Wednesday, November 28, 2012

አባ አርሳንዮስ




አባ አርሳንዮስ 360 . በሮም ተወለደ፡፡ በዘመኑ ትምህርት በሚገባ የተማረና ለሴናተርነትም መዓርግ የደረሰ ሰው ነበር፡፡ የሮሙ ንጉሥ ቴዎዶስየስ ለልዕልት አርቃድዮስ እና ለልዕልት አኖሬዎስ መምህር አድርጎ መድቦት ነበር፡፡ 394 . የሮምን ቤተ መንግሥት ንቆ ትቶ በድብቅ ወደ እስክንድርያ መጣ፡፡ በመቀጠልም ወደ ገዳመ አስቄጥስ ገብቶ የአባ ዮሐንስ ሐፂር ደቀ መዝሙር ሆነ፡፡ በገዳመ አስቄጥስ አጠገብ በሚገኘው በጴጥራ በምናኔ ይኖር ጀመር፡፡ የታወቁ ሦስት ደቀ መዛሙርት ነበሩት፡- እስክንድር፣ ዞይለስ እና ዳንኤል፡፡ ድሎት የለሽ ኑሮን በመኖር እና በአርምሞው የታወቀ አባት ነው፡፡ 434 . ገዳመ አስቄጥስ ለሁለተኛ ጊዜ ከጠፋ በኋላ ወደ ትሮኤ ተራራ ወጣ፡፡ እዚያም 449 . ዐረፈ፡፡

አባ አርሳንዮስ በቤተ መንግሥት በነበረበት ሰዓት ጌታ ሆይ በድኅነት ጐዳና ምራኝ እያለ ይጸልይ ነበር፡፡ እናም አርሳንዮስ ሆይ ከሰዎች ተለይ ያን ጊዜ ድኅነትን ታገኛለህ የሚል ድምጽ ሰማ፡፡ ወዲያውም ቤተ መንግሥቱን ትቶ ወደ ገዳም ገባ፡፡
ወደ ምናኔ ሕይ ወት ከገባም በኋላ ከቀድሞው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ጸሎት ይጸልይ ነበር፡፡ ያን ጊዜም ከሰማይ የመጣ ድምጽ አርሳንዮስ ሆይ ሽሽና በአርምሞ ኑር፤ ዘወትር ጸልይ፤ እነዚህ የንጽህና መገኛዎች ናቸውና ሲል ተናገረው፡፡
አባ አርሳንዮስ በበኣቱ እያለ አጋንንተ መጥተው ያውኩት ነበር፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ከሄዱበት ተመልሰው ከበኣቱ ደጅ ሲደርሱ እንዲህ እያለ ሲጸልይ ሰሙት እግዚአብሔር ሆይ አትተወኝ፣ በፊትህ መልካም የሚሆን ምንም ምግባር የለኝም፡፡ ነገር ግን ስለ ቸርነትህ ስትል መልካምን ነገር እንዴት እንደምጀምረው ግለጥልኝ
አንድ ጊዜ አባ አርሳንዮስ በኅሊናው እየተመላለሱ ስለ ሚያስቸግሩት ክፉ ሃሳቦች አንድን አረጋዊ የግብጽ መነኩሴ ሲያማክረው አንድ ሌላ ወጣኒ መነኩሴ ተመለከተው፡፡ ያም መነኩሴ በጣም ተደንቆ አባ አርሳንዮስ ሆይ በላቲንና በግሪክ ትምህርት የበሰልክ አንተን የመሰልክ ሊቅ ይህንን ማይም ገበሬ እንዴት ስለ ፈተናህ ተጠይቀዋለህ› አለው፡፡ አባ አርሳንዮስም በርግጥ ላቲንና ግሪክ በሚገባ ተምሬያለሁ፣ ነገር ግን የዚህን ገበሬ መንፈሳዊ የፊደል ገበታ ገና አላወቅሁትም ሲል መለሰለት፡፡
አባ አርሳንዮስ ለምን ከኛ ትርቃለህ ሲል ጠየቀው አባ አርሳንዮስም እንደምወዳችሁ እግዚአብሔር ያውቃል፣ ነገር ግን ከሰዎችም ከእግዚአብሔርም ጋር በአንድ ላይ መኖር አልችልም፡፡ እልፍ አእላፋት መላእክት በአንድ ቦታ ቢኖሩም ሃሳባቸው ግን አንድ ነው፡፡ ሰዎች ግን ሃሳባቸው በቁጥራቸው ልክ ብዙ ነው፡፡ ስለሆነም ከሰው ጋር ለመኖር ስል እግዚአብሔርን መተው አልሻም አለው፡፡
አባ አርሳንዮስ በተጋድሎ ውስጥ ለሚገኝ መነኩሴ የአንድ ሰዓት ዕንቅልፍ በቂ ነው ይል ነበር፡፡
በዕለተ ዓርብ ምሽት፣ ለታላቁ ሰንበት ለመዘጋጀት ሲል፣ ጀርባውን ለፀሐይዋ ሰጥቶ እጆቹን በመዘርጋት ወደ ሰማያት ይጸልያል፡፡ የሚያርፈው ፀሐይ በፊት ለፊቱ በኩል ብርሃንዋን መርጨት ስትጀምር በቀጣዩ ቀን ነው፡፡
አባ ዳዊት አንድ ጊዜ አርሳንዮስ የነገራቸውን ታሪክ እንዲህ ያወጉናል እርግጥ አባ አርሳንዮስ ይህንን ታሪክ የተናገረው ሌላ ሰው አደረገው ብሎ ነው፡፡ በርግጥ ግን የታሪኩ ባለቤት እርሱ ራሱ ነው፡፡
አንድ አረጋዊ መነኩሴ ከበኣቱ ወጥቶ ሳለ የሰው ልጆችን ሥራ አሳይህ ዘንድ የሚል ድምፅ ሰማ፡፡ እርሱም ከበኣቱ ወጥቶ የጠራውን ድምፅ ተከትሎ ተጓዘ፡፡ ድምፅ ወደ አንድ ቦታ አደረሰውና አንድ ኢትዮጵያዊ እንጨት እየፈለጠ ሲከምር አሳየው፡፡ እንጨት የሚፈልጥ ኢትዮጵያዊ ሊሸከመው ሞከረና አቃተው፤ ይሁን እንጂ በመቀነስ ፋንታ አሁንም እየቆረጠ መከመር ቀጠለ፡፡
 ጥቂት አለፍ ብሎ ደግሞ አንድ ሰው በሐይቅ አጠገብ ቆሞ በተሠበረ ማሰሮ ውኃ ሲቀዳ ተመለከተ፡፡ ማሰሮው የተሰበረ በመሆኑ ውኃው እንደገና ወደ ሐይቁ ይመለስ ነበር፡፡ ድምፅ በድጋሚ ሌላ ነገር ደግሞ አሳይሃለሁ ብሎ ወሰደው፡፡
በአንድ ሥፍራ ላይ መቅደስ አሳየው፡፡ ሁለት ሰዎች በፈረስ ጐን ለጐን ሆነው መጡ፡፡ በትከሻቸውም በትራቸውን ጫፍና ጫፍ ላይ አጋድመው ይዘውት ነበር፡፡ በበሩ ወደ ውስጥ ሊያልፉ ቢፈልጉም በትራቸውን አግድም ስለያዙት ያግዳቸው ነበር፡፡ አንዳቸውም ከሌላኛው ኋላ በመሆን በትሩን ፊትና ኋላ አድርገው ሊገቡ አልፈለጉም፡፡ ስለዚህም በፉክክር ከውጭ ቀሩ፡፡
ድምፅ ለዚያ አረጋዊ አባት እንዲህ አለው፡፡ እነዚህ ሰዎች የጽድቅን ቀንበር በትዕቢት ተሸክመውታል፣ ራሳቸውን ዝቅ ዝቅ አላደረጉም፤ ራሳቸውን ለማረምና በክርስቶስ የትኅትና ጉዞ ለመጓዝ አልፈለጉም፣ ስለዚህም ከመንግሥተ ሰማያት በአፍኣ ይቀራሉ፡፡
እንጨት የሚቆርጠው ሰውም በኃጢአት ላይ ኃጢአት የሚጨምርን ሰው ይመስላል፡፡ ንስሐ ከመግባት ይልቅ ሌሎች ኃጢኣቶችን እንደገና ይጨምራል፡፡ ውኃ የሚቀዳውም ሰው መልካም ሥራን የሚሠራ ሰውን ይመስላል፣ ነገር ግን መልካም ሥራው ከክፉ ሥራው ጋር የተቀላቀለ በመሆኑ ጥቂቱ መልካሙ ሥራው ይበላሽበታል፤ ስለሆነም እያንዳንዱ ለሚሠራው ነገር ሊጠነቀቅና በከንቱ እንዳይደክም ሊያስብበት ይገባል አለው፡፡

ከቅዱሱ አባታችን አባ አርሳንዮስ ረድኤት በረከት ይክፈለን

ዋቢ መጽሐፍት
ነገረ ቅዱሳን

No comments:

Post a Comment