Showing posts with label በእንተ ቅዱሳን. Show all posts
Showing posts with label በእንተ ቅዱሳን. Show all posts

Monday, September 18, 2023

መስከረም 7

 

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን


መስከረም 7-የብርሃን እናቱ የሆነች ድንግል ወላዲተ አምላክን የወለደቻት ቅድስት ሐና ልደቷ ነው፡፡

+ በ451 ዓ.ም በጉባዔ ኬልቄዶን ላይ ተገኝቶ ልዮንን የረታውና ያወገዘው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በዓለ ልደቱና ዕረፍቱ ነው፡፡

+ በአካል መሄድ ሳያስፈልጋቸው ደብዳቤ በመጻፍ ብቻ በንጉሡ ልጅ ላይ ያደረውን ሰይጣን ያስወጡትና በሀገርም ላይ የመጣውን የጠላትን ጦር በመርታት ድል ያደርጉ የነበሩት አቡነ ሳዊርያኖስ ዕረፍታቸው ነው፡፡




+ ቅድስት ራፊቃ እና 4 ልጆቿ ቁልቁል ተሰቅለውና አንገታቸውን በመሰየፍ ሰማዕትነታቸውን በድል ፈጸሙ፡፡

+ ዳግመኛም በዚኽች ዕለት ከቅዱስ ፋሲለደስ ጋር ማኅበርተኞቹ የሆኑ ሁለት ሺህ ሰባት ሰዎችም በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ የመጥምቁ ዮሐንስ እናት የቅድስት ኤልሳቤጥም የመታሰቢያዋ በዓል ነው፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡

+ + + + + 


ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ፡- ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት 25ኛው ነው፡፡ ስለ ቀናች ሃይማኖት ታላቅ ተጋድሎን ከፈጸመ በኋላ በተሰደደበት በደሴተ ጋግራ መስክረም 7 ቀን ዐርፏል፡፡ ንጉሡ መርቅያኖስ በጠራው ጉባዔ በጠሩት ጊዜ በቦታው ሲገኝ 636 ጉባኤተኞች ተሰብስበው ደረሰ፡፡ ‹‹ምን ጉድለት ተገኝቶ ነው ይህ ሁሉ የተጠራው?›› ሲላቸው ‹‹በንጉሡ ትእዛዝ ተጠርተን ነው›› አሉት፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም ‹‹ይህ ጉባኤ ስለ ጌታችን ክብር ቢሆን ኖሮ እኔ ተቀምጨ እግዚአብሔር በሰጠኝ በአንደበቴ እናገር ነበር ነገር ግን የጉኤው መሰብሰብ በንጉሡ ትእዛዝ ከሆነ ንጉሡ እንዳሻው ይምራው›› አላቸው፡፡


ከዚህም በኋላ የክርስቶስን ባሕርይ ለሁለት የሚከፍለው የክህደትን ቃል በውስጡ የያዘውን የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ልዮን የላከውን ደብዳቤ ቀደደው፡፡ ለጉባኤውም ርትእት የሆነች ሃይማኖትን ገለጸ፡፡ የተዋሕዶንም ምሥጢር በነፍስና በሥጋ እንዲሁም በእሳትና ብረት እየመሰለ አስዳ፡፡ ጌታችን ሰው እንደመሆኑ ወደ ሠርግ ቤት ተጠርቶ ሄደ፣ አምላክ እንደመሆኑ ውኃውን ለውጦ ወይን አደረገው›› እያለም በብዙ ምሳሌዎች ሲያስረዳቸው ከጉባኤው ሊከራከረው የደፈረ ማንም አልነበረው፡፡ ነገር ግን ክፉዎች ጉባኤውን በከሃዲው በልዮን ምክር ወዳዘጋጀው ንጉሡ መርቅያንና ወደ ሚስቱ ንግሥት ብርክያል መልዕክት ልከው ከዲዮስቆሮስ በቀር እነርሱ ያዘዙትን ሃይማኖትንና ትእዛዝ የሚቃወም እንደሌለ በመናገር ነገር ሠሩበት፡፡ ነገር ግን በጉባኤው ውስጥ ንስጥሮስን ያወገዙ አባቶችም ነበሩበት፡፡

ንጉሡም ቅዱስ ዲዮስቆሮስን አስጠርቶት ከሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት ጋር እስከ ማታ ድረስ ሲከራከሩ ዋሉ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ እንዳልተመለሰላቸው ባዩ ጊዜ ንግሥቲቷና ንጉሡ በእርሱ ተቆጥተው ክፉኛ አስደበደቡት፡፡ ጽሕሙን ነጭተው ጥርሱንም አስወለቁት፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም የተነጨ ጽሕሙንና የወለቀ ጥርሱን ሰብስቦ ወደ እስክንድርያ በመላክ ‹‹እነሆ የቀናች ሃይማኖት ፍሬ ይህ ነው›› አላቸው፡፡ ለጉበኤው የተሰበሰቡ ኤጲስ ቆጶሳትም በቅዱስ ዲዮስቆሮስ ላይ የደረሰውን ዐይተው ፈሩና ከከሃዲው ንጉሥ መርቅያኖስ ጋር ተስማሙ፡፡ ክብር ይግባውና ‹‹ለክርስቶስ ሁለት የተለያዩ ባሕርያት አሉት›› ብለው በንጉሡ መዝገብ ላይ በእጆቻቸው ጽፈው ፈረሙ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም እነርሱ የጻፉለትን መዝገብ እንዲልኩለት ሲጠይቃቸው ላኩለት እርሱም ጽፎ የሚፈርምበት መስሎአቸው ነበርና፡፡ እርሱ ግን አባቶቻችን ሐዋርያት ካስተማሯት ከቀናች ሃይማኖት በኒቅያ የተሰበሰቡ ሃይማኖታቸው የቀና የ318 ኤጲስ ቆጶሳት አባቶቻችን ከሠሯት ሕግ የሚወጣውን ሁሉ በደብዳቤው ግርጌ ጽፎ አወገዘ፡፡

መናፍቁ ንጉሥም ይህን ጊዜ እጅግ ተናዶ ጋግራ ወደምትባል ደሴት እንዲያግዙት አዘዘ፡፡ የሀገረ ቃው ኤጲስ ቆጶስ አባ መቃርስ አብሮት ተሰደደ፡፡ ሌሎቹ ግን ሸሹ፡፡ ከዚህም በኋላ እነዚያ የካዱ 636 ኤጲስ ቆጶሳት ተቀምጠው በኬልቄዶን ለራሳቸው መመሪያ የሚሆናቸውን ሥርዓት ሠሩ፡፡ በጋግራ ደሴት ያለው ኤጲስ ቆጶስም ከንጉሡ ጋር የተባበረ ነበርና አቡነ ዲዮስቆሮስ ላይ ብዙ መከራ አደረሰበት፡፡ የደሴቱ ሰዎች ግን በቅዱስ ዲዮስቆሮስ እጅ የሚፈጸሙ ተአምራትን እያዩ እጅግ ያከብሩት ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ አባ መቃርስን ወደ እስክንድርያ ሄዶ ሰማዕት እንደሚሆን ትንቢት ነገረውና ከነጋዴዎች ጋር ላከው፡፡ እንደተናገረውም አባ መቃርስ በእስክንደርያ ሰማዕት ሆኖ ዐረፈ፡፡ አቡነ ዲዮስቆሮስ ግን በዚያቹ በጋግራ ደሴት ሰማዕትነቱን ፈጽሞ በክብር ዐርፏል፡፡ ምእመናንም ሥጋውን በዚያው አኖሩት፡፡ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡

+ + + + + 


አቡነ ሳዊርያኖስ፡- የግሪክ አቴናን ፍልስፍናና ጥበብ ጠንቅቀው የተማሩ ናቸው፡፡ ምግባር ሃይማኖታቸው የሰመረ፣ ትሩፋት ተጋድሏቸው የቀና ነው፡፡ ብሉይን ከሐዲስም አጠናቀው ተምረዋል፡፡ ወላጆቻቸው ያወረሷቸውን እጅግ የተትረፈረፈ ንብረት ሸጠውና ለጦም አዳሪዎች መጽውተው ለድኆች ማደሪያና ለእንግዶች ማሪፊያ ቤት ሠርተው ነዳያንን ይንከባከቡ ጀመር፡፡ ይህንንም የጽድቅ ሥራቸውን የሮሜው ጻድቁ ንጉሥ አኖሬዎስ ሲሰማ እጅግ ደስ ተደስቶ አስመጥቶ ከእርሱ ጋር በቤተ መንግሥቱ አማካሪና አባቱ አድርጎ አኖራቸው፡፡ ከንጉሡም ጋር አብረው ሁልጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ሌሊቱን በሙሉ ለጸሎት ቆመው ያድራሉ፡፡

ጻድቁ የገብላው አገር ንጉሥ ሴት ልጁን ሰይጣን ይዟት ሳለ ደብዳቤ በመጻፍ ልከው በልጅቷ ላይ ያደረውን ሰይጣን በደብዳቤአቸው ብቻ አስወጥተውታል፡፡ አቡነ ሳዊርያኖስ ደብዳቤ በመጻፍ ብቻ በሀገር ላይ የመጣ የጠላትንም ጦር እያሸበሩ ድል ያደርጉ ነበር፡፡ ይኸውም የቍስጥንጥንያው ንጉሥ አርቃዴዎስና አኖርዮስ በገብላ አገር ኤጲስቆጶስነት ከሾሟቸው በኋላ የፋርስ ሰዎች እነዚህን ደጋግ ነገሥታት ሊወጓቸው ሽተው በኃይል በመጡባቸው ጊዜ ወደ አባ ሳዊርያኖስ መልአክትን ላኩ፡፡ አባታችንም ለቅዱሳን ነገሥታቱ ‹‹እኛ የክርስቶስ ከሆንን መንግሥታችንም የክርስቶስ ነው፣ እንዲህም ከሆነ የጦር መሣርያ የጦር ሠራዊትም አንሻም…›› ብለው ደብዳቤ ጽፈው እንደላኩ ነገሥታቱ ያለ ምንም ጦርነት የፋርስን ሀገር ሰዎች አሸንፈው ወደ ሀገራቸው መልሰዋቸዋል፡፡


አቡነ ሳዊርያኖስ በገብላ አገር ኤጲስቆጶስነት ከተሾሙ በኋላ የሙሴን ሕግ በማወቁ የሚመካ አንድ ስሙ ስቅጣር የሚባል አይሁዳዊ ወደ እርሳቸው መጥቶ ተከራከራቸው፡፡ የጻድቁንም ቃላቸውን ሊሰማቸው አልቻለም ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ ጌታችን ለአቡነ ሳዊርያኖስ ተለጠላቸውና ‹‹እኔ ካከበርኳቸው ወገኖች ይሆናል›› በማለት እንደሚያምን ነገራቸው፡፡ ያም አይሁዳዊ ወደቤቱ በገባ ጊዜ ወገኖቹ አይሁድ ሲኦል ውስጥ ሆነው ሲሠቃዩ በራእይ ተመለከተ፡፡ ‹‹ከሃዲዎች ዘመዶችህን እነሆ እይ›› የሚል ድምንም ሰማ፡፡ በማግሥቱም ይህ አይሁዳዊ ወደ አቡነ ሳዊርያኖስ መጥቶ ከእግራቸው ሥር ወድቆ እንዲያስተምሩትና የክርስቶስ ወገን እንዲያደርጉት ለመናቸው፡፡ እርሳቸውም አስተምረው ከሀገሩ ሰዎች ጋር አንድ ላይ አጠመቋቸው፡፡ የቀሩት ብዙ አይሁድም በጌታችን አምነው ተጠመቁ፡፡ አቡነ ሳዊርያኖስ ሥራየኛ ጠንቋዮችን ሁሉ እያሳመኑ አስተምረው አስጠምቀዋቸዋል፡፡


አቡነ ሳዊርያኖስ ስለ ዮሐንስ አፈወርቅ ስደትና እንግልት ያለችበት ድረስ ሄደው ንግሥት አውዶክስያን ቢመክሯትና ቢገሥጹዋትም በክፋቷ ጸንታ አልሰማቸው ብትል ተመልሰው ወደ አገራቸው ሄደዋል፡፡ አቡነ ሳዊርያኖስ ተአምራታቸው ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በጣም ብዙ ድርሳናትን ደርሰዋል፡፡ 100 ዓመት በሆናቸው ጊዜ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ከ10 ቀን በኋላ በሞት እንደሚያርፉ ነገራቸው፡፡ ሕዝቡንም ጠርተው በሃይማኖት እንዲጸኑ ከመከሯቸውና ከተሰናበቷቸው በኋላ መስከረም 7 ቀን በሰላም ዐርፈዋል፡፡ ይኸውም ዕረፍታቸው የተከናወነው ኤጲፋንዮስ ባረፈ በ2ኛ ዓመቱ ዮሐንስ አፈወርቅ ባረፈ በዓመቱ ነው፡፡ ጌታችን የብርሃን ሰረገላ ሰጥቷቸዋል፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
+ + + + + 

ሰማዕታቱ ቅድስት ራፊቃ እና አራት ልጆቿ፡- ለቅድስት ራፊቃ እና ለአራት ልጆቿ ማለትም ለአጋቶን፣ ለጴጥሮስ፣ ለዮሐንስና ለአሞን ጌታችን ለሁሉም በራእይ ተገልጦላቸው በስሙ መስክረው ሰማዕት እንሚሆኑ ነገራቸው፡፡ አስቀድሞም ታላቁ አጋቶን በአገሩ ተሹሞ በሥልጣን ሆኖ ነበር፡፡ የጌታችንንም የሰማዕትነት ጥሪ ተቀብለው ከላይኛው ግብጽ ከቁስ አውራጃ ተነሥተው በከሃዲው መኮንን በዲዮናስዮስ ፊት ስለ ጌታችን አምላክነት መሰከሩ፡፡ መኮንኑም ብዙ ሥቃዮችን አደረሰባቸው፡፡ ጌታችንም በተአምራት ከመከራቸው ሲያድናቸው ያየ ብዙ ሰዎች ሲያምኑ መኮንኑ እጅግ ተቆጥቶ ጽኑ ሥቃይ አደረሰባቸው፡፡ ማሠቃየትም በሰለቸው ጊዜ ወደ እስክንድርያው ገዥ አርማንዮስ ዘንድ ላካቸው፡፡ ከሃዲው አርማንዮስም ሥጋቸውን ቆራርጦ በመንኮራኩር ውስጥ ጨመራቸው፡፡ ነገር ግን ጌታችን ጤነኛ አድርጎ ፈወሳቸው፡፡ ዳግመኛም ዘቅዝቀውም ሰቀሏቸው፡፡ አሁንም ጌታችን አዳናቸው፡፡ በተአምራተቸውም ብዙዎች በጌታችን አመኑ፡፡ በመጨረሻም ራሶቻቸውንም በሰይፍ ቆርጠው ሥጋቸውን ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ ቅድስት ራፊቃና አራት ልጆቿም ሰማዕትነታቸውን በዚሁ ፈጸሙ፡፡ የታዘዘ መልአክም መጥቶ ለአንዱ ባለጸጋ የቅዱሳኑን ሥጋ ያለበትን ነግሮት እንያወጣውና በክብር እንዲያስቀምጠው ነአዘዘው፡፡ ባለጸጋውም የቅዱሳኑን ሥጋቸውን ከባሕሩ አወጥቶ የመከራ ዘመን እስኪያልፍ በክብር አኖረው፡፡ ከሥጋቸውም ብዙ ተአምራት ተገልጠው ታዩ፡፡ የሰማዕታቱ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
+ + + + +

+ ዳግመኛም በዚኽች ዕለት እመቤታችን ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክን የወለደቻት ቅድስት ሐና ልደቷ ነው፡፡ ሐና ማለት ‹‹ጸጋ›› ማለት ነው፡፡ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እናት ናት፡፡ እርሷም ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት ልጁ ናት፡፡ የቅድስት ሐና አባት ማጣትና እናቷ ሄርሜላ ከእርሷ በተጨማሪ ሶፍያና ማርያም የሚባሉ ሌሎች ሁለት ሴት ልጆችን ወልደዋል፡፡ ቅድስት ሐና ከይሁዳ ነገድ የሆነውን ጻድቅ ኢያቄምን አግብታ ቅድስት ድንግል ማርያምን ወለደች፣ ድንግል ማርያምም መድኃኔዓለም ክርስቶስን ወለደች፡፡ ሶፍያ ኤልሳቤጥን ወለደች፣ ኤልሳቤጥም መጥምቁ ዮሐንስን ወለደች፡፡ ከሦስቱም ታናሽ የሆነችው ‹‹ማርያም›› የተባለችው የማጣትና የሄርሜላ ልጅ ደግሞ ሰሎሜን ወለደቻት፡፡
ይኽችም ታላቅ እናት ቅድስት ሐና አምላክን በድንግልና ሆና በሥጋ ለወለደችው ለቅድስት ድንግል ማርያም ወላጇ ትሆን ዘንድ የተገባት ሆናለችና ከሴቶች ሁሉ እንደምትበልጥና እንደምትከብር እንረዳ፡፡ ለዓለም ሁሉ ድኅነት የተደረገባትን ልዩ ስጦታ የሆነች ድንግል ማርያምን እርሷ አስገኘቻት፡፡ ለክብር ባለቤት ለጌታችን ለአምላችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ አያቱ ሆናለችና ምን ያህል ክብርት እንደሆነችና እግዚአብሔር የመረጣት ንጽሕት ቅድስት እንደሆነች በዚህ ይታወቃል፡፡ ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ በጸሎቷ ይማረን፡፡


Saturday, January 22, 2022

❤ ቂርቆስ ወኢየሉጣ ❤


እንኳን ለሰማዕታት ቅዱሳን ቂርቆስ ወኢየሉጣ ወነቢይ አብድዩ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it)
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ
❤ ቂርቆስ ወኢየሉጣ ❤
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካሏት ዐበይት ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ቂርቆስ ነው። በተለይ በዘመነ ሰማዕታት ተነስተው እንደ ከዋክብት ካበሩትም አንዱ ነው።
ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል፦ "መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራል።"
(ማቴ. ፯፥፲፯)
መልካም ዛፍ ቅድስት ኢየሉጣ መልካም ፍሬ ብፁዕ ቂርቆስን አፍርታ ተገኝታለችና ክብር ይገባታል። ቡርክተ ማኅጸንም እንላታለን። የተባረከ ማኅጸኗ የተባረከ ልጅን ለዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ተሸክሟልና።
በዚያ ክርስቲያን መሆን መከራ በነበረበት ዘመን ይህንን ደግ ሕፃን እርሷን መስሎ እርሷንም አህሎ እንዲገኝ አስችላለችና። አበው በትውፊት እንዳቆዩልን ከሆነ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እናታችን ቅድስት ኢየሉጣ ብፁዕ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስን ወልዳለች።
በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮም ግዛት ክርስትና ቢስፋፋም በዚያው ልክ መምለክያነ ጣዖቱ የገነኑ ነበሩ። በተለይ ከነገሥታቱ ጀምሮ ዋና ዋና የሥልጣን ቦታዎች በአሕዛብ እጅ በመሆናቸው ለዘመኑ ክርስቲያኖች ፈታኝ ነበር።
ማንኛውም ክርስቲያን መሠረታዊ ፍላጐቶቹ እንዲሟሉለት አሕዛብ ላቆሟቸው ጣዖቶች መንበርከክ ነበረበት። መብቱን ከመገፈፉ ባሻገር "ተበድያለሁ" ብሎ ወደ ፍርድ ቤት ሔዶ እንኳ የመጮህ እድል አልነበረውም። ምክንያቱም የሚሰማው የለም።
በዚያ ላይ በየጊዜው ለክርስቲያኖች ፈታኝ የሆኑ አዋጆች ይወጣሉ። የክርስትናን ጐዳና ይበልጥ የሚያጠቡ ሕጐችም ዕለት ዕለት ይፈበረኩ ነበር። ስለዚህም በወቅቱ የነበረ አንድ ክርስቲያን ሃይማኖቱን ከወደደ ወይ እስከ ሞት መታገስ ካልሆነ ደግሞ ሃገሩ ጥሎ በዱር በገደል መሰደድ ነበረበት።
እውነት ለመናገር ዜና ሰማዕታትን የማያውቅ ክርስቲያን ክርስቶሳዊ ነው ሊባል አይችልም። ምክንያቱም ዛሬ እንዲህ እንደ ዋዛ የያዝናት ሃይማኖታችን እንዴት እንደ መጣችና ምን እንደ ተከፈለባት አብዛኛው ትውልድ አያውቅምና።
ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ብፅዕት ኢየሉጣም የዚህ ዘመን (የዘመነ ሰማዕታት) ፍሬ ናቸው። በጊዜው በሮም ግዛት ሥር እስክንድሮስ የሚሉት ክፉ ንጉሥ ነግሦ ነበርና ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ። ጣዖትን ላለማምለክም ተሰው።
በዚህ ጊዜ አንጌቤናይት (ኢጣልያዊት) ብፅዕት ኢየሉጣም በመበለትነት (ባሏ በሕይወት ባለ መኖሩ) ትኖር ነበር። ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ ምንም ገና ሦስት ዓመቱ ቢሆንም ነገረ ሃይማኖትን ታስተምረው ፍቅረ ክርስቶስን ትስልበት ነበር።
እስክንድሮስ የክህደት አዋጅን ሲያውጅም ቅድስቲቱ ለሕፃን ልጇ ራርታ ሽሽትን መረጠች። ሃብት ንብረቷን፣ ወገንና ርስቷንም ትታ ሕፃን ልጇን ተሸክማ ተሰደደች። መከራው ግን በሔደችበት አለቀቃትም።
እስክንድሮስ ተከትሎ ባለችበት ቦታም አገኛት። ወታደሮች ልጇን ሳያገኙ እርሷን ብቻ ይዘው ወደ መኮንኑ አቀረቧት። መኮንኑም "ስምሽን ንገሪኝ?" ቢላት "ስሜ ክርስቲያን ነው።" አለችው። ተቆጥቶ "ትክክለኛውን ስምሽን ተናገሪ?" ቢላት "እውነተኛው ስሜ ክርስቲያን ነው። ሞክሼ (ሞክሲ) ስም ከፈለግህ ኢየሉጣ እባላለሁ።" አለችው።
"ለጣዖት ልትሰግጂ ይገባል።" ሲላትም "እውነትን ይነግረን ዘንድ የሦስት ዓመት ሕፃን ፈልገህ አምጣና ተረዳ።" ስላለችው ወታደሮቹን እንዲፈልጉ ላካቸው። የሃገሩ ሰዎች ልጆቻቸውን ስለደበቁ የተገኘ ቅዱስ ቂርቆስ ነበር።
ቅዱሱ ሕፃን በወታደሮች ተይዞ ሲቀርብ መልኩ ያበራ ነበርና መኮንኑ "በሐከ ፍሡሕ ሕፃን - ደስ የተሰኘህ ሕፃን እንዴት ነህ?" ቢለው "ትክክል ነህ! እኔ በጌታዬ ክርስቶስ ዘንድ ደስታ ይጠብቀኛል። አንተ ግን በክህደትህ ወደ ገሃነም ትወርዳለህ።" አለው።
በሕፃኑ ድፍረት የደነገጠው መኮንኑ በብስጭት "እሺ! ስምህን ንገረኝ?" አለው። ያን ጊዜ "ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ ስሜ ክርስቲያን ነው። እናቴ የሰየመችኝን ከፈለክ ግን ቂርቆስ ነው።" ሲል መለሰለት።
ከዚያም እየደጋገመ "እኔ ክርስቲያን ነኝ።" ብሎ በመጮሁ መኮንኑ ስቃይን በቅዱሱ ሕፃን እና በቡርክት እናቱ ላይ አዘዘ። ከዚህ በኋላ በእነርሱ ላይ የተፈጸመውን ግፍና የወረደባቸውን የመከራ ዶፍ እናገር (እጽፍ) ዘንድ ግን የሚቻለኝ አይመስለኝም።
በግርፋት የጀመረ ስቃይ ሊሰሙት ወደ ሚጨንቅ መከራ ቀጠለ።
ሰባት ብረት አግለው በዓይናቸው፣ በጆሯቸው፣ በአፋቸውና በልባቸው ከተቱ።
በአራት ችንካሮች ላይ አስቀመጧቸው።
በእሳት አቃጠሏቸው።
ጸጉራቸውን ከቆዳቸው ጋር ገፈፉ። ከዚህ በላይ ብዙ ስቃይንም አመጡባቸው።
እናትና ልጅ ግን ለክርስቶስ ታምነዋልና ጸኑ። ቅድስት ኢየሉጣ ብትደነግጥ ልጇ አጸናት። ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት ሲያርፉ ጌታ እንደ ቃሉ የሕፃኑን ሥጋ በሠረገላ ኤልያስ አኑሮታል። ለእኛ የሚጠቅም ብዙ ቃል ኪዳንንም ሰጥቶታል።
❤ ቅዱስ አብድዩ ነቢይ ❤
"አብድዩ" ማለት "የእግዚአብሔር አገልጋይ" ማለት ነው። ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን የቅዱስ ኤልያስ ታላቁም ደቀ መዝሙር ነው። ቅዱሳን ነቢያት ዮናስና ኤልሳዕም ባልንጀሮቹ ነበሩ።
ቅዱስ አብድዩ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስምንት ዓመት አካባቢ የከሃዲው ንጉሥ የጦር መሪ ሆኖ በሃምሳ አለቃነት አገልግሏል። ግፈኛዋ ኤልዛቤል ነቢያተ እስራኤልን ስታስፈጅ ሃምሳውን በአንድ ዋሻ ሃምሳውን ደግሞ በሌላ ዋሻ አድርጐ አትርፏቸዋል። ዘጠኝ መቶው ግን ተጨፍጭፈዋል።
ያተረፋቸውንም ክፉ ዘመን እስኪያልፍ ድረስ መግቧቸዋል። አክአብና ኤልዛቤል ከሞቱ በኋላም ቅዱስ ኤልያስን ተከትሎ ሹመቱን ትቷል። እግዚአብሔር ገልጾለትም ትንቢት ሲናገር ሕዝቡንም ሲገሥጽ ኑሯል።
በብሉይ ኪዳን ካሉ የትንቢት መጻሕፍትም በጣም አጭሩን የጻፈው ይህ ነቢይ ነው። ትንቢተ አብድዩ ባለ አንድ ምዕራፍ ብቻ ናትና። ቅዱሱ በዚህች ቀን ዐርፎ ወገኖቹ ቀብረውታል።
አምላከ ሰማዕታት በምሕረቱ ይማረን። በይቅርታው ኃጢአታችንን ይተውልን። ከበረከተ ሰማዕታትም ይክፈለን።
ጥር ፲፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ
፪.ቅዱስ አብድዩ ነቢይ
፫.ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ
፬.ቅድስት ሶፍያ
፭.ቅድስት አድምራ
፮.አሥራ አንድ ሺህ አርባ አራት ሰማዕታት (ከቅዱስ ቂርቆስ ጋር በሰማዕትነት ያለፉ።)
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
፪.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት
፫.ቅድስት ክርስጢና
፬.ቅድስት እንባ መሪና
"በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ በልብህም 'ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው?' የምትል አንተ ሆይ! የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል። እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን 'ከዚያ አወርድሃለሁ።' ይላል እግዚአብሔር።"
(አብድዩ ፩፥፫-፬)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር https://www.facebook.com/tewahdohamanotachin/
No photo description available.
103
17 Shares
Like
Comment
Share

Wednesday, January 12, 2022

ይህን ያውቁ ኖሯል?

❤ ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it) ❤
የመነኮሳት ሕይወት
ምንም እንኳን የድንግልናና የምናኔ ኑሮ ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም የምንኩስና መሥራችና አባት ቅዱስ እንጦንስ ነው፡፡ አባ እንጦንስ ግብፅ ውስጥ በምትገኝ ቆማ በምትባል ቦታ በ251 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ወላጆቹ ሀብታሞችና ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከወላጆቹ ዕረፍት በኋላ የነበረውን ሀብት ለድሆች መጽውቶ መንኩሶ ብዙ ዓመት በብሕትውና ኖረ፡፡



በዚያን ጊዜ ብዙ ታምራትን ስለሠራ ሕዝቡ ግማሹ እሱን አይቶ ለማድነቅ የቀረው ደግሞ በእርሱ ጸሎት ለመፈወስ ወደነበረበት ቦታ ይጐርፍ ነበር፡፡ እርሱም በ356 ዓ.ም ዐረፈ፡፡
አባ ጳኩሚስ የተባለ ሌላው አባት በላይኛው ግብፅ ውስጥ ብዙ ገዳማትን በመሥራት የምንኩስናን ሕግና ሥርዓት በመወሰን ስለምንኩስና መስፋፋት ብዙ ደክሟል /290-347 ዓ.ም/፡፡ አንድ ቀን ወደ ዱር እንጨት ፍለጋ ሔዶ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጸለትና እንደ አባቶቻችን ሐዋርያት የአንድነትን ማኅበር ለመሥራት መነኮሳትን እንዲሰበስብ አዘዘው፡፡ ብዙ አማኞች እየናፈቁት ማግኘት ያልቻሉትን ገዳማዊ ሕይወት ያገኙ ዘንድ ገዳም ለመመሥረት የሚስችለውንና የሚያስተዳድርበትን በነሐስ ላይ የተቀረጸ ሕግ ሰጠው፡፡ አባ ጳኩሚስም ከመልአኩ በተሰጠው ሕግ መሠረት የሚተዳደር ገዳም አቋቋመ፡፡ ይኸውም መነኮሳቱ ጠዋትና ማታ አብረው እንዲፀልዩ በአንድነት እንዲሠሩ ገቢና ወጪያቸው አንድ ላይ እንዲሆን በአንድነት እንዲመገቡ፣ ልብሳቸው አንድ አይነት እንዲሆንና እነዚህን የመሳሰሉትን ደንቦች አወጣላቸው፡፡ በዚህ መሠረት መነኮሳቱ የዕለት ምግባቸውን የሚያገኙት እየሠሩ ነበር፡፡ ከሴቶችም የምንኩስናን ሕይወት የጀመረች የአባ ጳኩሚስ እህት ማርያም ናት፡፡
ከዚህ በኋላ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀምሮ ምንኩስና በግሪክ፣ በሮም፣ በሶሪያና በሌሎችም ሀገሮችም እየተስፋፋ ሄደ፡፡
የምንኩስናን ሕይወት ወደ ኢትዮጵያ ያመጡ በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በጉባዔ ኬልቄዶን /በሃይማኖት ስደት/ ምክንያት ከቁስጥንጥንያ፣ ከግብፅ፣ ከሶርያ፣ ከሮም፣ ከአንጾኪያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ዘጠኙ ቅዱሳን መነኮሳት ናቸው፡፡ ምንኩስና ከተመሠረተ ጀምሮ በየጊዜው ሕዝቡ ታላላቆችም ሳይቀሩ ወደ ገዳማቱ እየሄዱ ይመነኩሱ ነበር፡፡
ነገር ግን ከ9ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ በማኅበር ከሚኖሩት መነኮሳት መካከል ጥቂቶቹ ቀስ በቀስ ለብቻ በተለየ ቤት መኖር እያንዳንዱ መነኩሴ ለብቻ በፈለገበት ጊዜ መብላትና መተኛት ስለጀመረ በየገዳማቱ የመነኮሳቱ ኑሮ በማኅበር የሚኖሩትና ለብቻቸው የሚኖሩት ለሁለት ተከፈሉ፡፡
የድንግልና መሠረቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ስለ መንግሥተ ሰማያት ሰውነታቸውን ጃንደረባ ያደረጉ አሉና፤ መፈጸም የሚችል ግን ይፈጽም» ሲል የተናገረው የሕግ ቃል ነው፡፡ ማቴ. 19፡12
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
/ምንጭ፦ ‘የዛሬዋ ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ’ በዲ/ን አሐዱ አስረስ፣ ነሐሴ 1992 ዓ.ም/

Monday, September 16, 2013

የቅድስት አርሴማ ታሪክ በአጭሩ


እናታችን ቅድስት አርሴማ እግዚአብሔርን በቅንነት ያገለግሉ ከነበሩ ከከበሩ ካህናት ወገን ከሆኑ ከቅዱስ ቴዎድሮስና ከእናቷ ቅድስት አትናሲያ በስዕለት ተወለደች፡፡
ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ብሉይን ሐዲስን ተምራ እያነበበች እንዲሁም በተግባር እየተረጎመች ዘወትርም በጸሎት ትተጋ እንደነበር ገድሏ ይተርካል፡፡ በዚህ ዘመን ድርጣድስ የሚባል በአርመን የነገሠ አረማዊ ንጉሥ ለጣዖት የሚሰግድ' ፀሐይንም የሚያመልክ' ክርስቲያኖችንም እኔ ለማመልከው አምላክ መስገድ አለባችሁ በማለት መከራ ያጸናባቸው ነበር፡፡

እናታችን ቅድስት አርሴማም ተጋድሎዋን የጀመረችው የዚህ ጨካኝ ንጉሥ አገልጋይ ወይም ሹም ፳፯ ክርስቲያኖችን እንደልማዱ እየደበደበ' እየገረፈና ልዩ ልዩ ስቃይ እያደረሰባቸው ሲወስዳቸው በማየቷ ነበር፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‘‘ለእነርሱና ለአሕዛብ ምስክር እንዲሆን ስለኔ ወደገዢዎችና ወደ ነገሥታት ትወሰዳላችሁ፡፡’’ (ማቴ. ፲፡፲፮፡፲፱)፡፡ ያለውን በማሰብ ቅድስት አርሴማም ገና በሃያ ዓመቷ የዚህን ዓለም ንጉሥ እኩይ ግብሩን በመንቀፍ ስለ ክርስቶስ ከሚሰቃዩ ወገኖቿ ጋር ግንባር ቀደም በመሆን ትመሰክር ጀመር፡፡ የንጉሡም አገልጋይ በደም ግባቷና በንግግሯ ማማር ተደንቆ በዚች በፈቃዷ ልትሠዋ በወደደች ሴት ምንም ሊያደርግባት ስላልወደደ ወደ ንጉሡ ወደ ድርጣድስ ከሃያ ሰባቱ ክርስቲያኖች ጋር ወሰዳት፡፡ ንጉሡም ብዙ የተነገረላትን ወጣት ሲያይ በውበቷና በንግግሯ ተማርኮ ለዓለማዊ ደስታውና ፍላጎቱ ተመኛት፡፡ ለእርሱም ሙሽራ እንድትሆን ብዙ ወተወታት፡፡ ቅድስት አርሴማ ግን ናቀችው ‘‘እኔ የሰማያዊው ንጉሥ የክርስቶስ ሙሽራ እንጂ የዚህን ዓለም አላፊ ጠፊ የሆነውን ገንዘብና ደስታ የምሻ አይደለሁም፡፡’’ በማለትም መለሰችለት፡፡
ንጉሡም ይህንን ከእርሷ በመስማቱ እጅግ ተቆጣ፤ በመናቁም ተበሳጨ፤ አሽከሮቹንም ጠርቶ በቤተ መንግሥቱ የታሰሩትን አንበሶች እንዲለቀቅባቸው አዘዘ፡፡ አንበሶቹ ግን ይደሰቱ ነበር፡፡ በኋላም ፊታቸውን ወደ ንጉሡና አገልጋዮቹ በማዞር ሩጠው እስኪደበቁ ድረስ አሳደዷቸው፡፡ ንጉሡ ይበልጥ ነደደው ክርስቲያኖቹ በረሃብ እንዲያልቁ እንዲታሰሩ አዘዘ፡፡ እግዚአብሔርም በአምስተኛው ቀን በብርሃን ቤቱን ሞልቶት የሚበሉትን በመሶብ የሚጠጡትን በጽዋ ከሰማይ አወረደላቸው፡፡ ንጉሡም ይህንን በማየቱ ከዚያ አውጥቶ በእሳት ውስጥም አስገባቸው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅን የጠበቀ አምላክ እነርሱንም አዳናቸው፡፡ በሌላም በብዙ መንገድ ሊያጠፋቸው እንደሞከረ ገድሏ ይተርካል፡፡ በመጨረሻም ከአማካሪዎቹ ጋር ተማክሮ በሰይፍ እንዲያልቁ ይወስናሉ፡፡
እያንዳንዳቸውን ተራ በተራ ሲሰይፋቸው ቅድስት አርሴማ ለሚሰየፉት ሁሉ የድል አክሊል ከሰማይ ሲወርድላቸው ትመለከት ስለነበር የእርሷን ተራ በጉጉት ትጠብቀው ነበር፡፡ በመደሰቷም እየጸለየች አይዟችሁ ጽኑ ትላቸው ነበር፡፡
በመጨረሻም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽናቷን ተመልክቶ ቃል ኪዳን ይገባላታል፡፡ ንጉሡም ሌሎቹን አሰይፎ ሲያበቃ ወደሷ ዞሮ በቁጣ እየጮኸ አንቺን እንደ ባልንጀሮችሽ በቀላሉ አልገልሽም ስቃይሽን አጸናብሻለሁ ብሎ ለአገልጋዮቹ ትእዛዝ በመስጠት አይኗን አስወጥቶ በእጇ ያሲዛታል፤ ጡቷን ያስቆርጣል፤ በኋላም አንገቷን ያሰይፋታል በዚሁ ሁኔታ እናታችን ሰማዕትነትን ተቀበለች፡፡
ይህንን ሁሉ መከራ ስለአምላኳ ስትል እራሷን አሳልፋ የሰጠች ድንቅ ሰማዕት ናት፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ ‘‘ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ’’ (መዝ.) እንዳለ ለእናታችንም የገባላት ቃል ኪዳን ‘‘በእኔ ስም አምነሽ የዚህ ዓለም ተድላና ደስታ ሳያታልልሽ አንገትሽን ለሰይፍ ሰጥተሽ ተሰይፈሻል፤ የሰማዕትነት ተጋድሎ ፈጽመሻልና ስምሽን የጠራ፤ በዓልሽን ያከበረ፤ ዝክርሽን የዘከረ፤ ገድልሽን የጻፈና ያጻፈ፤ የሰማና ያሰማም እስከ ፲፪ ትውልድ ድረስ እምርልሻለሁ’’ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶላታል፡፡ በዚህም መሠረት በሷ አማላጅነት አምኖ እገዳሟም ሄዶ በጸሎት የተማጸናት ሁሉ ለችግሩ መፍትሄ አግኝቶ እንደሚመለስ እሙን ነው፡፡ የቅድስት አርሴማ ረድኤት በረከት ጸሎትና ምልጃ ከእኛ ጋር ይኑር፡፡ አሜን አሜን አሜን


አሜን የእናታችን በረከቷ ይደርብን!!!!

LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

Thursday, July 11, 2013

ሐምሌ 5


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ዱ አምላክ አሜን!


==> ወበዛቲ ዕለት ሐምሌ ፭ . . . . “ቅዱስ ጴጥሮስ ወቅዱስ ጳውሎስ”<==
“ክበር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤ (የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።”) መዝ. ፻፲፭/ ፻፲፮፡፲፭ (115/116፡15)
“ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፥ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም።”ማቴ.፲፫፡፲፩
እንኳን ለቅዱሳን ሰማዕታቱ ለቅዱስ ጴጥሮስ ወቅዱስ ጳውሎስ የሰማዕትነት ቀን በዓላቸው በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ አሜን።

==> ፨ ☆♥☆♥☆♥ቅዱስ ጴጥሮስ ☆♥☆♥☆♥ ፨

ቅዱስ ጴጥሮስ የተወለደው በገሊላ ባሕር ዳር በምትገኘው ቤተ ሳይዳ ነው፡፡ ጴጥርስ ማለት ኮኩኽ ሃይማኖት ማለት ነው። ማቴ. ፲፮፡፲፰ (16፡18) በዕራይስጥ ኬፋ ይለዋል። ቀዳሚ ስሙ ስምዖን ነው። ዮሐ.፩፡፵፭ (1፥45)፡፡ የአባቱ ስም ዮና ሲሆን ትውልዱም ከነገደ ሮቤል ነው፡፡ ዮና ከነገደ ስምዖን የምትሆን አንዲት ሴት አግብቶ ቅዱስ ጴጥሮስን ወለደ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ከተወለደ በኋላ እንደ ሕገ ኦሪት ትእዛዝ በስምንተኛው ቀን ወደ ግዝረት ቤት አግብተው ስሙን በእናቱ ነገድ ስም ስምዖን ብለው ሰይመውታል፡፡
እድሜው አምስት ዓመት ሲሆን እንደ አይሁድ ሥርዓት ሕገ ኦሪትን እየተማረ እንዲያድግ በቤተ ሳይዳ አጠግብ ወደሚገኘው ወደ ቅፍርናሆም ሰደዱት፡፡ በዘመኑ በባህር ዳር በምትገኘውና ታላቅ የንግድ መነኸርያ በነበረችው ቅፍርናሆም የሮም ጭፍሮች አለቃ የነበረችው በቅፍርናሆም የሮም ጭፍሮች አለቃ የነበረው ኢያኢሮስ አይሁድን ደስ ለማሰኘት አሰርቶት በነበረው ምኩራብ እየተማረ አደገ፡፡
ከዚያም በኋላ በዚያ ከተማ ቤት ሰርቶ ኮን ኮርድያ (ጴርጴቱዋ) የምትባል ሚስት አግብቶ እንደ አባቱ እንደ ዮና ይተዳደር የነበረው ከወንድሙ እንድርያስ ጋር ዓሣ በማጥመድ ነበር። ዓሣ እያጠመደና እየሸጠ ይኖር ነበር፡፡ ዓሣ ከሚያጠምድበት ተጠርቶ ሐዋርያ ሆኗለ። ማቴ. ፬፡፲፱ (4፡19) ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከተቀበሉ በኋላ መዲናቸው ኢየሩሳሌም አንድ ዓመት ካስተማሩ በኋላ ወንጌል ካልደረሰበት ለማድረስ ዓለምን ዕዳ በዕዳ ከተከፋፈሉ ጊዜ ርዕሰ ሐዋያ ነውና ሮምን ደርቦ ሰርቶታል። በሮምም ፳፭ (25) አስተምሯል። ከዚያ በፊ ግን በሰማርያ፣ በልዳ፣ በኢዮጴ፣ በአንጾኪያ፣ጳንጦስ፣ በገላቲያ፣በቀጳዶያና በቢታኒያ አስተምራል። በትምህርቱም ጣቢታ ከሞት አስነስቷል። ሐዋ. ፱፡፴፪-፴፬ (9፡32¬-34) ያስተማራቸው ምዕመናም ከሃማኖታቸው እንዳይወጡ ፪ (2) መዕክታትን ጽፎላቸዋል። ንጉሱ ኔሮን ቆሳር መምለኬ ጣኦት ነበርና በሃይማኖት ምክንያት አስሮት ነበር። ለጣዖትም እንዲሰግድ ባስገደደው ጊዜ ለጣኦ አልሰግድም በማለቱ በችንካር ተቸንክሮ በመስቀል ተሰቅሎ ይሙት ብሎ ፈረደበት። አይሁድ ሲጣሉት ወደ ጌታ ቢያመለክት እሳት ከሰማይ ወርዳ ታጠፋለት ነበር። ይዞ ዳግም ቢሰቅሉትም ፈቃድህስ ከሆነ ብሎ እንደ ጌታ አቁማችሁ ሳይሆን ቁልቁል ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ አላቸው። በራሱ ዘቅዝቀው ሰቅሎታል። ሥጋውን ደቀመዝሙሩ መርቄሎስ ከመስቀሉ አውርዶ በወተት በወይን አጥቦ ሽቱ ቀብቶ በነጭ ሐር ገንቦ እንዳይፈርስ በማረ በተመላ ሣጥን አድርጎ ቀብሮታል።



==> ፨ ☆♥☆♥☆♥ ቅዱስ ጳውሎስ ☆♥☆♥☆♥ ፨

ጳውሎስ ማለት ንዋይ ህሩይ ማለት ነው። ሐዋ. ፱፡ ፲፭ (9፡15) አንድም ብርሃን ማለት ነው። ዘዳ.፲፬፡፪ አንድም መድቅዕ ማለት ነው። ቀዳሚ ስሙ ሳዖል ነው። ሳዖ ማለት ጸጋ እግዚአብሔር የበዛለት ማለት ነው። ትውልዱ ከነገደ ቢኒያም ነው። ፊሊ. ፫፡፭ አባቱ ዮስአስ ይባላል። የተወለደው ጌታ በተወለደ በ፭ (5) ዓመት በጠርሴስ ነው። ከ፲፭ ዓመቱ ጀምሮ ኢየሩሳሌም በታላቅ እህቱ ቤት ተቀምጦ ከመምህር ገማልያል ህገ ኦሪትን ተምሯል።በወንጌል ያመነው ጌታ ባረገ በ፰ኛው ዓመት ነበር። ጌታም በደማቆ መብረቅ ጥሎበት ሳኦል ሳኦል ስለምን ታሳደኛለህ ብሎ ታርቆታል። ከ፸፪ (72) አርድእት አንዱ የሆነው ሐናንያ ጌታ በራዕይ ታይቶት ጳውሎን አስተምረህ አሳምነህ አጥምቀው አለው። እርሱም በእጁ ገና አይኑ በዳሰሰው ጊዜ አይኑን አሳውሮት የነበረው እንደ ቅርፊት ወድቆለታል። ሐዋ.፱፡፩-፲፱ (9፡1¬-19) ከዚያ በኋላ በክርስቶስ እመኑ እያለ አስተምሯል። ብዙዎችንም አስተምዎ አጥምቋል። ሐዋ. ፲፬፡፰-፲፰ ብዙውንም አሳምኗል። በወይኒም ታስሮ በነበረበት ወቅት ብዙ ሰዎችን አሳምኗል።
ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱ፤ ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ። ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤ ወደ ገዢዎችም አቅርበው። እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ።
እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ አሉ። ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፥ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ፤ በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፥ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፥ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸው። በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤ በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ የሁሉም እስራት ተፈታ። የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ። ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ። ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ ብሎ ጮኸ። መብራትም ለምኖ ወደ ውስጥ ሮጠ፥ እየተንቀጠቀጠም ከጳውሎስና ከሲላስ ፊት ተደፋ፤ ወደ ውጭም አውጥቶ። ጌቶች ሆይ፥ እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል? ኣላቸው።
እነርሱም። በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ አሉት። ለእርሱና በቤቱም ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሩአቸው። በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፥ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ፤ ወደ ቤቱም አውጥቶ ማዕድ አቀረበላቸው፥ በእግዚአብሔርም ስላመነ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ሐሤት አደረገ። ሐዋ. ፲፮፡፲፰-፴፬ (16፡18-34)
ሕሙማንንም ሕሙም መስሎ አስተምሯል። ፩ቆሮ.፱፡፳፪ (1ቆሮ.9፡22) ፲፬ መልዕክታትንም ጽፏል። ከዚህ በኋላ በ69 ዓ.ም ሮም ሲያስተምር ኔሮን ቆሣር አስጠሩት ሲል በንጉሱ ፊት ሲቀርብ መስቀሉን ይዞ ቀረበ። ንጉሱ ተቆጥቶ በሰይፍ ቅጡ አለ። በመጎናጸፊያም ሸፍኖ ሰይፎታል። ደሙም ሰማየ ሰማይ ወጥቶ ቀተሉኒ በዓመጻ እያለ ተካሷቸዋል። ሲያፍም የ72 አረጋዊ ነበር። ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር የሞቱት በአንድ ቦታ በአንድ ቀን ነበር። ይህም ሐምሌ ፭ ነው።

ምንጭ፡- ገድለ ሐዋርያት፣ ዜና ሐዋርያት፣ ነገረ ቅዱሳን ቁጥር ፪፣ መዝገበ ታሪክ
የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን ይቆየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡ አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን አሜን፡፡