Wednesday, November 28, 2012

አባ እንጦንስ





አባ እንጦንስ በበረሃ ከሚኖሩ መነኮሳት አንዱ ነው:: ሰይጣን ከኒህ አባት ከበኣታቸው እየመጣ በብዙ ፆር ይፈትናቸው ስለነበር አብዝተው ወደ አምላካቸው ይጸልዩ ነበር:: በሃይምሮአቸው ውስጥም ብዙ የጾር ፈተናዎች ይመላለሱበት ነበርና አምላካቸውን እንዲህ በማለት ጠየቁ:: እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ እንተን ብቻ እመልካለሁ መዳንንም እሻለሁ ስለዚህ ወደ እዚህ በረሃ አንተን ፈልጌ መጣሁ ነገር ግን እነዚህ የኃጢአት ምኞት ወይም ክፍ ሃሳቦች ሊተውኝ አልቻሉም ስለዚህ ካንተ የሚያለያዩኝ ናቸውና እባክህ ምን እንደማደርግ መንገዱን አሳየኝ? ምን ባደርግ ነው ይህ ፆር ሊተወኝ የሚችለው? በማለት ወደ አምላካቸው ጸሎታቸውን አቀረቡ:: ከተወሰነ ጊዜ በኃላ አባ እንጦንስ ከበኣቱ ሲወጣ እንድ ሰው ሥራ እየሰራ አየ:: ያም ሰው ሥራውን ከጨረሰ በኃላ ሲጸልይ ይመለከተዋል ደግሞም ጸሎቱን ከጨረሰ በኃላ ተመልሶ ሌላ ሥራ ሲሰራ ያየዋል አሁንም ሥራውን እንደጨረሰ ደግሞ ጸሎት እየጸለየ አምላኩን ያመሰግናል:: ለካ ያ ሰው ለአባ እንጦንስ ሥርዓተ ምንኩስናን ለማስተማር የተላከ መልአክ ነበርና እኔ እንዳሳየሁህ ብታደርግ ትድናለህ ብሎ ሲናገር አባ እንጦንስ ሰማው:: ይህን እንደሰማ አባ እንጦንስ ደስታቸው ወሰን አልነበረውም:: ከዚያም በሁዋላ አባ እንጦንስ መልአኩ እንዳስተማራቸውና እንደነገራቸው አደረጉ በምግባር ብዙ ሥራዎችንም ሰሩ:: ይህንን የእሳቸውን በጎ ምግባርና ደግ አባትነት ዝና የሰሙ ሰዎች ከገዳመ አስቄጥስ መጡ:; በጀልባ እየሄዱ እያለ አንድ በጣም ያረጀ አረጋዊ ሰው አገኙ:: እነዚህ ሰዎች ግን ይህ አረጋዊ ሰው ማን እንደሆነ አላወቁም ነበር:: አሁንም እነዚህ ሰዎች ስለ ቅዱሳት መጽሐፍት: ስለ አባቶቻችን እምነትና ምግባር ደግሞም ስለ ሚሰሩት ሥራ አጥብቀው ይወያዩ ነበር:: ያ በእድሜ የበለጸጉ አረጋዊ አባት ግን ምንም አይናገሩም ብቻ ዝም ብለው የሚነጋገሩትንና የሚወያዩትን ነገሮች እያደመጡ አብረዋቸው ከእነርሱ ጋር ይሄዱ ነበር:: ወደ ባህሩ ዳርቻ ሲደርሱ እነዚህ ሰዎች ወርደው ዕቃቸውን ይዘው ወደ ሚሄዱበት አቅጣጫ መራመድ ሲጀምሩ እኒህ አባት አብረዋቸው ወርዱና ከእነዚህ ሰዎች ጋር ጉዞአቸውን ቀጠሉ:: ከሄዱበት ቦታ እንደደረሱ አባ እንጦንስ ከበኣታቸው ወጡና ሰላምታ ሰጡአቸው በመቀጠልም ይህን የመሠለ አባት አብሮአችሁ በመኖሩ ታድላችሁአል አላቸው:: ያንንም አረጋዊ ብዙ ጥሩ ጥሩ ወንድሞችን ይዘኽልኝ መጣህ አለው:: አረጋዊው ግን ጥሩ መሆናቸው የማይካድ ነው ነገር ግን ለቤታቸው በር የለውም ማንም ደስ ያለው ሰው ወደ ጋጣው ገብቶ አህያዋን መፍታት ይችላል ብሎ አለው ይህም ማለት እነዚህ ወንድሞች ወደ ልብ የመጣውን ሁሉ ይናገሩታል ማለቱ ነበር:: በሌላ ጊዜ በአካባቢው ያሉት መነኮሳት ወንድሞቻቸው ስለ አንድ መነኩሴ እያመሰገኑ እያወደሱ ነገሩአቸው:: አባ እንጦንስም ያ የተመሰገነው እና እንደዚህ የተወራለት መነኩሴ ወደ እሳቸው በመጣ ጊዜ ቢሰድቡት ምን ያህል እንደሚታገስ ሊፈትኑት ስለወደዱ ያንን መነኩሴ በክፉ ቃል ተናገሩአቸው:: ያም መነኩሴ በጣም አብዝቶ ተቀየማቸው:: በዚህን ጊዜ አባ አንጦንስ አንተ ከውጭ በልዩ ልዩ ጌጥ የተዋበ ውስጡን ግን ሌቦች የዘረፉት መንደር ትመስላለህ አለው:: ይህም ማለት ቂም ኃጢአት ነውና ከኃጢአት መቆጠብ እንዳለበት ሲያስተምሩት ነው:: አንድ ጊዜ አባ እንጦንስ እንዲህ ብለው ነበር: ሰይጣን የቀመራቸውንና ያዘጋጃቸውን ወጥመዶች ሁሉ ተመለከትኩና ከዚህ ሁሉ ወጥመድ በምን አመልጣለሁ ብየ ራሴን ጠየኩት? እንድ ድምጽም በትሁት ስብእና ሲል መለሰልኝ:: አባ እንጦንስ እንዳሉት በጸሎት መትጋት; መልካም ሥራን መሥራት መልካም ነው:: ቅዱሳን አባቶቻችን በሕይወታችው ብዙ አስተምረውናል እኛስ ሕይወታችንን ለማነጽ እና ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ምን ያህል ዝግጁ ነን? አባ እንጦንስ ፈተና ሲገጥመን ምን ማድረግ እንዳለብን አስተምረውናል ስለዚህ እኛ በሕይወታችን ፈተና ሲገጥመን ምን ማድረግ አለብን ብለን እራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል እላለሁ:: የአባታችን የአባ እንጦንስ በረከታቸውና አማላጅነታቸው አይለየን:: በመልካም ምግባር ታንጸን አምላካችንን እንድናመሰግን አምላከ አባ እንጦንስ ይርዳን አሜን::

1 comment:

  1. ተዋህዶ-ሀይማኖታችን: አባ እንጦንስ >>>>> Download Now

    >>>>> Download Full

    ተዋህዶ-ሀይማኖታችን: አባ እንጦንስ >>>>> Download LINK

    >>>>> Download Now

    ተዋህዶ-ሀይማኖታችን: አባ እንጦንስ >>>>> Download Full

    >>>>> Download LINK

    ReplyDelete