በጐንደር ክፍለ ሀገር ስማዳ ወረዳ ዳህና ሚካኤል በተባለው ቦታ ከአባታቸው ከዘክርስቶስና ከእናታቸው ከእግዚእ ክብራ ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው 3ዐ ዓመት እስከሚደርስ ከቤተሰቦቻቸው ትምህርተ ሃይማኖትንና ግብረ ገብን ሲማሩ ከቆዩ በኋላ በ124ዐ ዓ.ም. ይኼንን ዓለም በመተው ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ገቡ፡፡ በደብረ ዳሞ ገዳም መነኰሳቱን እየረዱ፣ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን እያጠኑ፣ ትምህርተ ቅዲሳት መጻሕፍትን እየገለበጡ ለሰባት ዓመታት ከቆዩ በኋላ የደብረ ዳሞ 3ኛ አበ ምኔት ከሆኑት ከአባ ዮሐኒ ምንኩስናን ተቀበሉ (1247 ዓ.ም.)፡፡
አንድ ቀን ሌሊት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደርሳቸው መጥቶ (ገድልህና ትሩፋትህ በዓለም ሕዝብ ሁሉ ትተህ የስምህ መክበርያ ወደሆነው ሐይቅ ወደ ተባለው ሥፍራ ሂድ) አላቸው፡፡ አባታችን ‹‹ቦታውን እንዴት ዐውቀዋለሁ›› በማለት ቢጠይቁት ‹‹ተነሥ! ጉዞህን ጀምር ቦታውን እኔ አሳይሃለሁ›› አላቸው፡፡ አባ ኢየሱስ ሞዓ በመልአኩ እንደታዘዙት ከበአታቸው ተነሥተው ተከተሉት፡፡ የብዙ ወራት መንገድ የሆነው ጐዳናም በስድስት ሰዓት አለቀላቸው፡፡
በዚያን ወቅት ከሐይቅ ገዳም በስተ ሰሜን ወደነበረው ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ደረሱ፡፡ ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከመግባታቸውም በፊት ለ6 ወራት ያህል በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን አገልግለዋል፡፡ ያገለግሉበት በነበረው ቤተ ክርስቲያን ቀን ቀን ሕዝቡን ሲያስተምሩ በመዋል ሲመሽ ወደ ሐይቁ በመግባት ሲጸልዩ ያድሩ ነበር፡፡ በሐይቅ እስጢፋኖስና በዙርያው ለነበሩ አበውም ማታ ማታ አንድ ብርሃን ወደ ሐይቁ ሲገባ ጠዋት ጠዋትም ሲወጣ ይታያቸው እንደነበር ዛሬ በገዳማቸው የሚገኘው ገድለ ኢየሱስ ሞዓ ያስረዳል፡፡
በመጨረሻም በገዳሙ አባቶች ልመናና
በልዑል እግዚአብሔር ትዕዛዝ ወደ ሐይቅ ገዳም ገብተው አበምኔት ሆኑ፡፡ ሐይቅ እስጢፋኖስ ማለት ከደሴ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ
የሚገኝ ሲሆን የመሰረቱት ካልዕ ሰላማ የተባሉ ግብጻዊ ጻድቅ ናቸው፤ ገዳሙን ከሰሩ በኃላ የማንን ታቦት እናስገባ ብለው ሲያስቡ
ቶራ የምትባል እንስሳ ጭነት ተጭና ከመካከላቸው ተገኘች፤ ጭነቱን አውርደው ቢያዩት በሐር ጨርቅ የተጠቀለለ ሁለት ታቦት አገኙ
አንዱ የእስጢፋኖስ አንዱ የጊዮርጊስ " ይህንን ታቦት በእ...የሩሳሌም የሚኖሩ የተሰወሩ ቅዱሳን ከእግዚያብሔር ታዘው
የላኩት ነው" የሚል ጽሑፍም አገኙ ይላል። ይህ ከሆነ ከ 400 ዘመን በኃላ ነው አባ እየሱስ ሞኣ ወደዚህ ቦታ የመጡት
ለ 52 ዓመት ቀን ቀን መንፈሳዊ ስራቸውን ይሰራሉ ሌሊት ሌሊት ሐይቁ ውስጥ ቆመው ሲጸልዩ ያድራሉ
አባ ኢየሱስ ሞዓ በሐይቅ እስጢፋኖስ በአበምኔትነት በቆዩባቸው 45 ዓመታት ከየገዳማቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመገልበጥና በማስገልበጥ ብሎም በማሰባሰብ የመጀመርያው ዘመናዊ የቤተ ክርስቲያን ቤተ መጻሕፍት በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ በዚሁ ገዳም ውስጥም የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ቋሚ ት/ቤት በማቋቋም 8ዐዐ መነኮሳትን በትምህርተ ሃይማኖት አሠልጥነው በንቡረ ዕድነት ማዕረግ በመላ ሀገሪቱ እንዲሠማሩ አድርገዋቸዋል፡፡
ከተማሪዎቻቸውም መካከል አቡነ ተክለ ሃይማኖት (ዘደብረ ሊባኖስ)፣ተክልዬን ያመነኮሱ አባት ናቸው። አባ ኂሩተ አምላክ (ዘጣና ሐይቅ)፣ አባ ጊዮርጊስ (ዘጋሥጫ)፣ አባ ዘኢየሱስ፣ አባ በጸሎተ ሚካኤል፣ አባ አሮን (ዘደብረ ዳሬት) ጥቂቶች ናቸው፡፡ አፄ ይኩኖ አምላክንም በትምህርተ ሃይማኖት ያነፁት እርሳቸው ናቸው፡፡
እንደዚህ
ነው የመነኮሳት
አባት እንጦንስ
ነው እንጦንስ
መቃርስን ወለደ
መቃርስ ጳኩሚስን
ጳኩሚስ አቡነ
አረጋዊን አቡነ
አረጋዊ አባ
ዮሐኒን አባ
ዮሐኒ የሐይቁን
አባ እየሱስ
ሞአን ወለዱ
አባ እየሱስ
ሞኣ ደግሞ
ተክልዬን ወለዱ።
በዮዲት ጉዲት ተጐድታ የነበረችው ሀገራችን ዳግም የወንጌሉ ብርሃን እንዲበራባት ሊቃውንት እንዲይነጥፉባት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዳይቆነጻጸሉ፣ መነኮሳት አባቶች ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ወርደው ገዳማትን እንዲያስፋፉ ያደረጉት አባ ኢየሱስ ሞዓ ናቸው፡፡ በተለይም የሐይቅ እስጢፋኖስ ያፈራቸው 8ዐዐ ሊቃውንት በመላዋ ሀገሪቱ በመሠማራታቸው ዛሬ የምናያቸውን አብዛኞቹን ገዳማትና ቅዱሳት መጻሕፍት አቆይተውናል፡፡
አባታችን አባ ኢየሱስ ሞዓ ለ45 ዓመታት ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከቆዩ በኋላ ኀዳር 26/1292 ዓ.ም. በዕለተ እሑድ ዐረፉ፡፡ በዚያች ዕለትም በቦታው የታየው ብርሃን ሀገሪቱን መልቷት እንደነበረ ገድላቸው ይመሠክራል፡፡
የቅዱስ አባታችን ምልጃና በረከታቸው በሁላችን ላይ ይደርብን፡፡
አሜን
ምንጭ
ገድለ ኢየሱስ ሞዓ
No comments:
Post a Comment