Monday, December 31, 2012

ታህሳስ 22 ብስራተ ገብርኤል




በቤተክርስቲያን አስተምህሮ ብስራተ ገብርኤል ይባላል፤ ይህም ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ጌታን እንደምትወልድ ብስራቱን የነገረበት ቀን ነው፤ እንዴት ብስራቱንማ የነገራት መጋቢት 29 ቀን ካሉ ትክክል ነው፤ ብስራቱን የነገራት መጋቢት 29 ቀን በዕለተ እሁድ ከቀኑ ሦስት ሰዓት ላይ ነው፡ ታዲያ ዛሬ ለምን እናከብረዋለን ካሉ ምክንያቱ እንዲህ ነው፤ ምንግዜም ወርሃ መጋቢት ታላቁ ዓቢይ ጾም የሚውልበት ወር ነው በዚህ በዓቢይ ጾም ደግሞ ሐዘን፤ ለቅሶ፤ ጾም፤ ጸሎት እንጂ ደስታ፤ ፌሽታ እልልታ፤ ጭብጨባ የለም ፍጹም የሐዘን ወራት ነው ታቦት አውጥቶ በዓል ማክበርም ስህተት ነው ፍትሃ ነገስት አንድምታ አንቀጽ 15 ተመልከት ታዲያ ቅዱሳን አባቶቻችን እንደዚህ ዓይነት ስርዓት ሰሩ የመጋቢት 27 ስቅለቱን ጥቅምት 27 ቀን እንዲሁም የመጋቢት 5 አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ እረፍት ቀን ወደ ጥቅምት 5 ቀን ዞሮ እንዲከበር አደረጉ፡፡ የመጋቢት 29 ብስራቱን ደግሞ ታህሳስ 22 ቀን ዞሮ እንዲከበር ያደረገው ታላቁ አባት የጥልጥልያ ኤጲስ ቆጶስ ደቅስዮስ ይባላል በእመቤታች ፍቅር ልቡ የነደደ ታላቅ ጻድቅ ነው የእመቤታችንን ታአምራቷን የሚናገር መጽሐፍ የሰበሰበ አባት ነው፡፡ የጌታን ልደት ከመከበሩ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ብስራቱ መከበር አለበት ብሎ ስርዓት ሰራ አገሬውንም ሰብስቦ ታላቅ የደስታ በዓል አደረገ እመቤታችን ተገለጸችለት ወዳጄ ደቅስዮስ ባንተ ደስ አለኝ እንዳከበርከኝ እኔም አከብርሃለው አለችው ሰማያዊ ልብስና ሰማያዊ ወንበር ሰጠችው ይህችን ልብስ ካንተ ሌላ ማንም አይለብሳትም ይህችንም ወንበር ካንተ ሌላ ማንም አይቀመጥባትም አለችው፡ የዚህ ታላቅ አባት እረፍቱ ታህሳስ 22 በዛሬዋ ቀን ነው፡ ከእርሱ በኃላ ሌላ ኤጲስ ቆጶስ ተሾመ ልብሱን እለብሳለው በወንበሩም እቀመጣለው አለ ተው ይቅርብህ እመቤታችን እንዲህ ብላ ተናግራለች ይሉታል እርሱም ሰው እኔም ሰው እርሱም ኤጲስ ቆጶስ እኔም ኤጲስ ቆጶስ ብሎ በትዕቢት ልብሱን ለበሰው በወንበሩም ተቀመጠ ክፉኛ አወዳደቅ ወደቀ ሞተም ይህን ያዩ እመቤታችንን በጣም ፈሯት ይላል ተአምረ ማርያምን ተመልከት፡፡ ደቅስዮስ ሰርቶልን ያለፈውን ስርዓት ቤተክርስቲያን ተቀብላ ይኸው ዛሬም ድረስ ታከብረዋለች በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ብስራተ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፡፡ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡፡

Sunday, December 30, 2012

ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ


ቤተ ክርስቲያን የጌታችንን የልደቱን ብርሃን ለማየት እንዘጋጅ ዘንድ እነዚህን ሦስት ሳምንታት የጌታችንን ልደት በናፍቆት መበጠበቅ እንደ ብሉይ ኪዳን ሰዎች ሆነን እንድናሳልፍ ታደርጋለች፡፡
በእነዚህ ሳምንታት /በተለይም በእሑዶቹ/ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የአዳኙን መምጣትና የጌታን ቀን መገለጥ በመናፈቅ ስላሳለፏቸው ጊዜያት ደጋግመን በመማር እነዚያን የጨለማ ዘመናት እንድናስታውስና እኛም በእነርሱ መንፈስ ተቃኝተን ያለንበትን ሁኔታ በመመርመርና ዘወትር ልንመላለስበት ያጣነውን ነገር ግን በሃጢአታችን ያጣነውን የልደቱን ብርሃን ለማየት እንድንናፍቅ እንደረጋለን፡፡
ሦስቱን ሳምንታት በዚህ ሁኔታ ካሳለፍንና የልደቱን ብርሃን የማየት ፍላጎታችን ከተነሳሳ በኋላ የልደትን በዓል እናከብራለን፡፡ ደጋግመን እንዳልነውም የልደትን በዓል የምናከብረው እንዳለፈ ታሪክ መታሰቢያ አይደለም፡፡ ልክ በዚያች በልደቱ ቀን ከሰብአ ሰገልና ከእረኞች ጋር እንደተገኘን ሆነን እናከብራለን የልደቱን ብርሃን እናያለን እንጂ፡፡
ለዚህም ነው የልደትን በዓል ስናከብር
«ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ»
«ዛሬ በክርስቶስ ልደት ደስታ ሃሴት ሆነ፡፡» የምንለው፡፡
«ዮም፣ ዛሬ» ማለታችን በዓሉ የልደት መታሰቢያ /ትዝታ/ ብቻ ሳይሆን በዚያ በልደት ቀን እንደነበርን የምንሆንበት መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡
 

ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ

እነዚህ ከልደተ በዓል በፊት ያሉት ሦስቱ የጾመ ነቢያት ሳምንታት ስብከት፣ ብርሃን እና ኖላዊ ተብለው ይጠራሉ፡፡
እነዚህ ሳምንታት ነቢያት አምላክ ይህንን ዓለም እንዲያድን ያላቸውን ናፍቆት የገለጡባቸው እና ይህንን አስመልክተው ያስተማሩባቸው ሦስት የተለያዩ መንገዶች እና ጌታችንም ለእነዚህ መልስ የሰጠባቸው ሁኔታዎች ይታሰቡባቸዋል፡፡

1. ስብከት


ስብከት ማለት ማስተማር ማለት ነው፡፡ ይህ ሳምንት ከሙሴ ጀምሮ የነበሩ ነቢያት በሙሉ አዳኝ /መሲህ/ እንደሚመጣ ማስተማራቸው ጌታችንም እነርሱ ይመጣል ብለው ያስተማሩለት እኔ ነኝ ብሎ ራሱን መግለጡ የሚታሰብበት ነው፡፡ ሙሴ ለጊዜው የጌታችን ምሳሌ ለሆነው ለኢያሱ ፍጻሜው ግን ለጌታችን በሆነው ትንቢቱ «አምላክህ እግዚአብሔር ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳልሃል፤ እርሱንም ስሙት፡፡» ብሎ ለሕዝበ እስራኤል ነግሯቸው ነበር፡፡ /ዘዳ. 18.15/
እግዚአብሔር ወልድም በሥጋ ማርያም በተገለጠ ጊዜ ራሱን ያስተዋወቀው ያ ነቢያት የተናገሩለት አዳኝ /መሲህ/ እንደሆነ ነው፡፡ «ሙሴ እና ነቢያት ሁሉ ስለ እኔ ይናገራሉ፡፡» ይላቸው ነበር፡፡
ትንቢቱን ያውቁ የነበሩ በእግዚአብሔር መንገድ የሚሄዱ እስራኤላውያንም «መሲሁን አገኘነው»፣ «ሙሴ በህግ መጻሕፍት፣ ነበያትም ስለ እርሱ የጻፈለትን የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው» እያሉ ተከትለውታል፡፡ /ዮሐ. 1.41፣ ዮሐ. 1.45/
ሐዋርያትና ሌሎቹ ደቀመዛሙርቱም ከጌታችን ሞትና ትንሳኤ በተለይ የተነገሩትን ትንቢቶች ሁሉ ያውቁ ለነበሩት እስራኤላውያን ያስተማሩት እነዚህን የነቢያት ትምህርቶች እና ትንቢቶች እየጠቀሱ ነበር፤
ቅዱስ ጴጥሮስን በቤተ መቅደስ እንዲህ ብሎ አስተምሯል፤ «አሁንም ወንድሞቼ ሆይ አለቆቻችሁ እንዳደረጉ ይህን ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቃለሁ፡፡ እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በነቢያት ሁሉ አፍ እንደተናገረ እንዲሁ ፈፀመ» /ሐዋ. 3.17-18/፡፡
በሁለተኛው መልእክቱ ደግሞ እንዲህ ሲል ጽፏል፡- «ወንድሞች ሆይ የቀደሙ ቅዱሳን ነቢያት የተናገሩትን ቃልና ለእኛ ለሐዋርያትም ያዘዘውን የመድኃኒታችንና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ ታስቡ ዘንድ... ዕወቁ» /2ኛ ጴጥ. 3.1-3/
ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ መግቢያ ላይ እንዲህ ብሏል፤ «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዐይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፤ በኋላ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገው፣ ሁሉን በፈጠረበት በልጁ ነገረን፡፡» /ዕብ. 1.1-2/

2. ብርሃን


ነቢያት የአምላክን ማዳን ከጠበቁባቸው እና ከገለጡባቸው መንገዶች አንዱ ብርሃን ነው፡፡ ዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ፣ መከራ ነፍስ የፀናበት፣ ሁሉ ነገር አስጨናቂ የሆነበት፣ ሰው ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት ስለነበር ያሉበትን ዘመን «ጨለማ» ብለው በመግለጥ ይህንን ጨለማ የሚያስወግድና ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመራ ብርሃን እንዲመጣ እንዲህ እያሉ ይፀልዩ ነበር፡፡
«ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፣ እነርሱም ይምሩኝ፣
አቤቱ ወደ መቅደስህ ተራራና ወደ ማደራያህ ይውሰዱኝ» /መዝ. 42.3/ ጌታችንም ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ ለዚህ መልስ ሰጥቷል፤
«እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ» /ዮሐ. 8.12/
ደቀመዛሙርቱም ስለ ብርሃንነቱ በመመስከር ተባብረዋል፤
- ቅዱስ ዮሐንስ ስለጌታችን ሰው መሆን /ሥጋዌ/ በተናገረበት በወንጌሉ የመጀመሪያ ክፍል ጌታችንን ብርሃን ብሎታል፤ «ሕይወት በእርሱ ነበረ፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፤ ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም አላሰነፈውም» /ዮሐ. 1.4-5/

ቅዱስ ጳውሎስም ጌታችን በሚያንፀባርቅ ብርሃን አምሳል እንደተገለጠበት ተናግሯል፡፡ «እኩል ቀን በሆነ ጊዜ በመንገድ በሄደ ከፀሐይ ይልቅ የሚበራ መብረቅ በእኔና ከእኔ ጋር ይሄዱ በነበሩት ላይ ከሰማይ ሲያንፀባርቅ አየሁ፤ ... አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ አለኝ፡፡» /ሐዋ. 26.13/

3. ኖላዊ


ኖላዊ ማለት እረኛ ማለት ነው፡፡ ነቢያቱ ራሳቸውን እና ሕዝበ እስራኤልን ብሎም ዓለምን እረኛቸው እንደተዋቸው እና እንደተቅበዘበዙ በጎች በመቁጠር እንዲሰበስባቸውና እንዲያሰማራቸው እንዲህ እያሉ እራሳቸውን ይማፀኑ ነበር»
«ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ የእስራኤል ጠባቂ /እረኛ/ ሆይ፣ አድምጥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ፡፡» /መዝ. 79.1/

ጌታችንም ለዚህ ጥያቄ እንዲህ ሲል መልስ ሰጥቷል፤ «ቸር ጠባቂ /እረኛ/ እኔ ነኝ፡፡ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል፡፡»  /ዮሐ10.11/

Tuesday, December 25, 2012

ላፍቶ ሌንቃ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ሁኔታ

ላፍቶ ሌንቃ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ሁኔታ በአጭሩ


ቦታው ከአ. 210 . ርቀት ላይ ከምትገኘዋ ላፍቶ ሌንቃ የምትባል የገጠር ከተማ ሲደርሱ ወደ ቀኝ የሚገነጠለውን እና ወደ ስልጤ ዞን እና ቄልጦ ከተማ የሚወስደውን ኮረኮንቻማ የገጠር መንገድ ይዘው ሲጓዙ በግምት 4-5 . በኋላ ያገኙታል፡፡ ታሪክ ቤተክርስቲያኑ የተመሰረተበትን ዘመን በእርግጠኝነት ለማወቅ እና እና ለመናገር የሚያስችል በቂ መረጃ የሌለ ቢሆንም በጣም ብዙ የሆኑ ዘመናትን እንዳስቆጠረ የሀገር ሽማግሌዎች የተናገሩ እና በአካባቢው ላይ ያሉ የጥንት አባቶች ሲጠቀሙበት የነበሩ ዋሻዎች በውስጣቸውም የተገኘው የመስቀል ምልክት እና ፅሁፍ ምስክር ሲሆኑ በይበልጥ ግን ጥናት እና ምርምር ሊደረግበት የሚገባው ነገር ነው፡፡ ተጨባጭ ሁኔታ ይህ ቤተክርስቲያን አሁን ያለበት ሁኔታ እስከ ዛሬ ካየነው ከሠማነው ሁሉ የሚለይ እና እጅግ የሚያሳዝን ሁኔታ ነው፡፡ ሌሎች ቦታዎች ቢያንስ የሚያፈሱ ያረጁ በመቃብር ቤት ያሉ. ብቻ የሆነ ትንሽ ነገር ያላቸው ናቸው፡፡ እዚህ ግን ምንም የለም እንደ ቤተክርስቲያን የሚያገለግለው ዋርካ/ዛፍ/ ሲሆን ከስሩ ስዕለ መድኃኔዓለምን በማስቀመጥ ይጠቀሙበታል፡፡ በፊት የነበረው ቤተክርስቲያን በተለያየ ጊዜ የተነሱ አፅራረ ቤተክርስቲያን 3 ጊዜ ያፈረሱት ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ 1971 . ከዛሬ 32 ዓመታት በፊት በአህዛብ የተቃጠለ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ ለዚህን ያህል ዓመታት ሙሉ በአካባቢው ያሉት 7 ክርስቲያኖች ቤተክርስቲያን አግኝተው/አይተው/አያውቁም ነገር ግን ሃይማኖታችንን አንክድም ማተባችንን አንበጥስም በማለት ያለ መምህር በመፅናት ለብዙዎች አርአያ ለመሆን የሚችሉ ዕንቊ የቤተክርስቲያን ልጆች ያሉበት ቦታ ነው፡፡ እነዚህ ምእመናን 32 ዓመታት ያሳለፉትን ጭንቅ /መከራ/ ተናግሮ መጨረስ የማይቻል በሰው አእምሮ የማይገመት አሰቃቂ ለመግለፅም የሚከብድ ነው፡፡ የቤተክርስቲያኑን ይዞታ አንሰጥም በማለታቸው ምክንያት 4 ጊዜ በላይ ታስረዋል ተገርፈዋል መከራም ደርሶባቸዋል፡፡ ልጅ ወልደው ክርስትና ማስነሳት ንስሀ መግባት ማስቀደስ. የማይታሰቡ ነገሮች ናቸው፡፡ ሰው ሲሞት እንኳ ጸሎተ ፍትሀት ሳይደረግለት ዝም ብለው ቤተክርስቲያኑ የተቃጠለበት ቦታ አምጥተው ይቀብሩታል፡፡ አስከ አሁንም ድረስ የልጅነት ጥምቀት ያልተጠመቁ ህፃናት እና ወጣቶች ያሉ ሲሆን አንገታቸው ላይ ማህተብ በማሰር እኔ ክርስቲያን ነኝ በማለት በአህዛብ መካከል ይመሰክራሉ፡፡ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ በእለተ ሰንበት ተኝቶ አያረፍድም ወንዱም ሴቱም ህፃናቱም ትልልቆቹም ነጠላቸውን አጣፍተው ጋቢያቸውን አደግድገው ቤተክርስቲያኑ የተቃጠለበት ቦታ የምትገኝ አንድ ዛፍ ስር የመድኃኔዓለምን ስዕል በማኖር/በማስቀመጥ/ ይሰግዳሉ ይማፀናሉ፣ይለምናሉ ሥርዓተ አምልኮታቸውንም ይፈፅማሉ፡፡ ወር በገባ 27 የመድኃኔዓለም ዕለት ተራ ይዘው ዳቦ በመጋገር ጠላ በመጥመቅ / ጠበል ፀዲቅ በማዘጋጀት/ መድኃኔዓለምን ይዘክራሉ፡፡ በአጠቃላይ በአህዛብ ተከበው ሃይማኖትን በማፅናት አስደናቂ ተጋድሎ በመፈፀም ላይ ይገኛሉ፡፡

ተአምራት፡- በቦታው ላይ የተገለጡት ብዙ ተአምራት ቢሆኑም ለጊዜው ጥቂቶቹ

 1. ቤተክርስቲያኑን ያቃጠሉት 2 ወንድ እና 1 ሴት አህዛብ ሲሆኑ፡- ሴቲቱ እሳት በእንስራ ደብቃ ይዛ በመምጣት ቤተክርስቲያኑ በር ላይ ይጠብg ለነበሩ 2 ወንዶች በመስጠት ተባብረው ካቃጠሉት በኋላ በተለያየ ወር የመድኃኔዓለም እለት 2ቱም ወንዶች በመብረቅ የተቀጡ /የሞቱ/ መሆናቸው፡፡ሴቲቱም ከብቶችዋ በሙሉ በመብረቅ ማለቃቸው፤
 
2. ቤተክርስቲያኑ ሲቃጠል የነበሩ አገልጋይ መልሶ ለማሰራት የተሰበሰበውን ብዙ ገንዘብ በእጃቸው አድርገው ከአገልጋያቸው ጭምር ወደ እስልምና በገቡ በእለቱ አይነስውር መሆናቸው አገልጋዩም ሽባ መሆኑ እና እስከዛሬ በህይወት መኖራቸው፤

3. ቤተክርስቲያኑ በተቃጠለበት ቦታ እና አፀዶች መካከል ዝማሬ ቃጭልና እና ከበሮ የሚሰማ ዕጣን /ማዕጠንት/ የሚሸት መሆኑ

4. ጥንታውያን ዋሻዎች /ሰው የሚገባባቸው እና የማይገባባቸው/ሲኖሩ በድፍረት የገቡት አንደበተ-ዲዳ፤ዓይነ-ስውር መሆን እና በእሳት እየተቃጠሉ መውጣት በተጨማሪም ዝማሬ ቅዳሴ ወዘተ በዋሻዎቹ ውስጥ መሰማት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ በተጨማሪም በተለያዩ ቅዱሳት/ቅዱሳን/ ስም የተሰየሙ ፍል/ሙቅ/ጠበሎች ያሉ ሲሆን ህዝብም አህዛብም እየተጠቀሙባቸው በመፈወስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ቀጣይ ተግባር፡- በሀዲያ እና ስልጢ ሀገረ ስብከት ውስጥ ያሉትን ችግሮች እና በምእመናኑም ላይ የሚደርሰውን መከራ እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ለማስወገድ በማሰብ የቤተክርስቲያን ልጆች በመሰባሰብ እና በመምከር ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመነጋገር አብሮ በመስራት እና እውቅና በመውሰድ በመጀመሪያ ደረጃ የላፍቶ ሌንቃ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያንን በተገቢው ሁኔታ እና በአጭር ጊዜ ለማቋቋም፤ በቀጣይነት ደግሞ ሀገረ ስብከቱን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ ያሉትን ችግሮች ለዘለቄታው ለመቅረፍ እና ለማስወገድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሀዲያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት ቅዱስ እንጦንስ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር ማኅበር ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም የቤተክርስቲያን ነገር የሚያሳስበው አካል ማኅበራትም ሆኑ ምእመናን ከዚህ የባሰ ሁኔታ ስለሌለ በኅብረት ሆነን አስቸኳይ እና ዘለቄታዊ መፍትሄ እንድንሰጥ ሁላችንም የምንችለውን ሁሉ እና የሚጠበቅብንን እንድናደርግ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡  50 ሎሚ 1 ሰው ሸክሙ ነው 50 ሰዎች ግን ጌጥ ነው እንርዳዳ ይህችን ቤተክርስትያን እንጨርስ ከእግዚያአብሔር ጋራ
ህንፃ ቤተክርስቲያኑ እየተሰራ ሲሆን የቤተ ክርስቲያኑን ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ በተቸላችሁ መርዳት ይቻላል..ኑ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንስራ .ነህ 2:20ቅዱስ እንጦንስ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር  Commercial Bank of Ethiopia, Bomb Tera Branch. Account no. 1000017080249 mobile +251911143653, +251911780816, +251910016008 ክብር ምስጋና ለመድሓኔአለም ይሁን፡፡ለፍፃሜው አድርሶ የበረከቱ ተካፋይ ለመሆን ያብቃን፡፡በርቱ እመቤቴ ከነልጅዋ ትርዳችሁ ትርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!