Tuesday, January 1, 2013

ታህሳስ 23



በዚህች ቀን በእስራኤል ያይደለ ለእስራኤል የነገሰው ልበ አምላክ ዳዊት አረፈ፤ ለመሆኑ ዳዊት እንዴት ተወለደ ቢሉ ታሪኩ እንዲህ ነው፤- አባቱ እሴይ እናቱ ሀብሊ ይባላሉ፤ ጎረቤታቸው አንድ ወጠምሻ ጎረምሳ ነበር ሀብሊን ስትወጣ ባቷን ስትገባ ደረቷን ይመለከታት ነበር የዳዊት አባት ይህን ተመልክቶ ጠረጠረ መንገድ ልሄድ ነውና ስንቅ ሰንቂሊኝ አላት አዘጋጅታ ሰጠችው ደህና ሰንብቱ ብሎ ወጣ፤ሌሊት ተመልሶ መጣ ጎረምሳውን መስሎ ከሚስቱ ጋር አደረ አሷ አላወቀችም ጎረምሳው ነው የመሰላት፤ በዚያች ሌሊት ግንኙነታቸው ዳዊት ተጸነሰ ሚያዚያ 6 አባቱ እሴይን መስሎ ተወለደ፤ ለዚህም ነው ዳዊት በመዝሙር 51 ፤ 5 ላይ "እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ።" ብሎ የተናገረው። ቅዱስ ዳዊት ጥቅምት 12 ቀን ነብዩ ሳሙኤል ቀብቶ ሲያነግሰው ሰባት ሀብታት ተሰጥተውታል፤ ምንምን ናቸው ቢሉ ሀብተ መንግስት፤ ሀብተ ክህነት፤ሀብተ ኃይል፤ሀብተ በገና፤ሀብተ ፈውስ፤ ሀብተ ትንቢት እና ሀብተ መዊዕ ( የማሸነፍ ድል የማድረግ) ናቸው። አንበሳ በእርግጫ ነብርን በጡጫ ይገድል ነበር 1ሳሙ 17፤34 ሀብተ ፈውስ ያለው በገና ሲደረድር እርኩሳን አጋንንት ይርቁ ነበር በሽተኞችም ይፈወሱ ነበር፤ እግዚያብሔር እንደ ልቤ የሚሆን የእሴይ ልጅ ዳዊትን አገኘሁ ብሎ መስክሮለታል፤ ደግሞም ሰው ነውና ከኦርዮን ሚስት ከቤርሳቤህ ጋር በዝሙት ወድቋል፤ ኦርዮንንም አስገድሏል፤ በዚህም ተጸጸቶ እንባው ሳር እስኪያበቅል አንሶላውን እስኪያርስ ድረስ አልቅሷል፤ እግዚያብሔርም ይቅር ብሎታል። ቅዱስ ዳዊት የደረሰው 150 መዝሙረ ዳዊት የማይዳስሰው ነገር የለም ለዚህም ነው ቤተክርስቲያን በሁሉም አገልግሎቶች የምትጠቀምበት፤ እግዚያብሔር በጣም የሚወደው ጸሎት ዳዊትንና አቡነ ዘበሰማያትን ነው፤ እመቤታችን ደግሞ በጣም የምትወደው ጸሎት ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያምን ነው። ቅዱስ ዳዊት 40 ዓመት ነግሶ ታህሳስ 23 በዛሬዋ ቀን አርፏል። በረከቱ ይደርብን ከቅዱስ ጊዮርጊስም በረከት ያሳትፈን።


No comments:

Post a Comment