Tuesday, December 11, 2012

ምስጢረ ሥላሴ




የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ምስጢር

ምስጢር የሚለው ቃል አመሰጠረ፣ ሰወረ፣ አረቀቀ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ፍቺውም ረቂቅ፣ ስውር፣ ኅቡዕ ማለት ነው፡፡ ምስጢር መባሉም የሥላሴን ባሕርይ ፍጡር መርምሮ የማይደርስበት በመሆኑ፣ በፍጡር ባሕርይ መወሰን፣ መጨረሻውን ማወቅ የማይቻልና ከፍጡር እውቀት አቅም በላይ በመሆኑ ነው፡፡ ሥላሴ የሚለው ቃል ደግሞ ሠለሰ ሦስት አደረገ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሦስትነት ማለት ነው፡፡ ቅድስት ሥላሴ: - ለሥላሴ ቅድስት ብለን እንቀጽላለን፡፡ ቅድስት ሥላሴ ማለት ልዩ ሦስትነት ማለት ነው፡፡ ይህም ሦስት ሲሆን አንድ፣ አንድ ሲሆኑ ሦስት ስለሚሆኑ ልዩ ሦስትነት ተብሏል፡፡
ስለዚህ ነገር መጽሐፈ ቅዳሴያችን ሥላሴ ሦስት ናቸው ስንል እንደ አብርሃም እንደ ይስሐቅ እንደ ያዕቆብ ማለታችን አይደለም ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸው እንጂ፣ አንድ ናቸውም ስንል ቀዳሚ ሆኖ እንደተፈጠረው እንደ አዳም ማለታችን አይደለም አንድ ሲሆኑ ሦስት ናቸው እንጂ፡፡ /ቅዳሴ ማርያም/፡፡ ቅድስት ተብሎ በሴት አንቀጽ መጠራቱ ደግሞ እናት ለልጇ ስለምታዝንና ስለምትራራ ሥላሴም ለፍጥረታቸው ምሕረታቸው ዘለዓለማዊ ነውና ቅድስት ይባላሉ፡፡
በዚህ መሠረት ምሥጢረ ሥላሴ ማለት የአንድነት የሦስትነት ምስጢር ማለት ነው፡፡
ይኸውም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስት ሲሆኑ በባሕርይ በሕልውና፣ በመለኮት ደግሞ አንድ ናቸው፡፡ እንደዚህ ባለ ድንቅ ነገር አንድ ሲሆኑ ሦስት፣ ሦስት ሲሆኑ አንድ ይባላሉና፣ ይህም ልዩ ሦስትነት ረቂቅ እና በሰው አእምሮ የማይመረመር ስለሆነ ምስጢር ይባላል፡፡
የሰው ልጅ ሁሉን የመመርመርና የመረዳት መብትና ሥልጣን ከአምላኩ የተሰጠው መሆኑ ቢታወቅም የፈጣሪን ባሕርይና ጠባዮቹን ለመገንዘብ ውሱን ከሆነው አቅሙ በላይ ስለሚሆንበት በእምነት ከመቀበል በቀር ሌላ አማራጭ መንገድ ሊኖረውም አይችልም፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት በማድረግና ከቅዱሳን አባቶች በተላለፈልን ትምህርት መሠረት ኃያሉ እግዚአብሔርን በአንድነትና በሦስትነት እናምነዋለን፡፡ እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስት፣ ሦስት ሲሆን አንድ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡
የእግዚአብሔርን አንድነት የምናምነው፡- በፈጣሪነት፣ በአምላክነት፣ በአገዛዝ፣ በፈቃድ፣ በሥልጣን እነዚህን በመሳሰሉት የመለኮት ባሕርያት ነው፡ /መለኮት ወይም ማለኹት/ በዕብራይስጥ ቋንቋ መንግሥት ማለት ነው፡፡ በግዕዝ ግን ባሕርይ፣ አገዛዝ፣ ሥልጣን ማለት ነው፡፡ ሦስትነቱን የምናምነው ደግሞ በስም፣ በግብር /በኩነት/ በአካል ነው፡፡ «እንዘ አሐዱ ሠለስቱ ወእንዘ ሠለስቱ አሐዱ፣ ይሤለሱ በአካላት ወይትዋሐዱ በመለኮት» እንዳለ /ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ/፡፡
ሀ/ እግዚአብሔር በአንድነቱ የሚታወቅበት ስሞች
1. ፈጣሪ
2. አምላክ
3. ጌታ
4. መለኮት
5. እግዚአብሔር
6. ጸባኦት
7. አዶናይ
8. ኤልሻዳይ የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ለ/ እግዚአብሔር በሦስትነቱ የሚታወቅባቸው ስሞች ደግሞ
1. አብ
2. ወልድ
3.መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡

ሐ/ እግዚአብሔር በግብር ሦስትነቱ የሚታወቀው
1. አብ ወላዲ፣ አሥራፂ በመባል፣
2. ወልድ ተወላዲ በመባል፣
3. መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ በመባል ነው፡፡

የአብ ግብሩ መውለድ፣ ማስረጽ ሲሆን የወልድ ግብሩ መወለድ፣ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መስረጽ ነው፡፡ አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ /የወጣ፣ የተገኘ/ ነው፡፡ አብ አባት ነው፣ ወልድ ልጅ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ የሠረፀ ነው፡፡ /ዮሐ.14-26/፡፡ ሦስቱ አካላት አንድ መለኮት ናቸው፡፡ ሠለስቱ ስም አሐዱ እግዚአብሔር እንዳለ /አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው/፡፡
የአካል ሦስትነታቸውም ለአብ ፍጹም አካል፣ ፍጹም መልክ፣ ፍጹም ገጽ አለው፤ ለወልድም ፍጹም አካል፣ ፍጹም መልክ፣ ፍጹም ገጽ አለው፤ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል፣ ፍጹም መልክ፣ ፍጹም ገጽ አለው፡፡ እንዲህ ሲባል ግን የሥላሴ አካል አንደ ሰው አካል ውሱን፣ ግዙፍ፣ ጠባብ አይደለም፡፡ ምሉዕ፣ ስፉሕ፣ ረቂቅ ነው እንጂ፡፡ ምሉዕነታቸውና ስፋታቸው እንዴት ነው? ቢሉ ከአርያም በላይ ቁመቱ፣ ከበርባኖስ በታች መሠረቱ፣ ከአድማስ እስከ አድማስ ስፋቱ ተብሎ አይነገርም፣ አይመረመርም፡፡ ምክንያቱም ሥላሴ ዓለሙን ይወስኑታል እንጂ ዓለሙ ሥላሴን አይወስናቸውምና፡፡
ርቀታቸውስ እንዴት ነው? ቢሉ ከሁሉ ነፋስ ይረቃል፡፡ ከነፋስ መላእክት ይረቃሉ፡፡ ከነፍሳትና ከመላእክት ደግሞ ኅሊናቸው ይረቃል፡፡ ይህ የኅሊናቸው ርቀት በሥላሴ ዘንድ እንደ አምባ እንደ ተራራ ነው፡፡ በዚህም ርቀታቸው በፍጥረት ሁሉ ምሉዓን፣ ኅዱራን ናቸው፡፡ ባሕርያቸውም የማይራብ፣ የማይጠማ፣ የማይደክም፣ የማይታመም፣ የማይሞት ሕያው ነው፡፡ «ስምከ ሕያው ዘኢይመውት ትጉህ ዘኢይዴቅስ ፈጣሪ ዘኢይደክም» እንዳለ /ቅዲስ ባስልዮስ በማክሰኞ ሊጦን/፡፡
መ/ የኩነት /የሁኔታ/ ሦስትነት
ኩነት በህልውና /በአኗኗር/ እያገናዘቡ በአንድ መለኮት የነበሩ፣ ያሉ፣ የሚኖሩ ናቸው፡፡ እነርሱም፡-
1. ልብነት፡- በአብ መሠረትነት ለራሱ ለባዊ /አዋቂ/ ሆኖ ለወልድ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ልብ፣ ዕውቀት መሆን ነው፡፡
2. ቃልነት፡- በአብ መሠረትነት ለራሱ ነባቢ /ቃል/ ሆኖ ለአብ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ቃል መሆን ነው፡፡
3. እስትንፋስነት፡- በአብ መሠረትነት ለራሱ ሕያው ሆኖ ለአብ፣ ለወልድ ሕይወት መሆን ነው፡፡
ስለዚህ በአብ ልብነት ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸው ያስቡበታል፤ በወልድ ቃልነት አብ፣ መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸው ይናገሩበታል፤ በመንፈስ ቅዱስ አስትንፋስነት አብ፣ ወልድ ህልዋን ናቸው ሕያዋን ሆነው ይኖሩበታል፡፡
ታላቁ ሐዋርያ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ 1ዐ-17 ላይ «እምነት ከመስማት ነው፣ መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል ነው» ብሎ እንደተናገረው ከላይ የተጠቀሱትን መጠነኛ ማስረጃዎች በሙሉ ለመገንዘብ እንዲቻል የእግዚአብሔር እስትንፋስ የሆኑትን የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎችን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ሥላሴ የሚለው ስም እንዲያው የመጣ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በአንድነቱና በሦስትነቱ የሚጠራበት የከበረና ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም ነው፡፡ ለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ /ዐሥራው ቅዱሳት መጻሕፍት/ ማስረጃዎችን በዝርዝር እንመለከታለን፡፡
ምስጢረ ሥላሴ በብሉይ ኪዳን
1. እግዚአብሔርም አለ፡- «ሰውን በመልካችን እንደምሳሌአችን እንፍጠር» ዘፍ.1-26 እዚህ ላይ «እግዚአብሔርም አለ» ሲል አንድነቱ፣ «እንፍጠር» ሲል ከአንድ በላይ መሆኑን ግሱ /ቃሉ/ ያመለክታል፡፡ ሦስት መሆኑን ግን በዚህ ቃለ አልወሰነም፡፡
2. እግዚአብሔር አምላክ አለ፡- «እነሆ አዳም መልካሙንና ክፉውን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ» ዘፍ.3-22 በማለት ባለቤቱን አንቀጽን አንድ፣ አሳቡን ዝርዝሩን የብዙ አድርጐ ይናገራል፡፡ «እግዚአብሔር አለ » ሲል አንድነቱን፣ «ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ» ሲል ደግሞ ከአንድ በላይ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በዚህ ቃል ግን ሦስትነቱን አልወሰነም፡፡
3. እግዚአብሔርም አለ፡- «ኑ እንውረድ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው፡፡» ዘፍ.11.6-8፡፡ «እግዚአብሔር አለ» ብሎ አንድነቱ፣ «ኑ እንውረድ» ብሎ ደግሞ ከአንድ በላይ መሆኑን ያመለክታል፡፡
4. «በቀትርም ጊዜ እግዚአብሔር ለአብርሃም ተገለጠለት አብርሃም ሦስት ሰዎችን በፊቱ ቆመው አየ» ዘፍ.18.1-15 በማለት እግዚአብሔር አንድ መሆኑንና ሦስት አካል ያለው መሆኑን ወስኖ ያስረዳናል፡፡
5. «እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር ነኝ» ዘጸ.3-6 ሲል «አምላክ፣ አምላክ፣ አምላክ» ብሎ ሦስትነቱን፣ «እኔ እግዚአብሔር ነኝ» ብሎ ደግሞ አንድነቱን ገልጾ ተናግሯል፡፡
6. «የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች፣ በእግዚአበሔርም ቃል ሰማዮች ጸኑ፣ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ» መዝ.32-6፡፡
7. ነቢዩ ኢሳይያስም «ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በልዑል ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ አየሁት... ሱራፌልም ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያሉ ይጨሁ ነበር፡፡» ኢሳ.6.1-8 በማለት ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ብሎ ሦስትነቱን፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአበሔር ብሎ ደግሞ አንድነቱን አይቶ መስክሯል፡፡
ምስጢረ ሥላሴ በሐዲስ ኪዳን
በአዲስ ኪዳንም የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት /ምስጢረ ሥላሴ/ በምስጢረ ሥጋዌ በሚገባ ታውቋል፡፡ ይኸውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ /ሰው ሆኖ/ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ፣ አብ በደመና ሆኖ «የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚላችሁን ስሙት» ሲል፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በራሱ ላይ በርግብ አምሳል ሲወድቅበት ታይቶአል፡፡ /ማቴ.3.16-17፣ ማር.1.9-11፣ ሉቃ.3.21-22፣ ሉቃ.1.32-34/ በዚህም እግዚአብሔር በአካል ሦስት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤልም እመቤታችንን ባበሠራት ጊዜ «መንፈስ ቅዱስ በአንች ላይ ይመጣለ፣ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንች የሚለደው ቅዱሱ የአግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡» ብሎ የሥላሴን ሦስትነት በግልጽ ተናግሯል፡፡ሉቃ.1-35፡፡
እራሱ ባለቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የማዳን ሥራውን ፈጽሞ ከማረጉ በፊት ለደቀመዛሙርቱ ቋሚ ትዕዛዝ ሲሰጥ «እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ... ደቀመዛሙርት አድርጓቸው» ብሏል ማቴ.28.19-20፡፡
«ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፡፡» ብሏል ዮሐ.15.26፣ 14.16-17፣ 25-26፡፡
ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ የሥላሴን ሦስትነት ገልጾ ተናግሮአል፡፡ «የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔርም ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን» 2ኛ ቆሮ.13-14፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በጻፈው መልእክቱ «በሰማይ የሚመሰክሩ ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም አብ፣ ልጁም፣ መንፈስ ቅዱስም ናቸው፡፡ 1ኛ.ዮሐ.5-7፡፡ እነዚህ ሦስቱም አንድ ናቸው፡፡» በማለት የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት በግልጽ ያስረዳናል፡፡ /ይህንን ቃለ በ1886 ዓ.ም ከታተመው የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ እትም ይመልከቱ/፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የኪንግ ጀምስ የእንግሊዝኛውን መጽሐፍ ቅዱስ እትም ብንመለከት ይህነን አማናዊ የሥላሴን ምስጢር በትክክል ይመሰክራል/፡፡
ወንጌላዊው ቅድስ ዮሐንስም «በራእዩ እነሆም በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፣ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱም ስም የመንፈስ ቅዱስም ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ» ራእ.14-1፡፡ በማለት በገጸ-ልቡናቸው ስመ ወላዲ፣ ስመ ሠራፂ የተጻፈባቸውን የሥላሴን ልጆች አይቷል፡፡ በዚህም የሥላሴን ልዩ ሦስትነት በግልጽ መስክሯል፡፡
ከላይ በዝርዝር የተገለጹትና እነዚህን የመሳሰሉት ሁሉ እግዚአብሔር አንድነቱንና ሦስትነቱን የገለጸባቸው ምስክሮች ናቸው፡፡
የምስጢረ ሥላሴ ትምህርት/ምስክርነት በሊቃውንት


ምስጢረ ሥላሴ በሊቃውንትም ትምህርት የአብ መላዲነት፣ የወልድ ተወላዲነትና የመንፈስ ቅዱስ ሠራፂነት ነው፡፡ አብ ተወላዲ አይባልም፣ ወልድ ወላዲ አይባልም፡፡ ወላዲ፣ ተወላዲ፣ ሠራፂ የሚባሉት ቃላት ሦስት አካላት ለየብቻ የሚታወቁባቸው የግብር ስሞች ናቸው፡፡ ሊቃውንት አባቶቻችን በሃይማኖተ አበው ምሳሌ ሲመስሉ ምሳሌ ሠይሐጽጽ /ጎደሎ ምሳሌ/ በማለት አንዳንድ ምሳሌዎችን ያቀርባሉ፡፡ ምሳሌውንም ጎደሎ የሚሉበት ምክንያት ለምስጢረ ሥላሴ ሙሉ በሙሉ ምሳሌ የሚሆን ሲያጡ ነው፡፡ ይህንንም የሥላሴን ሦስትነትና አንድነት ሐዋርያት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በተማሩት መሠረት በሚከተሉት ሦስት ምስሌዎች በሚገባ ገልጸውታል፡፡

የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በነፋስ፣ በፀሐይ፣ በአሳት ይመሰላል፡፡
1. የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በሰው ምሳሌ ይገለጻል፡፡ ሰው በነፍሱ ሦስትነት አለውና ነው፡፡ የኸውም ልብነት፣ ቃልነት፣ ሕይወትነት ነው፡፡

ስለዚህ በሰው ነፍስ፡- በልብነቷ አብ፣ በቃልነቷ ወልድ፣ በሕይወትነቷ መንፈስ ቅዱስ ይመስላሉ፡፡ የነፍስ ልብነቷ፣ ቃልነቷን፣ ሕይወትነቷን ከራሷ ታስገኛለችና፡፡ ቃልና ሕይወት ከአንዷ ልብ ስለተገኙ በከዊን /በመሆን/ ልዩ እንደሆኑ በመናገርም ይለያሉ፡፡ እንዲሁም አብ ወልድን በቃል አምሳል ወለደው፣ መንፈስ ቅዱስንም በእስትንፋስ አንጻር አሰረጸው፡፡ ነፋስ ስትገኝ በሦስትነቷ በአንድ ጊዜ ተገኘች አንዷ ልብነቷ ቀድሞ ቃልነቷና እስትንፋስነቷ በኋላ አልተገኙም፡፡ ሰው በዚህ አኳኋን በነፍሱ የሚመስለው ስለሆነ እግዚአብሔር «ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር» ዘፍ.1-26 ብሎ ተናገረ፡፡ ስለዚህ ነፍስ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ /ሕይወት/ መሆን የከዊን /የመሆን/ ሦስትነትን ነገር በተናገረበት ድርሳን እንዲህ አለ፡፡
«አምላክ ውእቱ አብ፣ ወአምላክ ውእቱ ወልድ፣ በአምላክ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ወኢትበሀሉ ሠለስተ አማልእክተ አላ አሐዱ አምላክ ብሏል፡፡ ይህም ማለት አብ አምላክ ነው፣ ወልድም አምላክ ነው፣ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው ነገር ግን ሦስቱ አማልክት አይባሉም፣ አንድ አምላክ እንጂ፡፡» ማለት ነው፡፡
ሥላሴ በፀሐይ ይመሰላሉ፣ ፀሐይ አንድ ሲሆን ሦስትነት አለው፡፡ ይኼውም ክበቡ ብርሃኑ፣ ሙቀቱ ነው፡፡ ክበቡ አብ፣ ብርሃኑ ወልድ፣ ሙቀቱ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ፡፡ «አብ ፀሐይ፣ ወልድ ፀሐይ፣ መንፈስ ቅዱስ ፀሐይ አሐዱ ውእቱ ፀሐየ ጽድቅ ዘላዕለ ኩሉ» እንዳለ /ቅዱስ አባ ሕርያቆስ/፡፡
ሥላሴ በእሳት ይመሰላሉ፡፡ እሳት አንድ ሲሆን ሦስትነት አለው፡፡ ይኼውም አካሉ፣ ብርሃኑ፣ ዋዕዩ /ሙቀቱ/ ነው፡፡ በአካሉ አብ፣ በብርሃኑ ወልድ፣ በዋዕዩ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ፡፡ «አብ እሳት ወልድ እሳት ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ እሳተ ሕይወት ዘእምአርያም፡፡» እንዳለ /አባ ሕርያቆስ/ «አምላክህ እግዚአብሔር የሚባላ እሳት ቀናተኛም አምላክ ነው፡፡» ዘዲ. 4-24፡፡
ሥላሴ በፀሐይና በእሳት መመሰላቸውንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ለሐዋርያት «እኔና አባቴ መንፈስ ቅዱስም እሳትና ነበልባል ፍሕምም ነን» በማለት አስተምሮአቸዋል፡፡ ሐዋርያትም ይህንን ጽፈውት ቀሌመንጦስ በተባለው መጽሐፍ ይገኛል፡፡ /ቅዳሴ ሠለስቱ ምእትን/ ይመልከቱ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ አንድ ነፍስ፣ አንድ ፀሐይ፣ አንድ እሳት፣ እንጂ ሦስት ነፍስ፣ ሦስት እሳት፣ ሦስት ፀሐይ አይባሉም፡፡ ሥላሴም በአካል፣ በስም፣ በግብር ሦስት ቢባሉ በባሕርይ፣ በሕልውና፣ በፈቃድ፣ በመለኮት አንድ ናቸው አንጂ እማልክት አይባሉም፡፡ የቂሣርያው ሊጳጳስ ቅዱስ ባስልዮስ «እንዘ አሐዱ ሠለስቱ ወእንዘ ሠለስቱ አሐዱ ይሤለሱ በአካላት ወይትዋሐዱ በመለኮት» እንዳለ፡፡ ይህም ማለት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆኑ ሦስት ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸው፡፡ በአካል ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ናቸው፡፡ ማለት ነው፡፡ ይህም ሰው በሚረዳው መጠን ለመግለጽ ያህል ነው እንጂ ከፍጥረት ወገን ለሥላሴ የሚሆን በቂ ምሳሌ የለም፡፡ የተመሰለ ቢመስል ሕጸጽ /ጎደሎ/ ምሳሌ ነው፡፡


ወስብሐት ለእግዚአብሔር




Source : http://eotc-mkidusan.org/

7 comments:

  1. ቃለሕይዎት ያሰማልን

    ReplyDelete
    Replies
    1. ተዋህዶ-ሀይማኖታችን: ምስጢረ ሥላሴ >>>>> Download Now

      >>>>> Download Full

      ተዋህዶ-ሀይማኖታችን: ምስጢረ ሥላሴ >>>>> Download LINK

      >>>>> Download Now

      ተዋህዶ-ሀይማኖታችን: ምስጢረ ሥላሴ >>>>> Download Full

      >>>>> Download LINK oO

      Delete
  2. ቃለ ህይወትን ያሰማልን ሌላም ሌላም ማወቅ እፈለጋለሁ ካላስቸገርኳችሁ ምክንያቱም በግ የሚመስሉ ተኩላዎች በዝተዋልና ጥንቁቅ በግ መሆን ያስፈልጋል

    ReplyDelete
  3. ያ ነው ኢትዮጵያዊነት!

    ReplyDelete
  4. ቃለ ሂወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  5. ተዋህዶ-ሀይማኖታችን: ምስጢረ ሥላሴ >>>>> Download Now

    >>>>> Download Full

    ተዋህዶ-ሀይማኖታችን: ምስጢረ ሥላሴ >>>>> Download LINK

    >>>>> Download Now

    ተዋህዶ-ሀይማኖታችን: ምስጢረ ሥላሴ >>>>> Download Full

    >>>>> Download LINK

    ReplyDelete