Showing posts with label ወበዛቲ ዕለት. Show all posts
Showing posts with label ወበዛቲ ዕለት. Show all posts

Monday, September 18, 2023

መስከረም 7

 

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን


መስከረም 7-የብርሃን እናቱ የሆነች ድንግል ወላዲተ አምላክን የወለደቻት ቅድስት ሐና ልደቷ ነው፡፡

+ በ451 ዓ.ም በጉባዔ ኬልቄዶን ላይ ተገኝቶ ልዮንን የረታውና ያወገዘው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በዓለ ልደቱና ዕረፍቱ ነው፡፡

+ በአካል መሄድ ሳያስፈልጋቸው ደብዳቤ በመጻፍ ብቻ በንጉሡ ልጅ ላይ ያደረውን ሰይጣን ያስወጡትና በሀገርም ላይ የመጣውን የጠላትን ጦር በመርታት ድል ያደርጉ የነበሩት አቡነ ሳዊርያኖስ ዕረፍታቸው ነው፡፡




+ ቅድስት ራፊቃ እና 4 ልጆቿ ቁልቁል ተሰቅለውና አንገታቸውን በመሰየፍ ሰማዕትነታቸውን በድል ፈጸሙ፡፡

+ ዳግመኛም በዚኽች ዕለት ከቅዱስ ፋሲለደስ ጋር ማኅበርተኞቹ የሆኑ ሁለት ሺህ ሰባት ሰዎችም በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ የመጥምቁ ዮሐንስ እናት የቅድስት ኤልሳቤጥም የመታሰቢያዋ በዓል ነው፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡

+ + + + + 


ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ፡- ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት 25ኛው ነው፡፡ ስለ ቀናች ሃይማኖት ታላቅ ተጋድሎን ከፈጸመ በኋላ በተሰደደበት በደሴተ ጋግራ መስክረም 7 ቀን ዐርፏል፡፡ ንጉሡ መርቅያኖስ በጠራው ጉባዔ በጠሩት ጊዜ በቦታው ሲገኝ 636 ጉባኤተኞች ተሰብስበው ደረሰ፡፡ ‹‹ምን ጉድለት ተገኝቶ ነው ይህ ሁሉ የተጠራው?›› ሲላቸው ‹‹በንጉሡ ትእዛዝ ተጠርተን ነው›› አሉት፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም ‹‹ይህ ጉባኤ ስለ ጌታችን ክብር ቢሆን ኖሮ እኔ ተቀምጨ እግዚአብሔር በሰጠኝ በአንደበቴ እናገር ነበር ነገር ግን የጉኤው መሰብሰብ በንጉሡ ትእዛዝ ከሆነ ንጉሡ እንዳሻው ይምራው›› አላቸው፡፡


ከዚህም በኋላ የክርስቶስን ባሕርይ ለሁለት የሚከፍለው የክህደትን ቃል በውስጡ የያዘውን የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ልዮን የላከውን ደብዳቤ ቀደደው፡፡ ለጉባኤውም ርትእት የሆነች ሃይማኖትን ገለጸ፡፡ የተዋሕዶንም ምሥጢር በነፍስና በሥጋ እንዲሁም በእሳትና ብረት እየመሰለ አስዳ፡፡ ጌታችን ሰው እንደመሆኑ ወደ ሠርግ ቤት ተጠርቶ ሄደ፣ አምላክ እንደመሆኑ ውኃውን ለውጦ ወይን አደረገው›› እያለም በብዙ ምሳሌዎች ሲያስረዳቸው ከጉባኤው ሊከራከረው የደፈረ ማንም አልነበረው፡፡ ነገር ግን ክፉዎች ጉባኤውን በከሃዲው በልዮን ምክር ወዳዘጋጀው ንጉሡ መርቅያንና ወደ ሚስቱ ንግሥት ብርክያል መልዕክት ልከው ከዲዮስቆሮስ በቀር እነርሱ ያዘዙትን ሃይማኖትንና ትእዛዝ የሚቃወም እንደሌለ በመናገር ነገር ሠሩበት፡፡ ነገር ግን በጉባኤው ውስጥ ንስጥሮስን ያወገዙ አባቶችም ነበሩበት፡፡

ንጉሡም ቅዱስ ዲዮስቆሮስን አስጠርቶት ከሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት ጋር እስከ ማታ ድረስ ሲከራከሩ ዋሉ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ እንዳልተመለሰላቸው ባዩ ጊዜ ንግሥቲቷና ንጉሡ በእርሱ ተቆጥተው ክፉኛ አስደበደቡት፡፡ ጽሕሙን ነጭተው ጥርሱንም አስወለቁት፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም የተነጨ ጽሕሙንና የወለቀ ጥርሱን ሰብስቦ ወደ እስክንድርያ በመላክ ‹‹እነሆ የቀናች ሃይማኖት ፍሬ ይህ ነው›› አላቸው፡፡ ለጉበኤው የተሰበሰቡ ኤጲስ ቆጶሳትም በቅዱስ ዲዮስቆሮስ ላይ የደረሰውን ዐይተው ፈሩና ከከሃዲው ንጉሥ መርቅያኖስ ጋር ተስማሙ፡፡ ክብር ይግባውና ‹‹ለክርስቶስ ሁለት የተለያዩ ባሕርያት አሉት›› ብለው በንጉሡ መዝገብ ላይ በእጆቻቸው ጽፈው ፈረሙ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም እነርሱ የጻፉለትን መዝገብ እንዲልኩለት ሲጠይቃቸው ላኩለት እርሱም ጽፎ የሚፈርምበት መስሎአቸው ነበርና፡፡ እርሱ ግን አባቶቻችን ሐዋርያት ካስተማሯት ከቀናች ሃይማኖት በኒቅያ የተሰበሰቡ ሃይማኖታቸው የቀና የ318 ኤጲስ ቆጶሳት አባቶቻችን ከሠሯት ሕግ የሚወጣውን ሁሉ በደብዳቤው ግርጌ ጽፎ አወገዘ፡፡

መናፍቁ ንጉሥም ይህን ጊዜ እጅግ ተናዶ ጋግራ ወደምትባል ደሴት እንዲያግዙት አዘዘ፡፡ የሀገረ ቃው ኤጲስ ቆጶስ አባ መቃርስ አብሮት ተሰደደ፡፡ ሌሎቹ ግን ሸሹ፡፡ ከዚህም በኋላ እነዚያ የካዱ 636 ኤጲስ ቆጶሳት ተቀምጠው በኬልቄዶን ለራሳቸው መመሪያ የሚሆናቸውን ሥርዓት ሠሩ፡፡ በጋግራ ደሴት ያለው ኤጲስ ቆጶስም ከንጉሡ ጋር የተባበረ ነበርና አቡነ ዲዮስቆሮስ ላይ ብዙ መከራ አደረሰበት፡፡ የደሴቱ ሰዎች ግን በቅዱስ ዲዮስቆሮስ እጅ የሚፈጸሙ ተአምራትን እያዩ እጅግ ያከብሩት ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ አባ መቃርስን ወደ እስክንድርያ ሄዶ ሰማዕት እንደሚሆን ትንቢት ነገረውና ከነጋዴዎች ጋር ላከው፡፡ እንደተናገረውም አባ መቃርስ በእስክንደርያ ሰማዕት ሆኖ ዐረፈ፡፡ አቡነ ዲዮስቆሮስ ግን በዚያቹ በጋግራ ደሴት ሰማዕትነቱን ፈጽሞ በክብር ዐርፏል፡፡ ምእመናንም ሥጋውን በዚያው አኖሩት፡፡ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡

+ + + + + 


አቡነ ሳዊርያኖስ፡- የግሪክ አቴናን ፍልስፍናና ጥበብ ጠንቅቀው የተማሩ ናቸው፡፡ ምግባር ሃይማኖታቸው የሰመረ፣ ትሩፋት ተጋድሏቸው የቀና ነው፡፡ ብሉይን ከሐዲስም አጠናቀው ተምረዋል፡፡ ወላጆቻቸው ያወረሷቸውን እጅግ የተትረፈረፈ ንብረት ሸጠውና ለጦም አዳሪዎች መጽውተው ለድኆች ማደሪያና ለእንግዶች ማሪፊያ ቤት ሠርተው ነዳያንን ይንከባከቡ ጀመር፡፡ ይህንንም የጽድቅ ሥራቸውን የሮሜው ጻድቁ ንጉሥ አኖሬዎስ ሲሰማ እጅግ ደስ ተደስቶ አስመጥቶ ከእርሱ ጋር በቤተ መንግሥቱ አማካሪና አባቱ አድርጎ አኖራቸው፡፡ ከንጉሡም ጋር አብረው ሁልጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ሌሊቱን በሙሉ ለጸሎት ቆመው ያድራሉ፡፡

ጻድቁ የገብላው አገር ንጉሥ ሴት ልጁን ሰይጣን ይዟት ሳለ ደብዳቤ በመጻፍ ልከው በልጅቷ ላይ ያደረውን ሰይጣን በደብዳቤአቸው ብቻ አስወጥተውታል፡፡ አቡነ ሳዊርያኖስ ደብዳቤ በመጻፍ ብቻ በሀገር ላይ የመጣ የጠላትንም ጦር እያሸበሩ ድል ያደርጉ ነበር፡፡ ይኸውም የቍስጥንጥንያው ንጉሥ አርቃዴዎስና አኖርዮስ በገብላ አገር ኤጲስቆጶስነት ከሾሟቸው በኋላ የፋርስ ሰዎች እነዚህን ደጋግ ነገሥታት ሊወጓቸው ሽተው በኃይል በመጡባቸው ጊዜ ወደ አባ ሳዊርያኖስ መልአክትን ላኩ፡፡ አባታችንም ለቅዱሳን ነገሥታቱ ‹‹እኛ የክርስቶስ ከሆንን መንግሥታችንም የክርስቶስ ነው፣ እንዲህም ከሆነ የጦር መሣርያ የጦር ሠራዊትም አንሻም…›› ብለው ደብዳቤ ጽፈው እንደላኩ ነገሥታቱ ያለ ምንም ጦርነት የፋርስን ሀገር ሰዎች አሸንፈው ወደ ሀገራቸው መልሰዋቸዋል፡፡


አቡነ ሳዊርያኖስ በገብላ አገር ኤጲስቆጶስነት ከተሾሙ በኋላ የሙሴን ሕግ በማወቁ የሚመካ አንድ ስሙ ስቅጣር የሚባል አይሁዳዊ ወደ እርሳቸው መጥቶ ተከራከራቸው፡፡ የጻድቁንም ቃላቸውን ሊሰማቸው አልቻለም ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ ጌታችን ለአቡነ ሳዊርያኖስ ተለጠላቸውና ‹‹እኔ ካከበርኳቸው ወገኖች ይሆናል›› በማለት እንደሚያምን ነገራቸው፡፡ ያም አይሁዳዊ ወደቤቱ በገባ ጊዜ ወገኖቹ አይሁድ ሲኦል ውስጥ ሆነው ሲሠቃዩ በራእይ ተመለከተ፡፡ ‹‹ከሃዲዎች ዘመዶችህን እነሆ እይ›› የሚል ድምንም ሰማ፡፡ በማግሥቱም ይህ አይሁዳዊ ወደ አቡነ ሳዊርያኖስ መጥቶ ከእግራቸው ሥር ወድቆ እንዲያስተምሩትና የክርስቶስ ወገን እንዲያደርጉት ለመናቸው፡፡ እርሳቸውም አስተምረው ከሀገሩ ሰዎች ጋር አንድ ላይ አጠመቋቸው፡፡ የቀሩት ብዙ አይሁድም በጌታችን አምነው ተጠመቁ፡፡ አቡነ ሳዊርያኖስ ሥራየኛ ጠንቋዮችን ሁሉ እያሳመኑ አስተምረው አስጠምቀዋቸዋል፡፡


አቡነ ሳዊርያኖስ ስለ ዮሐንስ አፈወርቅ ስደትና እንግልት ያለችበት ድረስ ሄደው ንግሥት አውዶክስያን ቢመክሯትና ቢገሥጹዋትም በክፋቷ ጸንታ አልሰማቸው ብትል ተመልሰው ወደ አገራቸው ሄደዋል፡፡ አቡነ ሳዊርያኖስ ተአምራታቸው ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በጣም ብዙ ድርሳናትን ደርሰዋል፡፡ 100 ዓመት በሆናቸው ጊዜ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ከ10 ቀን በኋላ በሞት እንደሚያርፉ ነገራቸው፡፡ ሕዝቡንም ጠርተው በሃይማኖት እንዲጸኑ ከመከሯቸውና ከተሰናበቷቸው በኋላ መስከረም 7 ቀን በሰላም ዐርፈዋል፡፡ ይኸውም ዕረፍታቸው የተከናወነው ኤጲፋንዮስ ባረፈ በ2ኛ ዓመቱ ዮሐንስ አፈወርቅ ባረፈ በዓመቱ ነው፡፡ ጌታችን የብርሃን ሰረገላ ሰጥቷቸዋል፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
+ + + + + 

ሰማዕታቱ ቅድስት ራፊቃ እና አራት ልጆቿ፡- ለቅድስት ራፊቃ እና ለአራት ልጆቿ ማለትም ለአጋቶን፣ ለጴጥሮስ፣ ለዮሐንስና ለአሞን ጌታችን ለሁሉም በራእይ ተገልጦላቸው በስሙ መስክረው ሰማዕት እንሚሆኑ ነገራቸው፡፡ አስቀድሞም ታላቁ አጋቶን በአገሩ ተሹሞ በሥልጣን ሆኖ ነበር፡፡ የጌታችንንም የሰማዕትነት ጥሪ ተቀብለው ከላይኛው ግብጽ ከቁስ አውራጃ ተነሥተው በከሃዲው መኮንን በዲዮናስዮስ ፊት ስለ ጌታችን አምላክነት መሰከሩ፡፡ መኮንኑም ብዙ ሥቃዮችን አደረሰባቸው፡፡ ጌታችንም በተአምራት ከመከራቸው ሲያድናቸው ያየ ብዙ ሰዎች ሲያምኑ መኮንኑ እጅግ ተቆጥቶ ጽኑ ሥቃይ አደረሰባቸው፡፡ ማሠቃየትም በሰለቸው ጊዜ ወደ እስክንድርያው ገዥ አርማንዮስ ዘንድ ላካቸው፡፡ ከሃዲው አርማንዮስም ሥጋቸውን ቆራርጦ በመንኮራኩር ውስጥ ጨመራቸው፡፡ ነገር ግን ጌታችን ጤነኛ አድርጎ ፈወሳቸው፡፡ ዳግመኛም ዘቅዝቀውም ሰቀሏቸው፡፡ አሁንም ጌታችን አዳናቸው፡፡ በተአምራተቸውም ብዙዎች በጌታችን አመኑ፡፡ በመጨረሻም ራሶቻቸውንም በሰይፍ ቆርጠው ሥጋቸውን ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ ቅድስት ራፊቃና አራት ልጆቿም ሰማዕትነታቸውን በዚሁ ፈጸሙ፡፡ የታዘዘ መልአክም መጥቶ ለአንዱ ባለጸጋ የቅዱሳኑን ሥጋ ያለበትን ነግሮት እንያወጣውና በክብር እንዲያስቀምጠው ነአዘዘው፡፡ ባለጸጋውም የቅዱሳኑን ሥጋቸውን ከባሕሩ አወጥቶ የመከራ ዘመን እስኪያልፍ በክብር አኖረው፡፡ ከሥጋቸውም ብዙ ተአምራት ተገልጠው ታዩ፡፡ የሰማዕታቱ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
+ + + + +

+ ዳግመኛም በዚኽች ዕለት እመቤታችን ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክን የወለደቻት ቅድስት ሐና ልደቷ ነው፡፡ ሐና ማለት ‹‹ጸጋ›› ማለት ነው፡፡ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እናት ናት፡፡ እርሷም ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት ልጁ ናት፡፡ የቅድስት ሐና አባት ማጣትና እናቷ ሄርሜላ ከእርሷ በተጨማሪ ሶፍያና ማርያም የሚባሉ ሌሎች ሁለት ሴት ልጆችን ወልደዋል፡፡ ቅድስት ሐና ከይሁዳ ነገድ የሆነውን ጻድቅ ኢያቄምን አግብታ ቅድስት ድንግል ማርያምን ወለደች፣ ድንግል ማርያምም መድኃኔዓለም ክርስቶስን ወለደች፡፡ ሶፍያ ኤልሳቤጥን ወለደች፣ ኤልሳቤጥም መጥምቁ ዮሐንስን ወለደች፡፡ ከሦስቱም ታናሽ የሆነችው ‹‹ማርያም›› የተባለችው የማጣትና የሄርሜላ ልጅ ደግሞ ሰሎሜን ወለደቻት፡፡
ይኽችም ታላቅ እናት ቅድስት ሐና አምላክን በድንግልና ሆና በሥጋ ለወለደችው ለቅድስት ድንግል ማርያም ወላጇ ትሆን ዘንድ የተገባት ሆናለችና ከሴቶች ሁሉ እንደምትበልጥና እንደምትከብር እንረዳ፡፡ ለዓለም ሁሉ ድኅነት የተደረገባትን ልዩ ስጦታ የሆነች ድንግል ማርያምን እርሷ አስገኘቻት፡፡ ለክብር ባለቤት ለጌታችን ለአምላችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ አያቱ ሆናለችና ምን ያህል ክብርት እንደሆነችና እግዚአብሔር የመረጣት ንጽሕት ቅድስት እንደሆነች በዚህ ይታወቃል፡፡ ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ በጸሎቷ ይማረን፡፡


Monday, January 31, 2022

ጥር 18 - ወበዛቲ ዕለት

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈሰ ቅዱስ ስም አሜን

ጥር 18-ፀሐይ ዘልዳ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዐፅሙ ተቃጥሎ አጥንቱ ተፈጭቶ በደብረ ይድራስ ተራራ ላይ የተበተነበት ዕለት ነው፡፡



+ በ34 ዓ.ም ጥምቀትን ያመጣልን ለሀገራችንም ሆነ ለአፍሪካ የመጀመሪያ ሐዋርያችን የሆነው ቅዱስ አቤላክ (ባኮስ) በዚህች ዕለት በሰሜን ተራራዎች ላይ ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት ቦታ ተሰወረ፡፡ እርሱም በጌታችን የተመረጡ የከበሩ ሐዋርያት እንኳን ወንጌልን በዓለም ለመስበክ ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት ወቅት ወደ አፍሪካ መጥቶ ወንጌልን የሰበከ ነው፡፡
+ ለቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ መምህሩ የሆኑት አባ ያዕቆብ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+ ጌታችን ከሞት ያስነሣው የቅዱስ አልዓዛር እኅቶች ማርያምና ማርታ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡
አባ ያዕቆብ፡- በገድል ተጠምደው የኖሩ እጅግ የከበሩ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉት ንጽቢን በምትባል ከተማ ቢሆንም ሶርያዊ ተብለው ይጠራሉ፡፡ የሀገረ ንጽኒቢን ኤጲስ ቆጶስ ሲሆኑ የእመቤታችንን ውዳሴ ለደረሰው ታላቅ አባት ለቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ መምህሩ ናቸው፡፡ ይህ ታላቅ አባት ከልጅነታቸው ጀምሮ ዓለምን ንቀው በመንኩስና መኖርን መርጠው መንኩሰዋል፡፡ በጠጉር ከተሠራ ማቅ በቀር ሌላ ልብስ ለብሰው አያውቁም፡፡ በቀን በሌሊት፣ በበጋ ሐሩርም ይሁን በክረምት ቁር ቢሆን ይህንን ልብሳቸውን አውልቀውት አያውቁም፡፡ ምግብም ከቅጠላ ቅጠል ውጭ ተመግበው አያወቁም፡፡ የሚጠጡትም የዝናብ ውኃ ብቻ ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ ሀብተ ትንቢትና ሀብተ ፈውስ ተሰጥቷቸው እጅግ አስገራሚ የሆኑ ተአምራትን ያደርጉ ጀመር፡፡ በአንዲት ዕለት ሴቶች በውኃ ምንጭ ላይ እርቃናቸውን ያለ ማፈር ሲጫወቱና ሲሳለቁ አይተው የውኃውን ምንጭ ወዲያው እንዲደርቅ አድርገውታል፡፡ የሴቶቹንም የራሳቸውን ጸጉር በተአምራት ነጭ ሽበት አደረጉባቸው፡፡ ሴቶቹም ተጸጽተው በአባታችን እግር ሥር ወድቀው በለመኗቸው ጊዜ የውኃውን ምንጭ መልሰው አፈለቁላቸው፡፡ እንዳይታበዩ ሲሉ ግን የራሳቸውን ጸጉር ለምልክት ነጭ አድርገው ተውላቸው፡፡ ትሩፋታቸውና ዜናቸው በበየቦታው በተሰማ ጊዜ አቡነ ያዕቆብን በንጽቢን ሀገር ላይ ኤጲስ ቆጶስነት ሾሟቸው፡፡
ጻድቁ ንጉሥ ታላቁ ቈስጠንጢኖስ 318ቱን የከበሩ አባቶች በኒቅያ እንዲሰበሰቡ ሲያደርግ ገድላኛ የሆኑት ይህ ታላቅ አባትም አንዱ ነበሩ፡፡ በጉባኤውም መካከል ሙት አስነሥተው እንዲመሰክር አድርገውታል፡፡ እርሳቸውም አርዮስን አስተምረው መክረው እምቢ ቢላቸው ረግመው አውግዘውታል፡፡ የፋርስ ንጉሥ መጥቶ ሀገረ ንጽቢን ሊወር አስቦ በከበባት ጊዜ አቡነ ያዕቆብ በጸሎታቸው የጭጋግ ደመና በሠራዊቱ ላይ አመጡባቸው፡፡ ተናዳፊ ትንኞችም ፈረሶቻቸውንና ወታደሮቻቸውን ሁሉ ነደፏቸው፡፡ ፈረሶቹም ማሠሪያቸውን እየበጠሱ ፈርጥተው ጠፉ፡፡ ንጉሡም ይህን ተአምር አይቶ እጅግ ፈርቶ ወደ ኋላው ተመልሶ ሄዷል፡፡ ጻድቁ ሕዝበ ክርስቲያኑንና ሀገራቸውን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በጽድቅ ሲያገለግሉ ኖረው በሰላም ዐርፈዋል፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!
+ + +
ስብረተ ዐፅሙ ለሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ፡- ከሃዲው ንጉሥ ዱድያኖስ እጅግ አሠቃቂ በሆኑ ብዙ መከራዎች እያሠቃየ ሦስት ጊዜም ቢገድለው ጌታችን ግን ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሞት እያስነሣው ከሃድያንን ያሳፍራቸው ነበር፡፡ ንጉሥ ዱድያኖስ የሚያደርገው ቢያጣ ጭፍሮቹን ‹‹በመንኰራኩር ፈጭታችሁ አጥንቱን ደብረ ይድራስ ተራራ ላይ ወስዳችሁ ዝሩት›› ብሎ አዘዛቸው፡፡ ጭፍሮቹም የቅዱስ ጊዮርጊስን ሥጋ በመንኰራኩር ፈጭተው ወስደው በተራራው ላይ ቢረጩት ሥጋው ያረፈበት ሳር፣ ቅጠሉ፣ ደንጊያው፣ እንጨቱ ሁሉ ‹‹ጊዮርጊስ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር፣ ጊዮርጊስ ሰማዕቱ ለእግዚአብሔር›› እያሉ አመስግነዋል፡፡ አሁንም ጌታችን ለሦስተኛ ጊዜ ከሞት አስነሣውና ሥጋውን ፈጭተው በተራራም ላይ ሥጋውን በትነውት ወደ ንጉሡ የሚመለሱትን ወታደሮች በመንገድ ከኋላቸው ሄዶ ደረሰባቸውና ‹‹ቆዩኝ ጠብቁኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም እጅግ ደንግጠው ይህ እንዴት እንደሆነ ሲጠይቁት ‹‹አምላኬ ከሞት አዳነኝ›› አላቸው፡፡ ጭፍሮቹም እጅግ ደንግጠው ከእግሩ ስር ወድቀው ‹‹ይቅር በለን›› ብለው በአምላኩ እንደሚያምኑ መሰከሩለት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ከመሬት ላይ ውሃ አመንጭቶ በጸሎት ጌታችንን ቢጠይቅ ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ አጥምቋቸዋል፡፡ እነርሱም በንጉሣቸው ፊት ሄደው ስለጌታችን በመመስከር በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዐፅሙ ተቃጥሎ አጥንቱ ተፈጭቶ በደብረ ይድራስ ተራራ ላይ የተበተነው በዚህች ዕለት ነው፡፡

የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
የመጀመሪያው የአፍሪካ ሐዋርያ ቅዱስ አቤላክ (ባኮስ)፡- ይኽም ጃንደረባ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ንግሥት የሆነችው የህንደኬ የገንዘቧ ሁሉ ኃላፊና አዛዥ የነበረ ነው፡፡ ከአባቱ እብነ መላክ ከእናቱ ስሂነ ሕይወት ታኅሣሥ 29 ቀን ተወለደ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ለበዓለ ፋሲካ በቤተ መቅደስ ይሰግዱ እንደነበረው ሁሉ ይኽም ጃንደረባ ከ4 ሺህ ማይልስ በላይ ተጉዞ ኢየሩሳሌምን ተሳልሞ በመለስ ላይ ነበረ፡፡ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ በተለይም ስለ ጌታችን መከራ መስቀል በዝርዝር የሚናገረውን ክፍል 53ኛውን ምዕራፍ ያነብ ነበር ነገር ግን ጃንደረባው ስለማን እንደሚናገር አልገባውም ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር በአካባቢው ወንጌልን ይሰብክ የነበረውን ሐዋርያውን ቅዱስ ፊሊጶስን ላከለት፡፡ እርሱም ጃንደረባው ያነበው የነበረውን መጽሐፍ ተረጎመለት፣ የከበረች ወንጌልን ሰበከለት፣ በመጨረሻም አጠመቀው፡፡ ሐዋርያው ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በጃንደረባው ላይ ወረደ፡፡ ሐዋ 8፡26-40፡፡ ይህን ለእኛ ለኢትዮጵያውን እጅግ የሚያኮራን ታሪካችን ነው፡፡ ዛሬ በእጃችን ላይ በመገኘው መጽሐፍ ውስጥ ባይኖርም በቆዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች ላይ ግን ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ ጃንደረባውን ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በኢትዮጵያው ጃንደረባ ላይ እንደወረደ ተጽፏል፡፡ (ዝኒ ከማሁ ገጽ 87፣ v.39.cord.alexand. in bible reg. angl-alique plures codd.mss)
ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ጃንደረባውን ያጠመቀበት ወንዝ ‹‹ቤተ ሳሮን›› በተባለችውና እስከዛሬም ድረስ ከኢየሩሳሌም 20 ማይልስ ርቀት በምትገኘው መንደር በኬብሮን መካከል ባለው ኮረብታ ሥር የሚመነጭ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ጸሐፊ የሆነው ሊቁ ቅዱስ ጀሮም ጃንደረባውን ‹‹የኢትዮጵያውያን ሐዋርያ›› በማለት ይጠራዋል፡፡ በሰፊው ለኢትዮጵያውያን ወንጌልን የሰበከ እርሱ ነውና፡፡ ጌታችን የመረጣቸው የከበሩ ሐዋርያት እንኳን ወንጌልን በዓለም ለመስበክ ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት ወቅት በ34 ዓ.ም ነው ቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ በክርስቶስ አምና ወንጌልን የተቀበለችው፡፡ በምድሪቱም ላይ ወንጌል መነገር የጀመረው ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡
እንሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከኢየሩሳሌም ወንጌልን ተምሮና ተጠምቆ ወደ አክሱም እንደተመለሰ በመጀመሪያ ያጠመቀው ንግሥቲቷን ሕንደኬን ነው፡፡ ከእርሷም በኋላ መኳንንቱና መሳፍንቱ ሁሉ አምነው በባኮስ እጅ ተጠመቁ፡፡ ይኸውም በ34 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚህም በኋላ ባኮስ እስከ ኑብያ ድረስ ሄዶ ወንጌልን ሰብኮ ብዙዎችን አሳምኖ አጥምቋል፡፡ በዚህም ጊዜ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በባኮስ እየተሰጠ የነበረውን የወንጌል ብርሃን የበለጠ እንዲበራ አድርጓል፡፡ ከጃንደረባውም ጋር ሆነው በብዙ ቦታዎች አብረው ወንጌልን ሰብከው አምልኮተ ጣዖትን አጥፍተዋል፡፡
ከዚህም በኋላ ባኮስ ወደ የመን በመሄድ በዚያም ክርስትናን በማስተማር ብዙዎችን አሳምኖ ካጠመቀ በኋላ ወደ ፐርሺያ ከዚያም ወደ ሕንድ በመሄድ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሟል፡፡ በመጨረሻም ጥንት ታፕሮባና (taprobana) ዛሬ ሲሎን በምትባለው ደሴት ወንጌልን በማስተማር ላይ እያለ በሰማዕትነት እንዳረፈ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ (lives of the most eminent fathers of the church, page 87) በሌላም በኩል ሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከመጠመቁ በፊት 35 ዓመት ከተጠመቀ በኋላ ደግሞ 41 ዓመት ኖሮ በኢየሩሳሌምም 3 ዓመት ተቀምጦ ወንጌልን ዞሮ ካስተማረ በኋላ በመጨረሻ በ79 ዓመቱ ጥር 18 ቀን በሰሜን ተራራዎች ላይ ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት ቦታ እንደተሰወረ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ጽፈዋል፡፡

የቅዱስ አቤላክ (ባኮስ) ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!




Like
Comment
Share

Saturday, January 22, 2022

❤ ቂርቆስ ወኢየሉጣ ❤


እንኳን ለሰማዕታት ቅዱሳን ቂርቆስ ወኢየሉጣ ወነቢይ አብድዩ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
❤ ቂርቆስ ወኢየሉጣ ❤
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካሏት ዐበይት ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ቂርቆስ ነው። በተለይ በዘመነ ሰማዕታት ተነስተው እንደ ከዋክብት ካበሩትም አንዱ ነው።
ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል፦ "መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራል።"
(ማቴ. ፯፥፲፯)
መልካም ዛፍ ቅድስት ኢየሉጣ መልካም ፍሬ ብፁዕ ቂርቆስን አፍርታ ተገኝታለችና ክብር ይገባታል። ቡርክተ ማኅጸንም እንላታለን። የተባረከ ማኅጸኗ የተባረከ ልጅን ለዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ተሸክሟልና።
በዚያ ክርስቲያን መሆን መከራ በነበረበት ዘመን ይህንን ደግ ሕፃን እርሷን መስሎ እርሷንም አህሎ እንዲገኝ አስችላለችና። አበው በትውፊት እንዳቆዩልን ከሆነ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እናታችን ቅድስት ኢየሉጣ ብፁዕ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስን ወልዳለች።
በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮም ግዛት ክርስትና ቢስፋፋም በዚያው ልክ መምለክያነ ጣዖቱ የገነኑ ነበሩ። በተለይ ከነገሥታቱ ጀምሮ ዋና ዋና የሥልጣን ቦታዎች በአሕዛብ እጅ በመሆናቸው ለዘመኑ ክርስቲያኖች ፈታኝ ነበር።
ማንኛውም ክርስቲያን መሠረታዊ ፍላጐቶቹ እንዲሟሉለት አሕዛብ ላቆሟቸው ጣዖቶች መንበርከክ ነበረበት። መብቱን ከመገፈፉ ባሻገር "ተበድያለሁ" ብሎ ወደ ፍርድ ቤት ሔዶ እንኳ የመጮህ እድል አልነበረውም። ምክንያቱም የሚሰማው የለም።
በዚያ ላይ በየጊዜው ለክርስቲያኖች ፈታኝ የሆኑ አዋጆች ይወጣሉ። የክርስትናን ጐዳና ይበልጥ የሚያጠቡ ሕጐችም ዕለት ዕለት ይፈበረኩ ነበር። ስለዚህም በወቅቱ የነበረ አንድ ክርስቲያን ሃይማኖቱን ከወደደ ወይ እስከ ሞት መታገስ ካልሆነ ደግሞ ሃገሩ ጥሎ በዱር በገደል መሰደድ ነበረበት።
እውነት ለመናገር ዜና ሰማዕታትን የማያውቅ ክርስቲያን ክርስቶሳዊ ነው ሊባል አይችልም። ምክንያቱም ዛሬ እንዲህ እንደ ዋዛ የያዝናት ሃይማኖታችን እንዴት እንደ መጣችና ምን እንደ ተከፈለባት አብዛኛው ትውልድ አያውቅምና።
ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ብፅዕት ኢየሉጣም የዚህ ዘመን (የዘመነ ሰማዕታት) ፍሬ ናቸው። በጊዜው በሮም ግዛት ሥር እስክንድሮስ የሚሉት ክፉ ንጉሥ ነግሦ ነበርና ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ። ጣዖትን ላለማምለክም ተሰው።
በዚህ ጊዜ አንጌቤናይት (ኢጣልያዊት) ብፅዕት ኢየሉጣም በመበለትነት (ባሏ በሕይወት ባለ መኖሩ) ትኖር ነበር። ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ ምንም ገና ሦስት ዓመቱ ቢሆንም ነገረ ሃይማኖትን ታስተምረው ፍቅረ ክርስቶስን ትስልበት ነበር።
እስክንድሮስ የክህደት አዋጅን ሲያውጅም ቅድስቲቱ ለሕፃን ልጇ ራርታ ሽሽትን መረጠች። ሃብት ንብረቷን፣ ወገንና ርስቷንም ትታ ሕፃን ልጇን ተሸክማ ተሰደደች። መከራው ግን በሔደችበት አለቀቃትም።
እስክንድሮስ ተከትሎ ባለችበት ቦታም አገኛት። ወታደሮች ልጇን ሳያገኙ እርሷን ብቻ ይዘው ወደ መኮንኑ አቀረቧት። መኮንኑም "ስምሽን ንገሪኝ?" ቢላት "ስሜ ክርስቲያን ነው።" አለችው። ተቆጥቶ "ትክክለኛውን ስምሽን ተናገሪ?" ቢላት "እውነተኛው ስሜ ክርስቲያን ነው። ሞክሼ (ሞክሲ) ስም ከፈለግህ ኢየሉጣ እባላለሁ።" አለችው።
"ለጣዖት ልትሰግጂ ይገባል።" ሲላትም "እውነትን ይነግረን ዘንድ የሦስት ዓመት ሕፃን ፈልገህ አምጣና ተረዳ።" ስላለችው ወታደሮቹን እንዲፈልጉ ላካቸው። የሃገሩ ሰዎች ልጆቻቸውን ስለደበቁ የተገኘ ቅዱስ ቂርቆስ ነበር።
ቅዱሱ ሕፃን በወታደሮች ተይዞ ሲቀርብ መልኩ ያበራ ነበርና መኮንኑ "በሐከ ፍሡሕ ሕፃን - ደስ የተሰኘህ ሕፃን እንዴት ነህ?" ቢለው "ትክክል ነህ! እኔ በጌታዬ ክርስቶስ ዘንድ ደስታ ይጠብቀኛል። አንተ ግን በክህደትህ ወደ ገሃነም ትወርዳለህ።" አለው።
በሕፃኑ ድፍረት የደነገጠው መኮንኑ በብስጭት "እሺ! ስምህን ንገረኝ?" አለው። ያን ጊዜ "ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ ስሜ ክርስቲያን ነው። እናቴ የሰየመችኝን ከፈለክ ግን ቂርቆስ ነው።" ሲል መለሰለት።
ከዚያም እየደጋገመ "እኔ ክርስቲያን ነኝ።" ብሎ በመጮሁ መኮንኑ ስቃይን በቅዱሱ ሕፃን እና በቡርክት እናቱ ላይ አዘዘ። ከዚህ በኋላ በእነርሱ ላይ የተፈጸመውን ግፍና የወረደባቸውን የመከራ ዶፍ እናገር (እጽፍ) ዘንድ ግን የሚቻለኝ አይመስለኝም።
በግርፋት የጀመረ ስቃይ ሊሰሙት ወደ ሚጨንቅ መከራ ቀጠለ።
ሰባት ብረት አግለው በዓይናቸው፣ በጆሯቸው፣ በአፋቸውና በልባቸው ከተቱ።
በአራት ችንካሮች ላይ አስቀመጧቸው።
በእሳት አቃጠሏቸው።
ጸጉራቸውን ከቆዳቸው ጋር ገፈፉ። ከዚህ በላይ ብዙ ስቃይንም አመጡባቸው።
እናትና ልጅ ግን ለክርስቶስ ታምነዋልና ጸኑ። ቅድስት ኢየሉጣ ብትደነግጥ ልጇ አጸናት። ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት ሲያርፉ ጌታ እንደ ቃሉ የሕፃኑን ሥጋ በሠረገላ ኤልያስ አኑሮታል። ለእኛ የሚጠቅም ብዙ ቃል ኪዳንንም ሰጥቶታል።
❤ ቅዱስ አብድዩ ነቢይ ❤
"አብድዩ" ማለት "የእግዚአብሔር አገልጋይ" ማለት ነው። ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን የቅዱስ ኤልያስ ታላቁም ደቀ መዝሙር ነው። ቅዱሳን ነቢያት ዮናስና ኤልሳዕም ባልንጀሮቹ ነበሩ።
ቅዱስ አብድዩ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስምንት ዓመት አካባቢ የከሃዲው ንጉሥ የጦር መሪ ሆኖ በሃምሳ አለቃነት አገልግሏል። ግፈኛዋ ኤልዛቤል ነቢያተ እስራኤልን ስታስፈጅ ሃምሳውን በአንድ ዋሻ ሃምሳውን ደግሞ በሌላ ዋሻ አድርጐ አትርፏቸዋል። ዘጠኝ መቶው ግን ተጨፍጭፈዋል።
ያተረፋቸውንም ክፉ ዘመን እስኪያልፍ ድረስ መግቧቸዋል። አክአብና ኤልዛቤል ከሞቱ በኋላም ቅዱስ ኤልያስን ተከትሎ ሹመቱን ትቷል። እግዚአብሔር ገልጾለትም ትንቢት ሲናገር ሕዝቡንም ሲገሥጽ ኑሯል።
በብሉይ ኪዳን ካሉ የትንቢት መጻሕፍትም በጣም አጭሩን የጻፈው ይህ ነቢይ ነው። ትንቢተ አብድዩ ባለ አንድ ምዕራፍ ብቻ ናትና። ቅዱሱ በዚህች ቀን ዐርፎ ወገኖቹ ቀብረውታል።
አምላከ ሰማዕታት በምሕረቱ ይማረን። በይቅርታው ኃጢአታችንን ይተውልን። ከበረከተ ሰማዕታትም ይክፈለን።
ጥር ፲፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ
፪.ቅዱስ አብድዩ ነቢይ
፫.ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ
፬.ቅድስት ሶፍያ
፭.ቅድስት አድምራ
፮.አሥራ አንድ ሺህ አርባ አራት ሰማዕታት (ከቅዱስ ቂርቆስ ጋር በሰማዕትነት ያለፉ።)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
፪.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት
፫.ቅድስት ክርስጢና
፬.ቅድስት እንባ መሪና
"በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ በልብህም 'ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው?' የምትል አንተ ሆይ! የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል። እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን 'ከዚያ አወርድሃለሁ።' ይላል እግዚአብሔር።"
(አብድዩ ፩፥፫-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር https://www.facebook.com/tewahdohamanotachin/
No photo description available.
103
17 Shares
Like
Comment
Share