Thursday, October 31, 2013

ጥቅምት 20

ጥቅምት 20
በዚህች ቀን አባ ዮሐንስ ሐጺር አረፈ፤ ቁመቱ አጭር ስለሆነ ነው ዮሐንስ ሐጺር የተባለው፤በ18 ዓመቱ በገዳመ አስቄጥስ መንኩሶ በተጋድሎ ኖረ፤ ይህ አባት ነጽሮተ ስሉስ ቅዱስ የደረሰ አባት ነው፤እዚህ ደረጃ የደረሱ አባቶች ቀና ቢሉ ሥላሴን ይመለከታሉ ዝቅ ቢሉ እንጦሮጦስን ያያሉ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የገዳሙ አብምኔት ሊፈትነው ብሎ ደረቅ እንጨት ሰጠው ይህንን ተክለህ አለምልመህ ፍሬውን አምጣሊኝ አለው፤እርሱም እንጨቱን ተከለው 3 ዓመት ሙሉ ከሩቅ ቦታ ውሃ እየቀዳ አጠጣው በ3ኛው ዓመት ጸደቀ ለመለመ ትልቅ ዛፍም ሆነ፤ ፍሬም አፈራ፤ መነኮሳቱ ይህ የትእግስት ውጤት ነው ብለው ፍሬውን ቀምሰውለታል፡፡ አንዲት አትናስያ የምትባል ሴት ነበረች፤ መጀመሪያ ጻድቅ ነበረች በኃላ ላይ በዝሙት ወደቀች ዘማዊም ሆነች፤ የቀድሞ ቅድስናዋን የሚያውቁ መነኮሳት ሊመክሯት ቢመጡ ሳቀችባቸው አሁን ማንን እንላክ ብለው አሰቡ ዮሐንስ ሐጺርን ላኩት፤ ተራ ሰው መስሎ ገባ፤ ለዝሙት የመጣ መስሏት ተቀበለችው፤ተጫወት አለችው ዮሐንስ ሐጺር ማልቀስ ጀመረ ምን ያስለቅስሃል ትለዋለች መልክሽ ደስ ብሎኝ ይላታል፤ደስ የሚል መልክ ያስቃል እንጂ መች ያስለቅሳል ትለዋለች የለም ነገ ገሃነም እንደምትወርጂ ታይቶኝ ነው አንድም ብዙ አጋንንት በሰውነትሽ ሲወጡ ሲወርዱ አያለሁ አላት፤ ደነገጠች ምን ይሻለኛል ትለዋለች፤ ንስሃ ገቢ ማን ያስታርቀኛል ኃጢያቴ ብዙ ነው ትለዋለች፤እኔ አስታርቀሻለሁ ተከተይኝ ብሎ ወጣ ልዋል ልደር ሳትል በሯን እንደተከፈተ ተከተለችው በልስላሴ የኖረ እግር ተበጣጥሶ በበዙ ደካም ሲመሽ ከገዳሙ ደረሱ፤የምታርፍበትን ቦታ ለይቶ ሰጣት፤ ሌሊት ለጸሎት ሲነሳ መላአክት ሲወጡ ሲወርዱ ያያል፤ ምንድን ነው ብሎ አንዱን መልአክ ይጠይቀዋል፤ትላንትና አንተን ተከትላ የመጣችው ሴት ሞታ ነፍሷን እያሳረግን ነው ይለዋል፤ እግዚኦ ንስሃ ሳትገባ ብሎ ይደነግጣል፤ አንተን ልትከተል ገና አንድ እግሯን ከቤት ስታወጣ ኃጢያቷ በሙሉ ተፈቆላታል፤ አሁን ወደ ገነት እየወሰድናት ነው ይለዋል፤ዮሐንስ ተገረመ፤የመቃብሯስ ነገር አለው፤ አንበሶች ይመጣሉ ቦታውን ለካላቸው ይለዋል፤አንበሶች ቆፍረውለት ቀብሯታል፤ ዮሐንስ ሐጺር በተጋድሎ ኖሮ በዛሬዋ ዕለት አርፏል፤ በረከቱ ይደርብን፡

LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

No comments:

Post a Comment