Thursday, December 20, 2012

ታሀሳስ 12




በዚህች ቀን ታላቁ ኢትዮጰያዊው ጻድቅ አባ ሳሙኤል አረፈ። የትውልድ ቦታው አክሱም ነው፤ 18 ዓመቱ ከአቡነ መድሐኒነ እግዚ እጅ ምንኩስናን ተቀበለ በዚያው በደብረ ባንኮል 13 ዓመት በተጋድሎ ኖረ፤ከዚያም ወደ ጎንደር ደምቢያ ሄደ 3 ወር ከዘረጋ ሳያጥፍ ከቆመ ሳያርፈ እህል ውኃ ሳይቀምስ በተጋድሎ ኖረ፤ከድካም ብዛት አጥንቱ ተሰብሮ ወደቀ ጌታችን ተገለጸለት አበረታው ያንተ ክፍልህ እዚህ አይደለም ወደ ዋልድባ ሂድ አለው፤ ወደ ዋልድባ ሄደ በዚያም ግርማ ሌሊቱን ድምጸ አራዊቱን ታግሶ ማቅ ለብሶ ድንጋይ ተንተርሶ በተጋድሎ ኖረ። ይህ አባት ለእመቤታችን ልዩ ፍቅር ነበረው ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን በቀን 64 64 ጊዜ ይጸልይ ነበር፤ውዳሴዋን እየደገመ መንገድ ሲሄድ ከምድር ክንድ ከስንዝር ከፍ ይላል፤ እመቤታችን እንደ ጓደኛ ታነጋግረው ነበር ይላል። ውኃ ላይ ውዳሴ ማርያም ሲደግም ውኃው ተለውጦ ህብስት ይሆንለት ነበር፤ ከቦታ ቦታ የሚጓጓዘውም በአንበሳ ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከመሞቱ በፊት ጌታችን ብዙ ቃል ኪዳን ገብቶለታል፤ 100 ዓመቱ ታህሳስ 12 ቀን አርፏል። ታሪክን ታሪክ ያነሳዋል እንዲሉ፤ ስለ ዋልድባ ገዳም ገናንነት በድርሳነ ኡራኤል ላይ እመቤታችን እንዲህ ብላ ተናገረች:-     " ከኤሮድስ ፊት ሸሽቼ በተሰደድኩኝ ጊዜ ልጄ በእጁ ደመና ጠቀሰ በዚያች በምታበራ ደመና ላይ ተቀምጠን መጀመሪያ ወደ ናግራን ( የዛሬዋ  የመን) ሄድን ከዚያም ወደ ሐማሴን (ኤርትራ) አክሱምን ጎብኝተን፤ የተከዜን ወንዝ ተሻግረን ታላቅ ጫካ የለበሰ ገዳም አገኘን በዚያም አረፍን ያቺ ቦታ ዋልድባ ትባላለች፤ ልጄ ስለዚያች ገዳም እንዲህ አለኝ እናቴ ሆይ በኃላኛው ዘመን ለኔ የሚገዙ ባንቺም ፍቅር የነደዱ ቅዱሳነ መነኮሳት በዚህች ገዳም ይበዛሉ፤ የጣመ የላመ አይበላበትም የሞቀ የደመቀ አይለበስበትም፤   ምግባቸው ይህ መራራ የዛፍ ስር ነው ብሎ አሳየኝ አለች። ይህ የነገራት ትንቢት የተፈጸመው 485 / ነው። ይህ የሚገርም ሰፊ ታሪክ ቢኖረውም በአጭሩ እንዲህ ይነበባል፤ ከሸዋ ቡልጋ ብዙ መነኮሳት ወደ እየሩሳሌም እንሄዳለን ብለው ተነሱ፤ አዲስ አበባ መጡ ፉሪ ወጨጫንና እንጦጦን በማቋረጥ ወሎ አማራሳይንት አቋርጠው በጎንደር ሊቦ አድርገው ከምከም በለሳና ደባርቅን ጨርሰው የሊማሊሞን ጠመዝማዛ ተራራ በማቋረጥ ዋልድባ ደረሱ ይላል። እዚያም ጌታ ተገለጸላችው የናንተ ክፍላችሁ እዚህ ነው፤ በምጽአት እስክመጣ በዚህ ነው የምትኖሩት ለበቁ አባቶች እየተገለጻችሁ የገዳሙን ስርዓት ንገሩ ብሎ ሰውሯቸዋል፤ እነዚህ ስውራን መነኮሳት ዛሬም ድረስ አሉ፤ይህ በምን ይታወቃል  ቢሉ ዋልድባ  ጸጥ  ረጭ ብሎ የጸናጽል የደወል ድምጽ ይሰማል ልብን የሚማርክ የእጣን መአዛም ይሸታል፤አልፎ አልፎ እነዚህ ስውራን  በጾም በጸሎት የበረታ ሰውን ተገልጸው አነጋግረውት ይሰወራሉ፤ይህንንም እዚያ የሚኖሩ አባቶች መሰከሩልን። ጻድቁ ተክልዬ ከነዚህ ስውራን ቅዱሳን ጋር 3 አርባ ማለትም 120 ቀን አብረው እንደኖሩ ገድለ ተክልሃይማኖት ላይ ተጽፏል።  ከመልአኩ ከቅዱስ ሚካኤል  ከአባታችን  ከአቡነ  ሳሙኤል  በረከት ያሳትፈን ይህንን ገዳም ለመሳለም ያብቃን።

No comments:

Post a Comment