Showing posts with label ነገረ ማርያም. Show all posts
Showing posts with label ነገረ ማርያም. Show all posts

Monday, January 10, 2022

የእመቤታችን ሥዕል ከመንበር ላይ ለምን ይቀመጣል?

 ይህን ያውቁ ኖሯል?

የእመቤታችን ሥዕል ከመንበር ላይ ለምን ይቀመጣል?
በኦሪቱ የኪሩቤል ሥዕል በታቦቱ አጠገብ ይቀመጥ ነበር፡፡ ዘጸ. ፳፭፥፳፩-፳፪፤ዘኊ ፯፥፹፱፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ ነግሮ እንዲህ እንዲሆን ያደረገበት ምክንያት አለው፡፡ይህም ምክንያት ኪሩቤል የመንበሩ /የዙፋኑ/ ተሸካሚዎች በመሆናቸው ነው፡፡ ፩ኛ ሳሙ.፬፥፬፤ ሕዝ.፩፥፭፰፤ ፲፥፲፪፤ ፳፩፤ራእ.፬፥፮፡፡ በአዲስ ኪዳን ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአዲስ ኪዳን ኪሩብ ትባላለች፡፡ እንዲያውም ከኪሩቤል ትበልጣለች፡፡ ኪሩቤል የሚሸከሙት መንበሩን ነው፤ እመቤታችን ግን ማኅፀኗን መንበር አድርጋ እርሱን ተሸከመችው፡፡ እንግዲህ በብሉይ ኪዳን ዘመን በእግዚአብሔር ትእዛዝ የኪሩቤል ሥዕል በመንበረ ታቦቱ ይቀመጥ እንደ ነበር በአዲስ ኪዳን ደግሞ ኪሩብ የምትባል እመቤታችን ሥዕሏ በመንበረ ታቦቱ ላይ ይቀመጣል፡፡
ምንጭ፡ ነገረ ቅዱሳን ቁ. ፩




Monday, August 17, 2015

ነሐሴ 7 ጽንሰታ ማርያም



ከእመቤታችን 33ቱ ባዓላት አንዱና የመጀመሪያው ነው፤ ይኸውም የተጸነሰችበት ነው፤ ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ፍቅር ከሚቀዘቅዝበት ጭካኔ ከሚነግስበት ከስምንተኛው ሺ ዘመን አታድርሰኝ የዛን ዘመን እህል አታቅምሰኛ ውኃም አታጠጣኝ ብሎ ሲጸልይ የነበረው ጻድቁ ንጉስ አጼ ናኦድ ስምንተኛው ሺ መስከረም አንድ ሊጀምር እርሱ በዛሬዋ ቀን ዓለም ከተፈጠረ በ 7000 ዘመን አረፈ (5500 +1500)
ነሐሴ 7 በዚህች ዕለት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተጸነሰች::የእመቤታችን ወላጆችዋ ኢያቄም እና ሃና ይባላሉ:: እነዚህ ቅዱሳን ኢያቄም እና ሃና በአንድነት ተጋብተው ሲኖሩ ልጅ አጡ፤ከእለታት አንድ ቀን ወደ ቤተ እግዚአብሄር ሂደው ሲፀልዩ ሲያዝኑዋሉ:፡ሃዘናቸው እንዴትስ ነው ቢሉ ፡-
ኢያቄም:-"አቤቱ ጌታዬ ያባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለሁ አትጣለኝ አትናቀኝ ፀሎቴን ስማኝ ፈቃዴን ፈጽምልኝ፤ለአይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የሚሆን የተባረከ ወንድ ልጅ ስጠኝ" ብሎ ሲለምን ዋለ:፡
ሃናም በበኩሏ "አቤቱ ጌታዬ የአባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለሁ:ስማኝ ለአይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋየምትሆነኝ የተባረከች ሴት ልጅ የማህፀኔን ፍሬ ስጠኝ" ብላ ስትለምን ዋለች:፡ እንዲህ ብለው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ውለው ርግብ ከልጆቿጋር ስትጫወት አይታ አቤቱ ጌታዬ ለዚች ግእዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሳኸኝ ብላ ምርር ብላ አለቀሰች:፡እንዲህ ብለው ሲያዝኑ ሲፀልዩ ውለው ከዘካርያስ ከሊቀ ካህናቱ ሄደው አቤቱ ጌታችን ሆይ ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተእግዚአብሄርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን፤ሴት ልጅም ብንወልድ ማይ(ውሃ) ቀድታ መሶብ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን ብለው ስዕለት ገቡ:: ዘካርያስም እግዚአብሄር ጸሎታችሁን ይስማችሁ ስእለታችሁን ይቀበልላችሁ ብሎ አሳረገላቸው።
ከዚያም በሁአላ ቅድስት ሃና እና ቅዱስ እያቄም ዕለቱን ራእይ አይተው ነገር አግኝተው አደሩ:ራእዩም እንዴት ነው ቢሉ ኢያቄም 7ቱሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ አላት ፤
ሃናም እኔም አየሁ አለችው:ምን አየሽ ቢላት:ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማህጸኔ ስትተኛ አየሁ ይህንን ራእይ ያዩት ሐምሌ 30 ዕለት ነው:: እነሱም እንዲ ያለ ራዕይ ካየን ነገር ካገኘን ብለው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም፤ፈቃደ እግዚአብሄር ቢሆን ብለው አዳምንና ሄዋንን ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት ብሎ ያበሰረ አምላክ ለኛስ ይልክልን የለምን? ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ 7ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ፡፡ነሃሴ በባተ በሰባተኛው ቀን ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላቹህና ዛሬ በሩካቤ ስጋ ተገናኙ ብሎአቹሃል ጌታ ብሎ መልአኩ ለሃና ነገራት በፈቃደ እግዚአብሄር በብስራተ መልአክ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም እሁድ እለት ነሐሴ 7 ቀን ተፀነሰች፡: ምልጃዋ በረከቷ በሁላችን ላይ ይደርብን:: ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡፡



ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Thursday, August 6, 2015

ጾመ ፍልሰታ

ጾመ ፍልሰታ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም


<ፍልሰታ > የሚለው ቃል የሚገልጸው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለቆ መሔድን መሰደድን መፍለስን ያመለክታል :: ይህም የእመቤታችንን ሥጋ ከጌቴሴማኔ ወደ ገነት መፍለሱን
ኢትዮጵያ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአሥራት አገር ናት፡፡ ሊቃውንትም ነቢያት የተነበዩትን ትንቢት የቆጠሩትን ሱባዔ መሠረት በማድረግ ቅድስት ድንግል ማርያም በኪደተ እግሯ ኢትዮጵያን መባረኳን ያስተምራሉ፡፡ «ነቢዩ ዕንባቆም የኢትዮጵያ ድኳኖች ሲጨነቁ ዐየሁ፤» ዕንባ. 3፡7 ብሎ የተናገረው ቃለ ትንቢት እመቤታችን የኢትዮጵያን አውራጃዎች ለመባረኳ ማስረጃ መሆኑን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይተረጉማሉ፤ ያመሠጥራሉ፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን ለእናቱ አሥራት አድርጐ በመሥጠቱ በእርሷ በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሆን የነገረ ድኅነት ምሥጢር በመከናወኑ ኢትዮጵያውያን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተለየ ፍቅር አለን፡፡ የአብነት /የቆሎ/ ተማሪዎች በትምህርት ዓለም ከአንዱ ወደሌላው እየተዘዋወሩ /የአብነት/ ትምህርት ሲማሩ በእንተ ስማ ለማርያም፤ ስለማርያም እያሉ፡፡ የእመቤታችን ስም ስንቅ ምግብ ሆኗቸው ይጠቀሙበታል፡፡ ግሼን ደብረ ከርቤ የልጇ ግማደ መስቀል ከከተመበት አምባም የሚጓዙ ምእመናን «አንድ እፍኝ ሽምብራ አልያዝኩም ከቤቴ ስሟ ስንቅ ነው የእመቤቴ» እያሉ በፍቅሯ ተማርከው ግብር ሰፍረው ዕጣን ቋጥረው ሱባዔ እየገቡ ይማፀኗታል፡፡ እርሷም ከልጇ ዘንድ ባገኘችው የመወደድ ሞገስ ምልጃቸውን በመቀበል ጸሎታችውን በማሣረግ የእናትነት ሥራ ሥትሠራላቸው ኖራለች፡፡ ዛሬም እየሠራች ነው፡፡ እመቤታችን ከልጇ ያገኘችውን /የተቀበለችውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ በዐራቱ ማእዘን «ሰዓሊ ለነ ቅድስት፤ ቅድስት ሆይ ለምኝልን» የማይላት የለም፡፡


በፍቅሯ ተደስተው በአማላጅነቷ ተማምነው «የእመቤቴ ፍቅሯ እንደ ሰማይ ክዋክብት፣ እንደምድር አሸዋ በዝቶልኝ፣ እንደ ልብስ ለብሼው፣ እንደምግብ ተመግቤው» እያሉ ተማጽነው ልመናቸው ሠምሮ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊው፣ ቅዱስ ያሬድ ዘኢትዮጵያና አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ያዘጋጁላትን፣ አባ ጽጌ ድንግል የደረሱላትን የምስጋና መጻሕፍት በመድገም እመቤታችን ዘወትር መማጸን የቀደምት ኢትዮጵያውያንም የዛሬዎች ገዳማውያንና ምእመናን ዕለታዊ ግብር ነው፡፡


ጌታችን ለቀደሙት ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችን አማላጅ እና እናት ሆኗ እንድታገለግል በገቢርም በነቢብም ከአደራ ቃል ጋር አስረክቧል፡፡ በገቢር በቃና ዘገሊላ የሰውን ችግር ፈጥና የምትረዳ ርኅርኅሪት እናት አማላጅ መሆኗን አሳይቷል፡፡ «ለዚሁም የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል» ብላ ያቀረበችው ቃለ ምልጃ ምስክር ነው፡፡ እናት ሆኗ እንድታጽናናቸው በቅዱስ ዮሐንስ በኩል ከእግረ መስቀሉ ስር ሰባቱን አጽራሐ መስቀል ሲያስተጋባ ቅዱስ ዮሐንስን ጠርቶ «እኖኋት እናትህ፤ ድንግል ማርያምን ጠርቶ እነሆ ልጅሽ» ዮሐ. 19፡26፡፡ በማለት እመቤታችን የእናት ሥራ ለሁሉም ቅዱሳን ሐዋርያት እንድትሠራላቸው ምእመናንም ልጅ እንዲሆኗት በማያሻማ ቃሉ ተናግሯል፡፡


ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችንን በእናትነት ከተረከቧት ጊዜ ጀምረው ልጇ በዕርገት በአካለ ሥጋ ሲለይ እንደ ልጅ አገልግለዋታል፡፡ በቤታቸው አኑረዋታል፤ ብትሠወርባቸው ፈልገዋታል፡፡ ብትርቃቸው ናፍቀዋታል፡፡ እርሷም ሲጠሯት ታደምጣቸዋለች፣ ሲፈልጓት ትገኝላቸዋለች፡፡ ይኸውም የሆነው ልጇ በአዳምና በልጆቿ ኃጢአት ምክንያት የፈረደውን ለራሱም ያላስቀረውን ሥጋዊ ሞት እናቱ ብትቀምስ በእናትነት የተረከቧት ቅዱሳን ሐዋርያት መካነ ዕረፍት ለይተው በንጹሕ በፍታ ከፍነው በጌቴ ሰማኒ እንደቀበሯት ስለ እመቤታችን የተጻፉ መጻሕፍት በዝርዝር ያስረዳሉ፡፡


የእመቤታችን ሥጋዊ ዕረፍት «ከመ ትንሣኤ ወልዳ» እንደ ልጇ ትንሣኤ ነውና ሙስና መቃብር ሳያገኛት ከሦስት ቀናት ሥጋዊ ዕረፍት በኋላ ከሞት ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ በዕለተ ቀብሯ ያልተገኘው ቅዱስ ቶማስ ደመና ጠቅሶ በደመና ሰረገላ ሲመጣ ዕርገቷን ይረዳል፡፡ እማኝ ደግሞ የተከፈነችበትን በፍታ /ጨርቅ/ ይቀበላታል፡፡ ለቅዱስ ቶማስ የተገለጠው የዕረፍቷ ምሥጢር ሌሎች ቅዱሳን ሐዋርያት እንዲገለጥላቸው ቢማጸኑ እመቤታችን ዳግም ተገልጻላቸው፡፡ ትንሣኤዋን ለማየት በቅተዋል፡፡


እነዚህ በቅድስናቸው የተመሠከረላቸው ቅዱሳን እመቤታችንን በሁለት ሱባዔ ማግኘታቸውን መሠረት በማድረግ በቤተ ክርስቲያናችን ከነሐሴ 1-16 በየዓመቱ አንደሚጾም ይታወቃል፡፡ ይህ እመቤታችንን የምንማጸንበት ጾመ ፍልሰታ ቤተ ክርስቲያናችን መፍትሄ የምትፈልግባቸውን ጉዳዮች ለእመቤታችን የምታቀርብበት ሰዓት ነው ብለን እናምናለን፡፡


ኢትዮጵያ የእመቤታችን አሥራት አገር ስትሆን እመቤታችን ለኢትዮጵያውያን እናት መሆኗ እየተነገረ ለምን በፈተና ውስጥ አለፍን? ልጇ በአሥራት ኢትዮጵያን የሰጠባት ሀገር አባቶች ማስፈራሪያ ሲደርስባቸው መንፈሳዊነት /ኀይለ መንሳዊ/ ተዘንግቶ ሥጋዊ ጥበብ በቤተ ክርስቲያን መድረክ ሲታይ ምን ይባላል? «እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰችው ሥፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ» ማቴ. 24፡15፡፡ የተባለው ቀን ደርሶ ይሆንን?


ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ዓመታት ለገጠማት ችግር መፍትሔ እመቤታችን እጅ ላይ አለ ብለን እናምናለን፡፡ እመቤታችን ብትሠወርባቸው አባቶች ሱባዔ ገብተው እንዳገኟት የፍቅር እናት ናትና ፍቅር አንድነት እንድትሰጠን እርሷን መማጸን፤ የዶኪማስን ጓዳ እንደሞላች የጐደለውን እንድትሞላ ውዳሴዋን እየደገሙ ድንግልን መማጸን ያስፈልጋል፡፡


በውዳሴ ማርያም፣ በጸሎተ ማርያም የሚመካ በጉልበቱ አይመካም፡፡ ጊዜ ረዳኝ ብሎ በወገኖቹ ላይ ግፍ አይፈጽምም፡፡ ስለዚህ በዚህ በወርኀ ጾም እመቤታችን ምልጃዋ ከአገራችን፣ ከቤተ ክርስቲያናችን ጋር እንዲሆን በሱባዔ እንማጸናት፡፡


በጾመ ፍልሰታ ከሊሂቅ እስከ ደቂቅ በማስቀደስ፣ በጾምና በጸሎት ሁለቱን ሳምንታት እንደሚያሳልፉት ይታወቃል፡፡ በሱባዔው የቤተ ክርስቲያናችን ችግሮች የሚወገድበት ምእመናን በበረከት የሚጐበኙበት ቅድስና የሚሰፍንበት መንፈሳዊነት ትልቅ ከበሬታ የሚገኝበት ጾም እንዲሆን ሁሉም ምእመን መትጋት አለበት፡፡


ሁለቱ ሳምንታት በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር እየተገኘን ምሕላ የምናደርስበት፣ የተጣላነውን ይቅር ለእግዚአብሔር፣ የበደልነውን የምንክስበት ጾም መሆን አለበት፡፡


ቀናቱን እየቆጠርን እስከተወሰነው ሰዓት ብቻ መጾም ብቻ በሕይወታችን መሠረታዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ እመቤታችን የአገራችን አሥራት የሁላችን እናት በመሆኗ የእናትነት ሥራ እንድትሠራልን በሚገባ ልንማጸናት ይገባል እንጂ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ሱባዔ ብለን ውዳሴ ማርያም በደገመ አፋችን ሰው የምናማ በሰው ሕይወት ገብተን የምንፈተፍት ከሆነ እመቤታችንን አናውቃትም፡ እመቤታችንም አታውቀንም፡፡ ስለዚህ ጾመ ፍልሰታን እስኪ ሁላችን ኢትዮጵያውያን የተዋሕዶ ልጆች ድንግልን በአንድ ድምፅ እንጥራት፡፡


የእመቤታችንን ጾመ ፍልሰታ፤ እንደ ብርሃን ተስፋ በማድረግ በተለይም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚተጉ አባቶች እና ምእመናን ለተሰደዱ፣ ለተራቡ፣ በፈተና ውስጥ ለሚገኙ ይማጸኑ እንላለን፡፡ ውዳሴ ማርያሙ፤ ሰዓታቱ ጨለማን ተገን አድርጐ ከሚቃጣ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ድርብ ኀይል አለው፤ እስኪ ለቅድስና፣ ለንጽሕና ለመንፈሳዊነት ቅድሚያ እንስጥና የእግዚአብሔርን ብድራት እንጠብቅ፡፡ ጾመ ፍልሰታ መንፈሳዊነት፣ እውነት፣ ቅድስና የጠራ አሠራር፣ በቤተ ክርስቲያን የሚሰፍንበት እንዲሆን እንመኛለን፡፡ 


ወስብሐት ለእግዚአብሔር


Monday, June 9, 2014

ግንቦት 24

ግንቦት 24

 በዚህች ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን እግዚያብሔርን ይዛ ከዮሴፍና ከሶሎሜ ጋር ወደ ግብጽ የተሰደዱበት ቀን ነው፤ ይህን ቀን ቤተክርስቲያን በደማቁ አክብራው ትውላለች፤ በመዲናችን አዲስ አበባ እንጦጦ መንበረ ንግስት ቁስቋም ቤተክርስቲያን እንዲሁም ቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ታቦተ ሕጉ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል። “እነሆ፥ የጌታ መል...አክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ። ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ። ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ። ማቴ 2፤13 በስደት የቆዩት ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ነው የእመቤታችን ስደት ለኢትዮጵያ ታላቅ በረከት ነው የጣና ደሴቶችን የዋልድባ ገዳምን አክሱምና የትግራይ አውራጃዎችን፤ ድብረ ዓባይና የጎጃም ታላላቅ ገዳማትን በርካታ የኢትዮጵያ አውራጃዎችን በኪደተ እገራቸው ባርከውታል ቀድሰውታል።፤ “የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ አለ ነብዩ ዕንባቆም፤ ዕንባቆም 3፤7። ነብዩ ምን ማለቱ ነው ? መቼ ነው የኢትዮጰያ ድንኳኖች የተጨነቁት ? እመቤታችን በስደት ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣም እይደል። ግን ግን ስደቷ ግንቦት 24 ከሆነ ለምን ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 6 ቀን የጽጌ ጾም ብለን ስደቷን እናስባለን ካሉ፤ይህ ሊቃውንቱ የሰሩት ስርዓት ነው፤ ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 25 በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ዘመነ ጽጌ ይባላል የአበባ የልምላሜ ወቅት ነው፤ እመቤታችን ደግሞ በአበባ ትመሰላለች አበባ የፍሬ እናት ነው፡፡ እመቤታችንም የተባረከ ፍሬ መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርሰቶስን ያስገኘች አማናዊቷ አበባ ናት፡ ስለዚህም ይህን የስደቷን ወራት በዘመነ ጽጌ ባሉት 40 ቀናት ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 6 ቀን ታስቦ እንዲውል የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ስርዓትን ሰሩ። 
እግርሽ ጨረቃን የሚጫማ 
በአሸዋ ስትሮጪ እግርሽ ደማ
ውቅያኖሶቹ ግራ ቀኙ የሚሰፈሩት በእፍኙ
ለእርሱ ለእርሱ ለዝናብ ጌታ ውኃ ነሱ።
ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>

ግንቦት 21

ግንቦት 21

ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፤በዚህ ቀን ግብጽ ደብረ ምጥማቅ በተባለ ቦታ በተሰራች ቤተክርስቲያን እመቤታችን ጻድቃንን መልአክትን አስከትላ ትገለጽላቸው ነበር፤እስላምም ክርስቲያንም በግልጽ ይመለከቷት ነበር። ከየአገሩ ያሉ ሰዎች ይሰበሰባሉ ድንኳን ተክለው ሰቀላ ሰርተው አጎበር ጥለው ይከትማሉ ፤ድንግልም ከግንቦት 21 ቀን ጀምሮ ለአምስት ተ...ከታታይ ቀናት ሳታቋርጥ ትገለጽላቸው ነበር፤ህዝቡ የተለያየ ጥያቄ ይጠይቃታል አዳም አባታችንን አሳይን ይሏታል ገሚሱ ነብዩ ዳዊትን ገሚሱ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሳይን ይሏታል አንዳንዱም ከዚህ ቀደም የሞተ ዘመዱን እንድታሳየው ይጠይቃታል፤እርሷም ለሁሉም ፍቃዳቸውን ትፈጽምላቸው ነበር፤አዳምን ስትጠራው ከሔዋን ጋር ዳዊትን ስትጠራው ከበገናው ጋር ቅዱስ ጊዮርጊስን ስትጠራው ከጸአዳ ፈረሱ ጋር ነው። ወይ ግሩም ታዲያ ይህ በዚያ ደጉ ዘመን ነበር፤አሁን ግን ኃጢያታችን ሲበዛ በረድኤት ካልሆነ በገሃድስ ተገልጻ አትታይም ለበቁ ካልሆነ። ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን አባ መርትያኖስ አረፈ፤ ይህም በህጻንነቱ መንኩሶ ለ 67 ዓመት በፍጹም ተጋድሎ የኖረ ነው። ይህ ገድል ትሩፋቱ በሁሉ ዘንድ ተሰማ፤ እነሆ አንዲት በዝሙት ስራዋ እጅግ የምትታወቅ ሴት ዘንድ ወሬው ደረሰ፤ እርሱ እኮ የሴት ፊት ስላላየ ነው እንጂ በፍትዎት ይወድቃል ከክብሩም ይዋረዳል አለቻቸው ባልንጀሮቿም የለም በፍጹም አያደርገውም አሏት፤ እኔ በዝሙት ከጣልኩት ምን ትሰጡኛላችሁ አለቻቸው ብር እንሰጥሻለን አሏት፤በዚህ ተወራርደው ሄደች፤ ሽቶ ተቀባብታ አምራ ተውባ ሄደች፤ስንክሳሩ እጅግ ውብ መልከመልካም ነበረች ይላታል፤ እስኪመሽ ከገዳሙ አቅራቢያ ቆይታ በሩን አንኳኳች የመሸቢኝ እንግዳ ነኝ አሳድረኝ ትለዋለች፤ ነፍሱ ተጨነቀች ባስገባት የዝሙት ጦር ይነሳብኛል ብተዋት እንግዳ ሆኜ መጥቼ መቼ ተቀበላችሁኝ ብሎ ይፈርድቢኛል ደግሞም አውሬ ይበላታል ብሎ አሰበ፤ባስገባት ይሻለኛል ብሎ አስገባት የተቀበችው ሽቶ ዝሙት የሚቀሰቅስ ነው፤ ቀረበችው፤አባቴ በዚህ ማንም አያየንም አብረን እንተኛ አለችው፤እሳት እያነደደ ነበርና እሺ ምን ችግር አለው እዚህ አሳት ላይ ምንጣፍሽን አንጥፊና እንተኛለን አላት፤ አንድም እግሩን ወደ እሳቱ ማገደው ይላል አይንህ ብታሰናክልህ ካንተ አውጥተህ ጣላት አይደል የሚለው መጽሐፉ፤ ደነገጠች ምንድን ነው አባቴ አለችው፤ ይህ ያስደንቅሻልን የገሃነም እሳትን ታዲያ እንዴት ልትችይው ነው አላት እግሩ ስር ወድቃ ይቅር በለኝ አለችው እርሱም ሌሊቱን ሙሉ ሲያስተምራት አደረ፤ ሲነጋ አልተመለሰችም አመንኩሰኝ ከዚህ በኃላ ወደ ዓለም አልመለስም አለችው አመነኮሳት ከደናግል ገዳም ወስዶ ለእመምኔቷ አደራ ሰጣት፤የሚገርመው ይህች እናት ከብቃቷ የተነሳ የመፈወስ ሀብት ተሰጣት ብዙ በሽተኞች ወደርሷ እየመጡ ይፈወሱ ነበር፤ አባ መርትያኖስ ግን ድጋሚ ሌላ ሴት መጥታ እንዳትፈትነው ሰው የማይደርስበት ከባህር መካከል ባለች ደሴት ብቻውን መኖር ጀመረ፤ ከብዙ ዘመን በኃላ መርከብ ተሰብሮ ብዙዎች ሲሞቱ አንዲት ሴት በመርከቡ ስባሪ ተጣብቃ እርሱ ካለበት ደሴት ደረሰች ባያት ጊዜ ደነገጠ አደነቀም ከእርሷ ጋር በአንድነት ስለመኖሩም አዘነ፤ ይምትበላውን ሰጥቷት የምትለብሰውን አዘጋጅቶላት ሲያበቃ ተወርውሮ ወደ ባህሩ ገባ ዓሳ አንበሪም ተሸክሞ ወደ የብስ አደረሰው ከዚህ በኃላ በአንድ ቦታ ላለመቀመጥ ወስኖ በ108 አገሮች የሚገኙ ታላላቅ ገዳሞችን ዞረ በመጨረሻም በዛሬዋ ቀን በክብር አረፈ፤ እመቤታችንን ከሐና ማህጸን ፈጥሮ ከፍጥረተ ዓለም ለይቶ ከሁሉ አልቆ የእናት አማላጅ ትሁናችሁ ብሎ የሰጠን እግዚያብሔር ይመስገን፤ እኛንም ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>

ልደታ ለማርያም


ጴጥርቃ እና ቴክታ የሚባሉ ሰዎች በኢየሩሳሌም በአንድነት ተጋብተው ይኖሩ ነበር:እነዚህም በእግዚአብሄር የሚያምኑ የተወደዱ ጻድቃን ደግ ሰዎች ነበሩ:እነዚህም ሰዎች በእግዚአብሄርም በሰውም ዘንድ የበቁ ባለጸጎች ነበሩ:ነገር ግን የሚወርሳቸው ልጅ አልነበራቸውምና መካን ነበሩ:አንድ ቀን ጴጥርቃም ቴክታን እህቴ ሆይ ይህን ሁሉ የሰበሰብነውን ገንዘባችንን ምን እናደርገዋለን ልጅ የለን የሚወርሰን:አንቺም መካን ነሽ እኔም ካንቺ በቀር ሌላ ሴት አላውቅም አላት:እርሱአም ወንድሜ ሆይ አምላከ እስራኤል ለኔ ልጅ ቢነሳኝ አንተም እንደኔው ሆነህ ትቀራለህን? ከሌላ ደርሰህ ውለድ እንጂ ብላ ብታሰናብተው እንደዚ ያለ ነገር እንኩአንስ ላደርገው በልቦናዬ እንዳላስበው አምላከ እስራኤል ያውቅብኛል አላት:እሱአም አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን የሚያውቅ የለም:ትላንትና ማታ በህልሜ ነጭ ጥጃ ከማህጸኔ ስትወጣ ያችም ነጭ ጥጃ ሌላ ነጭ ጥጃ ስትወልድ እንዲሁ እስከ 7ት ትውልድ ሲዋለድ ሰባተኛይቱ ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃዋም ፀሃይን ስትወልድ አየሁ አለችው::
እርሱም በጠዋት ከህልም ፈቺ ዘንድ ሂዶ የነገረችውን ሁሉ ነገረው:ያም ህልም ፈቺ እግዚአብሄር በምህረቱ አይቱአቹአል በሳህሉ መግቡአችሁአል 7 አንስት ጥጆች መውለዳቹ 7 ሴቶች ልጆች እና የልጅ ልጆች ትወልዳላቹ ከቤታቹ ሰባተኛይቱ ጨረቃ መውለዱአ ከሰው የበለጠች ከመላእክትም የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላቹ የፀሃይ ነገር ግን አልታወቀኝም አለው:እርሱም የነገረውን ሁሉ ሄዶ ነገራት እርሱአም እንጃ አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን ማን ያውቃል ብላ ዝም አለች:ከዛም ፀንሳ በ9 ወሩአ ሴት ልጅ ወለደች:ስሙአንም ሄሜን ብለው አወጡላት:ሄሜንም አድጋ ለአካለ መጠን ስደርስ አጋብተዋት ሴት ልጅ ወለደች በስምንተኛ ቀኑአም ደርዲ ብለው ስም አወጡላት:ደርዲም አድጋ እንዲሁ ሴት ወለደች እና ቶና አለቻት:ቶናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሲካር አለቻት;ሲካርም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሴትና አለቻት:ሴትናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሄርሜላ አለቻት:ሄርሜላም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ንጽህት ቅድስት ክብርት የምትሆን እመቤታችንን የምትወልደውን ሃናን ወለደች::
ከጴጥርቃና ከቴክታ የተወለዱ 67 ወንዶች ልጆች አሉ የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ትውልድ ለመቁጠር ትንቢት አልተነገረላቸውም ሱባኤ አልተቆተረላቸውምና አልተፃፈም:ይህቺም ሃና በስራት በቅጣት አደገች:ለአእምሮ ስትበቃ አካለ መጠን ስደርስ ከቤተ መንግስት ወገን ከነቅዱስ ዳዊት ወገን ከሆነው(መጽሃፍ ቅዱስ ይገልጸዋል) ከቅዱስ እያቄም ጋር አጋቡአት::እነዚህ ቅዱሳን እያቄም እና ሃና በአንድነት ተጋብተው ሲኖሩ ልጅ አጡ:ከእለታት አንድ ቀን ወደ ቤተ እግዚአብሄር ሂደው ሲፀልዩ ሲያዝኑ ዋሉ:ሃዘናቸው እንዴትስ ነው ቢሉ:እያቄም:-"አቤቱ ጌታዬ ያባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለው አትጣለኝ:አትናቀኝ:ፀሎተን ስማኝ ፈቃዴን ፈጽምልኝ:ለአይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የሚሆን የተባረከ ወንድ ልጅ ስጠኝ" ብሎ ሲለምን ዋለ:ሃናም በበኩሉአ "አቤቱ ጌታዬ የአባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለው:ስማኝ ለአይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የምትሆነኝ የተባረከች ሴት ልጅ የማህፀኔን ፍሬ ስጠኝ" ብላ ስትለምን ዋለች: እንዲ ብለው ስይዝኑ ሲጸልዩ ውለው ርግብ ከልጆቹአ ጋር ስትጫወት አይታ አቤቱ ጌታዬ ለዚች ግእዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሳኅኝ ብላ ምርር ብላ አለቀሰች:እንዲ ብለው ሲያዝኑ ሲፀልዩ ውለው ከዘካርያስ ከሊቀ ካህናቱ ሄደው አቤቱ ጌታችን ሆይ ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተ እግዚአብሄርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን:ሴት ልጅም ብንወልድ ማይ ቀድታ መሶብ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን ብለው ስለት ገቡ::
ዘካርያስም እግዚአብሄር ጸሎታችሁን ይስማላቹ ስእለታችሁን ይቀበልላቹ ጻህቀ ልቦናችሁን ይፈጽምላቹ ብሎ አሳረገላቸው:
ከዚያም በሁአላ ቅድስት ሃና እና ቅዱስ እያቄም እለቱን ራእይ አይተው ነገር አግንተው አደሩ:ራእዩም እንዴት ነው ቢሉ ኢያቄም 7ቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ አላት:ወፍ የተባለው ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:ነጭነቱ ንጽሃ ባህሪው ነው:ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ ማለቱ:የኢያቄምን ባህርይ ባህርይ እንዳደረገው እወቅ ሲል ነው:7ቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ልዩ ልዩ ባህሪው:ምልአቱ:ስፍሃቱ:ርቀቱ:ልእልናው:ዕበዩ መንግስቱ ናቸው:ሃናም እኔም አየሁ አለችው:ምን አየሽ ቢላት:ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማህጸኔ ስትተኛ አየሁ አለችው::ርግብ የተባለች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት:ነጭነቱአ ንጽህናዋ:ቅድስናዋ ድንግልናዋ ነው:ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማህጸኔ ስትተኛ አየሁ ማለቱአ ብስራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን መፀነሱአ ነው:ይህንኑም ራእይ ያዩት ሃምሌ 30 ዕለት ነው::
እነሱም እንዲ ያለ ራዕይ ካየን:ነገር ካገኘን ብለው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም:ፈቃደ እግዚአብሄር ቢሆን ብለው አዳምንና ሄዋንን ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት ብሎ ያበሰረ አምላክ ለኛስ ይልክልን የለምን? ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ 7 ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ:ነሃሴ በባተ በሰባተኛው ቀን ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ዓለሙ ሁሉ ተሰብስቦ ቢመዘን አንድ የራሱአን ፀጉር የማያህል ደግ ፍጥረት ትወልዳላቹህና ዛሬ በሩካቤ ስጋ ተገናኙ ብሎአቹሃል ጌታ ብሎ መልአኩ ለሃና ነገራት በፈቃደ እግዚአብሄር በብስራተ መልአክ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም እሁድ እለት ተፀነሰች(በኦሪት ስርአት እሁድ ዕለት ባል እና ሚስት መገናኘት ልማድ ነበርና):እመቤታችን የተፀነሰች ዕለት አይሁድ ቀንተው ተነሱባቸው ቅናቱ እንዴት ነው ቢሉ:ሳሚናስ የሚባል የጦሊቅ ልጅ ከኤዶቅ ካጎቱ ቤት ሄዶ ሞተ እነርሱም እንቀብራለን ብለው ባልጋ ይዘው ሲሄዱ ከመንገድ አሳረፉት:የሃናም የአጎቱአ ልጅ ነበርና ለማልቀስ ብትደርስ ዘመዶቹአ ሁሉ ተሰብስበው ሲላቀሱ ቆዩአት:እርሱአም አብራ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ብድግ ብሎ ተነስቶ ስብሃት ለኪ ማርያም እሙ ለፀሃየ ጽድቅ ለአብ ሙሽራው ለወልድ ወላዲቱ ለመንፈስቅዱስ ጽርሃ ቤቱ ተፈስሂ ደስ ይበልሽ ብሎ ሰገደላት:አይሁድ ከዛ ነበሩና ምነው ሳሚናስ ምን አየህ? ምን ትላለህ? ቢሉት ከዚች ከሃና ማህፀን የምትወለደው ህፃን ሰማይ ምድርን:እመቅ አየርን የፈጠረ አምላክን ትወልዳለች እያሉ መላእክት ሁሉ ሲያመሰግኑአት ሰማሁአቸው እኔንም ያነሳችኝ የፈወሰችኝ ያዳነችኝ እርሱአ ናት አላቸው በል ተወው ሰማንህ ብለው ቅናት ጀመሩ::
""እመቤታችን እግዝትእነ ማርያም በተፀነሰች በ9 ወር ከአምስት ቀን የግንቦት መባቻ ዕለት ግንቦት 1 ተወለደች::""
እመቤታችን እግዝትእነ ማርያም የተወለደችበት እለት በአባት እናቱአ ቤት ፍስሃ ደስታ ተደረገበት ቤቱንም ብርሃን መላው በስምንተኛውም ቀን ""ማርያም"" ብለው አወጡላት::ስለምን ማርያም ብለው አወጡላት ቢሉ:እነሆ በዚ አለም ከሚመገቡት ሁሉ ምግብ ለአፍ የሚጥም ለልብ የሚመጥን "ማር" ነው:በገነትም በህይወት የተዘጋጁ ጻድቃን ቅዱሳን "ያም" የሚባል ምግብ አላቸው ::ከዚ ሁሉ የበለጥሽ የከበርሽ ነሽ ሲሉ ስለዚህ "ማርያም" ብለው አወጡላት::የእመቤታችን ማርያም ስም ተነቦ ሳይተረጎም ይቀር ዘንድ አይገባምና:-""ማ"" ማለት ማህደረ መለኮት: ""ር"" ማለት ርግብየ ይቤላ: ""ያ"" ማለት ያንቀዓዱ ኃቤኪ ኩሉ ፍጥረት:""ም"" ማለት ምስሃል ወምስጋድ ወምስትሥራየ ኃጥያት ማለት ነው::አንድም "ማርያም" ማለት ልዩ ከጣዖት:ክብርት እምፍጥረታት:ንጽህት እምሃጥያት:መልክ ከደም ግባት የተሰጣት ማለት ነው:ዳግመኛም "ማርያም" ማለት ተፈስሂ ቤተ ይሁዳ ወተሃሠዪ ቤተ እስራኤል ማለት ነው::
አንድም "ማርያም" ማለት መርህ ለመንግስተ ሰማያት ማለት ነው:ይህስ እንዴት ነው ቢሉ:እነሆ ዛሬ በዚህ አለም ለዕውር መሪ በትር እንዲሰጡት ሁሉ እርሱአም በፍቅሩአ:በጣዕመ ፍቅሩአ የሰውን ሁሉ ኃጥያት:ክፋት ፍቃ ከልጁአ ከወዳጁአ አስታርቃ ከገሃነመ እሳት አውጥታ መንግስተ ሰማያት የምታስገባ ስለሆነች ስለዚህ መርህ ለመንግስተ ሰማያት አሉአት::አንድም ማርያም ማለት ሰረገላ ፀሃይ ማለት ነው:አንድም ማርያም ማለት ተላኪተ እግዚአብሄር ወሰብእ ማለት ነው:አንድም ማርያም ማለት ውብህት(ስጥውት) ማለት ነው::
በግንቦት አንድ ቀን እመቤታችን አለምን ልታስምር ከቅድስት ሃና እና ከቅዱስ እያቄም በብዙ ልመና ተገኘች:: 
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅሩአ ጣዕሙአ በረከቱአ ረድኤቱአ አማላጅነቱአ በእውነት በኛ አማላጅነቱአን በምናምን ልጆቹአ ላይ ይደርብን::

https://www.facebook.com/photo.php?fbid=292837507541054&set=a.117306178427522.24396.117298008428339&type=1&theater

LIKE OUR PAGE >>>

Tuesday, December 3, 2013

ህዳር 21







እናታችን ጽዮን

በዲ/ን ኅሩይ ባየ


በቅዱሳት መጻሕፍት ጽዮን የሚለው ቃል ተደጋግሞ በነቢያቱ ተነግሯል፡፡ ሆኖም የጽዮን ትርጉም እንደተነገረበት ዐውደ ትንቢት እንደተሰበከበት መዋዕለ ትምህርት ምስጢሩ ይለያያል፡፡

በዚህ ጽሑፍ በጥቂቱ የምንመለከተው ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ እንዴት እንደመጣች፣ ኅዳር 21 ቀን ስለምናከብረው ዓመታዊ በዓል፣ በታቦተ ጽዮን እና በዘመነ ሐዲስ በተገለጠችው በእመቤታችን በቅድስትድንግል ማርያም ያለውን ምስጢራዊ ትርጉም ነው፡፡ታቦት አንቺ ነሽ» ብሏል፡፡ 

ታቦተ ጽዮን በፈቃደ እግዚአብሔር በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት ለሰው ልጆች ተሰጥታ እስራኤላውያን ሲባረኩባት፣ መሥዋዕታቸውን ሲያቀርቡባት ከእግዚአብሔር ሲታረቁባት ኖረዋል፡፡ከአራት ሺሕ ሦስት መቶ ሃያ ሰባት ዓመተ ዓለም (4327 ዓ.ዓ.) ጀምሮ ለአርባ ዓመታት ያህል እስራኤላውያንን በክህነት ያገለግል የነበረው ካህኑ ዔሊ ዕድሜው ሲገፋ ሁለት ልጆቹን ጠርቶ ምሉዕና ዱግ /ዋናና ምክትል/ አድርጎ ሾማቸው፡፡

በደብተራ ኦሪት ታቦተ ጽዮንን እንዲያገለግሉ የተሾሙት ሁለቱ ወጣት ካህናት /አፍኒን እና ፊንሐስ/ ፈቃደ እግዚአብሔርን ተላልፈው ሦስት ታላላቅ በደሎችን ፈጸሙ፡፡ የመጀመሪያው በደል፤ በሙሴ ሥርዓት በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት በርታ በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት የምትጠፋ መብራት እንድትቀመጥ የተሠራ ሥርዓት ነበር፡፡ ሆኖም አገልግሎት ከሌለ ሲበራ ማደሩ ለምን ? ብለው መቅረዙን አነሡ፤ መብራቱንም አጠፉ፡፡ ሁለተኛ፣ ለራሳቸው ሥጋዊ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው ለመሥዋዕት እንዲሆን ከመጣው እንስሳ ታርዶ ስቡ ሳይጤስ፣ደሙ ሳይፈስ ሥጋውን እየመረጡ ተመገቡ፡፡ሦስተኛ ጸሎት እናደርሳለን ሥርዓተ አምልኮ፣ እንፈጽማለን ብለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይመጡ ከነበሩት እስራኤላውያን ቆነጃጅት ጋራ በዝሙት ወደቁ፡፡ አባታቸው ካህኑ ዔሊም የልጆቹን በደል እያየ እንዳላየ እየሰማ እንዳልሰማ ቸል በማለቱ እግዚአብሔርአዘነ፡፡ በዚህም ምክንያት ፍልስጥኤማውያንን አስነሥቶ በጦርነት ቀጣቸው፡፡

ዕብራውያን በጦርነት ውሎ ያለልማዳቸው በአሕዛብ ተሸነፉ፡፡ ሕዝበ እስራኤልም ግራ ቢገባቸው «ድል የተነሣነው ታቦተ ጽዮንን ይዘን ባለመዝመታችን ነው» ብለው አፍኒን እና ፊንሐስ ጽላቱን እንዲሸከሙ አድርገው ወደ ፍልስጥኤማውያን የጦር ምሽግ ገሠገሡ፡፡ ሆኖም ያሰቡት ሳይሳካ ታቦተ ጽዮን ተማረከች፣ አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ፤ ዕብራውያንም በጦርነቱ ድል ተደረጉ፡፡ፍልስጥኤማውያንም ታቦተ ጽዮንን ማርከው ዳጎን ከተባለው ጣዖታቸው ላይ አስቀመጧት፡፡ በማግስቱ ሲመለሱ ዳጎን ተገልብጦ ታቦተ ጽዮን በላይ ተቀምጣ አገኟት፡፡ በማግስቱም ተመሳሳይ ድርጊት ተፈጽሞ ዳጎን ወድቆና ተሰባብሮ አገኙት፡፡ 1ሳሙ 5÷4 ይኽን በተመለከተ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጽጌ ድንግል ሰቆቃወ ድንግል በተባለው ድርሰቱ፤ 

«ታቦተ አምላከ እስራኤል ጽዮን ዘነገደት ምድረ ኢሎፍሊ፤ 

ወቀጥቀጠቶ ለዳጎን ነፍሳተ ብዙኃን ማህጎሊ፤ 

አመ ነገደት ቁስቋመ በኀይለ ወልዳ ከሃሊ፤ 

ወድቁ አማልክተ ግብፅ መናብርተ ሰይጣን ሐባሊ፡፡ 

ወተኀጉሉ ኲሎሙ ዘቦሙ አስጋሊ. . .፤ 

ወደ ኢሎፍሊ ምድር ተማርካ የሔደች የእስራኤል አምላክ የቃል ኪዳኑ ታቦተ ጽዮን የብዙዎችን ነፍሳት ያጠፋ ዳጎንን ሰባበረችው፡፡ ድንግል ማርያምም ሁሉን ማድረግ ከሚችለው ከልጇ ጋር ግብፅ ወደሚባል ሀገር በሔደች ጊዜ የሐሰተኛ ሰይጣን ዙፋኖች የሆኑ የግብፅ ጣዖታት ፈረሱ ጠንቋይ አስጠንቋይ ያላቸው ሁሉ ዐፈሩ» በማለት በንጽጽር አስቀምጦታል፡፡ ኢሳ 19÷1 ኃይል እና ድል ማድረጉን በዳጎን የጀመረችው ታቦተ ጽዮን የፍልስጥኤማውያንን መንደር በአባርና በቸነፈር በእባጭም መታች፡፡ ሕዝበ ፍልስጥኤምም ታቦተ ጽዮን ወደ እስራኤል ምድር እንድትመለስ አደረጉ፡፡

በእንደዚህ ዓይነት ታላቅ ክብር በሀገረ እስራኤል ትኖር የነበረችው ታቦተ ጽዮን ወደ ሀገራችን ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷ ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ ሐሴት እንዲሰማን ያደርጋል፡፡

የታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት

ከአርባ ሁለት ጊዜ በላይ ስሟ ተደጋግሞ የተጠቀሰው ሀገር ቅድስት ኢትዮጵያ በእግዚአብሔርየተወደደች ለመሆኗ ነቢያቱ መስክረዋል፡፡ ከነቢያት አንዱ አሞፅም፤ «የእስራኤል ልጆች ሆይ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን ?» ብሎ እግዚአብሔር መናገሩን ጽፏል /9÷7/፡፡ ከሁሉም ከፍ ባለመልኩ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት፤ «ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች» ብሎ ሕዝበ ኢትዮጵያ እደ ሕሊናውን እና እደ ልቡናውን ዘወትር በአምልኮተ እግዚአብሔር፣ በጾምና በጸሎት፣ በምጽዋትና በትሩፋት፣ ዘርግቶ በሃይማኖት ጸንቶ፣ በምግባር ቀንቶ የሚኖር በመሆኑ፤ ሕዝቡ ሕዝበ እግዚአብሔር ምድሪቱ ሀገረ እግዚአብሔር ተብለዋል፤ /መዝ.68÷31/፡፡

ለታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ዋናው ምክንያት በእስራኤል እና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው የሠመረ ግንኙነት ነው፡፡ ይኽም በመሆኑ የንግሥት ሳባ እና የንጉሥ ሰሎሞን ግንኙነት ሰፊውን ታሪክ ይዞ ይገኛል፡፡የንግሥተ ሳባ ዕቃ ግምጃ ቤት የነበረው ታምሪን ወደ ኢየሩሳሌም ሔዶ ንጉሥ ሰሎሞን ያሠራውን ቤተ መቅደስ ዓይቶ፣ የሰሎሞንን ጥበባዊ ዝና ሰምቶ በፍጹም መደነቅ ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡ ያየውንና የሰማውን ለንግሥቲቱ አጫወታት፡፡ እሷም የሰማችውን ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ የሰሎሞንን መንፈሳዊና ሥጋዊ ጥበብ ተመልክታ እግዚብሔርን አመስግና ተመለሰች፡፡



ከንጉሥ ሰሎሞን ምኒልክን ፀንሳ ከኢየሩሳሌም ተነሥታ ባሕረ ኤርትራን ተሻግራ፣ ሐማሴን አውራጃ ስትደርስ አሥመራ ከተማ በሚገኘው ማይበላ ከተባለው ቦታ ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ የሕፃኑንም ስም የንጉሥ ልጅ ስትል «እብነ መለክ» አለችው፡፡ ይኽ ስም በዘመን ሒደት ምኒልክ ተብሎ ተለወጠ፡፡



ምኒልክ ተወልዶ በአእምሮ እያደገ ሲሔድ አባቴ ማን ነው ? አድራሻውስ ወዴት ነው ? እያለ ጥያቄ ቢያበዛባት በሃያ ሁለት ዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ላከችው፡፡ ምኒልክም አባቱ ንጉሥ ሰሎሞንን አግኝቶ ሕገ ኦሪትንና የዕብራይስጥ ቋንቋ ሲያጠና ከቆየ በኋላ፤ ዐሥራ ሁለት ሺሕ እስራኤላውያንን አስከትሎ ከምድረ እስራኤል ወደ ኢትዮጵያ ጉዞውን አቀና፡፡



ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋር ለጉዞ የተነሡ ዕብራውያን ከቤተሰቦቻቸው መለየታቸው ሳያሳዝናቸው ከታቦተ ጽዮን መለየታቸው እጅግ ከበዳቸው፡፡ ወዲያው በፈቃደ እግዚአብሔር ታቦተ ጽዮንን ከመንበሯ አንሥተው በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ወደ ኢትዮጵያ ገቡ፡፡



ቀዳማዊ ምኒልክ እና እስራኤላውያን ታቦተ ጽዮንን ይዘው አክሱም የደረሱት ኅዳር 21 ቀን ነበር፡፡ ንግሥተ ሳባም የታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በጣም ስላስደሰታት በክብር ተቀበለቻቸው፡፡ «ወአንበርዋ ውስተ ሕፅነ ደብረ ሀገረ ማክዳ» እንዲል በአክሱም ከተማ መካከል ደብረ ማክዳ /ዛሬ ቤተ ጊዮርጊስ ከሚባለው/ ላይ ደብተራ ኦሪት ሠርተው አስቀመጧት፡፡



አሁን ያለው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በዘመናዊ ዐቅድ የታነፀው የአክሱም ጽዮን ገዳም ቅዳሴ ቤቱ ጥር 30 ቀን 1957 ዓ.ም ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ግርማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ /የታላቋ ብሪታንያ ንግሥት/ እና ልዑል ፊልፕ ከክብር ባለሟሎቻቸው ጋር በተገኙበት ተከብሯል፡፡

ኅዳር ጽዮን በአክሱም

አክሱም ማርያም ጽዮን በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ መሠረታቸው ስትሆን ከተማዋም የኢትዮጵያ ሥልጣኔ መነሻ ናት፡፡ አክሱም በሕገ ልቡና የጸናች፣ ሕገ ኦሪትን የፈጸመች፣ በሕገ ወንጌል ያመነች ናት፡፡ ለዚህም ነው «ሕግ ይወጽእ እምጽዮን፤ ከጽዮን ሕግ ይወጣል» የሚለው ጥቅስ የሚነገረው፡፡

በዓለ ልደትን በላሊበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር፣ ኅዳር ጽዮንን በአክሱም ጽዮን ሲያከብሩት ልዩ የሆነ ሥርዓት ስለሚቀርብባቸው ምእመናን መንፈሳዊ ደስታ ይሰማቸዋል፡፡

ኅዳር 21 ቀን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል ነው ብለን በተለየ መልኩ የምናከብርበት ምክንያት፡- 

1. በብሉይ ኪዳን ታቦተ ጽዮን የፈጸመችውን ልዩ ልዩ ገቢረ ተአምራትን ለማሰብ

2. ቀዳማዊ ምኒልክ ከዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል የበኲር ልጆች ጋር ሊቀ ካህናቱን አዛርያስንና ታቦተ ጽዮንን ይዞ አክሱም የደረሰበት ዕለት በመሆኑ

3. በሦስት መቶ ሠላሳ ዓመተ ምሕረት በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ መንግሥት ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት ይሁን ተብሎ ዐዋጅ የታወጀበት

4. ዘካርያስ በተቅዋመ ወርቅ ምሳሌ ራእይ ያየበት

5. ነቢዩ ሕዝቅኤል በተቆለፈች ቤተ መቅደስ 

6. ዕዝራ በቅድስት ሀገር ምሳሌ ራእይ ያየበት

7. አብርሃና አጽብሃ በወርቅና በዕንቁ ያሠሩት ባለ አሥራ ሁለት ክፍል ቤተመቅደስ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት

8. በዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዮዲት ጉዲት አብያተ ክርስቲያናትን ስታቃጥል ታቦተ ጸዮንን ይዘው ወደ ዝዋይ ሐይቅ ከተሰደዱ በኋላ ዘመነ ሰላም ሲጀመር አክሱም በነበሩ ካህናት አስታዋሽነት ከዝዋይ ወደ አክሱም የገባችበት ዕለት 

በመሆኑ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ከፍ ባለ መንፈሳዊ በዓል እናከብራለን፡፡ ይኽ ሲባል ግን በዓሉ የሚከበረው በአክሱም ጽዮን ማርያም ብቻ ነው ማለት ሳይሆን፤ ታቦተ እግዝእትነ ማርያም ባለችበት ቦታ ሁሉ መከበሩን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ ጋርም የመመኪያችን ዘውድ፣ የመዳናችን ምክንያት፣ የንጽሕናችን መሠረት ስለሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያልተነበየ ነቢይ፣ ያልሰበከ ሐዋርያ፣ ያልተቀኘ ባለቅኔ ከቶ የለም፡፡ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወረደ፣ በቤዛነቱ ዓለምን አዳነ፣ ዳግመኛም በክበበ ትስብእት፣ በግርማ መለኮት ለፍርድ ይመለሳል ብንል ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሥጋ በመሆኑ ያለ ወላዲተ አምላክ ምስጢረ ሥጋዌን፣ ነገረ ድኅነትን፣ ነገረ ምጽአትን ማሰብ ከቶ የማይቻል ነው፡፡

«ዕግትዋ ለጽዮን፤ ጽዮንን ክበቧት» እንዳለ ነቢዩ፤ ዐሥርቱ ቃላት የተጻፈባትን የእስራኤል አምባና መጠጊያ የሆነችውን ታቦተ ጽዮንን ሌዋውያን ከበዋት ውዳሴ ያቀርቡላት እንደነበረው፤ ዛሬም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ካህናትና ምእመናን ከሩቅ እና ከቅርብ ተሰብስበው በማኅሌት፣ በዝማሬ፣ በቅዳሴና በውዳሴ ያከብሯታል፡፡

በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም እና በቃል ኪዳኑ ታቦት መካከል ጥልቅ የሆነ ምስጢራዊ ትምህርት አለ፡፡ /ዘፀ. 25÷9-20/፡፡ ይህቺ የቃል ኪዳን ታቦት በደብተራ ኦሪት በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የኖረች፣ የዮርዳኖስን ባሕር የከፈለች /ኢያ. 3÷14-17/፤ ቅጽረ ኢያሪኮን ያፈረሰች /ኢያ 6÷1-21/፤ ዳጎን የተባለ የፍልስጥኤማውያንን ጣዖት የቆራረጠች /1ሳሙ 5÷1-5/፤ በድፍረት ሊነካ የሞከረውን ኦዛን የቀሰፈች /1ሳሙ 6÷6/፤ በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ተቀምጣ ቤቱን በበረከት የመላች /2ሳሙ 6÷12/፣ ዳዊት የዘመረላት /2ሳሙ 6÷14/፤ ጠቢቡ ሰሎሞን በቤተ መቅደስ በክብር ያኖራት/1ነገ 8÷1/፤ የእግዚአብሔር የክብር መገለጫ ናት፡፡

በታቦተ ጽዮን እና በዘመነ ሐዲስ በተገለጠችው በቅድስት ድንግል ማርያም መካከል ያለውን ረቂቅ እና ድንቅ ምስጢራዊ ንጽጽር አስመልክቶ ሦርያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም፤ «ታቦት በወርቅ ልቡጥ እምኩለሔ ዘግቡር እምዕፅ ዘኢይነቅዝ፤ ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረጸ በው ስጥ በአፍአ በወርቅ የተለበጠ 

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሐ ጠባይዕ ሳያድፍባትና የቅድስና ባሕርይ ሳይጎድፍባት በማየት፣ በመስማት፣ በመዳሰሰ፣ በማሽተት አንዳችም እድፍ ጉድፍ ሳያገኛት በንጽሕናና በቅድስና ጸንታ በኃጢአት ሳትለወጥ ኖራለች፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም፤ «አልብኪ ነውር ወኢምንትኒ ላዕሌኪ፤ ምክንያታዊ ነውር ኃጢአት የሌለብሽ የኃጢአት ሸታ ያልደረሰብሽ ንጽሕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና ክብርት በልዕልና አንቺ ነሽ» /መኃ 4÷7/ ሲል ተናግሯል፡፡

ታቦተ ጽዮን በከበረ ወርቅ እንደተሸለመች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ እና በንጽሐ ልቡና የተሸለመች ያጌጠች መሆኗን ያጠይቃል፡፡

ታቦተ ጽዮን የቃለ እግዚአብሔር ማደሪያ እንደሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያምም ለአካላዊ ቃል ለእግዚአብሔር ወልድ ማደሪያ ሆናለች፡፡ ይኽንንም ቅዱስ ኤፍሬም ሲያስረዳ፤ «ኮንኪ ታቦቶ ለፈጣሬ ሰማያት ወምድር ፆርኪዮ በከርስኪ ተሰዓተ አውርኃ አንቲ ማእምንት ለዘኢያገምርዎ ሰማያት ወምድር፤ ድንግል ማርያም ሆይ ሰማይና ምድርን ለፈጠረ አምላክ ለእርሱ ማደሪያ ሆንሽ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀንሸ ቻልሽው ተሸከምሽው ሰማይና ምድር የማይወስኑትን ለመወሰን የታመንሽ አንቺ ነሽ» ብሎ ተቀኝቶላታል፡፡ ስለሆነም ከብሉይ ኪዳን እስከ ሐዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበትን የቸርነት በዓል እግዚአብሔርበፈቀደልን ቦታ ሆነን ስናከብር ከእኛ የሚጠበቀውን በጎ ነገር እያሰብን በተግባርም እየገለጥን ከበዓሉ ረድኤትና በረከት ተሳታፊ እንሆን ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት የእናቱ የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡

የቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እና ምልጃ አክሊልና ጉልላት በሆነው በእናታችን በወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት ሁላችንንም ይማረን፡፡


/ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ህዳር 15-30 ቀን 2003ዓ.ም/



LIKE OUR PAGE >>>

https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

Friday, February 22, 2013

ኪዳነ ምህረት (የካቲት 16)



ኪዳነ ምህረት ማለት የምህረት መሐላ ማለት ነው፡፡ 33 በዓላተ እግዝእትነ ድንግል ማርያም አንዱ ነው፡፡ እመቤታችንም ከጌታችን መቃብር እየሄደች በምትለምንበት ጊዜ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ምን ልታመጣብን ነው በማለት ሊጣሏት ሲመጡ ጌታችንም ከዓይናቸው ሰውሯታል አይሁድም ጠባቂ ቢያቆሙ እመቤታችን ዕለት ዕለት መሄዷን አላቋረጠችን እመቤታችንም እንዲህ ብላ ስትጸልይ ልጄ ወዳጄ ሆይ ከስጋዬ ስጋ ከነፍሴ ነፍስ ነስተህ ሰው በመሆንህ ዘጠኝ ወር 5 ቀን በቻለችህ ማሕጸኔ ከአንተ ጋር ሀገር ለሀገር ስለ መሰደዴ መትተህ ልምናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ አለች በዚህ ጊዜ ንውጽውጽውታ ሆነ መቃብራት ተሰነጣጠቀ ጌታችንም እልፍ ከእልፍ መላዕክቱ ጋር መጥቶ ሰላም ለኪ ማርያም ምን እንዳደርግልሽ ትለሚኚኛለሽ አላት፡፡ እርሷም መታሰቢያዬን ያደረገውን ስለ ስሜ ለችግረኛ የሚራራውን በስሜ ቤተ ክርስቲያን ያነጻውን መባዕ የሰጠውን ከሃይማኖት ከፍቅር ጽናት ልጁን በስሜ የጠራውን ሁሉ ማርልኝ ከሞተ ስጋ ከሞተ ነፍስ አድንልኝ አለችው፡፡ ጌታችንም ይህን ሁለ እንዳደርግልሽ መሐልኩ ለኪ በርእስየ ወበ አቡየ ሕያው ወበመንፈስ ቅዱስ ብሎ ቃል ገብቶላት አርጓል፡፡

ሌላው በላዔ ሰብ በአማርኛ ሰው በላ ማለት ነው፤ ትክክለኛ ስሙ ግን ስምዖን ይባላል ቅምር በሚባል አገር የሚኖር እጅግ ባለጸጋ ነበር፤ እንደ አብርሃም እንግዶችን እየተቀበለ ድሆችን እየመገበ የሚኖር ጻድቅ ነበር፤ ሰይጣን በዚህ ስራው ቀናበት ሊፈትነውም በሦስት አረጋዊ ሽማግሌዎች ስላሴ ነን ብሎ ተገለጠለት ልክ እንደ አብርሃም፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ሰይጣን የብርሃን መልአክ መስሎ ይመጣል እንዳለ፤ እርሱም ሥላሴ መስለውት ተቀበላቸው ተንከባከባቸውም፤ ምግብ አቀረበላቸው ምግብ አንበላም የምንጠይቅህን ግን ትፈጽምልን ዘንድ ቃል ግባልን አሉት ቃል ገባላቸው እንግዲያውስ የምትወደን ከሆነ አንድያ ልጅህን ሰዋልን አሉት፤ መጀመሪያ ደነገጠ ኃላ  አብርሃም ልጁን ሊሰዋ አልነበረምን እኔንም ሊፈትኑኝ ይሆናል ብሎ ለማረድ ተዘጋጀ፤ተው የሚለው ድምጽ አልሰማም፤ አረደው አወራረደው ይዞላቸው ቀረበ፤ መጀመሪያ ቅመስልን አሉት ቀመሰው ወዲያው እነዚያ ሰዎች ተሰወሩበት እርሱም አህምሮውን ሳተ ተቅበዘበዘ ከዚያ በኃላ ምግብ አላሰኘውም የሰው ስጋ እንጂ መጀመሪያ ቤተሰቦቹን በላ ከዚያም ጓደኞቹን ጦርና የውኃ መንቀል ይዞ ከቤቱ ወጣ ያገኘውን ሰው እየገደለ ይበላል የበላቸው ሰው ቁጥር 78 ደረሰ፤ በመንገድ ተቀምጦ የሚለምን በደዌ የተመታ አንድ ደሃ አገኘ ሊበላው ወደ እርሱ ተጠጋ ግን ቁስሉን አይቶ ተጸየፈው፤ ደሃውምስለ እግዚያብሔር ከያዝከው ውኃ አጠጣኝአለውዝም በል ደሃብሎት አለፈ፤ኸረ በውኃ ጥም ልሞት ነው ስለ ጻድቃን ስለ ቅዱሳንአለው አሁንም ዝም ብሎት ሄደ ለሦስተኛ ጊዜስለ አዛኝቷ ስለ እምዬ ማርያምአለው፤ ሰውነቱን አንዳች ነገር ወረረውአሁን የጠራከውን ስም እስኪ ድገመው  ስለ ማን አልከኝአለው፤ ስለ አዛኝቷ ስለ እመቤቴ ማርያም አለው፤ ይህቺስ ደግ እንደሆነች በምልጃዋም ከሲኦል እንደምታወጣ ህጻን እያለው እናትና አባቴ ይነግሩኝ ነበር፤ በል እንካ አለው እጁን ዘረጋለት ጥርኝ ውኃ ጠብ አደረገለት ወደ ጉሮሮው አልወረደም የተሰነጠቀ እጁ ውስጥ ገባ እንጂ፤ በለዔ ሰብ ከዚያች ደቂቃ በኃላ አዕምሮው ተመለሰለት እንዲህም አለበአንድ ዋሻ ውስጥ ገብቼ ስለ ኃጢያቴ አለቅሳለሁ ስጋዬ ከአጥንቴ እስኪጣበቅ እጾማለሁ ወዮሊኝ ወዮታም አለቢኝ አለ፤ ወደ ዋሻ ገባ ምግብ ሳይበላ ውኃም ሳይጠጣ 21 ቀን ኖሮ በርሃብ ሞተ ይላል ተአምረ ማርያም። ጨለማ የለበሱ ሰይጣናት እያስፈራሩ እያስደነገጡ ነፍሱን ወደ ሲኦል ሊወስዷት መጡ፤ እመቤታችን ፈጥና በመካከላቸው ተገኘች፤ ልጄ ወዳጄ ይህችን ነፍስ ማርሊኝ አለችው እናቴ ሆይ 78 ነፍሳትን የበላ እንዴት ይማራል አላት፤ የካቲት 16 ቀን በጎለጎታ የገባህልኝ ቃል ኪዳን አስብ ስምሽን የጠራ መታሰቢያሽን ያደረገን እምርልሻለው ብለኸኝ የለምን አለችው፤ እርሱም እስኪ ይህቺን ነፍስ  በሚዛን አስቀምጧት አለ ቢያስቀምጧት ጥርኝ ውኃው መዝኖ ተገኘ፤ ስላቺ ስል ምሬታለው ሰባት ቀን ሲኦልን አስጎብኝታችሁ ወደ ገነት አግቧት አላቸው። ቦታሽ እዚህ ነበር እያሉ ሲኦልን አስጎብኝተው ወደ ገነት አገቧት። ልመናዋ ክብሯ የልጇም ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁን። ተአምረ ማርያም
ድንግል ማርያም በቃል ኪዳኗ አትለየን!


Tuesday, January 29, 2013

ጥር 21 የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት

“ ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ”
ጥር 21 በዓለ አስተርእዮ (የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት)
እንኳን ለዚህች ታላቅ በዓሏ አደረሰን፡፡ 

ወላዲተ አምላክ ምንም እንኳን የአምላክ እናት ብትሆንም ሞተ ሥጋ ለሁሉም ዕጣ ፈንታ በመሆኑ በስድሳ አራት አመቷ ከሞት ወደ ሕይወት ከመከራ ወደ ደስታ የተሸጋገረችበት ዕለት ነው፡፡
ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ያሬድም “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ” ትርጉሙ ሞት ለማናኛቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል፡፡ በማለት አደነቀ፡፡ በመሆኑም በዓሉ የወላዲተ አምላክ በዓለ ዕረፍት ከመሆኑ የተነሳ ታላቅ በረከት የሚያስገኝ ስለሆነ በየዓመቱ ይከበራል፡፡
... የእረፍቷስ ነገር እንደምን ነው ቢሉስድሳ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ ጥር 21 እሁድ ቀን ጌታ እልፍ አዕላፋት መላዕክቱን አስከትሎ መጥቶ እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ አላት፡፡ ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማህጸኔ ተሸክሜ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁミ አለችው፡፡ በሲዖል የሚሰቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ እናቴ ሆይ ሞትሽ ለእነዚህ ቤዛ ይሆንላቸዋል አላት፡፡ እኚህን ከማርክልኝስ ይሁን አለችው፡፡ ቅድስት ሥጋዋን ከቅስስት ነፍሷ ለይቶ በቃለ አቅርንት በዝማሬ መላእክት አሳረጋት፡፡ ደቀመዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ እመቤታችሁን ቅበሩ አላቸው፡፡ ባባ ይዘወት ወደ ጌሰማኒ ሲስደት አይተው ልጇን ተነሳ አረገ እያሉ ሲውኩን ይኖራሉ አሁን ደግሞ እሷን ተነሳች አረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለም ብሎ ኑ እናቃጥላት ተባባሉ፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ታውፋንያ ዘሎ ያልጋውን ሸንኮር ያዘ፡፡ የታዘዘው መላእክት መጥቶ በሰይፍ ሁለት እጁን ቀጣው፡፡ በድያለሁ ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት ድኖለታል፡፡ ከዚህ ቦሃላ ዮሐንስን ጨምሮ ከመካከላቸው ነጥቆ በእጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል፡፡
አንድም በዓሉ-፡ እግዚአብሔር ወልድ በሰውነት ተወልዶና ማንነቱ በይፋ ታውቆ በተገለጠበት በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ስለሚከበር የ“አስተርእዮ ማርያም” ተብሏል፡፡ አስቀድመው አሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል ወደ ዓለም ሁሉ ተበትነው ነበርና በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ሁሉም ደመናን ጠቅሰው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ መርቶ አመጣቸው እንጂ ለምን እንደመጡ አያውቁም ነበር፡፡ እመቤታችንም ለምን እንደመጡ ጠየቀቻቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም፡- “ጸጋን የተመላሽ ቅድስት ሆይ! የመምጣታችን ምሥጢርማ እኛ አንቺን እንጠይቅ እንጂ አንቺም እኛን ትጠይቃለሽን? ሁላችንም ለምን እንደመጣን አናውቅም፡፡ ለምሳሌ እኔ አስቀድሜ በአንጾክያ ነበርኩኝ አሁን ግን እነሆ እዚህ ነኝ፡፡ ለምን እንደመጣሁኝ ግን አላውቅም” አላት፡፡ እርሷም ሁሉም በአጠገቧ በተሰበሰቡ ጊዜ የሚሆነውን ነገር አስቀድማ ከልጇ ከወዳጇ አውቃ ተዘጋጅታ ነበርና ለምን እንደመጡ (ዕረፍተ ሥጋዋን ለማየት እንደሆነ) ነገረቻቸው፡፡ ሌሊቱንም በሙሉ በጸሎትና በማኅሌት ደግሞም በዝማሬ ሲያመሰግኑ አደሩ፡፡ ከዚህ በኋላ የተወደደችው እናት በረከቷን አሳድራባቸው በሰላም አንቀላፋች፡፡ ነፍሷም በዐብይ ዕልልታና በታላቅ ምስጋና በመላእክት እጅ ወደ አምላኳ ሄደች፡፡ ኋላ ሐዋርያቱ ዮሐንስን ሲያገኙት፡- “እመቤታችን እንደምን ሆነች?” አሉት፡፡ እርሱም “በገነት በዕጸ ሕይወት ሥር ዐርፋለች” አላቸው፡፡ የቀሩት ሐዋርያት “ዮሐንስ ያን ድንቅ የእግዚአብሔርን ሥራ አይቶ እኛስ ሳናይ እንዴት እንቀራለን?! አቤቱ ለእኛም ቸርነትህን አድርግልን” ብለው በነሐሴ መባቻ በአንድነት ሆነው ወደ ፈጣሪያቸው የሚቀርብ የአንድ ሳምንት ጾምና ጸሎት ጀመሩ፡፡ በሁለተኛው ሱባዔ ማብቂያ ዕለት ነሐሴ 14 ቀን እሑድ የእመቤታችንን ትኩስ ሥጋ መልአኩ ከገነት አምጥቶ ለሐዋርያቱ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ልመናቸው ስለ ተፈጸመላቸው ፈጣሪያቸውን በጸሎት አመስግነው በዚያችው ዕለተ እሑድ ቅዱስ ሥጋዋን ወስደው ቀብረውታል፡፡ እርሷም በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን ማክሰኞ ተነሥታለች፡፡ ትንሣኤዋ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ- እንደ ልጇ ትንሣኤ” ያሰኘው ይህ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይታ የመነሣቷ እውነታ ነው፡፡ የአዛኚቱ ድንግል አማለጅነትና በረከት አይለየን፡፡ ሁላችንም ባለንበት ይህ ታላቅ በዓሏን እያሰብን ጸልየን የበረከቷ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን አሜን፡፡ መልካም በዓል !!

Tuesday, December 18, 2012

THE GLORY OF THE HOLY VIRGIN MARY (ክብረ ቅድስት ድንግል ማርያም)

THE GLORY OF THE HOLY VIRGIN MARY  (ክብረ ቅድስት ድንግል ማርያም)

  Taken from: THE ETHIOPIAN ORTHODOX TEWAHEDO CHURCH FAITH, ORDER OF WORSHIP AND ECUMENICAL RELATIONS

  
 The holiness, virginity, covenant and intercession given to Our Holy Lady, the Virgin Mary is quite widely taught and deeply rooted in the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church.


 Holiness


 Our Lady, the Virgin Mary, who conceived and gave birth to Jesus Christ in virginity is free from the original sin derived from the descendants of Adam, clean from any sins of the flesh or soul; embedded in the conscience of God before the time of her birth, free and protected from human desires and frailties, and the choicest from among the chosen. Such is the Virgin Mary – Pure and Holy of Holies (Songs 4:7)


  She is graced and honored by the Saint Angles as indicated in Luke 1:28-30. Here it is written that the angel said to her, “Greetings, you who are highly favored the Lord is with you.”


 Our Lady, who is blessed in body, spirit and flesh, was chosen by God to be the abode of His Son and the dwelling of the Spirit (Heryacos Liturgy 45; Psalm 132:13).


 Purity of the flesh, purity of the soul and purity of the heart all belong and reside in Our Lady.


 Virginity


 One of the distinctive attributes of the Virgin Mary that makes her the select among the select and the honored among the honored is the fact that she conceived and gave birth to Christ in virginity (Matthew 1:18-20). Our Lady the Virgin Mary is virgin before she conceived the Lord, during her period of conception, after conception, before delivery, during delivery and after delivery. Our Lady, apart from all women is pure and virgin in thought, word and deed (Tewodotos 53:22). The word virgin rightfully denotes her sanctity and purity. No female, either past or present, has combined virginity with motherhood; as well as motherhood with virginity as Our Lady St. Mary.


 Our Lady is a virgin in perpetuity (The Liturgy of Basil 73; Ezekiel 44:3; Song 4:15) and the Evangelist Luke says, “God sent the angel Gabriel…to a virgin… The virgin’s name was Mary.” (Luke 1:27). Ephraim also says that Our Lady is the pride of all virgins (Ephraim 6:3).


 Honor of the Virgin


  Our Lady, the Virgin St. Mary, is the most prominent from all angels. She is pre-eminent in honor and intercession from all saints. Other ladies are honored for having given birth to prophets, saints and martyrs. But Our Lady is honored as the Mother of God. Hence, the honor accorded to the Virgin Mary is below the Creator but above His Creatures. She is, therefore, revered as such (John Chrysostomos, The Faith of the Fathers, Chapter 28:36-39). St. Luke in 1:30 says, “…Mary, you have found favor with God.”


 Devotion


 Several prophecies have been written about the honor and high esteem of Our Lady. Prophets have told about the virgin giving birth to Christ (Psalms 132:13; Isaiah 7:14; Ezekiel 44:3).


 Church fathers, have through the centuries glorified her guided by the Holy Spirit, about her ever sanctity and purity; and have also praised her in their writings and songs. Fathers such as St. Ephraim, Abba Heriakos, St. John Chrysostoms and Abba Giorgis of Gascha have venerated her greatly. The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church reveres her by speaking and writing on her sanctity and purity. The life of Our Lady is associated with God’s act of redemption.


 As Noah’s Ark became the cause for saving the lives of his family as well as himself and thus saving the human race from extinction; Our Lady, the Virgin St. Mary, is also God’s trusted repository for being the cause for God’s act of redemption by giving birth to the Savior Messiah. According to the doctrine and faith of our Church, the Virgin Mary is venerated as being above God’s creatures but below God.


 In our hymns and liturgy, we recite Mary’s praise right after reciting the Holy Trinity’s.


 The sacrifices that Christ paid for the human race for himself becoming man: when we think of this in conjunction with the trials He went through, i.e. the fact that He was born in the manger, that He was shrouded in a rug, that He was banished, driven away from place to place, His suffering, His crucifixion and death; we cannot separate the Holy Virgin Mary from these travails.


  Who else, outside of Mary has been honored thus, “Greetings, you who are highly favored…you have found favor with God…the Holy Spirit will come upon you, and the power of the Most High will overshadow you.” (Luke 1:28-35)


 From among her relatives, St. Elizabeth, inspired by the Holy Spirit said to Mary, “Blessed are you among women, and blessed is the child you will bear!”. Besides, she bore witness to the fact that Mary is the Mother God by exclaiming, “But why am I so favored, that the mother of my Lord should come to me!” (Luke 1:43). She thus confirmed that what was said by God about Mary would be accomplished and that she would believe in and carry out God’s Will.


 When St. Elizabeth heard Mary’s greetings, the baby leaped in her womb (St. John) and St. Elizabeth was filled with the Holy Spirit. Thus was it confirmed that He who was born of the Blessed Virgin Mary was God, the Son of God. Our Lady has herself said that, “From now on all generations will call me blessed.” (Luke 1:48; Psalm 45:17). On this basis, all Christians who believe in Her Son regard her as the basis of their purity, as a pride of their virginity, and a cause for their salvation.


 The Covenant of Intercession


  Our Church teaches about the covenant of intercession given to Our Lady with Biblical truth and absolute Apostolic tradition. Our Lady, the Virgin Mary has obtained the honor of motherhood and the covenant of intercession from her Son, Jesus Christ. Our Lord Jesus Christ performed the first miracle through the intercession of Our Lady, by changing water into wine at a wedding at Cana of Galilee (Feast of the First Miracle, John 2:1-5).


 When the Lord was on the Cross, He said, “Dear woman, here is your son,” (John 19:26), when He saw Our Lady the Virgin Mary standing there; and He also said, “here is your mother,” to His Disciple and thus gave her to the custody of the Church. She received an irreversible word from Jesus that all who beg for mercy and forgiveness in her name believing that she is the mother of Christ shall have their supplications answered.


 Hence the Church, preserving the word of her Son, Jesus Christ, reveres St. Mary as:


 · The abode for the Holy Spirit


 · The Mother of God


 · The Eternal Virgin


 · The Holy of Holies


 And since the Holy Bible attests to these honors of hers, and since Holy Angels and the sons of Adam revere her, the Church therefore honors, thanks, and implores in her name (Liturgy of Jacob of Serough 99)


 Our Lady, the Virgin St. Mary, departed on January 21 (Eth. Calen), aged 64, according to the tradition (Tewfit) that has been passed on from the Apostles. Angels carried her body to paradise and placed it under the plant of life in paradise.


Having thus been there in paradise till Nehase (August) 14 of that same year, angels carried and gave her body back to the Apostles and they laid it to rest at Gethsemani. On the third day of her burial, on the 16th of Nehase (August), she rose from the dead and her Assumption to heaven in glory took place. Thus is what the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church believes and teaches about the death, resurrection and Assumption of the Virgin St. Mary. Nehase 16th (August) of every year is thus commemorated with great ceremony by the Church (Synaxrium, August 16th Eth. Calen).