መግቢያ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
፩፡፩ ነገር
ማለት፡- በቁሙ ሲተረጐም ቃል ፥ ንባብ ፥ ወሬ ፥ የቃል ፍሬ ፥ ከድምጽ ጋር የሚስማማ ፤ በጽሕፈት ፥ በአንደበት
የሚገለጥ ፤ ከልብና ከአፍ የሚወጣ ፥ በአንደበት የሚነገር ማለት ነው። ይኸውም መንገርን ፥ መስበክን ፥
ማስተማርን ፥ ማውራትን ፥ ማብሠርን ፥ ነገርን ሳያቋርጡ እንደ ውኃና ዝናም ማፍሰስን ፥ ማውረድን ፥ ማንጐድጐድን ፤
አሳብን ምሥጢርን በቃል መግለጥን ፥ በንባብ ማስጌጥን ፤ መልክ እያወጡ ፥ ምሳሌ እየሰጡ ማነጽና መቅረጽን
የሚያመለክት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ « ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና
ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፡፡ » በማለት የዕብራውያን መልእክቱን የጀመረው ለዚህ ነው። ዕብ ፩፡፩ ። ግዕዙ «
በብዙኅ ነገር » ይለዋል፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ሙሴን፦ «እግዚአብሔር አምላክ በስድስተኛው ቀን ፍጥረቱን ሁሉ ፈጥሮ
እንደጨረሰ የፍጥረትን ነገር ሁሉ ጻፍ፤ » ብሎለታል፡፡ ግዕዙም የሚለው፦ « ጸሐፍ ኲሎ ነገረ ፍጥረት፤ » ነው።
ኲፋሌ ፪፥፬። በተጨማሪም የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመልከት።
- « ኢትኅፈር ነገረ ጌጋይከ ፤ የኃጢአትህን ነገር መናገር አትፈር ፤ » ሢራ ፬ ፥ ፳፮
- « መኑ ይክል ነጊረ ምሕረቱ ጥንቁቀ ፤ የምሕረቱን ነገር ጠንቅቆ መናገር የሚቻለው ማነው ? » ሢራ ፲፭ ፥ ፭
- « ዘአቅደመ ነጊረ በአፈ ነቢያት ፤ በነቢያት አፍ አስቀድሞ ያናገረው ፤ » ሮሜ ፩ ፥፪
- « ለምንት ትነግር ሕግየ፤ ለምን አንተ ሕጌን ትናገራለህ ? » መዝ ፵፱ ፥ ፲፭
- « ፈሪህየ ከመ እንግርክሙ ዘእኄሊ ፤ ዕውቀቴን የማስበውን እነግራችሁ ዘንድ ፈርቼ ዝም አልሁ ፤ » ኢዮ ፴፪ ፥
፮
፩፥፪ ፡- ቅዱስ ማለት በቁም ሲተረጐም ፦ የተቀደሰ ፥ ክቡር ፥ ምስጉን ፥ ልዩ ፥ ምርጥ ፥ ንጹሕ ፥ ጽሩይ ማለት ነው። ለብዙ ሲሆን ቅዱሳን ይባላል። በአጠቃላይ « ነገረ ቅዱሳን » የሚለው ሲተረጐም፦ የቅዱሳንን ነገር መናገር ፥ መስበክ ፥ ማስተማር ፥ ማብሠር ፥ መጻፍ ይሆናል።
፪፡- ቅዱስ ማነው?
ከሁሉ በላይ ቅዱስ የሚባለው እግዚአብሔር ነው። ጥንትም ፥ ዛሬም ፥ ለዘላለምም (ቅድመ ዓለም ፥ ማዕከለ ዓለም ፥ ድኅረ ዓለም) ቅዱስ ነው። በቅድስናም የሚመስለው ማለትም የሚተካከለው የለም፡፡ ነቢዩ አሳይያስ « እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ ፤ » በማለት የነገረን ይኽንን ነው ። ኢሳ ፵ ፥ ፳፭ ፡፡
፪፥፩ ስሙ ቅዱስ ነው ፤
የእግዚአብሔር
ስም ፍጡራን ከሚጠሩበት ስሞች ሁሉ የተለየ ነው። ባሕርዩን ግብሩን የሚገልጥ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «
ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስም » ያለው ለዚህ ነው። « ወተወከልነ በስሙ ቅዱስ በቅዱስ ስሙ ታምነናልና ፤» እንዲል ይህ
ስም መታመኛ ነው። መዝ ፴፪ ፥ ፳፩ ጠላቶቻችንን የምንወጋው ፥ በላያችን ላይ የቆሙትን የምናዋርደው በስሙ ነው።
መዝ ፵፫ ፥፭። ቅዱስ ዳዊት፡- ንብ ማርን
እንደሚከብ የከበቡትን አሕዛብ ያሸነፋቸው ፥ በእሳት እንደተያያዘ ደረቅ የእሾህ ክምር ያነደዳቸው ቅዱስ በሆነው
በእግዚአብሔር ስም ነው። መዝ ፩፻፲፯ ፥፲። በጐልያድ ፊት በቆመ ጊዜም « አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ
ትመጣብኛለህ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም
እመጣብሃለሁ።» ብሎታል። በጦር ተወግቶ ፥ በሰይፍ ተመትቶ ፥ በፈረስ በሰረገላ ተገፍትሮ የማይወድቀውን ጐልያድን
በእግዚአብሔር ስም በጠጠር ጥሎታል። ፩ኛ ሳሙ ፲፯ ፥ ፵፭ ።
በአዲስ
ኪዳንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስሙ አጋንንትን እንደሚያወጡ ለደቀመዛሙርቱ
ተናግሮላቸዋል። ማር ፲፮ ፥፲፯ ። ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ በቤተ መቅደስ ደጅ ያገኙትን አንካስ በስሙ
አርትተውታል። የሐዋ ፫ ፥፮ ። አይሁድ በተደነቁ ጊዜም « በስሙም በማመን ይህንን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ
ስም አጸናው ፤ » በማለት መስክረውላቸዋል። የሐዋ ፫፥፲፮ ። በኢዮጴ ጣቢታ ከሞት ልትነሣ የቻለችው ቅዱስ ጴጥሮስ
በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለቀሰቀሳት ነው። የሐዋ ፱፥፴። « ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት
ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ፤ » በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰከረለት ቅዱስ ጳውሎስም
ጠንቋዩን በርያሱስን በጌታ ስም ጨለማ አልብሶታል። የሐዋ ፲፫ ፥፲። የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባትንም ሴት
ፈውሷታል። የሐዋ ፲፮ ፥፲፮ ።
፪፥፪ ባሕርዩ ቅዱስ ነው ፤
የእግዚአብሔር
ባሕርይ ልዩ ነው። የባሕርይ መገለጫዎቹም ብዙ ናቸው። እግዚአብሔር ፈጣሪ ፥ጌታ ፥ አምላክ ፥ ንጉሥ ነው ፤ ሁሉን
የያዘ ሁሉን የጨበጠ ነው፤ ሁሉን የጀመረ ሁሉን የጨረሰ ነው ፤ ከዓለም አስቀድሞ የነበረ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር
ዘለዓለማዊ ነው፤ የሚሳነው የሌለ ሁሉን ቻይ ነው ፤ ምሉዕ በኲላሄ ነው ፤ ዐዋቂ ፥ ጥበበኛ ፥ ሕያው ፥ ኃያል ፥
ረቂቅ ፥ መሐሪና ቅዱስ ነው ፤ ፈታሒ በጽድቅ ኰናኒ በርትዕ ነው ፤ መፍቀሬ ሰብእ ነው ፤ መዓቱ የራቀ ምሕረቱ
የበዛ ትእግሥተኛ ነው ፤ መምህር ፥ ብርሃን ፥ አዳኝ ፥ መጋቢ ፥ ጠባቂ ፥ ረዳት ፥ ባዕለጸጋና አባት ነው።
ቅዱሳን
መላእክት የባህርዩን ቅዱስነት አውቀው፦ « ቅዱስ ፥ ቅዱስ ፥ ቅዱስ ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ
ከክብሩ ተሞልታለች ፤ » እያሉ በአንድነት በሦስትነት ያመሰግኑታል። ኢሳ ፮ ፥፫። እሥራኤል ዘሥጋ ከባርነት ቤት
የታደጋቸውን እግዚአብሔርን ፦ « አቤቱ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማነው? በምሥጋና የተፈራህ ፥ ድንቅንም
የምታደርግ ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማነው ፤ » እያሉ ዘምረውለታል። ዘጸ ፲፭ ፥ ፲፮። ነቢዩ
ኢሳይያስ እግዚአብሔርን « የእስራኤል ቅዱስ » ብሎታል። ኢሳ ፭ ፥ ፲፮ ፣ ፵፯ ፥ ፬። በአጸደ ነፍስ ያሉ
ሰማዕታትም፦ « ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ፤ ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ
እስከመቼ አትበቀልም። » ሲሉ ተሰምተዋል ። ራእ ፮፥፱-፲፩ ።
No comments:
Post a Comment