Tuesday, January 14, 2014

ጥር 4

ጥር 4 በዚህች ቀን ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ሞትን ሳይቀምስ የተሰወረበት ቀን ነው፤ ዮሐ 21 ፤ 20። ቅዱስ ዮሐንስ ብዙ ስሞች አሉት ፍቁረ እግዚ፤ታኦሎጎስ ( ነባቤ መለኮት ማለት ነው በአማርኛው ደግሞ ስለመለኮት የሚናገር ማለት ነው፤ ከአባቶቹ ነብያት ከወንድሞቹ ሐዋርያት መካከል እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ሚስጥረ ስላሴን አምልቶ አስፍቶ የተናገረ የለም፤ሌላ ስሙ አቡቀለምሲስ ይባላል ባለ ራዕይ የራዕይ አባት ማለት ነው፤ቁጽረ ገጽም ይባላ የጌታችንን ስቃዩን ካየ በኃላ ፊቱ ሳይፈታ 70 ዓመት ሙሉ አልቅሷል፤ ከመስቀል ስር ያልተለየው ብቸኛው ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ ነው፤ እመቤታችንን በአደራ የተቀበለ በእንድ ቤት ልጅ ሆኗት 15 ዓመት የኖረ ይህ ሐዋርያ ነው፤ መልኩ ጌታችንን ይመስል ነበር፤ ለዚህም ነው ይሁዳ ጌታን በመሳም ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠው መልካቸው ስለሚመሳሰል ተሳስተው ዮሐንስን እንዳይዙት፤ ስለዚህ ሐዋርያት ስንቱን እንናገር ብዙ መከራ ተቀብሏል ነገር ግን እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ደሙ ፈሶ በሰማዕትነት አይደለም የሞተው፤ በ 90 ዓመቱ በዛሬዋ ቀን ከነስጋው ተሰወረ እንጂ በረከቱ ይደርብን። "በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ...ቃልም ስጋ ሆነ" ይህን ቃል ያነበበ ሰው ግን እንዴት ይስታል፤ "አቤቱ ምሳሌ ስጠኝ እንጂ ምሳሌ አታድርገኝ" የምትለዋ ጸሎት እንዴት መልካም ነች፤ ወደ ነገራችን እንመለስ፤ በነገራችን ላይ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው በኤፌሶን ነው ዘመኑ መቼ ነው ቢሉ ጌታ ባረገ በ 30 ዓመቱ፤ የጻፈበት ቋንቋ ጽርዕ ይባላል፤ እናም ወንጌሉን ሲጀምር በመጀመሪያ ቃል ነበር ብሎ መጻፍ ሲጀምር ራዕይ ያያል ከዋንኞቹ መልአክት አንዱ ከትልቅ ሐይቅ ዳር ቁጭ ብሎ የሐይቁን ውኃ በእንቁላል ቅርፊት እየጨለፈ ወደ መሬት ያፈሳል ቅዱስ ዮሐንስ ጠጋ ብሎ ምን እየሰራህ ነው ይለዋል የሐይቁን ውኃ ወደ መሬት እፍስሼ ለመጨረስ ነው ይለዋል ይህ እንዴት ይሆናል ደግሞም በእንቁላል ቅርፊት ይለዋል፤ ይህ ሐይቅ ፍጡር ነው ከረጅም ዘመን በኃላ ሊሳካሊኝ ይችላል አንተስ አለክ አይደል ቢቀዱት የማያልቀውን ቢጀምሩት የማይጨርሱትን የመለኮት ነገር የምትመራመር አለው በዚህ ጊዜ ነው የሐንስ የጀመረውን አቁሞ ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ብሎ ወደ ሚስጢረ ስጋዌ የገባው ዮሐ 1፤14።

No comments:

Post a Comment