ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ማለት ነው፡፡ቦታው ከኢየሩሳሌም በስተምስራቅ የሚገኝ የወይራ ዛፍ የበዛበት ተራራ ሲሆን ስሙም ከወይራ ዛፉ:-ደብረ ዘይት (የወይራ ዛፍ ተራራ) በመሰኘት ተገኝቷል። በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ደብረ ዘይት በዓል ሆኖ የሚከበርበት ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረዘይት ተራራ ላይ ሳለ ለቅዱሳን ደቀመዛሙርቱ ስለ ዓለም ፍጻሜ እና ስለ ዳግም ምጽአቱ ስላስተማራቸዉ በጌታችን ትምህርት መሰረት ነገረ ምጽአቱን (የመምጣቱን ነገር) እንድናስታዉስ ወይም እያሰብን እንድንዘጋጅ ለማድረግ ነዉ።
ጌታችን “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያዉቅ የለም” ማቴ. 24፡36 ብሏል። ይህን ማለቱም በየዘመኑ የሚነሱ ክርስቲያኖች ሩቅ ነዉ ብለዉ እንዳይዘናጉ ጊዜዉ ሲቀርብ የሚነሱት ደግሞ ደረሰብን ብለዉም እንዳይሸበሩ/እንዳይታወኩ ለመጠበቅ ነዉ። ከላይ እንደጠቀስነው ጌታችን በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸዉ ወደ እርሱ ቀርበዉ “የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድር ነዉ? አሉት።” ማቴ. 24፡3 እርሱም በስፋትና በጥልቀት ስለ ዓለም መጨረሻና ስለ ዳግም ምጽአቱ ምልክቶች አስተማራቸዉ። ከነዚህምዋና ዋና የሆኑትን ምልክቶች ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታቸዋለን።
1. የምጥ ጣር መጀመሪያዎች ይታያሉ
ምጥ ሲመጣ አስቀድሞ የምጡ መጀመሪያ ሕመም (ጣር) እንዳለ ሁሉ የዓለምም ፍጻሜ በጣር ነዉ የሚጀምረዉ። ይህንንም ጌታችን በግልጽ አስረድቶናል፦ ጦርና የጦር ወሬ መሰማት፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግስትም በመንግስት ላይ መነሳት፣ ርሃብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ መታየት ለዓለም ፍጻሜ የምጥ ጣር መጀመሪያዎች ናቸዉ። እነዚህ ነገሮች በሁሉም ቦታ በአንድ ጊዜ ላይከሰቱ ይችላሉ፤ ነገር ግን በልዩ ልዩ ቦታዎች ለብዙ ዘመናት ታይተዋል፤ እየታዩም ናቸዉ።
2. ስለ ስሜ በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ስሜ (የክርስቶስ ተከታዮች/ ክርስቲያኖች በመሆናችሁ) በዓለም ዘንድ ትጠላላችሁ ብሎናል። ዓለም ክፉ ስለሚሠራ የጥሩ ነገር ተቃራኒ ሆኖ ለብዙ ዘመናት ቆይቷል። ጌታችን “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለመጣ ሰዎችም ሥራቸዉ ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ፍርዱ ይህ ነዉ። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፣ሥራዉም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እዉነትን የሚያደርግ ግን ሥራዉ በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።” ዮሐ. 3፡19-21 እንዳለንበክፉ ሥራ ዉስጥ ያለዉ ይህ ዓለም በጎ ሥራ የሚሠሩትን የክርስቶስን ተከታዮች ይጠላል። ጨለማ ብርሃንን ብርሃንም ጨለማን እንደሚጠላ፤ይህ ዓለም እኛን እንዲጠላን፣እኛ ክርስቲያኖች ደግሞ ይህንን ዓለም ልንጠላው ይገባል።
አሁን ባለንበት ዘመን ክርስትና እየተጠላ፣ እየተናቀ ነዉ ያለዉ። “ባደጉት” ዓለማት ባዶ አብያተ መቅደሶች ቀርተዉ እነሆ እንመለከታቸዋለን፤ ትዉልዱ በዓለም ስሜትና በሥጋ ፈቃድ ብቻ እየሄደ ነዉ።ክርስቲያን ነን በሚሉትም አውሮፓውያን ዘንድ የአንገት በላይ (የማስመሰል) ክርስትና እንጂ እንደ ቅዱስ ቃሉ የሚጓዝ አማኝ ማግኘት አይቻልም። እዉነተኞች አይወደዱም፤ ይገፋሉ፤ ይናቃሉ። ሁኔታዉ የዘመኑ ፍጻሜ እጅግ እየቀረበ መምጣቱን በእርግጥ ያስረዳል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህም በላይ፦ ስለ ስሜ ለመከራ አሳልፈዉ ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችሁማል ብሏል። ክርስቲያን በመሆናቸዉ ብቻ ማንንም ሳይበድሉ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ በልዩ ልዩ ሀገራት ክርስቲያኖች ሰማእትነትን እስከ አሁን ድረስ እየተቀበሉ ነው፡፡ቅዱስ ጳዉሎስ “ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ” ሮሜ 8፤36 እንዳለዉ። ይህ በቅዱሱ በክርስቶስ ስም መጠላትና መከራ መቀበል ከዓለም የሚጠበቅ የፍጻሜዉ ዘመን ምልክት መሆኑን አዉቀን መዘጋጀትና ከሐዋርያዉ ጋር “በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።” ሮሜ 8፤37 እያልን በእምነታችን ጸንተን መጋደል ይገባናል።
የክርስቲያኖች ቁጥር እያነሰ መምጣት፣ የአብያተ ክርስቲያናት መዘጋት፣ ሰዉ ሰዉ የሚያሰኘዉን ክብርና ሞገስ ትቶ በግብሩ እንስሳትን ሲመስል፦ የቅድስና ሕይወት ሲጠላና ሲናቅ፤ በአንጻሩ ደግሞ የሰዉ ልጅ ለረከሰዉ ለዚህ ዓለም ምኞትና ፈቃድ ሲገዛ ስናይ የዚህ ዓለም ፍጻሜ ጊዜዉ እየደረሰ መሆኑን አዉቀን፤ ኖኅ በብዙ ኃጢአተኞች መካከል ቢኖርም ራሱን በቅድስና ጠብቆ እንደኖረ (ዘፍ.6-8)፤ ሎጥም እንዲሁ በብዙ ኃጢአተኞች መካከል ሲኖር በነርሱ ኃጢአት እንዳልተባበረ (ዘፍ. 19) ከዚህ ዓለም ክፉ ሥራ ተለይተን ራሳችንን በቅድስና በመጠበቅ እንጋደል።ዓለሙ ስለ እምነታችን ቢጠላንም እኛም ስለ ክፉ ሥራዉ ንቀነው መኖር የግድ መሆኑን እንወቅ እንጂ ስለ እምነት፣ ስለ ቅድስናም ከዓለም በጎ ነገር አንጠብቅ። በተለያዩ ሁኔታዎች የሚደርሱብንን ፈተናዎች ሁሉ በትዕግስት እንቀበላቸዉ እንጂ በማማረር አንዘን፤ ምክንያቱም ስለ ስሜ በዓለም ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ ተብለናልና።
3. የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰዉ ስፍራ ይቆማል
ዓለም እራሱን በማርከስ ብቻ ሳይወሰን በፍጻሜ ዘመን በተቀደሰዉ ስፍራ እንኳን ሳይቀር የጥፋትን ርኩሰት ያቆማል። የተቀደሰዉ ስፍራ የተባለዉ በተቀደሰ ሃይማኖት የሚኖሩትን ሀገራት፣ ሕዝቦች የሚመለከት ነዉ። እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉትን ሀገራት ዲያብሎስ በመልእክተኞቹ ላይ አድሮ በብዙ ርኩሰት ተፈታትኗቸዋል፤ እየተፈታተናቸውም ነው። የየሀገራቱን እምነትና ታሪክ ለማጥፋት ጥሯል፤ ብዙዉንም የቅድስና ሥርዓት በርዞአል፤ የቻለዉንም ከነጭራሹ አጥፍቶታል። አሁን እንኳ አምልኮተ እግዚአብሔር በሚፈጸምባቸዉ ቅዱሳት መካናትና ገዳማት ሳይቀር በልዩ ልዩ ምክንያት የጥፋት ርኩሰት አዉጇል። ይህም የፍጻሜ ዘመኑ አንዱ ምልክት ስለሆነ አንባቢዉ ያስተዉል እንደተባለ የዘመኑን መፍጠን የጊዜዉን መድረስ በመረዳት መዘጋጀት ይገባናል።4. ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉ
ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት በየዘመኑ ተነስተዉ እዉነተኛይቱን ቤተ ክርስቲያን ታግለዋታል፤ ሊያጠፏት ባይችሉም እንኳን ብዙ ልጆቿን ነጥቀዉ አጥፍተዋቸዋል። የነዚህን ሐሰተኞች ሠራተኞች አመጣጥ ከባድ የሚያደርገዉ በተኣምራትና በድንቅ ምልክቶች መምጣታቸዉ ነዉ። ጌታችን እንደተናገረ “ቢቻላቸዉስ የተመረጡትን እንኳን እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ።” ስለዚህ በምትሐታዊ ምልክቶቻቸዉ የብዙ የዋሐንን ልብ በማታለል ከተቀደሰ እምነታቸዉ እያስኮበለሉ አጥፍተዋቸዋል፤ በማጥፋትም ላይ ይገኛሉ። ስለዚህም ሐዋርያዉ ቅ/ዮሐንስ “ወዳጆች ሆይ፦ መንፈስን ሁሉ አትመኑ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነዉ እንደሆነ መርምሩ “ 1ዮሐ. 4፡ 1-3 አለን። ቅዱስ ጳዉሎስም “የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸዉን እየለወጡ ዉሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞ ሠራተኞች ናቸዉ። ይህም ድንቅ አይደለም ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለዉጣልና።” 2ቆሮ. 11፡13-15 ብሏል። ሐዋርያት ሁሉ በየመልእክቶቻቸዉ ከሐሰተኞች አስተማሪዎች እንድንጠበቅ ደጋግመዉ አሳስበዋል። ብዙ ሰዉ ግን በየዋሕነት ስለሚጓዝ የነዚህ ተኩላዎች ሰለባ ሆኗል።
ጊዜዉ ክፉ ነዉና የሐሰተኞች ነቢያት መረብ ጠልፎ ወደ ሐሰተኞች ክርስቶሶች እንዳይወስደን በጥንቃቄ መጓዝ ይጠበቅብናል። ሐዋርያዉ ቅዱስ ይሁዳም በመልእክቱ ቁ .3 “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።“ ሲል እንደመከረን በተቀደሰ እምነታችን እስከመጨረሻ ለመጽናት እንጋደል።
5. የሰዉ ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ይመጣል
ክቡር ዳዊት በትንቢት “እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ፤ ወአምላክነሂ ኢያረምም። እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል፤ አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም።” መዝ. 49፡3 እንዳለ ጌታችን በብዙ ክብርና በብዙ ኃይል ከሰማይ መላእክት ጋር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። በዚያን ጊዜ ከመጀመሪያዉ ሰዉ ከአዳም ጀምሮ እስከ መጨረሻዉ ሰዉ ድረስ ሁላችንም በሕይወተ ሥጋ በነበርንበት ጊዜያችን የሠራነዉን ሥራ ይዘን በፊቱ እንቀርባለን (2ቆሮ. 5፡10)። ጌታችንም በጎ የሠሩትን ቅዱሳን በቀኙ፤ ክፉ የሠሩትን ኃጥአንን በግራዉ ያቆማቸዉና ፍርዱን ያስተላልፋል(ማቴ. 25፡31 እስከ ፍጻሜ)።
በዚህ ዓለም ፈቃድ የተጓዙ ኃጥአን ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጉስቁልና ይጣላሉ። በዚህ ዓለም ክፉ ሥራ መንፈሳቸዉን እያስጨነቁ በእምነትና በቅድስና የኖሩ ጻድቃን ደግሞ በደስታ እየዘመሩ ወደማታልፈዉ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ይገባሉ።
ከዚያ በኋላ ሐዘን የለም፤ ሀብታምና ድሃ የለም፤ኃይለኛና ደካማ የለም፤ በማያልቅ ደስታ ለዘላለም እንደ ቅዱሳን መላእክት ሕያው ሆኖ መኖር እንጂ።
ያን ጊዜ የእኛ እጣ በየት ይሆን?
በቀኙ ለመቆም እንዲያበቃን ዛሬ እንጋደል። የቅዱሳን ሐዋርያት መልእክት ፦
“ወደ እግዚአብሔር መንግስት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል…” ሐዋ. 14፡22 እንዲሁም፦
“ጻድቅ በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመጸኛዉና ኃጢአተኛዉ ወዴት ይታይ ዘንድ አለዉ?” 1ጴጥ.4፡18 የሚል ነዉ!
እንግዲህ እጅግ ባጭሩ የደብረ ዘይትን በዓል የምናከብረዉ እነዚህን እንድናስታዉስና “ድልዋኒክሙ ንበሩ:- ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” በተባልነው መሰረት ንስሐ ገብተን፤ ሥጋወ ደሙን ተቀብለን፤መልካም ፍሬ አፍርተን ሁልጊዜም የተዘጋጀን ሆነን እንድንጠብቅ ነው።
በቀኙ ለመቆም እንዲያበቃን የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን የርኅርኂተ ኅሊና የድንግል ማርያም አማላጅነት፣የቅዱሳን ሁሉ ረድኤት አይለየን፤ አሜን።
Source : http://www.mkeurope.org/am/spirituality/21-debre-zeit
ተዋህዶ-ሀይማኖታችን: ደብረ ዘይት- አምስትኛው ሳምንት >>>>> Download Now
ReplyDelete>>>>> Download Full
ተዋህዶ-ሀይማኖታችን: ደብረ ዘይት- አምስትኛው ሳምንት >>>>> Download LINK
>>>>> Download Now
ተዋህዶ-ሀይማኖታችን: ደብረ ዘይት- አምስትኛው ሳምንት >>>>> Download Full
>>>>> Download LINK