Wednesday, January 8, 2014

ታህሳስ 25


ታህሳስ 25 በዚህች ቀን አቡነ ዮሐንስ ከማ አረፈ።ይህ አባት ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚሉ አሉ፤ ነገር ግን ሊቀ ብርሃናት መርቆርዮስ አረጋ ብዙ ገድላትንና ድርሳናትን ዋቢ አድርገው፤ አገሩ ሰሜን ጎንደር እንደሆነ ትግራይ ውስጥ ሰለዋ በተባለ ቦታ ቀብጽያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳምን የመሰረተ አባት እንደሆነ “የኢትዮጵያ ተወላጆች ቅዱሳን ታሪክ” በሚል መጽሐፋቸው በስፋት ጠቅሰውታል፤ ስንክሳሩ ላይም ታሪኩ ተጽፏል። አባ ዮሐንስ ከማ ወላጆቹ ሚስት ድረውለት ነበር ነገር ግን ጫጉላቤት ሳሉ እህቴ ሆይ እኔ በድንግልና መኖር ነው የምፈልገው ይላታል እርሷም እኔም እንጂ እንዳንተው በድንግልና መኖር ነው የምፈልገው ትለዋለች፤ በአንድ አልጋ ይተኛሉ መልአከ እግዚያብሔር ክንፉን እያለበሳቸው፤ በግብር ሳይተዋወቁ ለረጅም ዘመን ኖረዋል ፤ ወቸው ጉድ እሳትን ታቅፎ የማያቃጥለው ሰው እንዳለ ያየ የሰማ ማን ነው ? አለ ደራሲው፤ ወላጆቻቸው እንዴት ነው ነገሩ ልጅ አይወልዱም ወይንስ ገና ልጆች ስለሆኑ ይሆናል እያሉ ይከራከሩ ነበር፤ በኃላ ላይ መልአከ እግዚያብሔር እየመራው አስቄጥስ ከአባ መቃርስ ገዳም አደረሰው በዚያም መነኮሰ በአባ ዮሐንስ ሐጺር ገዳምም ኖሯል፤ ኢትዮጰያ ውስጥም እንደነ አቡነ አሞጽ፤ አቡነ ቀጸላ ጊዮርጊስ የመሳሰሉ ታላላቅ የቤተክርስቲያን ከዋክብት የተሰኙ ብዙ መነኮሳትን አመንኩሷል፤ ትግራይ ውስጥ ቀብጽያ በተባለ ገዳሙ ተአምራትን የምታደርግ የነሐስ መቋሚያ አለችው፤ አሁንም ድረስ አለች፤ገበሬው ነው የሚጠብቃት። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ስለመቋሚያ ካነሳን ዘንዳ የአቡነ ቶማስ ዘሽሬ መቋሚያ ሴት ወደ ገዳሙ ሲገባ ትጮሃለች፤ የአቡነ አካለ ክርሰቶስ መቋሚያ ደገሞ ቤተክርስቲያኑ ካልታጠነ ትሰወራለች፤ የአቡነ ተክለ አልፋ መቋሚያ ነፍሰ ያጠፋ ወደ ቤተክርስቲያኑ ሲገባ ድምጽ ትሰጣለች፤ በመጽሐፍ ቅዱስም ከተመለከትን የሙሴ የአሮንና የዮሴፍ አረጋዊ በትር ገራሚ ገራሚ ተአምራትን ሰርተዋል። ጻድቁ በታህሳስ 25 ቀን አርፎ ትግራይ ውስጥ እራሱ በቆረቆረው ገዳም ተቀብሯል፤ ጎንደር ጸለምትም ትልቅ ገዳም አለው። በረከቱን ይደርብን፤

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

No comments:

Post a Comment