Thursday, December 6, 2012

ህዳር 27


በዚህች ቀን ቅዱስ ያዕቆብ በሰማዕትነት አረፈ፤ አገሩ ፋርስ ነው የንጉስ ወታደር ሲሆን ቀድሞ የሚያመልከው ጸሐይና ጨረቃን ነበር፤ በኃላ ጌታችን ጠራው ፍቅሩንም በልቡ ቀረጸበት ጣኦት ማምለኩን ተወ፤ በዚህም ንጉሱ ተቆጣ ደሙ እንደ ውሃ እስኪወርድ አስገረፈው፤ የሚገርመው እንደ ግንድ ድቡልቡል እስኪሆን ድረስ አካሉን ትንሽ ትንሽ እየቆረጡ ጨረሱት በመጨረሻም አንገቱን ቆርጠው ገደሉት፤ የዚህ አባት መቃብሩ ግብጽ ብሕንሳ ይገኛል፤ ብሕንሳ ማለት የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የትውልድ ስፍራ ናት። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ :- አርዮስን ለማውገዝ ኒቂያ ከተሰበሰቡት 318 ሊቃውንት መካከል በአርዮሳውያ... እንዲሁም በጣኦት አምላኪዎች መከራ ያልደረሰበት ያልተሰቃየ አባት የለም፤ ከሁሉም የሚገርመው ግን የቶማስ ነው፤ መርዓስ የምትባል አገር ኤጲስ ቆጶስ ነው፤ ጣኦት አምላኪዎች ይህን አባት 22 ዓመት አካሉን ትንሽ ትንሽ እየቆረጡ ወስደው ለጣኦታቸው ያጥኑት ነበር፤ ከጥፍሮቹ ጀምረው፤ ጣቶቹን፤ እጆቹን፤ ጆሮዎቹን፤ ከንፈሩን ምላሱን አፍንጫውን... ቆርጠው ጨረሱት በግንድ የተለበለበ ግንድ መሰለ ይላል፤ ነፍሱ ግን አልወጣችም ደቀ መዛሙርቱ በቅርጫት ተሸክመው በኒቂያ ከጉባዬው አስገቡት፤ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ ጉባዬውን ለማስጀመር ወደ አዳራሽ ሲገባ መጀመሪያ አቅፎ የሳመው ይህንን አባት ነው፤ አገላብጦ ሳመው ይላል፤ ይህ አባት እንዲህም ሆኖ በርካታ አሰደናቂ ተአምራቶች ይሰራ ነበር። ታሪካቸው ስለሚመሳሰል በጥቂቱ አነሳነው እንጂ ሰፊ ታሪክ አለው፤ በረከታቸውን ያድለን።

No comments:

Post a Comment