁሉ የእግራቸውን ትቢያ ያህል እንኳን ዋጋ የሌለው የመነኮሳት ሁሉ አባት በገዳም ለሚኖሩ ቅዱሳን እንደ ኮከብ የሚያበሩላቸው ገድል ትሩፋታቸው በቃል ተነግሮ የማያልቅ እጅግ የከበሩ ርዕሰ መነኮሳት አቡነ እንጦንስ ዕረፍታቸው ነው፡፡
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል በዓለ ሲመቱ ነው፡፡
ርዕሰ መነኮሳት አቡነ እንጦንስ፡- እንጦንስ አበ መነኮሳት በሌላኛው ስማቸው ‹‹የበረሃው ኮከብ›› እየተባሉም ይጠራሉ፡፡ ወላጆቻቸው እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ አቡነ እንጦንስ ገና በ7 ዓመታቸው ነው የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ተምረው አጠናቀው የጨረሱት፡፡ መልካም ትሩፋታቸውንና ታዛዥነታቸውን የልጅ አዋቂ መሆናቸውም በሁሉ ዘንድ በተሰማ ጊዜ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አባ ቲዎናስም የእንጦንስን የልጅነት ጸጋና ዕውቀት ተሩፋታቸውን ሰምተው መልእክተኞችን ልከው አስመጧቸው፡፡ ካስመጧቸውም በኋላ ዲቁና ሲሾሟቸው ‹‹ይህ ሕፃን በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናል፣ ዜናውም በዓለሙ ሁሉ ይዳረሳል›› በማለት ትንቢት ተናግረውላቸዋል፡፡ እንጦንዮስ (እንጦንስ) ግብፃዊ ወላጆቻቸው እጅግ ባለጸጎችና ደጋግ ነበሩ፡፡ ወላጆቻቸው ከሞቱ በኋላ አባ እንጦንስ የወላጆቻቸውን ሀብት ወርሰው ከአንዲት እኅታቸው ጋር መኖር ጀመሩ፡፡
አንድ ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ወንጌል ሲነበብ ጌታችን ስለሀብታሙ ሰው የተናገረውን ምዕራፍ ሲነበብ አዳመጡ፡፡ ‹‹ልትጸድቅ ብትወድድ ሂደህ ያለህን ሁሉ ሽጥና ለድኆች ስጥ፤ መጥተህም ተከተለኝ በሰማያት መዝገብ ታከማቻለህ›› (ማቴ 19፡21) የሚለውን የጌታችንን ቃል በሰሙ ጊዜ ‹‹ይህ ስለእኔ የተነገረ ቃል ነው›› በማለት ከቤተ ክርስቲያን ወጥተው ወደ ቤታቸው በመሄድ ወላጆቻቸው ሲሞቱ ያወረሷቸውን ብዙ ንብረታቸውን በሙሉ ሸጠው መጸወቱ፡፡ የወረሱትንም 300 ሄክታር ወይም 12 ጋሻ መሬት ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች አከፋፈሉ፡፡ የቀረቻቸውን እኅታቸውንም ወስደው ሴቶች ገዳም አስገቧትና እሳቸውም ከመንደር ወጣ ብለው በመኖሪያ ቤታቸው አጠገብ በብሕትውና ሕይወት ብቻቸውን መኖር ጀመሩ፡፡
እንጦንስ አበ መነኮሳት በአንድ መቃብር ቤት ገብተው ኖሩ፡፡ ሰይጣናትም መጥተው ደብድበው ከመንገድ ላይ ጥለዋቸው ሄዱ፡፡ ከወደቁበት አንስተው ወደ ቤተ ክርስቲያን ወሰዷቸውና ጌታችን ፈወሳቸው፡፡ ተጋድሎአቸውንም እንደገና ጀመሩ፡፡ አሁንም ሰይጣናት በዱር አውሬዎች በአንበሳ፣ በተኩላ፣ በእባብና በጊንጥ እንተመሰሉ እየመጡ ይዋጓቸው ነበር፡፡ በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ ምግባቸውን ያበስላሉ፡፡ ወደ በዓታቸውም ሰውን አያስገቡም ነበር-በውጭ ሆነው ያነጋግሯቸዋል አንጂ፡፡ እንዲህም ሆነው 20 ዓመት ተቀመጡ፡፡ ጌታችንም ተገልጦላቸው ወጥተው እንዲያስተምሩ አዘዛቸውና ወጥተው ደቀ መዛሙርትን ማፍራት ጀመሩ፡፡ የመከራ ዘመን በመጣ ሰዓት ሰማዕትነትን ለመቀበል ወደ እስክንድርያ ጎዳናዎች ወጥተው ታዩ፡፡ መኰንኑም እንዳይታዩ ብሎ መከራቸው ግን እሽ አላሉትም፡፡ ሰማዕትነት የእሳቸው ክፍል አልነበረምና ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ከተገደለ በኋላ በመልአኩ ትእዛዝ ወደ በዓታቸው ተመለሱ፡፡ ከዐረብ ነጋዴዎች ጋር ወደ ሩቅ ቦታ ሄደው በበረሃ ብቻውን መኖር ጀመሩ፡፡
አባ እንጦንስ በረሃ ለበረሃ ሲንከራተቱ አጋንንት ክፉኛ ይዋጓቸው ነበር፡፡ በረሃነቱም ጽኑ ነው፣ ከሐሩሩ ጽናት የተነሣ በቀትር ጊዜ ከደንጊያ ላይ ተልባ ቢያሰጡ ይቆላል፡፡ እርሳቸውም ከዚያ ሄደው ሲጋደሉ አጋንንት ጾር በማንሳት ግማሾቹ ‹‹ከዚህ በረሃ እንደምን ደፍረህ መጣህ?›› ሲሏቸው ሌሎቹ ደግሞ ተቀብለው ‹‹አዳም ከወጣበት ገነት እገባ ብሎ ነው…›› እያሉ ይዘብቱባቸው ነበር፡፡ አባ እንጦንስ ግን በፍጹም ትሕትና ይታገሷቸዋል፡፡ ‹‹መሆንማ ይሆን ብላችሁ ነውን? እናንተ ብዙ እኔ አንድ ብቻዬን፤ እናንተ ረቂቃን እኔ ግዙፍ፡፡ እናንተ ኀያላን እኔ ደካማ በኀይለ ክርስቶስ ብችላችሁ ነው እንጂ ያለዚያስ አልችላችሁም›› እያሉ በትሕትና ሲዋጓቸው ኖሩ፡፡ ከዕለታት ባንድ ቀን ‹‹ይኸን የአጋንንት ጾር አልቻልሁትም ልሂድ እንጂ›› ብለው ሲያስቡ አደሩ፡፡ በማለዳም ተነሥተው በትራቸውን ይዘው ከደጃፋቸው ላይ ቆሙ፡፡ እንዳይቀሩም ጾሩ ትዝ እያላቸው እንዳይሄዱም በዓታቸው እየናፈቃቸው አንድ እግራቸውን ከውስጥ፤ አንድ እግራቸውን ከአፍአ አድርገው ሲያወጡ ሲያወርዱ መልአኩ የሰሌን ቆብ ደፍቶ፤ የሰሌን መቋረፊያ ለብሶ፤ የሰሌን መታጠቂያ ታጥቆ ብትን ሰሌን ይዞ መጣ፡፡ ምን ሊያደርግ ይሆን? ሲሉም ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ቆመ፡፡ ወዲያው ጸሎተ ወንጌልን፤ ነአኲቶን፤ ተሰሃለኒን፤ ደግሞ መጀመሪያ ለሥላሴ እጅ ነሳ፡፡ ከዚያ በኋላ አንድ አቡነ ዘበሰማያት ሰላሳ ስድስት ሰጊድ አድርሶ በመጨረሻ አንድ ጊዜ እጅ ነሥቶ ተቀመጠ፡፡ ወዲያው ያን ብትን ሰሌን አቅርቦ ይታታ ጀመር፡፡ ‹‹እንጦንስም እንግዲህማ የዚህን ፍጻሜ ሳላይ እንዴት እሄዳለሁ?›› ብለው ተቀምጠው ይመለከቱት ጀመር፡፡ ሰለስት ሲሆን ደግሞ ተነሥቶ አቡነ ዘበሰማያቱንም ሰጊዱንም ያንኑ ያህል አደረሰው፡፡ የቀሩትንም የሰዓቱንም የሠርኩንም እንደዚሁ አድርጎ አሳያቸው፡፡ ‹‹እንጦኒ ሆይ እንደዚህ ሥራ፤ ይህንን ከሠራህ ከአጋንንት ጠብ ትድናለህ›› አላቸው፡፡ እርሳቸውም የአጋንንትን ጦር መከላከያውን ሁሉ መልአኩ ባሳያቸው መሠረት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንዲሁ የሚሠሩ ሆኑ፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ስንፍናና የሰይጣን ውጊያ ወደሳቸው አልመጣም፡፡
ንጉሥ ቈስጠንጢኖስም ከአባ እንጦንስ ይባረክ ዘንድ ብዙ ጊዜ ደብዳቤ ጻፈላቸው፡፡ እርሳቸውም ቸል ባሉት ጊዜ ልጆቻቸው ደግ ንጉሥ መሆኑን ስለነገሯቸውና ስለለመኗቸው አባ እንጦንስ ጽፈው በደብዳቤ ባርከውታል፡፡ የአፍርንጊያው ንጉሥም መጥተው እርሱንና ሠራዊቱን ሁሉ እንዲባርኳቸው በክርስቶስ መከራዎች አማጽኖ ደብዳቤ ጻፈላቸው፡፡ ጌታችንንም በጸሎት ሲጠይቁ ደመና መጥታ ወስዳ አደረሰቻቸውና ንጉሡንና ሕዝቡን ሁሉ ባርከዋቸዋል፡፡
አባታችን ሠላሳ ዓመት በሞላቸው ጊዜ ጌታችን በዕለተ ዓርብ የለበሰውን ልብስ አልብሷቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አባ እንጦንስ የአክሊለ ሦክ ምሳሌ የሆነውን ቆብን፤ የከለሜዳ ምሳሌ የሆነውን ቀሚስ፤ የሀብል ምሳሌ የሆነውን ቅናትን፤ እንዲሁም ሥጋ ማርያምን ከመልአክ ከተቀበሉ በኋላ ‹‹በዚህ ዓለም እኔ ብቻ ነኝን ወይስ ሌላም አለ?›› ብለው በጸሎት ወደ እግዚአብሔር አመለከቱ፡፡ ጌታችንም ‹‹አለ እንጂ፣ አንድ ጊዜ ተራምዶ ሁለተኛውን ሳይደግም የሚሠራውን ሥራ ዓለሙ ሁሉ ቢሰበሰብ የማይሠራው፣ በጸሎቱ ዝናም የሚያዘንም፣ ፀሐይን የሚያወጣ፤ እንደዚህ ያለ ወዳጅ አለኝ›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ይኽን ሰው ለማየት ልሂድን ልቅር? ቢሉት እንዲሄዱ ፈቀደላቸው፡፡
የታዘዘ መልአክም እየመራ አባ ጳውሊ ካሉበት በዓት አደረሳቸው፡፡ እርሳቸውም ከአባ ጳውሊ ጋር ብዙ መንፈሳዊውን ነገር ተጨዋወቱ፡፡ ተጨዋውተውም ሲያበቁ አባ ጳውሊ ለአባ እንጦንስ ለብቻቸው በዓት ሰጧቸው፡፡ እንጦንዮስም ከዚያ ሆነው ጸሎታቸውን ሲያደርግ ዋሉ፡፡ ወትሮ ለአባ ጳውሊ ግማሽ ሰማያዊ ኅብስት ይወርድላቸው የነበረ ሲሆን ማታ ግን አንድ ሙሉ ኅብስት ወረደላቸው፡፡ አባ ጳውሊም በፈቃደ እግዚአብሔር ወደ እርሳቸው መምጣታቸውን ያን ጊዜ ዐወቁ፡፡ ወዲያው ያን ኅብስት ከሁለት ከፍለው እኩሌታውን ለራሳቸው አስቀርተው እኩሌታውን ለአባ እንጦንስ ሰጧቸው፡፡ ያን ተመግበው ሌሊት ሁለቱም በየሥራቸው ክብራቸው ተገልጾ ሲተያዩ አድረዋል፡፡ ጳውሊ ዓሥር ጣቶቹን እንደ ፋና ሆነው እያበሩለት አራቱን ወንጌል ሲያደርስ እንጦንዮስም እንደ ዓምደ ብርሃን ተተክለው ሲያበሩ ተያይተዋል፡፡ በዚያች ሌሊት ከዚያ ቦታ ጨለማ ጠፍቶ አድሯል፡፡
በነጋው ሠለስት እላፊ ሲሆን ጸሎታቸውን አድርሰው ሲያበቁ ተገናኝተው ሲጨዋወቱ ጳውሊ እንጦንዮስ ያረጉትን ቆብ አይተው ‹‹ይህ ከማን አገኘኸው?›› አሏቸው፡፡ እንጦንስም ‹‹እርሱ ባለቤቱ ሰጠኝ›› አሉ፡፡ ጳውሊም የጌታችንን ቸርነት ያደንቁ ጀመር፡፡ እንጦንዮስም ‹‹እስኪ በኔ ብቻ የሚቀር እንደሆነ ለሌላም የሚያልፍ እንደሆነ አመልክትልኝ›› አሏቸው፡፡ ጳውሊም ሲያመለክቱ ወዲያው ተገለጸላቸውና ደስ አላቸው፡፡ ‹‹ምን አየህ?›› ቢሏቸው ‹‹ነጫጭ ርግቦች በጠፈር መልተው አንተ እየመራሃቸው ተከትለውህ ሲሄዱ አየሁ›› አሏቸው፡፡ ‹‹ይህስ ምንድን ነው?›› ቢሏቸው ‹‹እሊህማ በዚህ በቆቡ የምትወልዳቸው ንጹሐን ጻድቃን ልጆችህ ናቸው›› አሏቸው፡፡ ‹‹ሁለተኛ አመልክትልኝ›› አሏቸው፡፡ ጳውሊም ካመለክቱ በኋላ አዝነውና ተከፍተው ተመለከቷቸው፡፡ ‹‹ምነው?›› ቢሏቸው ‹‹በክንፋቸው ጥቁር ተቀላቅሎባቸው አየሁ›› አሉ፡፡ ‹‹ምንድን ናቸው?›› ቢሏቸው ‹‹ጽድቅና ኀጢአት እየቀላቀሉ የሚሠሩ ልጆችህ ናቸው›› አሏቸው፡፡ እንጦንስም ካዘኑ በኋላ ‹‹ሦስተኛም አመልክትልኝ›› አሏቸው፡፡ አባ ጳውሊም ለሦስተኛ ጊዜ ካመለከቱ በኋላ በድንጋጤ ቃላቸውን ከፍ አድርገው ጮኹ፡፡ አባ እንጦንስም ‹‹ምነው?›› ቢሏቸው አባ ጳውሊ እንዲህ አሉ፡- ‹‹ነገር ግን በመጨረሻ ዘመን የሚነሡቱ እንደ ቁራ ጠቁረው አየሁዋቸው›› አሉ፡፡ ‹‹ምንድን ናቸው?›› ቢሏቸው ‹‹ሀሳሲያነ ሢመት (ሹመት ፈላጊዎች)፣ መፍቀሪያነ ንዋይ (ገንዘብ የሚወዱ) እና ከመኳንንትም ጋር በጥዋት ማዕድ የሚቀመጡ በፍጻሜ ዘመን የሚነሡ ኀጥአን ልጆችህ ናቸው›› አሏቸው፡፡ ይህን ጊዜ አባ እንጦንስ ‹‹ያለ ንስሓ ባይጠራቸው እስኪ አመልክትልኝ›› አሉ፡፡ አባ ጳውሊም አመለከቱ ነገር ግን የዚህ ምላሽ አልመጣላቸውም፡፡
ከዚህ በኋላ አባ ጳውሊ ስለ ቆቡ አባ እንጦንስን ‹‹እንግዲህ ይህን ከራስህ ያደረግኸውን ለኔ ስጠኝ ላንተ ሌላ ሠርተህ አድርግ›› አሏቸው፡፡ አባ እንጦንስም ‹‹ይህንንስ እንዳልሰጥህ ከባለቤቱ ተቀብዬዋለሁ፡፡ ነገር ግን ሥራውን ለምጄዋለሁ ሌላ ሠርቼ ላምጣልህ›› አሏቸው፡፡ ጳውሊም ‹‹እንግዲያስ አትዘግይ ቶሎ ሠርተህ አምጣልኝ›› አሏቸው፡፡ እንጦንስም ሠርተው ይዘው ሲመጡ ጳውሊ ዐርፈው ነፍሳቸውን መላእክተ ብርሃን ይዘዋት ሲያርጉ ተመለከቱ፡፡ መላእክቱም ‹‹ጳውሊ ዐርፏልና ሂደህ ቅበረው›› አሏቸው፡፡ ‹‹ይህንሳ የያዝኩትን ቆብ ልተወውን?›› ቢሏቸው፡፡ ‹‹አትተው አድርግለት›› ብለው መለሱላቸው፡፡ ይህም በምንኩስና የሠሩት ሥራ ከንቱ እንዳይደለ ለማጠየቅ ነው፡፡ አባ እንጦንስም ቢሄዱ አባ ጳውሊ መጽሐፋቸውን ታቅፈው፣ አጽፋቸውን ተጎናጽፈው፣ ከበዓታቸው ዐርፈው አገኟቸው፡፡ ከራስጌአቸው ቆመው ሲያለቅሱ ሁለት አንበሶች መጡ፡፡ ‹‹የመቃብሩን ነገር እንደምን ላድርግ?›› እያሉ ሲጨነቁ አንበሶቹ በእጃቸው እንደመጥቀስ አድርገው የመቃብራቸውን ቦታ አሳዩአቸው፡፡ እርሳቸውም ለክተው ሰጧቸው፡፡ አንበሶቹም ከቆፈሩላቸው በኋላ አባ ጳውሊን ቀብረው ‹‹እንግዲህ ከዚህ እኖራለሁ›› ብለው አሰቡ፡፡ ነገር ግን ጌታችን ‹‹በዚህ መኖር አይሆንልህም ሂድ›› አላቸው፡፡ አጽፋቸውንና መጽሐፋቸውን ይዘው ሄደው እስክንድርያ ደርሰው ለሊቀ ጳጳሱ ለቅዱስ አትናቴዎስ ያዩትንና የሆነውን ሁሉ ነገሯቸው፡፡ አቡነ አትናቴዎስም ‹‹ልሄድና ከዚያ ልኑር?›› ሲሏቸው ‹‹አይሆንልህም አትሂድ እኔም አስቤ ነበር ነገር ግን የማይሆንልኝ ሆኖ መጣሁ እንጂ›› አሏቸው፡፡ ‹‹ባይሆን ለበረከት ያህል አጽፊቱን ጥለህልኝ ሂድ›› ብለው ሲለምኗቸው ትተውላቸው ሄዱ፡፡
አባ እንጦንስ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግና በፍጹም ትሕትናቸው ይታወቃሉ፡፡ ምንም እንኳ ታላቅና በትሩፋት የበለጸጉ ቢሆኑም በጳጳሳትና በካህናት ፊት ራሳቸውን በትሕትና ዝቅ አድርገው እጅ ይነሷቸው ነበር፡፡ ዲያቆንም ቢሆን ወደ እርሳቸው በመጣ ጊዜ ከእርሱ ጠቃሚ ነጥብን ለማግኘት ይሞክራሉ፤ ላገኙትም ዕውቀት ሳያመሰግኑ አያልፉም፡፡ የእርሳቸውንም ምክር ሽተው ለሚመጡ ሁሉ እጅግ ጠቃሚ የሕይወት ምክሮችን ይሰጣሉ፡፡ ዓለምን ንቆ ገንዘብ ስለመውደድ ከመነኮሰ በኋላ ለድሆች አከፋፍሎ ለራሱም ጥቂት ንብረት ያስቀረ አንድ ወንድም ወደ አባ እንጦንስ መጣ፡፡ አባ እንጦንስም ይህን ካወቁ በኋላ እንዲህ አሉት፡- ‹‹መነኩሴ ለመሆን ከፈለግህ ወደ መንደር ሂድና ጥቂት ሥጋ ገዝተህ ራቁትህን በሰውነትህ ላይ ተሸክመህ ተመለስና ወደእኔ ና›› አሉት፡፡ ያም ወንድም ይህን ባደረገ ጊዜ ወፎችና ውሾች በሰውነቱ ያለውን ሥጋ ለመብላት ሲሉ በሰውነቱ ላይ በማንዣበብ እየሞነጨሩ አቆሰሉት፡፡ በደረሰም ጊዜ አባ እንጦንስ እንዳዘዙት ማድረጉን ጠየቁት፡፡ እርሱም የቆሰለውን ሰውነቱን ባሳያቸው ጊዜ እንጦንስ ‹‹ዓለምን ከናቁ በኋላ ገንዘብ የሚመኙትም እንደዚሁ በአጋንንት ይገደላሉ›› አሉት፡፡
አቡነ እንጦንስ ዕረፍታቸው በደረሰ ጊዜ ዕለተ ሞታቸውን ዐውቀው ደቀ መዛሙርቶቻቸውን ሲሰናበቱ እንዲህ ብለው መከሯቸው፡- ‹‹ይህ ከእናንተ ጋር የማደርገው የመጨረሻው ግንኙነት ነው፡፡ በዚህም ሕይወት ዳግመኛ እንዳንተያይ ዐውቃለሁ፡፡ አሁን እኔ የምሞትበት ጊዜ ነው፡፡ ከጥረታችሁ ግዴለሽ አትሁኑ፡፡ በብሕትውና ሕይወት ፍጹም ተስፋ አትቁረጡ፡፡ ዕለት ዕለት እንደምትሞቱ ሆናችሁ ኑሩ፡፡ አስቀድሜ እንደተናገርኩት ነፍስን ከርኩስ አሳቦች ለመጠበቅ በሥራ ትጉ፡፡ ቅዱሳንን ምሰሉ፡፡ ቅድስና የሌለውን የስንፍና ትምህርታቸውን ታውቃላችሁና ወደ መናፍቃን አትቅረቡ፣ ኑፋቄያቸው ለማንም ግልጽ ነውና፡፡››
ከዚህም በኋላ ጊዜ ዕረፍታቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጦላቸው ቃልኪዳን ገባላቸው፡፡ እርሳቸውም ለልጃቸው ለመቃርስ ስለ ወደፊቱ መነኮሳትና ገዳማት ትንቢትን ነገሩት፡፡ ወደፊት መነኮሳት ከበዓታቸው እየወጡ በዓለም እንደሚቅበዘበዙ ተናገሩ፡፡ ዕረፍታቸው በደረሰ ጊዜ በትራቸውን ለልጃቸው ለመቃርስ፣ ምንጣፋቸውን ለአቡነ አትናቴዎስ፣ የፍየል ሌጦ አጽፋቸውን ልጃቸው ለሊቀጳጳሱ ለሰራብዮን እንዲሰጡ አዘዙና በ120 ዓመታቸው በ356 ዓ.ም ጥር 22 በታላቅ ክብር ዐረፉ፡፡
ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን አሜን!
+ + + 


ሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል፡- ኢዮር፣ ራማ እና ኤረር የተባሉ ሦስት የመላእክት ከተሞች አሉ፡፡ እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክት ከፈጠራቸው በኋላ በነገድ 100 በአለቃ 10 አድርጎ በሦስቱ ሰማያት አስፍሯቸዋል፡፡ ኢዮርን በ4፣ ራማን በ3፣ ኤረርንም በ3 ከፍሎ ነው በዓሥሩ ከተማ ያሰፈራቸው፡፡
በዚህም መሠረት ኢዮርን ላይና ታች አድርጎ በ4 ከተማ ከፍሏታል፡፡ በእርሷ ያሉትን መላእክትን በ40 ነገድ 4 አለቃ አድርጎ ከፈላቸው፡፡ የመጀመሪያው ነገድ ‹‹አጋእዝት›› ይባላሉ፡፡ አለቃቸው ሣጥናኤል ነበር፤ እርሱም የመላእክትን ሁሉ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ያሳርግ ነበር፡፡ ከክብሩ ሲዋረድ ቅዱስ ሚካኤል በምትኩ ተሹሞበታል፡፡ ሁለተኛው ነገድ ‹‹ኪሩቤል›› ይባላሉ፡፡ እነርሱም መንበረ ሥላሴን ይሸከማሉ፡፡ የቀሳውስት አምሳል ናቸው፡፡ አለቆቻቸው ገጸ ሰብና ገጸ አንበስ ናቸው፡፡ በሦስተኛው ከተማ በኢዮር ያሉት ሱራፌል ይባላሉ፡፡ የዲያቆናት አምሳል ናቸው፡፡ በትንቢተ ኢሳያስ በምዕራፍ 6 ላይ የተገለጹትና ኢሳያስን ከለምጹ እንዲፈወስ ያደረጉት ናቸው፡፡ አለቆቻቸው ገጸ ላህምና ገጸ ንስር ናቸው፡፡ (በነገራችን ላይ ‹‹ከሩቤል›› ወይም ‹‹ሱራፌል›› የሚባሉ የግለሰብ መጠሪያ ስሞች ስህተት ናቸው፡፡ አንደኛ እነዚህ ስሞች የብዙ መላእክት መጠሪያን የሚወክሉ ናቸው፡፡ ለአንዱ ሲሆን ‹‹ኪሩብ፣ ሱራፊ›› ይባላል፡፡ ‹ኪሩቤል› ወይም ‹ሱራፌል› ማለት ግን የብዙ ቁጥራቸው መጠሪያ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የቅዱሳን መላእክትን ስም እንዳለ በቁሙ ወስዶ ለግል መጠሪያ ስም ማዋል ተገቢ አይደለም፡፡ ‹‹ወለተ ሚካኤ፣ ክብፈ ገብርኤል….›› እየተባሉ ይሰየማሉ እንጂ ቀጥታ ‹ሚካኤል›፣ ‹ገብርኤል› እያሉ ሰዎችን መሰየም ስህተት ነው፡፡ 4ኛው ከተማ በኢዮር ያሉት ኃይላት ይባላሉ፡፡ የእሳት ሰይፍ ይዘው በሥሉስ ቅዱስ ፊት የሚቆሙ ናቸው፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት የዛሉና የደከሙ ክርስቲያኖችን የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ አለቃቸውም ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡)
ዳግመኛም እግዚአብሔር በራማ ያሉትን መላእክት በ30 ነገድ በ3 አለቃ አድርጎ ከፈላቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ‹‹አርባብ›› ይባላሉ፡፡ የሥላሴ እልፍኝ አስከልካዮች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን መንበር በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ ሁለተኞቹ በራማ ከተማ ያሉት ‹‹መናብርት›› ይባላሉ፡፡ ለእግዚአብሔርን እጅግ ቅርብ የሆኑ ናቸው፡፡ የመብረቅ ጋሻቸውን የእሳት ጦራቸውን ይዘው የሥላሴ ጋሻ ጃግሬዎች ሆነው በተጠንቀቅ ይቆማሉ፡፡ የሰውን ችግር ለእግዚአብሔር ያቀርባሉ፡፡ መዝ 88፡6፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሦስተኞቹ በራማ ከተማ ያሉት ‹‹ሥልጣናት›› ይባላሉ፡፡ መላውን ፍጥረት ለመጠበቅ ሥልጣን የተሰጣቸውና የምጽአት ዕለት አዋጅ ነጋሪዎች ናቸው፡፡ ዳን 12፡1፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ሱርያል ነው፡፡
ዳግመኛም እግዚአብሔር በኤረር ያሉትን መላእክት በ30 ነገድ በ3 አለቃ አድርጎ ከፈላቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ‹‹መኳንንት›› ይባላሉ፡፡ የስላሴ የእሳት ባለ ቀስት ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ልዩ ጠባቂዎች ናቸው፤ በተለይ በአደጋ ጊዜ ሎጥን እንዳዳኑት ፈጥነው ይደርሳሉ፡፡ በዕለተ ምጽዓት የሰውን ሁሉ ዐፅም ሰብስበው ለትንሣኤ ዘጉባኤ ያበቃሉ፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ሰዳካኤል ነው፡፡ ሁለተኛዎቹ ‹‹ሊቃናት›› ይላሉ፡፡ የሥላሴ የእሳት ፈረሶች ናቸው፡፡ በእሳት ፈረስ ይመላለሳሉ፡፡ እነዚህም 24ቱ ካህናተ ሰማይ ሲሆኑ አለቃቸው ቅዱስ ሰላታኤል ነው፡፡ በኤረር ከተማ የሰፈሩት ሦስተኛዎቹ ‹‹መላእክት›› ይባላሉ፡፡ ፍጥረትን ሁሉ የሚጠብቁ ናቸው፡፡ አለቃቸው ቅዱስ አናንኤል ነው፡፡ በእነዚህ የማይጠበቅ ፍጥረት የለም፡፡ ከአዝርእት ጀምሮ ሁሉን ይጠብቃሉ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ 7 መላእክትን አየሁ›› (ራዕ 8፡2) እንዳለ ሊቃነ መላእክት በቁጥር 7 ናቸው፡፡ እነርሱም፡- ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ሩፋኤል፣ ቅዱስ ራጉኤል፣ ቅዱስ ዑራኤል፣ ቅዱስ ፋኑኤል እና ቅዱስ አፍኒን ናቸው፡፡
‹‹ዑራኤል›› የሚለው ስም ‹ዑር› እና ‹ኤል› ከሚሉ ሁለት ቃላት የተመሠረተ ስም ነው፡፡ ‹‹ዑራኤል›› ማለት ትርጉሙ ‹‹የብርሃን ጌታ፣ የአምላክ ብርሃን›› ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ዑራኤል ከ7ቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ በመብረቅና በነጎድጓድ ላይ የተሾመ መልአክ ነው፡፡ በመሆኑም መጽሐፈ ሄኖክ እንደሚገልጸው መባርቅት ለጥጋብና ለበረከት እንዲበርቁ ነጎድጓድም ለሰላም እንዲሆን ያሰማራል፡፡ ምሥጢረ ሰማይንና ሰማያዊውን ዕውቀት ሁሉ ለሄኖክ የገለጸለት መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ የፀሐይን፣ የጨረቃን፣ የከዋክብትንና የሰማይ ሠራዊትን ብርሃንን የሚመራው ይኸው ገናና መልአክ ነው፡፡ መጽሐፈ ሄኖክ 28፡13፡፡
መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ሆኖ በተሰቀለ ጊዜ ክቡር ደሙን በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ በብርሃነ መነሳንስ በዓለም ላይ የረጨው ይኸው ገናና መልአክ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል ጽዋ ጥበብን አጠጥቶ ሰማያዊውን ምሥጢር የገለጠለት መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ ዕውቀት ተሠውሮበት ለነበረው ለኢትዮጵያዊው ሊቅ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም በእመቤታችን ትእዛዝ ጽዋ ጥበብን አጠጥቶ ሰማያዊውን ምሥጢር የገለጠለት ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ ‹‹ዑራኤል የተባለ መልአክ ሊረዳኝ መጣ፡፡›› መጽሐፈ ዕዝራ 2፡1፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር የሕይወትና የይቅርታ ዝናም በምድራችን ላይ ያዘንብ ዘንድ እንዲሁም የእርሻችንን አዝመራ በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ ለምግብነት እንዲበቃ ከፈጣሪ ዘንድ ምሕረትን የሚለምን መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
ሊቁ አባ ጊዮርጊስም በመልአኩ አማላጂነት እጅግ ብዙ ድርሰቶችን የደረሱት መልአኩ ጽዋ ሕይወትን ካጠጣቸው በኋላ ነው፡፡ በመጀመሪያም አባ ጊዮርጊስ የተወለዱት በቅዱስ ዑራኤል አብሳሪነት ነው፡፡ በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ የተመሠረቱ አብዛኞቹ ቅዱሳት ገዳማት በቅዱስ ዑራኤል መሪነት ነው፡፡ ድርሳኑ ላይ የማይጠቅሳቸው የሀገራችን የከበሩ ቅዱሳት ገዳማትና ቅዱሳን ነገሥታት የሉም፡፡
የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክን ከልጇ ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስትሰደድ መንገድ እየመራ ወደ ግብጽ እና ወደ አገራችንን ኢትዮጵያ ያመጣቸው ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ እመቤታችንን ከተወደደ ልጇ ጋር በደመና ጭኖ መላ ኢትዮጵያን ካስጎበኛት በኋላ ቅድስት አገራችንን ለእመቤታችን የዓሥራት አገር እንድትሆን ያደረገው መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል በዓመት 3 ዓበይት በዓላት አሉት፡፡ ጥር 22 በዓለ ሲመቱ ነው፡፡ መጋቢት 27 የጌታችንን ክቡር የሆነ ወርቀ ደሙን ለዓለም የረጨበት ነው፡፡ ሐምሌ 22 ቀን ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበትና ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል የዕውቀትን ጽዋ ያጠጣበት ዕለት ነው፡፡
የሊቀ መላእክት የቅዱስ ዑራኤል ጥበቃው አይለየን! በጸሎቱ ይማረን !

No comments:

Post a Comment