በቤተክርስቲያን አስተምህሮ ብስራተ ገብርኤል ይባላል፤ ይህም ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ጌታን እንደምትወልድ ብስራቱን የነገረበት ቀን ነው፤ እንዴት ብስራቱንማ የነገራት መጋቢት 29 ቀን ካሉ ትክክል ነው፤ ብስራቱን የነገራት መጋቢት 29 ቀን በዕለተ እሁድ ከቀኑ ሦስት ሰዓት ላይ ነው፡ ታዲያ ዛሬ ለምን እናከብረዋለን ካሉ ምክንያቱ እንዲህ ነው፤ ምንግዜም ወርሃ መጋቢት ታላቁ ዓቢይ ጾም የሚውልበት ወር ነው በዚህ በዓቢይ ጾም ደግሞ ሐዘን፤ ለቅሶ፤ ጾም፤ ጸሎት እንጂ ደስታ፤ ፌሽታ እልልታ፤ ጭብጨባ የለም ፍጹም የሐዘን ወራት ነው ታቦት አውጥቶ በዓል ማክበርም ስህተት ነው ፍትሃ ነገስት አንድምታ አንቀጽ 15 ተመልከት ፤ ታዲያ ቅዱሳን አባቶቻችን እንደዚህ ዓይነት ስርዓት ሰሩ የመጋቢት 27 ስቅለቱን ጥቅምት 27 ቀን እንዲሁም የመጋቢት 5 አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ እረፍት ቀን ወደ ጥቅምት 5 ቀን ዞሮ እንዲከበር አደረጉ፡፡ የመጋቢት 29 ብስራቱን ደግሞ ታህሳስ 22 ቀን ዞሮ እንዲከበር ያደረገው ታላቁ አባት የጥልጥልያ ኤጲስ ቆጶስ ደቅስዮስ ይባላል በእመቤታች ፍቅር ልቡ የነደደ ታላቅ ጻድቅ ነው የእመቤታችንን ታአምራቷን የሚናገር መጽሐፍ የሰበሰበ አባት ነው፡፡ የጌታን ልደት ከመከበሩ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ብስራቱ መከበር አለበት ብሎ ስርዓት ሰራ አገሬውንም ሰብስቦ ታላቅ የደስታ በዓል አደረገ እመቤታችን ተገለጸችለት ወዳጄ ደቅስዮስ ባንተ ደስ አለኝ እንዳከበርከኝ እኔም አከብርሃለው አለችው ሰማያዊ ልብስና ሰማያዊ ወንበር ሰጠችው ይህችን ልብስ ካንተ ሌላ ማንም አይለብሳትም ይህችንም ወንበር ካንተ ሌላ ማንም አይቀመጥባትም አለችው፡ የዚህ ታላቅ አባት እረፍቱ ታህሳስ 22 በዛሬዋ ቀን ነው፡ ከእርሱ በኃላ ሌላ ኤጲስ ቆጶስ ተሾመ ልብሱን እለብሳለው በወንበሩም እቀመጣለው አለ ተው ይቅርብህ እመቤታችን እንዲህ ብላ ተናግራለች ይሉታል እርሱም ሰው እኔም ሰው እርሱም ኤጲስ ቆጶስ እኔም ኤጲስ ቆጶስ ብሎ በትዕቢት ልብሱን ለበሰው በወንበሩም ተቀመጠ ክፉኛ አወዳደቅ ወደቀ ሞተም ይህን ያዩ እመቤታችንን በጣም ፈሯት ይላል ተአምረ ማርያምን ተመልከት፡፡ ደቅስዮስ ሰርቶልን ያለፈውን ስርዓት ቤተክርስቲያን ተቀብላ ይኸው ዛሬም ድረስ ታከብረዋለች በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ብስራተ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፡፡ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡፡
No comments:
Post a Comment