Monday, January 31, 2022

ጥር 18 - ወበዛቲ ዕለት

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈሰ ቅዱስ ስም አሜን

ጥር 18-ፀሐይ ዘልዳ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዐፅሙ ተቃጥሎ አጥንቱ ተፈጭቶ በደብረ ይድራስ ተራራ ላይ የተበተነበት ዕለት ነው፡፡



+ በ34 ዓ.ም ጥምቀትን ያመጣልን ለሀገራችንም ሆነ ለአፍሪካ የመጀመሪያ ሐዋርያችን የሆነው ቅዱስ አቤላክ (ባኮስ) በዚህች ዕለት በሰሜን ተራራዎች ላይ ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት ቦታ ተሰወረ፡፡ እርሱም በጌታችን የተመረጡ የከበሩ ሐዋርያት እንኳን ወንጌልን በዓለም ለመስበክ ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት ወቅት ወደ አፍሪካ መጥቶ ወንጌልን የሰበከ ነው፡፡
+ ለቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ መምህሩ የሆኑት አባ ያዕቆብ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+ ጌታችን ከሞት ያስነሣው የቅዱስ አልዓዛር እኅቶች ማርያምና ማርታ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡
አባ ያዕቆብ፡- በገድል ተጠምደው የኖሩ እጅግ የከበሩ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉት ንጽቢን በምትባል ከተማ ቢሆንም ሶርያዊ ተብለው ይጠራሉ፡፡ የሀገረ ንጽኒቢን ኤጲስ ቆጶስ ሲሆኑ የእመቤታችንን ውዳሴ ለደረሰው ታላቅ አባት ለቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ መምህሩ ናቸው፡፡ ይህ ታላቅ አባት ከልጅነታቸው ጀምሮ ዓለምን ንቀው በመንኩስና መኖርን መርጠው መንኩሰዋል፡፡ በጠጉር ከተሠራ ማቅ በቀር ሌላ ልብስ ለብሰው አያውቁም፡፡ በቀን በሌሊት፣ በበጋ ሐሩርም ይሁን በክረምት ቁር ቢሆን ይህንን ልብሳቸውን አውልቀውት አያውቁም፡፡ ምግብም ከቅጠላ ቅጠል ውጭ ተመግበው አያወቁም፡፡ የሚጠጡትም የዝናብ ውኃ ብቻ ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ ሀብተ ትንቢትና ሀብተ ፈውስ ተሰጥቷቸው እጅግ አስገራሚ የሆኑ ተአምራትን ያደርጉ ጀመር፡፡ በአንዲት ዕለት ሴቶች በውኃ ምንጭ ላይ እርቃናቸውን ያለ ማፈር ሲጫወቱና ሲሳለቁ አይተው የውኃውን ምንጭ ወዲያው እንዲደርቅ አድርገውታል፡፡ የሴቶቹንም የራሳቸውን ጸጉር በተአምራት ነጭ ሽበት አደረጉባቸው፡፡ ሴቶቹም ተጸጽተው በአባታችን እግር ሥር ወድቀው በለመኗቸው ጊዜ የውኃውን ምንጭ መልሰው አፈለቁላቸው፡፡ እንዳይታበዩ ሲሉ ግን የራሳቸውን ጸጉር ለምልክት ነጭ አድርገው ተውላቸው፡፡ ትሩፋታቸውና ዜናቸው በበየቦታው በተሰማ ጊዜ አቡነ ያዕቆብን በንጽቢን ሀገር ላይ ኤጲስ ቆጶስነት ሾሟቸው፡፡
ጻድቁ ንጉሥ ታላቁ ቈስጠንጢኖስ 318ቱን የከበሩ አባቶች በኒቅያ እንዲሰበሰቡ ሲያደርግ ገድላኛ የሆኑት ይህ ታላቅ አባትም አንዱ ነበሩ፡፡ በጉባኤውም መካከል ሙት አስነሥተው እንዲመሰክር አድርገውታል፡፡ እርሳቸውም አርዮስን አስተምረው መክረው እምቢ ቢላቸው ረግመው አውግዘውታል፡፡ የፋርስ ንጉሥ መጥቶ ሀገረ ንጽቢን ሊወር አስቦ በከበባት ጊዜ አቡነ ያዕቆብ በጸሎታቸው የጭጋግ ደመና በሠራዊቱ ላይ አመጡባቸው፡፡ ተናዳፊ ትንኞችም ፈረሶቻቸውንና ወታደሮቻቸውን ሁሉ ነደፏቸው፡፡ ፈረሶቹም ማሠሪያቸውን እየበጠሱ ፈርጥተው ጠፉ፡፡ ንጉሡም ይህን ተአምር አይቶ እጅግ ፈርቶ ወደ ኋላው ተመልሶ ሄዷል፡፡ ጻድቁ ሕዝበ ክርስቲያኑንና ሀገራቸውን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በጽድቅ ሲያገለግሉ ኖረው በሰላም ዐርፈዋል፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!
+ + +
ስብረተ ዐፅሙ ለሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ፡- ከሃዲው ንጉሥ ዱድያኖስ እጅግ አሠቃቂ በሆኑ ብዙ መከራዎች እያሠቃየ ሦስት ጊዜም ቢገድለው ጌታችን ግን ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሞት እያስነሣው ከሃድያንን ያሳፍራቸው ነበር፡፡ ንጉሥ ዱድያኖስ የሚያደርገው ቢያጣ ጭፍሮቹን ‹‹በመንኰራኩር ፈጭታችሁ አጥንቱን ደብረ ይድራስ ተራራ ላይ ወስዳችሁ ዝሩት›› ብሎ አዘዛቸው፡፡ ጭፍሮቹም የቅዱስ ጊዮርጊስን ሥጋ በመንኰራኩር ፈጭተው ወስደው በተራራው ላይ ቢረጩት ሥጋው ያረፈበት ሳር፣ ቅጠሉ፣ ደንጊያው፣ እንጨቱ ሁሉ ‹‹ጊዮርጊስ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር፣ ጊዮርጊስ ሰማዕቱ ለእግዚአብሔር›› እያሉ አመስግነዋል፡፡ አሁንም ጌታችን ለሦስተኛ ጊዜ ከሞት አስነሣውና ሥጋውን ፈጭተው በተራራም ላይ ሥጋውን በትነውት ወደ ንጉሡ የሚመለሱትን ወታደሮች በመንገድ ከኋላቸው ሄዶ ደረሰባቸውና ‹‹ቆዩኝ ጠብቁኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም እጅግ ደንግጠው ይህ እንዴት እንደሆነ ሲጠይቁት ‹‹አምላኬ ከሞት አዳነኝ›› አላቸው፡፡ ጭፍሮቹም እጅግ ደንግጠው ከእግሩ ስር ወድቀው ‹‹ይቅር በለን›› ብለው በአምላኩ እንደሚያምኑ መሰከሩለት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ከመሬት ላይ ውሃ አመንጭቶ በጸሎት ጌታችንን ቢጠይቅ ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ አጥምቋቸዋል፡፡ እነርሱም በንጉሣቸው ፊት ሄደው ስለጌታችን በመመስከር በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዐፅሙ ተቃጥሎ አጥንቱ ተፈጭቶ በደብረ ይድራስ ተራራ ላይ የተበተነው በዚህች ዕለት ነው፡፡

የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
የመጀመሪያው የአፍሪካ ሐዋርያ ቅዱስ አቤላክ (ባኮስ)፡- ይኽም ጃንደረባ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ንግሥት የሆነችው የህንደኬ የገንዘቧ ሁሉ ኃላፊና አዛዥ የነበረ ነው፡፡ ከአባቱ እብነ መላክ ከእናቱ ስሂነ ሕይወት ታኅሣሥ 29 ቀን ተወለደ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ለበዓለ ፋሲካ በቤተ መቅደስ ይሰግዱ እንደነበረው ሁሉ ይኽም ጃንደረባ ከ4 ሺህ ማይልስ በላይ ተጉዞ ኢየሩሳሌምን ተሳልሞ በመለስ ላይ ነበረ፡፡ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ በተለይም ስለ ጌታችን መከራ መስቀል በዝርዝር የሚናገረውን ክፍል 53ኛውን ምዕራፍ ያነብ ነበር ነገር ግን ጃንደረባው ስለማን እንደሚናገር አልገባውም ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር በአካባቢው ወንጌልን ይሰብክ የነበረውን ሐዋርያውን ቅዱስ ፊሊጶስን ላከለት፡፡ እርሱም ጃንደረባው ያነበው የነበረውን መጽሐፍ ተረጎመለት፣ የከበረች ወንጌልን ሰበከለት፣ በመጨረሻም አጠመቀው፡፡ ሐዋርያው ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በጃንደረባው ላይ ወረደ፡፡ ሐዋ 8፡26-40፡፡ ይህን ለእኛ ለኢትዮጵያውን እጅግ የሚያኮራን ታሪካችን ነው፡፡ ዛሬ በእጃችን ላይ በመገኘው መጽሐፍ ውስጥ ባይኖርም በቆዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች ላይ ግን ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ ጃንደረባውን ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በኢትዮጵያው ጃንደረባ ላይ እንደወረደ ተጽፏል፡፡ (ዝኒ ከማሁ ገጽ 87፣ v.39.cord.alexand. in bible reg. angl-alique plures codd.mss)
ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ጃንደረባውን ያጠመቀበት ወንዝ ‹‹ቤተ ሳሮን›› በተባለችውና እስከዛሬም ድረስ ከኢየሩሳሌም 20 ማይልስ ርቀት በምትገኘው መንደር በኬብሮን መካከል ባለው ኮረብታ ሥር የሚመነጭ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ጸሐፊ የሆነው ሊቁ ቅዱስ ጀሮም ጃንደረባውን ‹‹የኢትዮጵያውያን ሐዋርያ›› በማለት ይጠራዋል፡፡ በሰፊው ለኢትዮጵያውያን ወንጌልን የሰበከ እርሱ ነውና፡፡ ጌታችን የመረጣቸው የከበሩ ሐዋርያት እንኳን ወንጌልን በዓለም ለመስበክ ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት ወቅት በ34 ዓ.ም ነው ቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ በክርስቶስ አምና ወንጌልን የተቀበለችው፡፡ በምድሪቱም ላይ ወንጌል መነገር የጀመረው ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡
እንሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከኢየሩሳሌም ወንጌልን ተምሮና ተጠምቆ ወደ አክሱም እንደተመለሰ በመጀመሪያ ያጠመቀው ንግሥቲቷን ሕንደኬን ነው፡፡ ከእርሷም በኋላ መኳንንቱና መሳፍንቱ ሁሉ አምነው በባኮስ እጅ ተጠመቁ፡፡ ይኸውም በ34 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚህም በኋላ ባኮስ እስከ ኑብያ ድረስ ሄዶ ወንጌልን ሰብኮ ብዙዎችን አሳምኖ አጥምቋል፡፡ በዚህም ጊዜ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በባኮስ እየተሰጠ የነበረውን የወንጌል ብርሃን የበለጠ እንዲበራ አድርጓል፡፡ ከጃንደረባውም ጋር ሆነው በብዙ ቦታዎች አብረው ወንጌልን ሰብከው አምልኮተ ጣዖትን አጥፍተዋል፡፡
ከዚህም በኋላ ባኮስ ወደ የመን በመሄድ በዚያም ክርስትናን በማስተማር ብዙዎችን አሳምኖ ካጠመቀ በኋላ ወደ ፐርሺያ ከዚያም ወደ ሕንድ በመሄድ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሟል፡፡ በመጨረሻም ጥንት ታፕሮባና (taprobana) ዛሬ ሲሎን በምትባለው ደሴት ወንጌልን በማስተማር ላይ እያለ በሰማዕትነት እንዳረፈ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ (lives of the most eminent fathers of the church, page 87) በሌላም በኩል ሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከመጠመቁ በፊት 35 ዓመት ከተጠመቀ በኋላ ደግሞ 41 ዓመት ኖሮ በኢየሩሳሌምም 3 ዓመት ተቀምጦ ወንጌልን ዞሮ ካስተማረ በኋላ በመጨረሻ በ79 ዓመቱ ጥር 18 ቀን በሰሜን ተራራዎች ላይ ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት ቦታ እንደተሰወረ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ጽፈዋል፡፡

የቅዱስ አቤላክ (ባኮስ) ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!




Like
Comment
Share

No comments:

Post a Comment