Monday, April 22, 2013

ሚያዚያ 15



በዚህች ቀን ቅድስት እለእስክንድርያ በሰማዕትነት አረፈች፤ ይህች ቅድስት የአረመኔው የዱዲያኖስ ሚስት ነበረች። ዱዲያኖስ ማለት ቅዱስ ጊዮርጊስን ለሰባት ዓመት ያሰቃየው ጨካኝ ንጉስ ነው። የዚህችን የከበረች ሰማዕት ታሪክ እንካችሁ:- ዱድያኖስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሶስት ጊዜ ገድሎት ሶስት ጊዜም ተነስቷል ይልቁንም በመንኮራኩር ፈጭተው ይድራስ ተራራ ላይ ...በተኑት በኃላ በፈጣሪ ኃይል ተነስቶ ከፊቱ ቢቆምም ሊያምን አልቻለም ልቡ ደንድኗልና፤ አሁንም ለአጰሎን ስገድ እያለ እያሰቃየው ነው፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ እሺ እሰግዳለሁ አለ፤ ዱድያኖስ እጅግ ደስ አለው፤ ግን የምሰግደው ዛሬ አይደልም ቀኑ መሽቷል ጊዜው አልፏል ለነገ አዋጅ አስነግር ህዝቡም ነገስታቱም ሁሉ ይሰብሰቡና በአደባባይ እሰግዳለሁ፤ አሁን ግን እጅና እግሬን ከግንድ ጋር አስራችሁ እስር ቤት አሳድሩኝ አለ፤ዱድያኖስም የለም እስር ቤት አታድርም ቤተመንግስት በታላቅ ክብር ታድራለህ እንጂ አለው፤ቤተመንግስት ወሰዱት አንድ ያማረ እልፍኝ ሰጡት፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ አልተኛም ጸጥ ረጭ ባለበት በውድቅት ሌሊት የቅዱስ ዳዊትን መዝሙር በሚያስገመግም ድምጽ መዘመር ጀመረ እንዲህ ሲልለምንት ታንገለጉ አህዛብ ወህዝብኒ ነበቡ ከንቶአህዛብ ለምን ያጉረመርማሉ ህዝቡስ ለምን ከንቱን ይናገራል በእግዚያብሔርና በመሲሁ ላይመዝ 21፤በዚህን ጊዜ ንግስቲቱ እለእስክንድያ ተኝታ ታዳምጥ ነበር፤ አላስቻላትም ተነስታ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እልፍኝ ገባች፤ነገርህ ደስ አሰኝቶኛል የምሥጢር አገላለጥህም ልቤን ቀስቅሶታል፤የአንደበትህ ጣዕም ሁለንተናዬን ማርኮኛልና እባክህ ንገረኝ፤አህዛብ ያልከው እነማን ናቸው የሚያጉረመርሙትስ በማን ላይ ነው መሲሁስ ማን ነው እግዚያብሔርስ የቱ ነው ?” ቅዱስ ጊዮርጊስ ከስነፍጥረት ጀምሮ ይተርክላት ጀመር አፏን ከፍታ አዳመጠችው፤ሊነጋጋ ሲል ወደ እልፍኟ ገብታ ተኛች፤ እርሱ ግን ሲሰግድ ሲጸልይ አነጋ፤ ሲረፋፍድ አዋጅ ተነገር የአገሬው ህዝብ ሁሉ ተሰበሰበ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ጣኦታቱ አዳራሽ ገባ በሥላሴ ስም አማተበባቸው ሁሉም ተሰባበሩ አመድ ትቢያም ሆኑ፤ምድርም ተከፍታ ዋጠቻቸው፤ በጣኦታቱ ላይ ያደሩት አጋንንትም የኃያሉ የእግዚያብሔር ምስክር ጊዮርጊስ ጊዚያችን ሳይደርስ አታጥፋን እያሉ ለፈለፉ፤ዱድያኖስ ይህን አይቶ ተቆጣ እየተበሳጨ ወደ ቤተመንግስቱ ገባ፤ እለእስክንድርያ ምን ሆነክ ነው አለችው፤ የሆነውን ነገራት፤ የነዚህ የክርስቲያኖች አምላካቸው እየሱስ ክርስቶስ ኃያል ገናና ነው ተበቅሎ ያጠፋካል ተወቻው አታሰቃያቸው አለችው፤ ከአንደበቷ የክርስቶስን ስም ሲሰማ እጅጉን ተበሳጨ እየጎተተ ወደ ነገስታቱ ወሰዳት በጸጉሯ ሰቅለው ገረፏት አራት ሰው የማያንቀሳቅሰው ድንጋይ ጡቷ ላይ ጫኑባት ዘፍት የሚባል እንደ አሲድ ያለ አፍልተው አፈሰሱባት፤ ሌሎች መከራዎችን አደረሱባት እንዲያውም ገድሏ እጅግ አስጨናቂና አስፈሪ ይለዋል የደረሰባትን መከራ ሲገልጽ፤በመጨረሻም ሊገድሏት እየጎተቱ ሲወስዷት ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሩቅ አየችው፤ ጌታዬ ጊዮርጊስ የክርስትና ጥምቀትን አልተቀበልኩኝም አለችው፤ ደምሽ ጥምቀት ሆኖሻል እነሆ መላዕክት የክብር አክሊል ሊያቀዳጁሽ ዙሪያሽን ከበውሽ ይታዩኛል የገነት ደጅ ተከፍቶ ቅዱሳን በጉጉት አንቺን ሲጠብቁም እመለከታሉ አላት፤ አደባባይ አቁመው አንገቷን ሊቆርጧት ሲሉ አንዲት ጸሎት ልጸልይ ፍቀዱልኝ አለቻቸው፤ ፈቀዱላት ዞራ ተመለከተች ቤተመንግስቱ ክፍት ነው፤ አቤቱ አምላኬ ቤተመንግስቴን እንደተከፈተ ትቼ እንደወጣሁ አንተም የመንግስተሰማያትን በር ክፈትልኝ አለች፤ ጸሎቷን ጨርሳ አሜን ስትል በያዙት ሾተል አንገቷን ቆረጡት፤ ይህም ሚያዚያ 15 ቀን ነው። 8 ቀናት በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከትሏታል። ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን የከበረች የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ ራስ አስራ አምስት ዓመት ወንጌልን ከሰበከች በኃላ በደቡብ አረቢያ አካባቢ ወድቃ አረፈች። ከቅዱሳኑ በረከት ያሳትፈን። ስንክሳር፤ ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ገድለ መጥምቀ ዮሐንስ።

No comments:

Post a Comment