Thursday, November 29, 2012

♥እንኳን ለእናታችን ጽዮን ማርያም ታላቅ አመታዊ ክብረ በዓል አደረሰን አደረሳችሁ♥



እናታችን ጽዮን

በዲ/ ኅሩይ ባየ


በቅዱሳት መጻሕፍት ጽዮን የሚለው ቃል ተደጋግሞ በነቢያቱ ተነግሯል፡፡ ሆኖም የጽዮን ትርጉም እንደተነገረበት ዐውደ ትንቢት እንደተሰበከበት መዋዕለ ትምህርት ምስጢሩ ይለያያል፡፡



በዚህ ጽሑፍ በጥቂቱ የምንመለከተው ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ  እንዴት እንደመጣች፣ ኅዳር 21 ቀን ስለምናከብረው ዓመታዊ በዓል፣ በታቦተ ጽዮን እና በዘመነ ሐዲስ በተገለጠችው በእመቤታችን በቅድስትድንግል ማርያም ያለውን ምስጢራዊ ትርጉም ነው፡፡ታቦት አንቺ ነሽ» ብሏል፡፡  

ታቦተ ጽዮን በፈቃደ እግዚአብሔር በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት ለሰው ልጆች ተሰጥታ እስራኤላውያን ሲባረኩባት፣ መሥዋዕታቸውን ሲያቀርቡባት ከእግዚአብሔር ሲታረቁባት ኖረዋል፡፡ከአራት ሺሕ ሦስት መቶ ሃያ ሰባት ዓመተ ዓለም (4327 ..) ጀምሮ ለአርባ ዓመታት ያህል እስራኤላውያንን በክህነት ያገለግል የነበረው ካህኑ ዔሊ ዕድሜው ሲገፋ ሁለት ልጆቹን ጠርቶ ምሉዕና ዱግ /ዋናና ምክትል/ አድርጎ ሾማቸው፡፡

በደብተራ ኦሪት ታቦተ ጽዮንን እንዲያገለግሉ የተሾሙት ሁለቱ ወጣት ካህናት /አፍኒን እና ፊንሐስ/ ፈቃደ እግዚአብሔርን ተላልፈው ሦስት ታላላቅ በደሎችን ፈጸሙ፡፡ የመጀመሪያው በደል፤ በሙሴ ሥርዓት በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት በርታ በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት የምትጠፋ መብራት እንድትቀመጥ የተሠራ ሥርዓት ነበር፡፡ ሆኖም አገልግሎት ከሌለ ሲበራ ማደሩ ለምን ? ብለው መቅረዙን አነሡ፤ መብራቱንም አጠፉ፡፡ ሁለተኛ፣ ለራሳቸው ሥጋዊ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው ለመሥዋዕት እንዲሆን ከመጣው እንስሳ ታርዶ ስቡ ሳይጤስ፣ደሙ ሳይፈስ ሥጋውን እየመረጡ ተመገቡ፡፡ሦስተኛ ጸሎት እናደርሳለን ሥርዓተ አምልኮ፣ እንፈጽማለን ብለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይመጡ ከነበሩት እስራኤላውያን ቆነጃጅት ጋራ በዝሙት ወደቁ፡፡ አባታቸው ካህኑ ዔሊም የልጆቹን በደል እያየ እንዳላየ እየሰማ እንዳልሰማ ቸል በማለቱ እግዚአብሔርአዘነ፡፡ በዚህም ምክንያት ፍልስጥኤማውያንን አስነሥቶ በጦርነት ቀጣቸው፡፡

ዕብራውያን በጦርነት ውሎ ያለልማዳቸው በአሕዛብ ተሸነፉ፡፡ ሕዝበ እስራኤልም ግራ ቢገባቸው «ድል የተነሣነው ታቦተ ጽዮንን ይዘን ባለመዝመታችን ነው» ብለው አፍኒን እና ፊንሐስ ጽላቱን እንዲሸከሙ አድርገው ወደ ፍልስጥኤማውያን የጦር ምሽግ ገሠገሡ፡፡ ሆኖም ያሰቡት ሳይሳካ ታቦተ ጽዮን ተማረከች፣ አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ፤ ዕብራውያንም በጦርነቱ ድል ተደረጉ፡፡ፍልስጥኤማውያንም ታቦተ ጽዮንን ማርከው ዳጎን ከተባለው ጣዖታቸው ላይ አስቀመጧት፡፡ በማግስቱ ሲመለሱ ዳጎን ተገልብጦ ታቦተ ጽዮን በላይ ተቀምጣ አገኟት፡፡ በማግስቱም ተመሳሳይ ድርጊት ተፈጽሞ ዳጎን ወድቆና ተሰባብሮ አገኙት፡፡ 1ሳሙ 5÷4 ይኽን በተመለከተ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጽጌ ድንግል ሰቆቃወ ድንግል በተባለው ድርሰቱ፤
«ታቦተ አምላከ እስራኤል ጽዮን ዘነገደት ምድረ ኢሎፍሊ፤
ወቀጥቀጠቶ ለዳጎን ነፍሳተ ብዙኃን ማህጎሊ፤
አመ ነገደት ቁስቋመ በኀይለ ወልዳ ከሃሊ፤
ወድቁ አማልክተ ግብፅ መናብርተ ሰይጣን ሐባሊ፡፡
ወተኀጉሉ ኲሎሙ ዘቦሙ አስጋሊ. . .
 
ወደ ኢሎፍሊ ምድር ተማርካ የሔደች የእስራኤል አምላክ የቃል ኪዳኑ ታቦተ ጽዮን የብዙዎችን ነፍሳት ያጠፋ ዳጎንን ሰባበረችው፡፡ ድንግል ማርያምም ሁሉን ማድረግ ከሚችለው ከልጇ ጋር ግብፅ ወደሚባል ሀገር በሔደች ጊዜ የሐሰተኛ ሰይጣን ዙፋኖች የሆኑ የግብፅ ጣዖታት ፈረሱ ጠንቋይ አስጠንቋይ ያላቸው ሁሉ ዐፈሩ» በማለት በንጽጽር አስቀምጦታል፡፡ ኢሳ 19÷1 ኃይል እና ድል ማድረጉን በዳጎን የጀመረችው ታቦተ ጽዮን የፍልስጥኤማውያንን መንደር በአባርና በቸነፈር በእባጭም መታች፡፡ ሕዝበ ፍልስጥኤምም ታቦተ ጽዮን ወደ እስራኤል ምድር እንድትመለስ አደረጉ፡፡


በእንደዚህ ዓይነት ታላቅ ክብር በሀገረ እስራኤል ትኖር የነበረችው ታቦተ ጽዮን ወደ ሀገራችን ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷ ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ ሐሴት እንዲሰማን ያደርጋል፡፡

የታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት
ከአርባ ሁለት ጊዜ በላይ ስሟ ተደጋግሞ የተጠቀሰው ሀገር ቅድስት ኢትዮጵያ በእግዚአብሔርየተወደደች ለመሆኗ ነቢያቱ መስክረዋል፡፡ ከነቢያት አንዱ አሞፅም፤ «የእስራኤል ልጆች ሆይ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን ?» ብሎ እግዚአብሔር መናገሩን ጽፏል /9÷7/፡፡ ከሁሉም ከፍ ባለመልኩ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት፤ «ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች» ብሎ ሕዝበ ኢትዮጵያ እደ ሕሊናውን እና እደ ልቡናውን ዘወትር በአምልኮተ እግዚአብሔር፣ በጾምና በጸሎት፣ በምጽዋትና በትሩፋት፣ ዘርግቶ በሃይማኖት ጸንቶ፣ በምግባር ቀንቶ የሚኖር በመሆኑ፤ ሕዝቡ ሕዝበ እግዚአብሔር ምድሪቱ ሀገረ እግዚአብሔር ተብለዋል፤ /መዝ.68÷31/፡፡

ለታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ዋናው ምክንያት በእስራኤል እና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው የሠመረ ግንኙነት ነው፡፡ ይኽም በመሆኑ የንግሥት ሳባ እና የንጉሥ ሰሎሞን ግንኙነት ሰፊውን ታሪክ ይዞ ይገኛል፡፡የንግሥተ ሳባ ዕቃ ግምጃ ቤት የነበረው ታምሪን ወደ ኢየሩሳሌም ሔዶ ንጉሥ ሰሎሞን ያሠራውን ቤተ መቅደስ ዓይቶ፣ የሰሎሞንን ጥበባዊ ዝና ሰምቶ በፍጹም መደነቅ ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡ ያየውንና የሰማውን ለንግሥቲቱ አጫወታት፡፡ እሷም የሰማችውን ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ የሰሎሞንን      መንፈሳዊና ሥጋዊ ጥበብ ተመልክታ እግዚብሔርን አመስግና ተመለሰች፡፡

ከንጉሥ ሰሎሞን ምኒልክን ፀንሳ ከኢየሩሳሌም ተነሥታ ባሕረ ኤርትራን ተሻግራ፣ ሐማሴን አውራጃ ስትደርስ አሥመራ ከተማ በሚገኘው ማይበላ ከተባለው ቦታ  ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ የሕፃኑንም ስም የንጉሥ ልጅ ስትል «እብነ መለክ» አለችው፡፡ ይኽ ስም በዘመን ሒደት ምኒልክ ተብሎ ተለወጠ፡፡

ምኒልክ ተወልዶ በአእምሮ እያደገ ሲሔድ አባቴ ማን ነው ? አድራሻውስ ወዴት ነው ? እያለ ጥያቄ ቢያበዛባት በሃያ ሁለት ዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ላከችው፡፡ ምኒልክም አባቱ ንጉሥ ሰሎሞንን አግኝቶ ሕገ ኦሪትንና የዕብራይስጥ ቋንቋ ሲያጠና ከቆየ በኋላ፤ ዐሥራ ሁለት ሺሕ እስራኤላውያንን አስከትሎ ከምድረ እስራኤል ወደ ኢትዮጵያ ጉዞውን አቀና፡፡

ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋር ለጉዞ የተነሡ ዕብራውያን ከቤተሰቦቻቸው መለየታቸው ሳያሳዝናቸው ከታቦተ ጽዮን መለየታቸው እጅግ ከበዳቸው፡፡ ወዲያው በፈቃደ እግዚአብሔር  ታቦተ ጽዮንን ከመንበሯ አንሥተው በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ወደ ኢትዮጵያ ገቡ፡፡

ቀዳማዊ ምኒልክ እና እስራኤላውያን ታቦተ ጽዮንን ይዘው አክሱም የደረሱት ኅዳር 21 ቀን ነበር፡፡ ንግሥተ ሳባም የታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በጣም ስላስደሰታት በክብር ተቀበለቻቸው፡፡ «ወአንበርዋ ውስተ ሕፅነ ደብረ ሀገረ ማክዳ» እንዲል በአክሱም ከተማ መካከል ደብረ ማክዳ /ዛሬ ቤተ ጊዮርጊስ ከሚባለው/ ላይ ደብተራ ኦሪት ሠርተው አስቀመጧት፡፡

አሁን ያለው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በዘመናዊ ዐቅድ የታነፀው የአክሱም ጽዮን ገዳም ቅዳሴ ቤቱ ጥር 30 ቀን 1957 . ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ግርማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ /የታላቋ ብሪታንያ ንግሥት/ እና ልዑል ፊልፕ ከክብር ባለሟሎቻቸው ጋር በተገኙበት ተከብሯል፡፡



ኅዳር ጽዮን በአክሱም
አክሱም ማርያም ጽዮን በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ መሠረታቸው ስትሆን ከተማዋም የኢትዮጵያ ሥልጣኔ መነሻ ናት፡፡ አክሱም በሕገ ልቡና የጸናች፣ ሕገ ኦሪትን የፈጸመች፣ በሕገ ወንጌል ያመነች ናት፡፡ ለዚህም ነው «ሕግ ይወጽእ እምጽዮን፤ ከጽዮን ሕግ ይወጣል» የሚለው ጥቅስ የሚነገረው፡፡

በዓለ ልደትን በላሊበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር፣ ኅዳር ጽዮንን በአክሱም ጽዮን ሲያከብሩት ልዩ የሆነ ሥርዓት ስለሚቀርብባቸው ምእመናን መንፈሳዊ ደስታ ይሰማቸዋል፡፡
ኅዳር 21 ቀን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል ነው ብለን በተለየ መልኩ የምናከብርበት ምክንያት፡-

  1.  በብሉይ ኪዳን ታቦተ ጽዮን የፈጸመችውን ልዩ ልዩ ገቢረ ተአምራትን ለማሰብ
  2. ቀዳማዊ ምኒልክ ከዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል የበኲር ልጆች ጋር ሊቀ ካህናቱን አዛርያስንና ታቦተ ጽዮንን ይዞ አክሱም የደረሰበት ዕለት በመሆኑ
  3. በሦስት መቶ ሠላሳ ዓመተ ምሕረት በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ መንግሥት ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት ይሁን ተብሎ ዐዋጅ የታወጀበት
  4. ዘካርያስ በተቅዋመ ወርቅ ምሳሌ ራእይ ያየበት
  5. ነቢዩ ሕዝቅኤል በተቆለፈች ቤተ መቅደስ
  6. ዕዝራ በቅድስት ሀገር ምሳሌ ራእይ ያየበት
  7. አብርሃና አጽብሃ በወርቅና በዕንቁ ያሠሩት ባለ አሥራ ሁለት ክፍል ቤተመቅደስ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት
  8. በዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዮዲት ጉዲት አብያተ ክርስቲያናትን ስታቃጥል ታቦተ ጸዮንን ይዘው ወደ ዝዋይ ሐይቅ ከተሰደዱ በኋላ ዘመነ ሰላም ሲጀመር አክሱም በነበሩ ካህናት አስታዋሽነት ከዝዋይ ወደ አክሱም የገባችበት ዕለት

በመሆኑ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም  ጽዮን ከፍ ባለ መንፈሳዊ በዓል እናከብራለን፡፡ ይኽ ሲባል ግን በዓሉ የሚከበረው በአክሱም ጽዮን ማርያም ብቻ ነው ማለት ሳይሆን፤ ታቦተ እግዝእትነ ማርያም ባለችበት ቦታ ሁሉ መከበሩን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ ጋርም የመመኪያችን ዘውድ፣ የመዳናችን ምክንያት፣ የንጽሕናችን መሠረት ስለሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያልተነበየ  ነቢይ፣ ያልሰበከ ሐዋርያ፣ ያልተቀኘ ባለቅኔ ከቶ የለም፡፡ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወረደ፣ በቤዛነቱ ዓለምን አዳነ፣ ዳግመኛም በክበበ ትስብእት፣ በግርማ መለኮት ለፍርድ ይመለሳል ብንል ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሥጋ በመሆኑ ያለ ወላዲተ አምላክ ምስጢረ ሥጋዌን፣ ነገረ ድኅነትን፣ ነገረ ምጽአትን ማሰብ ከቶ የማይቻል ነው፡፡



«ዕግትዋ ለጽዮን፤ ጽዮንን ክበቧት» እንዳለ ነቢዩ፤ ዐሥርቱ ቃላት የተጻፈባትን የእስራኤል አምባና መጠጊያ የሆነችውን ታቦተ ጽዮንን ሌዋውያን ከበዋት ውዳሴ ያቀርቡላት እንደነበረው፤ ዛሬም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ካህናትና ምእመናን ከሩቅ እና ከቅርብ ተሰብስበው በማኅሌት፣ በዝማሬ፣ በቅዳሴና በውዳሴ ያከብሯታል፡፡

በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም እና በቃል ኪዳኑ ታቦት መካከል ጥልቅ የሆነ ምስጢራዊ ትምህርት አለ፡፡ /ዘፀ. 25÷9-20/፡፡ ይህቺ የቃል ኪዳን ታቦት በደብተራ ኦሪት በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የኖረች፣ የዮርዳኖስን ባሕር የከፈለች /ኢያ. 3÷14-17/ ቅጽረ ኢያሪኮን ያፈረሰች /ኢያ 6÷1-21/ ዳጎን የተባለ የፍልስጥኤማውያንን ጣዖት የቆራረጠች /1ሳሙ 5÷1-5/ በድፍረት ሊነካ የሞከረውን ኦዛን የቀሰፈች /1ሳሙ 6÷6/ በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ተቀምጣ ቤቱን በበረከት የመላች /2ሳሙ 6÷12/ ዳዊት የዘመረላት /2ሳሙ 6÷14/ ጠቢቡ ሰሎሞን በቤተ መቅደስ በክብር ያኖራት/1ነገ  8÷1/ የእግዚአብሔር የክብር መገለጫ ናት፡፡

በታቦተ ጽዮን እና በዘመነ ሐዲስ በተገለጠችው በቅድስት ድንግል ማርያም መካከል ያለውን ረቂቅ እና ድንቅ ምስጢራዊ ንጽጽር አስመልክቶ ሦርያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም፤ «ታቦት በወርቅ ልቡጥ እምኩለሔ ዘግቡር እምዕፅ ዘኢይነቅዝ፤ ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረጸ በው ስጥ በአፍአ በወርቅ የተለበጠ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሐ ጠባይዕ ሳያድፍባትና የቅድስና ባሕርይ ሳይጎድፍባት በማየት፣ በመስማት፣ በመዳሰሰ፣ በማሽተት አንዳችም እድፍ ጉድፍ ሳያገኛት በንጽሕናና በቅድስና ጸንታ በኃጢአት ሳትለወጥ ኖራለች፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም፤ «አልብኪ ነውር ወኢምንትኒ ላዕሌኪ፤ ምክንያታዊ ነውር ኃጢአት የሌለብሽ የኃጢአት ሸታ ያልደረሰብሽ ንጽሕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና ክብርት በልዕልና አንቺ ነሽ» /መኃ 4÷7/ ሲል ተናግሯል፡፡

ታቦተ ጽዮን በከበረ ወርቅ እንደተሸለመች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ እና በንጽሐ ልቡና የተሸለመች ያጌጠች መሆኗን ያጠይቃል፡፡

ታቦተ ጽዮን የቃለ እግዚአብሔር ማደሪያ እንደሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያምም ለአካላዊ ቃል ለእግዚአብሔር ወልድ ማደሪያ ሆናለች፡፡ ይኽንንም ቅዱስ ኤፍሬም ሲያስረዳ፤ «ኮንኪ ታቦቶ ለፈጣሬ ሰማያት ወምድር ፆርኪዮ በከርስኪ ተሰዓተ አውርኃ አንቲ ማእምንት ለዘኢያገምርዎ ሰማያት ወምድር፤ ድንግል ማርያም ሆይ ሰማይና ምድርን ለፈጠረ አምላክ ለእርሱ ማደሪያ ሆንሽ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀንሸ ቻልሽው ተሸከምሽው ሰማይና ምድር የማይወስኑትን ለመወሰን የታመንሽ አንቺ ነሽ» ብሎ ተቀኝቶላታል፡፡ ስለሆነም ከብሉይ ኪዳን እስከ ሐዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበትን የቸርነት በዓል እግዚአብሔርበፈቀደልን ቦታ ሆነን ስናከብር ከእኛ የሚጠበቀውን በጎ ነገር እያሰብን በተግባርም እየገለጥን ከበዓሉ ረድኤትና በረከት ተሳታፊ እንሆን ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት የእናቱ የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡

የቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እና ምልጃ አክሊልና ጉልላት በሆነው በእናታችን በወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት ሁላችንንም ይማረን፡፡

/ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ህዳር 15-30 ቀን 2003./