Wednesday, April 17, 2013

ሚያዚያ 9

በዛሬዋ ዕለት በዮርዳኖስ በርሃ በፍጹም ተጋድሎ ሲኖር የነበረው አባ ዞሲማስ አረፈ። ይህ አባት እጅግ የሚያስደንቅ ታሪኩ ብሔረ ብጹዓንን ጎብኝቶ በዚያ የሚገኙ የቅዱሳንን አኗኗር ዜና ታሪካቸውን ይዞ መምጣቱ ነው፤ ይህንን ኃላ እንመለስበታለን፤ ከዚህ በሻገር አባ ዞሲማስ ማርያም ግብጻዊትንም አግኝቷታል የጌታችንን ቅዱስ ስጋና ክቡር ...ደም አቀብሏታል፤ ለመሆኑ ይህች ቅድስት ማን ናት ካሉ፤ ታሪኳ እንዲህ ነው፤ ትውልዷ ግብጽ ሲሆን ገና በ 12 ዓመቷ ቤተሰቦቿን ጥላ ወጣች እስክንድርያ ከተማ ውስጥ 17 ዓመት በዘማዊነት ኖረች፤ከዕለታት በአንዱ ቀን ወደ እየሩሳሌም ከሚሄዱ ምዕመናን ጋር ተቀላቅላ በመርከብ ተሳፈረች፤ነገር ግን ለጽድቅ አይደለም በመርከብ የተሳፈሩ ምዕመናንን በዝሙት ልትጥል እንጂ፤ እየሩሳሌም ደረሱ ሁሉም የጌታን መቃብር ሊሳለም ወደ ቤተክርስቲያኑ ገባ፤ እርሷ ግን ልትገባ ስትሞክር አንዳቸ ኃይል ወደ ኃላ ይመልሳታል እስከ ሦስተ ጊዜ ያህል እንዲሁ ሆነባት፤ እግዚያብሔር በደሌን ቆጥሮ ነው ብላ አምርራ አለቀሰች፤ እመቤታችን ተገለጸችላት እንዲህም አለቻት "እግዚያብሔር ይቅር እንዲልሽ ወደ ዮርዳኖስ በረሃ ሂጂ በዚያም ታላቅ እረፍትን ታገኚያለሽ " ቁራሽ ዳቦ ይዛ ዮርዳኖስ በርሃ ገባች የሰው ፊት ሳታይ 47 ዓመት ቀን ሐሩሩ ሌሊት ቁሩ እያሰቃያት በፍጹም ተጋድሎ ኖረች፤ ሰውነቷ ከሰል መሰለ አጥንቷ ከቆዳዋ ጋር ተጣበቀ። ቅዱስ ዞሲማስ በ 3 ዓመቱ ነው ገዳም የገባው 53 ዓመት በበርሃ ኖረ፤ እንዲህ እያለ ዘወትር ይጸልይ ነበር “ አቤቱ አምላኬ ሆይ በዚህ በርሃ ከኔ የተሻለ የብህትውና ህይወት ያለው አባት አሳየኝ ” እግዚያብሔር ልመናውን ሰማው መልአኩን ላከለት መርቶ ማርያም ግብጻዊት ጋር አደረሰው ወድቆ ሰገደላት ታሪኳን ሁሉ ነገረችው ቅዱስ ስጋውን ክቡር ደሙን አቀበላት የዛሬ ዓመት እንዳትቀር ተመልሰህ ና ብላ ሸኘችው በዓመቱ ሲመለስ ሞታ አገኛት በጎኗ ተንበርክኮ ለረጅም ጊዜ አለቀሰ ገንዞም ቀበራት የቅድስት ማርያም ግብጻዊት እረፍቷ ሚያዚያ 6 ቀን 522 ዓ/ም ነው። ወደ ቅዱስ ዞሲማስ ታሪክ እንመለስ ለ 40 ዓመት ብሔረ ብጹአንን እንዲያሳየው ወደ እግዚያብሔር ይጸልይ ነበር፤ እግዚያብሔር ልመናውን ሰማው ወደ ብሔረ ብጹአንም አደረሰው፤ ብሔረ ብጹአን ምድር ላይ ነው ያለችው የሚኖሩባትም በነብዩ በኤርሚያስ ዘመን ከእየሩሳሌም ጥፋት የተረፉት የአሚናዳብ ቤተሰቦች ናቸው፤ ኤር 35፤1-11 ተመልከት። ወደዚህች ምድር በእግዚያብሔር ፈቃድ ደረሰ አኗኗራቸውንም አየ፤ ተመለከተ ደስ የምትል የገነት አምሳያ ናት ውኃዋ ልዩ ነው ዕጽዋቶቿ ታላላቅና ከመልካም ፍሬዎች ሁሉ የያዙ ናቸው ነፍሴን ደስ አላት ፈጣሪን አመሰገንኩት፤ አንድ ታላቅ ዛፍ ስር እንደ ጸሐይ የሚያበራ ሰው ሲጸልይ አየሁት ቀርቤ ሰገድኩለት እንዴት ወደዚህች ምድር ልትመጠጣ ቻልክ አለኝ የሆነውን ሁሉ ነገርኩት ከሐዋርያው ማቴዎስ በቀር ወደዚህች ምድር የመጣ አንዳች ሰው የለም ፈጣሪ ጸሎትህን ሰምቶሃል አለኝ ብጹአን ወገኖቹ ወዳሉበት ወሰደኝ ባዩኝ ጊዜ ተገረሙ የመጀመሪያውን ዓይነት ጥያቄ ጠየቁኝ ከዓለም የሆነ ሰው ኑ እዩ እያሉ ተጠራሩ፤ ሊመለከተኝ ከሚመጣው ሰው የተነሳ 3 ቀን ምንም እንቅልፍ አልተኛሁም፤ አኗኗራቸውን ነገሩኝ፤ መውጣት መውረድ መዝራት ማጨድም የለም ብርና ወርቅም የለም ደሃና ሀብታምም የለም ሁሉም እኩል ነው ዘወትር እሰከ 9 ሰዓት ጾመን ፍራፍሬዎችን እንመገባለን፤ እናገባለን እንጋባለን፤ ባል ሚስቱን 3 ጊዜ ብቻ በግብር ያውቃተያል 3 ልጆችንም ትወልዳለች ሁለት ወንድ አንድ ሴት፤ ታላቅ ከታናሽ ቀድሞ እይሞትም ከመካከላችን አንዱ ሲሞት በእልልታ እንቀብረዋለን.... ቅዱስ ዞሲማስ ይህንና ሌሎች ድንቅ ነገሮች ጽፎ ወደ ዓለም ተመልሷል የዚህ ቅዱስ አባት እረፍቱ በዛሬዋ ቀን ነው፤ ከቅዱስ ዞሲማስና ከማርያም ግብጻዊት በረከታቸውን ያድለን። ከዚህ በታች ያለው ስዕል የቅዱስ ዞሲማስና የማርያም ግብጻዊት ነው።

No comments:

Post a Comment