Thursday, July 3, 2014

ሰኔ 20

ሰኔ 20 ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፤ህንጸተ ቤተክርስቲያን ይባላል። የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የታነጸው በዛሬዋ ቀን ነው አናጺውም እራሱ ባለቤቱ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ቦታው ፊልጰስዩስ ነው፤ ቤተክርስቲያኗ የተሰየመችው ደግሞ በእመቤታችን ስም ነው። ጴጥሮስ፤ ዮሐንስ በርናባስና ሌሎችም ሐዋርያት በፊልጰስዩስ ተሰብስበው ሳለ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በኪሩቤል ጀርባ ላይ ሆኖ እልፍ አእላፍ መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል እመቤታችን በቀኙ ነበረች፤ 3 ድንጋዮችን አንስቶ ጎተታቸው እንደ ሰም ተለጠጡ እንደ ግድግዳም ሆኑ ዳግመኛም የብርሃን ምሰሶ ወረደ በሰማያዊቷ እየሩሳሌም እምሳያ አድረጎ አነጻት ሁለንተናዋም ተጠናቀቀ፤ ዳግመኛ በበነጋው ሰኔ 21 ቀን እመቤታችንን እና ቅዱሳን መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል ቅዳሴ ቀድሶ ለሐዋርያቱ አቆረባቸው ፍጹም ደስታም ሆነ። ከዚህ በኃላ ሐዋርያት ከጌታ እንዳዩት በዓለም ዞረው ቤተክርስቲያን አንጸዋል። ከዚያ በፊት የነበረው የነሶሎሞን ቤተመቅደስ የአይሁድ ምኩራብ የአይሁድ ስርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እንጂ የአዲስ ኪዳን የቁርባንም ሆነ የጥምቀት ስርዓት መፈጸሚያ አልነበረም፤ ታዲያ ሐዋርያት የት ነበር ህዝቡን የሚያጠምቁት የሚያቆርቡት ካሉ በየሰው ቤት ነበር። ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ታላቁ ነብይ ኤልሳዕ አረፈ። ይህ ነብይ በ 12 ጥማድ በሬ ሲያርስ ቴስቢያዊው ነብዩ ኤልያስ ተከተለኝ አለው ምንም ሳያቅማማ ሀብት ንብረቱን ትቶ ተከተለው፤ ኤልያስ በእሳት ሰረገላ ከማረጉ በፊት ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ ይለዋል ባንተ ላይ ያደረ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እጥፍ ድርብ ሆኖ ይደርቢኝ ይለዋል፤ እንደ ቃሉ ሆነለት ተደረገለት፤ ኤልያስ አንድ ሙት ሲያስነሳ ኤልሳዕ ሁለት ሙት አስነስቷል፤ ኤልያስ አንድ ጊዜ ባህር ሲከፍል ኤልሳዕ ሁለት ጊዜ ባህር ከፍሏል። እምቤታችንን የኤልሳዕ ጋን ይላታል ኤልሳ የመረረውን ውኃ እንዳጣፈጠ እመቤታችንም ይህን መራራ ዓለም ጌታን በመውለዷ አጣፍጣዋለች፤ የዚህ ነብይ ድንቅ ታሪኩ 2ኛ ነገስት ላይ በስፋት ተጽፏል ሰኔ 20 ቀን እረፍቱ ነው ቤተክርስቲያን የዛሬውን ቀን እመቤታችንን እና ነብዩን አስባ ትውላለች። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>

No comments:

Post a Comment