Tuesday, November 20, 2012

የእመቤታችን እናት ቅድስት ሐና


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
 
ህዳር 11 

በዚህች ቀን የእመቤታችን እናት ቅድስት ሐና አረፈች፤  የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ቴክታ በጥሪቃ ይባላሉ፤ ይህ ቀራቸው የማይባሉ ባለጸጎች ነበሩ፤ ብዕላቸውም የወርቅ፣ የብር፣ የፈረስ፣ የበቅሎ፣ የሴት ባሪያ፣ የወንድ ባሪያ ነው፡፡ ከወርቁ ብዛት የተነሣ እንደ አምባር እንደ ቀለበት እያሠሩ፤ ከበሬው ከላሙ ቀንድ ያደርጉት ነበር፡፡ ይህን ያህል አቅርንተ ወርቅ፤ ይህን ያህል አቃርንተ ብሩር ተብሎ ይቈጠር ነበር እንጂ፤ የቀረው አይቈጠርም ነበር፡፡ ከዕለታት ባንደኛው በጥሪቃ ከቤተ መዛግብት ገብቶ የገንዘቡን ብዛት አይቶ፤ቴከታ እኔ መካን፤ አንቺ መካን ይህ ሁሉ ገንዘብ ለማን ይሆናል?” አላትእግዚአብሔር እንጂ ከኔ ባይሰጥህ ወይ ከሌላ ይሰጥህ ይሆናል፤ አግብተህ አትወልድምን?” አለችው፡፡ይህንስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃልአላት፤ በዚህ ጊዜ አዘኑ፤ ወዲያው ራእይ አይተዋል፤ ነጭ እንቦሳ ከበረታቸው ስታወጣ፣ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ስታደርስ ስድስተኛይቱ ጨረቃን፣ ጨረቃ ፀሐይን ስትወልድ አይተው፥ በሀገራቸው መፈክረ ሕልም /ሕልም ተርጓሚ/ አለና ሂደው ነገሩት፤ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ፤ ጨረቃይቱ ከፍጡራን በላይ የምትሆን ልጅ ትወልዳላችሁ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም እንደ ነቢይ እንደ ንጉሥ ያለ ይሆናልአላቸው፡፡ እነርሱምጊዜ ይተርጉመውብለውት ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ፀነሰች፤ ወለደች ስሟን ሄኤማን አለቻት፤ ሄኤማን ማለት ረካብኩ ስእለትየ ረከብኩ ተምኔትየ /የፈለግሁትን የለመንኩትን አገኘሁ/ ማለት ነው፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፣ ቶና ሲካርን፣ ሲካር ሄርሜላን፣ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና አካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት::እያቄምና ሐና ደጋግ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም ነበሩ በንጽህና በቅድስና የሚኖሩ ልጅ ግን አልነበራቸውም ህዝቡም ቅድስት ሐናን ይህቺ የበቅሎ ዘመድ ቢወልዷት እንጂ የማትወልድ፤ እግዚያብሔር እኮ ያደረቃት በኃጢያቷ ነው እያሉ ይዘልፏት ነበር ወደ ቤተ እግዚያብሔር መባ ይዘው ሲሄዱ አይቀበለቸውም ነበር፤ በዚህም ሲያዝኑ ኖሩ ልጅ እንዲሰጣቸውም እግዚያብሔርን ዘወትር ይለምኑት ነበር፤ በኃላም እግዚያብሔር ጎበኛቸው ነሐሴ በባተ 7ኛው ቀን ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ዓለሙ ሁሉ ተሰብስቦ ቢመዘን አንድ የራሷን ጸጉር የማያህል ደግ ፍጥረት ተወልዳለችሁ ብሎ ቅዱስ ገብርኤል አበሰራቸው፤ ሐና ጸነሰች ይህም በአገሬው ታወቀ ሊጠይቋት የሚመጡ ማህጸኗን እየዳሰሱ ይፈወሱ ነበር፤ አይናቸው የበራላቸውም ነበሩ፤ ግንቦት 1 ቀን ሊባኖስ ተራራ ላይ በነብያት ብዙ የተባለላት የድህነታችን መጀመሪያ የንጽህናችንም መሰረት የሆነችውን እመቤታችንን ወለደች፤ቅድስት ሐና በቅድስና በንጽህና ኖራ በዛሬዋ ዕለት አረፈች፤ይህች ቅድስት እናት ኢትዮጰያ ውስጥ በስሟ በርካታ ቤተክርስቲያን አላት አዲስ አበባ ውስጥ ቀደምቱ ኮተቤ የሚገኘው ኢያቄም ወሐና ነው በዛሬዋ እለት በደማቁ ተከብሮ ይውላል። በረከቷን ያድለን።


No comments:

Post a Comment