Thursday, November 22, 2012

ነገረ ማርያም /ክፍል አንድ/



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

  ይህ ነገረ ማርያም ትምህርት ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ከፅንሰቷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ስላለው የሕይወቷን ዝክረ ታሪክ፣ ስለ እመ አምላክነቷ፣ ስለ ዘላለማዊ ድንግልናዋ፣ በነገረ ሥጋዌ ስላላት ሱታፌ (ድርሻ) ስለ ንጽሕናዋና ስለ ተሰጣት ክብር የምናጠናበት የሃይማኖት ትምህርት ክፍል ነው፡፡



የክርስትና እምነት በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምላካዊ የቤዛነት ሥራ፣ በፈሰሰው ወርቀ ደም የተመሠረተ የሕይወትና የድኅነት መንገድ ነው፡፡ ስለዚህም በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ነገረ ድኅነት (Soteriology) የትምህርተ ሃይማኖት ሁሉ አክሊል (ጉልላት) ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና ሥምረት በጥንተ ተፈጥሮ የተፈጠረው የሰው ልጅ ዳግመኛ በሐዲስ ተፈጥሮ በመታደሱ ምክንያት በመንፈስ ልደት ከብሯል፡፡ “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው አልፎአል፤ ሁሉም እንሆ አዲስ ሆኗል” /2ቆሮ.5፡17/፤ “አባ አባት ብለን የምጮህበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ” /ሮሜ.8፡15/፤ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ ለእነርሱ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” /ዮሐ.1፡12/፤ “ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ” /2ጴጥ.1፡23/ የሚሉት ቃላተ መጻሕፍት ይህን እውነት የሚያስረዱ ናቸው፡፡
  ይህ አምላካዊ የቸርነት ሥራም አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተዋሕዶ በነሣው ሥጋና ነፍስ የተከናወነ ነው፡፡ ስለሆነም የዚህ ፍሬ ድኅነት ተካፋዮች የሆንን ክርስቲያኖች ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስን ስለወለደች፣ የሰው ልጅ የመዳን ቀን ከሰው ልጆች በቅድሚያ ስላወቀች፣ ለእግዚአብሔር የማዳን ሥራ መሣርያ በመሆን አዳኙን መሲሑን ስለወለደች፣ የእግዚአብሔር ታማኝ የምሥጢር መዝገብ ስለሆነች ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ከፅንሰቷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ስላለው የሕይወቷን ታሪክ፣ ስለ እመ አምላክነቷ፣ በነገረ ድኅነት ውስጥ ስላላት ወሳኝ ሚናና ከፍተኛ ሱታፌ፣ ስለ ዘላለማዊ ድንግልናዋ፣ ስለ ንጽሕናዋና ስለ ተሰጣት ክብር በሚገባ ጠንቅቀን ማወቅና መረዳት ይገባናል፡፡
  ወደ ኋላ መለስ ብለን የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ስንመረምር ስናጠና ከአንደኛው እስከ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ነገረ ክርስቶስን (Christology) ከነገረ ማርያም (Mariology) ጋር ያለውን ጥልቅ የምሥጢር ግንኝነት በመረዳታቸው ምሥጢረ ሥጋዌን ከማስተማራቸው አስቀድሞ ነገረ ማርያምን በጥልቀት ይማሩና ያስተምሩ እንደ ነበር እናስተውላለን፡፡ ይህ ጥልቅና ድንቅ ምሥጢር ስፍሐ አእምሮ ያላቸውና የነገረ መለኰትን ትምህርት (Theology) በቅጥነተ ኅሊና የመመርመርና የማራቀቅ ተውህቦና ክኅሎት የተሰጣቸው እነዚህ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ባስተማሩት ሕያው ትምህርትና በጻፏቸው አያሌ የአዕማደ ምሥጢር (Pillars Of Mystery) መጽሐፎቻቸው ከርሠ ምሥጢር እንደ ዕንቁ ፈርጥ ሲያበራ የምናገኘው ነው፡፡ ሊቃውንቱ በትምህርታቸው ሁሉ ነገረ ማርያም የሃይማኖት ክፍል (Dogma) መሆኑን አብራርተው ገልጠውታል፡፡ ምክንያቱም “ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አካላዊ ቃል 5500 ዘመን ሲፈጸም ያለ አባት ከቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና ተወለደ፤ እርሱ በእውነት የባሕርይ አምላክ ነው፤ እርሷም በእውነት የአምላክ እናት ናት” ብሎ መመስከር ሃይማኖት ነውና፡፡ ማንኛውም በድንግል ማርያም ላይ የምንናገረው ነገር ነገረ ክርስቶስንና ነገረ ድኅነትን የሚነካ በመሆኑ ሃይማኖት ነው፡፡
  ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት የሆነችው ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን ይዛ በዘወትር ሥርዓተ አምልኮቷ ጊዜ በምትገለገልባቸው የተለያዩ የጸሎትና የቅዳስያት መጻሕፍት ሁሉ የነገረ ማርያም አስተምህሮዋን በስፋትና በጥልቀት ትመሰክራለች፡፡ ይልቁንም ደግሞ ፍጹም ሰማያዊና መንፈሳዊ የሆነው ሥርዓተ ቅዳሴዋ በማኅፀነ ድንግል ማርያም የተጀመረውን፣ በድንግልናዊ ልደት የተገለጠውን፣ በቀራንዮ አደባባይ የተፈጸመውንና በዕለተ ትንሣኤ የተረጋገጠውን የድኅነተ ዓለም ጉዞ ዘወትር የሚያዘክርና የነገረ ማርያምና የነገረ ድኅነት የምሥጢር መድብል ነው፡፡ በዚህም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሁለንተናዊ ሕይወት ከእግዚአብሔር የማዳን ሥራ (Soteriology) ጋር በእጅጉ የተዋሐደና በቀጥታ የተገናኘ መሆኑን እናስተውላለን፡፡
  ክብሯ ከመላእክትና ከደቂቀ አዳም ሁሉ ከፍ ከፍ ያለ መሆኑ፤ የባሕርይ አምላክ አካላዊ ቃል ክርስቶስን በኅቱም ድንግልና ፀንሳ በኅቱም ድንግልና የወለደች በመሆኗ ወላዲተ አምላክ (Theotokos- Mother Of God)፣ እመ እግዚአብሔር ጸባኦት፣ እመ ብርሃን፣ ማኅደረ መለኰት እያለች ሥያሜዋን ታስተምራለች፡፡ በሥጋዋ በኅሊናዋ ድንግል በክልኤ የተባለች ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ፀኒስ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ፀኒስ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ፀኒስ ድኅረ ወሊድ ጽንዕት (Perpetual Virgin) ናት፡፡ በመሆኑም አምላክን ስትወልደው ማኅተመ ድንግልናዋ አለመለወጡ አምላክም ሰው ሲሆን ባሕርየ መለኰቱ ላለመለወጡ፣ ዳግመኛም ድንግል ወእም ስትባል መኖሯ አምላክ ወሰብእ ሲባል የመኖሩን ይህንን ታላቅ የሥጋዌ ምሥጢር ያወቅንባት የተረዳንባት መሆኗን ታስረዳለች፡፡
  በተጨማሪም ቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና እያለች ከጡቶቿ ወተት ተገኝተው በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግብ መጋቤ ፍጥረታት አምላክን የመገበች፤ እሳታውያን የሚሆኑ ኪሩቤል ሱራፍኤል በፍርሐት በረዐድ በመንቀጥቀጥ ሁነው ዙፋኑን የሚሸከሙት እሳተ መለኰት ጌታን ዘጠኝ ወር ከአምስተ ቀን በማኅፀኗ የተሸከመች፣ በክንዷ የታቀፈች፣ በጀርባዋ ያዘለች፣ እናትነትን ከድንግልና፣ አገልጋይነትን ከእናትነት፣ ወተትን ከድንግልና ጋር አጣምራ የያዘች ምልዕተ ክብር ምልዕተ ጸጋ መሆኗን ዓለም እስከሚያልፍ ድረስ ስትመሰክር ትኖራለች፡፡  

Source: http://mekrez.blogspot.com 

No comments:

Post a Comment