Tuesday, December 18, 2012

ታህሳስ 10



 በዚህች ዕለት ቅድስት ስርስት አረፈች፤ አገሯ ቁስጥንጥንያ ነው ወላጆቿ በሀብት በዘመድ የከበሩ... ናቸው፤ 12 ዓመት ሲሆናት ለአንድ ታላቅ ባለጸጋ ሊድሯት አሰቡ እርሷ ግን ገዳማትን ተሳልሜ ልምጣ ብላ ከቤት ወጣች አልተመለሰችም፤ አንድ ማቅ የለበሰ ግርማው የሚያስፈራ መነኩሴ አገኘች፤ በምናኔ መኖር እንደምትፈልግ የልቧን ነገረችው የእግዚያብሔር ፈቃድ ይሁን ብሎ ጸጉሯን ላጭቶ አመነኮሳት፤ ከዚህ በኃላ አናብስት አናምርት አክይስት አቃርብት ካሉበት ነቀዐ ማይ ልምላሜ ዕጽ ከሌለበት ዘር ተክል ከማይገኝበት ከጽኑ በርሃ ሄደች፤ ሰው ሳታይ 27 ዓመት በተጋድሎ ኖረች፤ አንድ የበቃ አባት ነበር ሲላስ ይባላል፤ ዛሬ እናቶቻችን ስንቅ ቋጥረው መባ ይዘው ግብር ሰፍረው በገዳም ያሉ አባቴን ጠይቄ ልምጣ ብለው እንደሚሄዱት፤ ይህም አባት ስንቅ ይዞ በበርሃ የሚኖሩ አባቶችን ለመጠየቅ ራቅ ወዳሉ ገዳማት ሄደ፤ አንድ ወሻም አገኘ፤ ወደ ውስጥም ዘለቀ፤ ሰው እንዳለ አውቆ አባቴ ባርኩኝ አለ፤ ቅድስት ስርስትም አባ ሲላስ አንተ ካህን ስትሆን እንዴት ባርኩኝ ትላለህ አለችው፤ ደነገጠ ስሜን እንዴት አወቀችው ካህን መሆኔንስ ማን ነገራት አለ፤ አረፍ በል አለችው ጨዋታ ጀመሩ እንጀራ ሰጣት አልበላችም፤ አመጣጥህ መልካም ነው ብላ ታሪኳን ሁሉ ነገረችው እርሱም ጻፈው በዚያኑ ቀን አረፈች፤ ይህም ታህሳስ 10 ነው፤ ገንዞ በዚያው በገዳሟ ቀበራት፤ ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን። ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ሃይማኖታችንን ካቀኑት አርዮስን አውግዘው ከለዩት 318 ሊቃውንት አንዱ የሆነው አባ ኒቆላዎስ ያረፈበት ቀን ነው፤ ይህ አባት በህጻንነቱ እሮብና አርብ ቀን 9 ሰዓት ካልሆነ የእናቱን ጡት አይጠባም ነበር፤ 9 ዓመቱ ቅስና ተቀበለ፤ ታላቅ ጸጋ ድንቆችን የማድረግ ሀብት ተሰጥቶት ነበር፤ ዲዮቅልጥያኖስ ለብዙ ዘመናት በእስር ቤት አሰቃይቶታል፤ በኃላም ይህ ከሀዲ ንጉስ ሞቶ ደገኛው ንጉስ ቆስጠንጢኖስ ሲነግስ ከእስር ተፈታ በአገረ ሜራ ኤጲስቆጶስ ሆኖ ህዝቡን በፍቅር አገለገለ በዛሬዋ ቀንም በክብር አረፈ። የቅድስት ስርስትና የአባ ኒቆላዎስ በረከት ይደርብን።

No comments:

Post a Comment