Thursday, March 10, 2016

ቅዳሴ


ቅዳሴ በሥርዓተ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት በኅብረት የሚጸለይ የኅብረት ጸሎት ነው፡፡ ከፀሎቶች ሁሉ የላቀ የፀሎት ክፍል ነው፡፡ በቅዳሴ ጊዜ ፭ቱ ምሥዋዕቶች ተሞልተው ይገኙበታል እዚህንም ፭ቱን መሥዋዕቶች ማንኛውም ክርስተያን ለፈጣሪው የሚያቀርበው ነው፡፡
፩. የቁርባን መስዋዕት፡- በፀሎተ ቅዳሴ ጊዜ ውስጥ ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኮት ወይኑ ተለውጦ ደመ መለኮት የሚሆነው በቅዳሴው ፀሎት ነው ሳናስቀድስ አንቆርብምና የቁርባን መስዋዕት የሚፈጸመው በሥርዓተ ቅዳሴ ብቻ ነው፡፡ መስዋዕቱም በቤተልሔም ይዘጋጃል በቤተክርስቲያን ውስጥ በቤተ-መቅደስ ውስጥ ደግሞ ይቀርባል ወይም ይታደላል፡፡ ጌታችን ሲወለደ በቤተልሔም ተወልዶ ቀራንዮ ለዓለም ሁሉ መስዋዕት ሆኗልና ቀራንዮ በተባለች በቤተክርስቲያን ቅዱሱ መስዋዕት ለሕዝብ ይታደላል፡፡

፪. የከንፈር መስዋዕት፡- ካህኑ፣ ዲያቆኑና ሕዝቡ በመቀባበል በአንድነት ምስጋና ለፈጣሪያቸው የሚያቀርቡበት የከንፈራችን ፍሬ የሚሰዋበት የፀሎት ክፍል ፀሎተ ቅዳሴ ነው፡፡፫. የመብራት መስዋዕት፡- በቅዳሴ ጊዜ የሚበራው ጦፍ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የሚሰጥ የመብራት መስዋዕት ነው፡፡ ምሳሌነቱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው ይህውም ጌታችን ጨላመ ለሆነ ዓለም ብርሃን ሆኖ ብርሃንን ሊያበራ ወደ ዓለም መቷልና ነው፡፡

፬. የዕጣን መስዋዕት፡- የዕጣን ፀሎት ካህኑ ብቻ የሚያጥነው ሲሆን ይህውም በማዕጠንቱ አማካኝነት ቅዱሱን እጣን በመንበሩ፣ በቅዱሳን ስዕላቱ፣ በሕዝቡ መካከል ያጥናል ይህውም የሕዝቡን ፀሎት ወደላይ በደሥላሴ መንበር ይዞ ይወጣል በሰማይም ያሉ ቅዱሳን መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሥላሴን መንበር እንደሚያጥኑ ሁሉ በምድርም ያለው ካህን የሰማያዊው ምሳሌ ነውና በምድር ያውን መንበር በማጠን ለእግዚአብሔር የዕጣን መስዋዕት ያቀርባል፡፡

፭. የሰውነት መስዋዕትነት፡- በቅዳሴ ጊዜ አብዛኛውን ሰዓት ሙሉውን ማለት ይቻላል በመቆም የሚፀለይ የፀሎት ክፍል ነው፡፡ በመሐል 2 ጊዜያት ብቻ የስገዱ ትዕዛዝ ሲተላለፍ ሕዝቡ ሁሉ ፊቱን ወደ ፈጣሪው አዞሮ እራሱን አዋርዶ ይሰግዳል በእግዚአብሔር ፊት መቆምም ሆነ መስገድ ለእግዚአብሔር የሚሰጥ የሰውነት መሥዋዕት ነው፡፡


ይህ የፀሎት ክፍል (ቅዳሴ) በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላ
፩. የዝግጅት ክፍል
፪. የንባብና የትምህርት ክፍል
፫. ፍሬ ቅዳሴ እዚህ ፍሬ ቅዳሴያት እንደየበዓሉ ይለዋወጣተሉ ብዛታቸውም ፲፬ ናቸው እነዚህም፡-

፫.፩. ሥርዓተ ቅዳሴ
፫.፪. ቅዳሴ ዘሐዋርያት
፫.፫. ቅዳሴ እግዚእ
፫.፬. ቅዳሴ ማርያም
፫.፭. ቅዳሴ ዘዮሐንስ ወልደ ነጓድጓድ
፫.፮. ቅዳሴ ዘሠለስቱ ምዕት
፫.፯. ቅዳሴ ዘአትናቴዎስ
፫.፰. ቅዳሴ ባስልዮስ
፫.፱. ቅዳሴ ጎርጎርዮስ
፫.፲. ቅዳሴ ዘኤጲፋንዮስ
፫.፲፩. ቅዳሴ ዘዮሐንስ አፈወርቅ
፫.፲፪. ቅዳሴ ዘቄርሎስ
፫.፲፫. ቅዳሴ ዘያዕቆብ ዘሥሩግ
፫.፲፬. ቅዳሴ ዘዲዮስቆሮስ


የጌታችን በዓል ከሆነ … (ቅዳሴ እግዚእ)
የጌታችን ምጽአት፣ ጶጉሜ እሁድ ቀን ከዋለች ሰንበት … (ቅዳሴ አትናቴዎስ)
የእመቤታችን በዓል ከሆነ ቅዳሴ ማርያም … (ጎሳ ልብየ ቃለ ሰናየ)
የመላእክትና የሐዋርያት በዓል ከሆነ … (ቅዳሴ ዘያዕቆብ ዘሥሩግ)
ከዘመነ ልደት እስከ ዘመነ ግዝረት … (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ካልዕ)
ቅዳሴን ለመቀደስ ብዙ ጊዜ ፭ሆነው ይቀድሳሉ ይህው የአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሣሌ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከዚያም በሚያንስም ሆነ በሚበዛ ሰው ቅዳሴን መቀደስ ይቻላል ለምሳሌ ፯ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ይመስላሉ ፲፫ በ12ቱ ሐዋርያት እና በጌታችን ምሳሌ ሆነው ይቀድሳሉ፤ 24 በሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ይህ የሚሆነው እንደ ካህናቱ ብዛት ነው ጭራሽ ካህን ከጠፋ ደግሞ 1 ቂስና 1 ዲያቆን ሆነው መቀደስ ይችላሉ ሁለትነታቸው የመለኮትና የትስብዕት (የሥጋ) ምሳሌ ሆነው ይቀድሳሉ በሦስት ከሆነ በሦስቱ ሥላሴዎች አራት ከሆኑ በ4ቱ ወንጌላውያን ይመሰላሉ ከሁለት ባነሰ ግን 1 ሆኖ ግን ቅዳሴ አይቀደስም ቀኖናው የቤተክርስቲያኒቱ ሥርዓት ይከለክላል፡፡
“ጸልዩ” ይህ የቅዳሴው የፀሎት ዓይነት ሲሆን ለ13 ጊዜያት ይባላል፡፡ በሦስተኛው ክፍለ ቅዳሴ 4 ጊዜ ይባላል ፀልዩን ዲያቆኑ ሲያውጅ ፊቱን ወደ ህዝቡ ይመልስና እንዲጸልዩ ያውጃል፡፡ በዚህ ጊዜ ተሰጥዖ ካለ ተሰጥዖ ይመለሳል ከሌለ ግን “አቡነ ዘበሰማያት” ሕዝቡ እንዲደግሙ ያውጃል፡፡
ለምሳሌ፡-
ንፍቁ ዲያቆን “ፀልዩ በእንተ እለያበዕኡ መባዕ … መባን ስለሚያገቡ ሰዎች ፀልዩ” ሲል በዚህ ጊዜ አቡነ ዘበሰማያት አይደገምም ምክንያቱም የራሱ ተሰጥዖ ስላለው “ተወከፍ መባዖሙ ለአሃው ወተወከፍ መባዖን…” ይህ አቡነ ዘበሰማያት የሚተካ ፀሎት ነው፡፡
ድርገት ሲወርዱ “ፀልዩ በእንቲአነ” በሚባልበት ጊዜ እንድንጸልየው የሚያዘው የዳዊትን መዝሙር 150ኛውን መዝሙር ነው፡፡ ፀልዩ ብሎ ያዘዘው በዚህ ክፍል ያል የዳዊትን 150ኛውን የመዝሙር ክፍል ነው ማለት ነው፡፡
እኛ ክርስቲያኖች ቅዳሴን ባስቀደስን ቁጥር 1ኛ የኃጢአት ሥርየት ይገኛል ምክንያቱም በአንቃዕዶ ሕሊና ይቅርታን ስለሚጠይቅ፣ 2ኛ በነፍስም በስጋም በረከትን ያገኛል፣ 3ኛ ጸሎቱም ይደመጣል፣ 4ኛ የመላእክትን በረከት በቀጥታ እንሳተፋልን ቅዳሴን አስቀድሶ ሥጋ ወደሙ ሲቀበል የዘለዓለምን በረከት ያገኛል፡፡ በተጨማሪም ቅዳሴ በማስቀደስ 4 ነገሮች ይገኛሉ እነዚህም፡-

፩. ትምህርት
የቤተክርስቲያኒቱን ዶግማ እና የሥርዓተ ቤተክርስቲያን ትምህርት በቅዳሴ ገዚ ያገኛል፡፡ ለምሳሌ የማርያምን ቅዳሴ አባ ሕርያቆስ የደረሰውን ይህን ቅዳሴ ሲቀደስ በውስጡ ምሥጢረ ሥላሴ፣ እና ምሥጢረ ሥጋዊ እና ነገረ ማርያምን አምልቶ ይነግራል፡፡

፪. ታሪክ
14ቱንም ቅዳሴ የሚያስቀድስ ሰው የቤተክርስቲያንን ታሪክ በቅዳሴ ውስጥ እንማራለን፡፡

፫. ምክር
በቅዳሴ ውስጥ ተፋቀሩ፣ መጽውቱ፣ ተስማሙ፣ ጹሙ፣ ጸልዩ እየተባለ በቅዳሴ ውስጥ ሰፋ ባለመልኩ ምክር ይሰጣል ስለዚህ ቅዳሴን በማስቀደስ ምክርን ማግኝት ይቻላል ማለት ነው፡፡

፬. ተግሣጽ
ቅዳሴ ውስጡ ተግሣጽን ይዞ እናገኝዋለን ለምሳሌ በቅዳሴ እግዚእ ላይ ከወንድሙ ጋር የተጣለ ቢኖር ይተውለት ይላል በዚህ የቅዳሴ ክፍል ውስጥ ራሳችንን ምን ላይ እንደቆምን ከሰዎች ጋር ያለንን ኅብረት ስምምነት ለፈጣሪ ራሳችንን ማስገዛታችንን እየገሠፀ ይነግረናል፡፡ እነዚህን መሠረታዊ የሆኑትን ለሰው ልጆች ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ቅዳሴ በማስቀደስ እናገኛቸዋለን፡፡
ቅዳሴ ንባብም ዜማም የሚቀርብበት የፀሎት ክፍል ነው፡፡ ሁላችንም የምንሳተፍበት ቄሴም ዲያቆኑም ምእመኑም የሚሳተፉበት ነው፡፡ “ኢትቁም እራቀከ ቅድመ ነቢየ እግዚአብሔር … በእግዚአብሔር ነብይ ፊት ራቁትህን አትቁም” ይህ ማለት በቅዳሴ ጊዜ ሰው ካለ መባ፣ ካለ እጅ መንሻ በእግዚአብሔር ፊት መቆም እንደሌለበት ያጠይቃል፡፡ ምንም ባይኖረን እንኮ ያለንን አነሰ ብለን ሳንሳቀቅ ደግሞም ሳንንቃት ይዘን በፊቱ መቅረብ አለብን ከቻልን እጣኑን፣ ዘቢቡን፣ ጦፉን ሌላም ሌላሜ ይዘን መሄድ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ካህኑ በቅዳሴው መሃል ምዕናን ስለሚያስገቡት መባ የሚፀልየው ፀሎት አለ ምዕመኑም መባን ይዞ የማይመጣ ከሆነ ይህ ፀሎት ለማን ነው? ብሎ መጠየቅም ይገባል፡፡ ስለዚህ ቅዳሴን የምናስቀድሰው አስቀድመን ተዘጋጅተንበት መሆን አለበት፡፡ ለሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች ጊዜ ባይኖረን ለቅዳሴ ግን ጊዜ መድበንለት ልናስቀድስ ይገባል፡፡ ቅዳሴ ለማስቀደስ ወደ ቤተክርስቲያን ስንመጣ ራሳችን 1ኛ ቆምን ለማስቀደስ 2ኛ የሚነበቡትን መጻሕፍቶች ከሕይወታችን ጋር እያዛመድን ለማዳመጥ ለመስራት 3ኛ ቅዱስ ቁርባን ለመውሰድ የዘለዓለም ሕይወትንም ለማግኝት አምኖ መምጣት አለበት በቅዳሴው የመግቢያ ክፍል ይህንኑ በዜማ “እስመጨረሻው ቅዳሴውን ያላስቀደስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ሲነበቡ ቆሞ ያላዳመጠ በመጨረሻም ቅዱስ ቁርባን ያልተቀበለ ከቤተክርስቲያን ኅብረት ልጅነት ይሰደድ” ይላል ስዚህ ራሱን አዘጋጅቶ መምጣት ይገባል፡፡ በተጨማሪም ሰው ለቅዳሴ ሲቆም 5ቱን የሥሜት ሕዋሳቶቹን ሰብስቦ ወደ ቅዳሴው ትኩረት ሰጥቶ በንቃት ለቅዳሴ መቆም አለበት ለዚህም ዲያቆኑ በመሃል በመሃል “ለፀሎት ተነሱ” እያ ያውጃል ምዕመኑም ራሱን በእግዚአብሔር ፊት አዋርዶ ይቅርታን በመጠየቅ “አቤቱ ይቅር በለን” ይላል፡፡ አምስቱ የስሜት ሕዋሳት የሚባሉት አይን፣ ጆሮ፣ አፍንጫ፣ እጅ እና ምላስ በአንድት በፀሎተ ቅዳሴ ጊዜ ያስቀድሳሉ ለምሳሌ፡-
ዐይን፡- ካህኑ ቅዳሴን ሲቀድስ በመንበሩ አጠገብ ቆሞ ብቻ አይደለም የተለያዩ ዓይነት እንቅስቃሴዎች አሉ እነዛን እንቅስሴዎች ደግሞ ራሳቸውን የቻሉ መንፈሳዊ ምሥጢራዊ ትርጓሜዎች አሉዋቸው እነዚህን እንቅስቃሴዎች አይን ያያል ስለዚህ ዐይን ያስቀድሳል ማለት ነው፡፡
ጆሮ፡- ካህኑም ዲያቆኑም ምእመኑም በአንድትም ሆነ በተናጠል የሚያዜሙትን ዜማ፣ የሚያነቡትን ንባብ ይሰማል በዚህ ጊዜ ጆሮአችን ያስቀድሳል ማለት ነው፡፡
አፍንጫ፡- የዕጣኑን መዓዛ በማሽተት አፍንጫችን ያስቀድሳል
ምላስ፡- ቅዱስ ቁርባን በመውሰድ፣ የቅዳሴውን ፀበል በመጠጣት በዚህ ጊዜ የመቅመስ ስሜታችን ያስቀድሳል፡፡
የመዳሰስ፡-የመዳሰስ ስቀሜታችንም ስግዱ በተባለ ጊዜ፣ ወንጌል ከተነበበ በኋላ ወንጌሉን ሲስም በመጨረሻም ሰዓት የካህኑን እጅ ለመባረክ ስንስም የመዳሰስ ስሜታችን ያስቀድሳል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ አምስቱም የስሜት ሕዋሶቻችን በተሟላ መንገድ ከእግዚብሔር ጋር የሚገናኙበት መንገድ ምንድን ነው ቢባል ቅዳሴ ነው በቅዳሴ ውስጥ የምናገኘው ትምህርት በአውደምህረት በከኮርስ ከምናገኝው ትምህርት የተለየ ነው ይኽውም በዜማ የታሸ ብዙ ሊቃውንት የደከሙበት መንፈስ ቅዱስ እንደገለፀላቸው ለሰው በቀላሉ የሚገቡ ትምህርቶች ናቸው ሌላው ደግሞ ወንጌል ይነበባል መልዕክታት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ ከዓለም አቀፍ ከሆኑ ሁሉ እና በዜማ ስለሆነ ነው እንጂ (ምስባክ) የምንለው ከመዝሙረ ዳዊትም ውስጥ ይነበባል ስለዚህ 1 ሰው ቅዳሴን ሲያስቀድስ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስን ከብሉይ እስከ ሐዲስ ድረስ ይማራል ማለት ነው ረጅም ዘመን ያስቀደስ በሕይወቱ ውስጥ ምሁር ማለት እርሱ ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንዳልነው ነው፡፡ የመላእክትን ህይወት በምድር ላይ መኖር ማለት ነው፡፡
በቤተክርስቲያናችን ትልቁ ሱታፊ ቅዳሴን ማስቀደስ ነው ይህንንም ከራስ አልፎ ወገኖቻችን ይህን ምሥጢር እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባል ልጆቻችን ከቅዳሴው እንዲሳተፉ ተሰጥዖ እንዲመልሱ፣ መባን ይዘው እንዲመጡ፣ ቅዳሴ ለማስቀደስ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ፣ ቅዱስ ቁርባን እንዲቀበሉ ማድረግ ተገቢ ነው ያለበለዚያ የምሰጠውን የምናጣበት ደረጃ ላይ እንዳንደርስ የቀደመውን ሥርዓተ አምልኮ የሚፈፀምበት ሥርዓት እንዳይጠፋ የሚረከበን እንዳናጣ የቀደመው ለተተኪው ትውልድ ሚስረከብ መቻል አለበት
ሰማያዊ ምሥጢር በምድረ ከተሰራባት ከማልእክት ጋር አንድ ሆነን ፈጣሪን ከምናመሰግንባት ከቅድስት ቤተክርስቲያን ሳያናውጥ ያኑረን አሜን፡

source : https://elianaaddis905.wordpress.com

No comments:

Post a Comment