Sunday, December 2, 2012

ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
 
አቡነ ተክለኃይማኖት ቡልጋ ደብረ ጽላልሽ ወይም ዞረሬ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ክልል ከአባታቸው ከካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ መጋቢት መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው፤ በ፲፩፻፺፯ . ታሕሣሥ ፳፬ቀን ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸውም ፍስሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ትርጓሜውም የጽዮን ተድላዋ ደስታዋ ማለት ነው፡፡

ወላጅ አባታቸው በካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብ ግብረ ዲቁናን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው በአሥራ አምስት ዓመታቸው ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ /ጌርሎስ/ ዲቁናን ተቀብለዋል፡፡ በዚህም ቅድስት ቤተክርስቲያንን በወጣትነት ዕድሜያቸው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ዱር አደን ሄደው ሳለ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ መረጣቸው። ስማቸውንም «ተክለ ኃሃይማኖት» አለው፡፡ ትርጓሜውም የኃይማኖት ፍሬ ማለት ነው፡፡
አባታችንም ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ሲጀምሩ
«
አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ . . . ደካማ ለሆንኩ ለእኔ ያለ አንተ የሚያፀናኝ የለም። ለምፍገመገም ለእኔ ያለ አንተ ደጋፊ የለኝም። ለወደቅሁ ለእኔ ያለአንተ የሚያነሳኝ የለም። ለአዘንኩ ለእኔ ያለአንተ የሚያረጋጋኝ የለም። ለድሀው ለእኔ ያለ አንተ መጠጊያ የለኝም፡፡»
/
ገድለ ተክለ ኃይማኖት ምዕ ፳፰ -
ይህን ብለው ትሕትና በተሞላበትና በተሰበረ ልብ ወደ ፈጣሪያቸው ከለመኑ በኋላ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ኃይማኖት መልሰዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ፀሐይ ተብለዋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን ክታቡ ስለ ቅዱሳን መንፈሳዊ ተጋድሎ ሲገልፅ:-
«
እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሱ» /ዕብ. ምዕ ፲፩ ፴፫ / እንዳለ አባታችን ቅዱስ ተክለሃይማኖትም በመንፈሳዊ ተጋድሎ እንዲሁም በትህትና በተአምራት አላዊ የነበረውን ንጉሥ ሞቶሎሚን ወደ ክርስትና መልሰዋል፡፡
«
ጽድቅን አደረጉ» እንዳለው አባታችን ወንጌልን በተጋድሎ ሕይወታቸው ተርጉመዋል፡፡
«
የአንበሶችን አፍ ዘጉ» ምዕ ፲፩ ፴፫ /ምዕ ፲፩ ፴፬ /እንዳለው አባታችንም የአውሬውን የዘንዶውን ራስ ቀጥቅጠዋል።
«
ከሰይፍ ስለት አመለጡ» እንዳለው አባታችንም ሞቶሎሚ ከወረወረው ጦር በተአምራት ድነዋል፡፡
«
ከድካማቸው በረቱ» እንዳለው አባታችንም ያለ ዕረፍት በብዙ ተጋድሎ በጾምና በስግደት በብዙ መከራ በርትተዋል፡፡
ይህን ሁሉ ገድልና ትሩፋት እየፈጸሙ ዕረፍታቸውም በደረሰ ጊዜ ደቀመዝሙሮቻቸውን «ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኮስ መንግሥተ ሰማይ ይገባል ማለት አይደለም፤ ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ ይገባል እንጂ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ፤ ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ፤ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ትእዛዛቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ እያሉ ይመክሯቸው ነበር. . .» በኋላም «ለዓለም ጨው ለራሴ አልጫ ሆንኩ፤ ለዓለም ብርሃን ለራሴ ጨለማ ሆንኩ፣ ከእውነተኛው ዳኛ ከጌታዬ ፊት ስቆም ምን እመልሳለሁእያሉ በፍጹም ትህትና እና በልዩ መንፈሳዊ ተመስጦ ይጸልዩ ነበር፡፡
ለእግዚእ ኃረያ ሠናይት ወለጸጋ ዘአብ አዳም፤
እኔምሆሙ አንሰ በቃለ ሰላም፤
እለ ወለዱ ኪያከ ብርሃነ ዓለም፤
ተክለ ሃይማኖት ስቡረ ዓፅም እምብዝኃ ቀዊም፤
አውጽአነ እምአዘቅተ ሕርትምና ወእምፅቡር ዓምዓም፤
አቡነ ጸሊ በእንቲአነ ጸሎተከ ወትረ ይብጽሐነ፡፡

አንተን የዓለም ብርሃን የሆንክ የወለዱ መልካም የሆነች እግዚእ ኃረያና ጸጋ ዘአብን ሰላም እላቸኋለሁ፡፡ በቁመት ብዛት አግርህ የተሰበረ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ሆይ ዘወትር ከሚፈታተነን ወደ ጥልቁም ሊጥለን ከሚቃረነን ጠላት ዘወትር በጸሎትህ ስለእኛ እየማለድክ አድነን፡፡ የጸሎትህም በረከት ዘወትር ትድረሰን፡፡


"በዚህች ዕለት ህዳር ፳፬ የማይሰለች ተጋዳይ የክብር ኮከብ የገዳም መብራት ስም አጠራሩ የተመሰገነ ቅዱስ ደግ የአባታችን የኢትዮጵያ ፀሀይ ፃድቁ ተክለሀይማኖት በስዕሉ ላይ እንደምናየው ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር ሃያአምስተኛ ሆነው ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያለሁ የስላሴን መንበር ያጠኑበት ቀን ነው፡፡"


በዚህች ቀን ህዳር 24 ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት  24 ካህናተ ሰማይ እንደ አንዱ ሁነው መንበረ ጸባዎትን ያጠኑበት ታላቅ ዓመታዊ መታሰቢያ ክብረ በዓል በሰላም በፍቅር እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን የጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ረድኤት በረከታቸው ምልጃና ጸሎታቸው ከመላው ህዝበ ክርስቲያን ጋር ይሁን አሜን። እለቱ ካህናተ ሰማይ ተብሎ በቤተ ክርስቲያናችን ይከብራል፡፡ 
እኛንም ከጻድቁ ረድኤት በረከት ይክፈለን፡፡

2 comments: