Friday, June 21, 2013

ሰኔ 8


ከእመቤታችን ሠላሳ ሦስቱ ባዓላት አንዱ ነው፤ በዚህ ዕለት ልጇ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ግብጽ በስደት ሳሉ ለህሙማን ድህነት እንዲሆን ውኃን ከዓለት ላይ ያፈለቀበት ቀን ነው፤በዚሁ ቦታ በእመቤታችን ሥም ታላቅ ቤተክርስቲያን ተሰርቶ የተከበረበትም ቀን ነው፡፡እመቤታችንን ከፍጥረት ዓለም ለይቶ አክብሮ የእናት አማላጅ አድርጎ የሰጠን እግዚያብሔር ይመስገን፡፡
ከተአምር አስቀድሞ ይህ ይነበብ ህዝቡ ዕዝነ ልቦናቸውን ከፍተው ይስሙ፤ በዕብራይስጥ ማርያም የተባለች የእመቤታችንን ተአምር ለመስማት ቀላል አይምሰለው የከበረ ገናና ነውና ወደ ግዝት እንዳይገቡ መስማትን አያስታግሉ ፤ በእመቤታችን ሠላሳ ሦስቱ ባዓላትና እሁድ በተባለች ሰንበት ወንዶችም ሴቶችም ወደ ቤተክርስቲያን ይሰብሰቡ የተአምሯን መጽሐፍም ያንብቡ፤ ዛሬ ሰኔ 8 ቀን ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፤ ይህም በስደታቸው ወራት ልጇ ከደረቅ አለት ላይ ውኃን ያፈለቀበት ቀን ነው። ይህ ውኃ እንደ ማር እንደ ወተት የጣፈጠ እንደ ወተትም የነጻ ነው፤ ከዚህ ውኃ የጠጣ ሁሉ ይፈወስ ነበር። ታሪኩ እንዲህ ነው የግብጽ በረሃ በጣም ሲያደክማቸው ከአንድ መንደር ያርፋሉ በዚያም ጌታ ውኃ ይጠማዋል ይህን ባየች ጊዜ እምቤታችን ከመንደሩ ሴቶች ውኃ ልትለምን ሄደች፤ ዮሴፍና ሶሎሜ ግን ደከሟቸው ተኝተው ነበር፤ ውኃ የሚሰጣት የሚመጸውታት ስታጣ ልቧ በሐዘን ተወግቶ ተመልሳ መጣች ጌታን ከተቀመጠበት አንስታ ታቀፈችው ስቅስቅ ብላም አለቀሰች ህጻን ጌታም የእናቱን እንባ ከጉንጮቿ ላይ በእጆቹ ጠረገላት ትንሽዬ ጣቱን (ማርያም ጣት የምንለውን ነው ወደ ምድር አመለከተ ወዲያውኑ ጣፋጭ ውኃ ከአለት ላይ ፈልቆ ጠጡ፤ እንዲህም አለ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ለድህነት ይሁነው ብሎ ባረከው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚጠጣው ሁሉ ከደዌው ይፈወስ ነበር፤ የጠፋ በግ አዳምን የፈለገው ባገኘውም ጊዜ የተሸከመው እውነተኛ ቸር ጠባቂያችንን የወለድሽልን እመቤቴ ማርያም ሆይ ሠላምታ ይገባሸል የሄዋን ጽኑ የሚጎዳ ማሰሪያዋ ባንቺ የተቆረጠላት እመቤቴ ማርያም ሆይ ውዳሴም ይገባሻል እኛ ከምንወደው እርሱም ከሚወደን ልጅሽ ይቅርታ ያደርግልን ዘንድ ለምኝልን።

No comments:

Post a Comment