Tuesday, February 18, 2014

የካቲት 9

የካቲት 9 በዚህች ቀን ታላቁ አባት አባ በርሱማ አረፈ፤ አገሩ ሶሪያ ነው፤ ሶርያ የዛሬን አያድርገውና ውዳሴ ማርያምን የደረሰው ቅዱስ ኤፍሬምን ጨምሮ የብዙ ሊቃውንት መፍለቂያ ነበረች። አባ በርሱማ በልጅነቱ ከወላጆቹ ቤት ጠፍቶ ወጣ ገዳም ገባ በተጋድልም የሚኖር ሆነ፤ ታላላቅ ታአምራትን የማድረግ ስልጣን ተሰጥቶት ነበር እንደ እያሱ ጸሐይን አቁሟል (እያ 10፤13) እንደ ኤልያስ ዝንብ አዝንቧል (ያዕ 10፤13 ) ደግሞም እንደ ኤልሳ የመረረ ውኃ አጣፍጧል (2ኛ ነገ 2፤19-22)። 54 ዓመት ቆሞ ጸለየ፤ በ 7 ቀን አንዴ የሚመገብ ሆነ። በጉባዬ ኬልቄዶን የተዋህዶ ኩራት እምዬ ዲዮስቆሮስ ብቻውን ሊዮንን...ና ከእርሱ ጋር የቆሙ 636 ካቶሊካውያንን "አንድ አካል አንድ ባህሪ" ብሎ ተከራክሮ ሲረታቸው ንግስቲቱ ብርክልያ በንዴት የዲዮስቆሮስን ጥርስ አውልቃ ጽህሙን ነጭታ ተሰቃይቶ እንዲሞት ግዞት ስትፈርድበት ይህ አባት አባ በርሱማ ነበር ወደ ንግስቲቱ የገባው ሳይፈራና ሳያፍር በፊቷ ቆሞ የረገማት፤ እንዴት በእግዚያብሔር ቅዱስ ላይ እጅሽን ስትጭኚ አላፈርሽም፤ እርሱስ የክብር ሞት ይሞታል አንቺ ግን አትቆዪም በጻር ትሞቻለሽ አላት፤ ለትንሽ ቀናት ተሰቃይታ በክፉ አሟሟት ሞታለች። "ጻድቃንን የሚጠሉ ይጸጸታሉ" አለ ዳዊት መዝ 33(34)፤22 ግን እኮ መጸጸት ብቻ አይደለም ይሞታሉም። አባ በርሱማ ከአባ ስምዖን ዘአምድ ጋር እንደ ተገናኙ ስንክሳሩ ያትታል፤ አባ በርሱማ በቅድስና ኖሮ በዛሬዋ ቀን አርፏል። በረከቱ ይደርብን።

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

No comments:

Post a Comment