Tuesday, July 9, 2013

ቅዱስ ቂርሎስ


ሐምሌ 3 ቀን ታላቁ የእስክንድርያ ዻዻስ ቅዱስ ቄርሎስ አረፈ

ቂርሎስ ማለት መኀቶት ማለት ነው ሀገሩ እስክንድርያ ነው ሊቀዻዻሳት ቴዎፍሎስ አጎቱ ነውና እያስተማረ አሳድጎታል የነገሩትን ቀለም ባንድ ጊዜ ይይዝ ነበር 5 ዓመት ውስጥ ብሉይ ሐዲስን አጥንቷል ሥርዓተ ምንኩስናን አባ ሰራብዮን ተምሯል ::

ከቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ ልደት 378 . እስከ ዕረፍቱ 444 . ድረስ ያሉት ዓመታት 66 ይሆናሉ :: እነዚህ ጊዜያት የቅዱስ ማርቆስ መንበረዽዽስና ዘመን በዓለም ላይ በገናናነቱ ጫፍ ላይ የደረሰበት ነበር :: ሁለት ዋና ዋና ክስተቶች ዘመኑን ይገልጹታል :: 385 ዓም የቅዱስ ቄርሎስ አጎት ቴዎፍሎስ ወደ መንበረ ዽዽስና ሥልጣን መምጣቱና 411 . የቅዱስ ቄርሎስ ቴዎፍሎስን ተክቶ ወደ መንበረ ዽዽስናው መምጣት ናቸው ::

በእነዚህ ጊዜያት በእስክንድርያ የፓትርያርክነት ሥልጣን /ሥራ ቀላል አልነበረም ሃይማኖታዊ የሆነ ነገር በብዙ አደጋዎች መካከል ተከቦ ነበር :: ይኽ መንበር ጠንካራ የነበሩ ቅዱስ ቄርሎስ እና ቅዱስ ቴዎፍሎስ የመሩት ባይሆን ኖሮ ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖት ህልውናው አጠያያቂ ደረጃ ላይ በደረሰ ነበር :: ፈቃደ እግዚአብሔር እነዚህን አባቶች አስነሣ ::

አባ ቂርሎስ መናፍቁ ንስጥሮስን ተከራክሮ የረታ ድንቅ አባት ነው፤ ቀድሞ ንስጥሮ የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ ነበር፤ይህ ጳጳስ ሳተ ተሳሳተ አሳሳተ እመቤታችን ወላዲተ አምላክን ወላዲተ ሰብ እንጂ ወላዲተ አምላክ አይደለችም አለ፤ ለዚህም ጉባዬ በኤፌሶን ከተማ ተደረገ፤የወቅቱ ንጉስ ቴዎዶስዮስ ነበር፤ የተሰበሰቡት ሊቃውንት ደግሞ 200 ናቸው ሊቀ መንበሩ ቂርሎስ ነው፤ ክርክሩ ተጀመረ፤ አባ ቂርሎስ እንደ ሰይፍ የሚቆራርጡ ቃላትን ከመጽሐፍ ቅዱስ እያጣቀሰ መወርወር ጀመረ፤ ንስጥሮስ የሚመልሰው አጣ ተረታ፤ ወደ ቀደሞ ሃይማኖትህ ተመለስ አሉት አልመለስም ብሎ ወደ ላይላይ ግብጽ ይሰደዳል፤ ቂርሎስ መልካም ባልንጀራው ነበርና ተከትሎት ሄዶ ይመክረዋል ወንድሜ ንስጥሮስ የያዝከው መንገድ ስህተት ነው፤እመቤታችንን ወላዲተ አምላክ ነች ልጇም የባህርይ አምላክ ነው በል ይለዋል፤ አልልም ብሎ ይመልስለታል፤ እንግዲያውስ ለኔ እንዳልታዘዘክ አንደበትህ አይታዘዝህ ብሎ ይረግመዋል ወዲያውኑ ምላሱ ተጎልጉሎ ወጣ ደምና መግል እየተፋ ተቀብዝብዞ ሞቷል።

ዐይነ ስውሩ ዲዲሞስና ቄርሎስ ኑፋቄን በመከላከል ብዙ ጊዜ አሳልፈዋል :: ቄርሎስ የንስጥሮስን ሃይማኖታዊ ውዝግብ ተቃውሞ እስከ ደም ማፍሰስ የሚያደርስ ትግል አድርጉአል ምክንያቱም ዻዻስ እንደመሆኑ የነበረበት የእረኝነት ሐላፊነት ዕረፍት ስለሚነሣው ነበር ::  "በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።" (የሐዋ.ሥራ 20:28)

በአጠቃላይ ሕይወቱ በተጋድሎ ያሳለፈ እንደ ቅዱስ ዻውሎስ ምርጥ ዕቃ አድርጎ ጌታችን የሾመው ለተሾመበትም ኃላፊነት ታምኖ የተገኘ ጽድቅን የወጠነ የጀመረ የፈጸመ ተወዳጅ የቤተክርስትያን አባት ነበር ተጋድሎውን ፈፅሞ 444 ዓም 
ሐምሌ 3 ቀን ከአባቶቹ ጋር በሰላም አንቀላፋ ጸሎቱ በረከቱ አማላጅነቱ ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን
::
 

No comments:

Post a Comment