Tuesday, December 4, 2012

ዶግማ እና ቀኖና

ትምህርት ሃይማኖት (የሃይማኖት ትምህርት) በሁለት ይከፈላል፡፡ ይኸውም፦

1ኛ፡- ዶግማ   2ኛ፡- ቀኖና በሚል ነው፡፡

ዶግማ
፡- ቃሉ የግሪክ ሲሆን ፍችውም እምነት ማለት ነው፡፡
ቀኖና፡- ደግሞ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ሥርዓት ማለት ነው፡፡ ከእነዚህ ከሁለቱ ዶግማ ወይም እምነት አይጨመርበትም፤ አይቀነስበትም፤ አይሻሻልም፤ ችግርና ፈተናም ቢመጣ እስከ ሞት ድረስ አጥብቀን የምንይዘው ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረ፤ ቢመረምር እንጂ የማይመረመር ሁሉን ቻይ አምላክ፤ የሚሳነው ነገር የሌለ ፈጣሪ፤ የሰማይና የምድር ባለቤት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔር ነው፡፡
እግዚአብሔር (ፈጣሪ) የአካል ሦስትነት አለው፡፡ በመለኮት፣ በመፍጠር፣ በሥልጣን፣ በአገዛዝ፣ በፈቃድ ግን አንድ ነው፡፡ በሦስትነቱ አብ፤ ወልድ፤ መንፈስ ቅዱስ ሲባል በአንድነቱ አንድ መለኮት አንድ እግዚአብሔር ይባላል፡፡ በአዳም ምክንያት ከመጣው የዘለዓለም ሞትና ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ የወጣነው ከሦስቱ አካላት በአንደኛው አካል ማለትም በወልድ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህ ዶግማ ወይም እምነት ይባላል፡፡
ቀኖና ግን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ያደጉ ክርስቲያኖች የሚመሩበት ሥርዓት ስለሆነ፤ በሃይማኖት አባቶች ወይም በቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት እንደጊዜው ሁኔታ የሚሻሻል በመሆኑ የሚጨመርበት፤ የሚቀነስለት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል እኛ ኦርቶዶክሳውያን የምንጠመቀው ሴት በሰማንያ ወንድ በአርባ ቀናችን ነው፡፡ የተወለዱ ሕጻናት ሴቷ ሰማንያ ወንዱም አርባ ቀን ሳይሞላቸው ቢታመሙና በሽታው አስጊ ከሆነ በ10፣ በ20፣ በ30…ቀናቸው መጠመቅ ይችላሉ ቀኖና ነውና፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን የቀዳስያን ብዛት መነሻው አምስት ነው፡፡ ምናልባት ከአምስቱ አንዱ፤ ሁለቱ፤ ሦስቱ ቢታጡና ሌላም ተፈልጎ እስከ መጨረሻ የማይገኝ ከሆነ ከአቅም በላይም የሆነ ችግር ከገጠመ ሁለቱ ወይም አንዱ ብቻ ቀድሰው ማቁረብ ይችላሉ፡፡ ቀኖና ነውና፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ታቦት ሲከብር ቤተ ክርስቲያኑን የሚዞረው ሦስት ጊዜ ነው ችግር ካለ አንድ ጊዜ ብቻ ዑደት ተፈጽሞ ሊገባ ይችላል። ቀኖና ነውና፤ ስለቀኖና (ስለሥርዐት) ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ እንዲህ ሲል ጽፏል። 

1. ‹‹ነገር ግን ሁሉን በአግባብና በሥርዐት አድርጉ፡፡›› 1ኛ ቆሮ. 14፥40፡፡
2. ‹‹ወንድሞች ሆይ በሠራንላቸው ሥርዐት ሳይሆን በተንኮል ከሚሄዱት ወንድሞች ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዝዛችኋለን፡፡ እኛን ልትመስሉ እንደሚገባችሁ እኛም በእናንተ መካከል ያለ ሥራ እንዳልኖርን ራሳችሁ ታውቃላችሁ›› 2ኛተሰ. 3፥6-7›› ቀኖና (ሥርዐት) የሚወሰነው በሃይማኖት አባቶች እንደሆነና ወንጌልን የሚስተምር ሰው ለሚያስተምራቸው ክርስቲያኖች በሃይማኖት አባቶች የተወሰነ ቀኖና ማስተማርና መሰጠት እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ያስረዳል፡፡

በየከተማውም ሲሄዱ፥ ሐዋርያትና ቀሳውስት በኢየሩሳሌም ያዘዙትን /የወሰኑትን/ ሥርዐት አስተማሯቸው፡፡ አብያተ ክርስቲያናትም በሃይማኖት ጸኑ ዕለት ዕለትም ቁጥራቸው ይበዛ ነበር፡፡›› ይላል የሐዋ. 16፥4-5፡፡ በዚህ የእግዚአብሔር ቃል መሠረት ቅዱስ ጳውሎስ ደርቤንና ልስጥራን በተባሉ ቦታዎች ለነበሩ ክርስቲያኖች ወንጌልን ከሰበከ በኋላ ሐዋርያት የወሰኑትን ቀኖና (ሥርዐት) እነደሰጣቸው እንረዳለን፡፡ ስለዚህ ቀኖና ወይም ሥርዐት ቤተክርስቲያንን ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ በመሆኑም ዶግማንና ቀኖናን ወይም እምነትንና ሥርዓትን ጎን ለጎን ይዞ መጓዝ ሐዋርያትን መከተል
ነው፡፡ እንግዲህ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን የሚቃወሙ ሰዎች ሁሉ፤ የሚቃወሙት በቀኖና (በሥርዐት) የሚመሩትን ክርስቲያኖች ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል የሆነ መጽሐፍ ቅዱስን በመሆኑ እንዳይሳሳቱ አደራ እንላለን፡፡

1 comment: