Thursday, January 30, 2014

ጥር 13 -- ዕረፍቱ ለአቡነ ዘርዓ ብሩክ


እንኳን ለጻድቁ አባታችን አቡነ ዘርዓ ብሩክ የእረፍት በዓል አደረሳችሁ አደረሰን ከጻድቁ አባታችን ረድኤት በረከት ያሳድርብን አሜን !!!

የጻድቁ አባታችን የአቡነ ዘርዓ ብሩክ አባት እና እናት የተባረኩ ከቅዱሳን ወገን የሚሆኑ ነበሩ። የአባታቸው ስምም ቅዱስ ደመ ክርስቶስ ሲባል እናታቸው ደግሞ ቅድስት ማርያም ሞገሳ ትባላለች። ጻድቁ አባታችን ገና በእናታቸው ማህጸን እያሉ ነበር ብዙ ተአምራት የሚያደርጉት እግዚአብሔር መርጧቸዋልና። በኋላም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ8ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ በነሐሴ 27 ጻድቁ አባታችን ተወለዱ። በ40ኛ ቀናቸውም ተጠምቀው በካህናት አፍ "ጸጋ ክርስቶስ" ተባሉ ከዛም ቤተሰቦቻቸው በጥሩ እድገት አሳደጉአቸው። 7 አመትም በሞላቸው ግዜ "በልጅነቴ የዚን ዓለም ክፋቱን እንዳላይ" ብለው ቢጸልዩ ዓይናቸው ታውሯል። 
ቤተሰቦቻቸውም ጠቢቡ ሰሎሞን "የእግዚአብሔር ቃል ነውርን ይሸፍናል" እዳለው ትምህርት ሊያስተምሩአቸው አስተማሪ ጋር ቢወስዱአቸው ታመው ተመልሰዋል የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለምና። ነገር ግን የሚያስፈልጋቸውን እውቀት ፈጣሪ አምላክ ራሱ ገልጾላቸዋል:: ክህነትን እስከ ጵጵስና እራሱ መድሃኔ ዓለም ክርስቶስ ሰጥቷቸዋል። 12 አመትም በሞላቸው ግዜ በእግዚአብሔር ፈቃድ አይናቸው በርቶላቸው ታላላቅ ተጋድሎን ማድረግ ጀመሩ።

በእግዚአብሔር ዘንድ ጵጵስና እንደተሾሙ 

የሃጥያት ማሰርያን ያስሩና ይፈቱ ዘንድ ጵጵስናን በሾማቸው ግዜ እግዚአብሔር ያወጣላቸው ሁለተኛ ስም "ዘርዓ ብሩክ" ይባል ነበር። 3ኛውም ስማቸው ደግሞ "ጸጋ እየሱስ" ይባላል:: ጻድቁ አባታችን በዚህ አለም በህይወተ ሥጋ ሳሉ አቡቀለምሲስ እንደሚባል እንደ ዮሃንስ ወልደነጎድጉአድ እግዚአብሔር እሱ ወዳለበት ወደ ሰማይ አውጥቶ በገነት መካከል ያኖራቸው ነበር:: እግዚአብሔር አምላክ ለወዳጁ ለብጹዕ አባታችን ዘርዓ ብሩክ በጎ ነገር እንዳደረገለትና ያለ ድምጽ የሰማይ ደጆችን አልፎ የእሳት ባህርን ተሻግሮ ፈራሽ በስባሽ ሲሆን እንደ ህያዋን መላእክት በፍጥነት ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ከአድማስ እስከ አድማስ ይደርስ ዘንድ 12 ክንፍን ሰጣቸው። መላእክትም ለሌሎች ቅዱሳን ያልተሰጠ ይህንን ስልጣን አይተው ለምድራዊ ሰው ይህ ነገር እንዴት ይቻላል? እያሉ አደነቁ።ከዛም በኋላ ጻድቁ አባታችን ከፈጣሪ ዘንድ የመላእክትን አስኬማ፣ የሾህ አክሊል አምሳያ የሆነውን መንፈሳዊ ቆብን,ሰማያዊ ቅናትን እና የደረት ልብስን(ስጋ ማርያም) ተቀብሎ በጾም እና በጸሎት በልመና እና በስግደት እግዚአብሄርን ሲያገለግል ኖረ። ከዛም በላይ ወንጌልን እጅግ ብዙ በማስተማር ደከመ።

ከኢትዮጵያም አልፎ ግብጽ ድረስ ገባ የእስክንድርያውን ሊቀ ጳጳስ አባ ዮሐንስን አገኘውና እርስ በርስ ሰላምታን ተለዋውጠው እጅ ተነሳሱ ከዛም ተመልሶ ወደ ሃገሩ መጣ ከዛም ኢትዮጵያ ውስጥ እየተመላለሰ ወንጌልን አስተማረ እጅግ ስጋን በሚያስጨንቅ ትጋትም የኢትዮጵያን ህዝብ ማርልኝ እያለ እያለቀሰ ይጸልይ ነበር።

አቡነ ዘርዓ ብሩክ "ዓባይ" እና "ግሽ ዓባይ" የሚሉ ስሞች እንዳወጡ 

አንድ ቀን አባታችን የንጉስ ጭፍሮች ሲያሳድዷቸው ግዮን ደረሱ። እንደደረሱባቸው ሲያውቁ ዳዊታቸውንና ለወንጌል ስብከት ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 7 መጻሕፍት ሁሉ ለግዮን ወንዝ አደራ ሰጡዋት። ከ5 አመት በኋላ ሲመለሱ " ኦ ግዮን ግሥኢ መፃሕፍትየ -- ግዮን ሆይ መጻሕፍቴን ግሺ መልሺልኝ " (ግሽ ዓባይ -- የሚባልም ከዚህ የተነሳ ነው።) ቢሉአት አንድም የውሃ ጠብታ ሳይኖርባት ዳዊታቸውን ብትመልስላቸው ለደቀ መዝሙራቸው ዘሩፋኤል አሳዩት ሁለቱም የእግዚአብሔርን ሥራ አደነቁ። ከዛም በኋላ ግዮንን ባረክዋትና "ይኩን ፈውስ ዓብይ በውስቴትኪ -- በውስጥሽ ታላቅ ድኅነት ይደረግብሽ" አሉ። ከዛ ጊዜ ጀምሮ መካኖች ይወልዱ፣ ድዉዮች ይድኑ ጀመር "ወእም አሜሃ ተሰምየት ዓባይ ይእቲ ፈለግ -- ከዛ ጊዜ ጀምሮ ይህች ዓባይ ተብላ ተጠራች።" እስካሁንም በዚሁ ስም የሚጠራው ከዚ በመነሳት ነው:: ከዚህም ሌላ ጻድቁ አባታችን በዚሁ ወንዝ አካባቢ ለ 30 አመት ሲጸልዩ ፈጣሪ አምላክ ጸሎታቸውን ሰምቶ እጅግ ልዩ የሆነ ቃል ኪዳን ሰቶአቸዋል።

ዕረፍታቸው 

በስተመጨረሻም የሚያርፉበት እለት በደረሰ ሰአት መልአከ ሞት መቶ እስኪደነግጥ እና ወደ ኋላው እስኪያፈገፍግ ድረስ ነው ነው እግዚአብሔር ጸጋውንና ክብሩን ያበዛላቸው: በስተመጨረሻም ጥር በገባ በ13 ቀን በ482 አመታቸው ስጋቸው ከነፍሳቸው ተለይታ ገነትን ወርሰዋል::

ምንጭ: ገድለ አቡነ ዘርዓ ብሩክ 
የጻድቁ አባታችን ገድለ ዜና እንኳን በዚች በምታህል ጽሁፍ አይደለም የገድላቸውም መጽሃፍም አልበቃውም እንደው እግዚአብሔር አምላክ ከበረከታቸው እንዲያሳትፈን ነው እንጂ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር 
ወለወላዲቱ ድንግል 
ወለመስቀሉ ክቡር

No comments:

Post a Comment